የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን እና የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት

የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 እራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ከአዲስ አበባ እና ከድሬዳዋ ከተሞች ላይ የገፈፈ ስለመሆኑ እና የመፍትሔ አቅጣጫዎቹ፡፡  እራስን በራስ የማስተዳደር መብት የፌዴራል ሥርዓትን በሚከተሉ አገሮች የተለመደ አሰራር ሲሆን በዋናነትም ክልሎች ወይም ራስ ገዝ አስተዳድሮች ከፌዴራል መንግስቱ ተፅእኖ ውጪ የራሳቸው ሕግ አውጪ፤ ሕግ ተርጓሚ (የዳኝነት አካል) እንዲሁም የህግ አስፈፃሚ አካላት ኖሯቸው በcheck and balance መርህ ክልላቸውን ወይም አካባቢያቸውን የሚያስተዳድሩበት ቁልፍ ቃል-ኪዳናቸው ነው፡፡

ይህ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀፅ 39(3) ለኢትዮጵያ ብሄር፤ ብሄረተሰቦች፤ ሕዝቦች የሰጠ እንዲሁም በአንቀፅ 49(2) ላይ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን እንዳለው የሚደነግግ  ሲሆን በአንፃሩ የድሬዳዋ አስተዳደር ግን ይሄን መብት ሕገ-መንግስቱ እንደነፈገው የሚታወቅ ግልፅ ሐቅ ነው፡፡

በመሆኑም የዚህ ጽሑፍ ዋናው ትኩረት ከዳኝነት አካላት ውስጥ አንዱ ከሆነው የድሬዳዋ  እና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድሮች የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤን የዳኝነት ስልጣን ከሕገ-መንግስቱ (እራስን በራስ ከማስተዳደር መብት ለአዲስ አበባ ከተማ ከተሰጠ መብት አንፃር)፤ ከፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጁ እና ከተሞቹ ከሚመሩባቸው አዋጆች አንፃር ያሉ የሕግ ጉዳዮችን/ችግሮችን በንፅፅር በወፍ በረር በመዳሰስ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማመላከት ነው፡፡   

1.የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የዳኝነት ስልጣኑን ያጣ ስለመሆኑ፡-

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ በተሸሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 311/1994 አንቀፅ 48 መሰረት በከተማ አስተዳደሩ በሚሰበሰቡ ግብሮችና ቀረጦችን በተመለከተ የሚቀርብለትን ይግባኝ የማየት ስልጣን እንዳለውና አደረጃጀት እና አሰራሩ በከተማው ም/ቤት በሚወጣ ሕግ እንደሚወሰን  ይደነግጋል፡፡ በዚሁ መሰረትም ጉባኤው ተቋቁሞ በይግባኝ የሚቀርቡለትን ጉዳዮች ሲያይ የቆየና እያየም የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ ይሄን የዳኝነት ስልጣን የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 የከተማው አስተዳደር እራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር በሕገ መንግስቱ የተሰጠውን ስልጣን በሚፃረር ሁኔታ ነጥቆታል፡፡ ይህም ማለት የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጁ በአንቀፅ 86(1) ላይ የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን እንደተቋቋመ እና  በአንቀፅ 87(1) ደግሞ የታክስ ይግባኝ ኮሚሽኑ የታክስ ይግባኝ በሚባልባቸው ጉዳዮች ላይ ይግባኝ እንደሚሰማ የተደነገገ ሲሆን በአዋጁ አንቀፅ 2(2) ላይ ደግሞ ይግባኝ ሊቀርብበት ሚችል ውሳኔ ማለት ቅሬታ ላይ የተሰጠ ውሳኔ እንዲሁም የታክስ ውሳኔን እና የታክስ ውሳኔ በመስጠት ሂደት የሚሰጥ ውሳኔን ሳይጨምር ሌሎች ባለስልጣኑ የሚወስናቸው ማናቸውም ውሳኔዎች እንደሆኑና እንዲሁም በአዋጁ አንቀፅ 2(4) ባለስልጣን ማለት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን፤የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ እና የድሬዳዋ ገቢዎች ቢሮ ናቸው ሲል የደነገገ በመሆኑ ምንም እንኳ በፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጁ መሸጋገሪያ ድንጋጌ ላይ የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን እስከሚቋቋም ድረስ በስራ ላይ ያለው ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ስራውን እንደተለመደው ማካሄዱን ይቀጥላል ቢልም  ቀድሞ በአዋጅ ቁጥር 311/1994 ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ተሰጥቶ የነበረው ስልጣን ለፌዴራል መንግስቱ የሰጠ በመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የዳኝነት ስልጣኑን አጥቷል፡፡

2.የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የዳኝነት ስልጣኑን ያጣ ስለመሆኑ፡-

የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/1996(ምንም እንኳ የሕገ መንግስቱን የበላይነት አክብሮ የፀደቀ አዋጅ ባይሆንም ድሬዳዋ የምትተዳደርበት ስለሆነ ብቻ) በአንቀፅ 40 ላይ የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ከቦታ ማስለቀቅ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ጋር ተጣምሮ በከተማው አስተዳደር የሚሰበሰቡ ግብሮችና ቀረጦችን በተመለከተ የሚቀርብለትን ይግባኝ የማየት እና የከተማን ቦታ ስለመያዝ እንደገና ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 272/1994 መሰረት  እንደሚሰራ እና የጉባኤውን አደረጃጀትና አሰራር በተመለከተም በሕግ እንደሚወሰን ይገልፃል፡፡ በዚሁ መሰረትም ሐምሌ 18 ቀን 1996 ዓ.ም  በቁጥር 7/1996 በጊዜያዊ አስተዳደሩ የጉባዔውን ማቋቋሚያ አዋጅ አውጆ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

ይህ የዳኝነት ስልጣን በአንድ በኩል በማቋቋሚያ አዋጁ (አዋጅ 7/1996) ጉባዔው ሁለት ችሎት እንደ አስፈላጊነቱ ሊኖረው እንደሚችል ቢደነግግም ሁለት የተለያዩ ዘርፎችን በአንድ ጉባኤ እንዲመሩ በቻርተሩ መደንገጉ ተገቢነት የሌለው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባዔው የተሰጠውን የዳኝነት ስልጣን ከላይ ስለ አዲስ አበባ ከተማ የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ በተገለፀው አግባብ  የድሬዳዋ ከተማ  የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባዔንም ስልጣን የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 የነጠቀውና ስልጣኑን ለፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን የሰጠ በመሆኑ የከተማው ገቢዎች ቢሮ ግብር ከፋዮች ቢሮው በሚሰጠው አስተዳደራዊም ሆነ የግብር ቅሬታ ውሳኔዎች ላይ የይግባኝ አቤቱታ ለማቅረብ የግድ አዲስ አበባ ለሚገኘው የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን አቤቱታቸውን ማቅረብ ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በድሬዳዋ አስተዳደር ግብር ከፋዮች ላይ የጊዜ፤የገንዘብ፤የሀብት እና የጉልበት ብክነትና ድካም ከማስከተሉም በላይ ፍትሕን ተደራሽና ቀልጣፋ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡

3.የመፍትሔ አቅጣጫዎች

3.1 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤን በተመለከተ፡-

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን እንዳለው በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 49(2) የሚደነግግ በመሆኑና በተሻሻለው የከተማው ቻርተር አዋጅ ቁጥር 311/1994 መሰረትም የከተማው አስተዳደር ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ በከተማ አስተዳደሩ በሚሰበሰቡ ግብሮችና ቀረጦችን በተመለከተ የሚቀርብለትን ይግባኝ የማየት ስልጣን እንዳለው የተደነገገ በመሆኑ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 ከከተማው አስተዳደር የነጠቀውን የዳኝነት ስልጣን በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በኩል የታክስ አስተዳደር አዋጁ የፌዴራል መንግስቱ ባለስልጣን መ/ቤት (የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን) ብቻ በሚሰጠው አስተዳደራዊና የግብር  ውሳኔዎች ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን የታክስ ይግባኝ ኮሚሽኑ በይግባኝ ጉዳዮቹን ማየት እንደሚችል ተሻሽሎ ሊታወጅ ይገባዋል፡፡

3.2 የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤን በተመለከተ፡-

መፍትሔ 1. የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጁ መሻሻል ያለበት ስለመሆኑ፡-

ድሬዳዋን የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ፌዴራል መንግስት አልያም ራስ ገዝ አስተዳደር ሆና እራሷ በራሷ እንድታስተዳድር እውቅናን ያልሰጣት ቢሆንም አስተዳደሩ የሚተዳደርበት ቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/1996 (ሕገ-መንግስቱን የበላይነት አክብሮ ያለመፅደቁ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ) በመግቢያው ላይ የአዋጁን አስፈላጊነት ከሚገልፁት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ “ለድሬዳዋ ነዋሪ እራሱን በራሱ የማስተዳደር ስልጣን መስጠት….” እንደሆነ የሚገልፅ በመሆኑና በአዋጁ አንቀፅ 40(1)መሰረት የከተማው አስተዳደር ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ በከተማ አስተዳደሩ በሚሰበሰቡ ግብሮችና ቀረጦችን በተመለከተ የሚቀርብለትን ይግባኝ የማየት ስልጣን እንዳለው የተደነገገ በመሆኑ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 ከከተማው አስተዳደር የነጠቀውን የዳኝነት ስልጣን በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በኩል የታክስ አስተዳደር አዋጁ የፌዴራል መንግስቱ ባለስልጣን መ/ቤት (የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን) ብቻ በሚሰጠው አስተዳደራዊና የግብር ቅሬታ ውሳኔዎች ላይ የታክስ ይግባኝ ኮሚሽኑ በይግባኝ ጉዳዮቹን ማየት እንደሚችል ተሻሽሎ ሊታወጅ ይገባዋል፡፡

መፍትሔ2. የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽኑ ቅ/ፅ/ቤቱን በድሬዳዋ መክፈት ያለበት ስለመሆኑ፡-

የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ በአንድ በኩል ነዋሪው እራሱን በራሱ የማስተዳደር ስልጣን መስጠት በማስፈለጉ አዋጁ መፅደቁን ሲገልፅ በሌላ በኩል ደግሞ በአዋጁ አንቀፅ 51(1) ላይ የከተማው አስተዳደር የፌዴራሉ መንግስት አንድ አካል እንደሆነና ተጠሪነቱም ለፌዴራል መንግስቱ መሆኑን የሚገልፅ በመሆኑ ድሬዳዋ የፌዴራል መንግስቱ አካል ነች የሚል መከራከሪያ ማስነሳቱ የማይቀር በመሆኑ የፌዴራል መንግስቱ ባለስልጣን መ/ቤትም( የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የድሬዳዋ ቅ/ፅ/ቤትም) ሆነ የድሬዳዋ ገቢዎች ቢሮ   ግብር ከፋዮች በታክስ፤በቀረጥ እና በባለስልጣኑ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ላይ ለሚኖራቸው ቅሬታ በይግባኝ ደረጃ ለሚያቀርቧቸው አቤቱታዎች በድሬዳዋ ከተማ ላይ የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ቅ/ፅ/ቤቱን አቋቁሞ ጉዳያቸው ሊታይላቸው ይገባል፡፡                                                    

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

“ለእግረኛ ቅድሚያ በመከልከል…” ከሕግ አንጻር ሲታይ
የንግድ ፈቃድን ማከራየት በወንጀል ያስቀጣል?

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 29 March 2024