“And they said, Go to, let us build us a city and a tower, whose top may reach unto heaven; let us make as a name, lest we be scattered abroad upon the face of the whole earth…Therefore is the name of is called Babel; because the Lord did there confound the language of all earth…” Genesis 11:4-9
መግቢያ
የኮንስትራክሽን ውል በጣም ውስብስብና ብዙ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ውል ነው፡፡ በይዘትም ሆነ በጥልቀት በጣም ሠፊ ከመሆኑ የተነሳ ውቂያኖስ መሰል ውል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለምን ቢባል በተለያየ ዕውቀትና ሙያ ዘርፍ የሚሳተፋ ሰወች ከመኖራቸው አልፎ በየደረጃው ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች መኖራቸው፤ የተለያዩ ጊዜ ወሰድ የዲዛይን ለውጦችና ማሻሻያወች ስለሚስተዋሉበት ጭምር ነው፡፡
ኮንስትራክሽን የሰው ልጅ ወደ ምድር ከመጣ ጊዜ ጀምሮ የነበረ፤ ያለና የሚኖር እንቅስቃሴ ነው፡፡ የመጀመሪያው ግንባታ የሚባለውም በጥንታዊ ጋርዮሽ ሥርዓተ ማኅበር የሰው ልጅ ለመጠለያነት የተጠቀማቸው መጠለያ ጎጆወች ናቸው፡፡ በዓለም ታሪክም አንኳር የሚባሉ ግንባታወች ወስጥ ዋና የሚባሉት በጽሑፋ መግቢያ ላይ የተጠቆመው የባቢሎን ግንብ፤ ግብፅ (ምስር) ውስጥ በፈርዖኖች ከ2700-2500 ዓ.ዓ የተሰሩ ፒራሚዶች፤ በንጉስ ሽን ሁኣንግ ቲ ትዕዛዝ በጄኔራል ሜይንግ ቲን በ 220 ዓ.ዓ ገደማ የተሰራው ታላቁ የቻይና ግንብ እና የሮማዊያን የውሃ ማቆሪያ ግንባታወች ተጠቃሽ ናቸው፡፡