Font size: +
7 minutes reading time (1485 words)

ዘመን ሲለወጥ ያልተለወጡት ድንጋጌዎች

ሕግና ኅብረተሰብ ጠንካራ ቁርኝት አላቸው፡፡ ኅብረተሰብ በሌለበት ሕግን ማሰብ፣ ሕግ በሌለበት በሥርዓት የሚኖር ኅብረተሰብን ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ ግንኙነት አንዳንድ ጊዜ በመቀዳደም ሊፈጸም ይችላል፡፡ ሕግ ኅብረተሰብን ዘመናዊ ለማድረግና ለመለወጥ እንደ መሳሪያነት ሊያገለግል ይችላል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ጊዜ የሕጉ ዓላማ ኅብረተሰቡ ያልደረሰበትን ለውጥ ማስገኘት ነው፡፡ በተቃራኒው ከኅብረተሰቡ የሚወጡ እሴቶችና ባህሎችን ወደ ሕግ ደረጃ በማሳደግም የኅብረተሰቡን ሕልውና ማስቀጠል ይቻላል፡፡ እነዚህ የተሳሰሩ ግንኙነቶች ኅብረተሰቡ ከሕግ መጠቀም የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያሰፋ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በሆነ መልኩ ሕጉ ከኅብረተሰቡ ዕድገት ወደ ጓላ ከቀረ ሕጉ ከወረቀት ያለፈ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ ይህን ችግር በአገራችን የተወሰኑ ሕግጋት እናስተውለዋለን፡፡

የፍትሐ ብሔር ሕጋችንን ጨምሮ አገራችን በአሁኑ ወቅት የምትጠቀምባቸው ሕግጋት በ1950ዎቹ ከውጭ አገሮች በተወሰነ ማሻሻያ የገቡ ናቸው፡፡ ሕግጋቱ በጊዜው ሲወጡ አፄው የነበራቸው ዓላማ አገሪቱን ዘመናዊ ሕግጋት ከሚከተሉ አገሮች ማመሳሰል ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ሕግጋት ለአገሪቱ ባህል ሰፊ ቦታ አልሰጡም በሚል ትችት የሚቀርብባቸው ቢሆንም፣ አገሪቱን ላለፉት 50 ዓመታት በማስተዳደር ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች አብዛኛዎቹ አሁንም ድረስ የአገሪቱ ዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ለመምራት በቂ ቢሆኑም የተወሰኑት ድንጋጌዎች ከኅብረተሰቡ ባህል፣ ወግና ዘመናዊ አስተሳሰብ ጋር የማይጣጣሙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ባለፉት አሥር ዓመታት የተሻሻሉ አሉ፡፡ በዚህ ረገድ የቤተሰብ ሕጉ፣ የወንጀል ሕጉ፣ የመሬት ሕግ፣ የማኅበራት ሕግ ወዘተ. በዘመናዊ አስተሳሰብ በመቃኘት እንዲሻሻሉ ተደርገዋል፡፡ እስካሁንም ድረስ ግን ያልተሸሻሉና ዘመን ሲለወጥ የማይለወጡ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች ሕጉ ላይ ከመኖራቸው በቀር በኅብረተሰቡ የማይታወቁ፣ ሲገለጡ ባዕድ የሆኑ፣ በፍርድ ቤት መብት የማይጠየቅባቸው ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የፍትሐ ብሔር ሕጉን የተወሰኑ ድንጋጌዎች ለማሳያነት በመጠቀም ድንጋጌዎቹ ያልተለወጡበትን ምክንያት፣ አለመለወጣቸው ያስከተለውን አንድምታና መፍትሔ ለመጠቆም ጥረት ይደረጋል፡፡

ያልተለወጡ ድንጋጌዎች ማሳያ

በፍትሐ ብሔር ሕጋችን በተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ከዘመኑ ጋር የማይሄዱ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ የተወሰኑትን ለመጥቀስ እንሞክር፡፡ ከመጀመሪያው የሕጉ መጽሐፍ ብንጀምር የስም ሕግ በአገራችን ከወረቀት ያለፈ ተፈጻሚነት የሌለው ባዕድ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው፡፡ ሕጉ ከአንቀጽ 23-46 የተቀመጠ ሲሆን ሕጉ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በሕዝቡም በባለሙያውም የማይፈጸም ነው፡፡ በስም ሕጋችን መሠረት ማንኛውም ሰው ሦስት ስሞች ሊኖሩት ግድ ይላል፡፡ እነዚህም አንድ የቤተዘመድ ስምና አንድ ወይም ብዙ የግል ስሞችና የአባት ስም ይኖረዋል፡፡ በአስተዳደር ክፍል ጽሑፎች የግል ስሞችንና የአባቱን ስም በማስከተል በቤተዘመድ ስም እንደሚመለከት የፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 32 ተመልክቷል፡፡

የቤተዘመድ ስም በቤተሰቡ አንድና ወጥ ሲሆን ያለበቂ ምክንያት ሊለወጥ የማይችል ነው፡፡ የልጅ የቤተዘመድ ስም የአባት የቤተዘመድ ስም ነው፡፡ የግል ስም ግን በቁጥርም መብዛት የሚችልና እንደተፈለገም የሚሰረዝ ወይም የሚለወጥ ነው፡፡ ለልጅ የአባት ስም የሚሆነው የአባቱ የግል ስም ነው፡፡ አባቱ ባልታወቀ ጊዜ ሰውዬው የአባት ስም አይኖረውም፡፡

ይህ የፍትሐ ብሔር ሕጉ አቋም ነው፤ ድንጋጌዎቹ የተወሰዱት ከምዕራባውያኑ ሲሆን የአገራችንን ባህል ሳያገናዝብ በሕጉ እንዲካተት መደረጉ ላለመፈጸሙ ምክንያት ሆኗል፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2358/2359 መሠረት የፍትሐ ብሔር ሕጉ ከመጽናቱ በፊት የተወለደ ሰው የቤተዘመድ ስም እንዲኖረው አይገደድም፡፡ እንዲኖረው ከፈለገ የአባቱ ስም የቤተዘመድ ስም ይሆንለታል፡፡ ከሕጉ መጽናት በኋላ (ከመስከረም 1 ቀን 1953 ዓ.ም) የተወለደ ግን አንድ የቤተዘመድ ስም መያዝ ይኖርበታል፡፡ ሕጉ የቤተዘመድ ስም እንዲኖረው ሁሉንም ሰው የሚያስገድድ ቢሆንም፣ ሕጉ ሳይፈጸም 50 ዓመታትን አሳልፏል፡፡

የስም ሕጋችንንና በተግባር ሕዝቡ የሚከተለውን ሥርዓት ካስተዋልን የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳት እንችላለን፡፡ መጀመሪያ የቤተዘመድ ስም በሕዝባችን ዕውቅናም ተፈጻሚነትም የለውም፡፡ ሁለተኛው የግል ስምም ሆነ የአባት ስም አንድ ሲሆን፣ በአስተዳደራዊ አካል መጀመሪያ መጠሪያ የግል ስም ነው፡፡ የስም ሕጋችን ግን ብዙ የግል ስም የሚፈቅድ ሲሆን፣ የመጀመሪያ መጠሪያው የቤተዘመድ ስም ስለመሆኑ በግልጽ ተመልክቷል፡፡ በአገራችን ወጥ የስም አወጣጥና አጠራር ባህል ባይኖረንም በመደበኛው ሥርዓት የስም አጠራር ከግል ስም ወደ አባት ስም፣ አያት ስም በማለት የሚቀጥል ነው፡፡ ሦስተኛው በሕጉ አንድ ሰው ያለ አባት ስም በቤተዘመድ ስምና በግል ስም ብቻ ሊጠራበት የሚችልበት አጋጣሚ አለ፡፡ በተግባር ግን የአባት ስም የሌለው የግል ስም ዕውቅና እንደሌለው፣ የአያት ስምንም ካልጨመረ የፀና እንደማይሆን ይታሰባል፡፡ አራተኛው በፍርድ ቤቶች ያለው ተግባራዊ አፈጻጸም ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች በባህል ያለውን አጠራር በመቀጠል የስም ለውጥ ጉዳዮችን የሚያስተናግዱት የሕጉን ድንጋጌዎች በመጥቀስ ነው፡፡ ዳኞች ሕጉን መሠረት አድርገው የግል ስም እንዲለወጥ የሚፈቅዱት ስሙ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ያልተከለከለ (በቤተሰብ አባሉ ሌላ ሰው የማይጠራበት) መሆኑን በማረጋገጥ ነው፡፡ ሆኖም አንድ ሰው በብዙ የግል ስም መጠራቱ እንዲፀድቅለት ወደ ፍርድ ቤት ቢመጣ ዳኞች እንደማይቀበሉት የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ የሕጉና የተግባሩ ልዩነት ዳኞች በወጥነት ሕጉን እንዳያስፈጽሙ አድርጓቸዋል፡፡

ለሁለተኛ ማሳያነት ከውል ውጭ ሕጋችንን ሁለት ድንጋጌዎች እንጥቀስ፡፡ የመጀመሪያው ጌታው የለቀቀው እንስሳ ያደረሰውን ጉዳት ኃላፊነት በሚመለከት በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2074 የተደነገገው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የህሊና ጉዳት መጠንን በተመለከተ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2116 የተደነገገው ነው፡፡ በሕጉ መሠረት የሰው አገልጋይ የሆነ የቤት እንስሳ በሌላ ሰው ሀብት ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ የዚህ እንስሳ ባለቤት የሆነው ሰው እንስሳውን ጉዳት ላደረሰው ሰው የለቀቀ እንደሆነ ከኃላፊነት ለመዳን ይችላል፡፡ የቤት እንስሳት የሚባሉት ለመደሰት ወይም ከእነሱ ጥቅም ለማግኘት እንደተለመደው ሰው የሚያኖራቸው ስለመሆኑ ሕግ በግልጽ ደንግጓል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ ለመረዳት እንደሚቻለው አንድ የቤት እንስሳ (ለምሳሌ ውሻ) በጎረቤት ልጅ ላይ በንክሻ የአካል ጉዳት ቢያደርስበት፣ ባለቤቱ ውሻውን ጉዳት ለደረሰበት ሰው በመስጠት ከኃላፊነት ነፃ ይወጣል ማለት ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ዘመናዊነት የሚጎድለውና በድሮ ዘመን ለቤት እንስሳ ከሚሰጠው ከፍ ያለ ቦታ የሚመነጭ ነው፡፡ በውሻው ጉዳት የደረሰበት ሰው በብዙ ገንዘብ የሚተመን ወጪ ሊያስከትልበት የሚችልበት በመሆኑ እንስሳት በመልቀቅ የሚመለስ ኃላፊነት አይሆንም፡፡ ይህ ከሆነ ሰው ያስቸገረውን ውሻ በመስጠት የጠላውን ያስነክሳል፡፡

ሌላው ማሳያ ድንጋጌ ለህሊና ጉዳት የሚከፈለውን የገንዘብ መጠን የሚመለከት ነው፡፡ የህሊና ጉዳት ካሳ (Moral damage) በአንድ ሰው ድርጊት ምክንያት ለደረሰበት የስሜትና የመንፈስ ጉዳት በፍርድ ቤቶች የሚወሰን የካሳ ዓይነት ነው፡፡ የህሊና ካሳ በሕጉ በግልጽ በተመለከቱ ሁኔታዎች የሚከፈል ሲሆን፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2116(3) መሠረት የጉዳቱ ካሳው በማናቸውም ምክንያት ከአንድ ሺሕ የኢትዮጵያ ብር የበለጠ ሊሆን አይችልም፡፡ ማንም ሰው የህሊና ጉዳት ቢደሰርስበት (ሰውነቱ ያለአግባብ ቢያዝ፣ ስሙ ቢጠፋ፣ ቢታገድ፣ ሰው ቢሞትበት፣ ክብሩ ቢደፈር ወዘተ.) ሊከፈለው የሚችለው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን 1,000 ብር ብቻ ነው፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን ሕጉ በወጣበት ዘመን ከፍተኛ ነው ሊባል ቢችልም፣ በአሁኑ ጊዜ ግን በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ሕጉ የኅብረተሰቡን የሞራል ዋጋ ከ50 ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር በማስተካከሉ ላለመዘመኑ በቂ አስረጅ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶችም በተግባር የሞራል ካሳ ከ1,000 ብር የበለጠ ሲያስከፍሉ አያስተዋልም፡፡ በአንድ የቤተሰብ ጉዳይ ግን የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 10,000 ብር የሞራል (የህሊና ጉዳት) ካሳ መወሰኑን ጸሐፊው ያስታሳውል፡፡ በጉዳዩ ባል ከእርሱ የማትወለድ የሚስቱን ልጅ በመድፈሩ ምክንያት ጋብቻው በፍቺ የፈረሰ ሲሆን፣ ሚስት ለደረሰባት የህሊና ካሳ 10,000 ብር እንዲከፈላት ወስኗል፡፡ ፍርድ ቤቱ የገንዘብ መጠኑን ለማሻሻል የሰጠው ምክንያት የፍትሐ ብሔር ሕጉ ከወጣ በኋላ የቤተሰብ ሕጉ በተለየ የፖሊሲ አመክንዮ የተሻሻለ በመሆኑ በፍትሐ ብሔር ሕጉ የተቀጠውን መጠን መወሰን ፍትሐዊ አይሆንም በሚል ነው፡፡ በቤተሰብ ሕጉ ከሚኖረው ማኅበራዊና ሞራላዊ ትስስር አንፃር የፍርድ ቤቱ ዳኝነታዊ ንቁነት የሚደነቅ ቢሆንም፣ መጠኑን ያለምንም መስፈርት በዘፈቀደ መወሰኑ የሕግ አውጭውን ተክቶ እንዲሠራ አድርጎታልና ከትችት አያመልጥም፡፡ የቤተሰብ ሕግጋቱ ሲሻሻሉ ሕግ አውጪው የሞራል ካሳውን መጠን በገንዘብ መጠን ሳይወስን ዳኞች እንደጉዳዩ እንዲወስኑ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡ የደቡብ ክልል የቤተሰብ ሕግ ግን በባልና ሚስት መካከል ያለው የመከባበር፣ የመተጋገዝና የመተማመን ግዴታ ከተጣሰ እስከ ብር 10,000 ድረስ ካሳ ዳኞች ሊወስኑ እንደሚችሉ በሕጉ መቀመጡ የተሻለ ሕግ አድርጎታል፡፡ ዞሮ ዞሮ የተነሳንበት ነጥብ በፍትሐ ብሔር ሕጉ የህሊና ጉዳት ካሳ ብር 1,000 ተብሎ መወሰኑ ዘመኑን የማይዋጅና ሊለውጥ የሚገባ መሆኑን ነው፡፡ እነዚህን ድንጋጌዎች ለአብነት አነሳን እንጂ ሌሎች ዘመን ሲለወጥ ያልተለወጡ፤ ግን መለወጥ የሚገባቸው ድንጋጌዎች ብዙ አሉ፡፡

ያለመለወጣቸው አንድምታ

ዘመን ሲለወጥ መለወጥ ኖሮባቸው ያልተለወጡ ድንጋጌዎች ያስከተሉት አንድምታ አለ፡፡ ቀዳሚው ሕጉ ከኅብረተሰቡ ነባራዊ ሁኔታ እንዲርቅ ስለሚያደርገው ሕጉን የወረቀት ነብር ብቻ ያደርገዋል፡፡ ሕጉ ከባህሉ፣ ከዘመናዊነትም ጋር እንደማይሄድ እየታወቀ ስላልተሻረ የፀና ነው፡፡ ሰው እንዳይገለግልበት ደግሞ በባህርይው የተሻረ ያህል ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ድንጋጌዎችን (ለምሳሌ፡- የስም ሕግ ዓይነቶቹን) ባለመጠቀም ወይም ባለመተግበር የተሻሩ (Repealed by disuse) ይሏቸዋል፡፡ ሆኖም እንዲህ ዓይነት ትርጉም ሕጉ በግልጽ ባልተሻረበት ወይም የሚጣረስ ሌላ ሕግ ባልወጣበት ሁኔታ በሕግ ሙያ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ሕጉ ከኅብረተሰቡ ነባራዊ ሁኔታ መራቁ ተአማኝነቱም አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ ሌላው ድንጋጌዎቹ አለመለወጣቸው ለኅብረተሰቡ ባህልና አሁን ለሚከተለው ዘመናዊ አስተሳሰብ ሕጉ ቦታ እንደማያሰጣቸው አመላካች ነው፡፡ የስም ሕጋችን ከባህል ወይም ከልማዱ ጋር ያለው ፍቺ መስፋቱ፣ በእንስሳ ምክንያት የሚደርስ ጉዳትና የህሊና ጉዳት ካሳ ኋላ ቀር አስተሳሰብን መሠረት ማድረጉ ሕጉንም ኋላ ቀር እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የኅብረተሰቡ ሞራል አነስተኛ ቦታ እንደተሰጠው ቀጥሏል፡፡

ለምን አልተወጡም?

ዘመኑን የማይዋጁ ድንጋጌዎች በአገራችን ሳይለወጡ ለመቀጠላቸው የተለያዩ ምክንያቶች መስጠት ይቻላል፡፡ ቀዳሚው ሕግን በመጽሐፍ መልክ የማውጣት (Codification) አሉታዊ ባህርይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕግጋትን በቀላሉ መለወጥ አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙ ጥናት፣ ጊዜ፣ ባለሙያና ገንዘብ ይጠይቃል፡፡ የተወሰኑን ድንጋጌዎች በአዋጅ መልክ በማውጣት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ ሙሉውን አጥንቶ ለውጥ ማምጣት ጊዜ ፈጅ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የንግድ ሕጋችንና የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግጋትን እንደ ፍትሐ ብሔር ሕጉ ሁሉ እንዳረጁ ለዘመናት እየገዙን ቀጥለዋል፡፡ ስለዚህ በቂ ቦታ ካልተሰጠው ሙሉ ወጥ ሕግጋትን መቀየር አስቸጋሪ ነው፡፡ ሁለተኛውና ዋናው ምክንያት ግን የመንግሥት ቁርጠኝነት አለመኖር ነው፡፡ በአረጁ ሕግጋት የሚተዳደር ኅብረተሰብ ለዘለቄታው ልማት እንቅፋት እንደሚያጋጥመው ነጋሪ አያስፈልገውም፡፡ መንግሥት ያረጀ ሕግጋትን አጥንቶ ለመለወጥ ሰፊ ፕሮጀክት መንደፍ ይገባዋል፡፡ እስከአሁን የሕግ ሥርዓት ጥናትና ምርምር ተቋምና ፍትሕ ሚኒስቴር የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ቢገኙም፣ ከቤተሰብ ሕጉና ከወንጀል ሕጉ ባለፈ በሌሎቹ ሕግጋት ላይ የሚታይ ለውጥ አላሳዩም፡፡ ረቂቆች ይዘጋጃሉ፣ የምክክር ዓውደ ጥናት ይደረጋሉ፣ ረቂቆቹ ሕግ አውጭው ጋር እየደረሱ ይመለሳሉ ግን አሁንም አልተለወጡም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ትናንት ቢያልፍበትም ከነገ መዘግየት አይገባውም፡፡

እስከዚያው ምን ይደረግ?

ዘመናዊ ባልሆኑና ከሕዝቡ መንፈስ በራቁ ሕግጋት መተዳደር አስቸጋሪ ነው፡፡ ሕጉ ከባህሉ ከራቀ ሕዝባዊ አይሆንም፤ ከኅብረተሰቡ ዘመናዊነትም ከዘገየ ያረጀ መሆኑ አይቀርም፡፡ ከ50 ዓመታት በፊት ለተወሰኑት መፍትሔ መስጠት ይቻል ነበር፡፡ ያን ጊዜ የስም ሕጋችን ከአገራችን ሕዝቦች ባህል ቢመነጩ ኖሮ አሁንም የምንኮራባቸው፣ የሚፈጸሙም ይሆናሉ፡፡ ያን ጊዜ ግን አልሆነም፡፡ ምዕራባውያኑ በሕግ ውሰት (Legal Transplantation) ባህላቸውን ለማስረጽ በማሰብ ያደረጉት ጭፍን ዕርምጃ አልተሳካላቸውም፡፡ ሕግጋቱ ጠቃሚ ከሆኑና ወደ ኅብረተሰቡ ለማውረድ ቢታሰብም በጥናትና በምክክር ቢሠራ ውጤታማ ይሆን ነበር፡፡ ይህ መፍትሔ ለአሁን አይጠቅምም፡፡ በአሁኑ ወቅት መደረግ የሚገባው ሰፊ ጥናት ይመስለኛል፡፡ በአንድ በኩል በመጽሐፍ መልክ ለ50 ዓመታት ያሉንን ሕግጋት ክፍተት መፈተሸና መፍትሔ መጠቆም፡፡ በሌላ በኩል በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉት ባህላዊ፣ ልማዳዊና ሃይማኖታዊ ሕግጋትን በማጥናት ወደ ሕግ ደረጃ የሚያድጉበትን መፍትሔ ማፈላለግ ነው፡፡ አዲሱን የወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ማስቀመጥ ተገቢ አለመሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ አቁማዳው የወይን ጠጁን ጣዕምና ጥራት ያሳጣዋል፡፡ ስለዚህ አሁን ከምንከተለው ዘመናዊ ፖሊሲና አስተሳሰብ ጋር የሚሄዱ መርሆችና ሕግጋት ያስፈልጉናል፡፡ ይህን የማድረግ ዋናው ግዴታ ደግሞ የመንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ተገቢውን የተማረ የሰው ኃይልና ገንዘብ በመመደብ ሕግጋቱ ተጠንተው የሚቀየሩበትን ግልጽ አቅጣጫ አስቀምጦ መተግበር ይጠበቅበታል፡፡ ያልተለወጡት ሕግጋት ከኅብረተሰቡ ኑሮ፣ ነፃነት፣ መብትና ግዴታና የሚዛመዱ በመሆኑ ቸል ሊባል የሚገባው አይደለም፡፡ ዘመን ሲለወጥ፣ ያልተለወጡት ድንጋጌዎቻችም ተጠንተው እንዲለወጡ ማሰብ እንደሚገባ ልብ ማለት ይገባል፡፡

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የኮንስትራክሽን ዋስትና ምንነትና በተግባር የሚስተዋሉ የሕግ ክፍተቶች - ክፍል ...
ስለ “የታሰሩ ሰዎች መብቶች” አንዳንድ ነጥቦች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 08 November 2024