ስለ ዓለም አቀፍ እና ብሔራዊ አማራጭ የአለመግባባት መፍቻ ሥርዓት ጽንሰ-ሀሳብ አበይት ነጥቦች

መግቢያ

አለም ዐቀፍ፣ የግልግል የዕርቅና የሽምግልና ተግባራት መሠረታዊ አላማ፣ ከተለያዩ  ሀገራት ዜጐች ወይም ኩባንያዎች ጋር የንግድ ግንኙነት በመሠረቱ ወገኖች መካከል የሚያጋጥም የንግድ አለመግባባትን ከመደበኛው የፍርድ ሂደት ወይም ሥነ-ሥርዓት ውጪ በገላጋዮች፣ በአስታራቂዎች ወይም በሽምጋዮች እንደተዋዋይ ወገኖች ፍላጐት ለመፍታት ጥረት የሚደረግበት አለም ዓቀፋዊ ይዘት ያለውን አሠራር ለማስፈን ነው፡፡

ግልግሉ፣ አስታራቂነቱ ወይም ሽምግልናው ውጤት እንዲኖረው፣ በተዋዋይ ወገኖች  አስቀድሞ ተቀባይነት ያገኘ በፅሁፍ የተደረገ ስምምነት ወይም ልማዳዊ አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡ ተዋዋይ ወገኖች አስቀድመው ባልተስማሙበት አኳኋን የሚደረግ የግልግል፣ የዕርቅ ወይም የሽምግልና  አሰራር፣ በተዋዋይ ወገኖች ሙሉ ፈቃድ ካልሆነና በፅሁፍ፣ ጥያቄው ካልቀረበላቸው በቀር ይህንን ተግባር ለማከናወን የተመሠረቱ ተቋማት ጉዳዩን ያዩት አይችሉም፡፡ በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የግልግልም ሆነ የዕርቅ ወይም የሽምግልና አሠራር ከሚጠይቃቸው አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል በተዋዋይ ወገኖች የውል ስምምነት ውስጥ የተካተተ ወይም በልዩ የመገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት የተደረገ የጽሁፍ ስምምነት መኖር አንዱ እና ተቀዳሚው ጉዳይ እንደሆነ ተደርጐ በአለም አቀፍ የግልግል፣ የዕርቅና የሽምግልና ህግጋት ተደንግጐ ይገኛል፡፡

በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት መሠረት የሚሠጥ የግልግል ውሳኔበህግ በተገለጸ ክልከላ ካልሆነ በቀር፤ ምንጊዜም ቢሆን ተፈፃሚነት አለው፡፡ ስለሆነም፣ አለም ዐቀፍ የግልግል፣ የዕርቅና የሽምግልና አሠራር በአለም ዐቀፍ ንግድ በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት መሠረት የሚቋቋም ወይም በስምምነቱ መሠረት የሚፈጠር፣ የንግድ አለመግባባቶች የሚፈቱበት ስርዓት ነዉ ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ በአጠቃላይ አገላለፅ፣ የተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ውጤት ሆኖ ተዋዋዮቹ ያለ-መግባባት ቢኖር ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት መውሰድ ሳያስፈልግ እነርሱ በመረጡት መንገድ በግልግል፣ በዕርቅ ወይም በሽምግልና ለመፍታት በውላቸው ምስረታ ወቅት አስቀድመው የሚያደርጉት ውል ሲሆን የፍርድ ቤትን አሰራር የሚያስቀር አማራጭ ስምምነት ነው፡፡ ተዋዋይ ወገኖች በዚህ ስምምነታቸው ውስጥ በአደረጉት የተለየ ውል መሠረት ጉዳዩ እንደአስፈላጊነቱ በገላጋዮች በአስታራቂዎች ወይም በሸምጋዮች አማካኝነት እንዲያልቅ ከመወሰን በተጨማሪ ግልግሉ፡…… በየትኛው ሕግ ወይም ደንብ መሠረት መታየት እንዳለበት አስቀድመው መወሰን ይችላሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም ገላጋይ ተቋማትን ወይም ግለሰቦችን አስቀድሞ መምረጥና በዕነዚህ ተቋማት የሚሰጥ ውሳኔ የመጨረሻ እንዲሆን ሊስማሙ ይችላሉ፡፡

የዚህ ምዕራፍ ተቀዳሚ አላማም ዓለም አቀፍ የግልግል የዕርቅና፣ የሽምግልና አሰራርን በማመልከት ጉዳዩን የሚመለከቱ ሕጐችንና ደንቦችን በማስተዋወቅ የግልግል የዕርቅ ወይም የሽምግልና አለም አቀፋዊ  አህጐራዊ እና ብሄራዊ ሕግጋትን መሠረት በማድረግ የተቋቋሙ የግልግል ተቋማትን ለአብነት ያህል በመጥቀስ በሀገራችን የግልግል ስርአት የሚዘረጋበትን አሰራር በሚመለከት የተወሰነ የመግባቢያ ሀሳብ ለመፈንጠቅ ነው በጥናቱ የተካተቱት ተቃማትና ህግጋት፤ ከአላቸው ዓለም አቀፋዊ አህጉራዊና ብሄራዊ ተቀባይነት ወይም ተፈፃሚነት አንፃር ለጥናቱ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል የተባሉት ዕንጂ  በጉዳዩ አግባብነት ያላቸው ማዕከላትንና ሕግጋትን በአጠቃላይ  ለመዳሰስ የፅሁፍ አላማ አይደለም፡፡ ስለሆነም ከዓለም አቀፍ፤ ከአህጉራዊና ከብሄራዊ የግልግል ተቋማትና ህግጋት መካከል አብነት ሆነው ያገለገሉትን እና በማገልገል ላይ ያሉትን ብቻ  በመምረጥ ስለጉዳዮ ጠቅላላ ዕይታ እንዲኖር በማሰብ ቀጥሎ በሚቀርቡ ንዑሳን  ክፍሎች ለማካተት  ተሞክሮአል፡፡

Continue reading
  12486 Hits