Font size: +
9 minutes reading time (1791 words)

የሰበር ፍርድ ያለማክበር ልማድና ውጤቱ

ጸሐፊው በሚከታተለው አንድ የንግድ ችሎት ጉዳይ ጠበቃው የችሎቱን ዳኛ ያማርራል፡፡ የዳኛውን የችሎት አካሄድ እየተቸ በዕለቱ በሰጠው ፍርድ ጠበቃው ለጉዳዩ ጠቃሚ የሆነውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ የሕግ ትርጉም የችሎቱ ዳኛ በፍርዱ አለማካተቱ፣ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው መሆኑንና ይዘቱንም በፍርዱ ለማንፀባረቅ ፈቃደኛ አለመሆኑ እጅጉን አንገብግቦታል፡፡ እንደ ጠበቃው አነጋገር ‹‹ከሳሾች ባቀረቡት ክስ ለጉዳዩ አግባብነት ያለውን የሰበር ችሎት ቅጹን፣ የመዝገብ ቁጥሩንና ቀኑን አመልክተን አቀረብን፣ በቃል ክርክርም ይህንኑ በአጽንአት እንዲመዘገብልን አመለከትን፤›› ይላል፡፡ ውጤቱን ሲገልጽ ደግሞ ዳኛው በፍርዱ ሀተታውም ሆነ ትንታኔ የሰበር ችሎቱን ፍርድ አልገለጸም፣ የሰጠውም ፍርድ ሰበር ችሎቱ ከሰጠው አስገዳጅ ትርጓሜ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ በይግባኝ ከማሳረም ውጭ አማራጭ እንደሌለው ተናገረ፡፡ 

ከሰኔ 1997 .. ጀምሮ በአገራችን የሰበር ችሎት የሚሰጠው ትርጉም በሥር ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅ መሆኑ በሁሉም የሕግ ባለሙያዎች ዳኞችን ጨምሮ የታወቀ ነው፡፡ በተግባር ግን ጠበቃው የገጠመውን ዓይነት የፍርድ ቤቶች ልማድ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ አፈጻጸሙን በተመለከተ ግን አሁንም ያልጠሩ ወይም የማይፈጸሙ አሠራሮች መኖራቸውን የጠበቃው ተሞክሮ ያሳያል፡፡ ለመሆኑ የሥር ፍርድ ቤት ዳኞች የሰበር ሰሚ ችሎት የሰጣቸውን አስገዳጅ ፍርዶች ማወቅ (Judical notice መውሰድ) ይጠበቅባቸዋልን? የሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ፍርዶች ባልታተሙበት ሁኔታ አስገዳጅነት አላቸውን? አንድ የሥር ፍርድ ቤት ዳኛ የሰበር አስገዳጅ ፍርድ ተጠቅሶላት የማይቀበልበት ሁኔታ ይኖራልን? አስገዳጅ የሰበር ትርጉምን ወደ ጎን ማድረግ፣ አለመቀበል ወይም ከተሰጠው ትርጉም ተቃራኒ የሆነ ፍርድ መስጠት ዳኞችን በሥነ ምግባር አያስጠይቃቸውምን? የሚሉት ነጥቦች ምላሽ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ እነዚህን ነጥቦችና ከሰበር ችሎት ፍርድ አስገዳጅነት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት እንሞክራለን፡፡ 

አዋጅ ቁጥር 454/97 ዓላማውና ይዘቱ

ይህ አዋጅ በአንቀጽ 4 ላይ ‹‹የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ የፌዴራል ወይም የክልል ፍርድ ቤት ላይ አስገዳጅነት ይኖረዋል፡፡ ሆኖም የሰበር ችሎቱ በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ ጭብጥ የተለየ ትርጉም ሊሰጥ ይችላል፤›› ሲል ይደነግጋል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የሥር ፍርድ ቤቶች ሰበር ችሎቱ የሰጠውን የሕግ ትርጉም የመከተል፣ የመተግበር ግዴታ አለባቸው፡፡

ይህ አዋጅ በአገራችን አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ እንዲኖር የሚያደርግ በመሆን ደረጃ የመጀመርያ አለመሆኑን አንዳንድ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በንጉሡ ዘመን የታወጀው አዋጅ ቁጥር 195/55 በደርግ ዘመን የነበረው አዋጅ ቁጥር 9/1980 በሽግግር ወቅት የወጣው አዋጅ ቁጥር 40/85 ተመሳሳይ የሕግ ትርጉም በአገሪቱ እንዲኖሩ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ አዋጆቹ ተግባራዊ ባለመደረጋቸው፣ አልፎ አልፎም የትኛውን ፍርድ ቤት እንደሚያስገድዱ ግልጽ አለመሆናቸውም እንዲሁም የሰበር ትርጉሙ ከሕግ ጋር የሚጋጭ ቢሆን ሊኖረው የሚችለው ውጤት አለመገለጹ የታሰበውን አንድ ወጥ የሕግ አተረጓጎም ለማምጣት አላስቻለም፡፡

አዋጅ ቁጥር 454/97 ለምን ዓላማ እንደወጣ የሚገልጽ መግቢያ የለውም፡፡ ከዚህ የተነሳ በሕግ ባለሙያዎች ዘንድ ዓላማውን በየዓውዱ የተለያየ ትርጓሜ ሲሰጠው ይስተዋላል፡፡ የፌዴራል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ አለ መሐመድ አዋጁ ሲረቀቅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ያደረገውን ውይይት መነሻ በማድረግ አዋጁ በአገሪቱ ወጥ የሆነ የሕግ አተረጓጎም ለማስፈን ታልሞ የወጣ ስለመሆኑ ይገልጻሉ፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች በታተሙት የሰበር ፍርዶች ቅጾችም መግቢያ ላይም የሰበር ችሎቱ ሥልጣን በየፍርድ ቤቶች ለተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ይሰጥ የነበረውን የተለያዩ ውሳኔዎች በማስቀረት፣ የፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች ወጥነት እንዲኖራቸውና ተገማች እንዲሆን የማድረግ ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ይህ የአዋጁ ዓላማ በየዓውዱ የሚነገርና ብዙኃኑ የሕግ ባለሙያ የሚስማሙበት ነው፡፡

የሰበር ችሎቱ ፍርድ ባህርይም ላይ የሕግ ባለሙያዎች የተለያዩ አቋሞች ያንፀባርቃል፡፡ አንዳንድ ምሁራን አስገዳጅ ፍርዱ በኮመን ሎው የሕግ ሥርዓት እንደሚታወቀው ተመሳሳይ ጉዳዮችን ለመወሰን ምንጭና መሠረት (Stare decisis) ነው የሚል አቋም ሲያንፀባርቁ፣ ሌሎች ደግሞ ከሲቪል ሎው አገሮች የሕግ ሥርዓት ጋር የሚመሳሰል አንድ ወጥ የሕግ አተረጓጎም ለማስፈን ያለመ (Jurisprudence constante) ስለመሆኑ ይከራከራሉ፡፡ ከላይ ከተገለጸው ዓላማ አንፃር አሁን እየተተገበረ ያለው የሰበር ሥልጣን በኮመን ሎው የሕግ ሥርዓት እንደተለመደው ዳኛ ሠራሽ ሕግ ያለ ሳይሆን በሲቪል ሎው ከዳበረው ተመሳሳይ የሕግ ትርጉም ከማምጣት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ በዚህ ባህርይው ሰበር የሚሰጠው የሕግ ትርጓሜ በሥር ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅነት ያለው በመሆኑ እያንዳንዱ ዳኛ ወደ ጎን ሊለው፣ ሊተወው ወይም ሊሽረው የሚችል አይሆንም፡፡

የሰበር ትርጉምን በመተግበር የሥር ፍርድ ቤቶች ዳኞች ግዴታ

አዋጅ ቁጥር 454/97 በዳኞች ላይ ጠንካራ ግዴታ ይጥላል፡፡ በማንኛውም ደረጃ የሚገኝ የፌዴራልም ሆነ የክልል ፍርድ ቤት ዳኛ ሰበር ችሎቱ የሰጠውን የሕግ ትርጉም የመከተል ግዴታ አለበት፡፡ ዳኞች ይህንን ግዴታ ለመተግበር የቀረበላቸው ጉዳይ ሰበር ችሎቱ ከሰጠው የሕግ ትርጉም አንፃር መርምረው የሰበሩን ትርጓሜ ሥራ ላይ ማዋል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሰበር የሕግ ትርጉም ግልጽ ከሆነና ለጉዳዩ አግባብነት ካለው ዳኞቹ ትርጓሜውን ሥራ ላይ ከማዋል ውጭ ሌላ አማራጭ አይኖራቸውም፡፡ የሥር ፍርድ ቤቶች ሰበር ችሎቱ የሰጠው ፍርድ መሠረታዊ የሆነውን የሕግ ይዘት የሚቀይር፣ በእነርሱ ዕይታ ትክክል ያልሆነ ትርጉም ቢሆን እንኳን አዋጁ ትርጉሙን እንዲከተሉ ያስገድዳቸዋል፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ አሊ መሐመድ ሰበር ችሎቱ የሚሰጠው ገዥ ፍርድ ከሕግ ጥሬ ትርጉም ጋር የሚጋጭበት ሁኔታ እንኳን አስገዳጅ እንዳይሆን የሚያደርገው የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩን በመገንዘብ የሕጉን መሻሻል መፍትሔ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ዳኞች አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ከሕግ ጋር ቢጋጭ እንኳን ላለመፈጸም ምክንያት እንደማይኖራቸው ማሰብ ይቻላል፡፡ ማንኛውም ዳኛ የሰበር ፍርድ በተከራካሪዎች ተጠቅሶለት፣ ወይም የሰበር ፍርዱን እያወቀው ወይም ማወቅ እያለበት አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜን ወደ ጎን ማለትን የሕግ ሥርዓቱ አይፈቅድለትም፡፡  

የሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉምን ከመከተል አንፃር እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚነሳው አከራካሪ ነጥብ ዳኞች የሰበር ፍርዶችን እንዲያውቁ (Judical notice እንዲወስዱ) ይጠበቃል ወይ የሚለው ነው፡፡ እንደሚታወቀው በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ የወጣን የአገሪቱን ሕግ እንኳን ዳኞች ማንኛውም ዜጋ ያውቃል ተብሎ ነው ግምት የሚወሰደው፡፡ ለዳኞችማ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመርያን ማወቅ ከመብት ባለፈ የማወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ዳኞች ሕጉን አላውቀውም በሚል ግዴታቸውን ላለመፈጸም የሚቀርቡት መከላከያ በምንም ሁኔታ ተቀባይነት የለውም፡፡ ለሕግጋቱ ግልጽ የሆነው ዳኞች Judicial notice እንዲወስዱ የሚያስገድደው መርህ በሰበር ሰሚ አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ ላይ በተግባር አከራካሪ ሆኖ ይታያል፡፡ አንዳንዶች ዳኞች ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠው ፍርድ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በቅጽ መልክ ታትሞ ወጣ አልወጣ የእያንዳንዱን አስገዳጅ ትርጓሜ ይዘት የማወቅ ግዴታ አለባቸው ይላሉ፡፡ በተቃራኒው ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች የሰበር ሰሚ ችሎት የወሰናቸውን ፍርዶች ሁሉ ዳኞች እንዲያውቁ መጠበቅ ከባድ ኃላፊነት በመሆኑ፣ ዳኞች በጠቅላይ ፍርድ ቤት የታተሙትን  ገዥ ፍርዶች ብቻ ማወቅና መተግበር ይጠበቅባቸዋል ይላሉ፡፡ ሁለቱንም የሚያስማማው የጋራ ነጥብ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጣቸውንና በቅጽ መልክ ያሳተማቸውን የሕግ አስገዳጅ ትርጓሜዎች የሥር ፍርድ ቤቶች የማወቅና የመከተል ግዴታ ያለባቸው መሆኑን ነው፡፡ የዚህ ሁሉንም የሚያስማማ አቋም አንድምታ ዳኞች በያዙት ጉዳይ ላይ ጠቃሚ የሆነውን የታተመ የሰበር አስገዳጅ ትርጓሜ ያውቃሉ ተብሎ ግምት እንደሚወሰድ ነው፡፡ በታተሙት ፍርዶች አስገዳጅ ትርጓሜውን ተከራካሪዎች ለፍርድ ቤት ጠቅሰውት ወይም አቅርበውት አይደለም ባይጠቅሱት እንኳን የማወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ በክርክር ወቅት የሰበር ፍርዱን ከተቀሱማ የዳኛው ግዴታ ይቀልለታል፤ የተጠቀሰው ፍርድ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው ወይም የሌለው መሆኑን መርምሮ፤ አግባብነት ካለው ተፈጻሚ ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ 

ባልታተሙት የሰበር ፍርዶች ላይ የሥር ፍርድ ቤቶች ያለባቸውን ግዴታ ግን ከአዋጁ ይዘት በግልጽ መልስ ማግኘት ያስቸግራል፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 5 ‹‹የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የተሰጠባቸውን ውሳኔዎች በየደረጃው ላሉ ፍርድ ቤቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አሳትሞ ያሠራጫል፤›› ሲል ደንግጓል፡፡ ይህንን አንቀጽ ሲተረጉሙ አንዳንዶች ፍርዶቹ ካልታተሙና ካልተሠራጩ ዳኞችን አያስገድዱም የሚሉ ሲሆን፣ ሌሎቹ ግን አዋጁ የሰበር ፍርዶቹ ካልታተሙና ካልተሠራጩ በሥር ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅ እንደማይሆኑ የሚገልጽ ድንጋጌ ባለማካተቱ በአዋጁ አንቀጽ 4 መሠረት የሰበር ችሎት የሰጠውን የሕግ ትርጓሜ አስገዳጅነት መከተል ያለ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ የሥር ፍርድ ቤቶች ግዴታ ነው ይላሉ፡፡ 

የግራ ቀኙ ክርክር በነጠላ ለተመለከተው አሳማኝ የሚመስል ክፍል ቢኖረውም ከሁለቱ በአንዱ ጠርዝ ሆኖ ዳኞቹን መዳኘት ፍትሐዊ አይሆንም፡፡ በአንድ በኩል አዋጁ የሰበር ፍርዶቹን ማሳተምና ማሠራጨት ፍርዶቹን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ እንጂ ለአስገዳጅነቱ ቅድመ ሁኔታ ለማድረግ ያሰበ አይመስልም፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ተገኔ ጌታነህ በቅጽ 13 የሰበር ፍርዶች ሕትመት ላይ የሰበር ፍርድን የሕትመት ሥራ ተደራሽ ለማድረግ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለት ግዴታዎችን እንደሚተገብር ነው፡፡ የመጀመርያው በዓመት ሁለት ጊዜ ማተምና ማሠራጨት ሲሆን፣ ሁለተኛው ውሳኔዎቹ እንደተሰጡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት  ድረ ገጽ ማውጣት ነው፡፡ ይህ ንግግር የፍርዶቹ ሕትመትና ሥርጭት ፍርዶቹን ተደራሽ ለማድረግ እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡ 

በሌላ በኩል ግን የሥራ ፍርድ ቤቶች ሰበር ችሎቱ በየዕለቱ የሚሰጣቸውን ፍርዶች እንዲያውቁ የሕግ ግምት መውሰድ ሰው ለሆነ ዳኛ የማይቻል ነው፡፡ እንኳን ለሥር ፍርድ ቤት ዳኞች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሚያስችሉ ዳኞች የየዕለቱን የሰበር አስገዳጅ ፍርድ ለማወቅ የሚችሉበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜዎቹ ፍርድ በተሰጠበት ቀን ሁሉም ዳኛ እንዲያውቀው መጠበቅ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ የተሰጠውን ፍርድ ጋምቤላ አኮቦ ወረዳ ፍርድ ቤት ያለው ዳኛ እንዲያውቀው የመጠበቅ ያህል ከባድ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሕጉን መንፈስ የተከተለና ፍትኃዊ የሚሆነው አተረጓጎም ዳኞች ያልታተሙትን አስገዳጅ የሰበር ፍርዶች በፍርድ ቤቱ አስተዳደር በኦፊሴላዊ ደብዳቤ ወይም በጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረ ገጽ እንዲያውቁት ካልተደረገ ወይም ባለጉዳዮች በክርክር ሒደቱ አቅርበውላቸው እንዲገነዘቡት ካልተደረገ የተሰጠውን የሰበር ፍርድ ሁሉ እንዲያውቁ ማስገደድ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ አተረጓጎም የሰበር አስገዳጅ የሕግ አተረጓጎምንም ዋጋ አያሳጣም፤ ዳኞችም ላይ አምላካዊ ጠባይ እንዳላቸው አድርጎ ሁሉን ያልታተመ ፍርድ እንዲያውቁ ከባድ ግዴታም ከመጣል ይጠብቃል፡፡

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ያደረግነው ጉዳይ ግን አከራካሪ ያልሆነ ዳኞች ግዴታቸውን ያልተወጡበት መሆኑን መገንዘብ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ በጽሑፉ መጀመርያ ጠበቃው እንደተረከልን የታተመ የሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ዳኛው አላየሁም አልሰማሁም በሚል ዓይነት ብሂል በዝምታ አልፎታል፡፡ እንኳን ተከራካሪዎች ጠቅሰውለት ባይጠቅሱለት እንኳን ዳኛው የሰበር ችሎቱን አስገዳጅ ፍርድ አውቆ ሥራ ላይ ማዋል ይጠበቅበት ነበር፡፡ ለጉዳዩ አግባብነት የለውም የሚል ቢሆን እንኳን በፍርዱ ለምን አግባብነት እንደሌለው በመግለጽ ወደ ራሱ ትርጓሜ ማምራት በቻለ ነበር፡፡ ይህን አለማድረጉ በአዋጅ ቁጥር 454/97 በግልጽ የተቀመጠውን ግዴታውን እንዲጥስ አድርጎታል፡፡ 

ግዴታውን ያለማክበር ውጤት

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ በሆነው ጉዳይ ጠበቃው የሥር ፍርድ ቤቱን ስህተት በይግባኝ እንዲታረምለት መፈለጉ አንዱ አማራጭ ነው፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ጉዳዩን መርምሮ በሰበር ችሎቱ ፍርድ መሠረት ለጠበቃው ይፈርድለታል ወይም ይፈርድበታል፡፡ ከይግባኝም ውጭ ግን ልማዱን የሚያስቀር መፍትሔ እንዳለ ጸሐፊው ያምናል፡፡ የሥር ፍርድ ቤቶች በሆነ ባልሆነው የሰበር ችሎት አስገዳጅ ፍርድን ወደ ጎን የሚሉ ከሆነ አዋጁ የታለመለትን ግብ አይመታም፡፡ በፍርድ ቤት የሚሰጡ ፍርዶች አንድ ወጥ አተረጓጎም አይኖራቸውም፣ ፍርዶች ተገማቹ አይሆኑም፣ ይህ ደግሞ ሕዝቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለው መተማመን ፈጽሞ እንዲጠፋ ያደርገዋል፡፡

በሌላ በኩል የሥር ፍርድ ቤት ዳኞች ግልጽ የሰበር ችሎት አስገዳጅ ፍርዶችን በሥራ ላይ የማያውሉ ከሆነ እንደማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በሥነ ምግባር የሚያስጠይቃቸው ይሆናል፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ አሊ መሐመድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ባሳተመው ጆርናል ላይ ይህንን ሐሳብ በአጽንኦት ሲገልጹ ‹‹… የዳኝነት አካላት የሰበር ችሎቱ የሰጠውን የሕግ ትርጉም በተመሳሳይ ጉዳዮች የመከተል የሞራል ሳይሆን የሕግ ግዴታ ያለባቸው መሆኑን በመገንዘብ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል፤›› ይላሉ፡፡

የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት የዳኞችን ነፃነት ዋስትና የሚሰጠውን ያህል ተጠያቂነት እንዳለባቸውም ደንግጓል፡፡ በሕገ መንግሥት ከአንቀጽ 79 እስከ 81 በተደነገጉት አናቅጽ ዳኞች የተሰጣቸውን ነፃነት ያህል ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተደንግጓል፡፡ ከዳኞች ሥነ ምግባር አንፃር በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 81(6) በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ዳኞች የዲሲፕሊን ጉዳይ በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ እንደሚወሰን ግልጽ አድርጓል፡፡ 

ይህንን ተከትሎ በፌዴራል ደረጃ የወጣው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 24/1988 .. በአንቀጽ 9(4) 9(5) 9(6) እና በአንቀጽ 10 መሠረት ማንኛውም ሰው የዲሲፕሊንና የሥነ ምግባር ደንብን ተላልፎ በሚገኝ የፌዴራል ዳኛ ላይ ለጉባዔው አቤቱታ ማቅረብ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ከዚህ አንፃር ማንኛውም ባለጉዳይ በዳኞች ግልጽ ቸልተኝነት አስገዳጅ የሰበር የሕግ ትርጉምን ተግባራዊ ካላደረጉ በሥነ ምግባር እንዲጠየቁ ለዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አቤቱታ ማቅረብ ይችላል፡፡ 

የፌዴራል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን ጥር 16 ቀን 1993 .. የዳኞች ሥነ ምግባር ደንብን ያወጣ ሲሆን፣ በደንቡ አንቀጽ 4 ከተነሳንበት ጉዳይ ጋር አግባብነት ያለው ድንጋጌ ቀርጿል፡፡ አንቀጽ 4 ‹‹ሕጎችን በትክክል ሥራ ላይ ማዋል›› በሚል ርዕስ ‹‹በሚሰጠው ፍርድ፣ ውሳኔና ትዕዛዝ ሁሉ በአገሪቱ የወጡት ሕጎች በትክክል ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ የዳኛ ተቀዳሚ ተግባሩ ነው፤›› ሲል ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ዳኛ ሰበር ሰሚ ችሎት በአምስት ዳኞች የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በሥር ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅ ነው በሚል በሕግ (በአዋጅ ቁጠር 454/97) የተደነገገውን የሚጥስ ከሆነ የሥነ ምግባር ጥፋት ለመፈጸሙ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ የሰበር ችሎት የሕግ ትርጉም አስገዳጅ እንዲሆን ያደረገው ሕግ እንደመሆኑ መጠን የሰበር ችሎቱን ሥልጣን በመገዳደር አስገዳጅ ትርጓሜውን መተው፣ ወደ ጎን ማድረግ ወይም ከይዘቱ ጋር ተቃራኒ የሆነ ፍርድ መስጠት በሥነ ምግባር ተጠያቂ እንደሚያደርግ ሁሉም ሊረዳው የሚገባው ነጥብ ነው፡፡

የአዋጅ ቁጥር 454/97 ‹ከሌሎች አዋጆች ለየት የሚያደርገው በግልጽ በሥር ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅ ግዴታ መጣሉ ሲሆን፣ የግዴታው መከበር ወይም መጣስ አጠቃላይ በሕግ ሥርዓቱ ያለው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ አንዱ ዳኛ አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜውን አግልሎ ተጠያቂ የማይሆን ከሆነ ሌላኛውም ዳኛ የእርሱን ፈለግ የማይከተልበት አሳማኝ ምክንያት የለም፡፡ ድንጋጌውን አለማክበር በዳኞች መፈፀሙ ደግሞ የሕግ የበላይነትንና የዳኝነት አካሉን ሕገ መንግሥታዊ ተጠያቂነት ዋጋ የማያሳጣው ይሆናል፡፡ አዋጅ ቁጥር 454/97 ከነክፍተቱና ድክመቱ በሥር ፍርድ ቤቶች በአግባቡ እንዲከበር እያንዳንዱ ዳኛ፣ ፍርድ ቤቶችና የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የበኩላቸውን ዕርምጃ ካልወሰዱ የሕግ ትርጓሜ ወጥ መሆን፣ የሙግትና ፍርድ ተገማችነትና የሕዝበ አመኔታ መና ይቀራል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የልማድ አቤቱታ የፍርድ ጥራት ላይ ያለው ተፅዕኖ
በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት የቀዳሚ ምርመራ ድንጋጌዎችና አተገ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 24 July 2024