Font size: +
7 minutes reading time (1423 words)

ሰበር በአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ሥልጣን ላይ ያሰመረው ቀጭን መስመር

የአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሥልጣናቸውን የተመለከቱ የተለያዩ ክርክሮች ተነስተዋል፡፡ ዋናው ክርክር በተቋቋመበት ወቅት የተነሳው የሕገ መንግሥታዊነት ጭብጥ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 78 እስከ 80 የዳኝነት አካሉን ሲያዋቅር በተለያዩ ደረጃዎች ያሉት የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች እንደሚቋቋሙ በመግለጽ የፍርድ ቤት ሥልጣን ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች የሚወሰዱ ጊዜያዊና ልዩ ፍርድ ቤቶች እንደማይቋቋሙ ደንግጓል፡፡

ይህን መሠረት አድርገው አንዳንዶች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የተቋቋመው የከተማ ነክ ፍርድ ቤት (አሁን የከተማ ፍርድ ቤት) ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ሲሉ ሞግተዋል፡፡ የፍርድ ቤቱን ሕገ መንግሥታዊነት የሚደግፉ ወገኖች ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 49 በአዲስ አበባ የራስ አስተዳደር ስለፈቀደ አዲስ አበባ እንቅስቃሴዎቿን ለመከታተል የሕግ አውጭ፣ የሕግ አስፈጻሚ እንዲሁም የሕግ ተርጓሚ አካላትን ማቋቋም ትችላለች ብለዋል፡፡ የግራ ቀኙን የሕገ መንግሥታዊነት ለመደገፍ ሌሎችም ምክንያቶች ተጠቅሰዋል፡፡ ያም ሆኖ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት በአዋጅ ተቋቁሞ መደበኛ የፍርድ ቤት ሥራዎችን መሥራት ከጀመረ ሁለት አሠርት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ሥልጣኖች ተሰጥተውታል፡፡ በተቋቋመበት ወቅት በዋናነት የከተማ አስተዳደሩ የሚያከናውናቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የአስተዳደርና የቁጥጥር ሥልጣኖችን ከማስፈጸም ጋር የተያያዙ ክርክሮችን ይመለከት ነበር፡፡ ሁከት ይወገድልኝ፣ ደንብ መተላለፍ፣ ከቀበሌ ቤቶች ጋር የተያያዙ ክርክሮች፣ ከመሬት ጋር የተያያዙ ክርክሮችን ተቀብሎ እንዲያስተናግድ ተፈቀደለት፡፡ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ደግሞ ከመሬት ጋር የተያያዙት ጉዳዮች በአስተዳደሩ ስም ለተቋቋመ ቦርድ የተሰጠ ሲሆን፣ በምትኩ ጊዜ ቀጠሮ፣ እስከ አምስት ሺሕ ብር የሚደርሱ የፍትሐ ብሔር ክርክሮች፣ የስም ለውጥ፣ የወራሽነት የምስክር ወረቀት፣ የመጥፋት ውሳኔ፣ የባልና የሚስትነት፣ የሞግዚትነት የምስክር ወረቀት የመስጠት ሥልጣን በተሻሻሉ አዋጆች እንዲሠራ ተደርጓል፡፡

ለፍርድ ቤቱ በተለያዩ ጊዜያት ከተሰጡት ሥልጣኖች ለመረዳት የሚቻለው ፍርድ ቤቱ እንዲሠራቸው የተፈለጉት ክርክሮች ውስብስብነት የሌላቸው፣ በአጭር ጊዜ ሊጠናቀቁ የሚገባቸው፣ የገንዘብ መጠናቸው አነስተኛና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን (Municipality activities) መሠረት አድርገው የሚነሱ ክርክሮችን ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ ቀለል ያሉ ክርክሮችን እንዲመለከት ሥልጣን ይሰጠው እንጂ ፍርድ ቤቱን የሚያስተዳድሩ ኃላፊዎች፣ ጉዳዮቹን የሚመለከቱ ዳኞችና ረዳቶቻቸው ከፌዴራሉና ከክልሉ ፍርድ ቤቶች ጋር ተመሳሳይ የትምህርት ደረጃና የሥራ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ እንዲያውም ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ከአዲስ አበባ ፍርድ ቤቶች አንስቶ ወደ ፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መሾም ወይም ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኝነት መሾም ልማድ ሆኖ ነበር፡፡ በመደበኛ ፍርድ ቤቶችና በከተማው ፍርድ ቤቶች ዳኞች መካከል የትምህርትና የልምድ ልዩነት አለመኖሩ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት በሰበር ሰሚ ችሎት ከሚሰጡ ፍርዶች ለመገንዘብ እንደሚቻለው በአዋጅ ለከተማው ፍርድ ቤት የተሰጡ ሥልጣኖች ወሰን በጠባቡ እንዲተረጎም የሚደረግበት አግባብ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ሰበር ችሎቱ በሰጣቸው ፍርዶች የአዲስ አበባ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ቀለል ባሉ አስተዳደራዊና የምስክር ወረቀት የመስጠት ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባው አቋም ወስዷል፡፡ ችሎቱ ለዚህ አቋሙ መነሻ የሚያደርገው ለከተማው ፍርድ ቤቶች ሥልጣን የሰጡትን አዋጆች ቢሆንም፣ አተረጓጎሙ እንከን የለሽ የሚባል አይደለም፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሰበር ችሎቱ በቅርቡ በአሥራ ሰባተኛው ቮልዩም ከባልነት የምስክር ወረቀት አሰጣጥና በምስክር ወረቀቱ ላይ በሚቀርብ ተቃውሞ የከተማ ፍርድ ቤት ያስተናገደውን ጉዳይ አስመልክቶ የሰጠውን አስገዳጅ ትርጓሜ በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ

ጉዳዩ የጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት ነው፡፡ አመልካች ከፍርድ ቤቱ የባልነት የምስክር ወረቀት ጠይቀው ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ባልነቱን የሚቃወሙት ሴት በዚያው ፍርድ ቤት በተዘጋው መዝገብ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 358 መሠረት የተቃውሞ አቤቱታ በማቅረብ የባልነት የምስክር ወረቀት እንዲሰረዝላቸው ጠየቁ፡፡ ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን አከራክሮ የምስክሮችን ቃል አዳምጦ በግራ ቀኙ መካከል ጋብቻ በትዳር ሁኔታ መፈጸሙ ተረጋግጧል በሚል የባልነት የምስክር ወረቀቱ ሊሰረዝ አይገባም ሲል ፍርድ ሰጥቷል፡፡ የተቃውሞ አመልካች በፍርዱ ላይ ይግባኝ ቢያቀርቡም፣ ለከተማው ሰበር ችሎቱ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል ቢያመለክቱም የሥር ፍርዱ ፀና፡፡ በዚህ ጊዜ ነው የአመልካች ጠበቃ የባልነት ጉዳይ አከራካሪ በሆነበት ሁኔታ ጉዳዩ በከተማው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱ የታየው ያለሥልጣናቸው በመሆኑ፣ የባልነት ማስረጃው ከመጀመሪያውኑ በሕግ አግባብ አልተሰጠም በሚል ስህተቱ እንዲታረም የጠየቁት፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ በአብላጫ ድምፅ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ የአብላጫው ድምፅ የከተማ ፍርድ ቤቶች በባልነት ማስረጃ ላይ የሚቀርብ መቃወሚያን ተቀብለው ለመመርመር ሥልጣን የላቸውም የሚል ሲሆን፣ በአቋም የተለዩት የሰበር ችሎት ዳኛ ደግሞ የባልነት የምስክር ወረቀትን የመስጠት የከተማው ፍርድ ቤቱ ሥልጣን በተሰጠው ማስረጃ ላይ ተቃውሞ ሲቀርብም ተቀብለው የማስተናገድ ሥልጣን እንዳላቸው ተንትነዋል፡፡ የችሎቱን አቋም ቀጥለን እንመልከት፡፡

የአብላጫ ድምፅ ምክንያት

የሰበር ችሎቱ አብላጫ ድምፅ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት የወራሽነት፣ የባልና ሚስትነትና የሞግዚትነት የምስክር ወረቀት የመስጠት ሥልጣን ቢኖረውም፣ ይህ ሥልጣን የባልነት ወይም የሚስትነት ማስረጃው የሚሰጠው ስለ ጋብቻ መኖር አለመኖር ክርክር ባልቀረበበትና ግራ ቀኙ ማስረጃ ባላቀረቡበት ነው፡፡ እንደ ችሎቱ የአብላጫ ድምፅ አቋም የባልነት ወይም የሚስትነት ማስረጃ ይስጠን አቤቱታ ይዘቱና ፍርድ ቤቱ ሊከተለው የሚገባው ሥነ ሥርዓት ሲታይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የማስረጃ ይሰጠኝ ጥያቄውን ተገቢነቱን፣ ትክክለኛነቱንና ሕጋዊነቱን ከማረጋገጥ ባለፈ ጋብቻ አለ ወይስ የለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘው በጉዳዩ ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎችን በመስማት፣ ጉዳዩን በማጣራትና ሌሎች ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ክርክር ሲኖር አቤቱታውን ተቀብሎ ለማስተናገድ የዳኝነት ሥረ ነገር ሥልጣን የሌላቸው መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ አብላጫው ድምፅ ‹‹በጉዳዩ ላይ ሚስትነት ወይም ባልነት የለም የሚልና ተቃውሞውን ለማቅረብ መብትና ጥቅም ያለው ወገን ጋብቻው ያለመኖሩንና ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች ሕጋዊ ክርክሮችን መሠረት በማድረግ ተቃውሞ በማቅረብ ሕጋዊ መፍትሔ ሊያገኝ የሚገባው ጥያቄውን ወይም አቤቱታውን ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች በማቅረብ እንጂ ለአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች በማቅረብ አይደለም፤›› የሚል ፍርድ ሰጥተዋል፡፡


የሐሳብ ልዩነት

ከሰበር ችሎቱ ውስጥ አንዱ ዳኛ በአብላጫው ፍርድ ያልተስማሙ ሲሆን፣ የሀሳብ ልዩነታቸውን በፍርዱ ገልጸዋል፡፡ እንደ ዳኛው ሐሳብ የባልና የሚስትነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚቀርብ አቤቱታ፣ ባል ወይም ሚስት ነኝ በማለት አንድ ሰው የሚያቀርበውን ማመልከቻና መግለጫ ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ለመቃወም የሚቀርብ ክርክርን ጭምር ነው፡፡ ዳኛው በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 80(1) የተገለጸው የአቤቱታ ትርጉም ተቃውሞንም እንደሚጨምር በሰፊው ተንትነዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ይላሉ ዳኛው የአዲስ አበባ ፍርድ ቤቶች ባልነቴ ተረጋግጦ ውሳኔ ይስጥልኝ ለሚል አካል ሚስት በሕይወት ካለች የመከላከያ መልሷንና ማስረጃዋን እንድታቀርብ በማድረግ፣ ፍሬ ጉዳይ በማጣራት፣ ማስረጃ በመመርመርና በመመዘን በሁለቱ ተከራካሪዎች መካከል ሕጋዊ ዕውቅና ያለው ጋብቻ መኖር አለመኖሩን የመወሰን ሙሉ ሥልጣን ያላቸው መሆኑን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ዳኛው የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 358 ‹‹መቃወሚያው የሚቀርበው በአቤቱታ አቀራረብ መልክ ሆኖ ተገቢው ዳኝነት ተከፍሎበት መቃወሚያ የቀረበለትን ለወሰነው ፍርድ ቤት ነው፤›› በማለት ስለሚገለጽ፣ የተቃውሞ አቤቱታው ለአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት መቅረቡ ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሰበር ችሎቱ ከሥረ ነገር ሥልጣን ውጭ የሆነውን የሥር ፍርድ ቤቶች ተቃውሞውን በመቀበል የሰጡት ውሳኔ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ተመልክቶና አከራክሮ ውሳኔ ሊሰጥ ይገባ ነበር ሲሉ በአቋም ተለይተዋል፡፡


በፍርዱ ላይ አጭር ምልከታ

ለሰበር ችሎቱ የቀረበው ዋና ጭብጥ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከተማ ፍርድ ቤት በአዋጅ ቁጥር 408/1996 የተሰጠው ሥልጣን ወሰን በተመለከተ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት የአዲስ አበባ ፍርድ ቤት የወራሽነት፣ የባልና ሚስትነትና የሞግዚትነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚቀርብ አቤቱታን ተቀብለው የማስተናገድ ሥልጣን አላቸው፡፡ የሰበር ችሎቱ አብዛኛው ድምፅ እነዚህ አቤቱታዎች ላይ ማስረጃ የመስጠት (Declaratory Judgments) እንደመሆናቸው ፍርድ ቤቶች ግራ ቀኝ ሳይሰሙ፣ ተቃውሞ ሳይቀበሉ የሚሰጡት ውሳኔዎች ናቸው፡፡ ተቃውሞ ካለ በቤተሰብ ሕግ የተደነገጉ የጋብቻ መኖር አለመኖር ጥያቄ ካለ ሥልጣኑ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው የሚል ነው፡፡ የልዩነት አቋሙ ግን ማስረጃ ለመስጠት ሌላኛውን ወገን መጥራት፣ መልሱን መስማት፣ ማስረጃና ተቃውሞ መመርመር የሥልጣኑ አካል ነው የሚል ነው፡፡ አብላጫው ድምፅ ምስክር ወረቀት የመስጠት ሥልጣንን በተመለከተ ቀጭን መስመር ያሰመረ ሲሆን፣ ተከራካሪና ተቃዋሚ በሌለበት ብቻ የአዲስ አበባ ፍርድ ቤቶች ማስረጃውን መስጠት ይችላሉ የሚል መርህ ሠርቷል፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር ፍርድ ቤት ሥልጣንን በተመለከተ አዋጅ ቁጥር 361/1995 እና አዋጅ ቁጥር 408/1996 ዓ.ም. ተፈጻሚነት ያላቸው አዋጆች ናቸው፡፡ አዋጅ ቁጥር 408/1996 ቀደም ሲል በአዋጅ ቁጥር 361/1995 ከተሰጡት ፍትሐ ብሔራዊ ሥልጣኖች በተጨማሪ ፍርድ ቤቶች የወራሽነት፣ የባልና ሚስትነትና የሞግዚትነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚቀርብ አቤቱታን እንዲዳኝ ለአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት ሥልጣን ሰጥቷል፡፡ እነዚህ ሥልጣኖች የከተማ ፍርድ ቤቱን ሥልጣን ያሰፉ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ አቤቱታው በቀረበለት ሰዓት በመሠረታዊያን ሕግጋት ማለትም በውርስ ሕግና በጋብቻ ሕግ የተቀመጡት መስፈርቶች መሟላታቸውን አረጋግጦ ማስረጃውን የመስጠት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ የባልና የሚስትነት የምስክር ወረቀት ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ዋቢ የሚያደርገው የቤተሰብ ሕጉን ድንጋጌዎች ነው፡፡ በመሠረቱ የባልነትና የሚስትነት ሁኔታን ለማረጋገጥ በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 94 እስከ 97 ያሉትን መሠረት በማድረግ ጉዳዩን መመልከት ያስፈልጋል፡፡

በእነዚህ ድንጋጌዎች መሠረት ጋብቻ መፈጸሙን ለማስረዳት የሚቻለው ጋብቻው በተፈጸመበት ዕለት ወይም ከዚያ በኋላ በሕጉ መሠረት ተዘጋጅቶ የተሰጠውን የጋብቻ የምስክር ወረቀት በማቅረብ ነው፡፡ የጋብቻ ምዝገባ ሳይደረግ የቀረ ወይም መዝገቡ በመጥፋቱ ምክንያት ጋብቻ መፈጸሙን በጋብቻ ምስክር ወረቀት ለማስረዳት ያልተቻለ እንደሆነ ጋብቻ ለመፈጸም የትዳር ሁኔታ መኖሩን በማረጋገጥ ሲሆን፣ ሕጉ በአንቀጽ 96 እና 97 መሠረት ፍርድ ቤቶች የጋብቻ ሁኔታን መኖሩን ስለሚያረጋግጡበት ሁኔታ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ባልነት ወይም ሚስትነት ለማረጋገጥ የሚፈልግ አካል የጋብቻ የምስክር ወረቀት ካለው ፍርድ ቤት ሄዶ ዳኝነት መጠየቅ አይጠበቅበትም፡፡

በወሳኝ ኩነቶችና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004 ዓ.ም. ጋብቻን በመመዝገብ የጋብቻ የምስክር ወረቀት የሚሰጡ ተቋማት በመቋቋማቸው ባልነት ወይም ሚስትነት ለማረጋገጥ የሚያስችለውን የጋብቻ የምስክር ወረቀት የሚያገኙት ከእነዚህ ተቋማት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት የጋብቻ ምዝገባ ያላከናወኑ ወይም ምዝገባው የጠፋባቸው ግን ማስረጃውን ሊያገኙ የሚችሉት ከፍርድ ቤት ነው፡፡ እናም በአዋጅ ቁጥር 408/1996 የባልነት/ሚስትነት ማስረጃ ለአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት የተሰጠው በዚህ መንፈስ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለፍርድ ቤቱ የተሰጠው ሥልጣን ጋብቻን በትዳር ሁኔታ በማረጋገጥ አቤቱታ ላቀረበላቸው ሰው የባልነት ወይም የሚስትነት የምስክር ወረቀት የመስጠት ሥልጣን ይኖራቸዋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ማስረጃ መስማት፣ ምስክር ማስጠራት አስፈላጊም ሆኖ ከተገኘ ሌላውን ተጋቢ የመጥራት ሥራን ሊያከናውኑ ይችላሉ፡፡ ለፍርድ ቤቱ የተሰጠው ሥልጣን ተራ የምዝገባ ማስረጃ (Declaratory Judgment) ከመስጠት ያለፈ ነው፡፡ ምክንያቱም ተራ የማስረጃ ማወጅ ሥራ ከሆነ ፍርድ ቤቱ የወሳኝ ኩነት መዝጋቢን ሥራ እንዲተካ ማድረግ ነው፡፡

በዚህ መነሻነት በሐሳብ የተለዩት ዳኛ አቋም አሳማኝ ይመስላል፡፡ አዋጁ በግልጽ የባልነት የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ለከተማው ፍርድ ቤት ያልከለከለው ሥልጣን በትርጉም መከልከል ተገቢ አይሆንም፡፡ ማስረጃ ሰምቶ አከራክሮ ካልወሰነ፣ ተቃውሞን ካልተቀበለ የፍርድ ቤቱ ሚና አስተዳደራዊ ይሆናል፡፡ ማስረጃ እንዲሰጥ ፈቅዶም በማስረጃው ላይ የሚቀርብን ተቃውሞ መከልከል አሳማኝ አመክንዮ አይኖረውም፡፡ የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በከተማ ፍርድ ቤቱ የተሰጠውን ፍርድ ለመሻር ሥልጣኑንስ ከምን ሕግ ያገኘዋል? ከዚህ አንፃር ሰበር ችሎቱ በአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ሥልጣን ላይ ያሰመረው ቀጭን መስመር ጥናት የሚፈልግ፣ ግራ ቀኝ ሙግት የሚጋብዝ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የ‹‹ያስቀርባል … አያስቀርብም›› እንቆቅልሽ
ስለ እንደራሴ (ውክልና) ሕግ አንዳንድ ነጥቦች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 25 July 2024