መምህሩ ወጣቱን ተማሪ ጠየቀው፤ “በየዓመቱ ይህን ፎቶ ታሳየኛለህ፣ ሁሌም አስተያየቴ አንድ ነው፣ አይረባም። ይህን ያህል ፎቶውን ለምን ወደድከው?”
ወጣቱ መለሰ፤ “ምክንያቱማ፤ ይህን የተፈጥሮ ገጽታ ለመፎተት በጣም ትልቅ ተራራ በእንፉቅቅ መውጣት ስለነበረብኝ ነው”።
የመታደል ውጤት/ተጽእኖ
የተለያዩ ጥናቶችና ግንጥል-ታሪኮች (Anecdotes) እንደሚያሳዩት ሰዎች በእጃቸው ላለ ነገር የሚሰጡት ዋጋ/ቦታ/ግምት፣ ነገሩ ባይኖራቸው ኖሮ ከሚሰጡት ዋጋ ይበልጣል። ሰዎች የሚፈልጉትን ያውቃሉ፣ ፍላጎታቸው ደግሞ ሙሉ፣ ወጥ፣ እና ተሻጋሪ ነው ይሉናል የክላሲካል የምጣኔ ኃብት ምሁሮች፡፡ በእነሱ አባባል ለአንድ ነገር የምንሰጠው ዋጋ ተመሳሳይ ነው፣ ነገሩ በእጃችን ሲኖርና ሳይኖር፡፡ በዚህ ረገድ፣ በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል፣ በጉዋሮ ያለ ጸበል ልጥ መንከሪያ ይሆናል፣ ደብተራ ባገሩ አይከበርም፤ አወኩሽ ናኩሽ ከሚሉት ያገራችን አባባሎች ጋር ይጣረሳል፡፡ በእነዚህ አባባሎች መሠረት፣ በእጃችን ላለ ነገር የምንሰጠው ዋጋ ነገሩ ባይኖረን ከምንሰጠው ዋጋ ያንሳል። (የአገራችን አባባሎች መሰረታቸው ምንድን ነው? ነገሩ በእጃችን ከገባ በሁዋላ ለምንድን ነው የምንሰጠው ዋጋ የሚቀንሰው? ነገሩ እንደ ልባሽ/ያገለገለ ስለሚቆጠርና መልሰን ልንሸጠው ብንሞክር ስለሚቀንስ ነው? ነገሩ በገበያ የማይሸጥ ቢሆንስ? ስለነዚህ አባባሎች ለማውጋት አይደለም። እንዲህ አይነቱን አባባሎች ለማጣጣልም አይደለም። ምሳሌያዊ አባባሎች መቼና በምን ሁኔታዎች የውሳኔ ምክንያት ይሆናሉ፥ መቼ እንደ መሪና መካሪ መቁጠር አለብን ወይስ ወግ የማሳመሪያ ውብ አባባሎች (የቋንቋ ቀለማት) ብቻ ናቸው? ጊዜ ያለፈባቸው፥ ብስባሽ ቅሪቶች ናቸው? ይህን ለሌላ ጊዜ እናቆየው።) ለእነዚህ ምጣኔሃብት ምሁሮች ግን፣ ዋጋው ተመሳሳይ ነው፣ ወይም መበላለጥ የለበትም።