አንዳንድ ጉዳዮች ስለ ሕገ-መንግሥት እና ፍርድ (ትርጉም)

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመን ከማለቁ በፊት ምርጫን ማከናወን እንደማይችል፤ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ካሳወቀ ጊዜ ጀምሮ፤ የጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊ ገፅታዎች በተለያዩ መድረኮች ውይይት እየተደረገባቸው ነው። አራት አማራጭ መፍትሄዎች የቀረቡለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ በጉዳዩ ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም፤ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጠይቋል። የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ፤ ጥያቄውን ተቀብሎ፤ የሕገ መንግሥት ምሁሮች አስተያየታቸውን በፅሁፍ እንዲያቀርቡ ጋብዟል። በቃልም እንዲያስረዱና ጥያቄዎችን እንዲያቀርቡ ጋብዟል።

የቀረበውን ግብዣ መሰረት በማድረግ አሰተያየት ለማቅረብ ውስኜ ነበር። በተለያዩ ምክንያቶች ሳላደርገው ቀርቻለሁ። አንደኛ፤ ግብዣው ለሕገ መንግሥት ምሁራኖች የቀረበ ጥሪ ነበር። ሁለተኛ፤ ጉባኤው የቀረበለትን አሰተያየት የመመልከት ግዴታ እንደሌለበት አስታውቋል። ሶስተኛ፤ በጊዜ እጥረት፤ በዛው ሳምንት የመጀመሪያ ልጄ ስለተወለደና በዚሁ ትኩረቴ ተይዞ የቆየ ስለነበረ። እንዲያም ሆኖ ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች አንዳንድ አስተያየቶችን በማህበራዊ ሜዲያ ሳቀርብ ነበር። እነዚህን አስተያየቶቼን እንደሚከትለው አደራጅቼ አቅርቤያለሁ።

የቀረበው ጥያቄ

የሙያ አስተያየት እንዲቀብለት ባደረገው ይፋዊ ግብዣ፤ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ግልፅ እንዳደረገው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለት የትርጉም ጥያቄ የሚከተለው ነው።

የቅድመምርጫ ዝግጅቶች እና ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰት በዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው ምክር ቤቶች እና የአስፈፃሚው አካል የስራ ዘመን ምን ይሆናል? ምርጫውስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በሁዋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊከወን ይገባል? ለሚሉት ጥያቄዎች ሕገ መንግሥቱ ምላሽ አለመስጠቱ የገጠመንን ችግር በመፍታት ረገድ ክፍተት አለበት የሚያስብል ነው። በመሆኑም ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች (አንቀፅ 54/1, 58/3 93) ከሕገ መንግሥቱ አላማና ግቦች እንዲሁም መሰረታዊ መርሆች ጋር በማስተሳሰር በማገናዘብ ትርጉም እንዲስጣቸው ነው።

ይህን ጥያቄ በተመለከተ አስተያየት ከመስጠቴ በፊት የጥያቄውን ባህሪ መመርመር ተገቢ ነው።

አንደኛ፤ ጥያቄው የቀረበው "አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰት" በሚል ነው። እንዲህ አይነት አገላለፅ ጥያቄውን hypothetical ያደርገዋል። የፈተና ጥያቄ ይመስላል። የቢሆን ጥያቄ ያስመስለዋል።

በእርግጥ መንግሥት የአስቸኳይ አዋጅ አውጇል። ስለዚህ “ቢታወጅ” የሚል አባባል ለምን አስፈለገ?

"አንድ ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የሚችለው የስራ ዘመኑ እስኪያልቅ ብቻ ነው?" የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ይህን ጥያቄ በግልፅ ማስቀመጥ ነው።

ሁለተኛ፤ "በዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን"? ምን ማለት ነው?

የአስቸኳይ አዋጅ መታወጅ እኮ በቀጥታ ምርጫ ማድረግን አይከለክልም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ከውስን የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች በስተቀር፤ ብዙዎቹን ማገድ ይችላል። ይህ ማለት ግን ሁሉም አስቸኳይ ጊዜ አዋጆች በተመመሳሳይ መልኩ ሁሉንም ድንጋጌዎች ያግዳሉ ማለት አይደለም። ለአዋጁ መታወጅ ምክንያት ከሆነው ጉዳይ አንፃር አስፈላጊ የሆኑት ብቻ ናቸው የሚታገዱት።

ጥያቄው፤ አሁን የታወጀው አዋጅ ምን አይነት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ነው ያገደው? ምርጫ ማካሄድ ወይም ለነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አስፈላጊ የሆኑ ድንጋጌዎች ታግደዋል? 

በእርግጥ ለምርጫ አስፈላጊ የሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊያግድ ይችላል። ነገር ግን የእነዚህ ድንጋጌዎች መታገድ ለአዋጁ ምክንያት ከሆነው ጉዳይ አንፃር አስፈላጊ ናቸው ወይ የሚለው ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ነው?

ሶስተኛ፤ "የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው ምክር ቤቶች እና የአስፈፃሚው አካል የስራ ዘመን ምን ይሆናል?" ምን አይነት ጥያቄ ነው? ዋናው ጥያቄ፤ አንድ ምክር ቤት የሚያውጀው አዋጅ የምክር ቤቱን የስራ ዘመን የማራዘም ውጤት ሊኖረው ይችላል ወይ? በምን አይነት ሁኔታዎች? 

የምክር ቤቱ ስልጣን ከተራዘመ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲያበቃ፤ የስራ ዘመኑ ምን ያሆናል? ምርጫ በምን ያህል ጊዜ ምን ይሆናል?

አጣሪ ጉባኤው የሕገ መንግሥት ምሁሮችና ባለሙያዎች ሃሳብ እንዲሰጡ ጥሪ ማቅረቡ የሚመሰገን ነው።

ጥያቄውን ያቀረብው አካል፤ መንግሥት፤ ጥያቄ ማቅረብ ብቻ አይደለም ስራው። በጉዳዩ ላይ ያለውን ሙግትም ማቅረብ አለበት። ያቀረበው ሙግትም ለህዝብ ግልፅ መሆን አለበት።

አስተያየት ማቅረብ የሚችሉት የሕገ መንግሥት ምሁሮች ብቻ መሆን የለባቸውም። ማንኛውም ዜጋ፤ በተለይ ደሞ ሲቪል ማህበራትና የፓለቲካ ፓርቲዎችም እድል ሊሰጣቸው ይገባል። አንድ ዜጋ በራሱ የሕገ መንግሥታዊ አቤቱታ ማቅረብ ከቻለ፤ አሁን በምን ምክንያት ነው ምሁሮች ብቻ የሚባለው?

አጣሪ ጉባኤው አስተያየት እንዲቀርብ ግብዣ ካደረገ በሁዋላ፤ የቀረቡት አስተያየቶች ግን የመመልከት ግዴታ የለብኝም ማለትስ መሰረቱ ምንድር ነው? እንኳን ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ይቅርና፤ በተለይ በዚህ አጨቃጫቂ ጉዳይ፤ የአስተዳደር ተቋማት እንኳን የቀረበላችውን ሃሳብ ካልተቀበሉት ምክንያታቸውን ማሳወቅ አለባቸው።

የቀረበው አስተያየት ባጭሩ

ከዚህ በላይ ባለው ክፍል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን አስተያየት በማብራራት እንዳሳየሁት፤ አሁን የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕገ መንግሥታዊነት እንዲመረመር የተጠየቀ ጥያቄ የለም።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጨማሪ ስልጣኖችን እና በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ብዙ ዲሞክራሲያዊና ፓለቲካዊ መብቶችን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሰረት ማስፋትና መገደብ ይቻላል። ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ ምክንያት የሆነውን ነገር ለማስወገድና የህዝብን ደህንነትና የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ አስፈላጊ እስከሆኑ ድረስ። እንደነገሩ ሁኔታ፤ ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጅትና ክንውን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ለማስወገድ፥ የሀገርን ህልውና ለመጠበቅና፥ የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ እስከሆኑ ድረስ ሊታገዱ ይችላሉ። ነገር ግን መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ምርጫን ማዘጋጀትና መከወን ማገዱን አላሳወቀም። ያልታገደ ነገርን ደሞ ሕገ መንግሥታዊነት መመርመር አይቻልም።

ሕገ መንግሥቱን የሚተረጉመው የፌዴሬሽን ምክር ቤትና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን ለማጣራት በሕገ መንግሥቱ የተቋቋመው አጣሪ ጉባኤን የሚመሩት አዋጆች ብዙ ድንጋጌዎች ሕገ መንግሥታዊ አይደሉም። ከእነዚህ ውስጥ የአጣሪ ጉባኤው ስድስት የህግ ባለሙያዎች የዳኝነት ነፃነት ተጠቃሚ አለመሆናቸውና ለስድስት አመት ብቻ የተሾሙና ከዚያም በፊት ሊነሱ መቻላቸው አንደኛው ነው።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ መስራት ያለበት እንደ የዳኝነት አካል ሆኖ እያለ በአዋጁ መሰረት ግን እንደ ምክር ቤት እንዲሰራ ሆኗል። ይህም ሕገ መንግሥታዊ አይደለም።

በሕገ መንግሥቱ መሰረት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሚያጣራቸው ጉዳዮች ሁለት ናቸው። አንደኛው፤ የህጎች፥ ልማዳዊ አሰራሮችና፥ የመንግሥት ውሳኔዎች ሕገ መንግሥታዊነት ነው። ሁለተኛው፤ በፍርድ ቤት በመታየት ባሉ ጉዳዮች የሕገ መንግሥት ትርጉም ሲያስፈልግ ነው። ነገር ግን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጡት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዋጅና የአጣሪ ጉባኤው አዋጅ እነዚህን የአጣሪ ጉባኤውን ስልጣኖች የሚያሰፉና የሚያዛቡ በመሆናቸው ሕገ መንግሥታዊ አይደሉም።

በተለይ “በቢሆን ጉዳዮች” ላይ በምክር ቤቶችና በአፈፃሚ አካላት የሚቀርቡ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች የዳኝነት ጥያቄዎች ሳይሆን የምክር ጉዳዮች ናቸው። እነዚህ ደሞ ከአጣሪ ጉባኤው ነፃነት ጋር የሚፃረሩ ናቸው።

አሁን እየታየ ያለው የቢሆን ጉዳይም፤ ይህን ኢሕገ መንግሥታዊ የሆነ አዋጅ መሰረት ያደረገ በመሆኑ በአጣሪ ጉባኤው ሊታይ አይገባም።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የአጣሪ ጉባኤው አዋጆች በህዝብ ተወካይ ምክር ቤቶች የሚወጡበት ምንም አይነት ሕገ መንግሥታዊ መሰረት ስለሌለ ኢሕገ መንግሥታዊ መሆናቸው ሊታወጅ ይገባል።

አጣሪ ጉባኤው የሚከተለው ስነስርአት የዳኝነት ስነስርአት ሆኖ፤ በጉባኤው ተረቆ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መፅደቅ ሲኖርበት ይህ ስላልተከናወነ ጉድዩን እየመረመረ መቀጠል አይችልም።

ከዚህ በላይ ያነሳኋቸው ሃሳቦች ውድቅ ቢደረጉ እንኳን፤ አጣሪ ጉባኤው ለቀረበት ጥያቄ መስጠት የሚችለው ጠቅላላ ትርጉም ብቻ ነው። ይህ ጠቅላላ ትርጉም አስቸኳይ ግዜ አዋጁን እና ይህን ተከትሎ የሚወጡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንቦችን ሕገ መንግሥታዊነት የሚመለከት አይደለም። አጣሪ ጉባኤው የሚሰጠው ጠቅላላ ትርጉም ወደፊት በተደጋጋሚ የሚነሱ የኢሕገ መንግሥታዊ ሙግቶችን የሚዘጋ መሆን የለበትም።

ይህ በዚህ እንዳለ፤ አጣሪ ጉባኤው ጠቅላላ አስተያየት ወይም ትርጉም መስጠት አለብኝ ብሎ ከተነሳም እንኳን፤ ሊሰጠው የሚገባን ትርጉም ከዚህ በታች በዝርዝር ቀርቧል።

ህግ እና ፍርድ

ምርጫው በወቅቱ እንደማይካሄድ ከተገለፀ በኋላ የተነሱትን ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች የበለጠ ለመረዳት ይረዳን ዘንድ በዚህ ክፍል ስለ ህግና ፍርድ አንዳንድ ጉዳዮችን እንደ መግቢያነት አነሳለሁ። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዳኝነት የሚመስሉ ስልጣኖች ስላለው እና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤን የሚመለከቱ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች የዳኝነት አካላትን በሚመለከተው የሕገ መንግሥት ክፍሉ ውስጥ የምናገኛቸው በመሆኑ።

      “በፌዴራልም ሆነ በክልል የዳኝነት ስልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ” እንደሆነ በአንቀፅ 79(1) ተደንግጓል። ምን ማለት ነው? የዳኝነት ስልጣን ከፍርድ ቤቶች ውጭ ለሌላ አካል ሊሰጥ አይችልም ማለት ነው? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ፤ ሌላ ጥያቄ ማንሳት አለብን። የዳኝነት ስልጣንስ ማለት ምንድር ነው? 

ዳኝነት ማለት በሁለትና ከዚያ በላይ ባሉ ወገኖች መካከል በተከሰተ የጥቅም አለመግባባት ላይ ውሳኔ መስጠት ማለት ነው? 

ለምሳሌ፤ በሁለት ልጆቹ መካከል ያለን የጥቅም አለመግባባት ውሳኔ በመስጠት ወላጅ ይፈታል። ተደራራቢ አልጋ ብቻ ባለበት የልጆች ምኝታ ቤት የትኛው ልጅ ቆጥ ላይ ይተኛ በሚል ይሆናል አለመግባባቱ የተፈጠረው። ወላጅም በተለያየ መንገድ ውሳኔ በመስጠት አለመግባባቱን ሊያስቆመው ይችላል። ከልጆቹ ታላቅ የሆነው የመረጠው አልጋ ላይ እንዲተኛ በመወሰን። ወይም በባለፈው ሴሚስቴር የተሻለ የፈተና ውጤት ያለው በመረጠው እንዲተኛ በመወሰን። ወይም የቀደመ በመረጠው እንዲተኛ።

ከዚህ በላይ የተመለከትነው የወላጅ ስልጣን ግን የዳኝነት ስልጣን ሊባል አይችልም። የዳኝነት ስልጣን አለመግባባቶችን የሚወሰነው በተሟጋች ወገኖች መካከል ያለን የህግ እና የፍሬ ነገር ሙግትን እና ማስረጃን በመስማትና በመመርመር ነው። ማለትም ህግን በመተርጎም ነው። አንድን ስልጣን የዳኝነት የሚያደርገው የፍሬነገር ሙግቶች ላይ በሚሰጠው ውሳኔ አይደለም። በዋናነት የህግ ሙግቶች ላይ የሚሰጠው ውሳኔ ነው።

ስለዚህ የዳኝነት ስልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው ሲባል፤ በሰዎች መካከል ያለን አለመግባባት ለመፍታት ህግን በመተርጎምና ህግን መሰረት አድርጎ መወሰን የሚችለው ፍርድ ቤት ብቻ ነው ማለት ነው።

የፍሬነገር አለመግባባቶችን በውሳኔ የመፍታት ስልጣንን ከፍርድ ቤት ውጭ ለሆነ አካል መስጠት ከላይ የተጠቀሰውን የሕገ መንግሥት ድንግጌ ጋር አይጋጭም ማለት ነው? ህግን መሰረት አድርጎና ተርጉሞ ውሳኔ መስጠት ከፍርድ ቤት ውጭ ለሆነ አካል አይሰጥም ማለት ነው? አንድን አካል ፍርድ ቤት የሚያስብለው ምንድር ነው? ስሙ ነው? 

አንድ አካል ፍርድ ቤት የሚባለው፤ ዳኞቹ በሕገ መንግሥቱ አግባብ የሚሾሙ ከሆነና የዳኝነት ነፃነት ጥበቃዎች ተጠቃሚ ከሆኑ ነው። ዳኛ ሆኖ ለመሾም ደሞ የህግ ትምህርት፥ ባህሪ፥ ልምድና፥ ብቃት ወሳኝ ነው። ስለዚህ አንድን አካል ፍርድ ቤት የሚያሰኘው የዳኞቹ አሿሿምና ያላቸው ነፃነት ነው። ከዚህ እንደምናየው ህግ ትምህርት፥ ባህሪ፥ ልምድ፥ ብቃት፥ እና ነፃነት፤ ህግን ለመተርጎምና የህግ የበላይነትን ለማጠናከር ወሳኝ ናቸው። ለዚህም ነው የዳኝነት ስልጣን የፍርድ ቤቶች ነው የተባለው።

የፍሬነገር ክርክሮችን ለመወሰን ግን ዳኞች የተለየ ብቃት የላቸውም። እንደውም ከሌሎች ሙያዎች በዚህ ብቃታቸው ሊያንሱ ይችላሉ። ነገር ግን የፍሬነገር አለመግባባትም ቢሆን ህግን በተከተለ መልኩ ሊፈታ ይገባል። ምን አይነት ማስረጃ ህጋዊ ተቀባይነት አለውና የመሳሰሉት ጥያቄዎች በህግ የሚመለሱ ናቸው። ስለዚህ የማስረጃና የስነስርአት ህጎችን በመተርጎም ረገድ አሁንም የህግ ብቃትና ገለልተኝነት ስለሚጠይቅ የዳኝነት ስልጣን ነው ሊባል ይችላል። ከዚህ ውጭ ያሉ የፍሬነገር ሙግቶችን ለመፍታት ግን የህግ ሙያና ገለልተኝነት ሳይሆን ሌላ ሙያ የተሻለ ሆኖ ሊገኝ ይችላል።

በመሆኑም አንዳንድ የፍሬነገር ጉዳዮችን የመወሰን ስልጣን ከፍርድ ቤት ውጭ ለሆኑ አካላት ሊሰጥ ይችላል። ነገር ግን እነዚህ አካላት የሰጡት የፍሬነገር ውሳኔ የስነስርአት፥ የማስረጃና፥ የፍትሃዊነት ድንጋጌዎችን (እኩልነትን፥ የመደመጥ፥ የመከራከር መብቶችን) ስለማክበራቸው ውሳኔ መስጠት የዳኝነት እና የፍርድ ቤት ስልጣን ነው። እንዲሁም አንድ ጉዳይ “የፍሬነገር ነው ወይስ የህግ?” የሚለውን መወሰን የዳኝነት ስልጣን ነው።

አንድን ስልጣን የዳኝነት ስልጣን የሚያደርገው ህግ መተርጎም ከሆነና የዳኝነት ስልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው ማለት ሌላ አካል ይህን ስልጣን ሊጠቀም አይችልም ማለት ነው? የዳኝነት ስልጣን ለምን የፍርድ ቤት ስልጣን መሆን እንዳለበት ከዚህ በላይ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። የዳኝነት ስልጣን ለሌላ አካል አይሰጥም ማለት ነው?

በብዙ የፓሊሲ እና ሕገ መንግሥታዊ ምክንያቶች የተነሳ አጭሩ መልስ አይደለም ነው። አንደኛ፤ ሕገ መንግሥቱ ፍትህ የማግኘት መብትን “በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም በህግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል በማቅረብ ፍርድ ማግኘት” በሚል ይገልፀዋል። ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ ራሱ የተቀበለው ሃቅ ነው።ማለትም በህግ የተቋቋሙ የዳኝነት ስልጣን ያላቸው አካላት ይኖራሉ ማለት ነው።

ሁለተኛ፤ ስለ ልዩ ፍርድ ቤቶች የሚመለከተው ክልከላ ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ውጭ የሆኑ እና አስቀድሞ በህግ የተደነገገ ስርአት የማይከተሉ በሚል ይገልፃቸዋል. በስም ፍርድ ቤት ቢባሉም፥ ከመደበኛ ፍርድ ቤት ውጭ ቢሆኑም (መዋቅራቸውና የዳኞች አሿሿም)፤ የሚከለከሉት አስቀድሞ የተደነገገ ስርአት ካልተከተሉ ብቻ ነው።

ከዚህ ሁለት የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ማየት እንደሚቻለው ሕገ መንግሥቱ ራሱ የዳኝነት ስልጣን ለሌሎች በህግ ሊሰጥ እንደሚችል ነው።  ከእነዚህ ሕገ መንግሥታዊ መሰረት በተጨማሪ የፓሊሲ ምክንያቶች አሉ። ዘመናዊ መንግሥት በወንጀል እና በፍትህ ስርአት ብቻ አይመራም። አስተዳደራዊ ስራን ይጠይቃል።

ህግ አስፈፃሚውና ዜጎች ህግን ማክበር ይጠበቅባቸዋል። ህግን ለማክበር ደሞ መረዳት ይጠይቃል። ህግ ደግሞ ቋንቋ ነው። ሁልጊዜ ሁሉም ሰው በተመሳሳይ መልኩ ሊረዳው አይችልም። ህግን መረዳት የሚቻለው በመተርጎም ነው። ታዲያ መተርጎም የዳኝነት ስራ ከሆነ ዜጎችና መንግሥት የህጉን ትርጉም ለመረዳት ፍርድ ቤት እየሄዱ ያስተረጉማሉ ማለት ነው?

ይህ የማይቻል ብቻ ሳይሆን የማይገባም ነው። የማይገባ ነው ያልሁበት ምክንያት ከዳኝነት ነፃነት ታሪክ አኳያ ነው። የዳኝነት ነፃነት ተቀባይ እየሆነ ሲመጣ፤ የእንግሊዝ ነገስታት አንድ መላ ዘየዱ። ይህም የጠሉትን ሰው ከመክሰሳቸው በፊት፥ ዳኞችን ምክር ይጠይቃሉ። እስቲ ተርጉሙሉን ይሏቸዋል። “በህጉ መሰረት ያስቀጣል ወይ?” ይሏቸዋል። እንደ መልሱ ሁኔታ፤ ንጉሶቹ የወደዱትን ያደርጋሉ።

ያስከስሳል ከተባሉ፤ ሊያጠቁት የፈለጉትን ይከሱታል። ዳኛው አስቀድሞ ያስከስሳል ብሎ አቋም ስለያዘ ሃሳቡን መቀየር ይከብደዋል። ከራስ ጋር መጣረስ (cognitive dissonance) ይሉታል። አያስከስስውም የሚባል ከሆነ፤ ዳኛውን በተለያየ መልኩ ለማባረር ወይም ለመግፋት ወይም ሌላ ዳኛ ዘንድ ለመክሰስ ይሞከራል። ይህን የተገነዘቡ ዳኞች ምክር አንሰጥም ማለት ጀመሩ. ህጉን የምንተረጉመው ክስ ሲቀርብ ብቻ ነው ማለት ጀመሩ።

ከዚህ በላይ ማየት እንደሚቻለው የዳኝነት ስልጣንን ሌላ ማንም አካል ንክች አያድርጋት ማለት ሕገ መንግሥታዊም አይደለም። ከዳኝነት ነፃነት አኳያም ተገቢም አይደለም። ታዲያ "የፍርድ ቤቶች ብቻ" የሚለው አባባል ምን ማለት ነው? እንደ እኔ እምነት ይህ አባባል የሚከተሉት ትርጉሞች አሉት

አንደኛ፤ የመጨረሻው የዳኝነት ስልጣን የፍርድ ቤቶች ነው። ከፍርድ ቤቶች ውጭ ያሉ አካላት የሚሰጧቸውን ውሳኔዎች ህጋዊነት አስመልክቶ የመጨረሻውን ውሳኔ መስጠት የሚችለው ፍርድቤቶች ብቻ ናቸው። በህግ ጉዳዮች ዙሪያ ይግባኝ ማለት መብት ነው። አንዳንድ ሰዎች judicial review በሕገ መንግሥቱ እውቅና አልተሰጠውም ሲሉ ይህንን የሳቱ ይመስለኛል።

አንዳንድ አዋጆች የመንግሥት ድርጅት ውሳኔዎች የመጨረሻ ናቸው የሚል ድንጋጌዎች አሏቸው። ሕገ መንግሥታዊ አይደለም። ነገር ግን ፍርድ ቤቶች ድንጋጌዎቹ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እስኪሻሩ ድረስ ፍርድ ቤቶች በድንጋጌዎቹ መገዛት አለባቸው ማለት አይደለም። አዋጆቹን መተርጎም የፍርድ ቤት ስልጣን ነው። በመሆኑም የመጨረሻ ውሳኔ የሚሉት ድንጋጌዎች መተርጎም አለባቸው። ማንኛውም ህግ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንዲጣጣም ሆኖ መተርጎም አለበት። በዚህ መልኩ ድንጋጌዎቹ ሲተረጎሙ ደሞ በህግ ጉዳዮች ይግባኝን እንደማይከለክሉ ተደርገው መተርጎም አለባቸው።

ሁለተኛ፤ የፍርድ ቤቶች ናቸው ቢባልም እንኳን ሌሎች አካላት ሊዳኙ ይችላሉ። ስልጣኑ በህግ እስከተሰጣቸው። በህግ ስልጣን ሳይሰጣቸው የዳኝነት ስራን የሚሰሩ የመንግሥት ድርጅቶች አያሌ ናቸው።

ሶስተኛ፤ የዳኝነት ስልጣንን የሚጠቀሙ አካላት በህግ የተደነገገ ስርአት መከተል አለባቸው። ህግመንግሥታዊ የማይሆነው በህግ የተደነገገ ስርአት የማይከተሉ ከፍርድ ቤት ውጭ የሆነ አካላት አያሌ ናቸው። ይህን ድንጋጌ በመጠቀም መንግሥት የአስተዳደር ስነስርአት ህግ እንዲያወጣ ማስገደድ ይቻል ነበር። ከሃያአመታት በላይ የዘገየው ይህ ህግ ሰሞኑን ነው የወጣው።

አሁንም ግን ገና ብዙ ስራ ይጠይቃል. ከዚህ በላይ የተጠቆሙ ብዙ ስራዎች አሉ። የዳኝነት ስልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው ማለት የመጨረሻው ቃል የሚተውላቸው ጀግኖቹ እነርሱ ናቸው ማለት እንጂ ማንም አይተርጉም ማለት አይደለም።

እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ስልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው ማለት ፍርድ ቤቶች ንክች አያድርጉት ማለት አይደለም። ይልቅስ የመጨረሻው ቃልና እና ጀግናው እነርሱ አይደሉም ማለት ነው። በመሆኑም ፍርድ ቤቶቻችን ሕገ መንግሥት በተጠቀሰ ጊዜ ሁሉ ስራቸውን እየተው መዝገብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መላክ ማቆም አለባቸው።

 

ሙት በሆነ ጉዳይ ዳኝነት መስጠት ወይም ጠቅላላ ትርጉም መስጠት ከህግ የበላይነትና ከዳኝነት ነፃነት አኳያ እንዴት ይታያል? ሙት የሚባል ጉዳይ ምን እንደሆነ በምሳሌ ላብራራ። 

እንግሊዝ ሀገር ሁለት ህፃናት ተጣብቀው ተወለዱ። የተጣበቁት በጭንቅላታቸው ነው። በተለይ ወሳኝ የሆነ የአንጎልና የደም ስር ይጋራሉ። እንደ ዶክትሮቹ ምርመራ፤ ሁለቱን ህፃናት ማለያየት ይቻላል። ነገር ግን አንዷ ህፃን መሞቷ አይቀርም። እንደተጣበቁ ይቅር ቢባል ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሁለቱም ይሞታሉ። ወላጆች መወሰን አቃታቸው። ዶክተሮቹ ፈሩ፤ በወንጀል እንዳይጠይቁ። ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ማብራሪያ ጠየቁ.

አቃቤ ህግ ደግሞ ከይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ትርጉም ጠየቀ። ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሳይሰጥ ህፃናቱ ሞቱ። ከዚህ በኋላ ጉዳዪ ሙት ሊባል ይችላል። መዝገቡ ይዘጋል? መዘጋት አለበት?

ጠቅላላ ትርጉም ማለት ሙግት ከመከሰቱ በፊት ሙግትን ለማስቀረትና ህጉን ለመረዳት የሚያግዝ ትርጉም ነው። በግልፅ ከተለዩና በእውን ከተከሰቱ ሁኔታዎች ጋር ሳይያያዝ የሚሰጥ ትርጉም ጠቅላላ ትርጉም ይባላል።

ጠቅላላ ትርጉም ፍርድ ቤቶች መስጠት ይችላሉ? ከሰጡ በትርጉማቸው ይገደዳሉ? ጠቅላይ አቃቤ ህግስ?

 

ከዚህ በላይ ያሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲረዳን ፍርድ ቤቶች እንዴት ግጭትን እንደሚፈቱ እንመልከት። ፍርድ ቤቶች ግጭትን በሰላማዊ መንገድ ማስረጃ፥ ሙግትንና፥ ህግን መሰረት አድርገው ይፈታሉ ሲባል ምን ማለት ነው?

ሁለት ሰዎች ተጣልተው፥ ተጋጭተው ፍርድ ቤት ቀረቡ እንበል። ሙግታቸውን ሰምቶ፥ ማስረጃና፥ ህግን መርምሮ ፍርድ ቤቱ ፍርድ ሰጠ። በሰዎቹ መካከል ያለው ጠብ፥ አለመግባባት ተፈታ ማለት ነው? ከባላንጣነት ወደ ባልንጀራነት ተቀየሩ ማለት ነው?

ፍርድ ቤቶች እንዲህ የሚያደርጉ ቢሆን ኖሮ እንደ አስማተኞች ቆጥሬ ትርፍ ጊዜዬን ሁሉ ፍርድ ቤት ነበር የማሳልፈው። ፍርድ ቤቶች እንዲህ አይነት ታምራዊ አቅም የላቸውም። እንደውም ተቃራኒው ነው የሚሆነው። በሙግት ሂደቱ ሰዎቹ የበለጠ እየተራራቁ ይሄዳሉ።

ይህን እየጠቀሱ ዳኞች "እኛ እኮ ቢያንስ ግማሹ ወገን፥ የተፈረደበት፤ ይጠላናል" ይላሉ። ይህን የሚሉት "ህዝቡ ስለ ዳኞች ያማርራል" ሲባሉ ነው።

እንዴት ነው ታዲያ ፍርድ ቤቶች አለመግባባትን የሚፈቱት? እረ ለመሆኑ የፍርድ ቤት ስራ ምንድን ነው? ፍርድ ቤትስ ለምን አስፈለገ? ሳንቲም ወርውረው አንበሳ ከሆነ ተከሳሽ ዘውድ ከሆነ ከሳሽ በሚል ለምን ፈጣን ፍርድ አይሰጡም?

 

ማንኛውም ሰው በንግግሩ ወይም በድርጊቱ ወይም ባለማድረጉ የተነሳ በሌላ ሰው ጥቅም ላይ ይህ ነው የሚባል ጉዳት ካደረሰ፤ ላደረሰው ጉዳት ልክ ካሳ ይከፍላል።
እንዲህ የሚል ህግ በ1940 ወጣ እንበል።

ህጉ በመውጣቱ ብቻ የሚያስቀራቸው ብዙ ግጭቶችና አለመግባባቶች ይኖራል። እንዴት? 

ሰዎች እንዲጠነቀቁ በማድረግና ጉዳት እንዳይደርስ በማድረግ። ይህ አንደኛው ነው።

ነገር ግን ጉዳት ሊደርስ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ሳይጠነቀቁ ቀርተው ወይም ተጠንቅቀው እያሉም ሊሆን ይችላል። ቢሆንም መብትና ግዴታቸውን ከህጉ ስለሚያውቁ በስምምነት ይቋጩታል። ይህ ሁለተኛው ነው።

ህጉ በመውጣቱ ብቻ በዚህ መልክ ግጭቶችን ያስወግዳል። እንደ ህጉ ጥራት (ለምሳሌ ግልፅነት ደረጃ) ደሞ የሚቀሩት አለመግባባቶች ሊቀንሱ ወይም ሊጨምሩ ይችላል። ማለትም የህግን ጥራት (ውጫዊ ቁንጅና በማሻሻል) ግጭትን መቀነስ ይቻላል።

ነገር ግን ህግ ጠርቶ አይጠራም። ለምሳሌ፤ የኔ በሬ የሌላን ሰው በሬ ገደል ቢከተው በህጉ መሰረት ካሳ መክፈል አለብኝ?

ወድቆ ሊሰበር እንደሚችል እያወቅሁ ዛፍ ላይ ሲወጣ ዝም ያልኩት ሰው ወድቆ ቢሰባበር፤ "ተው ይቅርብህ" ስላላልኩት ካሳ እከፍላለሁ?

ቅን ልቦና ምንድር ነው? የልብ ጉዳይ ነው? ወይስ የአይምሮ? በሌላ ሰው ጥቅም ማለት ምንድር ነው? ይህ ነው የሚባል ማለት ምንድር ነው?

እነዚህ ነገሮች ግልፅ ባለመሆናቸው የተነሳ፤ ሰዎች በጥንቃቄ እንኳን የማያስቀሯቸው ጉዳቶች ይኖራሉ። እንዲሁም ሰዎች ከሚገባው በላይ ጊዜያቸውንና ሃብታቸውን በጥንቃቄ ያውሉታል። በልማት ሊውል የሚችል ሃብት ራስን በመከላከል ይባክናል። በተጨማሪም ጉዳት ሲደርስ ሰዎች መስማማት ስለማይችሉ ግጭት ይኖራል። እነዚህ ግጭቶች ፍርድ ቤት ይመጣሉ.

ፍርድ ቤት ህጉን ተርጉሞ ፍርድ ይሰጣል። እንበልና "ቅን ልቦና ማለት የልብ ጉዳይ ሳይሆን የአይምሮ ነው። አንድ ሰው ቅን ልቦና የለውም የሚባለው ጉዳት እንደሚደርስ የሚያውቅ ወይም ማወቅ የሚጠበቅበት ከሆነ ነው" ብሎ ፍርድ ቤቱ ፍርዱ ውስጥ አሰፈረ እንበል። ፍርዱ በተሰጠበት ጉዳይ ያሉ ወገኖች ድህረፍርድ ከፍርድ ቤት ተቃቅፈው ይመለሳሉ ማለት አይደለም። ነገር ግን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ህጉን ያጠራዋል።

ፍርዶች በተሰጡ ቁጥር ህጉ የበለጠ እየጠራ፥ ሰዎች ጉዳትን በጥንቃቄ እያስቀሩ፥ ጉዳት ሲደርስም በመግባባት እየጨረሱ ስለሚሄዱ፤ በጊዜ ሂደት ይህን ህግ አስመልክቶ የሚነሱ ግጭቶች እየቀነሱ ይሄዳሉ። ለምሳሌ፤ የእንግሊዝ የውል ህግ በመቶዎች አመታት በተሰጡ ፍርዶች አማካኝነት እየጠራ በመሄዱ የተነሳ ወደ ፍርድ ቤት የሚመጡ የውል ጉዳዮች እጅግ ጥቂት ናቸው። በፈንሳይና በሌሎች ሀገራትም ጭምር።

ፍርድ ቤቶች ግጭትን ይፈታሉ ሲባል የተጣላን ያስታርቃሉ ማለት ሳይሆን አንድ ፍርድ ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ብዙ ግጭቶችን ስለሚያስቀር ነው። አንድ የአውሮፓ ፅሁፍ እንደሚለው አንድ ፍርድ ቢያንስ ሃምሳ ግጭቶችን ማስቀረት መቻል አለበት። ለዚህ ነው ፍርድ ቤቶች የሚያስፈልጉት።

የፍርድ ፋይዳ ከተሟጋች ወገኖች በላይ ነው። በኢኮኖሚክስ public good የሚባል ነገር አለ። ካምራቹ በላይ ህዝብን የሚጠቅም ነገር። ለምሳሌ የመንገድ ላይ መብራት። ወጪውን ከፍለህ በርህ ላይ መብራት ብትተክል ካንተ ጥቅም በላይ ብዙ ሌላ ሰው ይጠቀማል። የPublic goods ችግር ማንም ሰው ትርፍ ስለማያገኝበት ለማምረት አይደክምም። 

ፍርድም እንደዛው ነው። ፍርድ ለመስጠት ተከሳሽና ከሳሽ ወጪ አውጥተው ለአመታት ቢሟገቱም፤ በፍርዱ ዋናው ተጠቃሚ ግን ህዝቡ ነው። ፍርድ public good ከሆነ ማበረታቻ ይፈልጋል። ለተሟጋቾች።

**

 

የእንግሊዝ ነገስታት ሰዎችን በወንጀል ከመክሰሳቸው በፊት የፍሬ ነገሩን ዝርዝር በመንገር ከዳኞች የህግ ምክር ይጠይቁ ነበር። መጀመሪያ አካባቢ ዳኞቹ ምክሩን ይሰጡ ነበር። በምክሩ መሰረት ክስ መመስረት የሚያዋጣ ሲሆን፤ ነገስታቱ ክስ ይመሰርታሉ። ካልሆነ ዳኞችን እስከመቀየር ድረስ ይሄዱ ነበር። እያደር ግን ዳኞች የሚቀርብላቸውን የምክር ጥያቄ አለመቀበል ጀመሩ። ለምን? የዳኝነት ነፃነትን ስለሚሸረሽር። እንዴት?

ዳኞች አስተያየት በሰጡበት ጉዳይ ፍርድ እንዲስጡ ሲቀርብላቸው፤ አስቀድመው በሰጡት አስተያየት ራሳቸውን ያስራሉ። ከዚህ በፊት cognitive dissonance በሚባለው ሃሳብ ዙሪያ እንዳስረዳሁት ሰዎች አስቀድመው በገለፁት ሃሳብ የመታሰር እድላቸው ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ከፍርድ ሂደቱ በፊት አስተያየት እንዲሰጡ ማድረግ የዳኝነት ነፃነትን መፃረር ነው። ለዚህም ነው ዳኞች ህግ በማውጣት ሂደት እንዳይሳተፉ የሚጠበቀው።

የአሰራሩ ኢፍታሃዊነት የበለጠ አግጥጦ የሚወጣው የመጀመሪያውን አስተያየት ሲሰጡ በተሟጋች ወገኖች የቀረቡ ክርክሮችን ሰምተውና መርምረው አስተያየት አለመስጠታቸው ነው። ይህ በዚህ እንዳለ፤ ከዚህ ቀደም ባሉ የፅሁፉ ክፍሎች ያየነው ተጣብቀው የተወለዱት ህፃናት ጉዳይ የኢፍትሃዊነትም ሆነ የዳኝነት ነፃነት ተቃውሞ ሊነሳበት አይችልም። ምክንያቱም የፍርድ ቤቱ አስተያየት የተሰጠው የሁለት ወገኖችን አስተያየት ከሰሙ በሁዋላ ስለሆነ። እንዲሁም የአስተያየቱ ፋይዳ ለወደፊት ህጉን የማጥራት ብቻ ስለሆነ።

 

ጠቅላላ ትርጉም ከspecific ትርጉም እንዴት እንደሚለይ አይተናል። ጠቅላላ ትርጉም፤ አንድን ህግ በጠቅላላው ማብራራት ነው። ለማብራራት ሲሉ የተለያዩ ምሳሌዎችን እና hypotheticals ሊጠቀም ይችላል። ህጉን የማጥራት ፋይዳ ይኖረዋል። ፍርድ ቤቶች በምን አይነት ሁኔታዎች ጠቅላላ ትርጉም ይሰጣሉ?

ጠቅላላ ትርጉም ህጉን የማጥራት ፋይዳ ቢኖረውም አስገዳጅነት ባህሪ የለውም። ዋናው ሃይሉ የሚመነጨው ትርጉም ከዳበረበት ሂደት፥ ትርጉሙን ከሰጠው አካልና፥ በቀረበው ማብራሪያ ይወሰናል። አንዳንድ የመጨረሻ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ጠቅላላ ትርጉም ይሰጣሉ። ለምሳሌ የቻይና ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዲስ የተደነነጉ ህጎችን አስመልክቶ ጠቅላላ ትርጉም ይሰጣል። መልእክቱ፤ ህጉን አስመልክቶ ሙግት ወደፊት ቢቀርብልኝ በዚህ መልኩ ነው የምረዳው የሚል መልእክት አለው።

ጠቅላላ ትርጉም የሚሰጡት ፍርድ ቤቶች ብቻ አይደሉም። የተለያዪ አካላት ይሰጣሉ። በተለይ ህጉን እንዲያስፈፅሙ ስልጣን የተሰጣቸው አካላት ጠቅላላ ትርጉም ይሰጣሉ። ለምሳሌ ጠቅላይ አቃቤ ህግ።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሚሰጣቸው ጠቅላላ ትርጉሞች በስሩ ላሉ ባለሙያዎች መመሪያ ነው። ወጥ አስራርን ለማስፈንና ቅልጥፍናን ለማምጣት ይረዳል። በተጨማሪም ለዜጎች ህጉን የማጥራት ፋይዳ አለው። አቃቤ ህግ በሚሰጠው ትርጉም ራሱ ይገደዳል።

 

ሕገ መንግሥቱ

ከዚህ ቀደም ባለው ክፍል ስለ ህግና ፍርድ ጉዳዮች ማብራሪያ ቀርቧል። በሀገራችን የሚስተዋሉ ችግሮችና መወሰድ ያለባቸው አንዳንድ የለውጥ ውሳኔ ሃሳቦችም እንዲሁ። በዚህ ክፍል ስለ ሕገ መንግሥታዊና ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ አንዳንድ ነገሮችን እንመለከታለን።

ከህጎች ሁሉ የበላይ ከሆነው ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረኑ ማናቸውም የመንግሥት ውሳኔዎች፥ ህጎችና፥ ልምዶች፥ አሰራሮች ዋጋ እንደሌላቸው በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል። ጥያቄው፤ እነዚህ ነገሮች ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጋጫሉና ዋጋ አልባ ናቸው ብሎ የሚወስነው አካል ማን ነው?

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 62 መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ስልጣን አለው።

በአንቀፅ 83(1) መሰረት “የሕገ መንግሥት ክርክር ጉዳይ ሲነሳ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ያገኛል”። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥታዊ ክርክሮችን በተመለከተ ውሳኔ የሚሰጠው የፍሬነገርና የህግ ሙግቶች/ክርክሮች ሲነሱ ነው። ውሳኔ ይሰጣል ሲባል በተነሱት ሕገ መንግሥታዊ የፍሬነገርና የህግ ሙግቶች ላይ ውሳኔ ይሰጣል ማለት ነው። ከውሳኔው ውስጥ ሕገ መንግሥቱን የሚመለከቱ የትርጉም ውሳኔዎች ሕገ መንግሥቱን የማዳበርና የበለጠ ግልፅ የማድረግ ፋይዳ አላቸው።

በአንቀፅ 62 መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ስልጣን እንዳለው ሲደነግግ በሕገ መንግሥታዊ ክርክሮች ላይ የሚሰጠውን የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚመለከት ነው? ወይስ የሕገ መንግሥት ክርክሮች ሳይነሱም ሕገ መንግሥቱን በጥቅሉ የመተርጎም ስልጣንን ይጨምራል?

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥታዊ ክርክሮችን በመፍታት ረገድ በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ እንደሚታገዝ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል። በአንቀፅ 82(1) መሰረት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ተቋቁሟል። ጉባኤው አስራ አንድ አባላት አሉት። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት (ሰብሳቢ)፥ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት (ምክትል ሰብሳቢ)፥ በፕሬዝዳንት የተሾሙ ስድስት የህግ ባለሙያዎች፥ እና ሶስት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት።

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 84(1) መሰረት “የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ስልጣን ይኖረዋል። በሚያደርገው ማጣራት መሰረት ሕገ መንግሥቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባል”።

የአማርኛው ቅጂ “ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች” የሚል አባባል ሲጠቀም የእንግሊዘኛው ቅጂ ሕገ መንግሥታዊ ክርክሮችን የሚለውን ቃል ይጠቀማል። የቀደመው የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ክርክር ጉዳዮችን እንደሚወስን ይደነግጋል። በመሆኑም በዚህ አንቀፅ የተጠቀሰው “ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች” የክርክር ጉዳዮች ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በሁለት አይነት ሁኔታዎች፤ የማጣራት ስራዎችን እንደሚሰራ ተደንግጓል።

አንደኛ፤ ማንኛውም የክልል ወይም የፌዴራል ህጎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናሉ የሚል ጥያቄ ሲቀርብለት ነው። እንዲህ አይነት ጥያቄ በፍርድ ቤት ወይም በባለጉዳዮ ሊቀርብ ይችላል። በዚህ ጊዜ አጣሪ ጉባኤው ጉዳዮን መርምሮ የውሳኔ ሃሳብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል። እንደ ነገሩ ሁኔታ ጥያቄ የቀረበበት ህግ ሕገ መንግሥቱን ስለሚቃረን ስለሚቃረን ህጉን ዋጋ አልባ የሚያደርግ የውሳኔ ሃሳብ ሊሆን ይችላል ወይም ሕገ መንግሥቱን ስለማይቃረን ጥያቄውን ውድቅ የሚያደርግ የውሳኔ ሃሳብ ሊሆን ይችላል። በሁለቱም አማራጭ የውሳኔ ሃሳቦች ሕገ መንግሥቱን መተርጎሙ ወይም ማብራራቱ አይቀርም።

ሁለተኛ፤ በፍርድ ቤት በመታዬት ባለ ጉዳይ ላይ ሕገ መንግሥቱ እንዲተረጎም ጥያቄ ሲቀርብለት ነው። ጥያቄው በፍርድ ቤቱ ወይም በባለጉዳዩ ሊቀርብ እንደሚችል ተደንግጓል። ጥያቄው የአንድን ህግ ሕገ መንግሥታዊነት የሚመለከት ሳይሆን የሕገ መንግሥቱን ትርጉም የሚመለከት ነው። በዚህም ጊዜ ሁለት አማራጭ ውሳኔዎችን ሊያቀርብ ይችላል። አንደኛው ሕገ መንግሥቱን መተርጎም አያስፈልግም የሚል ነው። በዚህ ውሳኔ የማይስማማ አካል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይግባኝ ሊል ይችላል። ሁለተኛው ሕገ መንግሥቱ በዚህ መልኩ መተርጎም አለበት የሚል የውሳኔ ሃሳብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊያቀርብ ይችላል።

በአንድ በኩል የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ስልጣን እንዳለው ይደነግጋል። በሌላ በኩል ደሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥታዊ ክርክሮች ላይ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን እንዳለው ተደንግጓል። ሕገ መንግሥታዊ ክርክሮች የሚባሉት ደሞ ሁለት አይነት እንደሆኑ የሕገ መንግሥት ጉድዮች አጣሪ ጉባኤን በሚመለከተው የሕገ መንግሥት ክፍል ተደንግጓል። አንደኛው ጉዳይ የህግን ሕገ መንግሥታዊነትን የሚመለከት ነው። ህጉ በፍርድ ቤት እየታዬ ያለ ሊሆን ወይም ላይሆን ይችላል። ሁለተኛው ጉዳይ በፍርድ ቤት እየታዬ ባለ ክርክር ላይ ሕገ መንግሥቱ መተርጎም አለበት የሚል ጥያቄ በፍርድ ቤቱ ወይም በባለጉዳዩ ሲቀርብለት ነው።

ከእነዚህ ውጭ ሌሎች ጉዳዮችን አጣሪ ጉባኤው ማስተናገድ እንደሚችል በሕገ መንግሥቱ አልተጠቀሰም። በሕገ መንግሥቱ ካልተጠቀሰ እና በግልፅ ለተጠቀሱት ስልጣኖች አስፈላጊ ነው ተብሎ ካልታመነ ደሞ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል። አጣሪ ጉባኤው፤ ከእነዚህ ጉዳዮች ውጭ፤ የሕገ መንግሥት ትርጉም የውሳኔ ሃሳብ፤ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ ካልቻለ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ስልጣን እንዳለው የሚደነግገው አንቀፅም እነዚህን ጉዳዮች ብቻ የሚመለከት ስልጣን ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣን ከእነዚህ ጉዳዮች ውጭ እንደሚሄድ አድርጎ መውሰድ፤ ሕገ መንግሥቱን ያለ አጣሪ ጉባኤው አጋዥነት እንዲተረጉም የሚያደርግ ነው። ይህ ደግሞ ከሕገ መንግሥቱ መንፈስ ጋር የሚጋጭ ነው። በአንድ በኩል ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ስልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ ማለትም ለፓለቲካዊ አካል፤ መስጠቱ የሚያስነሳውን የቅቡልነት ችግር ለመፍታት ሲባል አጋዥ የባለሙያዎች ቡድን (አጣሪ ጉባኤ) አቋቁሟል። በመሆኑም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ስልጣን ከሁለቱ ጉዳዮች ውጭ እንዲሻገር ማድረግ ይህን የሕገ መንግሥት መንፈስ ጋር መጋጨት ነው። ለመሆኑ ከሁለቱ ጉዳዮች ውጭ በምን አይነት ሁኔታ የሕገ መንግሥት ትርጉም ሊሰጥ ይችላል?

በቀደመው ክፍል፤ ህግና ፍርድ በሚል ርእስ የተለያዩ ጉዳዮችን አንስተን ነበር። ፍርድ (በተለይ ደግሞ በፍርድ ውስጥ የተካተተ የህግ ትርጉምና ማብራሪያ) ህጉን የማጥራት ፋይዳ እንዳለው ተመልክተናል። ከዚህ አንፃር ምንም እንኳ ፍርድ የተሰጠው ሁለትና ከዚያ በላይ ያሉ ወገኖች መካከል በተነሳ ክርክር ቢሆንም የፍርዱ ፋይዳ ግን ከእነርሱ በላይ እንደሚሻገር ተመልክተናል። እንዲያም ሆኖ ግን፤ በክርክሩ ጥቅሙ የማይነካ አካል ክርክሩ ውስጥ ገብቶ መሟገት አይችልም። ወይም ጥቅሙ በማይነካበት ጉዳይ ላይ፤ ወደፊት የሚሰጠው ፍርድ ህጉን የማጥራት ፋይዳ ስላለው ብቻ፤ ክስ መመስረት አይችልም።

ይህ የሆነበት ምክንያት፤ ጥቅሙ የማይነካበት አካል ባቀረበው ክስ ወይም ሙግት ተመስርቶ ፍርድ መስጠት የፍርዱን ዋጋ ስለሚቀንሰውና የህጉን ትርጉም ወደአልተፈለገበት አቅጣጫ ሊወስደው ስለሚችል ነው። የህጉን ትርጉም አስመልክቶ ጠንካራ ሙግት በማቅረብ በፍርድ ህጉ በላቀ ደረጃ እንዲጠራ የሚያስችለው በክርክሩ ጥቅም ያለው አካል ሲሳተፍ ነው።

ይህ እንዲህ እንዳለ፤ በውስን ሁኔታዎች፤ ህያው ክርክር ባይኖርም ወይም ባንድ ወቅት የነበረው ክርክር ሙት ቢሆንም እንኳ፤ በውስን አካላት አነሳሽነት ፍርድ ቤቶች ህጉን አስመልክቶ አስተያየት እንደሚሰጡ ተመልክተናል። በዚህም ሁኔታ ቢሆን፤ ያንድ ወገንንን ክርክር ብቻ በመስማት ህጉ እንዳይተረጎም፤ በመንግሥት ወጪ ቢሆንም ጠበቆች ሙግት እንዲያቀርቡ እንደሚበረታቱ ተመልክተናል።

ከዚህ ውጭ “እንዲህ ቢሆን ምን ይሆናል” የሚሉ ጥያቄዎች ለፍርድ ቤት ማቅረብ ለምሳሌ በእንግሊዝ ታሪክ የተለመደ አሰራር እንደነበረ አይተናል። ተገቢ ግን አልነበረም። አንደኛ፤ ሙግት ባልቀረበበት፥ በይሆናል በቀረቡ ሁኔታዎች ፍርድ ቤቶች አስተያየት እንዲሰጡና በኋላ እንኳን ሙግት ቢቀርብ በቀደመው አስተያየታቸው እንዲታሰሩ የሚያደርግና የዳኝነትን ነፃነት የሚሸረሽር ተደርጎ ተወስዷል። ለዚህም ነው ፍርድ ቤቶች መንግሥትን የማማከር ግዴታ እንደሌለባቸውና መንግሥትን ማማከር ነፃነታቸውን እንደሚጋፋ በመቁጠር ጥያቄውን ውድቅ ማድረግ የጀመሩት።

ሁለተኛ፤ በይሆናል የሚቀርብ ትርጉም በእውን በተከሰቱ የፍሬነገር ጉዳዮች ያልተወሰነ በመሆኑና የተለያዩ ወገኖች ሙግት ያላቀረቡበት በመሆኑ ከፋይዳው ይልቅ አሉታዊ ጎኑ ስለሚበዛ በጥንቃቄ መታዬት ያለበት ጉዳይ ነው። በተለይ፤ እንዲህ አይነት ጠቅላላ ትርጉሞች ወይም በይሆናል ሁኔታዎች የተሰጡ ትርጉሞች፤ ትርጉሙን በሰጠው አካል አስገዳጅ በመሆናቸው በጥንቃቄና ተገቢውን ሂደት ተከትለው መሰጠት አለባቸው።

የአንዳንድ ሀገሮች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ጠቅላላ ትርጉም እንደሚሰጡ ተመልክተናል። ሆኖም እንዲህ አይነት ጠቅላላ ትርጉሞች በፍርድ መልክ የሚሰጡ ሳይሆን በተርጓሚ ድንጋጌዎች መልክ የሚሰጡ ናቸው። ለምሳሌ፤ በፍርድ ቤቶች አዋጅና በሕገ መንግሥቱ መሰረት የፍርድ ሂደት ለህዝብ ግልፅ መሆን እንዳለበትና የህዝብ ጥቅምንና ሞራልን ለመጠበቅ ሲባል ግን በድብቅ ሊከወን እንደሚችል ይደነግጋሉ። “የህዝብ ጥቅምና ሞራል” የሚለውን አባባል የተለያዩ ዳኞች በተለያዬ መልኩ ሊረዱትና ሊተገብሩት ስለሚችሉ በዚህ ረገድ ግልፅነትና ወጥነት እንዲኖር ፍርድ ቤቶች ጠቅላላ ትርጉም ሊሰጡበት ይችላሉ። እነዚህ ግን ፍርዶች አይደሉም። እንዲያም ሆኖ ጠቅላላ ትርጉም በፍርድ ሂደት ከእንደገና ሊተረጎም የሚችል ነው።

ወደ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስንመጣ፤ በሕገ መንግሥት ክርክሮች የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ አካል ነው። ከእርሱ የበላይ የሆነ ሌላ አካል የለም። በመሆኑም የሚሰጣቸው ውሳኔዎች “በይሆናል” የሚቀርቡ ሁኔታዎችን የሚመለከቱ መሆን የለባቸውም። ከዚህ በላይ ለማስረዳት እንደተሞከረው በይሆናል ሁኔታዎች ውሳኔ ወይም ጠቅላላ ትርጉም መስጠት፤ ፍትሃዊ አይደለም ምክንያቱም ጥቅም ያላቸው የብዙ ወገኖችን ሙግት ሳይሰማ የሚሰጥ ስለሚሆን። ሁለተኛ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና አጣሪ ጉባኤው አስቀድመው አቋም እንዲይዙ በማድረግ፤ በኋላ ይሆናል የተባለው ጉዳይ ቢከሰትና ሙግት ቢቀርብ በቀደመው አቋሙ እንዲታሰር የሚያደርጉ ናቸው። በእርግጥ ጠቅላላ ትርጉም ህጉን በማጥራት ረገድ ፋይዳ አለው። ነገር ግን ጠቅላላ ትርጉም ለመስጠት እጅግ ብዙ አካላት አሉ። ምሁራን መፅሃፍቶችና ፅሁፎች ሲያዘጋጁ ጠቅላላ ትርጉም ሊሰጡ ይችላሉ። የምርምር ተቋማትና የሙያ ማህበራትም እንዲሁ። በመሆኑም የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የአጣሪ ጉባኤው በይሆናል በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ወይም ጠቅላላ ትርጉም መስጠት አይገባውም። እንዲህ ማድረግም ከሕገ መንግሥቱ መንፈስ፥ ከነፃ ዳኝነት፥ እና የሕገ መንግሥቱን ህያውነትና የበላይነት ከመጠበቅ አኳያ ተገቢ አይደለም።

በተጨማሪ፤ ህግና ፍርድ በሚል ርእስ በቀዳሚው ክፍል እንደተብራራው፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ስልጣን አለው ቢባልም፤ ከእርሱ ውጭ ሌላው ንክች አያድርግ ማለት አይደለም። ይልቅስ ክርክር ሲነሳ የመጨረሻውን ውሳኔ የመስጠት ስልጣኑ የእርሱ ነው ማለት ነው። ሕገ መንግሥቱን ማክበርና ማስከበር የዜጎች፥ የክልሎችና የፌዴራል መንግሥቱ እንደሆነ ተጠቅሷል። ሕገ መንግሥቱን ማስከበርና ማክበር የሚቻለው በተረዳነው ልክ ነው። ሕገ መንግሥቱን አስመልክቶ እያንዳንዳችን ያለን መረዳት ደግሞ የትርጉም ውጤት ነው። ከዚህ ውጭ ሕገ መንግሥቱን ማክበር አለብኝ፤ ግን ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ስላልገባኝ በሚል ዜጎችና መንግሥታት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እንዲያቀርቡ ሕገ መንግሥቱ አይጠብቅም። በተመሳሳይ መልኩ የዳኝነት ስልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ እንደሆነ ሲደነግግ እኮ፤ የህግና የፍሬጉዳዮች ክርክር ሲነሳ፤ በተለይ የህጉን ትርጉም አስመልክቶ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን የፍርድ ቤቶች ነው ማለት እንጂ፤ ህጉ ግልፅ ያልሆነለትና ውል መዋዋል የሚፈልግ ሰው ውሉን ከመዋዋሉ በፊት ህጉ እንዲተረጎምለት ለፍርድ ቤት ጥያቄ ያቅርብ ማለት አይደለም።

በሕገ መንግሥቱ መሰረት በሁለት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤው የማጣራት ስራና ይህን ተመስርቶም የውሳኔ ሃሳብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የማቅረብ ስልጣን እንዳለው ቢደነግግም የማጣራት ስራው በምን ሂደት መከናወን እንዳለበት አይደነግግም። ይልቅስ አጣሪ ጉባኤው እራሱ የአሰራር ስነስርአቱን አቅርቆ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚያቀርብ ብቻ ይደነግጋል። ከዚህ በመቀጠል የፌዴሬሽን ምክር ቤትንና አጣሪ ጉባኤውን የሚመለከቱ ሌሎች ህጎችን እንመለከታለን። እነዚህን ህጎች ለብቻ መመልከት ያስፈለገው ሕገ መንግሥታዊነታቸውን አብረን ለመመርመር ነው። ብዙ ጊዜ የአጣሪ ጉባኤውን ስልጣንና አሰራር ስንመለከተ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎችንና አዋጆችን አንድ ላይ መመልከት የተለመደ ነው። እንዲህ በመሆኑ የተነሳ የአዋጆቹን ድንጋጌዎች ሕገ መንግሥታዊነት ለመሞገት አዳጋች ያደርገዋል። ሕገ መንግሥቱን በአዋጆች አግባብ እንድንረዳው የሚያደርግ ነው። ተገቢው መንገድ፤ አዋጆችን በሕገ መንግሥቱ አጋባብ መረዳት ሆኖ እያለ።

 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዋጅ

አዋጅ ቁጥር 251/2001 የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከርና ስልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር የወጣ አዋጅ ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ የተቋቋመ የመንግሥት አካል ሆኖ እያለ፤ አዋጅ በማውጣት ምክር ቤቱን ማጠናከር ለምን አስፈለገ። ምክር ቤቱ ሊኖረው የሚገባ ጥንካሬ በሕገ መንግሥቱ በተሰጡት ስልጣኖች ይወሰናል። በሕገ መንግሥቱ ከተደነገጉት ስልጣኖች ተጨማሪ ስልጣን በመስጠት ምክር ቤቱን ማጠናከር ወይም በሕገ መንግሥቱ ከተደነገጉት ስልጣኖች አንዳንዶቹን በመቀነስ ምክር ቤቱን ማዳከም ሕገ መንግሥታዊ አይደለም። ለመሆኑ ማጠናከርና መዘርዘርስ ለምን አስፈለገ?

የአዋጁ መግቢያ የአዋጁን አስፈላጊነት አስመልከቶ የሚከተለውን ያስቀምጣል (ቃል በቃል ባይሆንም)፤ “የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንና ተግባር ጠቅለል ባለ መልኩ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠ ቢሆንም ለአፈፃፀም ያመች ዘንድ በመደበኛው ህግ ዘርዘር ብለው መደንገግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ ወጥቷል”። አዋጁ የወጣው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ሁለቱም ምክር ቤቶች በሕገ መንግሥቱ የተቋቋሙ ሆነው እያለ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አንደኛው ስልጣን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወጡ ህጎች ሕገ መንግሥታዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ሆኖ እያለ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባወጣው ህግ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ስልጣንና ተግባር ሲዘረዝር፤ እንደ ጠቅላላ ትርጉም እንጂ እንደ አስገዳጅ ህግ ሊወሰድ አይገባም። እንደ ጠቅላላ ትርጉም ለመውሰድም እንኳ፤ አዋጁን በመመሪያ መልክ ራሱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊያወጣው ይገባ ነበር። ይህን ለመግቢያነት ከተመለከትን በኋላ በአዋጁ ስለተደነገጉ ዋና ዋና ጉዳዮች እንመልከት።

በአዋጁ አንቀፅ 3(1) መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ስልጣን አለው። (በእርግጥ አዋጁ የሚለው “ይኖረዋል” ነው። ይህ የፓለቲካ ቋንቋ በህግ ይዘቶችን ሰርጎ እንደገባ ማሳያ ነው)። አንቀፅ 3(1) በሕገ መንግሥቱ ከተቀመጠው የሚጨምረው ነገር የለም።

አንቀፅ 3(2) መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥት ትርጉም የምክር አገልግሎት ለመስጠት አይገደድም። ምክር ለመስጠት አይገደድም ይላል እንጂ ምክር መስጠትን አይከለክልም። ይህ ማለት እንደነገሩ ሁኔታ አንዳንድ የምክር ጥያቄዎችን ሊቀበል አንዳንዶቹን ደግሞ ላይቀበል ይችላል። በምን አይነት ሁኔታዎች ጥያቄዎችን ሊቀበልና ላይቀበል እንደሚችል ግን የሚለው ነገር የለም። ዋናው ጉዳይ ግን፤ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከፈቀደ የምክር አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል ማለት ነው። የዚህ ድንጋጌ ሕገ መንግሥታዊነት በሚገባ መፈተሽ አለበት። “ምክር” የሚባለው ውሳኔ ሳይወሰን በፊት፥ አንድ ድርጊት ከመከወኑ በፊት፥ አንድ ህግ ከመውጣቱ በፊት፥ ወይም አንድ የህግ ጥያቄ ለሚመለከተው አካል ከመቅረቡ በፊት የሚሰጥ ያዋጣል ወይም አያዋጣም የሚል ጥያቄ ነው። አዋጭነቱ ደግሞ የሚለካው ከሕገ መንግሥቱ አኳያ ነው። የምክር አላማ፤ ክርክርን ማስቀርት ነው። የህጋዊነት ጥያቄ ሊያስነሳ የሚችልን ጉዳይ አስቀድሞ በማወቅ፤ ጥያቄው እንዳይነሳ፤ ማለትም ህጉን በማክበር፤ ክርክርን አስቀድሞ ለማስቀረት የሚደረግ ሙከራ ነው። የምክር ጥያቄው አቀራረብ “እንዲህ ቢሆን ምን ይሆናል” የሚል ነው።

ለምሳሌ፤ ጉዳዩ የውል ጉዳይ ቢሆንና ባለጉዳዩ “በውሉ መሰረት የገባሁትን ግዴታ በእነዚህ ሁኔታዎች ባልፈፅም የህግ ውጤቱ ምን ይሆናል?” ብሎ ቢጠይቅ፤ ምክር ሰጪው ሁኔታዎቹን ከህጉ አንፃር ህጉን በመተርጎም አገናዝቦ ውጤቱን ያስረዳል። የሚያስጠይቀው ከሆነ፤ ከሚያከትልበት ሃላፊነት አንፃር አገናዝቦ ግዴታውን ለመፈፀምና ላለመፈፀም ይወስናል። የማያስጠይቀው ከሆነ፤ ግዴታውን መፈፀምና አለመፈፀሙ ካለው ጥቅምና ኪሳራ አኳያ አገናዝቦ ይወስናል።

በተመሳሳይ መልኩ በሕገ መንግሥት ዙሪያ ሊቀርብ የሚችለው ጥያቄ “እንዲህ ቢሆንና እንደዛ ቢሆን፤ ሕገ መንግሥታዊ ውጤቱ ምን ይሆናል?” የሚል ነው። ለምሳሌ፤ በአዋጅ ውስጥ ለማካተት ያሰበው አንድ ድንጋጌ አለ። በዚህ ድንጋጌ መሰረት “የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ልማት ማካሄድ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው የልማት ፈቃዱን ማግኘት የሚገባው ከፌዴራል መንግሥቱ ነው”። ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ መሰረት ክልሎች መሬትንና የተፈጥሮ ሃብትን ያስተዳድራሉ። ድንጋጌውን አካቶ ሕገ መንግሥታዊ ሙግት ከሚቀርብበት ይልቅ አስቀድሞ የድንጋጌውን ሕገ መንግሥታዊነት በተመለከተ ምክር መጠየቅ አሰበ። ተገቢ እሳቤ ነው። ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ። ስለዚህ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህን ምክር ከጠቅላይ አቃቤ ህግ፥ ወይም ከምክር ቤቱ ፅህፈት ቤት፥ ወይም ከሌላ የህግ ባለሙያ ሊጠይቅ ይችላል።

የምክር ጥያቄውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊያቀርብ ይችላል? በአዋጁ መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የምክር አገልግሎት የመስጠት ግዴታ የለበትም። ነገር ግን አልተከለከለም። እንበልና ምክሩን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቀረበ። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደሞ ጉዳዮን ለአጣሪ ጉባኤው ላከው።

አጣሪ ጉባኤው በሕገ መንግሥቱ አግባብ ጥያቄውን መቀበል የለበትም። ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ ከተደነገጉት ሁለት ጉዳዮች ውጭ የሆነ ጉዳይ ነው። አጣሪ ጉባኤው ውድቅ ከማድረግ ይልቅ አስተያየት ሰጠ እንበል። እንበልና ሕገ መንግሥቱን በሆነ አግባብ በመተርጎም ድንጋጌው ሕገ መንግሥታዊ እንደሆነ አረጋገጠ። ምክር ቤቱ ይህን የውሳኔ ሃሳብ ተቀብሎ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቀረበ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን አፀደቀው።

እንበልና አንድ ክልል ይህን ድንጋጌ አስመልክቱ ሕገ መንግሥታዊነቱን የሚሞግት ማመልከቻ ለአጣሪ ጉባኤው አቀረበ። አጣሪ ጉባኤው አስቀድሞ ሙግት ሳይሰማ፥ ሕገ መንግሥታዊ ነው ብሎ ካረጋገጠ በኋላ እንዴት ብሎ ነው ፍትሃዊ የውሳኔ ሃሳብ ሊያቀርብ የሚችለው? የፌዴሬሽን ምክር ቤትም እንዲሁ።

ፍርድ ቤቶች መደበኛ ህጎችን ይተረጉማሉ። ነገር ግን ፍርድ ቤቶችን በሚመለከቱ አዋጆች ውስጥ “የህግ ትርጉምን በተመለከተ ፍርድ ቤቶች የምክር አገልግሎት ለመስጠት አይገደዱም” የሚል ድንጋጌ አናገኝም። ለምን ቢባል? ሊሆን የማይችል ጉዳይ ነው። አንድ ዳኛ ምክር በሰጠበት ጉዳይ ላይ በኋላ ሙግት ሲቀርብለት ፍታሃዊ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ስለማይታሰብ።

በአንቀፅ 5(1) መሰረት ሕገ መንግሥቱን መተርጎም ያስፈልጋል በማለት አጣሪ ጉባኤው በጉዳዩ ላይ የሚያቀርበውን የውሳኔ ሃሳብ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መርምሮ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል። አጣሪ ጉባኤው ትርጉም አያስፈልገውም በማለት ውሳኔ በሰጠባቸው ጉዳዮች ቅር የተሰኘ ወገን ይግባኙን ለምክር ቤት ማቅረብ ይችላል (አንቀፅ 5(2))። በአንቀፅ 6 መሰረት ፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀጥታ የሚቀርብለትን አዲስ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ለአጣሪ ጉባኤው ይልካል።

በአንቀፅ 7 የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥት ነክ ጉዳዮችን ለመወሰን የሚረዱትን የትርጉም መርሆች እንደሚለይና እንደሚተገብር ተደንግጓል። “ሕገ መንግሥት ነክ ጉዳዮችን” በማለት ያቀረበው በእንግሊዘኛው የአዋጁ ቅጂና በሕገ መንግሥቱ አግባብ ስንመለከተው የህግመንግሥት ክርክሮችን የሚመለከት አድርገን መወሰድ ይቻላል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ተጨማሪ አስተያየት ሊያሰባስብ ወይም ማስረጃ እንዲቀርብ ሊያዝ ይችላል (አንቀፅ 8)።

የመንግሥት ህጎችና ውሳኔዎች ህግመንግሥታዊነት ጥያቄ በቀረበበት ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት የፌዴሬሽን ምክር ቤት መንግሥትን በህግ ጉዳዮች የማማከር ስልጣንና ተግባር የተሰጠው አካል እንዲያስረዳ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊያዝ ይችላል (አንቀፅ 9)። ይህ ድንጋጌ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደ ፈቃጅ ድንጋጌ የተቀመጠ ነው። ነገር ግን ከትርጓሜ ፀባይ አንፃርና ከጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊነት አንፃር የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥትን ዋና አማካሪ መልስ እንዲሰጥ ወይም ሙግቱን እንዲያቀርብ ማድረግ ይገባዋል።

በተመሳሳይ በአንቀፅ 9(4) መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት እንደ አስፈላጊነቱ ጉዳዩን ከያዘው ፍርድ ቤት ማብራሪያ መጠየቅ ወይም ባለጉዳዩን ወይም ሌላውን ተከራካሪ ወገን ማነጋገር ይችላል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አግባብነት አላቸው ብሎ የሚያምንባቸውን ተቋማት፥ ባለሙያዎች ወይም ባለጉዳዮች ቀርበው አስተያየት እንዲሰጡ ሊያደርግ ይችላል (አንቀፅ 10)።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥት ትርጉም ላይ የሚሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ አጠቃላይ ውጤት ይኖረዋል፤ ወደፊት በሚነሱ ተመሳሳይ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ የአስገዳጅነት ባህሪ ይኖረዋል (አንቀፅ 11(1))። በመሆኑም ውሳኔዎቹ በሁሉም ዘንድ እንዲታወቁ ምክር ቤቱ ለዚሁ አላማ በሚያዘጋጀው ልዩ መፅሄት ታትሞ ይወጣል (አንቀፅ 11(2))።

የአንድ ህግ አካል ድንጋጌ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በሚል ውሳኔ የተሰጠበት እንደሆነ አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ በቀር ውጤቱ ተወስኖ የሚቀረው በዚያው ድንጋጌ ላይ ብቻ ነው (አንቀፅ 14)።

የምክር ቤቱ ውሳኔ የጉዳዩን ዝርዝር መግለጫ፥ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይም አያስፈልገውም ያለበትን ምክንያትና የደረሰበትን መደምደሚያ በግልፅ የሚያሳይ መሆን ይኖርበታል (አንቀፅ 15)።

 

የአጣሪ ጉባኤው አዋጅ

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አዋጅ ቁጥር 798/2013 የሚከተሉትን ዋና ዋና ድንጋጌዎች አካቷል። ድንጋጌዎቹን ከመመልከታችን በፊት የአዋጁን ሕገ መንግሥታዊነት መመርመር ተገቢ ነው።

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 84(4) መሰረት የህግመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሚመራበትን ስርአት አርቅቆ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል፥ ሲፈቀድም ተግባራዊ ያደርጋል። የጉባኤው ስልጣኖች በሕገ መንግሥቱ ከተደነገጉና የጉባኤው አባላት ከታወቁ፤ ዋና የሚቀረው ጉዳይ ጉባኤው የሚከተለው ስነስርአት ነው። ስነስርአቱን ደሞ ራሱ አርቅቆ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚያስፈቅድና እንደሚተገብር ሕገ መንግሥቱ ይደነግጋል። ከዚህ አንፃር ስንመለከተው፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣው፤ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አዋጅ ሕገ መንግሥታዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው። ከህጋዊ መሰረቱ አንፃር ብቻ ሳይሆን በይዘቱም ቢሆን የአዋጁ የተለያዩ ድንጋጌዎች ጥያቄ ውስጥ የሚገቡ ናቸው።

በአንቀፅ 3 መሰረት ማንኛውም ህግ፥ ልማዳዊ አሰራር ወይም የመንግሥት አካል ውሳኔ ወይም የባለስልጣን ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናል በሚል ጥያቄ በፅሁፍ ሲቀርብለት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ጉባኤ ያጣራል። ይህ ድንጋጌ በቁሙ ከወሰድነው ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ ሆኖ ሊታይ ይችላል። ምክንያቱም አጣሪ ጉባኤው የሚመለከታቸው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች በሕገ መንግሥቱ መሰረት ሁለቱ ናቸው። አንደኛው፤ ማንኛውም የክልል ወይም የፌዴራል ህጎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናሉ የሚል ጥያቄ ሲቀርብለት ነው። ሁለተኛው፤ በፍርድ ቤት በመታዬት ባለ ጉዳይ ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ሲቀርብለት ነው። በአንፃሩ በአዋጁ አንቀፅ 3(1) መሰረት ከህጎች ሕገ መንግሥታዊነት በተጨማሪ የልማዳዊ አሰራሮች፥ የመንግሥት አካል ውሳኔ ወይም የባለስልጣን ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊነት በአጣሪ ጉባኤው ሊጣራ ይችላል።

የአዋጁ አንቀፅ 3(1) በሕገ መንግሥቱ መሰረት ለአጣሪ ጉባኤው የተሰጠውን ስልጣን የሚያሳፋ ቢመስልም እንኳን የሚያሰፋ አይደለም። ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ መነበብ ያለበት በተናጥል ሳይሆን በአንድነት ስለሆነ ነው። ለሕገ መንግሥታዊነት ሙግት መሰረት የሆነው የሕገ መንግሥቱ የበላይነት ነው። ሕገ መንግሥቱ የህጎች ሁሉ የበላይ ባይሆን ኖሮ፤ ህጎችን አስመልክቶ የሕገ መንግሥታዊነት ሙግት ሊቀርብ አይችልም ነበር። የሕገ መንግሥቱን የበላይነት የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ ደግሞ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ማንኛውም ህግ፥ ልማዳዊ አሰራርና፥ ውሳኔ ዋጋ አልባ እንደሆነ የሚደነግግ ነው። በመሆኑም ምንም እንኳ የአጣሪ ጉባኤው የማጣራት ስልጣን ተብሎ የተጠቀሰው የህጎችን ሕገ መንግሥታዊነት ማጣራት ቢሆንም፤ የሕገ መንግሥቱን የበላይነት ከሚደነግገው አንቀፅ ጋር አብረን ካነበብነው፤ አጣሪ ጉባኤው የህጎችን ህግመንግሥታዊነት ብቻ ሳይሆን የውሳኔዎችንና የልማዳዊ አሰራሮችን ሕገ መንግሥታዊነትንም አብሮ የማጣራት ስልጣን እንዳለው ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አዋጅ ድንጋጌዎች ችግር የሚታዬው ከአንቀፅ 3(2) ጀምሮ ነው። በዚህ አንቀፅ ለአጣሪ ጉባኤ መቅረብ የሚችሉ ጉዳዮች ተዘርዝረዋል። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው። አንደኛ፤ በፍርድ ቤቶች ሊወሰን የሚችል ከሆነ፤ ጉዳዩ ለአጣሪ ጉባኤው መቅረብ የሚለው ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት ቀርቦ ሲታይ ነው። ሁለተኛ፤ ጉዳዩ በአስተዳደር አካል ሊወሰን የሚችል ከሆነ በአስፈፃሚው አካል የመጨረሻ ውሳኔ ሲያገኝ ነው። ሶስተኛ፤ በፍርድ ሊወሰን የማይችል በማንኛውም ጉዳይ ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ አንድ ሶስተኛ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ በፌዴራል ወይም በክልል ምክር ቤት አባላት ወይም በፌዴራሉም ሆነ በክልል አስፈፃሚ አካላት ለአጣሪ ጉባኤው ሊቀርብ ይችላል።

በተለይ ሶስተኛውን ሁኔታ እንመልከት። በፍርድ ሊወሰን የማይችልን ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊነት አስመልክቶ አጣሪ ጉባኤው ማጣራት የሚጀምረው በአስፈፃሚ አካላት ወይም በምክር ቤቶች ጥያቄ ሲቀርብለት ነው። አንደኛ፤ ሕገ መንግሥቱ እንዲህ አይነት ስልጣን ለአጣሪ ጉባኤው አይሰጥም። ይህ የአዋጅ ድንጋጌ በሕገ መንግሥቱ ለአጣሪ ጉባኤው የተሰጠውን ስልጣን የሚያሰፋ ነው። ሁለተኛ፤ “በፍርድ ሊወሰን የማይችል ጉዳይ” የሚለው አባባል በሕገ መንግሥቱም የተቀመጠ ነው። በተለይ ፍትህ የማግኘት መብትን የሚመለከተው የሕገ መንግሥት ድንጋጌ። በፍርድ ሊወሰን የማይችል ጉዳይ የሚባለው የፓለቲካ ጉዳዮችን ነው። ለምሳሌ፤ የበጀት አመዳደብን የሚመለከት ጉዳይ የፓለቲካ ጉዳይ ነው። እንዲሁም ገና በመንግሥት ውሳኔ ያልተሰጠበት ጉዳይ በፍርድ ሊወሰን የማይችል ጉዳይ ነው። ማለትም፤ ምክር ቤቶችና አስፈፃሚ አካላት ለአጣሪ ጉባኤው ያቀርቡታል ተብሎ የሚጠበቀው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ውሳኔ ከመወሰናቸው በፊት የሚቀርብ የሕገ መንግሥታዊነት ምክር ጥያቄ ነው። ይህን በተመለከተ ደግሞ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አዋጅ ጋር አያይዘን ከዚህ በላይ እንደተመለከትነው ህግመንግሥታዊ አይደለም።

የዚህ ድንጋጌ ኢሕገ መንግሥታዊነት በሚከተሉት ምክንያቶች ነው። አንደኛ በግልፅ ለአጣሪ ጉባኤው የተሰጡትን ሕገ መንግሥታዊ ስልጣኖች የሚያሰፋ ነው። ሁለተኛ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ምክርን ከጠቅላይ አቃቤ ህግና ከተለያዩ የህግና የሕገ መንግሥት ባለሙያዎች መጠየቅ እየቻለ ለአጣሪ ጉባኤው እንዲጠይቅ ማድረግ የአጣሪ ጉባኤውን ነፃነት የሚጋፋ ነው። በጉዳዩ ላይ ወደፊት ሙግት ቢቀርብ አጣሪ ጉባኤው ቀድሞ ከሰጠው የህግ ትርጉም ምክር/አስተያየት የተለየ ውሳኔ ሃሳብ እንዳይሰጥ የሚያስር ነው። አጣሪ ጉባኤው በሕገ መንግሥቱ እንዲቋቋም ያስፈለገበት ምክንያት ፌዴሬሽን ምክር ቤት በነፃ የህግ ባለሙያዎች እንዲታገዙ ሆኖ እያለ፤ የአጣሪ ጉባኤውን ነፃነት የሚሸረሽር ነው። ህግና ፍትህን በሚመለከት ከዚህ ቀደም ባለው ክፍል እንደተብራራው ለምሳሌ ከእንግሊዝ የዳኝነት ነፃነት ታሪክ መገንዘብ እንደሚቻለው ነገስታት ዳኞችን አሰቀድመው ምክር በመጠየቅ በሰጡት ምክር እንዲታሰሩ የሚያደርግ ነው። ፍርድ ቤቶች የህግ ትርጉምን አስመልክቶ ምክር አይሰጡም። ምክንያቱም ነፃነታቸውንና ፍትሃዊነትን ስለሚቃረን። በተመሳሳይ መልኩ ይህ ድንጋጌ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። ሶስተኛ፤ በእንዲህ አይነት የቢሆን ሁኔታዎች አስተያየት መስጠት በቂ ክርክርና ሙግት ሳይቀርብ አቋም መያዝ ይሆናል።

የአንቀፅ 3(2) ኢሕገ መንግሥታዊነታን ኢፍትሃዊነት ጎልቶ የሚወጣው አጣሪ ጉባኤውን ስነስርአት የሚመለከቱትን ቀጣይ ድንጋጌዎች ስንመለከት ነው። የሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ሲቀርቡለት፤ የአጣሪ ጉባኤው ሰብሳቢ የሙያ አስተያየት እንዲዘጋጅ ለንኡስ አጣሪ ኮሚቴ አባላት ወይም ለፅህፈት ቤት ባለሙያዎች በቅድሚያ ሊመራ እንደሚችል በአንቀፅ 8 ተደንግጓል። እንዲሁን በአንቀፅ 9 መሰረት ጉባኤው የሙያ አስተያየት አግባብነት አላቸው ብሎ ከሚያምንባቸው ተቋማት ወይም ባለሙያዎች ቀርበው አስተያየት እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚችል ተደንግጓል። እንዲሁም ማስረጃ አስቀርቦ ሊመረምር ወይም ባለሙያ ጠርቶ ሊጠይቅ እንደሚችል ተደንግጓል።

በአንቀፅ 10(2) መሰረት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ውይይቱ የሚመራበትና ውሳኔ የሚሰጥበት ወይም የውሳኔ ሃሳብ የሚቀርብበት ስነስርአት አጣሪ ጉባኤው በሚያወጣው መመሪያ ይወሰናል። አንድ ጉዳይ በሚታይበት ጊዜ በበቂ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ለተደጋጋሚ ቀጠሮ መተላለፍ የለበትም (አንቀፅ 10(3))። ጉባኤው የያዘውን ጉዳይ ለህዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ ሊያይ ይችላል፤ ዝርዝር ሁኔታው አጣሪ ጉባኤ በሚያወጣው መመሪያ ይወሰናል። እነዚህ ድንጋጌዎች ቢሆኑም ሕገ መንግሥቱን የሚቃረኑ ናቸው።

በሕገ መንግሥቱ መሰረት የጉባኤው ስነስርአቶች የሚፀድቁት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። ጉባኤው አርቅቆ፥ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲፈቅድ ብቻ ስነስርአቱን ይከተላል። አንደኛ ይህ አዋጅ የወጣው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ስለዚህ የሕገ መንግሥት መሰረት የለውም። ሁለተኛ ስነስርአቱ በጉባኤው ተረቆ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መፅደቅ እያለበት፥ በዚህ አዋጅ መሰረት ግን ስነስርአቶቹን ራሱ ጉባኤው በመመሪያ እንዲወስን የሚፈቅድ ነው። ሶስተኛ፤ ግልፅ ስነስርአትን አስገዳጅ የሚያደርግ ሳይሆን እንደመሰለው ጉባኤው እንዲወስን የሚፈቅድ ነው። አራተኛ፤ የሕገ መንግሥታዊነት ሙግት ያቀረቡ ሰዎች ሙግታቸውንና ማስረጃዎቻቸውን የማቅረብ መብት እንዳላቸው አይደነግግም። ይልቅስ ጉባኤው አግባብነት አለው ብሎ የሚያስበውን አካል ብቻ እንዲሰማ መብት የሚሰጡ ናቸው።

በአንቀፅ 11 መሰረት የጉባኤው ምልአት ጉባኤ የሚሟላው ሁለት ሶስተኛው አባላት ሲገኙ እንደሆነ ይደነግጋል። ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ የሚሰጥ ሲሆን ሰብሳቢው ያለበት ወገን ወሳኝ እንደሆነ ይደነግጋል። በውሳኔዎች ላይ በስብስበባው የተገኙ አባላት፥ የአቤቱታ አቅራቡዎችና ስምና አድራሻ፥ አስተያየት የሰጡ ሰዎች ዝርዝርና የተሰበሰቡ አስተያየቶች በውሳኔዎች ላይ መገለፅ እንዳለባቸው አዋጁ ይደነግጋል።

ከዚህ በላይ ካሉት ክፍሎች እንደምንመለከተው የአጣሪ ጉባኤውና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዋጆች አጣሪ ጉባኤውን የሚመለከቱት እንደ አንድ ነፃ የዳኝነት አካል (ውሳኔና የውሳኔ አስተያየት የሚሰጥ አካል) ሳይሆን እንደ አንድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ኮሚቴ ነው። ለዚህ ማሳያዎቹ የሚከተሉት ናቸው። አንደኛ፤ በሕገ መንግሥቱ ከተጠቀሱት ስድስት የህግ ባለሙያዎች ውስጥ በተለያየ ጊዜ የክልል ፍትህ ቢሮ ሃላፊዎች ይገኙበት ነበር።

ሁለተኛ፤የአጣሪ ጉባኤው በተለያዩ ጊዜዎች ጠበቆችን አንደ አባል አቅፏል። በተለይ በህግ አገልግሎት ገበያ ላይ አገልግሎት በመስጠት የተሰማሩ የህግ ባለሙያዎች በሕገ መንግሥት ጉባኤ አጣሪ መሆናቸው የሚያስነሳው የጥቅም ግጭት ይኖራል። ሊፈጠር ስለሚችሉ የጥቅም ግጭቶች አዋጁ የሚደነግገው መፍትሄ የለም። የፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔዎች ጭምር ለሕገ መንግሥት ጉባኤ እንደሚቀርቡ ግምት ውስጥ ስናስገባ እንዲህ አይነት አሰራር የሕገ መንግሥት ትርጉምን ፋይዳ ዋጋ የሚያሳጡ ወይም የሚቀንሱ ናቸው።

ሶስተኛ፤ ጉባኤው አስራ አንድ አባላት እንደሚኖሩት በሕገ መንግሥቱ ቢደነገግም ጉባኤው የሚሰየመው እንደ ዳኝነት አካል ወይስ እንደ ምክር ቤት ወይም ኮሚቴ በግልፅ አልተቀመጠም። ነገር ግን ጉባኤውን የሚመለከቱ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች የሚገኙት ፍርድ ቤቶችን በሚመለከተው የሕገ መንግሥት ክፍል ነው። በመሆኑም አጣሪ ጉባኤው የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክል ምክር ቤት ሳይሆን የዳኝነት ስራን የሚሰራ ተቋም ተደርጎ እንደተቀረፀ ነው። እንዲህ ከሆነ ደሞ፤ አስራ አንዱን አባላት ካልተሟሉ መሰየም የማይችል አካል መሆን ነበረበት። ነገር ግን አዋጁ ሁለት ሶስተኛው አባላት ሲሟሉ ምልአተ ጉባኤ እንደሚሟላ ይደነግጋል። ከእነዚህ ውስጥ አብላጫው የደገፈው የጉባኤው ውሳኔ ይሆናል። ማለትም ስምንት ሰዎች በስብሰባው ቢኖሩና አራቱ አንዱን የውሳኔ ሃሳብ ቢደግፉና ከእነዚህ ውስጥ ሰብሳቢው ካለበት የአጣሪ ጉባኤው ውሳኔ በአራት ድምፅ ተደግፎ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሄድ ይሆናል።

የሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ፋይዳነትን ስንመለከት እንዲህ አይነት አሰራር የሕገ መንግሥቱን የበላይነት የሚሸረሽር ነው። የሰበር ሰሚ ውሳኔ በአምስት ወይም በሰባት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች የሚሰጥ ውሳኔ ነው። ከአምስቱ ወይም ከሰባቱ አንድ ዳኛ በተለያየ ምክንያት መገኘት ባይችል ችሎቱ አይሰየምም። እንበልና አምስቱ ወይም ሰባቱ የሰበር ሰሚ ዳኞች የወሰኑት ውሳኔ ለአጣሪ ጉባኤው ቀረበ። አጣሪ ጉባኤው ስምንት ሆኖ ተሰበሰበ። ከስምንቱ ውስጥ አራቱ (ሰብሳቢው ያለበት) የሰበር ሰሚውን ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ስለሚቃረን በሚል ውድቅ ይሁን የሚል የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቀረቡ። ከአራቱ ውስጥ አንዱ ሰብሳቢው ቢሆንም ሶስቱ ግን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላቱ ሊሆኑ ይችላል።

አራተኛ፤ የስድስቱ የህግ ባለሙያዎች የስራ ዘመን ስድስት አመት እንደሆነና ከስድስት አመት በፊትም በፕሬዝዳንት ሊነሱ እንደሚችል ተደንግጓል። ይህም ቢሆን የአጣሪ ጉባኤውን ገለልተኝነት የሚሸረሽር ነው። ሕገ መንግሥቱ አጣሪ ጉባኤውን የሚመለከተው እንደ የዳኝነት አካሉ ነው። በመሆኑም የዳኝነት ነፃነት ተጠቃሚ መሆን አለባቸው።

በመጨረሻም የሕገ መንግሥት ጉዳዮች የዳኝነት ጉዳዮች ተደርገው ተወስደው አጣሪ ጉባኤው መከተል ያለበት የዳኝነት ስነስርአትን ነው። እንደ የዳኝነት ጉባኤ አንድን ጉዳይ ማጣራት የሚችለው ሁሉም አባላቱ ሲገኙ ብቻ ነው። ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት (ጥያቄ አቅራቢዎችን ጨምሮ) የመደመጥ መብት እውቅና መስጠት ይገባዋል።

አንድ የዳኝነት ተቋም (ፍርድ ቤት፥ አጣሪ ጉባኤውንና፥ ሌሎች አካላትን ጨምሮ የሚሰጠው ፍርድ ወይም ውሳኔ መቀበል ለምን ግዴታ ይሆናል? ወይም የቅቡልነቱ መሰረት ምንድር ነው? እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ አስፈላጊ ነው። በተለይ ለአጣሪ ጉባኤው። ምክንያቱም የአጣሪ ጉባኤው ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሃሳብ በፓለቲካ አካሉ፤ ማለትም በፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ ሊሻር ይችላል። የጉባኤው የውሳኔ ወይም የውሳኔ ሃሳብ ሃይል ያለው በቅቡልነቱ ስለሆነ።

አንደኛ፤ ሁለቱም ወገኖች እና ሌሎች ጥቅም ያላቸው ሰዎች የፍሬነገርና የህግ ሙግታቸውን የማሰማት እድል አላቸው። አንዱ ለሌላው ሙግትና ላቀረበው ማስረጃ መልስ የመስጠት መብት አለው። በመሆኑም አጣሪ ጉባኤው እንዲህ አይነት ስነስርአት ሊከተል ይገባዋል።

ሁለተኛ፤ ስህተት ተሰርቷል የሚል ወገን ይግባኝ ማለት ይችላል። በዛ ባሉና የተሻለ ልምድ ባላቸው ዳኞች ፍርዱ እንዲመረመርለት ማድረግ ይቻላል።

ሶስተኛ፤ በአብዛኛው ዳኞቹ የህግ ባለሙያዎች ናቸው። ህግን የመተርጎምና ለተለያዩ ሁኔታዎች አንፃር ውሳኔ የሚሰጡ። 

አራተ፤ ዳኞች የፍሬነገር ባለሙያዎች አይደሉም። ቢሆንም ተሟጋች ወገኖች ማስረጃ፥ ባለሙያ ምስክር ማሰማት፥ ማቅረብ ይችላሉ።

አምስተኛ፤ ፍርድ ቤቶች በዳኝነታቸው ነፃ መሆን አለባቸው። የሚገዙት በህግ ነው። የአጣሪ ጉባኤው አባላት፤ በተለይ ደግሞ ስድስቱ የህግ ባለሙያዎች የዳኝነት ነፃነት ተጠቃሚዎች መሆን አለባቸው። የስራ ዘመናቸው እንደ ማንኛውም ዳኛ መሆን አለበት። ከሹመታቸው የሚነሱበትም ስርአት ተመሳሳይ መሆን አለበት።

ስድስተኛ፤ የፍርድ ስርአቱ እና ፍርዱ ለሰዎች፥ ባለሙያዎች፥ ሜዲያ ግልፅና ተደራሽ መሆን አለበት።

 

 

ትርጉም ያስፈልገዋል?

ከዚህ በላይ ባለው ክፍል ለማስረዳት እንደተሞከረው አሁን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የምክር ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ ባለመሆኑ ተቀባይነት ማግኘት የለበትም። አማካሪ ጉባኤውም ሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥቱ የበላይነት ዋስትና እንጂ የመንግሥት አማካሪ አይደሉም። ሆኖም ግን ከተነሳው ጭብጥ አኳያ ሕገ መንግሥቱ ትርጉም አያስፈልገውም በሚል የሚስተጋባ ብዥታ አለ።

      አንደኛው ብዥታ ሕገ መንግሥቱ በጉዳዩ ላይ የሚናገረው ነገር ሳይኖር ምኑ ነው የሚተረጎመው የሚል ነው። በሌላ አነጋገር እንዴት ዝምታ ሊተረጎም ይችላል የሚል ሃሳብ ይደመጣል።

ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚቀርብ የትርጉም ጥያቄ አንድን ቃል ወይም አንቀፅ በመጥቀስ አይደለም። ይህን እንድል ያስገደደኝ፤ አንዳንድ ሰዎች እንዴት ዝምታ ይተረጎማል ሲሉ ሰምቼ ነው። ጥያቄው የሚቀርበው በጭብጥ መልክ ነው።

ለምሳሌ፤ "በበሽታና በሌሎች ምክንያቶች ምርጫ ማካሄድ በማይቻልበት ጊዜና የወቅቱ ምክር ቤት የስራ ዘመኑን ከጨረሰ፤ ምክር ቤቱን በትኖ በስድስት ወር ውስጥ ምርጫ ከማካሄድ ውጭ፤ ምን አይነት ህግ መንግሥታዊ አማራጮች አሉ?" ጠቅለል ባለ መልኩ ጭብጡን እንዲህ ያስቀመጥኩት መንግሥት እያሰባቸው ያሉ አማራጮችን በሙሉ ስላላወኳቸው ነው።

አንደኛው አማራጭ፤ የምክር ቤቱን የስራ ዘመን ማራዘም ከሆነ፤ ጭብጡ እንደሚከተለው ይሆናል። "በበሽታና በሌሎች ምክንያቶች ምርጫ ማካሄድ ባማይቻልበት ጊዜና የወቅቱ ምክር ቤት የስራ ዘመኑን ከጨረሰ፤ የምክር ቤቱን የስራ ዘመን ማን፥ እንዴት፥ በምን አይነት ሁኔታዎች፥ እስከ ምን ያህል ጊዜ ማራዘም ይችላል?"

ጥያቄው እንዲህ ነው የሚቀርበው እንጂ "እባክህ ቁጥር 7ን ተርጉምልኝ" በሚል አይደለም። ለዚህ ነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የማማከር አገልግሎት ለመስጠት አይገደድም የሚለው አዋጁ።

አንዳንድ ሰዎችና ባለሙያዎች ግልፅ የሆነ ነገር ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም አያስፈልገውም ሲሉ ይደመጣል።
ልክ ነው። እስማማለሁ። ጥያቄው፤ ጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ያስፈልገዋል? ግልፅነት ይጎድለዋል?
ይህ የፓለቲካ ጥያቄ አይደለም። በስምምነት ልንመልሰው አንችልም። ለጥያቄው የመጨረሻ መልስ የሚሰጠው የሕገ መንግሥቱ ተርጓሚ ነው።

 

ጠቅላላ ትርጉምና ውጤቱ

ከዚህ በላይ ባለው ክፍል ለማስረዳት እንደተሞከረው ለአጣሪ ጉባኤው የቀረበው ጥያቄ የሕገ መንግሥታዊነት ሳይሆን የሕገ መንግሥት ትርጉም ምክር ጥያቄ ነው። እንዲህ አይነት ምክር አጣሪ ጉባኤው መስጠት እንደሌለበትና፥ ሕገ መንግሥታዊ እንዳልሆነ፥ እንደውም ብዙውን የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የአጣሪ ጉባኤ አዋጆችን ኢሕገ መንግሥታዊ ስለሆኑ ውድቅ እንዲያደርግ እጠይቃለሁ።

አጣሪ ጉባኤው አስተያየቴን ባይቀበለውና ትርጉም ለመስጠት ከተነሳሳ፤ አስተያየቱን ወይም ትርጉሙን ጠቅላላና አስገዳጅ ያልሆነ ሊያደርገው ይገባል። ከዚህ በታች የበለጠ ተብራርቷል።

ከዚህ ቀደም፤ በጉዳዩ ላይ ጠቅላላ አስተያየት በማህበራዊ ድረገፆች ስሰጥ ቆይቻለሁ። በተለይ በመንግሥት የቀረበው ጥያቄ አወቃቀር ችግሮች በተመለከት አስተያየት ሰጥቼ ነበር። እንበልና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎ ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም መልስ ሰጠ። ጥያቄው፤ ጉዳዩን የመቋጨት ውጤት አለው?

በመጀመሪያ ግን ምን አይነት መልስ ሊሰጥ ይችላል? እርሱን የምናየው ሆኖ፥ የኔን አረዳድ እንደሚከተለው በቀላሉ አቅርቤዋለሁ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምን አይነት ሁኔታዎች እንደሚታወጅ ሕገ መንግሥቱ ይደነግጋል። ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት ነው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ ውጤቱ ምንድር ነው? አንደኛ፤ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጨማሪ ስልጣን ይሰጠዋል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስልጣን በሕገ መንግሥቱ የተደነገገና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚወጡ አዋጆች የተደነገገ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ግን ከእነዚህ ስልጣኖች ተጨማሪ ስልጣኖች ያገኛል። ምን አይነት ስልጣኖች የሀገርን ሰላምና ህልውና፥ የህዝብን ደህንነት፥ እና ህግና ስርአትን ለማስከበር የሚያስፈልጉ ስልጣኖች ያገኛል። የስልጣኑን ዝርዝሮች ራሱ በሚያወጣው ደንብ ይዘረዝረዋል።

ሁለተኛ፤ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን መሰረታዊ የፓለቲካና የዲሞክራሲ መብቶችን የማገድ ስልጣን ለምክር ቤቱ ይሰጣል። አዋጁ በመታወጁ ብቻ መብቶቹ አይገደቡም። ነገር ግን ከታወጀ በሁዋላ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መብቶቹን ማገድ ይችላል።

የትኞቹን እና በምን ያህል ደረጃ መታገድ ይችላሉ? ለአዋጁ መታወጅ መሰረት የሆነውን ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስፈልጉትን አስፈላጊ በሆነበት ደረጃ ልክ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወር ተፈፃሚ ነው። ነገር ግን በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ለአራት ወራት ሊታደስ ይችላል።

ለምን ያህል ጊዜ ሊታደስ ይችላል? የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ችግርን ለመፍታት የሚያስፈልጉ ተጨማሪ ስልጣኖችን ለመንግሥት ለመስጠትና መብቶችን ለመገደብ ነው። በመሆኑም ችግሩ እስኪፈታ እና ተጨማሪ ስልጣኖቹ አስፈላጊ እስከሆኑ ድረስ ሊታደስ ይችላል።

በዚህ መካከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስልጣን ዘመን ቢያልቅስ? አሁንም ሊታደስ ይችላል። ያለዚያማ መንግሥት ተጨማሪ ስልጣን ያስፈልገዋል እየተባለ የስራ ዘመኑ ስላለቀ መታደስ አይችልም ማለትማ ሀገርንና ህዝብን ለላቀ ችግር የሚያጋልጥ ነው። ስለዚህ ምንም እንኳ የምክር ቤት የስልጣን ዘመን አምስት አመት ነው ቢልም፥ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንቦች መሰረት ምርጫው ሊራዘም ይችላል።

ምርጫ ሳይከናወን የስራ ዘመኑ በማለቁ ብቻ መንግሥት ስልጣኑን መልቀቅ አለበት ማለት ከሕገ መንግሥቱ አላማ ጋር አብሮ አይሄድም። ሌላው ቢቀር መንግሥት የስራ ዘመኑ ሊያልቅ አንድ ቀን ሲቀረው እኮ ፓርላማውን በትኖ የስድስት ወር መንግሥታዊ ስልጣንን ይዞ መቀጠል ይችላል።

በዲሞክራሲያዊ ስርአት መንግሥት የህዝብ እንደራሴ ነው ተብሎ ይታሰባል። የሚሾመው ደሞ ከሌሎች ጋር ተወዳድሮ ነው። ህዝብ ወካይ ነው። በፍትሃብሄር ህግ እንኳን የምናገኘው መርህ፤ አንድ እንደራሴ የውክልናው ዘመን ሲያበቃ፤ ወትሮ የሚሰራቸውን ነገሮች በሙሉ እየሰሩ የመቀጠል ስልጣን ባይኖረውም እንኳን፤ ለወካዩ ወይም ለአዲሱ እንደራሴ እስኪያስረክብ ድረስ የወካዩን ጉዳዮች በማስተዳደር መቀጠል ይገባዋል። ግዴታው ነው። የዚህን መርህ ወደ ሕገ መንግሥቱ ብንወስደው፤ የስራ ዘመኑ ያለቀ መንግሥት አዲሱ መንግሥት እስኪረከበው ድረስ አስተዳደራዊ ስራዎችን እየሰራ መቀጠል ግዴታው ነው።

ፓርላማውን ሲበትን በስድስት ወር ውስጥ ምርጫ ማከናወን አለበትና መስራት የሚችለው ውስን ነገሮች ናቸው የሚለውን ድንጋጌ ወደ አስቸኳይ ግዜ ጉዳይ ማምጣት አንችልም። ምክንያቱም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅና መታደስ የሚወሰነው በአስፈላጊነቱ እንጂ በጊዜ ገደብ ስላልሆነ።

እንበልና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለስድስት ወር ታውጆ ምርጫውም ተራዘመ። አዋጁ ሳይታደስ ስድስት ወር ቢያፈውስ? የዛን ጊዜ ፓርላማው ወዲያው እንደፈረሰ ይቆጠራል ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማውን የማፍረስ ግዴታ ይኖርባቸዋል። በስድስት ወርም ምርጫ መከወን አለበት።

ይህ ማለት ግን መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በማወጅና በየጊዜው በማደስ ምርጫን የማራዘም ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊነት ጥያቄ አይቀርብበትም ማለት አይደለም። የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚሰጠው ትርጉም ጠቅላላ ትርጉም ነው። ሊራዘም ይችላል ወይ? ከተራዘመስ እስከ መቼ ድርስ? የሚሉትን በተመለከተ ጠቅላላ ትርጉም ነው የሰጠው። ይህ ማለት ግን አሁን ያለውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለራሱ የሰጣቸውን አዳዲስ ስልጣኖችና የመብት ገደቦች፤ ምርጫን የማራዘም ውሳኔን ጨምሮ ሕገ መንግሥታዊነት አረጋግጧል ማለት አይደለም። እነዚህን በተመለከተ ጥያቄ ከቀረበለት ከእንደገና ሊመረምር ይችላል።

በምክር ቤቱ የታወጀን ወይም የታደሰን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕገ መንግሥታዊነት መሞገት ይችላል? አዎ። በምን መሰረት? አንደኛ፤ ጦርነት ወይም አደጋ ወይም በሽታ ወይም የሕገ መንግሥታዊ ስርአት አደጋ የለም በሚል። ቢኖርም፥ ችግሩን ለመጋፈጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አያስፈልግም በሚል። ተጨማሪ ስልጣኖችና የመብት ገደቦች አስፈላጊ አይደሉም በሚል ወይም አስፈላጊነታቸውን አላስረዳም በሚል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለራሱ የሰጣቸውን ስልጣኖችና የመብት ገደቦች ሕገ መንግሥታዊነት መሞገት ይቻላል? አዎ። በምን መሰረት? አስፈላጊ አይደሉም በሚል ወይም መንግሥት አስፈላጊነታቸውን አላስረዳም በሚል።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የፍርድ ቤቶች በከፊል መዘጋት በማረምያ ቤት ከሚገኙ እስረኞች መብት አንጻር
በኮሮና ወረርሽኝ ፍርድ ቤቶችን እንዴት ማስቀጠል ይቻላል?

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 29 March 2024