Font size: +
6 minutes reading time (1170 words)

በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ወንጀለኛን (ተጠርጣሪን) የመያዝ አጠቃላይ አካሔድ

በዚህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ የወንጅል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ተጠርጣሪን በቁጥጥር ሥር ስለመዋል ወይም ስለመያዝ የሚመለከቱ መሠረታዊ ጉዳዮችን ለማብራራት ጥረት ተደርጓል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን የሰዎች የነፃነት መብትና በፖሊስ በወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር ስለመዋል መካከል ስላለስ ግንኙነት በትንሹ ገለፃ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ በተጨማሪም ተጠርጣሪዎች የሚያዙባቸውን መንገዶችና እንዴት በቁጥጥር ሥር እንደሚውሉ የሚደነግገውን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ክፍል በጥልቀት ለመርመር ሙከራ ተደርጓል፡፡

የመያዝና የሕገ መንግሥቱ የነጻነት መብት ግንኙነት

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 17 (1) ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ነፃነቱን እንደማያጣ በግልፅ ይደነግጋል፡፡ ይህም ማለት በንዑስ አንቀጽ (2) እንደተብራራው ማንኛውም ሰው ክስ ሳይቀርብበበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር እንደማይችል ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን በሌሎች ሕጎች በግልፅ በተደነገጉ ሁኔታዎች የዜጎች የነፃነት መብት ሊገደብ እንሚችል የሕገ መንግሥቱ ‹‹በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ›› የሚለው አገላለፅ ያሳያል፡፡ በመሆኑም  በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ማንኛውም የወንጀል ድርጊት የፈፀመ ሰው ወይም በወንጀል ድርጊት የተጠረጠረ ሰው በፖሊስ የሚያዝበት አግባብ ሊፈጠር እንደሚችል መረዳት ይቻላል፡፡  ይህም ሲሆን ወንጀሉን የፈፀመው ሰው የሕገ መንግሥቱን ዓላማና መንፈስ በጠበቀ መልኩ ነፃነቱ መገደቡን መረዳት እንችላለን፡፡ ከዚህ በመቀጠል በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ እውቅና የተሰጣቸውና በአሁኑ ሰዓት በማገልገል ላይ የሚገኙትን ወንጀለኛን የመያዣ መንገዶችን እንዲሁም የአያያዝ ሥርዓቶች እንቃኛለን፡፡

በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ወንጀለኛን የመያዣ መንገዶች

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ወንጀለኛን በሦስት ዓይነት መንገዶች በቁጥጥር ሥር ማዋል ይቻላል፡፡ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

በፖሊስ መጥሪያ መሠረት ወንጀለኛን መያዝ

በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝ

ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝ

ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት ዓይነት ወንጀለኛን የመያዣ መንገዶች መካከል በፖሊስ መጥሪያ መሠረት የሚደረግ አያያዝ እንደ መርህ ሲቆጠር የሚቀጥሉት ሁለት መንገዶች በልዩ ሁኔታ የሚተገበሩ (exceptions) ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ በሚከተለው ጽሑፍ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ለእያንዳንዱ የመያዣ ዘዴዎች የተቀመጡ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን እናያለን፡፡

በፖሊስ መጥሪያ መሠረት ወንጀለኛን /ተጠርጣሪን/ በቁጥጥር ሥር ስለማዋል

የፖሊስ መጥሪያ ማለት በመርማሪ ፖሊስ ተዘጋጅቶ ወንጀሉን ፈፅሟል ተብሎ ለተጠረጠረው ግለሰብ በፖሊስ ጣቢያ እንዲቀርብ በዚሁ መርማሪ ፖሊስ አማካኝነት የሚላክ የመጥሪያ ወረቀት ነው፡፡ ለዚህም አግባብነት ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 25 ነው፡፡ ይህ አንቀጽ እንደሚከተለው ይነበባል፡

አንቀጽ25. የተከሰሰውን ሰው ወይም የተጠረጠረውን ሰው ስለመጥራት

አንድ ሰው የወንጀል ስራ መፈፀሙን ለማመን መርማሪ ፖሊስ ምክንያት ያለው ሆኖ በሚገኝባቸው ሁኔታች ሁሉ የተባለው ሰው ቀርቦ እንዲጠየቅ ፖሊሱ እንድትቀርብ በሚል በጽሑፍ  ትዕዛዝ ሊጠራው ይችላል፡፡

ስለዚህ በዚህ ሕግ ቁጥር መሠረት በፖሊስ ፊት እንዲቀርብ መጥሪያ የደረሰው ሰው ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ በአንቀጽ 26 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪው እንዲያዝ አስፈላጊውን ርምጃ ይወስዳል፡፡ ነገር ግን በሕጉ በአንቀጽ 25 መሠረት የመጥሪያ ወረቀት ለመስጠትና የጥሪ ወረቀት ደርሶት በፖሊስ ፊት መቅረብ ያልቻለን ሰው ለመያዝ የሚከተሉት ቅድመ ሁኔታዎች ሊሟሉ የግድ ይላል፡፡

የመርማሪው ፖሊስ በቂ ምክንያት ያለው መሆኑ

ይህም ማለት መርማሪው ፖሊስ መጥሪያ ሊልክለት የተዘጋጀው ሰው ወንጀሉን ፈፅሞታል ብሎ እንዲያምን የሚያስችለው ምክንያት ሊኖረው ይገባል፡፡ በሌላ አገላለፅ መርማሪ ፖሊስ ያለምንም በቂ ምክንያት የመጥሪያ ወረቀት በማዘጋጀት መላክ አይችልም፡፡በዋነኛነት የዚህ ቅድመ ሁኔታ አላማ የመርማሪ ፖሊሱን ሥልጣን ገደብ ለማበጀት  ታስቦ የተቀረጸ ይመስላል፡፡ ስለዚህ መርማሪው ፖሊስ  መጥሪያ የሚላክለት ሰው ወንጀሉን ፈፅሟል ብሎ እንዲያምን ያደረገውን ምክንያት በዝርዝር እንዲገልፅ ሕጉ ያስገድዳል፡፡

የመርማሪው ፖሊስ ሥልጣን ብቻ ስለመሆኑ

ከዚሁ የሕግ አንቀጽ በቀላሉ እንደምንረዳው ተጠርጣሪውን እንዲቀርብ የማዘዝ ወይም ሳይቀርብ ሲቀር የመያዝ ሥልጣን የተሰጠው ለመርማሪ ፖሊስ ብቻ ነው፡፡ ይህንንም ‹‹መርማሪው ፖሊስ›› ተብሎ ከተገለፀው የአንቀጽ 25 ክፍል መረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ አገላለፅ ከመርማሪው ፖሊስ ውጭ ያሉ ግለሰቦች ተጠርጣሪውን የመጥራት ወይም የመያዝ ሥልጣን የሌላቸው መሆኑን እንረዳለን፡፡

የመጥሪያ ትዕዝዙ በጽሑፍ የቀረበ መሆን

ከላይ ከተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎች በተጨማሪ መርማሪ ፖሊሱ የመጥሪያ ትዕዛዙን ሕጉ በሚያዘው መልኩ ማለትም በጽሑፍ ያዘጋጀ መሆኑን እርግጠኛ መሆን አለበት፡፡ ከጽሑፍ ውጭ ያሉ የመጥሪያ መንገዶች ለምሳሌ፡-የቃል መጥሪያ በሕጉ ያልተፈቀደ በመሆኑ መርማሪው ፖሊስ ሊጠቀምባቸው አይችልም፡፡ በአጠቃላይ ከላይ የተዘረዘሩትና የተብራሩት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት ሲችሉ በፖሊስ መጥሪያ መሠረት ተጠርጣሪን በቁጥጥር ሥር የማዋል ዘዴ ተግባራዊ መሆን ይችላል፡፡

በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ስለመያዝ

የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ማለት ፖሊስ ተጠርጣሪን እንዲይዝ ያስችለው ዘንድ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት የሚሰጥ ሰነድ ነው፡፡  በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 54 መሠረት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚከተሉት ሁለት መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች ሊሟሉ ያስፈልጋል፡፡

ወንጀለኛውን /ተጠርጣሪውን/ ወደ ፍርድ ቤት ለማቅረብ በሌላ መንገድ የማይቻል መሆኑ

በዚህም መሠረት መርማሪው ፖሊስ ለጥያቄ የፈለገውን ሰው አቅርቦ ለመጠየቅ በማናቸውም መልኩ ያልቻለ እንደሆነ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ መጠየቅ ይችላል፡፡ መርማሪው ፖሊስ ተጠርጣሪውን ሊይዝ የሚችልባቸው አመቺና ህጋዊ መንገዶች ካሉ ፍርድ ቤቱ የመያዣ ትዕዛዝ መስጠጥ አይኖርበትም፡፡ ለምሳሌ፡- በአንቀጽ 25 መሠረት የመጥሪያ ወረቀት ለተጠርጣሪው በመጀመሪያ ደረጃ መላክ ሲችል ይህን ሳያደርግ ቀርቶ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ መጠየቅ አይችልም፡፡

ወንጀለኛው በፍርድ ቤት መቅረቡ ፍፁም አስፈላጊ ሲሆን

ፍርድ ቤቱ የመያዣ ትዕዛዝ ከመስጠቱ በፊት የሰውየው በፍርድ ቤት ወይም በፖሊስ ፊት መቅረብ ፍፁም አስፈላጊ መሆኑን ማጣራት ይኖርበታል፡፡ ተጠርጣሪው በፖሊስ ፊት በቅረቡ በብዙ ምክንያቶች የተነሳ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ከነዚህም መካከል፡- ቃልን ለመቀበል፣ ለአካል ምርመራ፣ ለአሻራ ምርመራ፣ ማስረጃዎችን እንዳያጠፋ ለማገድ ወይም ምስክሮች ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ለማድረግ ተጠርጣሪውን በፖሊስ ወይ በፍርድ ቤት ማቅረብ አስፈላጊ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ወንጀለኛውን በፍርድ ቤት ማቅረብ  አስፈላጊ የማይሆንባቸው ጊዜዎች አሉ፡፡

ለምሳሌ፡- ጉዳዩ ተከሳሹ በሌለበት (trial in abstentia) በፍርድ ቤት መታየት የሚችል ከሆነ የማያዣ ትዕዛዝ የማይሰጥበት አግባብ ይኖራል፡፡ ሲጠቃለል ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች መሟላት መርማሪ ፖሊሱ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ እንዲያገኝና ወንጀለኛውን እንዲይዝ ያስችሉታል፡፡

ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ስለመያዝ

የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች፡- የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 21(2) አንዳንድ የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች ሲፈፀሙ ፖሊሱ ወንጀለኛውን የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ሳያስፈልገው ሊይዘው እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡ ወንጀሉ የእጅ ከፍንጅ ከመሆኑ በተጨማሪ አንቀጽ 21 (2) እና 50 እንደየቅደም ተከተላቸው የሚከተሉትን ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀምጣሉ፡፡

ወንጀሉ የክስ አቤቱታ መቅረብ የማያስፈልገው መሆን

የእጅ ከፍንጅ ወንጀሉ ከ3 ወር በማያንስ እስራት የሚያስቀጣ መሆን ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት ከላይ የተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት ሲችሉ በአንቀጽ 50 መሠረት ማንኛውም ሰው ወይም የፖሊስ ሰራዊት ባልደረባ የእጅ ከፍንጅ ወንጀል ሲፈፅም የተገኘውን ግለሰብ መያዝ ይችላሉ፡፡

የእጅ ከፍንጅ ያልሆኑ ወንጀሎች፡- የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 51(1) ፖሊስ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወንጀል አድራጊውን የሚያዝበት ሁኔታዎች በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ ይህም ማለት ወንጀል አድራጊው ወንጀሉን ሲፈፅም በአካል ያልተያዘ ቢሆንም እንኳን ፖሊስ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወንጀለኛውን የሚይዝባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ አንቀጽ ከዘረዘሩት ሁኔታዎች መካከል እጅግ አወዛጋቢና ውይይት የሚያስፈልገው ጉዳይ ቢኖር  በንኡስ አንቀጽ 1 (ሀ) ሥር ተፅፎ የምናገኘው ድንጋጌ ነው፡፡ ይህም ቃል በቃል እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

 አንቀጽ 51 (1)

ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የፖሊስ ሰራዊት ባልደረባ መያዝ የሚችለው፡-

ሀ/ ከአንድ አመት በማያንስ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ለመስራት ዝግጁ የሆነውን ወይም ሰርቷል ተብሎ በሚገባ የተጠረጠረውን ሰው፡

በዚህ አንቀጽ መሠረት ፖሊስ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወንጀለኛን ለመያዝ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት ይኖርባቸዋል፡፡

ፖሊሱ የሚይዘው ሰው ወንጀሉን መፈፀሙን በሚገባ የጠረጠረው መሆን

ወንጀሉ ከአንድ አመት በማያንስ እስራት የሚያስቀጣ መሆን ናቸው፡፡

ከዚህ አንቀጽ መረዳት እንደምንችለው የፖሊስ ሰራዊት ባልደረባ ወንጀለኛውን /ተጠርጣሪውን/ ለመያዝ የሚያስችል እጅግ የተለጠጠ ሥልጣን መጎናፀፋቸውን ነው፡፡ ምክንያቱም በ1997 ዓ.ም በወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ መሠረት አብዛኛዎቹ የወንጀል ዝርዝሮች አንድ አመትና ከዚያ በላይ የሚያስቀጡ በመሆናቸው ይህ አንቀጽ የፖሊስ ባልደረባዎች በብዙ ወንጀሎች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተጠርጣሪዎችን እንዲይዙ ሊያደርግ ያስችላል ይህ ደግሞ የፖሊስ ባልደረባዎች ስልጣናቸውን በአግባቡና በሕጉ መሠረት እንዳያከናውኑ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

የአያያዙ ሁኔታ

በዚህ ክፍል ፖሊስ ወንጀለኛውን ለመያዝ ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ ምን ምን ሁኔታዎችን ማሟላት እንዳለበት እንመለከታለን፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 56 እንደሚያስቀምጠው የመጀመሪያው የፖሊስ ስራ የሚሆነው ለመያዝ የተዘጋጀውን ሰው ማንነት በደንብ ለይቶ ማወቅ (ማጣራት) ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በመቀጠል የፍርድ ቤት የመያዝ ትዕዛዝ የተሰጠው እንደሆነ ይህንኑ ትዕዛዝ ለሚይዘው ሰው ማንበብ ይጠበቅበታል፡፡ በተጨማሪም ይህን የፍርድ ቤት የመያዝ ትዕዛዝ የሚይዘው ሰው የጠየቀው እንደሆነ ማሳየት እንዳለበት ከሕጉ መረዳት እንችላለን፡፡

ከላይ የተጠቀሱት መስፈርቶች መሟላት ሲችሉ የሚያዘው ሰው  በቃል ወይም እጁን በመስጠት እንዲያዝ ፈቃደኝነቱን ካላሳየ ፖሊሱ ሰውየውን በመንካት ወይም በመጨበጥ ለመያዝ ይችላል፡፡ ነገር ግን የሚያዘው ሰው አልያዝም ብሎ በሃይል የተከላከለ ወይም ለማምለጥ የሞከረ እንደሆነ ሁኔታው በሚፈቅደው ተመዛዛኝ ዘዴ ፖሊሱ ሰውየውን ለመያዝ ይችላል፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ፖሊሱ ሊወስደው የሚችለው ››ተመዛዛኝ ዘዴ›› ምን ያክል ነው?  የሚለው ነው፡፡ ይህም ጥያቄ  መልስ ሊያገኝ የሚችለው ተጠርጣሪ የሚያሳየውን ባህሪ ወይም ምላሽ ግምት ውስጥ በማስገባት ስለሚሆን ይህ ነው ብሎ እርግጠኛ የሆነ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የእንደራሴነት ሕግ (Agency Law) ዋና ዋና ነጥቦች
የኢትዮጵያ የይቅርታ ሕግ አንዳንድ ነጥቦች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 16 July 2024