ጋብቻ ክቡር፣ ምኝታውም ቅዱስ እንደ ሆነ የሀይማኖት መጻህፍት ያስተምራሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ጋብቻ የህብረተሰብ ተፈጥሯዊ መነሻ የሆነው ቤተሰብ የሚመሰረትበት በመሆኑ ከመንግስትና ከህብረተሰብ ያላሰለሰ የህግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ ይህም ጉዳይ በበርካታ አለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ብሄራዊ ህጎች እውቅና አግኝቷል፡፡
ይሁንና የጋብቻው ክቡርነትም ይሁን የምኝታው ቅዱስነት የሚረጋገጠው እንዲሁም መንግስትና ህብረተሰብ ህጋዊ ጥበቃ የሚያደርጉለትን ቤተሰብ ለመመስረት ብቁነት የሚኖረው ጋብቻው በህግ መሰረት የተፈጸመ ሲሆን ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒው በአማራ ክልል ከሚመሰረቱ ትዳሮች መሀከል ሰማኒያ ሁለት ከመቶ የሚሆኑት ያለ እድሜ ጋብቻ የሚፈጸምባቸው ናቸው፡፡
ከላይ የተገለጸው አሀዝ ከፍተኛነት ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነ ሲሆን ጽሁፉ ያለ እድሜ ጋብቻን ምንነት፣ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ስለ ያለ እድሜ ጋብቻ ያላቸውን አቋምና ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአጭሩ ይዳስሳል፡፡ በመቀጠልም በያለ እድሜ ጋብቻ የሚጣሱ መብቶችንና ያለ እድሜ ጋብቻ መፈጸም የሚያስከትለውን የህግ ተጠያቂነት በዝርዝር ይመለከታል፡፡
ያለ እድሜ ጋብቻ ምንነትና የሰብአዊ መብት ስምምነቶች አቋም
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ140 በላይ የሚሆኑ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱና ዋናው ደግሞ ያለ እድሜ ጋብቻ ነው፡፡ በዚህ ያለ እድሜ ጋብቻ የአማራ ክልል በሀገር ደረጃ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘ ሲሆን ይሄው ድርጊት ከገጠሩ የክልሉ ክፍሎች አልፎ በከተሞች አካባቢም ይፈጸማል፡፡