Font size: +
29 minutes reading time (5885 words)

በኢትዮጵያ ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰብ የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ አዙሪት ጥያቄዎችና መውሰብስቦች

በኢትዮጵያ የታክስ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የተጨማሪ እሴት ታክስ እና የተርን ኦቨር ታክስን በመጠቀም ከሕግ አገልግሎት ሽያጭ ላይ ታክስ እንደሁኔታው በፌዴራሉ እና በክልል መንግሥታት በመጣሉ በተግባርም እየተሰበሰበ ይገኛል። ይሁን እንጅ ይህ ታክስ ሕጋዊ መሠረቱን እና አግባብነቱን በተመለከተ፤ ከታክስ መሠረቱ፣ ከታክስ ምጣኔው እና ከአስተዳደር ሂደቱ ጋር ተያይዞ በርካታ አዙሪት ጥያቄዎችና መውሰብስቦች ይስተዋላሉ፡፡ የዚህ ጥናት ዓላማም አነዚህን አዙሪት ጥየቄዎችና መውሰብስቦች በዓይነታዊ የምርምር ዘዴ በማጥናት የመፍትሔ ኃሳብ መጠቆም ነው፡፡ ለዚህም ያስችል ዘንድ የተለያዩ መዛግብቶች፣ ቃለመጠይቆችና ቡድንተኮር ውይይቶች በግብዓትነት ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን  ለንፅፅር ይረዳ ዘንድ የሌሎች አገራት ተሞክሮንም ለመቃኘት ተሞከሯል፡፡ በዚህም መሠረት ጥናቱ ባለሶስት አማራጭ የመፍትሔ ኃሳብ ያቀረበ ሲሆን የመጀመሪያው አሁን ከሕግ አገልግሎት በአገሪቱ እየተሰበሰበ ያለውን የሽያጭ ታክስ እንዳለ በማስቀጠል ለፍትሕ ተደራሽነትና ለሕገመንግስታዊ መብቶች መከበር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መወሰድ ያለባቸውን ርምጃዎች አመላክቷል፡፡

በሌላኛው የአማራጭ መፍትሔ ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰበውን የሽያጭ ታክስ ሙሉ በሙሉ በማስቀረት ሌሎች አማራጭ የገቢ ምንጮችን መጠቀም እንደሚቻል ጠቁሟል፡፡ የመጨረሻው የመፍትሔ ኃሳብ ደግሞ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ስልት በመቀየስ ለሕግ አገልገሎት ራሱን የቻለ አዲስ ሠንጠረዥ ማዘጋጀትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ለዚህም ያግዝ ዘንድ የሕግ አገልግሎቶችን አስፈላጊነትና በሕገመንግስት ጥበቃ ከተደረገላቸው መብቶች ጋር ያላቸውን ቁርኝት፣ የሕግ አገልግሎት ተጠቃሚውን የመክፈል አቅምና የመንግስትን የገቢ ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ በሠንጠረዥ በመከፋፈል በተለያዩ የታክስ ምጣኔዎች የሽያጭ ታክስ እንዲሰበሰብ የሚመክር ነው፡፡

 መግቢያ 

ተመራማሪውን ለዚህ ጥናት ያነሣሣው በአማራ ክልል የጠበቆች ማኅበር አቤቱታ አቅራቢነት ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት (ከዚህ በኋላ አብክመ) የሕገመንግስት ጉዳዬች አጣሪ ጉባኤ የቀረበው አቤቱታ ነው፡፡ አቤቱታው በምንም መልኩ ቢወሰን ውሳኔው የመጨረሻ የሚሆነው በክልሉ ብቻ ስለሆነ ጥያቄው ለወደፊቱ በሌሎች ክልሎችና በፌዴራል ደረጃ ለፌዴሬሽን ምክርቤትና ሌሎች ተቋማት ሊቀርብ የሚችል በመሆኑ ጉዳዩ ላይ ከወዲሁ ጥናት ማድረጉ አስፈላጊ ነው፡፡

የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታት በሕገመንግስቱ የተሰጧቸውንና ሌሎች ግዴታዎችን በመወጣት አንድን አገር ወይም ክልል ለማስተዳደር ብሎም የሕዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር ከፍተኛ የሆኑ ወጭዎችን ማውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ወጭ (Public Expenditure) ደግሞ የሚሸፈነው በዋናነት በመንግስት በልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከሚደረጉ ኢኮኖሚነክ እንቅስቃሴዎች ከሚሰበሰብ ግብር ነው፡፡ ለነዚህና ለሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዓላማዎች የሚሰበሰቡት ግብሮችም ቀጥታ ግብር (Direct Tax) እና ቀጥተኛ ያልሆነ ታክስ (Indirect Tax) ይባላሉ፡፡ ቀጥታ ግብር የሚባሉት ግብሩን የከፈለው ሰው እስከመጨረሻው ራሱ የሚወጣው ሆኖ ከሌሎች ሰዎች መልሶ መተካት የማይችለውና ማስተላለፍ (Shift of Burden) የሌለበት የግብር ዓይነቶች ሲሆኑ እንደገቢ ግብር፣ ንብረት ግብር፣ የውርስ ግብርና የመሳሰሉት በዚሁ በቀጥታ ግብር ምድብ ውስጥ እንደአብነት የሚነሱ ናቸው፡፡ ቀጥታ ያልሆኑ የታክስ ዓይነቶች ደግሞ የመጨረሻ ኃላፊነቱ የሚወድቀው ታክሱን ለመንግስት የሚከፍለው ሰው ላይ ሳይሆን ሌሎች ሰዎች ላይ ነው፡፡ ይህም ማለት ለመንግስት ታክሱን ገቢ ያደረገው ሰው ታክሱን የሚከፍለው ከራሱ ካዝና ሳይሆን ከሌሎች ሰዎች በመሰብሰብ ወይም ከራሱ ካዝና የከፈለውን ታክስ ደግሞ የአቅርቦቱ ዋጋ ላይ በመጨመር ወደተጠቃሚው በማስተላለፍ ነው፡፡ የነዚህ የታክስ ዓይነቶችን በተመለከተ እንደዋና ምሳሌነት የሚጠቀሱት የሽያጭ ታክስ፣ የኤክሣይዝ ታክስና ቀረጥ ናቸው፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የታክስ ታሪክ ስንመለስም የሽያጭ ታክስ ከንጉሱ ስርዓት ጀምሮ በዘመነ ደርግና በሽግግር መንግስቱ ወቅትም ሲሰበሰብ የኖረና ከነሐሴ 15 1987 . ጀምሮ ተፈፃሚ በሆነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ከዚህ በኋላ ኢፌዴሪ) ሕገመንግስትም እውቅና ተሰጥቶት እንደሁኔታው በፌዴራሉና በክልል መንግስታት የሚጣልና የሚሰበሰብ መሆኑን ከኢፌዲሪ ሕገመንግስት መገንዘብ ይቻላል፡፡

ከታህሳስ 23 1995 . ጀምሮ የሽያጭ ታክስን በዘመነ መልክ ለማስተዳደርና በተግባር ላይ የነበረው የሽያጭ ታክስ ተደራራቢ ግብር የማስከፈል ውጤት (Cascading Effect) ያለውና ሌሎች ውስንነቶች የነበሩበት በመሆኑ ተጨማሪ እሴት ታክስ ተርን ኦቨር ታክስእንዲተካ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚሰበሰበው ዓመታዊ ሽያጫቸው ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ የዕቃ ወይም የአገልግሎት (የሕግ አገልግሎትን ጨምሮ) አቅራቢዎች በሚያደርጉት አቅርቦት ላይ ሲሆን የማስከፈያ ምጣኔውም 15% እና 0% መሆኑን ከተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 7 መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የሆኑ ግብይቶች ደግሞ በአንቀጽ 8 ላይ ተዘርዝረዋል፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስን መጣልና መሰብሰብ የፌዴራል መንግስቱ ስልጣን እንዲሆን በኢፌዴሪ ሕገመንግሰት አንቀፅ 99 መሠረት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤትና በፌዴሬሽን ምክርቤት ጣምራ ጉባዔ ተወስኗል፡፡ በተመሳሳይ ዓመታዊ የሽያጭ መጠናቸው ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ የሆኑት ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ እየሰበሰቡ ዓመታዊ ሽያጫቸው ከአንድ ሚሊየን ብር በታች የሆኑትን ነፃ ማድረግ ገበያውን ለውድድር ያልተመቸና ኢፍትሓዊ የሚያደርግ በመሆኑ እንደሁኔታው የፌዴራሉና የክልል መንግስታት ዓመታዊ ሽያጫቸው ከአንድ ሚሊየን ብር በታች የሆኑ አቅራቢዎች (የሕግ አገልግሎትን ጨምሮ) ላይ የተርን ኦቨር ታክስ እንዲሰበስቡ ተደርጓል፡፡

የሌሎች አገራት ተሞክሮን በተመለከተ የሽያጭ ታክስ በተለያዩ ዓይነቶች ተቀርጾ እናገኘዋለን፡፡ በአብዛኛው የዓለማችን አገራትየተጨማሪ እሴት ታክስበመሰብሰብ ይታወቃሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር የአውሮፓ ህብረትና የገልፍ ትብብር ጉባኤ አባል አገራት አንድ ተቀናጀየተጨማሪ እሴት ታክስ አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት ችለዋል፡፡ በሌላ በኩል እንደአውስትራሊያ፣ ኒውዝላንድ፣ ካናዳና ህንድ ያሉ "ኮመን" ሕግ ስርዓት (Common Law Legal System) የሚከተሉ አገሮችየዕቃና አገልግሎት ታክስ” (Goods and Services Tax) የሚለውን የሽያጭ ታክስ ዓይነት ይጠቀማሉ፡፡ ኩራካኦ (Curacao) እና ሱሪኔም (Suriname) የተርን ኦቨር ታክስ የሚለውን ማለትም “Omzetbelasting” አገር በቀል የሽያጭ ታክስ ዓይነት ሲጠቀሙ ጃፓንና ጆርዳን ደግሞ እንደየቅደምተከተላቸውየፍጆታ ታክስንጠቅላላ ሽያጭ ታክስ ይጠቀማሉ፡፡ ፒወርቶ ሪኮ ደግሞ “Sales and Use Tax” የምትሰበስብ ሲሆን 45 የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ይህንኑ በመሰብሰብ ይታወቃሉ፡፡

በአጠቃላይ የዚህ ጥናት ዓብይ ዓላማ በኢትዮጵያ ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰበውን የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ በተመለከተ ከሕጋዊ መሠረቱና አግባብነቱ ጋር ተያይዞ፤ የታክስ መሠረቱን፣ ምጣኔውንና የአስተዳደር ሂደቱን በተመለከተ የሚስተዋሉ አሻሚ ጉዳዮችንና ውስብስብነቶችን መመርመር ሲሆን ለዚህም ያስችል ዘንድ ዓይነታዊ (Qualitative) የምርምር ዘዴን በመከተል የተለያዩ መዛግብቶች፣ ቃለ መጠይቆች እና ቡድን ተኮር ውይይቶች በግብዓትነት ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ በተጨማሪም ለንፅፅር ይረዳ ዘንድ የሌሎች አገራት ተሞክሮንም ለመቃኘት ተሞከሯል፡፡

የጥናቱን አደረጃጀት በተመለከተ በመጀመሪያው ክፍል በአገራችን ከሕግ አገልግሎት የሽያጭ ታክስ ለመሰበሰብ ያለውን ሕጋዊ መሠረትና ተግባር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች ይተነተናሉ፡፡ በቀጣዩ ክፍልም የታክሶቹ ሕገመንግስታዊነት ይዳሰሳል፡፡ በሶስተኛው ክፍል ደግሞ የሌሎች አገራት ከሕግ አገልግሎት የሚሰበስቡት የሽያጭ ታክስ የሚተነተን ሲሆን በአራተኛው ክፍል በአገራችን ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰብ የሽያጭ ታክስ አግባብነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችን እናጠናለን፡፡ በመጨረሻም መደምደሚያና የመፍትሔ ኃሳቦችን የምናይ ይሆናል፡፡

 1. በኢትዮጵያ ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰብ የሽያጭ ታክስና ሕጋዊ መሠረቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች

በዚህ ክፍል ለማየት የተሞከረው በፌዴራል መንግስቱና በአራት የክልል መንግስታት ያለውን የሽያጭ ታክስ አስተዳደር ሕጋዊ መሠረት ነው፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰቡት የተጨማሪ እሴት ታክስንና የተርን ኦቨር ታክስን የታክስ መሠረት፣ ምጣኔንና አስተዳደሩን የተመለከቱ ጥየቄዎችና መውሰብስቦች ይጠናሉ፡፡ ሕገመንግስታዊነቱን በተመለከተ በሌላ ክፍል ስለሚሸፈን የዚህ ክፍል ከሕገመንግስት በታች ባሉ የሽያጭ ታክስ ሕጎች ላይ ብቻ ያተኮረ ነው፡፡ 

1.1 በፌዴራል መንግስቱ ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰቡ የሽያጭ ታክሶችና ሕጋዊ መሠረትን የሚመለከቱ ውዝግቦች 

1.1.1 ከሕግ አገልግሎት ስለሚሰበሰብ የተጨማሪ እሴት ታክስ 

በኢትዮጵያ በፌዴራል መንግስቱ የሚሰበሰቡ የሽያጭ ታክሶች ሁለት ዓይነት ማለትም የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ ሲሆኑ የተጨማሪ እሴት ታክስን በተመለከተ የፌዴራል መንግስቱ ስልጣን ብቻ እንዲሆን በፌዴሬሽን ምክርቤትና በህዝብ ተወካዬች ምክርቤት ጣምራጉባዔ በኢፌዲሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 99 መሠረት ስለተወሰነ17 የፌዴራል መንግስቱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994፣ የሚኒስትሮች ምክርቤት የተጨማሪ እሴት ታክስ ደንብ ቁጥር 79/1995 እና ማሻሻያዎችን መሠረት በማድረግ የተጨማሪ እሴት ታክስ በሁሉም የአገሪቱ ግዛቶች ላይ ጥሏል፡፡ ይህ ታክስም እየተሰበሰበ ያለው ዓመታዊ ሽያጫቸው ከአንድ ሚለዮን ብር በላይ በሆኑ የዕቃና አገልግሎት አቅራቢዎች በሚከናወኑ ሽያጮች ላይ ሲሆን21 የፌዴራል መንግስቱ የክልል ገቢዎችን በክልላቸው ውስጥ የሚገኙ ተመዝጋቢዎች ላይ ከመስከረም 1፣ 1997 ዓ.ም ጀምሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲሰበስቡ ውክልና ሰጥቷቸዋል፡፡ ይሁን እንጅ በአማራና በትግራይ ክልል እስካሁን ድረስ ዓመታዊ ሽያጫቸው ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ ጠበቆች ባለመገኘታቸው የውክልና ስልጣኑ በሕግ አገልግሎት ላይ አልተተገበረም፡፡ በኦሮሚያም ዓመታዊ ሽያጩ ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ የሆነ ጠበቃ አንድ ብቻ በመሆኑ በውክልና ሥልጣኑ መሠረት የተጨማሪ እሴት ታክስ ይሰበሰብበታል፡፡ የደቡብ ክልል ዓመታዊ ሽያጫቸው ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ ጠበቆች ላይ በውክልና የተጨማሪ እሴት ታክስ እየሰበሰበ ይገኛል፡፡

የተጨማሪ እሴት ታክስ መደበኛ ምጣኔን በተመለከተ በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ በግልፅ እንደተቀመጠው 15% በመሆኑ ዓመታዊ ሽያጫቸው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በሆኑ አቅራቢዎች የሚደረጉ የዕቃና አገልግሎት አቅርቦቶች በፌዴራል መንግስቱ 15% የተጨማሪ እሴት ታክስ ይሰበሰብባቸዋል ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ አዋጁ ካናዳና ህንድ ወይም የተርን ኦቨር ታክስ አዋጁ እንዳደረጉት የተለያዩ መደበኛ ምጣኔዎችን ከማስቀመጥ አልያም እንደፈረንሣይ ተሞክሮ የተቀነሰ ምጣኔ ከማካተት ይልቅ ወጥ 15% መደበኛ ምጣኔ ብቻ ማስቀመጡ የሕግ አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች ትኩረት የሚሹ አቅርቦቶች አላግባብ በአንድ መደበኛ ምጣኔ ውሰጥ እንዲታጨቁ ምክንያት ሆኗል፡፡

ከመደበኛ ምጣኔ በተጨማሪ በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅና በተጨማሪ እሴት ታክስ ደንብ መሠረት “ወደውጭ የሚላኩ ዕቃዎችና አገልግሎቶች፣ የዕቃዎች ወይም የመንገደኞች ዓለምአቀፍ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚቀርብ ወርቅና በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ድርጅትን መሸጥ” በዜሮ ምጣኔ የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚስተናገዱ በመሆናቸው ምክንያት ምንም ዓይነት የሽያጭ ታክስ የማይሰበሰብባቸው ሲሆን ከዚህ በፊት የተከፈሉ የግብዓት ታክሶች ካሉ ለአቅራቢው ተመላሽ ይሆናሉ፡፡ የዜሮ ምጣኔ የተጨማሪ እሴት ታክስን በተመለከተ የሕግ አገልግሎት በዚህ ስብስብ ውሰጥ ቢካተት ውጤቱ ምን ሊሆን ይችል ነበር? የሚለውን ማጤን ተገቢ ነው፡፡ የሕግ አገልግሎትን የዜሮ ምጣኔ አቅርቦት ማድረግ ትርፉ ለጠበቃው የሚኖረው የአስተዳደር ውስብስበነት ነው፡፡ ምክንያቱም አገልገሎቱን ለመስጠት ጠበቆች የሌሎች ተመዝጋቢ አቅርቦቶችን በግብዓትነት ከመጠቀም ይልቅ በአብዛኛው የሚጠቀሙት የራሳቸውን ዕውቀትና ክህሎት በመሆኑ ተመላሽ የሚደረጉ የግብዓት ታከሶች እምብዛም አይኖሯቸውም፡፡ ይሁን እንጅ ይህ ጉዳይ ከሕግ አገልግሎት ለሚሰበሰብ የተርን ኦቨር ታክስ እንደአጀንዳ ሊነሳ አይችልም፡፡ ምክንያቱም የተጨማሪ እሴት ታክስን ዓይነት የዜሮ ምጣኔ ጣጣ ዓመታዊ ገቢው ከአንድ ሚሊየን ብር በታች የሆነ ሰው ሊወጣው አይችልም ተብሎ ስለሚታሰብ በተርን ኦቨር ታክስ አስተዳደር ውስጥ የዜሮ ምጣኔ አቅርቦቶች አለመኖራቸው ነው፡፡ 

ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የተደረጉ ግብይቶችን በተመለከተ ደግሞ በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ እና በተጨማሪ እሴት ታክስ ደንብ እንተገለጸው፤  

•    ያገለገሉ መኖሪያ ቤቶች ሽያጭና ኪራይ፣
•    የፋይናንስ አገልግሎቶች፣
•    የህክምና አገልግሎቶችና በሀኪም የሚታዘዙ መድሀኒቶች፣
•    የትምህርት አገልግሎቶች፣
•    የፖስታ አገልግሎቶችና
•    የትራንስፖርት አገልግሎቶች ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ የዋስትና ሰነዶችን መሸጥ ወይም ማስገባት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚቀርብ ወርቅ ወደ አገር ማስገባት፣ የሃይማኖት ወይም ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ አቅርቦቶች፣ ለሰብዓዊ ዕርዳታ የሚውሉ አቅርቦቶች፣ በፋብሪካ ከታሸጉ ውጭ ያሉ የውሃ ሽያጮች፣ የኤሌክትሪክና የኬሮሲን አቅርቦቶች፣ መጻሕፍት፣ ፈቃድ ለማግኘት የሚፈፀሙ ክፍያዎችና ከ60% በላይ አካል ጉዳተኛ ተቀጣሪዎች ባሏቸው ድርጅቶች የሚደረጉ አቅርቦቶችም ይገኙበታል፡፡  

እዚህ ላይ የሕግ አገልግሎት ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ አለመደረጉን በተመለከተ የፍትሕን አስፈላጊነት ከላይ ካሉት መዘርዝሮች በተለይም ከመጠለያ፣ ፋይናንስ፣ ህክምናና ትምህርት አሰፈላጊነት ጋር ማነፃፀር ተገቢ ነው፡፡ በተጨማሪም ፍትሕ እነዚህን ፍላጎቶች ከማሟላት አኳያ የሚኖረው ሚናም ሊጤን ይገባል፡፡ 

ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰብ የተጨማሪ እሴት ታክስን በተመለከተ ከላይ እንደተገለጸው በተጨማሪ እሴት ታክስ ሕጎች ከታክስ ነፃ ያልተባለ ወይም ዜሮ ምጣኔ ውስጥ ያልተካተተ “አገልግሎት” በመሆኑ የሕግ ባለሙያው ዓመታዊ የገቢ መጠን ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ እስከሆነ ድረስ በመደበኛ ምጣኔ 15% የተጨማሪ እሴት ታክስ ይሰበሰብበታል፡፡ በተጨማሪም አገልግሎትን የሚተረጉመው የሕጉ ክፍል በግልጽ እንዳስቀመጠው “አገልግሎት” ማለት ‘የዕቃን ዝውውር የማይጨምር በክፍያ የሚከናወን ማናቸውም ተግባር ነው’ ሲል ሰፊ ትርጉም በመስጠት በፌዴራል ፍርድቤት ጠበቆች አዋጅ “የጠበቃ አገልገሎት” የተሰጠውን ፍቺ የሚያካትት ትርጉም ሰጥቶት እናገኛዋለን፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከነዚህ በግልፅ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ከተደረጉ ግብይቶች በተጨማሪ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር በሚያወጣው መመሪያ ሌሎች አቅርቦቶችም ነፃ እንዲሆኑ ሊፈቀድ እንደሚችል ከተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዚህም መረዳት የሚቻለው ምንም እንኳ አሁን ባለው የሕግ ስርዓት መሠረት የሕግ አገልግሎት 15% የተጨማሪ እሴት ታክስ የተጣለበትና በተግባርም እየተሰበሰበበት ያለ ቢሆንም በቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር በአሁኑ የገንዘብ ሚኒስትር አዋጁ ሳይነካ በመመሪያ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ሊደረግ የሚችልበት የሕግ አግባብ መኖሩን ነው፡፡ እዚህ ላይ ሌሎች ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች የገንዘብ ሚኒስትር የሕግ አገልግሎትን በዜሮ ምጣኔ ውስጥ ማስገባት አልያም የተቀነሰ የታክስ ምጣኔ መጣል ይችላል ወይ? የሚሉት ናቸው፡፡ የመጀመሪያውን ጥያቄ በተመለከተ የውክልና ስልጣኑ በግልጽ ያላካተተው ከመሆኑ በተጨማሪ ከተሰጠው ከታክስ ነፃ የማድረግ ስልጣን አልፎ የግብዓት ታክስን ተመላሽ የማድረግ ውጤት ስለሚኖረው የሕግ አገልግሎትን በመመሪያ ዜሮ ምጣኔ ውስጥ የምናስገባበት የሕግ ማሕቀፍ አለመኖሩን መረዳት አያዳግትም፡፡

በተጨማሪም የሕግ አገልግሎትን በዜሮ ምጣኔ ውስጥ ማካተት የሚኖረውን ጫና በተመለከተ ከዚህ በፊት የተሰጠውን ማብራሪያ መመልከት ተገቢ ነው፡፡ የሁለተኛውን ጥያቄ በተመለከተ የውክልና ስልጣኑ በግልጽ ያላካተተው ከመሆኑ ባሻገር የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ያልተከተለውን የተቀነሰ የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ የመጣል ተሞክሮ  በውክልና ለሕግ አገልግሎት ተግባራዊ ማድረግ የሚከብድ ነው፡፡   

1.1.2. በፌዴራል መንግስት ከሕግ አገልግሎት ስለሚሰበሰብ የተርን ኦቨር ታክስ  

ዓመታዊ ሽያጫቸው ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ አቅራቢዎች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ እየሰበሰቡ ዓመታዊ ሽያጫቸው ከአንድ ሚሊየን ብር በታች የሆኑ አቅራቢዎችን ከታክስ ነፃ ማድረግ የንግድ ሚዛንን የሚያዛንፍና ኢፍትሓዊ በመሆኑ ዓመታዊ ሽያጫቸው ከአንድ ሚሊየን ብር በታች የሆኑ አቅራቢዎች የሚያደርጓቸው አቅርቦቶች የተርን ኦቨር ታክስ ይሰበሰብባቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት በኢፌዴሪ ሕገመንግስት የፌዴራል መንግስቱ የሽያጭ ታክስ ስልጣን ባገኘባቸው ግብይቶች ላይ የተርን ኦቨር ታክስ እየሰበሰበ ይገኛል፡፡ ለዚህም ሕጋዊ መሠረቱ የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ ቁጥር 308/95 እና የተርን ኦቨር ታክስ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 611/2001 ናቸው፡፡ በመሆኑም በተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ እንደተገለጸው በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 7 ወይም አዋጁን መሠረት በማድረግ በወጣ መመሪያ ነፃ ካልተደረጉ በስተቀር ለተጨማሪ እሴት ታክስ ያልተመዘገቡ ሰዎች በአገር ውስጥ በሚያደርጓቸው አቅርቦቶች ላይ የተርን ኦቨር ታክስ ይከፈላል፡፡ በአዋጁ በአንቀጽ 4 እንደተገለጸውም የተርን ኦቨር ታክስ መደበኛ ምጣኔ በሚከተለው መጠን ማለትም፤  

•    በማናቸውም በአገር ውስጥ በሚሸጡ ዕቃዎች ላይ 2%፤
•    የሥራ ተቋራጮች፣ የዕህል ወፍጮቤቶች፣ የትራክተሮችና ኮምባይን ሀርቨስተሮች አገልግሎት 2%፤ እና
•    በሌሎች አገልግሎቶች 10% እንዲሰበሰብ ያስገድዳል፡፡

ከዚህም መረዳት የሚቻለው ከዕቃ የሚሰበሰበው የተርን ኦቨር ታክስ መደበኛ ምጣኔ አንድ ወጥ 2% መሆኑን ነው፡፡ ይሁን እንጅ የአገልግሎት የተርን ኦቨር ታክስ መደበኛ ምጣኔ ከተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጁ በተለየ ሁለት የተለያዩ ምጣኔዎችን ማለትም 2% እና 10% ምጣኔዎች ዕውቅና አግኝተዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው በተርን ኦቨር ታክስ ሕጉ የአገልግሎት አቅርቦቶች እንደአስፈላጊነታቸው በተለያየ ምጣኔ እንዲስተናገዱ የተደረገውን ጥረት ነው፡፡ ነገርግን የሕግ አገልግሎት 2% የተርን ኦቨር ታክስ ከሚሰበሰብባቸው የአገልግሎት ዝርዝር ውስጥ ባለመካተቱ 10% የተርን ኦቨር ታክስ እንዲሰበሰብበት ሕግ ያስገድዳል፡፡ ሆኖም የሕግ አገልግሎትን አስፈላጊነት 2% የተርን ኦቨር ታክስ ከሚሰበሰብባቸው የአገልግሎት ዝርዝር ማለትም የሥራ ተቋራጮች፣ የእህል ወፍጮቤቶች፣ የትራክተሮችና ኮምባይን ሀርቨስተሮች አገልግሎት አስፈላጊነት ጋር ማነፃፀር ተገቢ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለ“አገልግሎት” የተሰጠውን ትርጉም ስንመለከት እንደተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጁ “አገልግሎት” ማለት ‘የዕቃን ዝውውር የማይጨምር በክፍያ የሚከናወን ማናቸውም ተግባር ነው’ ሲል ሰፊ ትርጉም በመስጠት በፌዴራል ፍርድቤት ጠበቆች አዋጅ “የጠበቃ አገልገሎት” የተሰጠውን ፍቺ የሚያካትት ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ ሰለዚህ የፌዴራል መንግስቱ ዓመታዊ ገቢያቸው ከአንድ ሚሊየን ብር በታች የሆኑ የፌዴራል ጠበቆች የሚሰጡት አገልገሎት ላይ የሕግ ስርዓትን ተከትሎ 10% የተርን ኦቨር ታክስ በመጣል በተግባርም እየሰበሰበ ይገኛል፡፡

ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ የተደረጉ ግብይቶችን በተመለከተ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 7(1) በግልፅ የተዘረዘሩ ሲሆን ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ከተደረጉ ግብይቶች ጋር ምንም አይነት ልዩነት የሌለ በመሆኑ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ስለተደረጉ ግብይቶች የተሰጠውን ማብራሪያ መመልከት በቂ ነው፡፡ በዚሁ አንቀጽ የተዘረዘሩት ከታክስ ነፃ የመሆን መብቶች አፈፃፀም በገቢዎች ሚኒስትር በሚወጣ መመሪያ እንዲወሰን የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም እንደተጨማሪ እሴት ታክስ ሁሉ የገንዘብ ሚኒስትር በሚያወጣው መመሪያ ሌሎች ግብይቶችን ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ ሊያደርግ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ የገንዘብ ሚኒስትር የሕግ አገልግሎት ላይ የተቀነሰ የታክስ ምጣኔ ማለትም 2% መጣል ይችላል ወይ የሚለው ነው፡፡ ይህን በተመለከተ ሚኒሰትሩ የተሰጠው የውክልና ስልጣን ስለሆነ በግልጽ የተሰጠውን ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ የማድረግ የውክልና ስልጣን ብቻ ነው መተግበር ያለበት የሚል ሙግት ሊነሳ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ሙሉ ለሙሉ ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ ለማድረግ የውክልና ስልጣን ከተሰጠው በይበልጥ አመክንዮ ትርጉም የሕግ አገልግሎት ላይ የሚሰበሰበውን የተቀነሰ ምጣኔ ማለትም 2% የተርን ኦቨር ታክስ ለማድረግ የሚከብድ አይሆንም፡፡ ሆኖም ይህን ውዝግብ ለመፍታት ያስችል ዘንድ ውክልናው በግልጽ ተሰጥቶ ቢሆን መልካም ነበር፡፡ ስለዚህ ከሕግ አገልግሎት ላይ የሚሰበሰበውን የተርን ኦቨር ታክስ ቀሪ ለማድረግም ሆነ ለመቀነስ የግድ አዋጁን ማሻሻል አይጠይቅም፡፡ ሌላው በተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ የዜሮ ምጣኔ ታክስ አይታወቅም፡፡

1.2. በክልል መንግስታት ከሕግ አገልግሎት ስለሚሰበሰብ የሽያጭ ታከስና ሕጋዊ መሠረትን የሚመለከቱ ውዝግቦች 

በዚህ ክፍል የኦሮሚያ ክልል፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ የትግራይና የአማራ ብሔራዊ ክልል የሽያጭ ታክስ ተሞክሮ እንደየቅደምተከተላቸው ይዳሰሳል፡፡ በኢትዮጵያ የታክስ አስተዳደር ውስጥ የተጨማሪ እሴት ታክስ የመሰብሰብ ስልጣን ለፌዴራል መንግስት ብቻ የተሰጠ ስልጣን በመሆኑ የክልል መንግስታት በስልጣናቸው የሚሰበስቡት የሽያጭ ታክስ የተርን ኦቨር ታክስ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በአራቱም ክልሎች ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰበው የተርን ኦቨር ታክስ ይጠናል፡፡ ሌሎች ክልሎች ካለው የጊዜ ጥበት እና የክልሎቹ ሕጎች ተደራሽ አለመሆናቸው በጥናቱ እንዳይሸፈኑ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይሁን አንጅ ከአራቱ ክልሎች የተርን ኦቨር ታክስ አስተዳደርና ክልሎች ካላቸው የሕግ ተሞክሮ አንፃር በጥናቱ ያልተሸፈኑት ክልሎች ላይ የተለየ ነገር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ለዚህም ሌላኛው ማጠናከሪያ በአገሪቱ የተጣጣመ (Harmonized) የታክስ አስተዳደር ለመዘርጋት ያስችል ዘንድ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን  መዋቅር ውስጥ በሚገኘው የታክስ ስርዓት ማጣጣምና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

1.2.1. በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከሕግ አገልግሎት ስለሚሰበሰብ የተርን ኦቨር ታክስ 

በኦሮሚያ ክልል ዓመታዊ ሽያጫቸው ከአንድ ሚሊዮን ብር በታች የሆኑ ግለሰብ አቅራቢዎች ላይ የተርን ኦቨር ታክስ የሚሰበሰብ ሲሆን ሕጋዊ መሠረቱም በክልሉ መንግስት ምክርቤት ጠባቂነት የወጣው የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ እና ማሻሻያው ናቸው፡፡ አዋጁ በይዘትም ሆነ በቅርጽ ከፌዴራሉ የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ መሠረታዊ ልዩነት የሌለው ሲሆን፤

•    ማናቸውም በአገር ውስጥ የሚሸጡ ዕቃዎች ላይ 2%፣
•    በስራ ተቋራጮች፤ የዕህል ወፍጮ ቤቶች፣ የትራክተሮችና ኮምባይን ሀርቨስተሮች አገልግሎቶች 2%፣ እና
•    ሌሎች አገልግሎቶች 10% የተርን ኦቨር ታከስ ይሰበሰብባቸዋል፡፡

ለ“አገልግሎት” የተሰጠውን ትርጉም ስንመለከትም እንደ ፌዴራሉ ሁሉ “አገልግሎት” ማለት ‘የዕቃን ዝውውር የማይጨምር በክፍያ የሚከናወን ማናቸውም ተግባር ነው’ የሚል ሰፊ ትርጉም ነው፡፡ በአጠቃላይ በክልሉ ያለውን የሕግ ስርዓት በተከተለ መልኩ የሕግ አገልግሎት በመደበኛ የአገልግሎት ተርን ኦቨር ታክስ ምጣኔ 10% የተርን ኦቨር ታክስ ይሰበሰብበታል ማለት ነው፡፡ በተግባር ላይ ያለው የታክስ አስተዳደር ሂደትም የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡

በተጨማሪም በዚህ ክልል ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ የተደረጉ ግብይቶች በፌዴራል የተርን ኦቨር ታክስና የተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ከተባሉ ግብይቶች ጋር ፍፁም ተመሳሳይ በመሆናቸው መድገም አስፈላጊ አይደለም፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የክልሉ መስተዳደር ምክርቤት በሚያወጣው መመሪያ በሌሎች ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ የሚሰበሰብ የተርን ኦቨር ታክስ ቀሪ እንዲሆን ሊፈቅድ ይችላል፡፡ ከዚህም መረዳት የሚቻለው የሕግ አገልግሎት ምንም እንኳ  በክልሉ የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ ነፃ ያልተደረገ ቢሆንም የክልል መስተዳደር ምክር ቤት በሚያወጣው መመሪያ ቀሪ ሊያደርገው ወይም ወደ 2% ዝቅ ሊያደርገው እንደሚችል ነው፡፡ በተጨማሪም በዚሁ አዋጅ እንደተገለጸው በሕጉ የተዘረዘሩት ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ የመሆን መብቶች አፈፃፀም የኦሮሚያ የገንዘብና ልማት ቢሮ በሚያወጣው መመሪያ ይወሰናል፡፡

1.2.2. በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከጥብቅና ስለሚሰበሰብ የተርን ኦቨር ታክስ 

በዚህ ክልል የተርን ኦቨር ታክስ አስተዳደር በክልሉ የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ ቁጥር 57/9572 እና በክልሉ የተርን ኦቨር ታክስ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 134/05 የሚከናወን ሲሆን እንደኦሮሚያ ክልል የተርን ኦቨር ታክስ አስተዳደር ሁሉ የፌዴራሉን የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ ቁጥር 308/95 በቀጥታ በመውሰዱ ተመሳሳይ የሆነ መደበኛ ምጣኔና ከታክስ ነፃ አሰራር ስለሚከተል መድገም አስፈላጊ አይደለም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የክልሉ የተርን ኦቨር ታክስ መደበኛ ምጣኔ በአዋጅ ቁጥር 57/95 አንቀጽ 4 ላይ የተመለከተ ሲሆን አንቀጽ 7(1) ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ የተደረጉ ግብይቶችን ይዘረዝራል፡፡ በተጨማሪም ለአገልግሎት የተሰጠው ትርጉም ከዚህ በፊት እንዳየናቸው ሁሉ ሰፊና የሕግ አገልግሎትንም የሚጨምር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በመሆኑም የሕግ አገልግሎት በመደበኛ የአገልግሎት ተርን ኦቨር ታክስ ምጣኔ 10% ይሰበሰብበታል ማለት ነው፡፡ በክልሉ በተግባር ያለው የታክስ አስተዳደር ሂደትም የሚጠቁመው ይህንኑ ነው፡፡

ከታክስ ነፃ የመሆን መብቶች አፈፃፀም የክልሉ የገቢዎች ቢሮ በሚያወጣው መመሪያ የሚወሰን ሲሆን ሌሎች አቅርቦቶችን ከታክስ ነፃ የማለት ስልጣን ደግሞ ለፌዴራሉ የገንዘብ ሚኒስትርና ለክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ማስተባባሪያ ቢሮ ኃላፊ ተስጥቷል፡፡ ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው ከኦሮሚያ ክልል በተለየ በክልሉ ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰበውን የተርን ኦቨር ታክስ ያለው አዋጅ ሳይሻሻል በሁለት ዓይነት አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ቀሪ ወይም ዝቅ ማድረግ እንደሚቻል ነው፡፡ የመጀመሪያው የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ማስተባባሪያ ቢሮ ኃላፊ በሚያወጣው መመሪያ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የፌዴራሉ የገንዘብ ሚኒስትር በሚያወጣው መመሪያ ነው፡፡ ነገርግን ሁለቱ አስፈፃሚዎች ከሕግ አገልገሎት በሚሰበሰበው የተርን ኦቨር ታክስ ላይ የሚጋጭ መመሪያ ቢያወጡስ? ለምሣሌ አንደኛው ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰበውን የተርን ኦቨር ታክስ ቀሪ የሚያደርግ መመሪያ ሲያወጣ ሌላኛው ደግሞ የተቀነሰ ማለትም 2% እንዲከፈልበት የሚያደርግ መመሪያ ቢያወጣስ የሚል ነው፡፡ በርግጥ በኋላ የወጣው መመሪያ ቀድሞ የወጣውን መመሪያ እንደሻረው መቁጠር ይቻል ይሆናል፡፡ መመሪያዎቹ በተለያዩ ተቋማት መውጣቸው ችግሩን ይበልጥ ስለሚየጎላው ክፍተቱን አስቀድሞ መድፈን አስፈላጊ ነው፡፡

1.2.3. በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከሕግ አገልግሎት ስለሚሰበሰብ የተርን ኦቨር ታክስ 

በትግራይ ክልል የተርን ኦቨር ታክስ አስተዳደር ተገዥ የሚሆነው በክልሉ የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ ቁጥር 72/96 እና በተርን ኦቨር ታክስ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 182/02 ነው፡፡ ክልሉ የራሱ የተርን ኦቨር ታክስ አስተዳደር ከመቅርፅ ይልቅ በክልሉ የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ አንቀፅ 3 ከተደረጉ ሦስት ለውጦች ውጭ የፌዴራል የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ ቁጥር 308/95ን ሙሉ  በሙሉ በክልሉ ተፈፃሚ አድርጓል፡፡ ይህም ማለት በፌዴራል የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ ከታክስ ነፃ የተባሉ ግብይቶች በትግራይም ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ ይሆናሉ ማለት ሲሆን የሕግ አገልግሎትም በመደበኛ የአገልግሎት የተርን ኦቨር ታክስ ምጣኔ መሠረት 10%  የተርን ኦቨር ታክስ ይሰበሰብበታል ማለት ነው፡፡ በክልሉ በተጨባጭ ከሕግ አገልግሎት እየተሰበሰበ ያለው የተርን ኦቨር ታክስም በከፍተኛው የአገልግሎት ተርን ኦቨር ታክስ ምጣኔ ልክ 10% ነው፡፡

በክልሉ የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ ከተደረጉት ለውጦች አንዱና መሠረታዊው በአዋጁ ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ ከተባሉ ግብይቶች ውጭ ያሉ አቅርቦቶች የሚሰበሰበው የተርን ኦቨር ታክስ በመመሪያ ቀሪ ስለሚሆንበት አግባብ ሲሆን ይህ ስልጣንም በውክልና ለክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚያዊ ልማት ቢሮ ብቻ ተሰጥቶታል፡፡ ክልሉ የፌዴራሉን የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ እንዳለ ቢቀበለውም ከደቡብ ክልል በተለየ መልኩ የፌዴራሉ የገንዘብ ሚኒስትር በሚያወጣው መመሪያ የሚደረጉ ለውጦችን ግን መቀበል አልፈለገም፡፡ ለውጡ በአዋጅ የተደረገ ቢሆንስ የሚለው ሌላ መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡ ይህም ማለት የፌዴራሉ የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ ቢሻሻል በክልሉ የተርን ኦቨር ታክስ አስተዳደር ላይ ውጤቱ ምንድን ነው? የሚል ነው፡፡ ይህን በተመለከተ አዋጁ በዝምታ ያለፈው ስለሆነ ለትርጉም ተጋላጭ ነው፡፡ ስለዚህ ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰበው የተርን ኦቨር ታክስን በተመለከተ በፌዴራል መንግስቱ በአዋጅም ሆነ በመመሪያ የሚደረጉ ለውጦችና ማሻሻያዎች በትግራይ ክልል ተፈፃሚ አይሆኑም ማለት ሚዛን የሚደፋ ነው፡፡   

1.2.4. በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከሕግ አገልግሎት ስለሚሰበሰብ የተርን ኦቨር ታክስ 

በአብክመ የተርን ኦቨር ታክስ ተገዥ የሚሆነው በዋናነት በክልሉ የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ ቁጥር 83/9589 ሲሆን በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 191/03 እና 212/06 ማሻሻያዎች ተደርገውበታል፡፡ በፌዴራልና በሌሎች ክልሎች ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ የተደረጉት የዕቃና አገልግሎት አቅርቦቶች ሁሉም በአማራ ክልል ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ ከመባላቸው በተጨማሪ በገጠር ሴቶች ላይ የሚኖረውን የሥራ ጫና ለመቀነስ ሲባል በፌዴራልና በሦስቱ ክልሎች 2% የተርን ኦቨር ታክስ የሚሰበሰብበት የእህል ወፍጮቤቶች አገልግሎት ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ ተደርጓል፡፡ በዚህም ክልሉ አስፈላጊ ነው ብሎ ያመነበትን የእህል ወፍጮቤቶች አገልግሎት ከፌዴራሉና ከሌሎች ክልሎች አካሄድ ተለይቶ ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ በማድረግ ምሣሌ መሆን ችሏል፡፡ የሕግ አገልግሎትን በተመለከተ ግን ከሌሎች ስርዓቶች መለየት አልፈለገም አልያም አላሰበበትም፡፡ ይሁን እንጅ ከሌሎች የመለየት ተሞክሮ ያለው ክልል በመሆኑ የሕግ  አገልግሎትን አስፈላጊነት ለክልሉ ሕግ አውጭ ወይም ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ማስረዳት እስከተቻለ ድረስ ከሌሎች በተሻለ ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰብ የተርን ኦቨር ታክስን ቀሪ ማድረግ አልያም ወደ 2% መቀነስ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ በሚያወጣው መመሪያ በሌሎች ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ የሚከፈለው ታክስ ቀሪ እንዲሆን ሊፈቀድ እንደሚችል እየገለጸ ከታክስ ነፃ የመሆን መብቶች አፈፃፀም ደግሞ ቢሮው በሚያወጣው መመሪያ እንደሚወሰን ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ የክልሉ የተርን ኦቨር ታክስ አስተዳደር እንደፌዴራልና ሌሎች ክልሎች ሁሉ የሕግ አገልግሎትን በመደበኛ የአገልግሎት ምጣኔ 10% የተርን ኦቨር ታክስ ይሰበስብበታል፡፡ በተግባር ያለውም የሚያሳየው ይህንኑ እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ ሆኖም ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰበውን የተርን ኦቨር ታክስ በተመለከተ አዋጁ ሳይሻሻል የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ በሚያወጣው መመሪያ ቀሪ ሊያደርገው አልያም ቀንሶ 2% ሊያደርገው የሚችለበት የሕግ አግባብ መኖሩን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

2. ከሕግ አገልግሎት ላይ የሚሰበሰብ የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታከስ ሕገ መንግስታዊ መሠረት

በኢፌዲሪ ሕገመንግስት መሠረት የክልል መስተዳደሮች በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ግለሰብ ነጋዴዎች ላይ የሽያጭ ታክስ የመጣልና የመሰብሰብ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ግለሰብ ነጋዴዎች የሚለው ቃል በጠባቡ ሳይሆን በልዩ ድንጋጌ የሚተዳደሩ ዘርፎችን ጨምሮ በሰፊው መተርጎም ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም በተሻሻለው የአብክመ ሕገመንግስት የክልሉ መንግስት ለክልሉ በተወሰኑ የገቢ ምንጮች ላይ ግብርና ታክስ የመጣልና የመሰብበሰብ ስልጣን እንዳለው ያሳያል፡፡ ተመሣሣይ ድንጋጌም የኦሮሚያ ክልል፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ እና የትግራይ ብሔራዊ ክልል በሕገመንግስታቸው አካተዋል፡፡ ከዚህ የምንረዳው የክልል መንግስታት ከሕግ አገልግሎት የሽያጭ ታክስ (የተርን ኦቨር ታክስ) የመጣልና የመሰብሰብ ሕገመንግስታዊ ስልጣን ያላቸው መሆኑን ነው፡፡ 

ከዚህ በፊት እንደተገለጸው የፌዴራል መንግስቱ ዓመታዊ ሽያጫቸው ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ ባላቸው ጠበቆች የሚሰጡ የሕግ አገልግሎቶች ላይ 15% የተጨማሪ እሴት ታክስ ይሰበስባል፡፡ ለዚህም እንደሕገመንግስታዊ መሠረትነት የሚጠቀሰው በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 99 መሠረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በፌዴሬሽን ምክርቤት ጣምራጉባዔ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተለይቶ ያልተሰጠ የታክስ ሥልጣን ስለሆነ  በፌዴራል መንግስቱ እንዲጣልና እንዲሰበሰብ በመወሰኑ ነው፡፡ የጣምራጉባዔው ውሳኔን ሕገመንግስታዊነት በተመለከተ በሌሎች ጥናቶች በበቂ ሁኔታ የተሸፈነ ነው፡፡ የዚህ ጥናት ዓብይ ዓላማም ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰብ የተጨማሪ እሴት ታክስን ሕገ-መንግስታዊነት ማጥናት እንጅ በየትኛው የመንግስት ደረጃ ይጣል/ይሰብሰብ የሚለው ስላልሆነ ይህ ጉዳይ ለዚህ ጥናት ጭፍጫፊ ነው፡፡ በርግጥ አንድ ጠበቃ የፌዴራልና የክልል ወይም የሁለትና ከዚያ በላይ ክልሎች የጥብቅና ፈቃድ ሲኖረው የሽያጭ ታክሱ በየትኛው መንግስት ይጣል/ይሰብሰብ፤ የሚለው ሌላ ራሱን የቻለ ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ በፌዴራል መንግስቱ ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰብ የተርን ኦቨር ታክስን በተመለከተም የፌዴራል ጥብቅና ፈቃድ በሳቡና ዓመታዊ ሽያጫቸው ከአንድ ሚሊየን ብር በታች በሆኑ አቅራቢዎች የሚደረጉ አቅርቦቶች ላይ የተርን ኦቨር ታክስ የመጣልና የመሰብሰብ ሕገ-መንግስታዊ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡  

3. ስለሌሎች አገራት ተሞክሮ

በዚህ ክፍል የካናዳን፣ የህንድን፣ የፈረንሳይን፣ የኬንያንና የኡጋንዳን የሽያጭ ታክስ ልምድ ለመዳሰስ ተሞከሯል፡፡ መደበኛ ምጣኔን በተመለከተ በህንድ የዕቃዎች አቅርቦት ላይ እንደሁኔታው 0.25%፣ 3%፣ 5%፣ 12%፣ 18% እና 28% የዕቃ ታክስ የሚሰበሰብ ሲሆን አገልግሎቶችም 5%፣ 12%፣ 18% እና 28% የአገልግሎት ታክስ ይሰበሰብባቸዋል፡፡ ከዚህም መረዳት የሚቻለው ህንድ እንደዕቃውና አገልገሎቱ አስፈላጊነት ከ0.25% እሰከ 28% የተለያዩ (graduated) ምጣኔዎች መጠቀሟን እንደተሞክሮ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡በፈረንሳይ ደግሞ ከ20% መደበኛ የተጨማሪ እሴት ታክስ በተለየ መልኩ በመድሃኒት አቅርቦቶች ላይ 2.1%፤ በምግብነክ ሸቀጦች ላይ 5.5%፤ እንዲሁም በአኮምዴሽን ላይ 10% የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚሰበሰብ ሲሆን የፈረንሳይ ግዛት በሆነችው የኮርሲካ (Corsica) ደሴት ደግሞ በተወሰኑ አቅርቦቶች ላይ የ0.9% እና የ13% የተጨማሪ እሴት ታክስ ይሰበሰባል፡፡ እነዚህ ምጣኔዎችም በፈረንሳይ “የተቀነሱ ምጣኔዎች” በመባል ይታወቃሉ፡፡ በዚህም ፈረንሣይ የተቀነሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔዎችን ዕውቅና በመስጠት ምሣሌ መሆን የቻለች ሲሆን የፈረንሳይ ግዛት የሆነችው የኮርሲካ ደሴት ደግሞ በተወሰኑ አቅርቦቶች ላይ ከማዕከላዊው መንግስት የተለዩና የተቀነሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ መጣልን አስተምራናለች፡፡ ይሁንና በኛ የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር ክልሎች በሕግ አገልግሎት ላይ የተቀነሰ የተጨማሪ እሴት ታክስ መጣል ይችላሉ ወይ? የሚለው ሰፊ ጥናት ይጠይቃል፡፡  

በሌላ በኩል በነዚህ አገራት የዜሮ ምጣኔ የዕቃና አገልግሎት አቅርቦቶች ይገኛሉ፡፡ በካናዳ ወደውጭ አገር የሚላኩ ዕቃዎችና አገልግሎቶች፣ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች፣ አለማቀፋዊ ማጓጓዞች፣ የታዘዙ መድሃኒቶች፣ የህክምና መገልገያዎች የግብርናና የዓሣ ዕርባታ ግብዓቶችና ሌሎችም ተካተዋል፡፡ በህንድ፣ በኬንያ እና ኡጋንዳም መሠል አቅርቦቶች በዚሁ ምጣኔ ይሰተናገዳሉ፡፡ በፈረንሳይ የዜሮ ምጣኔ ግብይት የሚባል ሕገ ስያሜ የለም፡፡ ይሁን እንጂ የተመረጡ የፋይናንስ ተግባሮችና ከአውሮፓ ህብረት ውጭ ወደአሉ አገራት የሚላኩ አቅርቦቶች ከተመላሽ ጋር ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የተደረጉ በመሆናቸው በግብዓትነት የተከፈለ የተጨማሪ እሴት ታክስ ካለም ለመጨረሻ አቅራቢው ይመለሳል፡፡ ይሁን እንጅ በሁሉም አገራት የሕግ አገልግሎት በዜሮ ምጣኔ አቅርቦቶች ዝርዝር ውስጥ አይገኝም፡፡

ከታክስ ነፃ ግብይቶችን በተመለከተ በካናዳ የአገለገሉ መኖሪያቤት ሽያጮች፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች፣ በግብረሰናይ ድርጅቶችና በመንግስት ተቋሞች የሚከወኑ አቅርቦቶች፣ የጤና አገልግሎቶች፣ ትምህርትና የመሳሰሉት አቅርቦቶች ከታክስ ነፃ ሲሆኑ በፈረንሳይም የመሬት ግብይቶች፣ የፋይናንስ ግብይቶች፣ ከተጠናቀቁ አምስት ዓመት የሆናቸው ህንፃዎች ላይ የሚደረጉ ግብይቶች፣ ትምህርት፣ ጤናና ደህንነትና ውርርዶች በዚሁ ዝርዝር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በኡጋንዳና ኬንያ ደግሞ በዛ ያሉ ግብይቶች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የተደረጉ ሲሆን በኡጋንዳ የፋይናንስ አገልግሎቶች፣ ከጤና መድን ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች፣ የትምህርት አግልግሎት፣ ሎቶሪና ውርርዶች፣ የቀብር አገልግሎቶች፣ የሕክምና ዕቃዎች፣ የህፃናት ንጽህና መጠበቂያ ጨርቆች (Diapers)፣ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያና የፀሐይ ብርሃን ኃይል ዕቃዎች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በኬንያ ያልተቀነባበሩ የግብርና ምርቶች፣ አውሮፕላኖች፣ የአቅጣጫ መፈለጊያ ኮምፓሶች፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች፣ የህክምና አገልግሎቶችና ሌሎች ተመሳሳይ አቅርቦቶች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ሆነዋል፡፡ ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው እነኝህ አፍሪካዊያን ታዳጊ አገራት የህዝባቸውን የኑሮ ሁኔታና ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ የሽያጭ ታክስ ለመጣል ሙከራ ያደረጉ መሆኑን ነው፡፡ በህንድም ብራንድአልባ ጥራጥሬዎች፣ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች፣ ለመኖሪያ ቤት የሚከራዩ ቤቶች፣ በቀን ከአንድ ሽህ የህንድ ገንዘብ በታች የሚከፈልባቸው በሆቴል የሚሰጡ አገልግሎቶች (accomodations)፣ በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ድርጅቶችን የተመለከቱ ማስተላለፎችና የመሳሰሉት አቅርቦቶች ከታክስ ነፃ የተደረጉ ቢሆንም የሕግ አገልግሎት ግን የአገልግሎት ታክስ የሚሰበሰብበት ግብይት ነው፡፡ በአጠቃላይ በነኝህ አገራት የሕግ አገልግሎት የዜሮ ምጣኔ ግብይትም ሆነ ከታክስ ነፃ የተደረገ ግብይት ባለመሆኑ መደበኛ የሽያጭ ታክስ ይሰበሰብበታል ማለት ነው፡፡

የአስተዳደር ሂደቱን በተመለከተ በሁሉም አገሮች የዕቃና አገልግሎት ታክሶች በአቅራቢዎች ተሰብስቦ ለመንግስት ገቢ የሚደረግ ቢሆንም በጠበቆች የሚሰጥ አገልግሎትን በተመለከተ ግን በህንድ በተለየ ሁኔታ አገልግሎት የተሰጠው ሰው በራሱ ቀንሶ (Reverse Charge Mechanism) ለመንግስት ገቢ እንዲያደርገው ይጠበቃል፡፡ ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰብ የሽያጭ ታክስ በጠበቃው ብቻ ሳይሆን በተጠቃሚው ተቀንሶ ለመንግስት ገቢ እንዲያደርገው ማድረግ የሚቻል መሆኑን ነው፡፡

4. በኢትዮጵያ ስለጥብቅና አገልግሎት የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ  አግባብነት የሚነሱ ጥያቄዎች

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በሕጉ በግልጽ ነፃ ያልተደረገ ቢሆንም የተለያዩ ምክንያቶችን በመጥቀስ ከጥብቅና አገልግሎት የተጨማሪ እሴት ታክስም ሆነ የተርን ኦቨር ታክስ ሊሰበሰብ አይገባም፤ በማለት መሞገት የተለመደ ሲሆን ከነዚህ ምክንያቶች አንዱ ከሕገመንግስት ትርጓሜ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ሲሆን ሌሎቹ ግን ከሕገመንግስት ትርጓሜ ጋር ይገናኛሉ ለማለት ያዳግታል፡፡ ይሁን እንጅ ሁሉንም አብሮ ማየቱ ከሕግ አገልግሎት በሚሰበሰብ ታክስ ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ የሚያስችል በመሆኑ በዚህ ክፍል በመጀመሪያ ከሕገመንግስት ትርጓሜ ጋር የተገናኘውን ምክንያት ከመዘንን በኋላ የሕገ-መንግስት ትርጓሜ የማይፈለጉ ምክንያቶችንም የምንመዝን ይሆናል፡፡ 

4.1. ከጥብቅና አገልግሎት የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ መሰብሰብ በሕገመንግስት ጥበቃ የተደረገላቸውን መብቶች የሚገደብ ስለመሆን/ስላለመሆኑ 

በሕገመንግስት እውቅና የተሰጣቸው መብቶችን በመጥቀስ ከሕግ አገልግሎት የተጨማሪ እሴት ታክስም ሆነ የተርን ኦቨር ታክስ መሰብሰብ እነዚህን ሕገመንግስታዊ መብቶች ይገድባል፤ በማለት መሞገት የተለመደ ነው፡፡ በርግጥ የተጨማሪ እሴት ታክስም ሆነ የተርን ኦቨር ታክስ የመጨረሻ የመክፈል ኃላፊነት የሚወድቀው ከጥብቅና አገልግሎት ተጠቃሚው ላይ ነው፡፡ ይህም በአገልግሎት ተጠቃሚው ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ግልፅ ነው፡፡ እነዚህ ታክሶች የሚሰበሰቡት የዳኝነት፣ የጠበቃና ሌሎች ተጨማሪ ወጭዎች ካሉባቸው ፍትሕ ፈላጊዎች መሆኑ ችግሩን የከፋ የሚያደርገው በመሆኑ ዜጎች ጉዳያቸውን ወደፍርድቤት ከመውሰድ ይልቅ በጃቸው መጠቀምን እንዲመርጡ ሊያስገድዳቸው ስለሚችል አለመረጋጋትንም ያመጣል፡፡ በአገራችን ያለው ነፃ የሕግ ድጋፍ ሽፋን ውስን ከመሆን ባለፈ መንግስት ተከላካይ ጠበቃ የሚያቆምባቸው አግባቦች መጥበብም ችግሩን ይበልጥ ያጎላዋል፡፡ ከዚህም የምንረዳው ከሕግ አገልገሎት የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክሰ መሰብሰብ አቅም የሌላቸው ሰዎች ፍትሕ እንዳያገኙ ምክንያት መሆኑን ነው፡፡

እንዲሁም የሕግ አገልግሎት ተጠቃሚው ወደ ባለሙያው የሚሄደው ተገዶ እንጅ እንደሌሎች አቅርቦቶች ፈልጎ ባለመሆኑ ፍትሕ ደግሞ እንደሌሎች ሸቀጦች አለመሆኑ ታሳቢ ተደርጎ የተጨማሪ እሴት ታክስም ሆነ የተርን ኦቨር ታክስ ሊሰበሰብበት አይገባም፡፡129 የፍትሕ አገልግሎትን ከፍይናንስ፣ ሕክምናና ትምህርት ነጥሎ ማየት ተገቢ ሊሆን አይችልም፡፡ መንግስት በተመረጡ የወንጀል ጉዳዮች ላይ ተከላካይ ጠበቃ የሚያቆምበት መሠረታዊ አመክንዮም ፍትሕ ከሌሎች ሸቀጦች የተለየና በሕይወት ከመኖርና ከነፃነት መብት ጋር በቀጥታ ስለሚገናኝ እንደሕክምናና ትምህርት አንገብጋቢ በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩልም ፍትሕ ማግኘት ለፋይናንስ፣ ሕክምና፣ ትምህርትና ሌሎች መብቶችና ጥቅሞች መከበር የሚኖረውን ሚና ግምት ውስጥ ማስገባትም ያሻል፡፡ በተጨማሪም የሕግ አገልግሎት ዘርፍ በአገሪቱ ገና በጅምር ያለና ልዩ ትኩረት የሚሻ አስፈላጊ ዘርፍ በመሆኑና በሕጉ መሠረትም ከዘርፉ ሊሰበሰብ የሚችለው የመንግስት ገቢ አናሳ በመሆኑ መንግስት ሌሎች አማራጭ የገቢ ምንጮችን እንዲጠቀም የሚመክሩ አሉ፡፡

ይሁን እንጂ እዚህ ላይ መጤን ያለባቸው ሌሎች እይታዎችም አሉ፡፡ በመጀመሪያ እነዚህ ሕገመንግስታዊ መብቶች እንዲከበሩ ጠበቆች ብቻቸውን ይቻላቸዋል ወይ? የሚለው ነው፡፡ ከዚህም የምንረዳው ጠበቆች ብቻቸውን እነዚህን ሕገመንገስታዊ መብቶች ማስከበር የማይችሉ ከመሆናቸውም በላይ እንደፍርድቤት፣ ዓቃቢ ሕግ፣ ፓሊስ፣ መከላከያ፣ እንባጠባቂ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ወዘተ ያሉ በመንግስት ፋይናንስ የሚደረጉ ተቋማት የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ረገድ መንግስት ከጠበቆች የበለጠ ኃላፊነት ያለበት ከመሆኑ በተጨማሪ ከፍተኛ ወጭ በሚጠይቅ መልኩ እነዚህን መብቶች የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ለአብነትም መንግስት ፍትሕን ተደራሽ ለማድረግና ለድሆች ተከላካይ ጠበቃ ለማቆም የሚያወጣው ወጭ ከፍተኛ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ሲባል ደግሞ መንግስት የግድ ገቢ መሰብበሰብ ያለበት በመሆኑ ከሕግ አገልግሎት የተጨማሪ እሴት ታክስም ሆነ የተርን ኦቨር ታክስ መሰብሰብ ሕገመንግስታዊ መብቶችን ያጣብባል፤ ብሎ ለመደምደም ያዳግታል፡፡ መንግስት ይህን በማድረጉ የመክፈል አቅም ካላቸው ሰዎች በመሰብሰብ አቅም ለሌላቸው ሰዎች ሕገመንግስታዊ መብቶች መከበር የራሱን ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡ ይህን አለማድረግ ደግሞ የታክስ መሠረትን በማጥበብ መንግስትን ማዳከም በመሆኑና ደካማ መንግስት ደግሞ ሕገመንግስትን የማስፈፀም አቅም ስለማይኖረው በሕገመንግስታዊ መብቶች መከበር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም እንኳንስ ደካማ ኢኮኖሚ ላላቸው ታዳጊ አገራት ጠንካራ ኢኮኖሚ ላላቸው የአደጉ አገራትም የታክስ መሠረቶችን ማስፋት የሚመከር ነው፡፡ በአጠቃላይ ከሕግ አገልግሎት የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ መሰብሰብ በሕገመንግስታዊ መብቶች ላይ ከሚያደርሰው አሉታዊ ተፅዕኖ የሚጫወተው አዎንታዊ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ሕገመንግስታዊ መብቶችን የሚገድብ ነው፤ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ለዚያም ይመስላል በምርምሩ በተሸፈኑ ሌሎች አገራትም ሆነ በኢትዮጵያ ከሕግ አገልግሎት የሽያጭ ታክስ መሰብሰብ የተለመደ ነው፡፡

በሌላ በኩል የሕግ አገልገሎት ምንድን ነው የሚለውን በቅጡ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከሕግ አገልግሎት የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ ሊሰበሰብ አይገባም፤ ሲሉ የሚሞግቱ ባለሙያዎች መነሻቸው የሕግ አገልግሎት ጠባብ ትርጓሜ ነው፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ፍርድቤት ጠበቆች አዋጅ እንደተገለፀው የሕግ አገልግሎት ማለት በወንጀልና ፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍርድቤት ቀርቦ ከመካራከር ባለፈ የውል ስምምነት፣ የድርጅት ማቋቋሚያ፣ ማሻሻያና ማፍረሻ ሰነዶችን እንዲሁም ኑዛዜና ፍርድቤት የሚገቡ አቤቱታዎችና መልሶች ማዘጋጀትን ጨምሮ ማናቸውንም ዓይነት የሕግ ምክር አገልግሎት መስጠትን የሚያጠቃልል ሰፊ ተግባር ነው፡፡ የድርጅት ማቋቋሚያ፣ ማሻሻያና ማፍረሻ ሰነዶች ዝግጅት አገልግሎት ከተሰጠው ደንበኛ ታክስ መሰብሰብ አግባብ ቢሆንም ራሱን ካልተገባ የወንጀል ኃላፊነት ለማዳን የጠበቃ አገልግሎት ከሚጠቀም ፍትሕፈላጊ ታክስ መሰብሰብ በምንም መለኪያ ተገቢ ሊሆን አይችልም፡፡ የዳኝነት ክፍያ የመክፈል አቅም እንደሌለው በመረዳት ከዳኝነት ክፍያ ነፃ የተደረገ ሰውም ቢሆን ነፃ የሕግ አገልግሎት በማጣቱ የጠበቃ አገልግሎት በክፍያ ቢጠቀም ታክስ እንዲከፍል ይገደዳል፡፡ ይህ ደግሞ ፍትሕ እንዲያገኝ ዕድል ከተሰጠው በኋላ መልሶ በመነጠቁ መልሶ የመውሰድ (claw-back) ውጤት ይኖረዋል፡፡ የሕግ አገልግሎት ለመንግስት የሰጠ ጠበቃም ቢሆን ‘ከመንግስት’ ‘ለመንግስት’ ታክስ እንዲሰበሰብ ይገደዳል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነበት ምክንያትም ከሕግ አገልግሎት ታክስ የሚሰበሰብበት የታክስ መሠረት ሰፊ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህም የምንረዳው ከሁሉም የሕግ አገልግሎቶች ታክስ ከመሰብሰብ፤ ወይም ከሁሉም የሕግ አገልግሎቶች የሚሰበሰበውን ታክስ ሙሉ በሙሉ ቀሪ ከማድረግ ይልቅ ለሕግ አገልገሎት ራሱን የቻለ አዲስ ሠንጠረዥ ማዘጋጀት እንደሚሻል ነው፡፡ ለዚህም ያግዝ ዘንድ የሕግ አገልግሎቶችን አስፈላጊነት እና በሕገ መንግስት ጥበቃ ከተደረገላቸው መብቶች ጋር ያላቸውን ቁርኝት፤ እንዲሁም የሕግ አገልግሎት ተጠቃሚውን የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ በሠንጠረዥ በመከፋፈል በተለያዩ የታክስ ምጣኔዎች የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ መሰብሰብ ይሻላል፡፡ ሠንጠረዡ የመንግስትን የገቢ ፍላጎትም ግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባል፡፡ ከሕግ አገልግሎት ይሰበሰብ የነበረውን የታክስ ገቢ በሌሎች የገቢ ምንጮች በጥንቃቄ መተካትንም የሚጠይቅ አማራጭ ነው፡፡ በሌላ በኩል መንግስት በሠንጠረዡ መሠረት ከሕግ አገልግሎት ታክስ ሲሰበስብ ከዘርፉ በሰበሰበው መጠን ትይዩ ፍትሕን አቅም ለሌላቸው ተደራሽ ለማድረግ ያስችል ዘንድ ነፃ የሕግ ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማትን ማጠናከርና ማስፋፋት፣ እንዲሁም ተከላካይ ጠበቃ የሚያቆምባቸውን የሕግ አግባቦች ማስፋት ይኖርበታል፡፡ ጠበቆች የሚሰጡት የ50 ሰዓት ነፃ የሕግ አገልግሎት በአግባቡ መፈፀሙን መከታተልም ተገቢ ነው፡፡

4.2. የጥብቅና አገልግሎት በልዩ ፈቃድ የሚተዳደር ስለመሆኑ 

ጥብቅና እንደሌሎች በንግድ ሕግ መርህ የማይመራና በልዩ ሕግ የሚመራ ስለሆነ በልዩ ፈቃድ አሰጣጥ የሚተዳደር በመሆኑ እንደሌሎቹ የአገልግሎት ንግድ ዘርፎች የተጨማሪ እሴት ታክስም ሆነ የተርን ኦቨር ታክስ ሊሰበሰብበት አይገባም የሚል ሙግትም የተለመደና በተጨባጭም ጥያቄ የቀረበበት ጉዳይ ሆኗል፡፡ እዚህ ላይ መታየት ያለበት ዋና ነጥብ ጥብቅናን በልዩ ሕግና ፈቃድ ማስተዳደር ያስፈለገበትን ዓላማ ነው፡፡ በመሠረቱ ጥብቅና በአግባቡ ካልተያዘ በደንበኞች ላይ የሕይወትና ነፃነት አላግባብ ማሳጣትን ጨምሮ የፍትሕ መጓደልን የሚያስከትል በመሆኑ የተለየ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ሙያ ከመሆኑ በተጨማሪ የዕውቀትና የአቅም ደረጃ ልዩነት ባላቸው ሰዎች መካከል ያለ ግንኙነት በመሆኑ በዓይነት የተለየና የጠበቀ ድንጋጌ ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህም የምንረዳው ልዩ ፈቃድና ድንጋጌ ያስፈለገው ለታክስ ዓላማ አለመሆኑን ነው፡፡ 

ከዚህ ጋር በተያየዘ ሌሎች የሚነሱ ሁለት ጉዳዮች ያሉ ሲሆን የመጀመሪያው የሕግ አገልግሎትን ማስተዋወቅ የማይቻል በመሆኑ የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ ሊከፈልበት አይገባም የሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ገደብ ታክስ ከመክፈል ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ በተጨማሪም የማስተዋወቅ ገደብ የተጣለው ጠበቃው ላይ ሲሆን ታክስ የሚከፍለው ደግሞ አገልግሎት ተጠቃሚው መሆኑ ምክንያቱን የበለጠ ደካማ ያደርገዋል፡፡ ሁለተኛው ተያያዥ ጉዳይ ደግሞ የጥብቅና አገልግሎት ክፍያ ምጣኔ በሕግ የተወሰነ ስለሆነ የተጨማሪ እሴት ታክስም ሆነ የተርን ኦቨር ታክስ ሊሰበሰብበት አይገባም የሚል ነው፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ መሠረት ሲጀመር ዋጋን መሠረት ያደረገ የዕቃና አገልግሎት ግብይት በመሆኑ በሕግ የተወሰነ የክፍያ ምጣኔ መኖር የሚሰበሰብ ታክስን አያግድም፡፡ እንዲያውም የተወሰነ የክፍያ ምጣኔ መኖር የታክስ አስተዳደር ሂደቱን የበለጠ ግልፅና ውጤታማ (Efficient) ያደርገዋል፡፡

4.3. የሕግ አገልግሎት ክፍያ ተግዳሮቶች

የሕግ አገልግሎት ሲሰጥ መሸነፍ ያለ በመሆኑ፤ ነፃ የሕግ አገልግሎት መስጠት ግዴታ ስለሆነ፤ ክፍያ አለማግኘት የተለመደ ስለሆነ፤ ክፍያ ዘግይቶ ከዓመታት በኋላ መፈፀም የተለመደ ስለሆነና ሌሎች የመሳሰሉ የክፍያ ተግዳሮቶች ያሉ በመሆኑ ከጥብቅና የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ ሊሰበሰብ አይገባም የሚሉ ሙግቶች አሉ፡፡ ይህ ሙግት በመጀመሪያ በሕግ የተወሰነ የክፍያ ምጣኔ አለ ከሚለው ጋር የሚቃረን ሲሆን በተጨማሪም ከታክስ ሕጎችና ከተግባር እንደምንረዳው ክፍያ እስካልተፈፀመ ድረስ የተጨማሪ እሴት ታክስም ሆነ የተርን ኦቨር ታክስ የማይሰበሰብ መሆኑን ነው፡፡ ይሁን እንጅ የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ አስተዳደር በጠበቃው ላይ ያልተገባ ጫና ስለሚፈጥር ሙያዊ ግዴታውን እንዳይወጣ ስለሚያደርገው በአገሪቱ ያለውን የፍትሕ እጦት ያባብሳል፡፡ ጠበቃው በሂሣብ አያያዝ በቂ ዕውቀት የሌለውና ባለሙያም ለመቅጠር እንደሌሎች ንግዶች በካፒታል የሚተዳደር ስላልሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለዚህም ነው የጥብቅና ፈቃድ ለማውጣት የብቃት እንጅ የካፒታል ቅድመሁኔታ ያልተቀመጠው፡፡ 

መደምደሚያና የመፍትሔ ኃሳብ 

በጥናቱ እንደተመለከተው የተለያዩ አገራት ከሕግ አገልግሎት የሽያጭ ታክስ ይሰበስባሉ፡፡ ለአብነትም ካናዳና ህንድ ከሕግ አገልግሎት በመደበኛ ምጣኔ የአገልገሎት ታክስ የሚሰበስቡ ሲሆን ፈረንሳይ፣ ኡጋንዳና ኬንያም የተጨማሪ እሴት ታክስ በመሰብሰብ ይተወቃሉ፡፡ ይሁን እንጅ ከሌሎቹ በተለየ በህንድ ለመንግስት የሚሰጥ የሕግ አገልገሎት ከአገልግሎት ታክስ ነፃ ከመደረጉ በተጨማሪ ከሌሎች አቅርቦቶች በተለየ በጠበቆች ከሚሰጥ አገልግሎት የሚሰበሰብ የአገልግሎት ታክስን አገልግሎት የተሰጠው ሰው በራሱ ቀንሶ ለመንግስት ገቢ እንዲያደርገው ይጠበቃል፡፡ ካናዳና ህንድ የኮመን ሕግ ስርዓት ተከታይ ቢሆኑም እንደኢትዮጵያ ሁሉ የፌደራል ስርዓት የሚከተሉ አገራት ሲሆኑ ፈረንሳይም ብትሆን እንደኢትዮጵያ የሲቪል ሕግ ስርዓት የምትከተል አገር ከመሆኗ በተጨማሪ የተጨማሪ እሴት ታክስን በመሰብሰብ ግንባርቀደምና አርዓያ የሆነች አገር ናት፡፡ ኡጋናዳና ኬንያም ከኢትዮጵያ ጋር የሚቀራረብ የሽያጭ ታክስ ስርዓትና ተመሳሳይ የሆነ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ሁኔታ አላቸው፡፡ ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ከነዚህ አገሮች ጠቃሚ ኃሳቦች በመውሰድ የራሷን ውጤታማ ስልት መቅረጽ እንጅ የታክስ ሕጋቸውን እንዳለ መውሰድ ተገቢ አለመሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ 

ወደኢትዮጵያ ስንመለስም ዓመታዊ የአገልግሎት አቅርቦታቸው ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ በሆኑ ጠበቆች ከሚሰጥ የሕግ አገልግሎት የፌዴራል መንግስቱ የተጨማሪ እሴት ታክስ በብቸኝነት ይሰበስባል፡፡ ይህም የሆነው የተጨማሪ እሴት ታክስን የፌዴራል መንግስቱ በብቸኝነት እንዲጥልና እንዲሰበሰብ በፌዴሬሽን ምክርቤትና በህዝብ ተወካዬች ምክርቤት የጣምራጉባዔ በመወሰኑ ነው፡፡ የተርን ኦቨር ታክስም የፌዴራል መንግስቱና የክልል መንግስታት በመዘገቧቸው ጠበቆች በሚሰጡ የሕግ አገልግሎቶች ላይ ይሰበስባሉ፡፡ በርግጥ ይህ የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ አሰባሰብ ሕግን የተከተለ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ከጥናቱ ለመገንዘብ እንደሚቻለው የታክስ መሠረቱን፣ ምጣኔውንና የአስተዳደር ሂደቱን በተመለከተ በአዙሪት ጥያቄዎችና መውሰብስቦች የተሞላ ከመሆኑ ባሻገር አግባብነቱ ላይም ጥያቄዎች ይስተዋላሉ፡፡ በመሆኑም ለችግሩ መፍትሄ ማበጀት አስፈላጊ ነው፡፡ ለችግሩ መፍትሄም ሦስት አማራጮችን ማበጀት ይቻላል፡፡ 

የመጀመሪያው አማራጭ አሁን እየተደረገ እንዳለው ከሕግ አገልግሎት በመደበኛ ምጣኔ የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ መሰብሰብ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ፍትሕን አቅም ለሌላቸው ተደራሽ ለማድረግ ያስችል ዘንድ ነፃ የሕግ ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማትን ማጠናከር የሚጠይቅ ሲሆን መንግስት ተከላካይ ጠበቃ የሚያቆምባቸውን የሕግ አግባቦችም ማስፋት ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም ጠበቆች የሚሰጡት የ50 ሰዓት ነፃ የሕግ አገልግሎት በአግባቡ መፈፀሙን መከታተል ያስፈልጋል፡፡ እዚህ አማራጭ ላይ ታክሱ በጠበቆች ከሚስበሰብ ይልቅ ህንድ እንዳደረገችው አገልግሎት የተሰጠው ሰው በራሱ ቀንሶ ለመንግስት ገቢ እንዲደርግ ሀሳቦች ይነሳሉ፡፡ ይሁን እንጅ ይህ የአሰባሰብ ሂደት የሕግ አገልግሎት ተጠቃሚውን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው፡፡ በተጨማሪም የአሰባሰብ ሂደቱን ውጤታማነትም ይቀንሰዋል፡፡ 

ሌላኛው አማራጭ ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰበውን የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ ማስቀረት ነው፡፡ ሌሎች አገራት ከሕግ አገልግሎት የሽያጭ ታክስ ስለሰበሰቡ ኢትዮጵያም የግድ መከተል አለባት ሊባል አይገባም፡፡ ይህን አማራጭ ለመተግበር ሁለት መንገዶች ይኖሩታል፡፡ የመጀመሪያው  ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰበውን ታክስ ለማስቀረት ያስችል ዘንድ የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ አዋጆችን ማሻሻል ነው፡፡ ሌላኛው መንገድ ደግሞ በተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ አዋጆች ከታክስ ነፃ ከተደረጉ አቅርቦቶች በተጨማሪ ሌሎች አቅርቦቶችን ከታክስ ነፃ የማድረግ ሥልጣን በውክልና ለአስፈፃሚው ስለተሰጠው ይህንን የውክልና ሥልጣን በመጠቀም አስፈፃሚው በመመሪያ የሕግ አገልግሎትን ከተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ ነፃ ማድረግ ነው፡፡ ነገርግን መንግስት ይህን አማራጭ ካስቀደመ ከሕግ አገልግሎት ይሰበስብ የነበረውን የታክስ ገቢ በሌሎች የገቢ ምንጮች በጥንቃቄ መተካት ያስፈልጋል፡፡  

ሦስተኛው አማራጭ መነሻው ሁለቱም አማራጮች ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያላስገቡ ናቸው፤ የሚል በመሆኑ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ስልት መቀየስ ያሻል፡፡ ይህ አማራጭ ለሕግ አገልገሎት ራሱን የቻለ አዲስ ሠንጠረዥ ማዘጋጀትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ለዚህም ያግዝ ዘንድ የሕግ አገልግሎቶችን አስፈላጊነትና በሕገመንግስት ጥበቃ ከተደረገላቸው መብቶች ጋር ያላቸውን ቁርኝት፣ እንዲሁም የሕግ አገልግሎት ተጠቃሚውን የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ በሠንጠረዥ በመከፋፈል በተለያዩ የታክስ ምጣኔዎች የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ መሰብሰብ ይሻላል፡፡ ሠንጠረዡ የመንግስትን የገቢ ፍላጎትም ግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዘርፉ ይሰበሰብ የነበረውን የታክስ ገቢ በሌሎች የገቢ ምንጮች በጥንቃቄ መተካትንም የሚጠይቅ አማራጭ ነው፡፡ በሌላ በኩል መንግስት በሠንጠረዡ መሠረት ከሕግ አገልግሎት ታክስ ሲሰበስብ ከዘርፉ በሰበሰበው መጠን ትይዩ ፍትሕን አቅም ለሌላቸው ተደራሽ ለማድረግ ያስችል ዘንድ ነፃ የሕግ ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማትን ማጠናከርና ማስፋፋት፣ እንዲሁም ተከላካይ ጠበቃ የሚያቆምባቸውን የሕግ አግባቦች ማስፋት ይኖርበታል፡፡ ጠበቆች የሚሰጡት ነፃ የሕግ አገልግሎት በአግባቡ መፈፀሙን መከታተል በሶስቱም አማራጮች የሚመከር ነው፡፡  

በአጠቃላይ ከዚህ ጥናት ለመደምደም የሚቻለው ከላይ የተሰጡትን አማራጭ መፍትሔዎች በመተግበር በኢትዮጵያ ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰቡ የሽያጭ ታክሶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስፈልገው የሕገመንግስት ትርጓሜ ሳይሆን የአዋጅ ማሻሻያዎች አልያም የውክልና ስልጣንን መሠረት ያደረጉ የአስፈፃሚው መመሪያዎች ናቸው፡፡  

ይህ ጽሑፍ በባሕርዳር ዩኒቨርስቲ የሕግ መጽሔት በቮሉየም 8 ቁጥር 2 (.. ጁን 2018) የታተመ ነው። ጸሑፉ በኢትዮጵያ ከሕግ/ጥብቅና አገልግሎት የሚሰበሰብ ግብር/ታክስ ላይ ሰፊ መረጃን እና የመፍትሔ ሐሳብ የሚሰጥ በመሆኑ ለግንዛቤ ጽሑፉን በዚህ አቅርበናል። ጥናታዊ ጽሑፉ በርካታ ማጣቀሻ እና የግርጌ ማስታወሻ ያለው ሲሆን በዚህ ያቀረብነው ካለማጣቀሻው ነው፤ በመሆኑም የጽሑፉን ዋና ቅጂ እስከማጣቀሻ እና የግርጌ ማስታወሻው ከዚህ ባለው ማስፈንጠሪያ/ሊንክ ማውረድ/ዳውንሎድ ማድረግ ይችላሉ።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በፍርድ ቤት አወዛጋቢ የሆኑ የውርስ ጉዳዮች እና መፍትሔዎቻቸው
የማስረጃ ሕግ - ሕጉ እና አተገባበሩ

Related Posts

 

Comments 1

Abebe
Guest - Debebe Shanko on Tuesday, 30 January 2024 21:39

Nice

Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024