ከውርስ ኃብት ክፍፍል ጋር የተያያዙ አንዳንድ ነጥቦች ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከሰጣቸው ውሰኔዎች ጋር በማገናዘብ የቀረበ

የሟች የውርስ ኃብት ተጣርቶ ከተዘጋ በኋላ የውርስ ኃብት ባለቤትነት ወደ ሟች ወራሾች ይተላለፋል፡፡ በመሆኑም ውርስ ከተዘጋ በኋላ ወራሾች መሀከል ክፍያ እስኪፈጸም ድረስ የሟች ወራሾች በሀብቱ ላይ ያላቸው መብት ምንድነው? ክፍፍሉ ከመፈጸሙ በፊት በጋራ ወራሾች የተያዘ ንብረት በአንደኛው ወራሽ ብቻ ለሶስተኛ ወገን በሽያጭ ቢተላለፍ ፈቃዳቸውን ያልሰጡ ወራሾች መብታቸው እስከምን ድረስ ነው? ገዥውን ያለውስ መብት ምንድነው? የውርስ ሀብት ክፍፍል የሚደረግባቸው ስነ-ስርዓቶችንና ክፍፍል ከተደረገ በኋላ የሚገኙ የውርስ ኃብት የሆኑ ንብረቶች ለወራሾች ሊከፋፈሉ የሚችሉባቸው የህግ ስርዓቶችን በተመለከተ በወራሾችና ወራሽ ባልሆኑ ሶስተኛ ወገኖች መሀከል እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ የደረሱ አከራካሪ ጉዳዮች አሉ፡፡ በዚህ ጽሁፍ እነዚህን ነጥቦች በተመለከተ ከፍትሐብሔር ሕጉና ከተመረጡና አስገዳጅ ከሆኑ የሰበር ውሳኔዎች አንጻር አጭር ዳሰሳ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡

1) የውርስ ሀብት ክፍፍል እስኪደረግ ድረስ የውርስ ሀብት የሆነ ንብረት የማይነጣጠል ስለመሆኑ

የውርስ ኃብት ተጣርቶ ውርሱ ከተዘጋ በኋላ በወራሾች መሀከል የውርስ ሀብት ክፍፍል እስኪደረግ ድረስ የውርስ ኃብቱ በወራሾች መካከል የጋራ ኃብት ሆኖ ይቆያል፡፡ ይህም ማለት የሟች ወራሾች ከሟች ጠቅላላ ኃብት ውስጥ ድርሻቸው የትኛው ንብረት እንደሆነ ሳይለይና ሳይነጣጠል ጠቅላላ ንብረቱ የወራሾች የጋራ ኃብት ሆኖ ይቆያል ማለት ነው፡፡ በዚህ ርዕስ ስር የሟች ወራሾች ስል የሟች ያለኑዛዜ ወራሾችን እና የሟች ጠቅላላ የኑዛዜ ስጦታ ተጠቃሚ የሆነ ሰው ማለቴ ነው፡፡ ምክንያቱም የሟች ልዩ የኑዛዜ ተጠቃሚ የሆነ ሰው ልዩ የኑዛዜ ስጦታው የሟች ውርስ ንብረት እዳ በመሆኑ ውርሱ ከመዘጋቱ በፊት ከሟች ድርሻ በኑዛዜ የተሰጠውን ንብረት ስለሚወስድ ከሟች ያለኑዛዜ ወራሾች ጋር በወራሽነት የሚካፈለው ጠቅላላ የኑዛዜ ተጠቃሚ የሚሆን ሰው ብቻ ስለሚሆን ነው፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1060 ድንጋጌዎች መሰረት በማድረግ የሟች ወራሾች ባልተከፋፈለ የውርስ ኃብት ላይ ያላቸው መብት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1257 እስከ 1277 ስለ ጋራ ባለሀብትነት፣አላባ ስለመጠቀምና ስለ ግዙፍ መብት በተደነገጉት መሰረት የሚተዳደርና የሚወሰን መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለሆነም በእነዚህ ድንጋጌዎች መሰረት ወራሾች የውርስ ሀብትን በፍርድ ቤት አልያም በስምምነት የድርሻ ክፍፍል ጥያቄ አቅርበው እስኪከፋፈሉ ድረስ የውርስ ሀብቱ ላይ በተናጠል የመወሰን ወይም ማዘዝ አይችሉም፡፡

2)የውርስ ሀብት ክፍፍል ስነ-ስርዓት

የኢትዮጲያ የውርስ ህግ በመሰረታዊ መርህነት የውርስ ክፍያው ወራሾቹ በሚያደርጉት ስምምነት መሆን እንዳለበት ይገልጻል፡፡ ወራሾች ያልተስማሙ እንደሆነ አንደኛው ወራሽ የክፉፉሉን አሰራር ካረቀቀ በኋላ በፍርድ ቤት እንዲጸድቅለት ማቅረብ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ሆኖም በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች የመከፋፈሉን አሰራር ዳኞች ካላጸደቁት በቀር ፈራሽ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ የመጀመሪያው ከወራሾቹ አንዱ ሳይኖር የቀረ እንደሆነ ወይም ወኪል ያልተወከለ እንደሆነ ሲሆን ሁለተኛው ከጋራ ወራሾች መሀከል የውርስ ኃብት ከመከፈሉ በፊት የአንደኛው ወራሽ ገንዘብ ጠያቂ የሆነ ሰው ስለ ውርሱ አከፋፈል ትዕዛዝ እንዲሰጥለት የጠየቀ እንደሆነ የውርስ ክፍያ ዳኛ ማጽደቁ የግድ አስፈላጊ መሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1080 እና 1081 ተደግጓል፡፡ የክፍፍሉ አፈጻጸምን በተመለከተ ሟች ኑዛዜ አድርጎ ከሆነ ሟች በኑዛዜ በሰጠው መመሪያ መሰረት መፈጸም እንዳለበትና ሟች ስለ ክፍፍሉ አፈጻጸም ያደረገው ኑዛዜ ከሌለ ከፍ/ብ/ሕ/ቁ 1082 እስከ 1096 በተደነገገው መሰረት መከወን እንደለበት የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1083 በግልጽ ደንግጓል፡፡ የውርስ ኃብት ክፍፍልን ዘርዘር ባለ ሁኔታ ስንመለከተው ወራሾች የውርሱን ንብረት እንዲገምቱ፣ወራሾች በግምቱ ላይ ያልተስማሙ እንደሆነ እነርሱ በመረጧቸው የሽምግልና ዳኞች ግምቱ እንደሚሰራ ፣ንብረቱ የማይንቀሳቀስ ንብረት በሆነ ጊዜ በልዩ አዋቂዎች ግምቱ ተሰርቶ ፕሮፖዛሉ መቅረብ እንዳለበት የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1083 እና 1084 ድንጋጌዎች በመመልከት ለመረዳት ይቻላል፡፡ አልፎ አልፎ በፍርድ ቤቶች ባለው ክርክር ለክፍፍል የቀረበው የውርስ ኃብት ቤት በሚሆንበት ወቅት ቤቱ ተገምቶ በግምቱ መሰረት ወራሾች ድርሻቸውን በገንዘብ ለመካፈል በሆነ ጊዜ ግምቱ ሊሆን ሚገባው ቤቱን ለማሰራት ለሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች መግዣ የወጣውና ለሰራተኞች የተከፈለው ገንዘብ ብቻ መሰረት ሊደረግ ይገባል የሚል መከራከሪያ የሚቀረብ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ግምቱ መሰረት ሊያደርግ የሚገባው ቤቱን ለመስራት ለግብአት መግዣ የወጡ ወጪዎችና ለሰራተኛ ጉልበት የተከፈሉ ክፍያዎች ብቻ ሳይሆን ቤቱ ለገበያ ቢቀርብ የሚያስገኘው በአከባቢውና በወቅቱ ያለ የገበያ ዋጋ መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል በሚል ክርክር የሚያቀርቡ አሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መዝገብ ቁጥር 40510 በቅጽ 8 ላይ የሕግ ትርጓሜ የሰጠ ሲሆን በውሳኔውም " አንድ የውርስ ቤት ለወራሾች በእኩልነት ለማከፋፈል በተለይ ንብረቱ ተገምቶ በግምቱ መሰረት ለሌሎች ወራሾች ገንዘብ የሚከፈል በሆነ ጊዜ ቤቱ ሊገመት የሚገባው ቤቱን ለመስራት ለሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች መግዣ የሚወጣውን ገንዘብና የሰራተኞች ክፍያ ብቻ መሰረት በማድረግ የግንባታ ዋጋ ሳይሆን ቤቱ ለገበያ ቢቀርብ የሚያስገኘው በአከባቢው ያለ የገበያ ዋጋ መሰረት ያደረገ መሆን አለበት" የሚል ነው ከዚህ ውሳኔ መገንዘብ እንደሚቻለው ወራሾች የውርስ ኃብት የሆነ ንብረትን አስገምተን በግምቱ ልክ ክፍፍል እናደርጋለን የሚሉ ከሆነ ግምቱ መሰረት ሊያደረግ የሚገባው የቤቱን ወቅታዊ እና አከባቢያዊ የገበያ ዋጋ መሆኑን ነው፡፡

3) የውርስ ኃብት በወራሾች መሀከል በፍርድ ቤት ውሳኔ ከተከፋፈለ በኋላ ስለሚገኙ የውርስ ንብረቶች

የውርስ ክፍፍል እንዲደረግ ወራሾች ጥያቄያቸውን ለፍርድ ቤት አቅርበው በፍርድ ቤት በነበረ ክርክር ክፍፍሉ ሊከናወን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ክፍፍልን መሰረት ያደረገው ክርክር የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ አግኝቶ የውርስ ሀብቶቹም በወራሾች ከተከፋፈሉ በኋላ በክፍፍሉ ውስጥ ያልተካተቱ ነገር ግን የውርስ ኃብት የሆኑ አዳዲስ ንብረቶች ሲገኙ ይስተዋላል፡፡ አነዚህን አዲስ የተገኙ ንብረቶችን መሰረት በማድረግ ወራሾች አዲስ ክስ ለፍርድ ቤት በሚያቀርቡበት ወቅት ክስ የቀረበበት ንብረት ወራሹ ሆን ብሎ ቀንሶ ያስቀረው ንብረት ነው በማለት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 216(3) መሰረት ውድቅ ሊደረግ ይገባል የሚል መቃወሚያ የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ፡፡ ከዚሁ ጭብጥ ጋር በተገናኘ የፈዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መ/ቁ 153231 በቅጽ 23 ላይ የሕግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ በውሳኔውም ላይ የውርስ ንብረት ክፍያው ከተደረገ በኋላ በክፍያው ውስጥ ያልገቡ በውርስ ንብረት ውስጥ ገብተው የሚቆጠሩ አዲስ ሀብቶች የተገኙ እንደሆነ አዲስ የክፍያ ስርዓት መፈጸም እንደሚቻል ከፍ/ብ/ሕ/ቁ 1103 እና 1104 ድንጋጌዎች መገንዘብ ስለሚቻል በድጋሚ የቀረበው የከፍያ ጥያቄ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 216 መሰረት ውድቅ ሊደረግ አይገባም በማለት ጠቅሷል፡፡ ስለዚህ የውርስ ንብረት ክፍፍል በፍርድ ቤት ውሳኔ ከተከፋፈለ በኋላ በክፍፍል ውስጥ ያልተካተተ አዲስ ንብረት የተገኘ እንደሆነ ወራሽ የሆነ ወገን አቤቱታውን ለፍርድ ቤት ቢያቀረብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 216(3) መሰረት የክስ ምክንያቶችን በመነጣጠል በሚል መቃወሚያ ጥያቄው ውድቅ ሊደረግ አይገባም፡፡

4) ክፍፍል ሳይደረግ ከወራሾች መሀል በአንደኛው ብቻ የሌሎቹ ፈቃድ ሳይኖር የውርስ ንብረት ለ3ኛ ወገን መሸጡ የሚያስከትለው ውጤት

የውርስ ኃብት የሆነ ቤት ከወራሾች መሀከል በአንደኛው ብቻ ለሶስተኛ ወገን በተሸጠ ጊዜ ሌሎች ወራሾች ሽያጩ ከተከናወነ በኋላ ያለአግባብ የተያዘብን ቤቱ ይለቀቅልን በማለት በገዥ ላይ ክስ ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡ በገዥ በኩል ደግሞ ንብረቱን በህጋዊ መንገድ የያዝኩት ስለሆነ ልለቅቅ አይገባም የሚል መከራከሪያ ያቀርባል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 2331 በቅጽ 7 ላይ በሰጠው የህግ ትርጓሜ ከወራሾች መሀከል በአንዱ ብቻ የውርስ ኃብት የሆነ ንበረት ( ቤት) ለሶስተኛ ወገን በሸጠ ጊዜ ለሽያጩ ይሁንታ ያልሰጡ ሌሎች ወራሾች ያለአግባብ በገዥ የተያዘ ቤት ይለቀቅልኝ በሚል የሚያቀርቡት አቤቱታ አግባብነት የለውም በማለት ወራሾች ቤቱ የተሸጠው ያለአግባብ ነው የሚል እምነት ካላቸው ውሉ የሚፈርስበት ምክንያት ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል እንጂ ውሉ ባልፈረሰበት ሁኔታ ገዥው በቤቱ ላይ መብት የለውም ስለሆነም የገዛውን ቤት ለወራሾች ሊለቅቅ ይገባል የሚባልበት የህግ አግባብ የለም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ የሰበር ውሳኔውን መሰረት በማድረግ መገንዘብ እንደሚቻለው የወራሾች የጋራ ኃብት የሆነ ቤት ከወራሾች በአንደኛው ብቻ ለሶስተኛ ወገን በሽያጭ ቢተላለፍ በሽያጩ ተሳታፊ ያልሆኑት ወራሾች የሽያጭ ውሉ ላይ በፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበው ሊፈርስ የሚችልበትን የህግ አግባብ በማስረዳት ከማስፈረስ በስተቀረ ውሉ ጸንቶ ባለበት ገዥው ቤቱን ለቅቆ ሊያስረክበን ይገባል በማለት የሚያቀርቡት ክስ የህግ መሰረት የሌለው መሆኑን ነው፡፡

የሽያጭ ውሉ ሊፈርስ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለውን ጭብጥ በተመለከተ ገዥ ቤቱን በሚገዛበት ወቅት ሻጭ በስሙ ያዞረ ከሆነ እና ህጋዊ ሰነዶችን በአግባቡ አይቶ የገዛ በሚሆንበት ወቅት እንደ ገዥ ተገቢውን ትጋትና ጥንቃቄ አድርጌ የገዛሁ በመሆኔ የሽያጭ ውሉ ሊፈርስ አይገባም የሚል መከራከሪያ በገዥ በኩል ይነሳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወራሾች በጋራ ይዘነው የምንገኘውን ቤት ከወራሾች መሀከል ሌሎች ወራሾች ሳያውቁ የቤቱን ስመ-ንብረት በስሙ አዙሮ ለሌላ ሰው አንዱ ወራሽ ብቻ የሸጠው በመሆኑ ሰለ ሽያጩ ፈቃዳችንን ያልሰጠን ስለሆነ የሽያጭ ውሉ ሊፈርስ ይገባል የሚል ክርክር ይነሳል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅጽ 10 በሰበር መ/ቁ 41857 ላይ በሰጠው ውሳኔ የውርስ ኃብት ሳይከፋፈል ወራሾች በጋራ ይዘውት የሚገኝ ቤት ከወራሾች መካከል ሌሎች ወራሾች ሳያውቁ የቤቱን ስመ- ንብረት በስሙ አዙሮ ለሌላ ሰው ቢሸጥለት ገዥው የሻጩን የማይንቀሳቀስ ንብረት የምስክር ወረቀት አይቶ ባለሀብት እንደሆነ ገምቶ የገዛው ስለሆነ የሽያጭ ውሉ ሊፈርስ አይገባም፡፡ የሌሎች ወራሾች መብት ሊሆን የሚገባው ውሉ ፈርሶ ቤቱን ተረክቦ መከፋፈል ሳይሆን የሽያጩን ብር በየድርሻው መከፋል ነው፡፡ በተጨማሪም በቅጽ 10 በሰ/መ/ቁ 46527 ላይ በተሰጠው የህግ ትርጓሜ መሰረት ገዥ ቤቱን በገዛበት ወቅት የቤቱ ስመ-ሀብት በሻጭ ስም ከነበረ እንዲሁም ሽያጩን ህጉ በሚጠይቀው የአጻጻፍ ስርዓት መሰረት ያከናወኑ ከሆነ ገዥ ቤቱን የገዙት በቅን ልቦና መሆኑን ስለሚያመለክት የቤት ሽያጩ መብቴን ይነካል የሚል ወራሽ ድርሻ አለው የሚባል ከሆነ ሻጭን ከሚጠይቅ በስተቀር ገዥው በህጋዊ መንገድ የገዛውን ቤት እንዲያስረክበው የሚደረግበት የህግ አግባብ የለም፡፡ በሌሎች ሁኔታዎች ግን የወራሾች ሁሉ የጋራ ሀብት የሆነው ንብረት ለመሸጥ፣ለመለወጥ፣ለማስተላለፍ ወይም በዋስት ለማስያዝ ወይም የተመደበበትን አገልግሎት ለመለወጥ የጋራ ባለሀብቶች ሁሉ ስምምት አስፈላጊ እንዲሆን በፍ/ብሕ/ቁ 1262 ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም አንደኛው ወራሽ የውርስ የጋራ ንብረት የሆነውን ቤት ሲሸጥ ውሉን የተፈራረመው የጋራ ባለሀብት የሆኑት ወራሾች ሁሉ ስምምት ሳያገኝ ከሆነ ሌሎች የጋራ ባለሀብት ወራሾች ውሉ እንዲፈርስ ጥያቄ ሲያቀርቡ ውሉ እንዲፈርስ ሊወሰን ይገባል፡፡ ( ሰ/መ/ቁ 64371 ቅጽ 13)

መደምደሚያ

ከዚህ በላይ በተጠቀሰው መሰረት የውርስ ኃብት ተጣርቶ ውርሱ ከተዘጋ በኋላ ሀብቱ ሳይነጣጠልና ሳይከፋፈል ወራሾች መሀከል በጋራ የሚያዝ እና የሚተዳደር ይሆናል፡፡ የውርስ ክፍፍልን በተመለከተ ወራሾቹ በሚያደርጉት ስምምነት መሆን እንዳለበት ይገልጻል፡፡ ወራሾች ያልተስማሙ እንደደሆነ አንደኛው ወራሽ የክፉፉሉን አሰራር ካረቀቀ በኋላ በፍርድ ቤት እንዲጸድቅለት ማቅረብ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ሆኖም በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች የመከፋፈሉን አሰራር ዳኞች ካላጸደቁት በቀር ፈራሽ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ የመጀመሪያው ከወራሾቹ አንዱ ሳይኖር የቀረ እንደሆነ ወይም ወኪል ያልተወከለ እንደሆነ ሲሆን ሁለተኛው ከጋራ ወራሾች ከጋራ ወራሾ መሀከል የውርስ ኃብት ከመከፈሉ በፊት የአንደኛው ወራሽ ገንዘብ ጠያቂ የሆነ ሰው ስለ ውርሱ አከፋፈል ትዕዛዝ እንዲሰጥለት የጠየቀ እንደሆነ የውርስ ክፍያ ዳኛ ማጽደቁ የግድ አስፈላጊ መሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1080 እና 1081 ተደግጓል፡፡

የኢትዮጲያ የውርስ ህግ በመሰረታዊ መርህነት የውርስ ክፍያው ወራሾቹ በሚያደርጉት ስምምነት መሆን እንዳለበት ይገልጻል፡፡ ወራሾች ያልተስማሙ እንደሆነ አንደኛው ወራሽ የክፉፉሉን አሰራር ካረቀቀ በኋላ በፍርድ ቤት እንዲጸድቅለት ማቅረብ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ሆኖም በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች የመከፋፈሉን አሰራር ዳኞች ካላጸደቁት በቀር ፈራሽ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ የመጀመሪያው ከወራሾቹ አንዱ ሳይኖር የቀረ እንደሆነ ወይም ወኪል ያልተወከለ እንደሆነ ሲሆን ሁለተኛው ከጋራ ወራሾች መሀከል የውርስ ኃብት ከመከፈሉ በፊት የአንደኛው ወራሽ ገንዘብ ጠያቂ የሆነ ሰው ስለ ውርሱ አከፋፈል ትዕዛዝ እንዲሰጥለት የጠየቀ እንደሆነ የውርስ ክፍያ ዳኛ ማጽደቁ የግድ አስፈላጊ መሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1080 እና 1081 ተደግጓል፡፡

የውርስ ንብረት ክፍፍል በፍርድ ቤት ውሳኔ ከተከፋፈለ በኋላ በክፍፍል ውስጥ ያልተካተተ አዲስ ንብረት የተገኘ እንደሆነ ወራሽ የሆነ ወገን አቤቱታውን ለፍርድ ቤት ቢያቀረብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 216(3) መሰረት የክስ ምክንያቶችን በመነጣጠል በሚል መቃወሚያ ጥያቄው ውድቅ ሊደረግ እገባም፡፡

የወራሾች የጋራ ኃብት የሆነ ቤት ከወራሾች በአንደኛው ብቻ ለሶስተኛ ወገን በሽያጭ ቢተላለፍ በሽያጩ ተሳታፊ ያልሆኑት ወራሾች የሽያጭ ውሉ ላይ በፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበው ሊፈርስ የሚችልበትን የህግ አግባብ በማስረዳት ከማስፈረስ በስተቀረ ውሉ ጸንቶ ባለበት ገዥው ቤቱን ለቅቆ ሊያስረክበን ይገባል በማለት የሚያቀርቡት ክስ የህግ መሰረት የሌለው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በደርግ ዘመን አዋጅ ቁጥር 47/67 ተግባራዊ በሆነበት ወቅት ያላግባብ የተወረሱ...
ጠበቃ በጋብቻ ፍቺ ሂደት ስለሚኖረው የሙያ ወሰን እና የሰበር ተቃርኖ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 24 April 2024