በኮንስትራክሽን ውሎች አፈጻጸም ወቅት የመሀንዲሱ ሚና እና የጥቅም ግጭት

እንደሚታወቀው በኮንስትራክሽን ውሎች አፈጻጸም ወቅት መሀንዲሱ የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ አንዳንዴም መሀንዲሱ በውኑ የመሀንዲስ አድራጎት የማይመስሉ ተግባራትን ሲያከናውን ይሰተዋላል፡፡ ይህም ነገሩ አጀብ! ቢያሰኝም እውነታው ግን ከዚህ የራቀ አይደለም፡፡

እርግጥ ነው መሀንዲሱ ብዙ አልፎ አልፎም እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ ተግባራትን የሚያከናውንበት ጊዜ አለ፡፡ ለአብነት ያህልም፡-የግንባታው ዲዛይነር፣ የአሰሪው ወኪል (employer’s agent)፣ አማካሪ (supervisor)፣ የሥራ ርክክብ አረጋጋጭ (certifier)፣ ብሎም አንዳንዴ አራጊ ፈጣሪ ገላጋይ ዳኛ ወይም ከፊል አስታራቂ (adjudicator or quasi-arbitrator) ሊሆን ይችላል፡፡

በነገራችን ላይ የመሀንዲሱ ሚና ከላይ በጠቀስናቸው ተግባራት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በግንባታ ውሉ አፈጻጸም ወቅት አስቀድሞ ለፕሮጀክቱ አፈጻጸም የሚሆኑ ሥራዎን በራሱ አነሻሽነት (proactive works) ወይም ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ለውሉ አፈጻጸም የሚሆኑ ተግባራት እና ሥራዎችን በአሰሪው ወይም ሥራ ተቋራጩ ትእዛዝ (reactive works) እንዲሁም በውሉ በግልጽ ተለይተው ባይሰጡትም ለፕሮጀክት አፈጻጸም አንድ መደበኛ መሀንዲስ ሊሰራቸው የሚችሉ ሥራወችን ሊያከናውን ይችላል፡፡

አንዳንዴም ባለሃብቶች የመገንባት ሃሳቡ ኑሯቸው ወደ ስራው ሊገቡ ሲሉ ዘርፈ ብዙ የቴክኒክ ችግሮች፣ የምርታማነት እና ንግድ ጉዳዮች እንዲሁም የሕግ መወሳሰብ ባለማወቃቸው ብሎም ከግምት ባለማስገባታቸው የተነሳ እክል ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ በሲቪል ምህንድስናው ዘርፍም ይህንን የባለሃብቱን ሃሳብ እና ስጋት ወደ እውነት ለመተግበር አማካሪ መሀንዲሱ ወይም መሀንዲሱየተባለውን ጉዳይ ሊፈጽምለት ይችላል፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው! መሀንዲሱም ሆነ አማካሪ መሀንዲሱ በውል የተጣለባቸውን ሥራወች ሲሰሩ ግልጽ የሆነ የጥቅም ግጭት (manifest conflict of interest) ሊከሰት ይችላል፡፡ እነዚህ የጥቅም ግጭቶችም በሥራው ላይ ከተፈጥሮ ሕግ እና ርትዕ(natural law and equity) አንጻር የፍትሃዊነት ጥያቄ ስለሚያስነሳ በጥልቀት እና በአንክሮ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

የዚህ ጽሁፍ አላማ አንድ መሀንዲስ የሚያከናውናቸው ተግባራት ማብራራት እንዲሁም ከላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት በሚያከናውንበት ወቅት  ሊገጥሙ የሚችሉ የጥቅም ግጭቶችን እንዴት መከላከል ይቻላል የሚሉ ተያያዥ ጉዳዮች መዳሰስ ነው፡፡

1.   መሀንዲስ እና አማካሪ መሀንዲስ ዝምድና እና ልዩነታቸው

በተለምዶው መሀንዲስ ወይም አማካሪ መሀንዲስ የሚሉት ቃላት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘንድ በጣም የተለመዱ እና የታወቁ ናቸው፡፡ አንዳንዴም ሁለቱን ቃላት እያቀያርን ስንጠቀም ይስተዋላል፡፡ ዳሩ ግን በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ሁለቱ ቃላት እጅግ የተለያዩ ናቸው፡፡ እንደ ሥራ እና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ውል አንቀጽ 1(ሐ) ትርጓሜ መሰረት መሀንዲስ ማለት፡-በሥራ እና ከተማ ልማት ሚኒስቴር(አሁን የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በሚባለው) መሀንዲስ ተብሎ በጹሁፍ ማረጋገጫ የተሰጠው የተፈጥሮ ሰው ወይም የሕግ ሰው ነው፡፡  የእንግሊዘና ቅጅው እንደወረደ እንዲህ ይነበባል፡- [T]he Engineer is natural or juridical person designated as Engineer in writing by The Ministry of Works and Urban Development (MoWUD) Addis Ababa, Ethiopia.[Ministry of Works and Urban development standard conditions of contract(1994) Clause 1(c).’’

ከላይ የቀረበው ትርጓሜ ከትችት አላመለጠም፣ለምን ቢባል አንድም በምን ሙያ የተመረቁ ሰዎች ናቸው መሀንዲስ ሚሆኑ ሚለው ግልጽ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል መሀንዲስ ሲባል የሲቪል መሀንዲስ፣የውሃ መሀንዲስ ወይም የአካባቢ ጥበቃ መሀንዲስ የሚለው ቃል በትርጉሙ ያልተመለከተ እና ያለየለት ጉዳይ ነው፡፡

ሌላው ስለ መሀንዲስ ትርጉም በዓለም አቀፉ የአማካሪ መሀንዲሶች ማህበር(FIDIC Redbook 1999) አንቀጽ 1.1.2.4 ላይ የሚከተለው ትርጉም  ሰፍሮ እናገኛለን፡-ውሉን ወደ ስራ ለማስገባት በአስሪው መሀንዲስ ሆኖ እንዲሰራ የሚሾም ሰው ወይም በጨረታ ሰነዱ ስሙ አባሪ የሆነ ሰው ወይም ሥራ ተቋራጩን በማሳወቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ  በአሰሪው የሚተካ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ አይነቱ ትርጉምም መሀንዲስ የሚለውን ቃል ከቃሉበመነሳት ትርጉም ባለመስጠቱ (lexical definition) ትችት ይሰነዘርበታል፡፡

ወደ አማካሪ መሀንዲስም(consulting engineer) ስናመራም ድርሳናት የተለያዩ መገለጫ እና ትርጉም ሰጥተውት እናገኛለን፡፡ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃም አማካሪ መሀንዲስ ማለት ራሱን ችሎ ሙያዊ የምክርአገልግሎት የሚሰጥ አካል ሲሆን በተለይም የፕሮጀክቱ እንቅስቃሴ ምን ዓይነት ተግዳሮቶች ሊገጥመው ይችላል በማለት በመንግስታዊ አስተዳደር ያሉ የፖሊሲና የሕግ ጉዳዮች፣የሳይንስ እና ቴክኖሎጅዊ ምክሮችን እንዲሁም የሲቪል ምህንድስና ትንተናዎችን የሚሰጡ ናቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የማማከር ሥራዎች በአማካሪ መሀንዲስነት አገልግሎት ሙያ በተሰማሩ ካምፓኒዎች ይከናወናል ነገር ግን ይህ ተግባር አልፎ አልፎ በግለሰቦችምሲከናወንይስታዋላል፡፡ የዓለም አቀፉ የአማካሪ ማሃንዲሶች ማህበርም ሆነ የኢትዮጵያው የሥራ እና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ውሎች አማካሪ መሀንዲስ ማን ነው የሚለውን ጉዳይ በግልጽ ትርጉም አለሰጡትም፡፡

ሆኖም ግን የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ አንቀጽ 2(7) ላይ አማካሪ መሀንዲስ ከማለት ይልቅ አማካሪ በማለት ትርጉም ለመስጠት ይሞክራል፡፡  ረቂቅ አዋጁም አማካሪ ማለት በኮንስትራክሽን ወቅት የዲዛይኑ ተስማሚነት ጥናት፣የቁጥጥርና የማማከር ሥራ እንዲሁም ውል የማስተዳደር አገልግሎት የሚሰጥ ሰው ወይም ድርጅት ነው በማለት ይገልጸዋል፡፡

በዓለም አቀፋ አማካሪ መሀንዲሶችማህበር ጥናታዊ ምልከታ መሰረት አማካሪ መሀንዲሶች የሚከተሉትን ተግባራት ሊያከናውኑ ይችላል፡፡ ለአብነት ያህልም (ሀ) ደንበኛው ሊፈልግ የሚችለውን ዲዛይን በጥሩ ሁኔታ ሰርቶ ማቅረብ ይህም ሲባል የግንባታውን ስዕል ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ስለ ሚገነባው ነገር በዲዛይኑ መሰረት በግልጽ      ቋንቋ ለባለቤቱ መግለጽ እና ማስረዳት አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሚያስፈልጉ የግንባታ ማቴሪያሎች(ግብዓቶችን) ብሎም የሚያስፈልገውን የሰው ሃይል መጠን አስቀድሞ ማርቀቅ አለበት ይህን በሚያደርግበት ጊዜም አማካሪ መሀንዲሱ የግንባታ ወጪወች ዝርዝር(Bill of quantities) ማዘጋጀት አለበት፡፡ (ለ)ተወዳዳሪ የሆነ የግንባታ ዋጋ በሥራ ተቋራጮች እንዲቀረበለት አሰፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን ማዘጋጀት ብሎም ለተወዳዳሪዎች ክፍት ማድረግ እንዲሁም በጨረታው ሂደት የተቀበላቸውን ጨረታዎች እና የመረጣቸውን ኮንትራክተሮች ላይ ተገቢውን ምክር አክሎ ለፕሮጀክቱ ባለቤቱ ማሳወቅ አለበት፡፡ (ሐ) የፕሮጀክቱ ሥራ ከተጀመረ በኋላም የሥራውን ሂደት በታቀደለት የዲዛይን ዕቅድ መሄድ ለመሄዱን መመርመር ብሎም መቃኘት አለበት፡፡ (መ) በመጨረሻም ውሉን ማስተዳደር፣ይህም በውሉ አፈጻጸም ወቅት ለሚነሱ ጉዳዮች አስፈላጊ ምላሽ መስጠትን ጨምሮ ሥራው መጠናቀቁን ተከትሎ የማረጋገጫ ሰርቴፊኬት ለሥራ ተቋራጩ መስጠትና አንዳንዴም ግጭቶች ሲፈጠሩ የዳኝነት ሥራ መስራትን ይጨምራል፡፡

አማካሪ መሀንዲስ ከላይ በተራ ቁጥር (ሀ) እና (ለ) የተዘረዘሩትን ተግባራት ሲያከናውን የፕሮጀክቱ ዋና አማካሪ እና ተቆጣጣሪ (adviser and consultant) ሆኖ ያገለግላል፡፡ በሌላ በኩል አማካሪ መሀንዲስ በተራ ቁጥር (ሐ) እና (መ) ያሉትን ተግባራት ሲያከናውን የመሀንዲስ(engineer) ተግባር ከመሆኑም በላይ የአሰሪው ወኪል(agent of the employer) እንደሆን ይታወቃል ይህም በተለያዩ ወጥ ውሎች ላይ ተመልክቷል፡፡

በተለምዶው የሲቪል ግንባታ ፕሮጀክት ሥራዎች በሚከናወኑበት ወቅት ሁለት ውሎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ አንድም በአማካሪ መሀንዲስ እና በአሰሪ መካከል አሊያም በአሰሪውና በሥራ ተቋራጩ መካከል ሊሆን ይችላል፡፡ በመጀመሪያው ውልም ሥራ ተቋራጩ የውሉ አካል አይደለም በተመሳሳይም መሀንዲሱም በአሰሪውና በሥራ ተቋራጩ መካካል በሚደረገው ውል ተሳታፊ አይደለም፡፡ ይህም ዓይነት አሰራር የራሱ የሆኑ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ፡-(1)የፕሮጀክቱ ሥራ ለሥራ ተቋራጮች ከመሰጠቱ በፊት የፕሮጀክቱ ዲዛይን እንዲያልቅ ከማድረጉም በላይ ተፎካካሪ የፕሮጀክት ጨረታ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ (2)የፕሮጀክቱን ሥራ ከመቆጣጠር ባለፈ ጥራት ያለው ሥራ ለመስራት ያስችላል፡፡  (3)ሌላው ደግሞ የመጨረሻው የፕሮጀክት ዲዛይን ከመጽደቁ በፊት እንደልብ ዝርዝር ዲዛይኖችን እንድንቀያይር በር ይከፍታል፡፡ (ዶ/ር ናኤል፡ቡኒ፡እኤአ 2005፡157)

በዚህ አጋጣሚ ከውል ሕግ መሰረታዊ ነጥቦች አንጻር የሚነሳ አንድ ጥያቄ አለ፡፡ እሱም ውል ከተዋዋይ ወገኖች ውጭ ተፈጻሚነት እንደሌለው የታመነ ነው፡፡ ይህም በእንግሊዘኛው “Principle of Privity of contract” የሚባለው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፍትሃብሄር ሕግም በአንቀጽ 1952 ላይ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት ውሎች ልዩ ሁኔታዎች(exceptions) እንደተጠበቁ ሆነው በሦስተኛ ወገኖች ላይ ተፈጻሚ አይሆኑም ማለት ነው፡፡ ታዲያ! ከዚህ መርሆ ተቃርኖ በሚመስል መልኩ መሀንዲሱ እንዴት በአሰሪው እና በሥራ ተቋራጩ መካከል በተደረገ ውል ላይ ሊገባ ይችላል ብሎም የተለያዩ ሚናዎች ሊኖሩት ቻሉ የሚሉ ጥያቄዎች ከዚህም ከዚያም ይስተጋባሉ፡፡ የሆነው ሆኖ በጹሁፋ መግቢያም እንደተመለከተው መሀንዲስ የአሰሪው ወኪል መሆኑ በራሱ የተለያዩ በሕግ ፊት ሊጸኑ የሚችሉ ተግባራትን(juridical acts) ሊፈጽም ይችላል እንደ ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በወጥ ውሎች ላይ እንደተመለከተው የፕሮጀክቱ ተሳታፊ በመሆኑ የተለያዩ ተግባራትን እንደሚያከናውን ግልጽ ነው፡፡

ይህንን ንዑስ ክፍል ለማጠቃለል ያህል  መሀንዲስ እና አማካሪ መሀንዲስ አንድም በአንድ ሙያ ውስጥ ሊኖሩ መቻላቸው ብቻ ሳይሆን የኮንስትራክሽን ሂደት መሪ ተዋንያን መሆናቸው ሰፊ ቁርኝት እንዳላቸው እንረዳለን፡፡ ሆኖም ግን ከላይ ትረጓሜ ለመስጠት እንደተሞከረው መሀንዲስ ሲባል የአሰሪው ቀኝ እጅ ወይም ወኪል ሆኖ ፕሮጀክቱን የሚከታተል ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ አማካሪ መሀንዲስ ራሱን ችሎ የሙያ አገልግሎት የሚሰጥ ሰው ወይም ድርጅት እነደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

2.  የመሀንዲስ ተግባራት

በዚህ ክፍል ጸሀፊው ትኩረቱን ያደረገው አንድ መሀንዲስ በአንድ ፕሮጀክት አፈጻጸም ወቅት ምን ሊያደርግ ይገባል የሚለውን ይሆናል፡፡ በዋናነት ግን አንድ ማሃንዲስ የሚከተሉትን ተግባራት ያከናውናል፡-ዲዛይን ማውጣት፣ የማማከር፣ የውክልና ተግባራት፣የፕሮጀክት ቅድመ ሥራዎች፣የፕሮጀክት ድህረ ሥራዎች፣በርክክብ ወቅት የማረጋገጥ ሥራዎች እና የዳኝነት ብሎም ከፊል ሽምግልና ሥራዎችን ያጠቃልላል፡፡

2.1 ዲዛይን ማውጣት /Acting as a designer/

እንደሚታወቀው የመሀንዲሱ የበኩርና የመጀመሪያ ሥራው ሊሆን የሚችለው የግንባታውን ዲዛይን መንደፍ ነው በተለይም የፕሮጀክቱ ዋና ውል ወደ ሥራ በሚገባበት ወቅት መጠናቀቅ እና መከናወን ያለበት ተግባር ነው፡፡ በነገራችን ላይ ዲዛይን የማውጣት ሂደት ውሳኔ የሚያስወስኑ በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ ለአብነት ያህልም የፕሮጀክቱን ይዘትና ቅርጽ መወሰን፣ትክክለኛውን የዲዛይን ስዕል ጨምሮ የግብዓትና የሰው ሃይል ዝርዝር ሁኔታዎች እንዲሁም የሚጠበቀውን የጥራት ጉዳይ ይጨምራል፡፡

ዲዛይን ማለት ምን ማለት ነው? የሥራ እና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ውል ትርጉም አልሰጠውም ሆኖም ግን ከአንቀጽ 1(በ) እና 1(ተ) ድንጋጌዎች የጣምራ ንባብ እንደምንረዳው ዲዛይን ማለት ሥዕሎችን(drawings) ጨምሮ የፕሮጀክቱ ዝርዝር መገለጫዎችን  (Specifications) ሊይዝ እነደሚችል ነው፡፡

በመጨረሻም አንድ የእንግሊዝ ፍ/ቤት በሞሬስክ እና ሒክስ በነበረው ክርክር እንደተወሰነው አንድ ዲዛይነር(እንደነገሩ ሁኔታ ቀራጺ) የተሰጠውን ሥራ ለሌላ አሳልፎ በውክልና መስጠት አይችልም፡፡ ፍ/ቤቱም በሰጠው ሀተታ አንድ የህንጻ ባለቤት የዲዛይን ስራውን ለቀራጺው( architect) ከሰጠው ባለቤቱ ቀራጺው በውሉ ማከናወኑን ማረጋገጥ ይችላል፡፡

የዚህ ዓይነቱ ውሳኔ በፍትሃብሄር ህጋችንም ላይም ስለውል በጠቅላላው አንቀጽ 1740(1) ላይ እንደ ተቀመጠው ባለዕዳው ራሱ ውሉን መፈጸም እንዳለበት ከሚናገረው ድንጋጌ ጋር ይመሳሰላል፡፡

2.2            የአሰሪው ወኪል /The employer’s agent/

በዚህ ንዑስ ክፍል የምንመለከተው ደግሞ መሀንዲሱ የአሰሪው ወኪል በመሆኑ ሊያከናውናቸው የሚችሉ ተግባራትን ይሆናል፡፡ ይህም የሚሆነው ባለቤት(አሰሪ) አንድ ፕሮጀክት ለማሰራት ብሎ ሥራ ተቋራጭ ቢቀጥር እና ለፕሮጀክቱ አፈጻጸም የሚሆኑ በርካታ ሥራዎች ማለትም ከበጀት ጀምሮ እሰከ ጥራት ሥራዎች መሰራት ቢጠበቅበት በዚህ ጊዜ ታዲያ ባለቤቱ በጊዜ እጥረት ወይም በቦታ አለመመቸት ወይም በሌላ ምክንያት ይህን ማድረግ ካልቻለ በህጋዊ ወኪሉ ማከናወን ይችላል፡፡  ይህንንም የውክልና ተግባር የሚያከናውነው መሀንዲስ ይባላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ውክልና ማለት ተወካዩ በሕግ ፊት ሊጸና የሚችል አንድ ወይም በርካታ ተግባራት ለወከለው አካል ለማድረግ የሚገባው ውል ነው፡፡ /የፍ/ሕ/ቁ 2199/ ይመልከቱ፡፡   

ውክልና ከሕግ ወይም ከውል ሊመነጭ እንደሚችል የኢትዮጵያ የፍትሃብሄር ሕግ አንቀጽ 2179 ላይ ተመልክቷል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በኮንስትራክሽን ፕሮጀከቶችም እንደሚስተዋለው በአሰሪውና በመሀንዲሱ መካከል የሚፈጠረው ውክልና የሚመነጨው አርስ በርሳቸው በሚያደርጉት ውል ነው፡፡

በሥራው አፈጻጸም ወቅት መሀንዲሱ ወኪል በመሆኑ ምን ዓይነት ተግባራትን ያከናውናል የሚለው ጥያቄ ተገቢ ነው፡፡ ወኪል በመሆኑም ከላይም እነደተመለከተው ዲዛይን ማውጣት፣የጥራት ቁጥጥር(quality control) እና የአስተዳደር ሥራዎችን ማከናወንን ይጨምራል፡፡

ሌላው መታየት ያለበት ጉዳይ መሀንዲሱ የአስተዳደር ሥራዎች ይሰራል ሲባል ምን ዓይነት ሥራዎችን ይጨምራል የሚለው ነጥብ ነው፡፡ አርግጥ ነው የዓለም አቀፋ የአማካሪ መሀንዲሶች ማህበር (FIDIC Redbook 1999) ወጥ ውልም ሆነ የሥራ እና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ውል የአስተዳደር ጉዳይ የሚለውን ሀረግ አላብራሩትም፡፡ ዳሩግን ከፍትሃብሄር ሕግ አንቀጽ 2203 እና 2204 ምንባብ እንደምንረዳው አንድ መሀንዲስ የአስተዳደር ሥራ ይሰራል ሲባል አንድም አጠቃላይ የማስተዳደር ሥራዎች(Acts of management)ይጨምራል፡፡ አሊያም ደግሞ ንብረቱን የመጠበቅ፣የማቆየት ብሎም መሰል ሥራዎች መስራትን ያጠቃልላል፡፡

2.3            የማማከር/ supervision/

የማማከር ተግባር የሚባለውም መሀንዲሱ ስለጠቅላለው የሥራ አካሄድና ሁኔታ የመከታተል እና አካሄዱ ሲበላሽም የእርምት አርምጃን መውሰድን ያጠቃልላል፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ መሀንዲሱ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ማነኛውንም ጊዜያዊ የሥራ መጠናቀቅ እንዲሻሻል ወይም እንዲስተካከል ማደረግ ይችላል ወይም ሥራው ከደረጃ በታች ነው ብሎ ሲያስብ ሥራውን አልቀበልም ወይም አልረከብም ለማለት ይቸላል፡፡ ይህ የማማከር ሚናው በፕሮጀክቱ አካሄድ እና ውል አፈጻጸም ላይ በጣም ወሳኝ ሆኖም ግን ሚናው ሥራ ተቋራጩን ስለ ሠራው ጥራት የማገዝ (supportive role) እንጂ ሙሉ በሙሉ የጥራቱን ሥራ ስለማሳካቱ አይደለም፡፡

በዚህ አጋጣሚ የመሀንዲሱ የማማከር ተግባሩ እስከምን ድረስ የሚለው ጥያቄ ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ እርግጥ ነው መሀንዲሱ አማካሪ ነው ሲባል በዋናነት የሚከናወነውን ስራ መቆጣጠር(Monitoring) ነው ይህም ሲሆን ሥራው በታቀደለት መሰረት እየሄደ መሆኑን ጨምሮ ተጨማሪ ትዕዛዞችን በመስጠት አስፈላጊ የሆነ ምርመራ( inspection) እንዲሁም ሙከራን( testing) ያካትታል፡፡ መሀንዲሱ የመቆጣጠር ሥራም ይሰራል ሲባል፡(1) ሥራው በተቀመጠለት ጥራት መሆን አለመሆኑን መከታተል (2) ሥራው በታቀደለት ፕሮግራም መሄድ አለመሄዱን መቆጣጠር (3)በግንባታው ፕላን ወጪ መሰረት ሥራው ስለመሰራቱ የበጀት ቁጥጥር ማድረግ እና (4) በመጨረሻም ከሌሎች ጉዳዮች ማለትም የጥንቃቄ እርምጃዎች(safety measures)፣ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች እና ሌሎች ተያያዥ ነገሮች ጋር መሄድ አለመሄዱን መቆጣጠርን ይጨምራል፡፡

ለማጠቃለል ያህል የማማከር ሥራ ወሳኔ የሚያሻው ሥራ እንደመሆኑ መሀንዲሱ ይህን በሚያደርግበት ጊዜ በጥንቃቄ መስራት ይጠበቅበታል፡፡

2.4            የመሀንዲሱ ቅድመ ሥራዎች/ Doing Proactive duties/

የቅድመ ሥራዎች ሲባል እግንዲህ አንድ መሀንዲስ አንድ ሥራ ወደ ተግበር ከመግባቱ በፊት የሚያደርገው ተግባር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ታዲያ መሀንዲሱ ለሥራ ተቋራጩ ወይም ለአሰሪው የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መልዕክት ሲያስተላልፍ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የቅድመ ሥራዎች የሚባሉት በመሀንዲሱ አነሳሽነት እና ውል አስተዳዳሪነት የሚደረጉ ተግባራትና ሥራዎችን ያጠቃልላል፡፡ (ዶ/ር ናዔል ቡኒ፡2005፡164)

በተለይም በወጥ ውሎች ላይ በእንግሊዝኛው “notify” ወይም ማሳወቅ የሚል ቃል በተደጋጋሚ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ በዚህ ረገድም ከመሀንዲሱ ጋር ቀጥታ ተያያዥነት ያለው ሆኖ ሲገኝ የመሀንዲሱ ቅድመ ሥራ እንደሆነ ያጠይቃል፡፡ ለምሳሌ አንዱ የመሀንዲሱ ተግባር በየጊዜው የሚሾሙ ረዳትመሀንዲሶች ለሥራ ተቋራጩ ማሳወቅ እንደሆነ ይታወቃል፡፡  ይህም በዓለም አቀፋ አማካሪ መሀንዲሶች ማህበር ወጥ ውል ላይም በአንቀጽ 3(2) እንደሚከተለው ይነበባል፡-“The engineer may appoint assistants to the engineer’s representative.Notifythe contractor of the names, duties and scope of authority of assistants.”.

በነገራችን ላይ መሀንዲሱ ሌሎች በርካታ የቅድመ ሥራዎች አሉበት በጥቂቱ ለመዘርዘርም፡-(1)ማነኛውንም ሥራ ከመስራቱ በፊት የአሰሪውን ፈቃድ ማግኘት አለበት፡፡ (2) የመሀንዲሱ ተወካዮችን መሾም ይችላል፡፡ (3)በጽሁፍ ለመሀንዲሱ የተሰጡትን ሥልጣንና ተግባር ለአሰሪውና ለሥራ ተቋራጩ በማሳወቅ ለሚወክለው ሰው ውክልና መስጠት፡፡ (4) በራሱ ያለማስታወቅ ችግር ምክንያት የሚደርሰውን የመዘግየት መጠን በአንክሮ ከተወያየ በኃላ የማራዘሚያ ጊዜውን እንዲሁም የኪሳራውን መጠን ለሥራ ተቋራጩ ማሳወቅ ከዚህ በተጨማሪም ለአሰሪው ግላባጭ እንዲደርሰው ማድረግ አለበት፡፡ (5)መሀንዲሱ ሥራ ተቋራጩን ስለ ሥራው አካሄድ ላይ ባሉ መነሻ ነጥቦች፣መስመሮች፣የማመሳከሪያ እረከኖች እና ቅርጾችን ማሳወቅ አለበት፡፡ እንዲሁም ሥራ ተቋራጩ በተዘረዘሩት ጉዳዮች ላይ ስህተት ከፈጸመ በራሱ ወጪ ወይም መሀንዲሱ በሚወስነው የዋጋ ውሳኔ መሰረት እንዲያስተካክል መናገር አለበት፡፡ ሥራ ተቋራጩ በወሰዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች ካልረካ እና የተባሉት ጉዳዮች የሥራ ተቋራጩ አደጋ(contractor’s risks) ከሆኑ ተጨማሪ አርምጃ እንዲወሰድ መወሰን፤ ዳሩግን ጉዳት ወይም ጥፋት የደረሰው በአሰሪው አደጋ( employer’s risks) ከሆነ የደረሰውን ጉዳት በማየት የጥገናውን መጠን መወሰን  ይህንንም ጉዳይ ለሥራ ተቋራጩ ማሳወቅ እንዲሁም ለአሰሪው በግላባጭ እንዲደርሰው ማደረግ አለበት፡፡

በመጨረሻም መሀንዲሱ በውሉ መሰረት የሚቀርቡትን መሳሪያዎች እና ግባዓቶች ሥራ ተቋራጩን በማሳወቅ መመርመርና መሞከር ይችላል፡፡  ይህን በሚያደርግበት ወቅትም ሙከራውን ያላለፉ መሳሪያዎች ወይም ግብዓቶች ዳግም ሙከራ እንዲያደርጉ አሊያም ደግሞ ከሥራ ተቋራጩ ጋር በሚገባ በመነጋገር ወጪያቸውን በኪሳራ መልክ እንዲሸፍን ማሳወቅ አለበት እነደተለመደውም ለአሰሪው ግልባጭ መላክ ይጨምራል፡፡

2.5           የመሀንዲሱ ድህረ ሥራዎች /Doing reactive duties/

ድህረ ሥራዎች የሚባለው ደግሞ በሥራ ተቋራጩ አነሳሽነት ወይም በአሰሪው ቀስቃሽነት መሀንዲሱ የሚወስድ እርምጃ ወይም የሚሰራው ሥራ ነው፡፡ (ዶ/ር ናዔል ቡኒ፡ዝኒ ከማሁ)

ለምሳሌ፡-መሀንዲሱ እንድ አሰፈላጊነቱ ለሥራ ተቋራጩ ሥራውን ለሌላ ንዑስ ተቋራጭእንዲያሰራ ፈቃድ ቢችረው ወይም ስዕሎችን (drawings)፣ ዝርዝር መገለጫዎችን( specifications) እና ሌሎች ሰነዶችን ሥራ ተቋራጩ ለሌላ ሦስተኛ ወገን ማሳየት በሚፈልግበት ወቅት መሀንዲሱ አስፈላጊ ነው ብሎ ከታየው ፈቃዱን መስጠት አለበት፡፡

በመጨራሻም የመሀንዲሱ ድህረ ሥራዎች በተለያዩ ወጥ ውሎች ተመልክቷል፡፡ ለአብነት ያህልም በዓለም አቀፋ የአማካሪ መሀንዲሶች ማህበር ወጥ ውል አንቀጽ 3(2)(ለ) ላይ የሚከተለው ይነበባል፡ሥራ ተቋራጩ የረዳት መሀንዲሱን ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ከተጠራጠረ ጉዳዩን ወደ መሀንዲሱ መምራት ይቸላል ሆኖም ግን መሀንዲሱ እነደነገሩ ሁኔታ የቀደመውን ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ሊያጸናው፣ሊቀለበሰው ወይም ሊያሻሽለው ይቸላል፡፡

2.6           የርክክብ አረጋጋጭ /Acting as a certifier/

ይህ ዓይነቱ የመሀንዲስ ተግባር ደግሞ በጣም ጥንቃቄን የሚሻ እና ውሳኔ መወሰን የሚያስፈልገው ተግባር ነው፡፡ ለምን ቢባል መሀንዲሱ አረጋግጦ ማህተም ካሳረፈበት የፕሮጀክቱ ሥራ በጊዚያዊነት ወይም በዘላቂነት አንደተቋጨ ይታመናል፡፡

በዚህ ረገድ ታዲያ መሀንዲሱ የማረጋገጥ ሚና ሲወጣ ምን ዓይነት ተግባራት ከፊቱ ይጠብቁታል የሚለው ጭብጥ ማብራራቱ ተገቢ ነው፡፡ አንደኛ በርክክብ ወቅት የምስክር ወረቀት በማዘጋጀት ፕሮጀክቱ መጠናቀቁን ማብሰር አለበት፡፡ ይህም በዓለም አቀፋ የአማካሪ መሀንዲሶች ማህበር ወጥ ውል አንቀጽ 14(13) ላይ መሀንዲሱ በሃያ ስምንት(28) ቀናት ውስጥየመጨረሻ ምልከታ ካደረገ በኋላ የክፍያ ማረጋገጫሰርተፍኬት መስጠት ሲጠበቅበት በአንጻሩ ደግሞ በሥራ እና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ውል አንቀጽ 48 እና 60(3) ላይ በግልጽ እንደተመለከተው በሃያ አንድ(21) ቀናት የተባለውን የማረጋገጥ ሥራ ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡

ሁለተኛም መሀንዲሱ ልክ እንደ ሥራ ተቋራጮች ሁሉ ለታወቁና ለተፈቀደላቸው ንዑስ ተቋራጮችም የምስክር ወረቀት (certifying payments to nominated sub-contractors) መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ (የዓለምአቀፋ የአማካሪ መሀንዲሶች ማህበር ወጥ ውል አንቀጽ 5(3) እንዲሁም የሥራ እና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ውል አንቀጽ 59(5) ይመለከተዋል፡፡ )

በመጨረሻም መሀንዲሱ የማረጋገጥ ሥራ የሚያከናውነው ከላይ በተጠቀሱት ሥራዎችና ሁኔታዎች የተገደበ አይደለም፡፡ አልፎ ተርፎም በየጊዜው የፕሮጀክቱን አፈጻጸም በማየትም ምስክርነት ሊሰጥ ይችላል፡፡ አሊያም ደግም ጊዜዊ (interim payment certificate) ሊሰጥ ይችላል፡፡

2.7    አግባቢ ዳኛወይም ከፊል ገላጋይነት /Adjudicator or quasi-arbitrator/

በዚህ ክፈል ደግሞ መሀንዲሱ ከወትሮው ለየት ያለ ተግባር የሚያከናውንበት ሲሆን እንዚህ ድርጊቶች ደግሞ በባህሪያቸው የሕግ ባለሙያ ማለትም ዳኛ ወይም ነገረ ፈጂ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ልዩ እውቀት እና ክህሎት የሚጠይቅ በመሆኑ የማግባባት ዳኝነት (adjudication) ወይም የመገላገሉን (arbitration) ጉዳይ ለመሀንዲሱ የተሰጡ ናቸው፡፡

ወደ ዝርዝር ጉዳዩ ከመግባታችን በፊት እስኪ ስለ የማግባባት ዳኝነቱና ግልልሉ ጥቂት ነጥቦችን እናንሳ፤በመጀመሪያ ደረጃ የማግባባት ዳንኝነት (adjudication) ማለት ተዋዋዮች ጉዳያቸውን በስምምነት ለመጨረስ በማሰብ ለአንድ አግባቢ ሦስተኛ ወገን በአብዛኛውም ጊዜ ለጊዜያዊ ውሳኔ እንዲሰጥ በማድረግ የሚደረገ ሲሆን ውሳኔውም በፍ/ቤት ወሳኔ ወይም በገላጋይ ውሳኔ(arbitral award) ካልተሻረ በቀር ተፈጻሚ ሚሆንበት መንገድ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የግጭት መፍቻ መንገድ በኮንሰትራክሽን ኢንዱስትሪው ተቀባይነት ያተረፈውም ከግልግል(arbitration) ወይም መደበኛ ፍ/ቤት አንጻር አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም የሚወስደው ጊዜና ወጪ አንስተኛ መሆኑ ነው፡፡ የማግባባት ዳኝነት ለተከራካሪ ወገኖች የመከራከሪያ ማስረጃዎችና ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ በማስቻሉ እና በሂደቱ ውስጥም ለተከራካሪዎች ከፍተኛ የተሳትፎ መጠን በመስጠቱ ይመሰገናል፡፡ (ሜልቪን አይዘንበርግ፡1992፡411)

በሌላ በኩል የግልግል ዳንኝነት ምንነት ለመረዳት የፍትሃብሄር ሕግ አንቀጽ 3325 ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ በዚህም መሰረት የግልግል ስምምነት ማለት ተዋዋይ ወገኖች ያንድን ክርክር ውሳኔ ለአንድ የዘመድ ዳኛ ለሆነው ለአንድ ለሦስተኛ ሰው አቅርበው የዘመድ ዳኛው ውል በሕግ አግባብ መሰረት ይሀንኑ ክርከር ለመቋረጥ የሚያደርገው ውል ነው፡፡ ስለዚህ በግልግል ሂደት ገላጋይ ሆኖ የሚመረጠው ሦስተኛ ወገን አስገዳጅ የሆነ ውሳኔ መስጠት ይችላል፡፡

በዓለም አቀፋ የአማካሪ መሀንዲሶች ማህበር ወጥ ውልም በአንቀጽ 20(2) ላይ የግጭት አግባቢ ቦርድ(Dispute Adjudication Board) የሚነሱ አለመግባባቶችን ማየት ይችላል፡፡  በተለይም በሥራ ተቋራጩና በባለቤቱ(አሰሪው) መካከል ባለው ክርክርና አለመግባባት ሲነሳ እና በጨረታ ሰነዱ ላይ አባሪ ሆኖ የማግባባት ሥራ እንዲሰራ ስሙ ከተጠቀሰ መሀንዲሱ የማግባባት ዳኝነት ተግባሩን በመጠቀም ማስታረቅ ይችላል፡፡

በሌላ በኩል በሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ውል አንቀጽ 67 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ማነኛውንም አለመግባባት በአሰሪውና በሥራ ተቋራጩ መካከል ሲነሳ በመጀመሪያ ለመሀንዲሱ መቅረብ እንዳለበት ይናገራል፡፡

“If any dispute or difference of any kind whatsoever shall arise between the Employer and the Contractor in connection with or arising out of the Contract, or the execution of the Works whether during the progress of the work or after their completion and whether before or after the termination, abandonment or breach of the Contract, it shall, in the first place, be referred to and settled by the Engineer who shall, within a period of ninety days after being requested by either party to do so give written notice of his decision to the Employer and the Contractor…sic…”

 

ከላይ በፊዴክ ውል በአንቀጽ 20(2) በተቋቋመው የግጭት አግባቢ ቦርድ ውሳኔ ያልተስማማ ወገን በአንቀጽ 20(4)(5) መሰረት በግልግል(arbitarion) መውሰድ ይችላል፡፡

በመጨረሻም አሁን አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጁ ወጥ ውሎች ላይ እንደሚስተዋለው ለሚዛናዊነት ሲባል በተለምዶው መሀንዲሱ የማግባባትና የመገላገል ሥራዎችን እንዳያከናውን ሲያደረጉ በአንጻሩ ግን የግጭት ገላጋይ ቦርድ ጉዳዮችን እንዲመለከቱ ያደረጉበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡

3.  የጥቅም ግጭቶችን እንዴት ማስወገድ ይቻላል /Synchronizing Conflict of interests/?

በዚህ ክፍል የምንመለከተው ደግሞ መሀንዲሱ ከላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት ሲያከናውን የሚነሱ የጥቅም ግጭቶችን እንዴት ማስወገድ ይቻላል የሚለውን ጥያቄ በማንሳት እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን፡፡  እንደሚታወቀው መሀንዲሱ የፕሮጀክቱን ስራዎች ጨምሮ ከላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት በሚያከናውንበት ወቅት ከሥራ ተቋራጩም ሆነ ከአሰሪው ትችቶችን ያስተናግዳል፡፡

በተለይም ሥራ ተቋራጩ መሀንዲሱን ለአሰሪው ያደላል በማለት በተደጋጋሚ ይከሳል፡፡ ለምን ቢባል አንድም መሀንዲሱ የአሰሪው ቅጥረኛ በመሆኑና የአሰሪው ዋና አማካሪ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ ሁለትም መሀንዲሱ በፕሮጀክት አፈጻጸም ወቅት ለሚነሱ ማነኛውም ውሳኔ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ሁሉ አሰሪውን በጥልቀት ስለሚያወያየው ነው፡፡ ሌላው መነሳት ያለበት ነጥብ በአንዳንድ ጉዳዮች ደግሞ መሀንዲሱ ግልጽ ትዕዛዝ እና ፈቃድ ከአሰሪው በመቀበሉ ነው፡፡

በሌላ በኩል አሰሪውም ቢሆን መሀንዲሱን ለሥራ ተቋራጩ ታደላለህ በማለት ይከሳል፡፡ ለምን ቢባል መሀንዲሱ የፕሮጀክቱን ውል በሚስተዳድርበት ወቅት ያለአግባብ ለሥራ ተቋራጩ የጊዜ ማራዘሚያ በማድረጉ፣ ብሎም ሥራ ተቋራጩ የሚያነሳቸውን መብቶች (claims) መጠን በመወሰን ረገድ አድሎ ማድረግ፣አንዳንዴ ደግሞ መሀንዲሱ ቸላ በማላት ሥራ ተቋራጩ በውል የተቀመጡትን ግዴታዎች እንዳይወጣ በማድረጉ እና ሥራ ተቋራጩን የሚጠቅም ትዕዛዞች በመስጠት ሊሆን ይችላል፡፡

ከላይ በመሀንዲሱ ላይ የቀረቡት ወቀሳዎችና ክሶችን የሚያጠናክረው ሌላ ጥያቄ እናንሳ፡ እንደሚታወቀው በንዑስ ክፍል 2.7 ለማቅረብ እንደተሚከረው መሀንዲሱ አግባቢ ዳኛ (adjudicator) ሊሆን እንደሚችል አይተናል፡፡ በተለይም በሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ውል አንቀጽ 67 ሀለተኛ መስመር ላይ ጉዳዩ ማለትም በአሰሪውና በሥራ ተቋራጩ መካከል ያለው አለመግባባት በመሀንዲሱ እልባት ሳያገኝ ቀርቶ ወደ ሌላ አካል ማለተም ለሚኒስቴር መ/ቤቱ አሊያም ለሌላ ገላጋይ(arbitrator) በሚቀርብበት ወቅት መሀንዲሱ ምስክር ሆኖ ማስረጃ ከመስጠት አያግደውም፡፡ ይህን የኢትዮጵያውን እንደ ምሳሌ አነሳን አንጂ በዓለምአቀፋ የአማካሪ መሀንዲሶች ወጥ ውል አንቀጽ 20(6) ላይም በተመሳሳይ መልኩ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

ታዲያ በዚህ ግዜ ነው የጥቅም ግጭትን (Conflict of interests) ጨምሮ የፍትሃዊነት ጥያቄም የሚነሳው፡፡ በተፈጥሮ ሕግ አስተምህሮ አንደ የታወቀ የላቲን አባባል አለ፡፡ ይህም “Nomo judex in causa sua” ትርጉሙም ማነኛውም ሰው ራሱ በሚያውቀው ጉዳይ ወይም ጥቅም ባለው ነገር ላይ ዳኛ መሆን አይችልም፡፡ በተለይም ልክ እንደመደበኛው የፍትህ ሥርዓት ልክ አንድ ዳኛ ሚዛናዊ ውሳኔ እንዳይወስን ሊያደርጉ የሚችሉ ምክንያቶች በመከሰታቸው ከችሎት እንደሚነሳው ሁሉና አንደ ገላጋይ ዳኛ ሊነሳ እንደሚችለው (የፌዴራል ፍ/ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ.25/1988 አንቀጽ 27 ወይም የፍትሃብሄር ሕግ አንቀጽ 3340 ይመለከቷል፡፡ ) መሀንዲሱም የማግባባቱን ሥራና ከፊል የመገላገሉን ስራ በሚዛነዊነት አይወጣውም ተብሎ ሲታመን ከዚህ ተግባሩ የሚነሳበት መንገድ ተቀርጾ ወጥ ውሎች ቢሻሻሉ መልካም ነው፡፡

4.  መደምደሚያ

መሀንዲሱ ከላይ በአጭር በአጭሩ ለማብራራት እነደተሞከረው በርካታ ተግባራት እንዳሉበት ለመዘርዘር ተሞክሯል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ዲዛይን ማውጣት፣ የአሰሪው ወኪል ሆኖ መስራት፣ የማማከርና ቁጥጥር ሥራዎች፣ በራሱ አነሳሽነት የሚሰራቸው ቅድመ ሥራዎች፣ በትዕዛዝ የሚሰራቸው ድህረ ሥራዎች ጨምሮ በርክክብ ኣነ ክፍያ ወቅት የማረጋገጥ ሥራዎችን ይሰራል፡፡ በመጨረሻም ልክ እንደ ሕግ ባለሙያ ሁሉ የማግባባት ዳኝነትና የመገላገል ስራዎች ላይ ይሳተፋል፡፡  ሆኖም ግን የመሀንዲሱ ተግባራት በነዚህ ብቻ ይወሰናል ማለት አይደለም ለፕሮጀክቱ አፈጻጸም ሲባል በርካታ ሌሎች ሥራዎችን ሊያከናውን ይቸላል፡፡ ለማጠቃለል ያህልም መሀናዲሱ የተባሉትን ተግባራት ሲያከናውን የጥቅም ግጭት መነሳቱ የማይቀር ነው ዳሩ ግን ሚዛናዊነቱ ላይ ጥርጣሬ የሚያጭር ነገር ከተከሰተ መሀንዲሱ ከተግባሩ እንዲታቀብ አሊያም እንዲነሳ ቢደረግ ከተፈጥሮ ሕግና ርትዕ አንጻር መልካም ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ወጣቱ ፎቶ አንሺ፣ ጃንሆይ እና ማርክስ
Derogation of the right to life and its Suspension...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Monday, 29 April 2024