ሕግና ኅብረተሰብ ጠንካራ ቁርኝት አላቸው፡፡ ኅብረተሰብ በሌለበት ሕግን ማሰብ፣ ሕግ በሌለበት በሥርዓት የሚኖር ኅብረተሰብን ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡
ይህ ግንኙነት አንዳንድ ጊዜ በመቀዳደም ሊፈጸም ይችላል፡፡ ሕግ ኅብረተሰብን ዘመናዊ ለማድረግና ለመለወጥ እንደ መሳሪያነት ሊያገለግል ይችላል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ጊዜ የሕጉ ዓላማ ኅብረተሰቡ ያልደረሰበትን ለውጥ ማስገኘት ነው፡፡ በተቃራኒው ከኅብረተሰቡ የሚወጡ እሴቶችና ባህሎችን ወደ ሕግ ደረጃ በማሳደግም የኅብረተሰቡን ሕልውና ማስቀጠል ይቻላል፡፡ እነዚህ የተሳሰሩ ግንኙነቶች ኅብረተሰቡ ከሕግ መጠቀም የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያሰፋ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በሆነ መልኩ ሕጉ ከኅብረተሰቡ ዕድገት ወደ ጓላ ከቀረ ሕጉ ከወረቀት ያለፈ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ ይህን ችግር በአገራችን የተወሰኑ ሕግጋት እናስተውለዋለን፡፡
የፍትሐ ብሔር ሕጋችንን ጨምሮ አገራችን በአሁኑ ወቅት የምትጠቀምባቸው ሕግጋት በ1950ዎቹ ከውጭ አገሮች በተወሰነ ማሻሻያ የገቡ ናቸው፡፡ ሕግጋቱ በጊዜው ሲወጡ አፄው የነበራቸው ዓላማ አገሪቱን ዘመናዊ ሕግጋት ከሚከተሉ አገሮች ማመሳሰል ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ሕግጋት ለአገሪቱ ባህል ሰፊ ቦታ አልሰጡም በሚል ትችት የሚቀርብባቸው ቢሆንም፣ አገሪቱን ላለፉት 50 ዓመታት በማስተዳደር ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች አብዛኛዎቹ አሁንም ድረስ የአገሪቱ ዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ለመምራት በቂ ቢሆኑም የተወሰኑት ድንጋጌዎች ከኅብረተሰቡ ባህል፣ ወግና ዘመናዊ አስተሳሰብ ጋር የማይጣጣሙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ባለፉት አሥር ዓመታት የተሻሻሉ አሉ፡፡ በዚህ ረገድ የቤተሰብ ሕጉ፣ የወንጀል ሕጉ፣ የመሬት ሕግ፣ የማኅበራት ሕግ ወዘተ. በዘመናዊ አስተሳሰብ በመቃኘት እንዲሻሻሉ ተደርገዋል፡፡ እስካሁንም ድረስ ግን ያልተሸሻሉና ዘመን ሲለወጥ የማይለወጡ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች ሕጉ ላይ ከመኖራቸው በቀር በኅብረተሰቡ የማይታወቁ፣ ሲገለጡ ባዕድ የሆኑ፣ በፍርድ ቤት መብት የማይጠየቅባቸው ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የፍትሐ ብሔር ሕጉን የተወሰኑ ድንጋጌዎች ለማሳያነት በመጠቀም ድንጋጌዎቹ ያልተለወጡበትን ምክንያት፣ አለመለወጣቸው ያስከተለውን አንድምታና መፍትሔ ለመጠቆም ጥረት ይደረጋል፡፡
ያልተለወጡ ድንጋጌዎች ማሳያ