Font size: +
4 minutes reading time (754 words)

የፍርድ ቤት ወይስ የችሎት ስልጣን? (Jurisdiction of Courts or Divisions)

ይህን ለመጻፍ ያስገደዱኝን እና የገጠመኙን ሁኔታዎች በቅድሚያ ላብራራ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው አንድ ሰራተኛ አሰሪው በነበረው ድርጅት ላይ ህገ-ወጥ የስራ ውል መቋረጥ ተፈጽሞብኛል በማለት ላቀረበው ክስ አሰሪው ድርጅት በተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠኝ ሰራተኛው የስራ ውሉን ስላቋረጠ ካሳ እንዲከፍለኝ የሚልና ሰራተኛው ስራ ላይ በነበረ ጊዜ ለስራው አገልግሎት የተሰጠውን ላፕቶፕ ኮምፒውተር ሳይመልስ በመቅረቱ ንብረቱን እንዲመልስ ወይም የንብረቱን ግምት ብር 23,000 (ሃያ ሶስት ሺ) እንዲከፍለኝ በማለት ክስ አቀረበ፡፡ ጉዳዩን ሲያይ የነበረው የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት የስራ-ክርክር ችሎትም በድርጅቱ የላፕቶፕ ንብረትን በተመለከተ የቀረበውን የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ይህ ችሎት (ልብ በሉ ፍ/ቤቱ አይደለም) የማየት ስልጣን ስለሌለው ጉዳዩን በዚሁ ፍ/ቤት በፍትሐብሄር ችሎት ክስ የማቅረብ መብታቸውን ጠብቄ አቤቱታውን ውድቅ አድርጌዋለሁ በማለት ብይን ሰጥቷል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም ተከራይ ከአከራዩ ድርጅት ሶስት ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎችን በተለያየ ጊዜ የተከራየ ሲሆን በቅድሚያ ለተከራያቸው ሁለት ክፍሎች የውል ሰነድ ያለው ሲሆን ለሶስተኛው ክፍል ግን ከቃል ስምምነት ባለፈ በጽሁፍ የተደረገ ውል የለም፡፡ ነገር ግን ለሶስተኛው ክፍልም ቢሆን ለአራት ወራት ያህል በየወሩ ከተከራይ የኪራይ ገንዘብ የተቀበለበትን ደረሰኝ በማስረጃ አያይዟል፡፡ ይህንንም የኪራይ ውልና የኪራይ ክፍያ ደረሰኝ መሰረት በማድረግ አከራይ ላልተከፈለው እና ተከራይ ለተገለገለበት ጊዜ የኪራዩ ክፍያ ይከፈለኝ በማለት በፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ክስ ያቀረበ ሲሆን ጉዳዩን ሲመረምር የነበረው የፍ/ቤቱ የኪራይ ችሎትም (ልብ በሉ ፍ/ቤቱ አይደለም) የኪራይ ውል ሰነድ ያላቸውን  ክፍሎች አስመልክቶ ጉዳዩን የማየት ስልጣን ያለኝ ሲሆን የኪራይ ውል የሌለውን ሶስተኛውን የቢሮ ኪራይ ክፍያ ክስ በተመለከተ ግን ጉዳዩን የማየት ስልጣን ያለው በዚሁ ፍ/ቤት የንግድና ልዩ ልዩ ችሎት ስለሆነ በዚህ ችሎት ክስ የማቅረብ መብታችሁን ጠብቄ በሶስተኛው ቢሮ ላይ ያቀረባችሁትን ክስ ዘግቼዋለሁ በማለት ብይን ሰጥቷል፡፡

ለመሆኑ በአዎጅ የተቋቋሙ ፍ/ቤቶች እንጂ ችሎቶች ይህን መሰሉ ስልጣን አላቸው? የፍትሐብሔር የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ዓላማስ ከዚህ አኳያ እንዴት ይመዘናል የሚለውን በጥቂቱ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡- የፌደራል ፍ/ቤቶችን ያቋቋመው አዎጅ ቀ. 25/88 በፌደራል ደረጃ የሚኖሩት ፍ/ቤቶች የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት፣ ከፍተኛ ፍ/ቤት እና ጠቅላይ ፍ/ቤት መሆናቸውን ሲገልጽ የእነዚህ ፍ/ቤቶችም በመጀመሪያ ደረጃ ስልጣንም ሆነ በይግባኝ ደረጃ ጉዳዮችን ተቀብለው አይተው እና አከራክረው ወሳኔ ሊሰጡ የሚችሉባቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ደንግጓል፡፡

ይህ አዎጅ ይህንንም ሲገልጽ እነዚህ የፌደራል ፍ/ቤቶች ጉዳየን ለማየት እንዳለቸው ስልጣን የተፋጠነ ፍትህን ለመስጠት እንዲያስችል እያንዳንዱ ፍ/ቤት ቢያንሰ ሶስት ችሎቶች እነዚህም የፍትሐብሄር፣ የወንጀል እና የስራ-ክርክር ችሎቶች ሊኖሩት እንደሚገባ (በፌ/ፍ/ቤቶች አዎጅ 25/88 አ.ቁ 20(1) ፣23(1)) ሲደነግግ እንደሚቀርቡለት የጉዳዮች ብዛትና ዓይነት በስሩ እንደ ነገሩ ሁኔታ ሊይዛቸው የሚችሉ ችሎቶችን ፍ/ቤቱ በራሱ አስተዳደራዊ ውሳኔ የማብዛት መብት አለው (በተሻሻለው ፌ/ፍ/ቤቶች አዎጅ 454/97 አ.ቁ 23(1))፡፡

በመሆኑም ፍ/ቤቶች በአዎጅ የተቋቋሙና በስራቸው በአዎጁ ከተጠቀሱት ውጪ ያሉትን ችሎቶች  የሚያዋቅሩት ደግሞ በአስተዳደራዊ ውሳኔ እና የዚህም ዓይነተኛ እና ዋና ዓላማ ደግሞ የፍትሐብሄር ሥነ-ሥርዓት ሕጉን ዋና ዓላማ ለማስፈጸም ሲሆን ይህም የተፈጠነ ፍትህ ለማግኘት እና የተከራካሪዎችንና የፍ/ቤት ጊዜና ወጪን መቆጠብ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ከፌዴራል እና የክልል ሰበር ሰሚ ችሎቶች ውጪ  (የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አ.ቁ 80፣ የፌ/ፍ/ቤ/አ 25/88 እና የተሻሻለው 454/97) በማንኛውም ፍ/ቤት ውስጥ ያሉ ችሎቶች ከተቋቋሙበት ፍ/ቤት ውጪ ያራሳቸው የሆነ የስረ-ነገርም (material jurisdiction) ሆነ የግዛትም ሥልጣን (local jurisdiction) የላቸውም፡፡ ነገር ግን በፌ/ጠ/ፍ/ቤት ስር ያለው ሰበር ሰሚ ችሎት ከፌ/ጠ/ፍ/ቤቱ በሕግም ሆነ በፍሬ ነገር ስህተት ላይ በስር ፍ/ቤት በተሰጡ ውሳኔዎች ላይ በይግባኝ ጉዳዩን የማየት ስልጣን ውጪ በሀገሪቷ ላይ በሚገኙ ፍ/ቤቶች በተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የተፈጸመ የሕግ ትርጉም ስህተትን ብቻ የማረም እና የሚሰጠውም የሕግ ትርጉም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ፍ/ቤቶች እና ውሳኔ ለመስጠት የተቋቋሙ ተቋማትን የሚያስገድድ ሲሆን በክልል ጠ/ፍ/ቤቶች የሚገኙ ሰበር ሰሚ ችሎቶች ደግሞ በየክልሎቻቸው በሚገኙ ፍ/ቤቶች በተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሕግ ስህተትን የማረም ስልጣን ሲኖራቸው ይህ ግን ክልሎች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አ.ቁ 80 መሰረት በውክልና በሚያዩት የፌደራል ጉዳይ ላይ በተሰጡ የመጨረሻ ውሳኔዋች ላይ ግን ጉዳዩን የማየት ስልጣን አይኖራቸውም፡፡ ብሔራዊ የዳኝነት ስልጣን (Judicial Jurisdiction) ያልገለጽኩት ከሀገራዊ ሁኔታ ጋር የሚመዘን ወይም የአንድ ሀገር ፍ/ቤት የቀረበለትን ጉዳይ ከማየት እና ከማስፈጸም አኳያ የሚታይ እና የስልጣኑ ምንጭም ዓለም አቀፍ የግለሰብ ሕግ እና በሀገራት መካከል የሚደረግ የሁለትዮች ወይም የሶስትዮሽ ውል ( ለምሳሌ የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 461(1)(ሀ) principles of reciprocity ይመለከቷል) በመሆኑ ሲሆን የተቀሩት የግዛትና የስረ-ነገር ስልጣን ምንጭ ግን በሀገራት በራሳቸው ሕግ (domestic or national laws) የሚወሰን በመሆኑ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት በአሰሪና ሰራተኛ በነበረው ክርክር አሰሪው ያነሳው የንብረት ይመለስልኝ ክርክር በፍትሐብሄር ክስ ለማቅረብ ቢፈልግ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን ያለው እራሱ የስራ-ክርከሩ ችሎት የሚገኝበት የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ሆኖ ሳለ እና ተከራካሪዎቹ ተመሳሳይ ሆነው ሳለ፤ እንደዚሁም በአከራይና በተከራይ በነበረው ጉዳይ እንዲያው የጽሁፍ የኪራይ ውል የሌለውን ቢሮ የኪራይ ክፍያ አስመልክቶ ያለውን ጉዳይ ለመዳኘት ስልጣን ያለው እራሱ ጉዳዩ የቀረበለት የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ሆኖ ሳለና ተከራካሪዎቹ ተመሳሳይ ሆነው ሳለ፤ በተጨማሪም ማንኛውም ወገን ክስ በሚያቀርብበት ጊዜ ጉዳዩ በየትኛው ፍ/ቤት ሊቀርብ እንደሚገባ የመለየትና የትኛው ችሎት ጉዳዩን ማየት እንዳለበት መመደብ ያለበት ሬጅስትራሉ ሆኖ ሳለ ( ምክንያቱም የችሎት ምደባ ስራ አስተዳደራዊ በመሆኑ አቤቱታ አቅራቢ ሊያውቀው ይገባ ነበር የማይባልባት ጉዳይ ነው) ጉዳዩን የተመለከቱት የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ችሎቶች እራሳቸውን በፍ/ቤት ደረጃ የተቋቋሙ አድርገው በመቁጠር የቀረበላቸውን ጉዳይ ለማየት ስልጣን የለንም በማለት ብይን መስጠታቸው አግባብ አይደለም፡፡

ፍ/ቤቶች የተፈጠነ ፍትህ ለመስጠት ባላቸው አቅም በሚጥሩበት ሁኔታ አንዱ ችሎት ሊያየው የሚገባን ጉዳይ ለአስተዳደራዊ ስራ ምቹነትና የተፋጠነ ፍትህን ለመስጠት በውስጥ ደንብ የተደራጁት ችሎቶች እራሳቸውን በአዋጅ እንደተቋቋመ ፍ/ቤት በማየት ችሎቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለውም በማለት በፍ/ቤቶች ላይ የስራ ጫና ማብዛት በተከራካሪዎች ላይ የጊዜና የገንዘብ ኪሳራ ማብዛት ሕግን መሰረት ያላደረገ በመሆኑ በቶሎ ሊስተካከል የሚገባው እይታ ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የተሻሻለው የአማራ ክልል የገጠር መሬት አዋጅ እና አከራካሪው የይርጋ ድንጋጌ
‘ጠባቂ የሌለው ጠበቃ’ ጥቂት ስለ ኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያዎች ማህበር

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 03 October 2024