Font size: +
8 minutes reading time (1514 words)

ወጣቱ ፎቶ አንሺ፣ ጃንሆይ እና ማርክስ

 መምህሩ ወጣቱን ተማሪ ጠየቀው፤ “በየዓመቱ ይህን ፎቶ ታሳየኛለህ፣ ሁሌም አስተያየቴ አንድ ነው፣ አይረባም። ይህን ያህል ፎቶውን ለምን ወደድከው?”

ወጣቱ መለሰ፤ “ምክንያቱማ፤ ይህን የተፈጥሮ ገጽታ ለመፎተት በጣም ትልቅ ተራራ በእንፉቅቅ መውጣት ስለነበረብኝ ነው”።

 የመታደል ውጤት/ተጽእኖ

የተለያዩ ጥናቶችና ግንጥል-ታሪኮች (Anecdotes) እንደሚያሳዩት ሰዎች በእጃቸው ላለ ነገር የሚሰጡት ዋጋ/ቦታ/ግምት፣ ነገሩ ባይኖራቸው ኖሮ ከሚሰጡት ዋጋ ይበልጣል። ሰዎች የሚፈልጉትን ያውቃሉ፣ ፍላጎታቸው ደግሞ ሙሉ፣ ወጥ፣ እና ተሻጋሪ ነው ይሉናል የክላሲካል የምጣኔ ኃብት ምሁሮች፡፡ በእነሱ አባባል ለአንድ ነገር የምንሰጠው ዋጋ ተመሳሳይ ነው፣ ነገሩ በእጃችን ሲኖርና ሳይኖር፡፡ በዚህ ረገድ፣ በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል፣ በጉዋሮ ያለ ጸበል ልጥ መንከሪያ ይሆናል፣ ደብተራ ባገሩ አይከበርም፤ አወኩሽ ናኩሽ ከሚሉት ያገራችን አባባሎች ጋር ይጣረሳል፡፡ በእነዚህ አባባሎች መሠረት፣ በእጃችን ላለ ነገር የምንሰጠው ዋጋ ነገሩ ባይኖረን ከምንሰጠው ዋጋ ያንሳል። (የአገራችን አባባሎች መሰረታቸው ምንድን ነው? ነገሩ በእጃችን ከገባ በሁዋላ ለምንድን ነው የምንሰጠው ዋጋ የሚቀንሰው? ነገሩ እንደ ልባሽ/ያገለገለ ስለሚቆጠርና መልሰን ልንሸጠው ብንሞክር ስለሚቀንስ ነው? ነገሩ በገበያ የማይሸጥ ቢሆንስ? ስለነዚህ አባባሎች ለማውጋት አይደለም። እንዲህ አይነቱን አባባሎች ለማጣጣልም አይደለም። ምሳሌያዊ አባባሎች መቼና በምን ሁኔታዎች የውሳኔ ምክንያት ይሆናሉ፥ መቼ እንደ መሪና መካሪ መቁጠር አለብን ወይስ ወግ የማሳመሪያ ውብ አባባሎች (የቋንቋ ቀለማት) ብቻ ናቸው? ጊዜ ያለፈባቸው፥ ብስባሽ ቅሪቶች ናቸው? ይህን ለሌላ ጊዜ እናቆየው።) ለእነዚህ ምጣኔሃብት ምሁሮች ግን፣ ዋጋው ተመሳሳይ ነው፣ ወይም መበላለጥ የለበትም።

እነዚያ የምጣኔሃብት ምሁሮች ከሚሉት ተቃራኒ በሆነ መልኩ፤ በእጃችን ላለ ነገር የምንሰጠው ዋጋ፣ ሳይኖረን ከምንሰጠው ዋጋ ይለያል ብቻ ሳይሆን ይበልጣልም። ይህ የሚሆነው መቼ እና ለምንድን ነው የሚለውን እንመልከት። ይህን ጉዳይ የመታደል ውጤት/ተጽእኖ (Endowment effect) ይሉታል፣ የታደልንበትን ነገር ባንታደለው ኖሮ ከምንሰጠው በላይ ዋጋ እንሰጠዋለን። ለምንድን ነው ቢሯችን እና ቤታችን የማይፈለግ ወረቀት የሚበዛውና ለማቃጠልም ሆነ በሌላ መልኩ ለማስወገድ (ለምሳሌ ለሸቀጥ መጠቅለያ በመሸጥ) የሚያዳግተን? ለምንድን ነው የማንጠቀማቸው ልብሶቻችንን ለማስወገድ የማንደፍረው? ለምንድን ነው ለረጅም ጊዜ አብሮ የቆየን አቋም ለመቀየር የምንቸገረው፤ ምንም እንኩዋ የማይረባ ስለመሆኑ አሳማኝ ምክንያት ቢቀርብልን እና ብናምንበትም? በሌላ አነጋገር የማናምንበትን የቆየ አስተሳሰብ ለምን ይዘነው እንጉዋዛለን? እንደ አቋም የምንይዘው የምናምንበትን ብቻ አይደለም፤ አንዳንዴ የማናምንበትንም የሙጥኝ እንላለን።

ልብ በሉ ነገሩ በእጃችን በመቆየቱ የተነሳ ብቻ የሚመጣ ሁኔታ አይደለም። ለአፍታም ቢሆን የቆየው፣ የዋጋ ልዩነት ይኖራል። በእጃችን የቆየው ብዙ ጊዜ ከሆነ ደግሞ የዋጋው ልዩነት ሊበዛ ይችላል። ለነገሩ ጥያቄው፤ በእጃችን ለቆየ ነገር ለምን ትልቅ ዋጋ እንሰጣለን የሚል አይደለም። ጥያቄው ሳይኖረን በፊት የምንሰጠው ዋጋ፣ ለምን ከኖረን በኋላ ጨመረ የሚል አይደል። የተለያዩ ጊዜዎችን እያወዳደርን አይደለም። በተለያየ ጊዜ ያሉ ዋጋዎችን እንዳሉ በቀጥታ ማወዳደር አይቻልም። ያማ ዱባን እና ዱባለን ማወዳደር ይሆናል፡፡ በተለያየ ጊዜ ያሉ ዋጋዎችን ለማወዳደር፣ የግድ አንደኛውን በወለድ መጠን አስልተን ወደ ሌላኛው ጊዜ መለወጥ ስላለብን። ጥያቄው የሚመለከተው ተመሳሳይ ጊዜን ነው። ነገሩ በእጃችን እያለ የምንሰጠው ዋጋ፤ ነገሩ ባይኖር ኖሮ ከምንሰጠው ዋጋ ለምን ይለያል ነው ጥያቄው። ለምሳሌ አምስት ብር የገዛነው እስክርቢቶ ወዲያው እንደገዛነው ካምስት ብር የበለጠ የሙጥኝ የምንለው። ምናልባት ዋጋው አምስት ብር ካምስት ሳንቲም ነው ብንባል ኖሮ ላለመግዛት የምንወስን ሰዎች፣ እስክርቢቶውን ባምስት ብር ከገዛነው በኋላ ግን የምንሰጠው ዋጋ ካምስት ብር ወድ አስር ብር ከፍ ይላል፤ ምሳሌ ነው (በዚህ ምሳሌ በሁለቱ ሁኔታዎች የጊዜ ልዩነት የለም ብለን እናስብ፣ ለዛ ነው ወዲያው የሚለውን ቃል የተጠቀምኩት)። ሰዎች በእጃቸው ላለ ነገር የሚሰጡት ዋጋ ቀድሞ ከሚሰጡት ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ያሁኑ ዋጋ ይበልጣል፤ ይህ የሚሆነው ጊዜ በማለፉ የተነሳ የሚመጣ አይደለም፤ እንዳልኩት በተለያየ ጊዜ ያሉ ሁለት ዋጋዎችን በቀጥታ ማወዳደር የለብንም፣ ወደ ተመሳሳይ ጊዜ ማምጣት አለብን። ይህን የምናደርገው ደግሞ የቀድሞው ዋጋ ወደ አሁን በመለወጥ ወይም ያሁኑን ዋጋ በፊት ቢሆን ኖሮ ወደሚኖረው ዋጋ በመቀየር ነው፣ በገበያ ያለውን የገንዘብ ዋጋን (ወይም የወለድን መጠንን) ግምት ውስጥ በማስገባት። ነገር ግን ያነሳሁት ጉዳይ በተመሳሳይ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ፤ሲኖረን እና ሳይኖረን የምንሰጠው ዋጋ ለምን ተለያየ የሚል ነው። ለምሳሌ የጊዜ ልዩነትን ለማስተካከል፣ የወለድ መጠን አባዝተነውም ቢሆን ተመሳሳይ መሆን አለበት ይሉናል የክላሲካል ምጣኔሃብት ምሁሮች። የሙከራ ጥናቶች ያነሱት ጉዳይ ደግሞ በተግባር ግን ዋጋው ይለያያል፣ ምንም የጊዜ ልዩነት ሲኖር (ወደተመሳሳይ ጊዜ ተለውጦም) እና ሳይኖር። ይህ ለምን ሆነ? የጊዜ ልዩነት የገንዘብ የመግዛት አቅምን ስለሚቀይር ነው የሚለው ምክንያት ሊሆን አይችልም፣ ምክንያቱም ያንን ግምት ውስጥ አስገብተነዋልና።

ክላሲካል የምጣኔሃብት ባለሙያዎች ሰዎች የሚፍልጉትን ያውቃሉ፤ ስለፍላጎታቸው ከነሱ በላይ ያወቀ ቡዳ ነው ይሉናል። እንዲሁም ፍላጎታቸው ሙሉ ነው። ሁለት ምርጫ ብንሰጣቸው፣ ፍላጎታቸው ከሶስት አማራጮች ውጭ አይወጣም። ለምሳሌ የተሰጣቸው ምርጫ እንድ ኪሎ ሙዝ ወይስ እንድ ኪሎ ገንፎ የሚል ይሆናል። ስለዚህ አንድ ሰው ፍላጎቱ ከሶስት አንዱ ነው የሚሆነው። ሙዝን ይመርጣል፣ ወይም ግንፎን ይመርጣል፣ ወይም ሁለቱንም በተመሳሳይ መልኩ ሊሆን ይችላል የሚያያችው። እንዲሁም ሰዎች የሚፈልጉትን ያውቃሉ ሲባል፣ በተመሳሳይ ጊዜ አንዴ ሙዝን፣ አንዴ ደግሞ ገንፎን ሊመርጥ አይችልም። ከላይ እንዳልኩት ደግሞ፣ ሙዝን መርጦ፣ ወዲያው ደግሞ ገንፎን ሊመርጥ ይችላል።

እንድርድሪት

ይህን ለመተንተን/ለማስረዳት እንድርድሪት (Inertia) የሚባለው ክስተት ወይም ጽንሰ ሃሳብ ይጠቅመናል። በአውቶብስ ቆሞ የሚሄድ ሰው ድንገት መኪናው ቢቆም፣ ሰውየውን ወደ ፊት ያንደረድረዋል። ልክ መቆም እንዳልፈለገ ሰው፣ ጉዞውን መቀጠል እንደፈለገ ሁሉ (ምንም እንኩዋን አውቶብሱ እንዲቆምለት የጠየቀው እሱ ቢሆንም)። በተመሳሳይ መልኩ መኪናው ቆሞ ከነበረና፣ መንቀሳቀስ ሲጀምር በውስጡ ያሉት ውደ ሁዋላ እንደሚንደረደሩት ሁሉ።

መላመድ

ሁለተኛው ማብራሪያ፣ በተለይ ደግሞ የጊዜ ልዩነት ካለና በወለድ በማስላት ወደ ተመሳሳይ ጊዜ ለውጠነውም የዋጋን ልዩነት ካየን፣ መላመድ የሚፈጥረው ስሜታዊ ዋጋ ሊሆን ይችላል። በወለድ ለማጣጣም ሲሞከር፣ መላመድ የሚፈጥረውን ስሜታዊ ዋጋ ግምት ውስጥ አናስገባም። እናም ልዩነቱ የተፈጠረው በመላመድ ነው ሊባል ይችላል። ይህ ከእንድርድሪት ማብራሪያ የተለየ ነው።

ዋናው አነጻጻሪው ነው

ሶስተኛ ሰዎች እንዴት ነው ለእንድ ነገር የሚሰጡትን ዋጋ የሚተምኑት የሚለውን ማወቅ ተገቢ ነው። እንደ ክላሲካል ምጣኔሃብት ምሁሮች አባባል ሰዎች ለማንኛውም ነገር የፍላጎታቸውን ልክና ደረጃመወስን ይችላሉ። ነገር ግን የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች የፍላጎታቸውን ልክ ለመወስን ባብዛኛው በንጽጽር ነው የሚያሰላስሉት። ይህ በመሆኑ የተነሳ የቀረበላቸው ንጽጽር ፍላጎታቸውን ይወስነዋል።

በመሆኑም ሰዎችን በምክር፣ በጥቅምና፣ በዱላ ብቻ አይደለም መቆጣጠር የሚቻለው። የምናቀርብላቸውን ንጽጽር በመቀየር ወደ ምንፈልገው ምርጫ እንዲያዘነብሉ ማድረግ ይቻላል። (ካስ ሳንስቴይን እና ታለር ይህን በተመለከተ ሲጽፉ፤ መንግስት ነጻነትን የማይሸረሽር የአባትነትን (libertarian paternalism) ሚና መጫወት ይችላል፥ ይገባልም ይላሉ።) ለዛ ነው ልታማልላት ወደምትፈልገው ሴት ስትሄድ፣ ፉንጋ ጉዋደኛህን አስከትል፣ እጅግ ቆንጆ ነህ ብላ ታስባለች፣ ቆንጆ ጉዋደኛህን አስከትል፣ ፉንጋ ነህ ብላ ታስባለች። ስለዚህ አንተ እንዳስከተልከው ሰው አይነት፣ ወይ ቆንጆ ወይ ፉንጋ ትሆናለህ ለልጅቱዋ። ተመሳሳይ ሰው አይደለህም፣ ያንተ ማንነት እንደ ሁኔታው ይለያያል። እስስትን ያስታውሱዋል። እስስትስ እየተቀያየርች ነው።

በተመሳሳይ ሁኔታ የእስክርቢቶውን ምሳሌ ስንወስድ፣ ሁለት ሁኔታዎችን ማየት እንችላለን። አንደኛው እስክርቢቶው የራስህ ሲሆን እና ሁለተኛው እስክርቢቶው የእኔ ሲሆን። እስክርቢቶው የእኔ ሲሆን፣ ለእክስርቢቶው የምትሰጠው ዋጋ አምስት ብር ነው፣ ከዛ አምስት ሳንቲም አይጨምርም። በመሆኑም ከእስክርቢቶውና ከአራት ብር ሲባል እስክርቢቶውን ትመርጣለህ። ነገር ግን እስክርቢቶው የራስህ ሲሆን፣ ለእስክርቢቶው የምትሰጠው ዋጋ ወዲያው ወደ ስድስት ብር ያሻቅባል፤ በመሆኑም ከስድስት ብር በላይ ካልሆን በሰተቀር አትሸተውም። ይህ ለምን ሆነ ቢባል፣  በሁለቱ አማራጮች ያሉት እስክርቢቶዎች የተለያዩ ናቸው የሚል ነው። የንጽጽሮቹ ልዩነት የማንነት (የአይነትና የጥራት) ልዩነት ያመጣል። አንተ ከፉንጋ ጉዋደኛህ ጋር ስትሆን እና ከቆንጆ ጉዋደኛህ ጋር ስትሆን የተለያየህ ነህ (በአይነትና በጥራት)። (ጉዋደኛህን ንገረኛና ማንነትህን ልንገርህ፥ ወይም ከአህያ ጋር የዋለች ጊደር ፈስ ተምራ መጣች ከሚለዉ አባባል ይለያል።) ያለህን ታውቀዋለህ፣ ስለዚህ የምትሰጠው ዋጋ ከፍ ይላል። በእጅህ ያለው አምስት ብር ካምስት ሳንቲም ሲሆን፣ እና እስክርቢቶው በእኔ እጅ ሲሆን፣ ያለህ ነገር ይበልጥብሃል፣ ስለዚህ አምስት ብር ካምስት ሳንቲም ይበልጥብሃል። ነገር ግን እስክርቢቶው ባንተ እጅ ሲሆን እና በእኔ እጅ ያለው አምስት ብር ካምስት ሳንቲም ሲሆን፣ አሁንም ያለህ ይበልጥብሃል፣ ስለዚህ እስክርቢቶው ይበልጥብሃል። 

ከማያውቁት መላእክት የሚያውቁት ሰይጣን ይባላል። ይህ ከጉዳዩ ጋር ተመሳሳይ አይደልም። በዚህ አባባል መሰረት ሁልጊዜ የለመድከውን፣ የምታውቀውን ትመርጣለህ ሰይጣንም ቢሆን። በዚህ ሶስተኛ ማብራሪያ መስረት ግን፣ ሁልጊዜ የለመድነውን የምናውቀውን እንመርጣለን ሳይሆን፣ የምርጫዎቹ አቀማመጥና ልዩነት ለተመሳሳይ ነገር የምንሰጠውን ዋጋ ያለያየዋል። ጥያቄው ሰይጣኑ አንድ ቢሆንም ስናውቀውና ሳናውቀው ግን አንድነቱ ይቆማል። ያ ማለት ስናውቀው ሁልጊዜ እንመርጠዋለን ሳይሆን፣ አንጻራዊ ዋጋው ግን ይለያል።

አንድ ሰው እራቱን መብላት ፈልጎ ሚዳቆ ተኩሶ ገደለ እና ምላሱን ጠብሶ በላ። ጡዋት ደግሞ ሲነቃ ያደረ ሚዳቆ ከምበላ ብሎ ሌላ ሚዳቆ ገድሎ ቁርሱን ዱለት በላ፡፡ ስለዚህ ድርጊት ተገቢነት ጥያቄ ቢነሳ፣ መልስ መስጠት እንደሚያዳግት ጋሬት ሃርዲን የተባለ ጸሃፊ ይናገራል። ነገር ግን ይህ የሆነው በሁለት አማራጭ ሁኔታዎች ነው ብለን እናስብ። አንደኛው ሚዳቆ ከሚገባው በላይ በዝቶ በሚያስቸግርበት ወቅት እና ሚዳቆ ተመናምኖ ሊጠፋ በደረሰብት ሁኔታ። በሃርዲን እምነት በእነዚህ ሁለት አማራጮች ድርጊቱ ተመሳሳይ ነው ብለን መናገር ይከብደናል፣ ባንደኛው ሁኔታ ድርጊቱን ኮንነን፣ በሌላኛው ሁኔታ ደግሞ ድርጊቱን እንደግፋለን። ሃርዲን ይህን ምሳሌ በመጥቀስ አትግደል፣ አታመንዝር የሚሉት አይነት ትእዛዞችን ለመቀበል ያስቸግራል ይለናል። መግደል ሁሉ አንድ አይነትአይደለም፣ አንደኛው ነፍስ ማጥፋት ሲሆን ሌላኛው ነፍስ ማዳን ነው። ዋናው አንጻጻሪው ነው።

ቀሊጥ ወጪ

አራተኛው ማብራሪያ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ቀሊጥ ወጪ (sunk cost) የሚሉት ነው። ቀሊጥ ወጪ የምንለው አንዴ ከወጣ በሁዋላ፣ መልሶ ሊሽጥ የማይችል አይነት ወጪ ነው፣ ወይም ሊመለስ የማይችል ወጪ። እንዲህ አይነት ወጪዎች ሰዎች ወደ አንድ የኢኮኖሚ ዘርፍ እንዳይገቡ ወይም ከገቡ በሁዋላም እንዳይወጡ መሰናክል የሚሆኑናቸው። ምክንያቱም እንዲህ አይነት ወጪ፣ ባገለገል እቃ ገበያም እንኩዋን የረባ ዋጋ ስለሌለው ነው። ለምሳሌ፣ ነገሩን ለማግኝት አንድ ሰው ከከፈለው ገንዘብ በተጨማሪ ያወጣው ቀሊጥ ወጪ ካለ፣ እንደ ቀሊጥ ወጪው መጠን ለነገሩ የሚሰጠው ግምት/ቦታ ይጨምራል። ምንም እንኩዋን ቀሊጥ ወጪውን መልሶ ማግኝት ባይችልም፣ ነገሩን አብዝቶ ዋጋ በመስጠት፣ ቀሊጥ ወጪውን ባያወጣ ኖሮ ሊኖረው ከሚችለው የበለጠ ግምት ይሰጠዋል። ሚስትህን ሳታገባ፣ ሳትተዋወቃት፣ ካገባህ በሁዋላ፣ አብራቹ ከኖራቹ በሁዋላ የምትሰጣት ቦታ ይለያያል። ያወጣህው ቀሊጥ ወጪ በበዛ መጠን የምትሰጠው ዋጋም ይጨምራል። ለምሳሌ፣ ሴቲቱን የበለጠ ለማወቅ የምታጠፋው ጊዜ፣ አብረህ ያሳለፍከው ጊዜ ተመልሶ ተሽጦ ዋጋ አያወጣም። ልብ ማለት የሚገባው በዚህ አብሮ ቆይታ የተማርከውና ያዳበርከው ችሎታ ካለ እና ሌላ ሴት ወይም ወንድ ወይም ንግድን አስመልክቶ በሙሉ የሚጠቅምህከሆነ እንደ ቀሊጥ ወጪ ሊቆጠር አይገባም። ይህን ካልኩኝ ዘንዳ፣ እስክርቢቶውን ለመግዛት ያወጣነው ቀሊጥ ወጪ ካለ፣ ለእስክርቢቶው የምንሰጠው ቦታ ከከፈልነው ገንዝብ ከፍ ይላል።

የወጣቱ ተማሪ መልስንም ከዚህ አንጻር ማብራራት ይቻላል። ልብ ይሉዋል፣ ይህ ማብራሪያ የማርክስ የዋጋ መላምት (Marx’s labor theory of value) እየተባለ ከሚጥራው ይለያል፣ እንዴት ማለት ጥሩ ነው፣ ማለቴ ጥሩ የቤት ስራ። ውሃ ከአልማዝ ይልቅ ለህይወታችን አስፈላጊ ነው፣ ታዲያ ይህ ሆኖ እያለ ለምን አልማዝ ከውሃ የበለጠ ተወደደ? የማርክስ መልስ የፈሰሰበት ጉልበት የሚል ነው። ጃንሆይ ብሄራዊ ትያትር በር ላይ ያለውን አንበሳ ሲመርቁ አሉ እንደተባለው፣ ‘ምንም እንኩዋ ይህ በፊታችን የቆመው ሃውልት በምንም መልኩ አንበሳ ባይመስልም፣ የወጣበት ወጪ ግን አንበሳ አስመስሎታል’። ውድ ዋጋ ተከፍሎበታል።

በእነዚህ አራት ማብራሪያዎች ለመተንተን የተሞከረው ጉዳይ (የመታደል ውጤት/ተጽእኖ) ሰፊ እንድምታዎች ያሉት ነው። ለምሳሌ

·        ከአስር ብር ሽልማት ይልቅ የአስር ብር ቅጣት ያተጋል

·        አንዳንድ ማህበራት አዲስ አባሎቻቸውን ሲመርጡ/ሲመለምሉ፣ ዘግናኝ እና/ወይም አስቸጋሪ እና እንደ ቀሊጥ ወጪ ሊቆጠር የሚችል ቅድመሁኔታን ያስቀምጣሉ

·        ሞክረክ ከወደድከው ትገዛዋለህ፣ ወይም ላንድ ወር በነጻ ተጠቀምና ከወደድከው ትገዛዋለህ የሚል የሽያጭ መንገድ

·        ለተወሰነ ጊዜ ክፍት ሆኖ የሚቆይ ዲጂታል ጨረታ

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ያላቸው ደረጃ
በኮንስትራክሽን ውሎች አፈጻጸም ወቅት የመሀንዲሱ ሚና እና የጥቅም ግጭት
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 25 July 2024