በጽሑፍ የሰፈረን የውል ቃል የምስክርና ሌላ ዓይነት ማስረጃን በማቅረብ ማሻሻል ይቻላል?

የጉዳዩ መነሻ

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ በመዝገብ ቁጥር 78398 በአቶ ሽፈራዉ ደጀኔ እና ወ/ሮ ጸሀይ ተስፋዬ በአንድ በኩልና በአቶ ሲሳይ አበቡ በሌላ በኩል በተደረገ ሙግት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ጥቅምት 19 2005 የሰጠዉ ዉሳኔ ነዉ፡፡ ጉዳዩ የተጀመረዉ በወረዳ ፍርድ ቤት በአቶ ሲሳይ አበቡ ከሳሽነትና በአቶ ሽፈራዉ ደጀኔ እና ወ/ሮ ጸሀይ ተስፋዬ ተከሳሽ ነዉ፡፡ ከሳሹ እንደሚለዉ በእሱና በተከሳሹ መካከል ሐምሌ 17 2003 የተቋቋመ የቤት ሽያጭ ዉል አለ፡፡

በዚህ ዉል መሰረት በአንደኛዉ ተከሳሽ ስም ተመዝግቦ የሚገኝን ቤት በሃያ ሺ ብር ለመግዛት ተስማምቶና ክፍያ ፈጽሞ እያለ፤ ተከሳሾች ግን የተሸጠዉን ቤት እና ሰነዱን ለማስረከብ እንቢ ብለዋልና ይህን በገቡት ዉል መሰረት እንዲፈጽሙ ይታዘዙልኝ ሲል ከሳሽ የወረዳ ፍርድ ቤቱን ተማጽኗል፡፡ ሁለቱ ተከሳሾች በበኩላቸዉ ዉል መቋቋሙን ሳይክዱ የተስማሙት የመሸጫ ዋጋ ግን አርባ ሺ ብር እንደሆነና ምንም አይነት ክፍያ እንዳልተከፈላቸዉ የሰዉ ምስክር እንዳላቸዉ አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም በዉላቸዉ መሰረት ከሳሽ በአስር ቀናት ዉስጥ ሊከፍል ተስማምቶ አልከፈለም፤ ስለዚህ ቤታቸዉን አሁን ሊሸጡ እንደማይገደዱ ተከራክረዋል፡፡

ወረዳ ፍርድ ቤቱ

የወረዳ ፍርድ ቤቱ ዉል ሰለመኖሩ ተከራካሪ ወገኖች እንደተስማሙ፤ ነገር ግን ልዩነታቸዉ የዋጋዉ መጠንና ስለመከፈሉ ጉዳይ ላይ ስለሆነ በነዚህ ሁለት ነጥቦች ላይ የሰዉ ማስረጃዎች ከሰማ በኋላ እንደዉም መስማት እንደማያስፈልግ ወስኗል፡፡ በጽሁፉ ላይ ዋጋዉ ሃያ ሺ እንደሆነና እሱም እንደተከፈለ በዉሉ ላይ በግልጽ ተመልክቷል፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2005(1) እንደተደነገገዉ ደግሞ በጽሁፍ ማስረጃ ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ ቃልና ቀን በፈረሙት ሰዎች መካከል እምነት የሚሰጠዉ ማስረጃ ነዉ፡፡ በዚህ የጽሁፍ ማስረጃ ላይ የሚገኘዉን ቃል መቃወም የሚቻለዉ በመሃላ ቃል ብቻ እንጂ በሰዉ የምስክርነት ቃል ማስተባበል አይቻልም፡፡ ስለሆነም ሻጮች ግዴታቸዉን ስላልተወጡ ቤቱን ለከሳሽ እንዲለቁና አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን በማቅረብ ድጋፍ ያድርጉ፡፡ ግዴታቸዉንም ባለመፈጸማቸዉም ገደብ ብር አስር ሺ ይክፈሉ በማለት ወስኗል፡፡

ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ

ይግባኝ የቀረበለት ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመቀጫ ገንዘቡን ብቻ አንስቶ የወረዳ ፍርድ ቤቱን ዉሳኔ አጽንቷል፡፡

ኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት

የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በሚል መዝገቡን ዘግቶታል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የሰበር ሰበር

የሰበር ሰበር አቤቱታ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ፤ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል በማለት እንደሚከተለዉ ያብራራል፡፡

እኛም ጉዳዩን እንደሚከተለዉ መርምረናል፡፡ እንደመረመርነዉም በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2005 እንደተደነገገዉ በጽሁፍ ሰነዱ ላይ ስለሚገኝ የስምምነት ቃል እንዲሁም ስለ ተፃፈዉ ቀን በተፈራራሚዎቹ መካከል ሙሉ እምነት የሚጣልበት በቂ ማስረጃ ነዉ ብሎ ሊደመደም የሚችለዉ እንደዉለታዉ ዓይነት የጽሁፍ ዉል አደራረግን ስርአት አስመልክቶ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1678 (ሐ)፤ 1719(2) የተመለከተዉን በሕግ ሊጸና የሚችል ዉል ለመያዝ አስፈላጊ የሆነዉን የዉል አደራረግ ስርአት አሟልቶ የያዘ ስለመሆኑ ሊታይ የሚገባዉ ጉዳይ ነዉ፡፡

በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1678(ሐ) እና 1719(2) መሰረት የዉሉ አደራረግ ስርአት በተለየ አኳኋን እንዲደረግ በሕግ ተለይቶ ከተመለከተዉ ድንጋጌ አንዱ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1723(1) የተመለከተዉ ይገኝበታል፡፡ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ያለን የባለቤትነት መብት በሽያጭ ለማስተላለፍ ሲባል የሚደረገዉ የዉል ስምምነት በጽሁፍ ሆኖ ዉል ለማዋዋል ስልጣን ባለዉ አካል ፊት መደረግ ያለበት ስለመሆኑ ተደንግጓል፡፡ በዚህ አኳኋን ዉል ለማዋዋል ስልጣን ባለዉ አካል ፊት መደረግ አለበት የሚለዉም የሕግ መሟያ ክፍል አስፈላጊነት የሽያጭ ዉል ተደርጓል ወይስ አልተደረገም? ተደርጎ ከሆነስ መቼ በምን ያህል ዋጋ፤ የትኛዉ ንብረት ወዘተ የሚለዉን አስመልክቶ አላስፈላጊ የሆኑ ዉግቶችን ለማስቀረት ታስቦ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚፈጸሙ የባለቤትነትን መብት የሚያስተላልፉ ዉሎች ዉሉ ስለመኖሩ እስካልታመነ ድረስ በአዋዋይ ፊት መደረግ ይኖርባቸዋል፡፡

በዚህ በተያዘዉ ጉዳይ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2005(1) እንደተመለከተዉ በጽሁፍ ሰነድ ላይ ስለሚገኘዉ የስምምነት ቃል እንዲሁም በላዩ ላይ ስለተጻፈዉ ቀን በተፈራራሚዎቹ መካከል ሙሉ እምነት የሚጣልበት በቂ ማስረጃ ነዉ የሚለዉ ድንጋጌ ከላይ በተገለጸዉ አኳኋን ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1678(ሐ)፤ 1719(2) እና 1723(1) ድንጋጌዎች ጋር ተገናዝቦ ሲታይ ለማናቸዉም የጽሁፍ ዉል ስምምነት ተፈጻሚ ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡

ይህ አከራካሪ የሆነዉ ሽያጭ ዉል የተደረገዉ የማይንቀሳቀስ በሆነዉ ንብረት በቤቱ ላይ ነዉ፡፡ ዉሉ የተደረገዉ በፍ/ብ/ሕ ቁጥር 1723 የተመለከተዉን ድንጋጌ አሟልቶ አይደለም፡፡ ዉል ለማዋዋል ስልጣን ባለዉ አካል ፊት ተደርጎ ቢሆን ኖሮ የቤቱን ዋጋ እና ይህንኑ ዋጋ ተቀብለዋል አልተቀበሉም የሚለዉን አስመልክቶ በጽሁፍ ከሰፈረዉ ቃል ዉጭ የመቅረብ ማናቸዉም ክርክር በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2005(1) እንደተደነገገዉ ተቀባይነት ያለዉ ክርክር አይደለም፤ ከጽሁፍ ሰነዱ በቀር የሚቀርብ ማናቸዉም ማስረጃ የሰዉም ምስክሮች ቃል ተቀባይነት የለዉም በማለት መደምደም ባልተቻለ ነበር፡፡

ስለሆነም በሕግ ፊት ሊጸና በሚችል ዉል ለመመደብ ቋሚ ማሟያ ሆኖ የተያዘዉን በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1678(ሐ)፤ 1719(2) እና 1723 የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ተከትሎ የተደረገ ስምምነት ባለመሆኑ ይህ አይነት ስምምነት በሕግ ፊት ዋጋ ያለዉ ሆኖ፤ ሊጸና የሚችል ስምምነት ነዉ ብሎ ዉጤት ለመስጠት የሚቻል ባለመሆኑ የአሁን ተጠሪ ይህን በሕግ ፊት ሊጸና የማይችለዉን ዉል መነሻ በማድረግ እንደዉሉ ይፈጸምልኝ በማለት በአመልካቾች ላይ ክስ ለማቅረብ የሚቻል ሆኖ አላገኘነዉም፡፡

ሆኖም የአሁን አመልካቾች ይህንኑ ቤት ብር 40000.00 /አርባ ሺህ ብር/ ሸጠናል በማለት በፍሬ ነገር ረገድ ገልጸዉ የተከራከሩ ከመሆኑ እና የሽያጭ ዋጋም አልተቀበልንም በማለት የተከራከሩ በመሆኑ የአሁን ተጠሪ በዚሁ አመልካቾች በጠቀሱት የሽያጭ ዋጋዉን ከፍለዉ ቤቱን ለመረከብ እና አስፈላጊ ሰነዶችን ለመጠየቅ ከፈለጉ ግን ይህ ዉሳኔ ይህንኑ መብትን ቀሪ ሊያደርግ የሚችል አይደለም፡፡ ስለሆን በዚህ ሁሉ ምክንያት በግራ ቀኙ መካከል የተደረገዉ ሽያጭ ዉል በማይንቀሳቀስ የሆነዉን ቤትን አስመልክቶ የተደረገ እንደመሆኑ መጠን በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2005(1) የተመለከተዉ ድንጋጌ አፈጻጸም ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸዉ ድንጋጌዎች ጋር አገናዝቦ ሳይመለከት በዚህ በዉል አዋዋይ ፊት ባልተደረገ የቤት ሽያጭ ዉል ላይ የሰፈሩት ማናቸዉም የዉል ቃሎች ሁሉ ያለቅድመ ሁኔታ እንዳሉ የሚታሙ ናቸዉ፤ በማናቸዉም አይነት ምስክርነት ቃል ማስተካከል አይቻልም በሚል የሰጠዉ ትርጉም መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡

 

አንድ ዳኛ ምንም እንኳ በዉጤቱ ቢስማሙም እንዲህ የሚል የልዩነት ሃሳብ አስፍረዋል፤  አብላጫዉ ድምጽ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥሮች 1723(1) እና 2005ን በማጣመር በሰጠዉ ትርጉም አልተስማማሁም፤ በእኔ እምነት የአመልካቾችን የትምህርት ሁኔታ በማጣራት በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1728(3) መሰረት በማድረግ ጉዳዩን መወሰን የተሻለ ነዉ የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

የፓሮል ማስረጃ ሕግ

ይህ ጉዳይ በዉል ሕግ ከሚነሱት ዋነኛ ጥያቄዎች ዉስጥ አንዱ የሆነዉና በጽሁፍ ስለተደረጉ ስምምነቶችን ይመለከታል፡፡ ሕጉ አንዳንድ ዉሎችን በተመለከተ የተለየ የቅርጽ ድንጋጌዎችን (ለምሳሌ በጽሁፍ እንዲሆኑ እና ባለስልጣን ፊት እንዲዋዋሉ) ያስቀምጣል፡፡ ወይም ተዋዋይ/ተገበያይ ወገኖች ወደዉና ፈቅደዉ ዉላቸዉን በጽሁፍ ለማድረግ ወስነዉ ሊሆን ይችላል፡፡ የጽሁፍ ስምምነታቸዉን ከመፈራረማቸዉ በፊት ተገበያይ ወገኖች ብዙ ጊዜ የፈጀ ዉይይትና ድርድር አድርገዉ ይሆናል፡፡ ይህ ዉይይት ፊት ለፊት ወይም በሰነድ ልዉዉጥ ወይም በደብዳቤ የተካሄደ ሊሆንም ይችላል፡፡ በዋና ዋና ነገሮች ላይ ስምምነት ላይ እንደደረሱ ባመኑ ጊዜ የጽሁፍ ስምምነት ይፈራረማሉ፡፡ ታዲያ በዚህ ሂደት ከሚፈጠሩ ችግሮች ዉስጥ አንደኛዉ ስምምነቱን ከመፈራረማቸዉ በፊት የተደረሱ መግባባቶች ሙሉ ለሙሉ በጽሁፉ ላይካተቱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ መግባባቶች በሕግ የሚኖራቸዉ ዉጤት ምንድን ነዉ የሚለዉ አንደኛዉ ጥያቄ ነዉ?

ሁለተኛ የጽሁፉ ስምምነት ከያዛቸዉ የዉል ቃላት መካከል አንዱ ወይም ሌላኛዉ ከስምምነቱ በፊት ከተደረሰባቸዉ መግባባቶች ዉስጥ ይጋጫል፡፡ በዚህ ጊዜ የትኛዉ ተቀባይነት ይኖረዋል?

ሶስተኛ የጽሁፍ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የተደረጉ የጽሁፍ ወይም የቃላት መግባባቶች (ከጽሁፍ ስምምነቱ ጋር የሚጋጩም ሆነ የማይጋጩ) የሚኖራቸዉ የሕግ ዉጤት ምንድን ነዉ?

ለዚህ የሕግ ሙግት መነሻ የሆነዉ ጉዳይ እዚህ ከተጠቀሱት ሶስት ጉዳዮች ጋር ይገናኛል፡፡ የጽሁፍ ዉሉ የቤቱ ዋጋ ሃያ ሺ እንደሆነና ይህም ወዲያዉ እንደተከፈለ በግልጽ ሲያስቀምጥ ሻጮች ግን የቤቱ ዋጋ አርባ ሺ እንደሆነ፤ ምንም እንዳልተቀበሉ፤ እና በአስር ቀናት ዉስጥ ገዢ ለመክፈል ተስማምቶ እንዳልከፈለ ከጽሁፍ ሌላ ማስረጃ እንዳላቸዉ ይናገራሉ፡፡ ጥያቄዉ እነዚህ ማስረጃዎች ተቀባይነት አላቸዉ ወይ የሚል ነዉ?

ወደ ሀገራችን ሕግ ከመምጣታችን በፊት እነዚህን ጉዳዮች ሌሎች ሀገሮች እንዴት እንደሚፈቷቸዉ አንመልከት፡፡ የአንግሎ-አሜሪካን የሕግ ስልትን የሚከተሉ ሀገራት የፓሮል ማስረጃ ሕግ የሚሉት አላቸዉ፡፡ ፓሮል ማለት ከጽሁፉ ዉል ዉጭ ያለ የቃልም ሆነ ሌላ ስምምነት ማለት ነዉ፡፡ ይህንን ስምምነት ለማስረዳት የሰዉ ወይም የሰነድ ጽሁፍ ማቅረብን ይመለከታል፡፡ የፓሮል ማስረጃ ሕግ በጽሁፍ የሰፈረን ስምምነት በፓሮል ማስረጃ ማሻሻል ወይም መጨመር እንደማይቻል ይደነግጋል፡፡

ምንም እንኳ የፓሮል የማስረጃ ሕግ እየተባለ ቢጠራም የማስረጃ ሕግ ሳይሆን የፍሬ ነገር ሕግ (substantive law) እንደሆነ ነዉ፤ ይህን ሕግ በሚቀበሉ ሀገሮች የሚታመነዉ፡፡ ለምሳሌ አንድ መጽሀፍ ይህን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፤ Even though the parol evidence rule is exclusionary, making certain type of evidence inadmissible, the parol evidence rule is not a rule of evidence. The parol evidence rule is a rule of substantive law. At issue is what are the terms of the contract and not what type of evidence is admissible to demonstrate the terms of the contract. A rule of evidence would not bar the proof of the terms of the contract. It would bar a method of proving the terms of the contract. The fact could be established by a different method.

በእነዚህ ሀገራት ፓሮል ማስረጃ ሕግ የሚባለዉ ከምርጥ ማስረጃ ሕግ/ድንጋጌ (best evidence rule) ይለያል፡፡ ለምሳሌ የሚከተሉትን ተመልከቱ፤

1.  እንቅስቃሴዎች ሁሉ የሚባል የዳንስ ድርጅት አለማየሁን እንደ ዳንስ ዳይሬክተር ቀጠረዉ፡፡ ዉሉ በጽሁፍ የተደረገና ለአንድ አመት የሚቆይ ነዉ፡፡ በመካከሉ ድርጅቱ ያለበቂ ምክኒያት አለማየሁን ከስራ አባረረዉ፡፡ አለማየሁ ድርጅቱን በዉል መጣስ ከሰሰዉ፡፡ ዉል በመካከላቸዉ መኖሩን ለማስረዳት አለማየሁ የሰዉ ምስክር ማሰማት ፈለገ፡፡ ነገር ግን ምርጥ የማስረጃ ሕግ የሚባለዉ የጽሁፍ ማስረጃን ብቻ ነዉ የሚፈቅደዉ፡፡ ይህ የማስረጃ ሕግ ነዉ፡፡ እንደ ጠቅላላ ድንጋጌ የሰዉ ምስክርን በመጠቀም አንድ በጽሁፍ የተደረገን ዉል ማስረዳት አይቻልም፡፡ ጽሁፉን ራሱን ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

2.  ነገር ግን እላይ ባለዉ ምሳሌ አለማየሁ የጽሁፍ ዉሉን አቅርቦ ከሱ በተጨማሪ ሌላ የቃል ስምምነት አድርገን ነበርና የሰዉ ምስክር ላሰማ ብሉ ፍርድ ቤቱን ጠየቀ እንበል፡፡ ይህ የቃል ስምምነት የዉሉ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ከሆነ የሰዉ ምስክር ማቅረብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን የቃል ስምምነቱ የዉሉ አካል አይደለም የሚባል ከሆነ የሰዉ ምስክር ማቅረብ አይቻልም፡፡

ልብ ማለት የሚገባን ነገር የፓሮል ማስረጃ ሕግ የሚባለዉ የሚያገለግለዉ ተገበያይ ወገኖች የጽሁፍ ስምምነታቸዉን እንደ መጨረሻና ሁሉን አቀፍ ስምምነት እንዲቆጠር አስበዉ የተስማሙ እንደሆነ ነዉ፡፡

ሌላኛዉ ፓሮል ማስረጃ ሕግ የጋራ ስህተት፤ የሀይል ተግባር፤ እና ማጭበርበር ተፈጽሞ ከሆነ ስራ ላይ አይዉልም፡፡

ሶስተኛ ተዋዋይ ወገኖች የዉላቸዉን የተወሰነዉን ክፍል ብቻ የመጨረሻና ሁሉን አቀፍ በሚል አሳብ ሊስማሙ ይችላሉ፡፡

አራተኛ ፓሮል ማስረጃ ሕግ የሚከለክለዉ ከጽሁፍ ዉሉ በፊት ወይም አንድ ላይ የተደረጉ ስምምነቶችን ነዉ፡፡ ከዛ በኋላ የተደረጉ ከሆነ ይህ ክልከላ አይመለከታቸዉም፡፡

አምስተኛ የሚከለከለዉ ጽሁፍን የሚያሻሽል ወይም የሚጨምርን ነዉ፡፡ ለማብራራት ከሆነ አይከለከልም፡፡

የኢትዮጲያ ሕግ በቃላት፤ በጽሁፍና፤ በድርጊት የተደረጉ መግባባቶች ዉልን ለመተርጎም ያላቸዉ ጠቀሜታ

በኢትዮጲያ ሕግ በጽሁፍ የተደረገ ዉል ግልጽ ካልሆነ እና መተርጎም ካለበት ዉሉን ከመፈራረማቸዉ በፊትና በኋላ ያደረጓቸዉ ግንኙነቶችና የተለዋወጧቸዉ ሰነዶች በሙሉ በመጠቀም የተዋዋይ ወገኖችን የጋራ አሳብ ለማወቅ ይቻላል፡፡ ይህም በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1734 ተመላክቷል፤ የዉሉ ቃል የሚያሻማ በሆነ ጊዜ የተዋዋዮች ሐሳብ ምን እንደነበር ለማወቅ መፈለግ ይገባል፤ ስለዚህም ተዋዋዮች ዉላቸዉን ከመዋዋላቸዉ አስቀድሞ ወይም ከተዋዋሉ በኋላ የነበሩበትን ሁኔታ ማመዛዘን ያስፈልጋል፡፡ ቺቺኖቪች ይህን አስመልክቶ እንዲህ ሲል   ጽፏል፤

Sub-article (2) prescribes considering the parties’ conduct in the search for their common intention. Their conduct is shown by what they wrote, said or did in connection with the ambiguous terms. Their conduct after the contract can also consist in the performance of the dispute provision in a certain sense, which may bar them from claiming another sense for it. In Canada, where an area of land is sold with its boundaries obscurely traced, and a problem arises whether a particular plot is included in the sale, evidence as to precedent negotiations may help to solve the difficulty. Otherwise, the buyer’s claim that the plot is so included can be supported by evidence that the vendor has allowed him to occupy and keep it (1896, Canadian Supreme Reports, 102). The vendor’s post-contractual conduct of performing the disputed terms of a contract in a certain way is good evidence of his initial contractual intention.

በቃላት፤ በጽሁፍና፤ በድርጊት የተደረጉ መግባባቶች በጽሁፍ የተደረገን ዉል ይለዉጣሉ? ያጠናክራሉ?

የጽሁፍ የተደረገዉ ስምምነት ግልጽ ከሆነ ነገር ግን ሙሉ ካልሆነ ከጽሁፍ ስምምነቱ በፊት ወይም በኋላ የተደረጉ መግባባቶችን የዉሉ አካል ተደርገዉ ሊቆጠሩ ይችላሉ ወይ የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ልብ ማለት የሚገባን በአንድ በኩል በጽሁፍ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በቃላት ወይም በሌላ መልኩ የተደረገዉ መግባባት እርስ በርሳቸዉ የማይጋጩ መሆናቸዉን ነዉ፡፡ በእንደዚህ አይነት ጉዳዮች ጊዜ ታዲያ ከጽሁፍ ስምምነቱ በፊት የተደረጉ ስምምነቶችን እንደ ተቀዳሚ ዉሎች መቁጠር ይቻላል፡፡ ይህን አስመልክቶ  ምን አልባት ልንጠቀመዉ የምንችለዉ ቁጥር 1721 ነዉ፡፡ 1721 ስለተቀዳሚ ዉሎች እንዲህ ይላል፤ ተቀዳሚ ዉሎች ለመጨረሻዉ ዉል በተወሰነዉ አጻጻፍ (ፎርም) አይነት መሰራት አለባቸዉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ደግሞ ምንም እንኳ በጽሁፍ ስምምነቱንና ከዛ በፊት ወይም በኋላ የተደረጉ መግባባቶች መካከል ግጭት ቢኖርም ከኋላ የመጣዉ ከፊት የነበረዉን ለዉጦታል ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ለዋጩ ተለዋጩ ዉል የተደረገበትን ፎርም መከተል አለበት፤ ማለትም ከኋላ የመጣዉ ዉል ከፊት የነበረዉን ዉል ፎርም መከተል ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1722 የተቀመጠዉ ነዉ፡፡ 1722 ዉልን ስለመለዋወጥ እንዲህ ይላል፤ ዋናዉን ዉል የመለወጥ ጉዳይ ለዚሁ ዉል በተደነገገዉ አጻጻፍ (ፎርም) መሰራት አለበት፡፡

እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን ነገር 1721ን እና 1722ን ለመጠቀም እያንዳንዳቸዉ ስምምነቶች ዉሎች መሆን አለባቸዉ፡፡ ማለትም ራሳቸዉን ችለዉ ሊቆሙ የሚችሉ ዉሎቸ፡፡ ራሳቸዉን ችለዉ የሚቆሙ ዉሎች ከሆኑና 1721 እና 1722 በሚያዙት መሰረት የተቋቋሙ ከሆነ አንዱ የሌላዉ ተቀዳሚ ወይም ተከታይ ወይም ተለዋጭ ዉል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህ ማለት ምንድን ነዉ በጽሁፍና በምስክር ፊት መደረግ ያለባቸዉ ዉሎች በሌላ ስምምነት/መግባባት ሊለወጡ ወይም ሊታገዙ የሚችሉት እነዚህ ስምምነቶች/መግባባቶች በጽሁፍና በምስክር ፊት መደረግ ያለባቸዉ ከሆነ ነዉ፡፡ ነገር ግን መጀመሪያዉኑ ለስምምነቶቹ የተቀመጠ የተለየ ፎርም ከሌለ በማንኛዉም ፎርም በተደረገ ስምምነት/መግባባት ሊለወጥ ወይል ሊሻሻል ይችላል ማለት ነዉ፡፡ ይህ ማለት ምንድን ነዉ፤ በጽሁፍ የተደረገ ስምምነት በቃላት ሊለወጥ ወይም ሊሻሻል ወይም ሊጠናከር ይችላል ማለት ነዉ፡፤ ይህ ሊሆን የሚችለዉ ግን ስምምነቱ በጽሁፍ የተደረገዉ ሕጉ ሳያስገደድ ወይም ተዋዋይ ወገኖች በዚህ ፎርም ብቻ ነዉ የምንዋዋለዉ ሳይሉ የተደረገ ከሆነ ነዉ፡፡

አሁንም መድገም የምፈልገዉ ነገር፤ በጽሁፍ የተደረገ ዉል በቃላት፤ በድርጊት ወይም በጽሁፍ ሊሻሻል ወይም ሊደገፍ እንደሚችል ነዉ፡፡ ይህ ደግሞ ከዚህ በፊት በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠ ሌላ አስገዳጅ ትርጉምን መሰረት ያደረገ ነዉ፡፡ እኔም በእንግዘሊዘኛ ተርጉሜ ከዚህ በፊት ተጠቅሜበት ሰለነበር አሁንም ራሱን ከዚህ በታች አስቀምጨዋለሁ፡፡

ሰበር መዝገብ ቁጥር 12719

The following is the summary of the facts and the decision of the Cassation Division of the Federal Supreme Court, on issues relating to variation of contracts and its formal requirements, in Lukeser Tourism and Travel Agency Plc v Biruneyes Plc [2007] Cassation File No.12719. On 21 Miazia 1991, the respondent and a company called Cacciamali S.p.A. concluded a contract under which the former agreed to pay US$540,000 to the latter. More than a month later (to be precise on 30 Sene 1991), the respondent signed a document which expresses its agreement to deliver five buses (the value of which is US$452,338), to the appellant, with a view to partially settle its debt. When the respondent failed to deliver the five buses, the appellant brought an action for delivery of the five buses and payment of damages. In its submissions, the respondent raised about five points. First, it argued that the appellant is not a party to neither of the documents signed between the respondent and Cacciamali and hence could not bring an action on the basis of such documents. Second, it argued that even though the name of the appellant is mentioned in the second document he is only supposed to take delivery of the buses on behalf of Cacciamali and the document is not meant to transfer property rights to the appellant. Third, unlike the first contract, the respondent argued, the second document was not signed by two witnesses and hence is not a valid contract. Fourth, the respondent claimed that the second document is not an additional contract; instead it is an ordinary letter which has proposed a new arrangement regarding payment of an existing debt and hence it does not impose any contractual obligation.

The case started in the Federal High Court which held that the second document is a document that contains a new proposal and is not an additional contract and hence is not legally enforceable and the respondent is not required to neither deliver the buses nor pay damages to the appellant. An appeal brought to the Supreme Court was not accepted. The Cassation Division of the Supreme Court considered the matter and held as follows: 

There is no doubt that rights and obligations emanating from contracts affect only those parties who have established the contract through their consent and agreement. Third parties, who were not contracting parties at the time when the contract was established, cannot be bearers of the resulting rights and obligations. This general principle is known as privity of contract (relative effect of contract). This is consistent with Article 1731 which provides that contracts are laws for the contracting parties. It should however be noted that the civil code also provides for exceptional cases where contracts could have effects on third parties. One is where it is made for the benefit of a third party. The second document can be said to have been made for the benefit of the appellant and hence the appellant acquired the right to bring action. By drafting the contents of the second document, the respondent has made an offer to vary the terms of the original contract and proposed that he, as a partial payment of his debt from the original contract, deliver the five specified buses to the appellant and pay off the remaining debt through installments to Cacciamali. It is clear that the appellant was not a party to the original contract. This new proposal to vary the terms of the original contract could have been accepted by silence based on Article 1684. However Cacciamali has signed the offer indicating its agreement to the variation. In addition, the law does not prescribe any special form for the validity of the main contract and hence it could be varied in any form.

 

What is the significance of this case? This decision clarifies one provision of the Civil Code relating to formal requirements. Article 1722 provides that a contract made in a special form shall be varied in the same form. This rule could be interpreted in two ways. First, it could be considered to imply that all contracts which are written should be varied only in written form; contracts which are written and signed by witnesses should be varied only in written document signed by witnesses. This is a liberal interpretation. The second approach is to regard this provision to apply to only those contracts for the validity of which the law or the parties have prescribed a special form-meaning that in such cases the same form must be observed in varying the terms of the original contract. According to the second approach the issue is not whether the original contract was made in writing; rather it is whether or not the law or the parties have prescribed writing as a requirement.

Rene David, while commenting on Articles 1721 and 1722 of the Civil Code, wrote: Formal requirements for particular contracts, as a result either of the law or of an agreement of the parties, also apply to preliminary contracts and to modifications that are to be made in these contracts. On this point, the Code follows the Greek Civil Code (Articles 164-166); it was not thought wise to retain the limitations that are found in the Swiss Code (Article 12, Code of Obligations) on this point. Nevertheless, the term 'modifications' does not include the various ways of extinguishing contracts....Article 1725 of the Code requires that the contract of partnership be in writing. A concludes a contract of partnership with B. The parties later agree to modify the provisions of this contract. This modification of their original contract must be in writing in order to be valid.

The above quotation from the drafter suggests the second interpretive approach to Article 1722: contracts for the validity of which the law or the parties prescribe a special form shall be varied in the same form. In the above case the Supreme Court has also adopted the same approach. But the Supreme Court also made reference to Article 1684 suggesting that a proposal for variation of an existing contract can be accepted through silence; this however does not apply to contracts which can be made in a special form.

 

የቤት ሽያጭ ዉሉን ከዚህ በፊት በተነሱት ነጥቦች አንጻር

በሁለቱ ወገኖች መካከል የሽያጭ ዉል እንደነበር ስምምነት ተደርሶበታል፡፡ ይህም ዉል በጽሁፍ የተደረገዉ ሲሆን የቤቱ ዋጋ ሀያ ሺ እንደሆነና ይህም እንደተከፈለ ይናገራል፡፡ ነገር ግን ሻጮች ዋጋዉ ከጽሁፍ ዉሉ በተለየ መልኩ አርባ ሺ እንደሆነ እና በአስር ቀናት ዉስጥ ገዢ ሊከፍል እንደተስማማ ነገር ግን እንዳልከፈለ የሚያስረዱ ምስክር እንዳሏቸዉ ተናግረዋል፡፡ አባባላቸዉ ሁለት ነገርን ሊጠቁም ይችላል፡፡

1.  በድርድር ወቅት አርባ ሺ ብለን ተስማምተን እያለና ይህንንም በአስር ቀናት ለመክፈል ተስማምቶ እያለ፤ በጽሁፍ ሲቀየር ግን ሃያ ሺ ተብሏል፡፡ ይህ ደግሞ በስህተት/በማታለል ነዉ የሚል

2.  በጽሁፍ ሃያ ሺ የሚል ቢሰፍርም እንኳ ከዛ በኋላ የተደረጉ የቃል ስምምነቶች ግን አርባ ሺ እንደሆነ ይገልጻሉ፤ በመሆኑም ዋጋዉ በዚህ መልኩ ተሻሽሏል የሚል ነዉ፡፡

አሁን የሽያጭ ስምምነቱ በሕጉ መሰረት የተደገ ነዉ እንበልና እላይ ከ1721 እና 1722 ጋር ተያይዞ ከተደረገዉ ገለጻ አንጻር ብንመለከተዉ ዉጤቱ ምን ይሆናል? በ1722 መሰረት ሕጉ ወይም ተዋዋይ ወገኖች በተለየ ፎርም/መልኩ እንዲሆን የሚያዙት ዉል ከሆነ ይህ ዉል ሊቀየር/ሊሻሻል የሚችለዉ በዚሁ በተለየ ፎርም ነዉ፡፡ የቤት ሽያጭ ዉል በጽሁፍ፤ በምስክር የተረጋገጠና፤ በባለስልጣን ፊት የተፈረመ እንዲሆን ሕጉ ያዛል፡፡ በመሆኑም ይህ ዉል ሊቀየር የሚችለዉ በጽሁፍ፤ በምስክር የተረጋገጠና፤ በባለስልጣን ፊት በተፈረመ ሌላ ስምምነት ብቻ ነዉ፡፡ በቃል ስምምነት ብቻ መቀየር አይቻልም፡፡

ነገር ግን የሻጮቹ አባባል በቃላት ባደረግነዉ ስምምነት ዋጋዉ አርባ ሺህ ነዉ፤ በጽሁፍ ሲቀየር ነዉ ልዩነቱ የተፈጠረዉ የሚል ከሆነ፤ ምን አልባት የማታለል ተግባር እንደተፈጸመ ወይም ስህተት የሚጠቁም ስለሚሆን ሊፈተሸ የሚገባዉ ጉዳይ ሊሆን ይችል ነበር፡፡

ሊሆን ይችል ነበር የምለዉ፤ መጀመሪያ ዉሉ በሕጉ መሰረት የተቋቋመ ነዉ በሚል እሳቤ ስለጀመርኩ ነዉ፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ፍርደ ቤቱ እንዳለዉ ዉሉ በሕጉ መሰረት የተቋቋመ ስላልሆነ ዉል ሳይሆን የዉል ረቂቅ ነዉ፡፡

ተገበያይ ወገኖች ዉል ሲሉት ሕጉ ረቂቅ ይለዋል

ዉሉ በተለየ ፎርም እንዲሆን ሕጉ ወይም ተዋዋይ ወገኖች ከወሰኑና ይህን ፎርም ካላሟሉ ዉል ሳይሆን ያለዉ የዉል ረቂቅ ነዉ ይላል ቁጥር 1720፡፡ ይህ ማለት ምንድን ነዉ፤ ሕጉ በጽሁፍ እንዲሆን የሚያዝ ዉል ከሆነ እና ገና ስምምነቱ በቃል ደረጃ ያለ ከሆነ፤ ይህ የቃል ስምምነት ዉል ሳይሆን የዉል ረቂቅ ነዉ፡፡ በዚህ አግባብ መሰረት ነዉ ይህ በጽሁፍ የተደረገ የቤት ሽያጭ ዉል ፍርድ ቤቱ ዉል እንዳልሆነ የቆጠረዉ፡፡ ምክኒያቱም የቤት ሽያጭ ዉል፤ በጽሁፍ፤ በምስክር የተፈረመና በአዋዋይ ባለስልጣን ፊት የተደረገ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን የቀረበዉ ሰነድ በአዋዋይ ባለስልጣን ፊት የተደረገ/የተፈረመ አይደለም፡፡ በመሆኑም ዉል ሳይሆን ረቂቅ ነዉ፡፡

በእርግጥ ተገበያይ ወገኖች ዉል የሚሉትና ሕጉ ዉል የሚለዉ ሊለያይ ይችላል፡፡ የአሁኑን ጉዳይ እንደምሳሌ መዉሰድ ይቻላል፡፡ ሕጉ ዉል የለም ይላል፡፡ ሁለቱም ወገኖች ግን በዚህ ጉዳይ ያለልዩነት ዉል እንደነበር ይስማማሉ፡፡ ሕጉ ዉል የለም ብቻ ብሎ ዝም አይልም፡፡ ይህን የለለዉን ዉል የማፍረስ ስርአት ያስቀምጣል፡፡ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1808 እና ተከታዮቹ ይህን ስርአት ያስቀምጣሉ፡፡ ትንሽ ግራ የሚገባ ነዉ? ሕጉ ዉል አይደለም ረቂቅ ነዉ የሚለዉን ለማፍረስ ስርአት ማስቀመጥ፡፡ በእንግሊዘኛዉ ይህን አይነት ስምምነት void contract ይባለል፡፡ አባባሉ የዉል አይነት ያስመስለዋል፡፡ ስለዚህ ይህን ዉል (void contract) ስለማፍረስ የተቀመጠዉ ስርአት ትርጉም ያለዉ ያስመስለዋል፡፡ ሲመነዘር ግን ትርጉም የለሽ/የተምታታ ያስመስለዋል፡፡ void contract ማለት no contract ማለት ነዉ፡፡ ይህ ከሆነ እንዴት የለለን ዉል ማፍረስ ይቻላል?

ነገሩ እዚህ ላይ ነዉ፤ ሕጉ ዉል የሚለዉና ተገበያይ ወገኖች ዉል የሚሉት ይለያያል፡፡ ሕጉ ዉል የለም ቢልም ቅሉ ተዋዋይ ወገኖች ዉል እንዳለ አስበዉና አምነዉ ንብረትና ገንዘብ ተለዋዉጠዉ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ መስተካከል አለበት፡፡ ለዚህ ነዉ የሌለን ዉል ስለማፍረስ ሕጉ የሚያወራዉ፡፡ እርሱ በርሱ የተምታታ ነገር ግን አላማ ያለዉ ነዉ፡፡

ወደ ተያዘዉ ጉዳይ ስንመጣ የዉል ረቂቅ እንጂ ዉል የለም ብለናል፡፡ ይህ ማለት ግን ጽሁፉ ዋጋ የለዉም ማለት አይደለም፡፡ ጽሁፉ ሃያ ሺ ብር ተከፍሏል ይላል፡፡ እነዛ ምንም አልተከፈለንም እያሉ ነዉ፡፡ እዚህ ላይ ክፍያ ተፈጽሟል ወይ? ከተፈጸመስ ምን ያህል? የሚሉት ጭብጦች ተይዘዉ የተለያየ ማስረጃዎች ሊፈተሹ ይገባ ነበር፡፡ በዚህ  ሂደት የቃልም የጽሁፍም ማስረጃዎች ሊፈተሹ ይገባል፡፡ ነገሩ ከተጣራ በኋላ ሁለቱም ተገበያይ ወገኖች ወደ ነበሩበት ቦታ ይመለሳሉ ማለት ነዉ፡፡ የተፈጸመ ክፍያ ካለ ይመለሳል፡፡

ሰበር ሰሚዉ ችሎት

ሰበር ሰሚዉ ችሎት ዉሉ ሕጉ በሚያዘዉ መሰረት አለመፈጸሙን አስምሮበታል፡፡ እንዲሁም በሕጉ መሰረት ያልተቋቋመን ዉል መሰረት አደርጎ ገዢ እንደዉሉ ይፈጸምልኝ ማለት እንደማይችል ችሎቱ ከገለጸ በኋላ፤ ምንም አይነት የሕግ መሰረት የሌለዉን ዉሳኔ እንዲህ ሲል ሰጥቷል፤ ሆኖም የአሁን አመልካቾች ይህንኑ ቤት ብር 40000.00 /አርባ ሺህ ብር/ ሸጠናል በማለት በፍሬ ነገር ረገድ ገልጸዉ የተከራከሩ ከመሆኑ እና የሽያጭ ዋጋም አልተቀበልንም በማለት የተከራከሩ በመሆኑ የአሁን ተጠሪ በዚሁ አመልካቾች በጠቀሱት የሽያጭ ዋጋዉን ከፍለዉ ቤቱን ለመረከብ እና አስፈላጊ ሰነዶችን ለመጠየቅ ከፈለጉ ግን ይህ ዉሳኔ ይህንኑ መብትን ቀሪ ሊያደርግ የሚችል አይደለም፡፡

በምን የሕግ መሰረት ነዉ የቤቱ ባለቤቶች ቤቱን በአርባ ሺ ብር እንዲሸጡ የሚገደዱት? የተዋዋልነዉ በአርባ ሺ ለመሸጥ ነዉ ብለዉ መከራከራቸዉ አሁን ሰበር ችሎቱ በዚህ እንዲሸጡ ለማስገደድ ምን የሕግ መሰረት አለዉ? እኔ እስከሚገባኝ ምንም የሕግ መሰረት የለም፡፡ መሰረታዊ የሕግ ስህተትን ለቅሞ ማዉጣት የሚገባዉ ፍርድ ቤት ይህን ካደረገ በኋላ ሌላ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ሰርቶ አልፏል፡፡

እንዲሁም የቤቱ ባለቤቶች ምንም ብር አልተቀበልንም ብለዋል፤ ጽሁፉ ደግሞ ሃያ ሺ ብር ተቀብለዋል ይላል፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ እንዴት ነዉ ሰበር ችሎቱ የአልተቀበልንም ባዮችን ቃል ብቻ አምኖ የሚሄደዉ? የእነሱን ቃል የሚደግፍና የጽህፉን ቃል የሚቃወም ሌላ ማስረጃ አግኝቶ ነዉ? ይህ ለመሆኑ ዉሳኔዉ የሚለዉ አንዳች ነገር የለም፡፡

2005ን መቼ ነዉ የምንጠቀመዉ?

ለጉዳዩ መቅረብ ምክኒያት የሆነዉ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2005 አድማስ ግን አሁንም ሰበር ችሎቱ ግልጽ ሳያደርግ ነዉ ያለፈዉ? 2005ን ከ2006 ጋር አብሮ ማየት ሰለሚገባ እዚህ ላይ ሁለቱም ቁጥሮች የሚሉትን እንይ፤

2005፡ የጽሑፍ ማስረጃ በቂነት

(1) የጽሑፍ ሰነድ በላዩ ስለሚገኘዉ የስምምነት ቃል እንዲሁም በላዩ ላይ ስለተጻፈዉ ቀን በተፈራራሚዎቹ መካከል ሙሉ እምነት የሚጣልበት በቂ ማስረጃ ነዉ፡፡

(2) እንዲሁም በእንደራሴ በተፈጸመላቸዉ ሰዎች በኩልና የተዋዋዮች ወገኖች ወራሾች በሆኑት ዘንድም ሙሉ እምነት የሚጣልበት በቂ ማስረጃነት አለዉ፡፡

   2006፡ መቃወሚያ ማስረጃ

(1) በጽሑፍ ዉስጥ ያሉትን ቃሎች ተዋዋዮች ለመቃወም የሚችሉት ቃሉ ይኸዉ ነዉ የሚለዉን ወገን በማስማል ብቻ ነዉ፡፡

(2) በዉሉ ዉስጥ ስለተጻፉት ቃላቶች የሰዉ ምስክር ወይም የሕሊና ግምት ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም፡፡

 

በጽሁፍ የተደረገን ዉል በቃላት ወይም በሌላ መልኩ በተደረገ ስምምነት/መግባባት ማሻሻል የሚቻል ከሆነ እንዴት ነዉ ታዲያ 2005 ስራ ላይ የሚዉለዉ? ማለትም በጽሁፍ የተደረገን ስምምነት በቃላት ማሻሻል በተወሰኑ ሁኔታዎች ዉስጥ እንደሚቻል ካየን፤ 2005 የጽሁፍ ስምምነቱ በቃላት ስምምነት መሻሩን ለማስረዳት ይከለክላል ወይ? እንደኔ አመለካከት ሊከለክል አይገባም፡፡ ምን አልባት  ሌላ ስምምነት (ከጽሁፉ ሌላ) የለም የሚለዉ ወገን መሃላ እንዲደርግ ሊደረግ ይችላል፡፡ ይህ ወገን ሌላ ስምምነት አላደረግንም የጽሁፉ ብቻ ነዉ የሚል ከሆነና ስለዚህም የሚምል ከሆነ ምንድን ነዉ የሚደረገዉ?

ሌላኛዉ የሚነሳዉ ችግር ይኽ ነዉ፤ አንድ ሕጉ በጽሁፍ እንዲሆን የሚያዘዉን ስምምነት አንደኛዉ ወገን አይ በቃል ለዉጠነዋል ቢልና በ2006 መሰረት መሀላ ተፈጽሞ ማስረጃ ላቅርብ ቢል ይቻላል ወይ? አሁን እያየነዉ ባለዉ ጉዳይ መጀመሪያዉኑ ዉሉ በሕጉ መሰረት ተፈጽሞ ቢሆንና ሻጮች ግን ዋጋዉ ግን በኋላ ወይም በፊት ባደረግነዉ ስምምነት መሰረት አርባ ሺ ነዉ፤ ለዚህ ደግሞ መስረጃ አነን ቢሉ በ2006 መሰረት መሀላ ተፈጽሞ ማስረጃ ይሰማል ወይ? የኔ አቋም 2005ና 2006 የማስረጃ ድንጋጌዎች ናቸዉ፤ ይህ ማለት በsubstantive ድንጋጌዎች የተቀመጡጥን ባከበረ መልኩ ስራ ላይ ሊዉሉ ይገባል፡፡

መደምደሚያ

እንደመደምደሚያ የሚከተሉትን ነጥቦች መጥቀስ እፈልጋለሁ፤

1.  የፓሮል ሕግ የሚሉትና በተለይ የአንግሎ-አሜሪካን የሕግ ስልትን የሚከተሉ ሀገሮች እዉቅና የሚሰጡት በኢትዮጲያ ሕግ የለም፡፡በኢትዮጲያ የዉል ሕግ መሰረት፤ ሕጉ ወይም ተዋዋይ ወገኖች የተለየ ፎርም ካላስቀመጡ በስተቀር፤ ዉልን በማንኛዉም ፎርም በተደረገ ስምምነት ማሻሻልና መጨመር ይቻላል፡፡ ሕጉ ወይም ተዋዋይ ወገኖች የተለየ ፎርም ካስቀመጡ ግን፤ ዉሉ ሊሻሻል ወይም ሊጨመርበት የሚችለዉ በተመሳሳይ ፎርም በተደረገ ስምምነት ነዉ፡፡

2.  የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2005ና 2006 የተቀመጡት ድንጋጌዎች የማስረጃ ድንጋጌዎች በመሆናቸዉ ስራ ላይ የሚዉሉት በsubstantive ሕጉ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች በማይሸረሽር መልኩ መሆን አለበት፡፡

3.  ሰበር ሰሚ ችሎቱ የቤቱ ባለቤቶች ቤቱን በአርባ ሺ እንዲሸጡ ይገደዳሉ ያለዉ ምንም የሕግ መሰረት የሌለዉ ነዉ፡፡

4.  ሰበር ሰሚ ችሎቱ ዉሉ ዋጋ የለዉም ብቻ ሳይሆን በእርግጥ በጽሁፉ እንደተገለጸዉ ሃያ ሺ ብር ተከፍሏል የሚለዉን በተጨማሪ ማስረጃ በመፈተሸ የተከፈለ ብር ካለ እንዲመለስ ማዘዝ ይኖርበታል፤ ወይም ይህን ጠቁሞ ጉዳዮን ለታችኛዉ ፍርድ ቤት መምራት ይገባዉ ነበር፡፡

5.  ሰበር ሰሚ ችሎቱ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የ2005ና 2006ን በተመለከተ የማብራሪያ/አሳማኝ ትርጉም (obiter dictum) ሊሰጥ እየቻለ እድሉና አሳልፏል፡፡

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Why always Hamle? - Tax Thoughts
The New Ethiopian Commercial Code: Uncovering the ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 17 April 2024