ይህን ለመጻፍ ያስገደዱኝን እና የገጠመኙን ሁኔታዎች በቅድሚያ ላብራራ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው አንድ ሰራተኛ አሰሪው በነበረው ድርጅት ላይ ህገ-ወጥ የስራ ውል መቋረጥ ተፈጽሞብኛል በማለት ላቀረበው ክስ አሰሪው ድርጅት በተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠኝ ሰራተኛው የስራ ውሉን ስላቋረጠ ካሳ እንዲከፍለኝ የሚልና ሰራተኛው ስራ ላይ በነበረ ጊዜ ለስራው አገልግሎት የተሰጠውን ላፕቶፕ ኮምፒውተር ሳይመልስ በመቅረቱ ንብረቱን እንዲመልስ ወይም የንብረቱን ግምት ብር 23,000 (ሃያ ሶስት ሺ) እንዲከፍለኝ በማለት ክስ አቀረበ፡፡ ጉዳዩን ሲያይ የነበረው የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት የስራ-ክርክር ችሎትም በድርጅቱ የላፕቶፕ ንብረትን በተመለከተ የቀረበውን የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ይህ ችሎት (ልብ በሉ ፍ/ቤቱ አይደለም) የማየት ስልጣን ስለሌለው ጉዳዩን በዚሁ ፍ/ቤት በፍትሐብሄር ችሎት ክስ የማቅረብ መብታቸውን ጠብቄ አቤቱታውን ውድቅ አድርጌዋለሁ በማለት ብይን ሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታም ተከራይ ከአከራዩ ድርጅት ሶስት ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎችን በተለያየ ጊዜ የተከራየ ሲሆን በቅድሚያ ለተከራያቸው ሁለት ክፍሎች የውል ሰነድ ያለው ሲሆን ለሶስተኛው ክፍል ግን ከቃል ስምምነት ባለፈ በጽሁፍ የተደረገ ውል የለም፡፡ ነገር ግን ለሶስተኛው ክፍልም ቢሆን ለአራት ወራት ያህል በየወሩ ከተከራይ የኪራይ ገንዘብ የተቀበለበትን ደረሰኝ በማስረጃ አያይዟል፡፡ ይህንንም የኪራይ ውልና የኪራይ ክፍያ ደረሰኝ መሰረት በማድረግ አከራይ ላልተከፈለው እና ተከራይ ለተገለገለበት ጊዜ የኪራዩ ክፍያ ይከፈለኝ በማለት በፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ክስ ያቀረበ ሲሆን ጉዳዩን ሲመረምር የነበረው የፍ/ቤቱ የኪራይ ችሎትም (ልብ በሉ ፍ/ቤቱ አይደለም) የኪራይ ውል ሰነድ ያላቸውን ክፍሎች አስመልክቶ ጉዳዩን የማየት ስልጣን ያለኝ ሲሆን የኪራይ ውል የሌለውን ሶስተኛውን የቢሮ ኪራይ ክፍያ ክስ በተመለከተ ግን ጉዳዩን የማየት ስልጣን ያለው በዚሁ ፍ/ቤት የንግድና ልዩ ልዩ ችሎት ስለሆነ በዚህ ችሎት ክስ የማቅረብ መብታችሁን ጠብቄ በሶስተኛው ቢሮ ላይ ያቀረባችሁትን ክስ ዘግቼዋለሁ በማለት ብይን ሰጥቷል፡፡
ለመሆኑ በአዎጅ የተቋቋሙ ፍ/ቤቶች እንጂ ችሎቶች ይህን መሰሉ ስልጣን አላቸው? የፍትሐብሔር የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ዓላማስ ከዚህ አኳያ እንዴት ይመዘናል የሚለውን በጥቂቱ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡- የፌደራል ፍ/ቤቶችን ያቋቋመው አዎጅ ቀ. 25/88 በፌደራል ደረጃ የሚኖሩት ፍ/ቤቶች የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት፣ ከፍተኛ ፍ/ቤት እና ጠቅላይ ፍ/ቤት መሆናቸውን ሲገልጽ የእነዚህ ፍ/ቤቶችም በመጀመሪያ ደረጃ ስልጣንም ሆነ በይግባኝ ደረጃ ጉዳዮችን ተቀብለው አይተው እና አከራክረው ወሳኔ ሊሰጡ የሚችሉባቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ደንግጓል፡፡
ይህ አዎጅ ይህንንም ሲገልጽ እነዚህ የፌደራል ፍ/ቤቶች ጉዳየን ለማየት እንዳለቸው ስልጣን የተፋጠነ ፍትህን ለመስጠት እንዲያስችል እያንዳንዱ ፍ/ቤት ቢያንሰ ሶስት ችሎቶች እነዚህም የፍትሐብሄር፣ የወንጀል እና የስራ-ክርክር ችሎቶች ሊኖሩት እንደሚገባ (በፌ/ፍ/ቤቶች አዎጅ 25/88 አ.ቁ 20(1) ፣23(1)) ሲደነግግ እንደሚቀርቡለት የጉዳዮች ብዛትና ዓይነት በስሩ እንደ ነገሩ ሁኔታ ሊይዛቸው የሚችሉ ችሎቶችን ፍ/ቤቱ በራሱ አስተዳደራዊ ውሳኔ የማብዛት መብት አለው (በተሻሻለው ፌ/ፍ/ቤቶች አዎጅ 454/97 አ.ቁ 23(1))፡፡