በደርግ ዘመን አዋጅ ቁጥር 47/67 ተግባራዊ በሆነበት ወቅት ያላግባብ የተወረሱ የግለሰብ ቤቶች አሁን ላይ ለግለሰቦቹ ወይም ለሕጋዊ ወራሾቻቸው ሊመለሱ የሚችሉበት የሕግ አግባብን በተመለከተ ከሰበር ውሳኔዎች ጋር ተገናዝቦ የቀረበ

የንጉሣዊ ሥርዓት መውደቁን ተከትሎ ወደ መንግሥታዊ ሥልጣን የመጣው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት የመንግሥት ንብረት ለማድረግ በሚል አዋጅ ቁጥር 47/1967 በማወጅ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ይህ አዋጅ ሊታወጅ ያቻለበት ዋነኛ መነሻ ምክንያት “በከተሞች ውስጥ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ቦታዎችና ቤቶች በጥቂት መሳፍንት፣ መኳንንትና በከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣኖችና ከበርቴዎች በመያዛቸው እንዲሁም የሀብታም ክፍሎች ያላቸውን ከፍተኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኃይል ያለ አግባብ በመጠቀም ሰው ሰራሽ የከተማ ቦታ እጥረት በመፍጠር የከተማ ቦታ ዋጋን እንዲወደድ በማድረግ በጠቅላላው የብዝበዛ ሥርዓት ጠንክሮ ለከተማው እድገትና ለብዙኃኑ የከተማ ነዋሪዎች የኑሮ መሻሻል ከፍተኛ እንቅፋት በመሆናቸው” በሚል አዋጁን መሠረት በማድረግ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት የመንግሥት ንብረት ሊሆን ችሏል፡፡

አዋጁ በከተማ ያሉ ትርፍ ቤቶችና የከተማ ቦታ በአብኛው የከበርቴው መደብ የያዛቸው ናቸው በሚል እሳቤ የመንግሥት እንዲሆኑ በሚልመንግሥት የሚወርስበትን የህግ ሥርዓት ያስቀመጠ ቢሆንም በወቅቱ አዋጁ ከሚያስቀምጠው መስፈርት ውጪ በዘፈቀደ የተወረሱ እና ለረጅም አመታት በመንግሥት እጅ ያላግባብ ተይዘው የሚገኙ የግለሰብ ቤቶች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ ከአዋጁ ውጪ ያላግባብ የተወረሱ ቤቶች ለግለሰቦች ሊመለሱ ስለሚችሉባቸው ሁኔታዎችን መነሻ በማድረግ በዚህ ጽሁፍ.. አንድ ቤት በመንግሥት በአዋጅ ተወረሰ ለማለት ምን ምን መስፈርቶችን ማሟላት አለበት? ያላግባብ ቤቴ ተወርሶብኛል የሚል ወገን ቤቱ እንዲመለስልት ክስ ለማቅረብ መብትና ጥቅሙን በምን አግባብ ሊያረጋግጥ ይገባል? እነዚህን ያላግባብ ተወርሰውብኛል የሚላቸውን ቤቶች በተመለከተ ይመለሱልኝ የሚል ክስ በፍርድ ቤት ሊቀርብ የሚችልበት የጊዜ ገደብ ይኖረው ይሆን? የሚሉ ነጥቦችን መሰረት በማድረግ ዳሰሳ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡

  • አንድ ቤት በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሰረት በመንግሥት ተወረሰ ለማለት ምን ምን መስፈርቶችን ማሟላት አለበት?

በአዋጁ አንቀጽ 11 መሰረት ግለሰቦች ከአንድ በላይ የከተማ ቤት በሚኖራቸው ወቅት ለመኖሪያ የሚመርጡትን ቤት እንዲመርጡ ይደረግና ቀሪው በመንግሥት የሚወረስ ይሆናል፡፡ ይህ የመምረጥና የመውረስ ስነ-ሥርዓት ሲከናወን በመንግሥት በኩል ቅጽ 003 ፣ቅጽ 004 በሚል የሚሞሉ ቅጾች አሉ፡፡ ቅጽ 003 የተወረሰው ቤት የትኛው እንደሆነ የሚያመላክት ሲሆን ቅጽ 004 ደግሞ ግለሰቡ በምርጫው ያስቀረው ቤት የትኛው እንደሆነ ያመላክታል፡፡ ስለዚህ በቅጽ 003 እና በቅጽ 004 የተወረሱ ቤቶች በቅጽ 008 የመንግሥት ቤት ተብለው ይመዘገባሉ፡፡ ቅጽ 008 ቤቱ በህጋዊ አግባብ ተወርሶ የመንግሥት መሆኑን የሚያስረዳ ሲሆን በዚሁ አግባብ በቅጽ 008 የተመዘገበውን ቤት የመንግሥት ሆኖ ለግለሰቦች በኪራይ የሚተላለፍ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ በቅጽ 003 እና 004 አግባብ የመውረስና የመምረጥ ሂደት ሳይከናወን በማናቸውም ሁኔታ ቤቱ በህጋዊ አግባብ የተወረሰ ነው ተብሎ በቅጽ 008 ላይ የመንግሥትት የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ሊመዘገብ አይችልም፡፡ እነዚህን አስገዳጅ ሂደቶች ሳያሟላ በቅጽ 008 ላይ የመንግሥት ቤት ነው በሚል ተመዝግቦ ቢሆን እንኳ በአዋጅ 47/67 አግባብ የተወረሰ መሆኑን ሰለማያስረዳመንግሥት በህገ ወጥ መንገድ ቤቶቹን እንደያዘ ይቆጠራል፡፡ በመንግሥት በአዋጅ የሚወረሰው ቤትም በወቅቱ የቤቱ ባለቤት የሆኑት ግለሰቦች የምርጫ ቤታችን ነው ብለው ለመኖሪያነት የመረጡት ቤት ሊሆን አይገባም፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መዝገብ ቁጥር 228002 በቀን መጋቢት 28/2015 ዓ.ም (ያልታተመ) በሰጠው የህግ ትርጓሜ ክርክር የቀረበበት ቤት በቅጽ 003 እና 004 አግባብ የማስመረጥና የመውረስ ሒደቱ በህጋዊ መንገድ መከናወኑን የሚያሳይ ማስረጃ በቅጾቹ ተሞልቶ ባልቀረበበት ሁኔታ ቤቱ በቅጽ 008 ላይ ብቻ የመንግሥት ተብሎ መመዝገቡ ቤቱን የመንግሥት ሊያስብል የሚያስችል ባለመሆኑ ለግለሰቦቹ ሊመለስ ይገባል በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ የህግ ትርጓሜ መገንዘብ የሚቻለው በደርግ ዘመን በአዋጅ ቁጥር 47/67 የተወረሱ ቤቶች በህጋዊ መንገድ በመንግሰት ተወርሰዋል ለማለት በቅጽ 003 እና 0004 ላይ ግለሰቦች ለመኖሪያነት የመረጡት ቤትናመንግሥት ትርፍ ነው በማለት የወረሰው ቤት ተለይቶ መመላካት አለበት፡፡ ይህ በሌለበት ሁኔታ ቤቱ በመንግሥት ስም በቅጽ 008 ላይ ተመዝግቦ መገኘቱ ቤቱን የመንግሥት ሊያስብለው አይችልም፡፡ ለግለሰቦች ሊመለስ ይገባል ማለት ነው፡፡

  • ከአዋጅ ውጪ ቤቴ ተወርሶብኛል የሚል ወገን ፍርድ ቤት አቤቱታ ለማቅረብ መብትና ጥቅሙን እንዴት ሊያረጋግጥ ይችላል?

ከአዋጅ 47/67 ውጪ በሆነ መንገድ የግለሰቦች ቤት በመንግሥት ተወርሰው ለረጅም አመታትመንግሥት እያስተዳደራቸው እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ቤቶች በተመለከተ አንዳንዴ የቤቱ ባለቤት የነበሩ ግለሰቦች አልፎ አልፎ ደግሞ የባለቤቱ ህጋዊ ወራሾች የሆኑት እንዲመለሱላቸው በሚል ቤቱን እያስተዳደረ የሚገኘውን የመንግሥት አካልና ከዚሁ አካል ተከራይ በመሆን ቤቱን ይዘው የሚገኙ ግለሰቦች ላይ የመፋለም ክስ ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መዝገብ ቁጥር 45161 በቅጽ 10 ላይ በሰጠው የህግ ትርጓሜ ግለሰቦች ለረጅም ጊዜ በመንግሥት ቁጥጥር ስር የሚገኝ ቤትን በማስመልከት የሚያቀርቡት ክስ ክርክር የቀረበበት ቤት በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሰረት የተፈቀደላቸው መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ ሊያቀርቡ ይገባል በሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በላይ በጠቀስኳቸው ቅጽ 003 እና 004 ላይ የሰፈሩ ማስረጃዎች በመንግሥት እጅ የሚገኘው ቤት የግለሰቡ የምርጫ ቤት መሆኑን የሚያስረዱ ከሆነ እነዚህን ማስረጃዎች በማቅረብና በማስቀረብ አልያም ቤቱ በማናቸውም አግባብ የግለሰቡ የምርጫ ቤት የነበረ መሆኑን ማስረዳት ከተቻለ ለረጅም አመታት በመንግሥት የተያዙ ቤቶች እንዲመለሱላቸው ግለሰቦች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33/2/ መሰረት ክስ ለማቅረብ መብትና ጥቀም ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡

  • ከአዋጅ ውጪ ቤቴ ተወርሷል ሊመለስልኝ ይገባል የሚል የመፋለም ክስ መቼ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

ከዚህ በላይ በጠቀስኩት አግባብ በመንግሥት ያለአግባብ የተያዙ በተለይም የግለሰቦች የምርጫ ቤታቸው የነበሩ ቤቶች እንዲመለሱ የሚል ክስ ለማቅረብ ቤቱ የምርጫ መሆኑን ካስረዱ መብትና ጥቅማቸውን ለማሳየት በቂ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ መብትና ጥቅማቸውን በዚህ አግባብ ካረጋገጡ ክሱ በምን ያህል ጊዜ ሊቀርብ ይገባል የሚለው በተለይም ቤቶቹ ለረጅም አመታት በመንግሥት እጅ ያሉ በመሆናቸው የይርጋ ጊዜ ያግዳቸዋል የሚል መቃወሚያ ሲነሳ ይችላል፡፡ ይህን መሰረት በማድረግ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መዝገብ ቁጥር 43600 በቅጽ 10 ላይ በሰጠው የህግ ትርጓሜ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1677፣1845፣1206፣1188፣1192 መሰረት በማድረግ የማይንቀሳቀስ ንብረት አስመልክቶ የሚቀርብ የመፋለም ክስ በይርጋ ቀሪ አይሆንም በሚል የህግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ ከአዋጅ ውጪ ያላግባብ ቤቴ ተወርሶብኛል በሚል የሚቀርቡ ክሶችም በተመለከተ ከዚህ በላይ በተሰጠው የሰበር ትርጓሜ መሰረት ምንም እንኳ በመንግሥት ለረጅም አመታት የተያዙ ቢሆንም ክስ ለማቅርብ የይርጋ ገደብ የሌለው መሆኑን በመጥቀስ ሰበር በመ/ቁ 228002 (ያልታተመ) ላይ የህግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡

ስለዚህ ከአዋጅ ቁጥር 47/67 ውጪ አዋጁ ተግባራዊ ሆኖ ባለበት ወቅት ያላግባብ ቤቴ ተወርሷል የሚል ወገን ክሱን በማንኛውም ጊዜ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት ሊያቀርብ ይችላል ማለት ነው፡፡

መደምደሚያ

የንጉሱ ሥርዓት ማብቃቱን መሰረት በማድረግ ወታደራዊው የደርግመንግሥት የከተማ ቦታንና ትርፍ ቤቶችን የግል ለማድረግ በሚል አዋጅ ቁጥር 47/67 በማወጅ ትርፍ የግለሰብ ቤቶችን ወርሷል፡፡ እነዚህን ቤቶች በሚወርስበት ወቅት ቅጽ 003 እና ቅጽ 004 በማለት የሚታወቁ ቅጾች ላይ የሚወረሱ ትርፍ ቤቶችንና በግለሰቦቹ ለመኖሪያነት የተመረጡ የምርጫ ቤቶችን ለይቶ አስፍሯል፡፡ በዚህ መልኩ ቤቶቹ ተለይተው ከተገለጹ በኋላ በቅጽ 008 ላይ ቤቶቹ በመንግሥት ስም የሚታወቁ መሆኑን በመጥቀስ ማህደር አደራጅቷል፡፡ ስለዚህ አንድ ቤት በህጋዊ መንገድ በአዋጅ ቁጥር 47/67 አግባብ በመንግሥት ተወርሷል ለማለትመንግሥት በቅጽ 003 እና 004 ላይ ግለሰቦቹን ለመኖሪያ ቤት ያስመረጠበትና ትርፉን ቤት በትርፍነት መዝግቦ የወረሰበት ማስረጃ በማቅረብ የማስረዳት ሸክሙን መወጣት ይኖርበታል፡፡ ይህን የማስረዳት ሸክሙን ሳይወጣ በቅጽ 008 ላይ ብቻ ቤቱ የመንግሥት ነው ተብሎ በመመዝቡ ቤቱ በህጋዊ መንገድ በመንግሥት ተወርሷ ለማለት አያስችልም፡፡

በአንጻሩ ግለሰቦች ከአዋጅ ውጪ በህገ ወጥ መንገድ ቤቴ ተወርሶብኛል በማለት ክስ ለማቅረብ በቤቱ ላይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33 መሰረት መብትና ጥቅም ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን መብትና ጥቅማቸውን የሚያረጋግጡት ደግሞ ቤቱ የምርጫ ቤታቸው መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ በማቅረብ ነው፡፡

ከዚህ በላይ በተገለጸው አኳን መብትና ጥቅማቸውን ማረጋገጥ የሚችሉ ግለሰቦች ምንም አይነት የይርጋ ገደብ ሳያግዳቸው ቤቱን እያስተዳደረ የሚገኘው የመንግሥት አካል ላይ ቀጥተኛ የሆነ የመፋለም ክስ በማቅረብ ቤታቸው እዲመለስላቸው ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ ክሱን የማቅረብ መብት የተሰጠው በቤቱ ቀጥተኛ ባለቤቶች ለነበሩት ብቻ ሳይሆን ለህጋዊ ወራሾቻቸውም ጭምር ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

አካለመጠን ባልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ የኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀ...
ከውርስ ኃብት ክፍፍል ጋር የተያያዙ አንዳንድ ነጥቦች ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤ...

Related Posts

 

Comments 1

Abebe
Guest - Mekdem on Wednesday, 04 October 2023 13:36

ይህ ውሳኔ መንግስት ከአዋጅ 47/67 ውጪ ያለምንም ምክንያትና የሰነድ ማስረጃ በእጁ ያስገባቸውን እና የሚያስተዳድራቸውን ቤቶች በተመለከተ የሚኖረው እንደምታ ምን ይሆን?

ይህ ውሳኔ መንግስት ከአዋጅ 47/67 ውጪ ያለምንም ምክንያትና የሰነድ ማስረጃ በእጁ ያስገባቸውን እና የሚያስተዳድራቸውን ቤቶች በተመለከተ የሚኖረው እንደምታ ምን ይሆን?
Already Registered? Login Here
Abebe
Sunday, 19 May 2024