Font size: +
25 minutes reading time (4951 words)

ስለ ወንጀል ተጎጂዎች - የአዲስ ዕይታ አስፈላጊነት በረቂቁ የወንጀል ሕግ የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ላይ

መግቢያ ፡- ተበዳዮች በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ የነበራቸው የተሳትፎ ሚና፡ ጥቅል ምልከታ

በኢትዮጵያ የወንጀል ተጎጂዎች በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ ያላቸው ሚና ከነበረበት የማማ ደረጃ በጊዜ ሂደት ‹‹ከማማ የመውረድ›› ያህል ዝቅ እያለ መጥቷል። ሀገሪቱ በዳግም የኢጣሊያ ወረራ ተፈፅሞባት ከመያዝዋ እ.እ.አ ከ 1935 ዓ.ም በፊት በወንጀል ጉዳት ደርሶባቸው በቀጥታ ተበዳይ የሆኑ ሰዎች ወይም የተበዳይ ተወካይና ቤተዘመዶች በደል ካደረሰባቸው ሰው ፍትሕን በገዛ እጃቸው ያገኙ ነበር። ተበዳይ ጥቃት ያደረሰበትን ሰው ሲፈልግ ይበቀላል፣ ሲፈልግ በፍርድ አደባባይ ይከሳል ወይም ለደረሰበት በደል ከተበዳይ ከሳ ይቀበላል። አይ ይህን ሁሉ አልፈልግም ካለም ከሁሉም ታቅቦ ፍትሕን ከእግዚአብሔር እየጠየቀ ይኖራል። በዚህ ጊዜ ምርመራ አጣርቶ ክስ የሚመሰርት የዐቃቤ ሕግ ተቋም በሀገሪቱ አልነበረም። በግለሰቦች መሀከል የሚፈጠር አለመግባባቶችን ‹‹የወንጀል›› ጉዳይ እና የግለሰቦች የፍትሐብሔር ጉዳይ ብሎ የሚከፋፍል የሕግ ስርአት ባለመኖሩ ጥቂት በሀይማኖትና በመንግስት ላይ የሚፈፀሙ በአሁኑ ሰአት የፓለቲካ ወንጀል እየተባሉ ከሚጠሩ ወንጀሎች በስተቀር ሁሉም አለመግባባቶች ላይ ግለሰቦች በራሳቸው ከሳሽ በመሆን ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤት ያቀርባሉ ወይም ፍትሕን በእጃቸው ያገኙ ነበር። ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት የሚወስዱ ከሆነ ክስ የመመስረት፣ የተጀመረን ክስ የሟቋረጥ፣ ቅጣትን በመምረጥ ተበዳይ ግለሰብ ሁሉን አድራጊ ነበር። የወንጀል ይዘት ያላቸው ጉዳዮችን ከፍትሀብሔር ጉዳዮች ጋር በማጣመር የጉዳት ካሳን መጠየቅም ይቻል ነበር። በዘመኑ የወንጀል ተበዳዮች በወንጀል ጉዳይ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤቶች ነበሩ።

ዳግም ኢጣሊያ ወረራ ፈፅሞ ለአምስት አመት ግዛቱን ባስተዳደረበት ጊዜና ኢጣሊያን በእንግሊዝ አጋዥነትና በሀገር ውስጥ በነበሩ አርበኞች ያላቋረጠ ትግል ከሀገር ሲባረር ስልጣን በቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ ቁጥጥር ስር ቢገኝም የእንግሊዝ መንግስት አስተዳደር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ ፓሊቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጣልቃ ገብነት ያደርግ ነበር። የአምስት አመቱ የኢጣሊያ የማስተዳደር ዘመን፣ የእንግሊዝ ጣልቃ ገብነትና ቆይቶም ቀዳማዊ ሀይለስላሴ በሀገሪቱ የሕግ ስርአት ላይ ማሻሻያ ማድረግ መፈለጋቸው ከ 1935-65 ዓ.ም ባለው 30 አመታት ጊዜ ውስጥ የምዕራቡ አለም ተፅእኖ ያለባቸው በርካታ የሕግ መፀሀፎች ወጥተው ተግባራዊ ሊደረጉ ችለዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ባህላዊ የሕግ ስርአትና ተበዳዮች በወንጀል ፍትሕ ስርአቱ ላይ የነበራቸው የጎላ ሚናና ተሳትፎ ከፍተኛ ተፅእኖ ውስጥ ሊገባ ችሏል።

በ 1930 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣው የተጠቃለለው የወንጀል ሕግ የ 1930 የመቅጫ ሕግ ነው። በዚህ ሕግ በርካታ የወንጀል ተግባራቶች ተከልክሎ የሚገኝ ሲሆን ወንጀልን በተበዳይ ፍቃድ መነሻነት ( upon complaint crime) እና ያለተበዳይ ፍቃድ (accusation crime) በሚል ተከፋፍሎ አልተቀመጠም። በዚህም የተነሳ በሕጉ ተመልክተው በሚገኙ የወንጀል ተግባራቶች ላይ ተበዳዮች በፍርድ ቤት በግል ክስ እያቀረቡ ሲቀጥሉ ነበር። በመሆኑም ተበዳይ የወንጀል ፍትሕ ስርአቱ ላይ ያለው ተሳትፎ በ 1930 ዓ.ም የወጣው የመቅጫ ሕግ ከወጣም ቀጥሎ ነበር።

ለመጀመሪያ ጊዜ የወንጀል ጉዳዮችን የመክሰስ ስልጣን እንዲኖረው የተቋቋመው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት በ 1942 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 29 እንዲፀና ተደረገ። ይህ ተቋም በወንጀል ጉዳዮች ላይ የመንግስትንና የህዝብን ጥቅም የሚነካ ጥሰት አለ ተብሎ ሲታሰብ በሚሰጠው መመሪያ መሰረት በፍርድ ቤት ክስ እንዲመሰርት ተደረገ። የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክፍል አሁን እንዳለው አደረጃጀት በፍትሕ ሚንስቴር ስር ሆኖ እንዲደራጅ የተደረገ ክፍል ነበር። ምንም እንኳን ክፍሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ክስ መስርቶ የመከታተል ስልጣን ቢሰጠውም ተበዳዮች በቀደመ ጊዜ የነበራቸው የወንጀል ክስ የመክሰስ ስልጣናቸው ይዘው ቀጥለው ነበር። ዐቃቤ ሕግ ክስ የመመስረት ስልጣን ያለው ትዕዛዝ ሲደርሰው እንደመሆኑ መጠን ትዕዛዝ ባልደረሰባቸው ጉዳዮች ወይም ትዕዛዝ ደርሶትም መክሰስ ባልቻለባቸው ወይም ባልከሰሰባቸው ሁሉም አይነት የወንጀል ድርጊቶች ላይ ተበዳዮች ክስ በማዘጋጀት ወደ ፍርድ ቤት ይዘው በመውሰድ ክርክር ያደርጉ ነበር። ተበዳዮች በእርቅ በጨረሱባቸው ጉዳዮች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መመስረት ይችላል ወይስ አይችልም የሚለውን አዋጁ በዝምታ ያለፈው ሲሆን በወቅቱ በነበረ ተለምዶ ግን ተበዳዮች በታረቁባቸው ማንኛውም ጉዳይ ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ የማቅረብ እድሉ እምብዛም ነበር።

በ 1957 የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግና እርሱን ተከትሎ የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ተበዳዮች በወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ ላይ ቀድሞ የነበራቸውን ሰፊ ሚናና ተሳትፎ የቀነሰ አዋጅ ነበር። የወንጀለኛ መቅጫ አዋጁ በሕጉ የተመለከቱ የወንጀል ተግባራትን በተበዳይ ፍቃድ ላይ በመመስረት የሚያስቀጡ በሚልና የተበዳይ ፍቃድ ባይኖርም የሚያስቀጡ ወንጀሎች በሚል ከፋፍሎ የደነገገ አዋጅ ነበር። በአዋጁ ያሉ አብዛኛዎቹ ድንጋጌዎችም በመደበኛ ወንጀልነት የተበዳዩን አቤቱታ የማቅረብ፣ ክስ የማስቀጠል፣ ክስ የሟቋረጥ ይሁንታን ሳይፈልጉ በመንግስት አስፈፃሚ አካላት መርማሪነትና ከሳሽነት የሚቀርቡ ወንጀሎች ሆኑ። ከዚህም በመለስ በርካታ ድንጋጌዎች በግል ክስ አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስከስሱና የሚያስቀጡ ነበሩ።

የወንጀለኛ መቅጫ ስነ/ስርአት ሕጉ የተበዳዮችን ሚና በተመለከተ ሕጉ ሲረቀቅ በተለያዩ ሰዎች በመረቀቁ የተነሳ የኮመን ሎው ወይስ የሲቪል ሎው ሀገራትን ስርአት ነው የተከተለው የሚለው ላይ ግልፅ የሆነ ምልከታ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው። ሕጉን በመነሻነት ያረቀቁት ጂ ግሬቨን የተባሉ ምሁር የሲቪል ሎው ሀገራትን ስርአት ለመከተል የሞከሩ ሲሆን በ 1942 ዓ.ም ወጥቶ በነበረው የዐቃቤ ሕግ ቢሮ ሟቋቋሚያ አዋጅ ላይ ለተበዳዮች ተሰጥተው የነበሩ ሚናዎችን መጠነኛ ማሻሻያ በማድረግ አካተው ረቂቁን አዘጋጅተው ነበር። ተበዳዮች ዐቃቤ ሕግ ክስ አልመሰርትም ባለባቸው የወንጀል ጉዳዮች ላይ በራሳቸው ክስ መመስረት እንዲችሉ፣ በግል ክስ አቤቱታ አቅራቢነት በሚያስቀጡ ድንጋጌዎች ላይ ተበዳዮች በራሳቸው ክስ መመስረት እንዲችሉ ተደርጎ ነበር። ይህ በምሁሩ ተረቆ የነበረው ረቂቅ አዋጅ በስተመጨረሻ የኮመን ሎው የሕግ ስርአትን ተከታይ በሆኑት ማቲው በተባሉ ግለሰብ ታይቶና ታርሞ የመጨረሻ አዋጅ የሆነው ረቂቅ የተዘጋጀ ሲሆን በዚህ የሥነ-ሥርዓት ሕግ ላይ ተበዳዮች የነበራቸው ሚና ቀድሞ በግሬቨን ተዘጋጅቶ በነበረው ረቂቅ ውስጥ ከነበረው ሚናቸው ዝቅ እንዲል ተደረገ። በዚህ መሰረት ተበዳይ በግል ክስ የማቅረብ የረጅም ዘመን ታሪኩ እጅግ በከፋተኛ ደረጃ እየቀነሰ መጣ። ሁሉም በግል ክስ አቤቱታ አቅራቢነትም ሆነ በመንግስት ክስ የሚቀርቡ የወንጀል ተግባራቶች ላይ ክስ መስርቶ የመከራከር ስልጣን በዐቃቤ ሕግ እንዲሆን ተደረገ። ብቸኛው ተበዳዮች ክስ በራሳቸው ማቅረብ የሚችሉት ዐቃቤ ሕግ በግል ክስ አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስቀጣ ወንጀል ላይ በቂ ማስረጃ የለም ብሎ መዝገቡን ሲዘጋው የውሳኔውን ግልባጭ ለተበዳይ በመላክ ተበዳይ በራሱ ወጭ በፍርድ ቤት ክስ እንዲያቀርብ ስልጣን በሚሰጥበት ጊዜ ብቻ ሆነ። በዚህ ጊዜም ተበዳዮች ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት ሲወስዱ ፍርድ ቤቱ ወደ ክርክር ከመግባቱ በፊት ተከራካሪ ወገኖችን ለማስታረቅ ጥረት ማድረጉ በመነሻ የሚተገበር ሆኖ ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩ በወንጀል ክስ አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስጠይቅ ፍሬ ነገር ካለው በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት በክሱ ላይ የመከራከር ስልጣንን ከተበዳዮች መውሰድ የሚችል ሆነ። ከዚህ ውጭ ባለ ሁኔታ በግል ክስ አቤቱታ አቅራቢነት በሚያስቀጡ ሆነም በመደበኛ ወንጀሎች ላይ ተበዳዮች በወንጀል ክሱ ውስጥ ተከራካሪ የሚሆኑበት እድል በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርአቱ እንዳይኖራቸው ሆነ። በዚህም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል ጉዳዮች ላይ ክስ መመስረት፣ ክስን ሟቋረጥ፣ የምርመራ መዝገብን መዝጋትና በመሳሰሉት ላይ ከፍተኛውን ድርሻ እንዲኖረው ሆነ። ተበዳዮች የነበራቸው የወንጀል ተሳትፎ ሚና ዝቅ ማለት ጀመረ። በ 1942 በወጣው የዐቃቤ ሕግ መመስረቻ አዋጅ ላይ እንዲሁም በሌሎች ሀገራት ላይ ተበዳዮች በራሳቸው ከሳሽ በመሆን የሚጫወቱትን ከፍ ያለ ሚና በ 1961 የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ስነ/ሰርአት ሕግ አሳጣ።

የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ሀገሪቱን ለአራት ዞን በመክፈል መቀመጫውን በዋና ከተማው አዲስ አበባ በማድረግ በምርመራ መዛግብት ላይ ውሳኔ የመስጠት ተግባራቶችንና ሌሎች በሕግ የተሰጡትን ስራዎች ማከናወን ጀመረ። በወቅቱ ከነበሩት ዐቃቤ ሕጎች መሀከል ፓሊስ በመሆን የዐቃቤ ሕግነትን ተግባር የሚያከናውኑት በእጅጉ ይልቁ ነበር። በተደጋጋሚ እንደሚስተዋለው ዐቃቤ ሕግ በአቤቱታ የሚቀርቡ ወንጀሎችን ክስ ባለመመስረት ተበዳዮች ላይ ቅሬታ ይፈጥር ነበር። በዚህ ጊዜ ተበዳዮች በግል ክስ አቤቱታ በሚቀርቡ ክሶች ላይ በራሳቸው የግል ክስ ማቅረብ የሚችሉት መዝገቡ በቂ ማስረጃ የለውም ተብሎ ሲዘጋና በግል ክስ ማቅረብ እንደሚችሉ የፍቃድ ስልጣን በዐቃቤ ሕግ ሲሰጥ ብቻ ነበር። ከዚህ ውጭ ባሉ በወንጀል ክስ አቅራቢነት በሚያስጠይቁ ወንጀሎች ላይ ዐቃቤ ሕግ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 42 (1)(ሀ) መሰረት የአያስከስስም ውሳኔ ሲሰጥ የግል ተበዳዩ ግልባጩ እንዲደርሰው ከሚደረግ በስተቀር ተበዳዩ በራሱ ክስ እንዲያቀርብ እድል አይሰጠውም። ያለው ብቸኛ የነበረው አማራጭ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 42(1)(ሀ) በተሰጠው ውሳኔ ላይ የውሳኔው አግባብነት ላይ አስተዳደራዊ ደረጃን በመጠበቅ ቅሬታ ማቅረብ ወይም ለፍርድ ቤት ይግባኝ ማለት ነው። ዐቃቤ ሕግ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 42(1)(ሀ) ከተመለከተው ሁኔታ ውጭ ክስ አልመሰርትም ቢል ወይም የተመሰረተ ክስን በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 122 መሰረት ቢያነሳ የዐቃቤ ሕግን ውሳኔ ፍርድ ቤት በመውሰድ እንዲታረም ለማድረግ የሚያስችል የይግባኝ ስርአት የለም። በክስ ማንሳት ሂደትም ዐቃቤ ሕግ ክሱን ማንሳት ለምን እንደፈለገ ለተበዳዩ ምክንያት እንዲገልፅ የሚያርግ ስርአት አልተዘረጋም። ያለቅድመ ሁኔታ የዐቃቤ ሕግ የበላይ ሀላፊዎች ክስ ማንሳት ይችላሉ። በቀረቡ ክሶች ላይ ተከሳሾች በነፃ ቢሰናበቱ ወይም ዝቅ ያለ ቅጣት ቢጣል በቅጣቱ ላይ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ መቅረብ አለበት ብሎ ካመነ ይግባኝ የሚያቀርብ ከሚሆን በስተቀር ይግባኝ አላቀርብም የሚል ውሳኔ ካሳለፈ የዐቃቤ ሕግን የይግባኝ አላቀርብም ውሳኔ አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ ለማስቀየር ቅሬታ ከሚቀርብ በስተቀር ተበዳዩ በራሱ ይግባኝ እንዲያቀርብ ወይም የዐቃቤ ሕግን ውሳኔ በፍርድ ቤት ይግባኝ የሚልበት ስርአት የለም። በግል ክስ አቅራቢነት በሚያስቀጡ ወንጀሎች ላይ ዐቃቤ ሕግ ተበዳዮች ክስ እንዲመሰርቱ ፍቃድ የሚሰጥበት እድል እጅግ ያነሳ ስለመሆኑ በፍርድ ቤቶች ከሚደረጉ የክርክር ሂደቶች ማየት ይቻላል።

ተበዳዮች በግል ክስ ማቅረብ እንደሚቻል የማያውቁ መሆኑ፣ ዐቃቤ ሕግ በግል ክስ እንዲቀርብ ፍቃድ መስጠት ላይ ፍላጎት አለማሳየት፣ በወንጀለኛ መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 42(1) በሚዘጉ በግል ክስ አቤቱታ አቅራቢነት በሚቀርቡ ወንጀሎች ላይ በግል ክስ በማቅረብ የሚከሰትን የጊዜና የገንዘብ ብክነት ለማስቀረት በሚል ተበዳዮች ውሳኔውን አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ በማስቀየር ዐቃቤ ሕግ እንዲከስ ማድረግ መፈለግ ተበዳዮች በግል ክስ ማቅረብን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ የሚጠቀሱ ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው። የዐቃቤ ሕግ ተቋም በ 42(1)(ሀ) መሰረት የሚሰጡ ውሳኔዎችን የተዘጋበትን ምክንያት በግልፅ በማስፈር ለተበዳይና ለሌሎች ለሚመለከታቸው ሰዎች መላክ እንዳለበት የተመለከተ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ የውሳኔው ግልባጭ ለተበዳዮች የማይደርስ ከመሆኑ ባለፈ በውሳኔው ላይ ተበዳዩ በግሉ ክስ ማቅረብ እንደሚችል አይጠቀስም። በዚህና በሌሎች በርካታ ምክንያቶች በግል ክስ አቤቱታ አቅራቢነት የወንጀል ጉዳዮችን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ክርክር ማድረግ ተግባራዊ አልሆነም ማለት ይቻላል።

በኢትዮጵያ ያሉ ተበዳዮች ከ 1930ዎቹ በፊት በነበሩ ጊዜያቶች የወንጀል ድርጊት ተፈፅሞባቸው ሲገኝ የፍትሐብሔር የካሳ ጉዳዮችን በማጣመር በቀላሉ የሚካሱበት እድል ነበር። በ 1961 በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ላይ የፍትሐብሔር ጉዳቶችን ከወንጀል ክሶች ጋር አጣምሮ ማቅረብ የሚቻልበት እድል ያለ ቢሆንም በተግባር ግን በስፋት ጥቅም ላይ ሲውል አይስተዋልም።

በጥቅሉ በኢትዮጵያ ተበዳዮች በወንጀል ፍትሕ ስርአቱ ውስጥ ክስ በማስጀመርና ባለማስጀመር፣ በወንጀል ፍትሕ ስርአት ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ፣ በወንጀል ጉዳዮች በግል ክስ በመመስረትና የፍትሐብሔር ጉዳቶችና ከወንጀል ድርጊቶች ጋር በማጣመር መክሰስና መካስ መቻል ላይ በ 1957 እና በ1961 ዓ.ም ከወጣው የወንጀለኛ መቅጫና የሥነ-ሥርዓት ሕግ መውጣት በኋላ እጅግ ዝቅ እንዲል ሆኗል። የዐቃቤ ሕግ ተቋም በወንጀል ፍትሕ ስርአት ውስጥ ከሌሎች የምርመራና የፍርድ ተቋማት ጋር በመሆን የፊት ለፊትን ድርሻን ይዟል። ተበዳዮችን ያገለለ የፍትሕ ስርአት በባለፉት ሀምሳ አመታት የወንጀል ፍትሕ ስርአቱ መገለጫ ወደመሆን እየመጣ ይገኛል። በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ የተዘረጉ የተበዳዮችን ተሳትፎ የሚፈልጉ በግል ክስ አቤቱታ አቅራቢነት በሚያስቀጡ ወንጀሎች ላይ ተበዳዮች ክስ እንዲመሰርቱ የመቻል መብት፣ በወንጀል ጉዳዮች የፍትሐብሔር የጉዳት ካሳን አጣምሮ ክስ ማቅረብ በሚፈለገው መልኩ እየተተገበሩ አይደለም።

በወንጀል ፍትሕ ስርአት ውስጥ ተበዳዮች ያላቸው ሚና ዝቅ እያለ ቢመጣም በአለምአቀፍ ደረጃ እ.እ.አ ከ 1970 ወዲህ በተለያዩ ሀገራት ስለወንጀል ተጎጂዎች መብት የሚሉ ሰፋፊ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ነበር።

የወንጀል ተግባራት በማህበረሰቡ ላይ ፍርሀትን በመፍጠር ራስን ለመከላከል የጥንቃቄ እርምጃ ለመውሰድ በሚል የመከላከያ መንገዶችን በማበጀት ኢኮኖሚያዊ ጫና ይፈጥራል። ወንጀል ይፈፀምብኛል ብሎ በመፍራት ለቤቱ በር የማይገጥም፣ አጥሩን ከቻለ በእሾህ አቅም ካለ ደግሞ ግንብ አጥሮ የኤሌትሪክ ሽቦ ቀጥሎ ካሜራም መግጠም አየተለመደ ነው። መንግስት የግብር ከፋዩን ገንዘብ በመጠቀም ወንጀልን ለመከላከል በሚል የፀጥታ ሀይል በማደራጀት፣ የወንጀል ፍትሕ ተቋማት በማደራጀት፣ ለድንገተኛ የወንጀል ተጎጂዎች የህክምናና መሰል አቅርቦት በማቅረብ፣ አጥፊዎችን ለማረም ማረሚያ ተቋማትን በሟቋቋም ከፍተኛ ወጪ ያወጣል። የወንጀል ጉዳት ማህበረሰባዊ ሲሆን በወንጀሉ ቀጥተኛና ላቀ ያለ ጉዳት የሚደርስባቸው ግን የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመባቸው ሰዎች ናቸው። የወንጀል ድርጊት ቀጥተኛ ሰለባዎች አካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊ፣ ቁሳዊ ጉዳት ይደርስባቸዋል። ከቀጥታ ከወንጀል ሰለባዎቹ ባለፈ ከወንጀል ሰለባዎቹ ጋር ቅርበት ያላቸው የተጎጂው ቤተሰብ፣ ጓደኛና ሌሎችም በወንጀል ድርጊቱ ቅርበት ያላቸው የወንጀል ተጎጂዎች ናቸው። ወንጀል በተጎጂዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በቀጥታ በወንጀሉ ከሚመጣው ጉዳት በዘለለ የወንጀል ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላ የወንጀል ፈፃሚዎቹን ለፍትሕ አደባባይ እንዲቀርብ በማድረግ ሂደት ተበዳዮች ለሌላ በደል ይጋለጣሉ። የፍትሕ ተቋማት አግባብ ያለው መስተንግዶ አለመስጠት፣ አሳታፊ ያልሆነ የምርመራና የክርክር ሂደት፣ ግልፅነት የሌለው አሰራር ተበዳዮች ላይ ድጋሚ ህመም እንዲፈጠርባቸው ያደርጋል።

ከ 1970 ዎቹ በኋላ በተለያዩ ሀገራት ሲተገበሩ የነበሩ ተበዳይ መር እንቅስቃሴዎች ተበዳዮች በፍትሕ ስርአቱ የሚፈጠርባቸውን የድጋሚ በደል ለመቀነስ ተጠርጣሪ መር ከሆነ የፍትሕ ስርአት በመውጣት የተጠርጣሪንና የተበዳዮችን መብት ያጣጠመ የወንጀል ፍትሕ ስርአት መዘርጋትን ማቀንቀን ጀመረ። በዚህም በበርካታ የሲቪል ሎውና የኮመን ሎው በሚከተሉ ሀገራት ለአብነትም ያህል በአሜሪካና በአውስትራሊያ ተበዳይ መር የሆነ መብቶችና ጥበቃዎች በሕግ እየወጣ መተግበር ጀመረ። በአለም አቀፍ ደረጃም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.እ.አ በ 1985 ዓ.ም መሰረታዊ የተበዳዮን መብት የሚመለከት ዲክላራሼን አወጣ።

 

2.ስለ ወንጀል ተጎጂዎች አዲስ እይታ መኖር ፡ መነሻዊ ምክንያቶች ከረቂቁ ሕጉ መነሻነት

2.1.ሁሉም ወንጀሎች በመርህ ደረጃ ዋስትና የማያስከለክል መሆን።

በወንጀል ተጠርጥረው የሚያዙ ወይም የሚከሰሱ ሰዎች ክርክሩ በፍርድ ቤት ተጠናቆ ውሳኔ እሲኪያገኙና በወንጀል ጥፋተኛ እስኪባሉ ጊዜ ድረስ ነፃ ሆነው ይገመታሉ። ይህ ነፃ ሆኖ የመገመት ህገ መንግስታዊ መርህ ተጠርጣሪዎች ወይም ተከሰው የሚገኙ ሰዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እስኪያልቅ ጊዜ ድረስ የዋስትና መብት እንዲከበርላቸው መሰረታዊ ምክንያት ነው። የዋስትና መብት ለማንኛውም በወንጀል ለተጠረጠረ ሰው በሕጉ የተፈቀደ ሲሆን ዋስትና በልዩ ሁኔታ በሕግ በተቀመጡ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ሊከለከል እንደሚችል የህገ-መንግስቱ አንቀፅ 19(6) ደንግጎ ይገኛል። የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ሕጉ የዋስትና መብት በመርህ ደረጃና በልዩ ሁኔታ ሊከለከልበት የሚችልበትን ስርአት በሕጉ አንቀጽ 63 እና 67 ላይ ደንግጎ ይገኛል።

በወ/መ/ስ/ስህ/ቁ 63 መሰረት ዋስትና በመርህ ደረጃ ሊከለከል የሚችለው ተከሳሽ የሚከሰስበት/የተከሰሰበት የሕግ ድንጋጌ ከ 15 አመት በላይ የሚያስቀጣ ሲሆንና በወንጀሉ ጉዳት የደረሰበት ሰው ከሞተ ሲሆን በልዩ ሁኔታ ዋስትና የሚከለከለው በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 67 ስር በተደነገጉ ሶስት ሀኔታዎች ሲሆን እነርሱም ተከሳሽ በዋስትና ቢወጣ በዋስትና ግዴታው ላይ የተመለከተውን የፍርድ ቤት ቀጠሮን እየተከታተለ የመገኘት ግዴታውን አይወጣም ተብሎ ሲገመት፣ በዋስትና ቢወጣ ሌላ ወንጀል ይሰራል ወይም ምስክሮችን ያባብላል ተብሎ ሲገመት ናቸው። ሌሎች የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌን የያዙ እንደአደገኛ ቦዘኔ አዋጅና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ዋስትና በመርህ ደረጃ የሚከለክሉበትን ድንጋጌዎች ይዘዋል። ዋስትናን በመርህ ደረጃ የወንጀሉን አይነትና ቅጣትን መሰረት አድርጎ መከልከል ኢ-ህገመንግስታዊ ነው በሚል በበርካታ ሙህራን ትችት ይቀርባል። ለዚህም መነሻው የኢፌዲሪ ሕግ-መንግስት ዋስትና የሚከለከለው በሕግ-የሚቀመጡ ሁኔታዎች ላይ ፍርድ ቤቶች ተመልክተዋቸው እነዚያ ምክንያቶች ተሟልተዋል ወይስ አልተሟሉም የሚለውን በማየት ነው የሚል ሲሆን የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 63 ሆነም ሌሎች በአዋጅ ዋስትናን በመርህ ደረጃ የከለከሉ አዋጆች ላይ የፍርድ ቤቶች ስልጣን የምክንያቶቹን መኖር አለመኖር የመመመርመር ስለጣን አልሰጣቸውም በሚል ነው። ዋስትናን በመርህ ደረጃ በከለከሉ አዋጆች የተከሰሰ ሰው ላይ ፍርድ ቤቶች ሕጉን ተግብሮ ዋስትና ከመከልከል በዘለለ የምክንያት /የሁኔታ መመርመር ውስጥ እንዲገቡ አያስችላቸውም ። በዚህም ፍርድ ቤቶች በሕግ የተመለከተን ሁኔታ በመመርመር ዋስትናና የመፍቀድና የመከልከል ህገ-መንግስታው ስልጣን እንዳይኖራቸው ተደርጓል። ይህም በህገ-መንግስቱ የተሰጣቸውን ስልጣን የሸራረፈ ነው ይላሉ።

በአዲስ መልክ በመረቀቅ ላይ ያለው የወንጀል ሕግ የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ አዋጅ ይዞ ከመጣቸው አዳዲስ ለውጦች መካከል ዋስትናን በመርህ ደረጃ ቅጣትን ወይም የወንጀል አይነትን መሰረት በማድረግ መከልከልን ሙሉ በሙሉ ማስቀረቱ ነው። ስለዚህ በረቂቅ አዋጁ መሰረት በሰው መግደል የተከሰሰ ሰው ወይም ከባድ የሙስና ወንጀል የፈጸመ ወይም ደግሞ በአደገኛ ቦዘኔነት የሚከሰስ ሰው በተከሰሰባቸው ክሶች የተነሳ ብቻ ዋስትና በመርህ ደረጃ ሊከለከል አይችልም። በተለመደው ሁኔታ ብዙውን ጊዜ በእነደነዚህ አይነት ወንጀሎች የሚከሰስ ሰው ላይ በፍርድ ቤት የዋስትና ክርክር ራሱ አይደረግም። ይህ ሁኔታ በረቂቅ አዋጁ ላይ ቀርቶ በመርህ ደረጃ ዋስትና መከልከል እንዲቀርና በሕጉ የተመለከቱ የልዩ ሁኔታዎች መከሰት ብቻ ዋስትና እንዲከለከል ሆኗል። በዚህም መሰረት እነዚህ ልዩ ሁኔታዎችን ተከሳሹ አያደርጋቸውም ወይም አይከሰቱም ተብሎ ከታሰበ በማንኛውም ወንጀል የሚከሰስ ሰው የዋስትና መብቱ ተከብሮለት ውጭ ሆኖ ክርክሩን ሊያቀርብ የሚችልበት እድል ይኖራል። ከነዚህ ልዩ ሁኔታዎች ውስጥ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተመለከቱት ውስጥ አንደኛው የተከሰሰው ሰው በዋስትና ቢለቀቅ በሕግ የተመለከተውን ግዴታ አይወጣም ተብሎ ሲታሰብ ሲሆን ሌላው ደግሞ ምስክርን ያስፈራራል ወይም ማስረጃን ያጠፋል ተብሎ በበቂ ምክንያት ሲታመን የሚሉት ናቸው።

ዋስትና በመርህ ደረጃ የወንጀሎቹን ሁኔታ አይቶ የሚከለከልበት ስርአት በቀረበት ሁኔታና በልዩ ሁኔታ ብቻ የሚከለከል ከሆነ ደግሞ እነዚህ ልዩ ሁኔታዎች በተለያየ ምክንያት ሊከሰቱ ይችላሉ ወይስ አይችሉም የሚለውን ዐቃቤ ሕግ በአግባቡ ማጣራትና መመርመር ይኖርበታል። የሚከሰሰውን ሰው ባህሪ፣ ከተበዳዮች ጋር ያለውን ቅርበትና ግንኙነት፣ ተበዳዮች ለጥቃት ያላቸውን ተጋላጭነት፣ የተከሰሰው ሰው የሀብትና የስልጣን ደረጃ፣ የማህበራዊ ሁኔታ መሰረቱ ተከሳሹ ቢለቀቅ በተበዳዮች ላይ የሚያስከትለውን ተፅእኖና ስጋት እና ሌሎችንም ሁኔታዎች ማጥናት ያስፈልጋል። በዚህ የሁኔታ ጥናት ዳሰሳ ላይ ተበዳዮች፣ የተበዳዮች ቤተሰቦች ወይም የተበዳይ ተወካዮች ሚና ከፍተኛ ነው።

በዋስትና ክርክሩ ላይ የተሟላ መረጃ በመያዝ ክርክር ለማድረግ ከተበዳይ ወገን የሚመጡ መረጃዎች፣ ስጋቶችና፣ ተከሳሹ በዋስትና ቢለቀቅ ተበዳዮች ላይ ስለሚያስከትለው አሉታዊ ተፅእኖ እና ሌሎች አስተያየቶች መስማት እጅግ ጠቃሚ ናቸው። በአዲስ መልኩ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሊጀመር የታሰበው ዋስትናን በመርህ ደረጃ ለሁሉም ወንጀሎች እንዲፈቀድ በማድረግ በልዩ ሁኔታ ብቻ መከልከል ላይ ተበዳዮች በዋስትና ክርክር ወቅት የሚኖራቸውን ተሳትፎ ከፍ እንዲል የሚደርግ ያደርገዋል። የተከሳሽ በዋስትና መለቀቅ ከተበዳይ ወገን የሚኖረውን አሉታዊ ተፅእኖ ለመገምገም የሚረዱ የተበዳዮችን አስተያየት መቀበል በዐቃቤ ሕግና በፍርድ ቤቶች ላይ በአስገዳጅነት እንዲቀመጥ መደረግን ያስከትላል።

2.2.ስለ ተጠርጣሪዎች መብት ተጨንቆ ተበዳይን ማግለል፣

በረቂቅ ደረጃ ያለው የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ በግል አቤቱታ በሚቀርቡ ወንጀሎች ላይ ተበዳዮች በራሳቸው ክስ ስለሚመሰርቱበት ሁኔታ አሁን በስራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ የሥነ-ሥርዓት ሕግ ያለበትን ክፍተት በሚሞላ መልኩ አዲስ ለውጥ ቢያመጣም ፣ በወንጀል ክርክሮች ወቅት ተበዳዮች የፍትሐብሔር ጉዳያቸውን በማጣመር ክስ ለመመስረት የሚያስችል የተሻሻሉ ድንጋጌዎችን የያዙ አንቀፆች ቢጨመሩም ተበዳዮች በምርመራ ሂደት በምን አግባብ እንደሚስተናገዱ፣ ተበዳይ በሆኑባቸው መዝገቦች ላይ የምርመራውንና የክርክሩን ሂደት በተመለከተ መረጃ ስለሚያገኙበት ስርአት፣ የተፋጠነ ፍትሕ ተበዳዮችን መሰረት ባደረገ መልኩ ስለሚገኝበት ሁኔታ፣ በኤግዚብትነት የተያዙ ንብረቶች ፈጣንና ቀልጣፋ በሆነ ሁኔታ ስለሚለቀቁበት ስርአት፣ ክብርና ድፍረት ያልተሞላበት መስተንግዶ በሁሉም ምርመራውንና ክርክሩን በሚመሩ አካላቶች ስለሚያገኙበት፣ ምርመራውን በተመለከተ ሀሳባቸውንና አስተያየታቸውን ስለሚሰጡበት፣ በፓሊስ ወይም በዐ/ሕግ ስለሚደረጉ የዋስትና ክርክሮች ላይ አስተያየት ስለሚሰጥበት ስርአት፣ ተበዳዮች በሚደረስባቸው የስነ-ልቦና ጉዳት ላይ ስለሚያገግሙበት ሁኔታ እርዳታ በመንግስት ስለሚሰጥበት ሁኔታ፣ በመዝገብ ላይ የሚሰጡ የውሳኔዎችን ይዘት አስቀድሞ ስለሚያውቁበትና ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ውሳኔውን በአስተዳደራዊ ወይም በፍርድ ቤት ቅሬታ ስለሚቀርብበት ሁኔታ፣ በፍርድ ቤት ተበዳዮች ላይ በሚቀርቡ መስቀለኛ ጥያቄዎች ተበዳዮች የዳግም ጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ ስለሚቻልበት ስርአት፣ የፍርድ ቤት ቀጠሮን በቀላሉ አውቀው ክትትል እንዲያደርጉ ስለሚችሉበት ሁኔታ፣ በሚቀርቡ የቅጣት አስተያየቶች ላይ ሀሳባቸውን ስለሚሰጥቡት ሁኔታ፣ የገደብ መለቀቅ አቤቱታ ላይ ተበዳዮች ስለሚሳተፉበት ስርአትና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የተበዳዮች ተሳትፎ ላይ ምንም አይነት የመብት ጥበቃ ሳይደረግ ተጠርጣሪዎች በተቃራኒው ሰፊ የሕግ መብትና ጥበቃ እንዲያገኙ ተደርጓል።

በግልና በወንጀል ክስ አቅራቢነት በሚያስቀጡ ወንጀሎች ላይ ዐቃቤ ሕግ ምርመራውን በመምራትና በመከታተል የተበዳዮችን መብት በማስጠበቅ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ቢታሰብም በተለያዩ ምክንያቶች የወንጀል ፍትሕ ስርአቱ ውጤታማ እንዲሆን የወንጀል ተጎጂዎች የሚኖራቸው ሚና የማይተካ ነው። ወንጀል ጉዳቱ ማህበረሰባዊ ነው ቢባልም ከማህበረሰቡ ክፍሎች ውስጥ ያሉ ግለሰብ ተጎጂዎች በወንጀል ድርጊቱ የሚደርስባቸው ሁሉ አቀፍ ተፅዕኖና ጉዳት ግን ሌላው ላይ ከሚደርሰው የላቀ ነው። በዚህም የሥነ-ሥርዓት ሕጎች ለተከሳሽ ወይም ለተጠርጣሪዎች ከሚሰጡት መብት በእኩሌታው ለተበዳዮች መብትና ጥቅም መጠበቅ ስርአት ሊያበጁ ይገባል።

በረቂቅ ደረጃ ያለው የወንጀል ሕግ የሥነ-ሥርዓት የማስረጃ ሕግ በተግባር በምርመራ ሂደት ተጠርጣሪዎችና ተከሳሾች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከልና በምርመራ እውነትን ለማውጣት፣ ምርመራ ህጋዊነቱን ጠብቆ እንዲከናወን ለማድረግ የሕግ ከለላ በሰፊው ሰጥቶ ይገኛል። ተጠርጣሪዎች በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሆነው እስኪገኙ ጊዜ ድረስ ነፃ ሆነው የሚገመቱ ሲሆን ዐቃቤ ሕግም ለሚከሰው ክስ በበቂ ሁኔታ በሕግ በተፈቀደ መንገድ የተገኘ ማስረጃ አቅርቦ የማስረዳት ግዴታ ተጥሎበታል። ተከሳሽ ራሱን ለመከላከል የሚችል ሲሆን በራሱ ላይ እንዲመሰክር ወይም ወንጀሉን እንዲያምንም አይገደድም። በአንድ ወንጀል ድጋሚ ክስ የተከለከለ ሲሆን በወንጀል ተጠርጥረው የሚያዙ ወይም የሚከሰሱ ሰዎች በሕግ ፊት ያለምንም ልዩነት ይስተናገዳሉ። ማንም ሰው ወንጀል ስለመፈፀሙ በቂ ጥርጣሬ ሳይኖር የማይያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰርም እንደማይችል ተደንግጎ ይገኛል። ኢ-ሰበአዊ አያያዝ በተያዙና በታሰሩ ሰዎች ላይ መፈፀም እንደማይቻል በመርህ ደረጃ በረቂቅ ሕጉ ላይ የተመለከተ ሲሆን በራሳቸው ጠበቃ ማቆም ለማይችሉ ከ 10 አመት በላይ በሚያስቀጣ ወንጀል ለተከሰሱ ሰዎች የግዴታ ጠበቃ እንዲቆም የሚደረግ ሲሆን የተጠረጠሩ ሰዎች በራሳቸው ቢከራከሩ ፍትሕ ሊዛባ ይችላል ተብሎ በሚታሰብበት ጊዜ በዋናነትም ወጣት አጥፊ የሆነ ሰው፣ የጥፋተኝነት ድርድር ሲደረግ በመንግስት ጠበቃ መወከል እንደግዴታ ሆኖ በሥነ-ሥርዓት ሕጉ ላይ ተመልክቶ ይገኛል። በምርመራ፣ በክስና በፍርድ ሂደት ፈጣን ውሳኔ መስጠት፣ ጉዳዮች በግልፅ ችሎት እንዲዳኙ ማድረግ፣ በሁሉም ሂደቶች ተጠርጣሪዎች ወይም ተከሳሾች በሚገባቸው ቋንቋ ሂደቶች እንዲከናወኑ ማድረግ፣ እውነትን ማውጣትን መሰረት ያደረገ፣ ያልተራዘመ የምርመራ ሂደትን የሚከተል ምርመራና የፍርድ ሂደት መከተልን ተጠርጣሪዎች ወይም ተከሳሾች ከብዙ በጥቂቱ በረቂቅ ሕጉ ላይ የተጎናፀፏቸው መብቶች ናቸው።

የፍትሕ ተቋማት በዋናነትም የፓሊስ ተቋም፣ ዐቃቤ ሕግና ፍርድ ቤቶች፣ የማረሚያ ተቋማቶችና የተከላካይ ጠበቆች በስራቸው ሂደት በሕጉ በመርህነት የተመለከቱ ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ መር የሆኑ መርሆችንና ሌሎች ግዴታዎችን አክብረው መስራት እንደግዴታ የተጣለባቸው ሲሆን ረቂቅ ሕጉ ከተጠርጣሪዎች መብት ጎን ለጎን የተጠርጣሪ መብት በማይጎዳ መልኩ የተመዛዘነ መብት ለተበዳዮች በጉልህ ደረጃ የሚሰጥ አይደለም ።

የወንጀል ተጎጂዎች በሚፈፀምባቸው የወንጀል ተግባር አካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊና የቁስ ጉዳት ያጋጥማቸዋል። በፍርሀት የመኖር፣ ድብርት፣ ጥቃት ይደርስብናል ብሎ መስጋት፣ ዘላቂ የሆነ ጤናማ ግንኙነት ለመፍጠር ያለመፈለግ ስነ-ልቦናዊ ጫና ይፈጠርባቸዋል። አካላዊ ጥቃቶች ጊዜያዊ ህመም ከመፍጠር በዘለለ የአካል ጉዳት እክል እንዲፈጠር በማድረግ እስከ ሞት የሚደርስ ጉዳትን ያስከትላሉ። በወንጀል ተግባር የንብረት ውድመት ከመድረስ ባለፈ፣ በንብረት የሚገኝ ጥቅምን ተበዳዮች የሚያጡ ሲሆን በቀጣይ በሚደርስባቸው ስነ-ልቦናዊ ጫና የተነሳ በስራቸው ላይ ምርታማ እንዳይሆኑ በማድረግ የገቢ መታጣት ጉዳትን ያስከትላል። የወንጀል ጉዳት በቀጣይነትም ወንጀሉ ከተፈፀመ በኋላ ወንጀሉን መርምረው ለፍትሕ በሚያቀርበው ፓሊስ፣ ክስና ውሳኔ በሚሰጠው ዐቃቤ ሕግ፣ ክርክሩን በሚመራው ፍርድ ቤት ባሉ የስርአት ጉድለቶች የወንጀል ተጎጂዎች ለዳግም ጥቃት ሰለባነት ይዳረጋሉ። ይህ ጉዳት ለወንጀል ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ህፃናትና ሴቶች ላይ እጅግ የከበደ ይሆናል።

በምርመራ ሂደት ለተበዳዮች ተገቢውን ክብር በመስጠት ባለማስተናገድ፣ ለተበዳዮች የምርመራውን ሂደት በተመለከተ ወቅታዊ መረጃ ባለመስጠትና ለመስጠትም ባለመተባበር፣ ተበዳዮች ለሚደርስባቸው ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ህክምና የሚያገኙበት በመንግስት የተመቻቸ ማገገሚያ አለመኖር፣ ለደረሰባቸው የንብረት ጉዳት ካሳ በቀላሉ ሊካሱበት የሚችል ስርአት ባለመኖሩ፣ በምርመራው ሂደትና አቅጣጫ ላይ የሚሰጡትን አስተያየት አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ የሚሰማበት ስርአት ባለመበጀቱ፣ በዋስትና ክርክር ላይ ሀሳብና አስተያየታቸውን ለመቀበል የሚያስችል በሕግ የታሰረ አሰራርን ምርመራውን በሚያከናውነውም ሆነ ክስ በሚያቀርበው አካል እንዲሰማ አለመደረጉ፣ በዐቃቤ ሕግ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ተበዳዮች ምንም አይነት ሚና እንዲኖራቸው አለመደረጉና የዐ/ሕግን ውሳኔ ፈጣን በሆነ ሁኔታ፣ ያለምንም ወጪ እንዲያውቁ የሚደረግበት ስርአት አለመኖሩ፣ በሚወሰኑ ማንኛውም አይነት ውሳኔዎች ላይ ፈጣንና ቀልጣፋ አስተዳደራዊ ወይም ፍርድ ቤት መር የይግባኝ አቀራረብ ስርአት አለመኖሩ፣ የተያዙ የግል ተበዳይ ንብረቶች ለረጅም ጊዜ ተይዘው መቆየት ወይም እስከነአካቴው ያለመመለስ፣ በተጠርጣሪ ወይም በተጠርጣሪ ቤተሰቦችና ጓደኞች የሚፈጠሩ ማስፈራራቶችና ዛቻዎች፣ ለማስፈራሪያውና ዛቻው በቂ ጥበቃ አለማግኘት፣ በቤተሰብና በማህበረሰቡ ዘንድ በቂ ድጋፍ እንዲያገኙ አለማድረግ፣ በፍርድ ቤቶች በመስቀለኛ ጥያቄ ሰበብ እንዲሸማቀቁ የሚያደርግ ክብር የሌለው ጥያቄ በተከሳሾች እንዲጠየቁ መፍቀድ፣ የተበዳዮች ጉዳይ በሚዲያ በተፈለገው መልኩ ያለስርአት እንዲቀርብ መደረግ፣ ተከሳሽ በገደብ ሲለቀቅ የተበዳዮችን ሀሳብ ያለመቀበል፣ በምህረትና በይቅርታ አሰጣጥ ተበዳዮች በበቂ ሁኔታ እንዲሳተፉና ሀሳባቸውን እንዲሰጡ የሚያደርግ ስርአት አለመኖር፣ ወንጀሉ ያደረሰባቸውን ሁሉአቀፍ ጉዳት እንደፈለጉ ሀሳባቸው ሳይቆራረጥ በፍርድ ቤት እንዲገልፁ ያለማድረግና ይህን ጥበቃ የሚያደርግ ስርአት አለመኖርና በሌሎችም አጠቃላይ ጉዳዮች በሚሄዱበት ሂደት ላይ መረጃ የሚያገኙበት፣ ሀሳባቸው የሚጠየቅበት፣ መብታቸው የሚከበርበት በቂ የሕግ ስርአት ባለመኖሩ የተነሳ ተበዳዮች ለዳግም የመንፈስ መረበሽ፣ የደህንነት አለመሰማት፣ የፍትሕ ማጣትና የተበዳይነት ስሜት እንዲጋለጡ ይደረጋሉ።

ይህን የዳግም ተበዳይነት ችግር ለመፍታት፣ ለተጠርጣሪዎች ወይም ለተከሳሽ ያጋደለውን ስርአት የተጠርጣሪዎችን መብት ባልጎዳ መልኩ ለተበዳዮች መብት፣ ጥበቃና ተገቢውን ተሳትፎ በሚሰጥና በሚያረጋግጥ መልኩ በረቂቅ የወንጀል ሕግ የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕጉ እንዲካተት ማድረግ በእጅጉ ያስፈልጋል።

2.3.አማራጭ የግጭት መፍቻ መንገዶች ፡ የባህላዊ እርቅ እውቅና፣ የጥፋተኝነትና የቅጣት ድርድር ስርአት መጀመር።

በረቂቅ ሕጉ ላይ በአዲስ መልኩ ከተካተቱ ስርአቶች ውስጥ ባህላዊ የእርቅ መፍቻ መንገዶችና የድርድር ስርአት መጀመር ሲሆን የነዚህ ስርአቶች መጀመር የወንጀል ተጎጂዎች በወንጀል ፍትሕ ስርአት ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ከፍ እንዲል የሚያስገድድ ነው።

3.የወንጀል ተጎጂዎች በረቂቁ የወንጀል ሕግ የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ውስጥ ሊኖራቸው ስለሚገባ ጥበቃ።

3.1.የወንጀል ተጎጂዎች የተሳትፎ መብት በምርመራ ሂደት፡

  1. የምርመራውን ሂደት ማሳወቅ፡- ምርመራውን የመመርመር ስልጣን ያለው ፓሊስም ሆነ ምርመራውን የሚመራው ዐቃቤ ሕግ የምርመራውን ሂደትና በምርመራው እየታዩ ያሉ ለውጦችን፣ እንዲሁም ለምርመራው አስቸጋሪ የሆኑ ተግባራትን ለተበዳዮች ማሳወቅ የሚገባቸው ሲሆን ይህም በረቂቅ ሕጉ እንደግዴታ ሊቀመጥ ይገባዋል። የምርመራን ሂደት የማሳወቅ ተግባር የምርመራው ቀጣይነትና ሚስጥራዊነት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳይኖረው ግን ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባዋል።
  2. በምርመራ ሂደት ተበዳዮች ክብር በተሞላት ሁኔታ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ፡-

በሚጣሩ የወንጀል የምርመራ መዝገቦች ላይ ተበዳዮች ማስረጃ ከመሆን በዘለለ የጉዳዩ ባለቤት እንደሆኑ ተቆጥረው የተበዳዮችን ቃል መቀበል ጊዜ፣ ሌሎች ምስክሮች ቃል ሲሰጡ ከመከታተል አንፃር፣ ተጠርጣሪዎች ሲያዙና ቃል ሲሰጡ እንዲከታተሉ በማድረግ ልዩ በሆነ ሁኔታ ክብራቸው ተጠብቆ፣ ያልተገባ የድፍረት መስተንግዶ ሳይቃጣባቸው ሊስተናገዱ ይገባል። ይህ በመርማሪ ፓሊስ ብቻ ሳይሆን፣ ውሳኔ የሚሰጠው ዐቃቤ ሕግም ሆነ ክርከሩን የሚመራው ፍርድ ቤት ላይ መጣል የሚኖርበት ግዴታ ሊሆን ይገባዋል።

  1. በምርመራ ስራዎች ላይ ምክር የመስጠት መብት

ተበዳዮች እየተከናወነ ባለ ምርመራ ምርመራው እየሄደበት ባለው አቅጣጫ ላይ ምክርና አስተያየት ሲሰጡ ምርመራውን የሚያጣሩና ምርመራውን የሚከታተሉ የስራ ክፍሎች ምክሮቹን የመስማት ግዴታ እንዲኖርባቸው ማድረግ የሚገባ ሲሆን የሚሰጡት ምክርና አስተያየት ለምርመራው ከሚኖረው ፋይዳ አንፃር እየታየ ሊመዘን የሚገባው መሆን አለበት።

  1. ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ ማስረጃ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን በተበዳይ በኩል መረጃ ሲሰጥ የማጥራት ስራ መስራት፣ ተጠርጣሪዎችና ምስክሮች ቃል ሲሰጡና ምርመራ ሲደረግባቸው የመከታተልና የማናገር መብት እንዲኖራቸው ማድረግ።
  2. ፓሊስ የተጠናቀቁ የምርመራ መዝገቦችን ለዐ/ሕግ ሲልክ ለተበደሉ ሰዎች የማሳወቅ ግዴታና ዐቃቤ ሕግም በምርመራ መዝገቡ ላይ የሚወስነውን ማንኛውንም አይነት ውሳኔ ለተበዳዮች እንዲያሳውቅ ማድረግ። የምርመራ መዝገቦች ከተጠናቀቁ በኋላ በምርመራ መዝገቡ ላይ የመጨረሻ የሆነ ውሳኔ የመስጠት ሀላፊነት የዐቃቤ ሕግ ሲሆን መርማሪ ፓሊስ የምርመራ መዝገቡን ለውሳኔ ወደ ዐቃቤ ሕግ ሲልክ መላኩን ለግል ተበዳዩ የማሳወቅ ግዴታ ሊኖርበት ይገባል። ከዚህም ባለፈ በምርመራ መዝገቡ ላይ ውሳኔ የሚሰጠው ዐቃቤ ሕግ ውሳኔውን ከመወሰኑ በፊትም ሆነ በኋላ የሚወሰነውን ማንኛውንም ዐይነት ውሳኔ ለግል ተበዳይ የማሳወቅ ግዴታ ሊጣልበት ይገባል።
  3. የጥፋተኝነትና የቅጣት ድርድር ስርአት ላይ ተበዳዮች ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ።
  4. የውሳኔ ግልባጭ ለተበዳይ እንዲደርስ ማድረግ

በዐቃቤ ሕግ የሚወሰነው ውሳኔ ከክስ ውጭ ያለ ውሳኔ ሲሆን የውሳኔውን ይዘት በዝርዝር የሚያሳይ ግልባጭ ያለምንም ወጪ ለተበዳዮች እንዲደርስ ማድረግ ይገባል። ለተበዳዮቹ ውሳኔው በምን ያህል ጊዜ መሰጠት እንዳለበት ስታንዳርድ ከማስቀመጥ በዘለለ በውሳኔው ላይ ቅሬታ የሚኖር ከሆነ ለቅሬታው መፍተሔ ለመስጠት የሚረዳ አስተዳደራዊ ተቋም ማደራጀት ወይም ፍርድ ቤት መር የሆነ የቅሬታ ስርአት መዘርጋት ይገባል። የቅሬታ አፈታት ስርአቱም ግልፅ፣ ፈጣን፣ በስርአት የሚመራ እንዲሆን ሊሆን ይገባል። ይህ አይነት ለተበዳዮች ጥቅም የሚሰጥ ስርአት በረቂቁ ሕጉ ውስጥ ሊካተት ይገባል።

  1. በኤግዚቢትነት የተያዙ ንብረቶች ሳይዘገዩ ተመላሽ እንዲሆኑ የሚያስችል ግዴታ መጣል፡-ከተበዳዮች እጅ የሚገኝ ንብረት ወይም ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ የተበዳዮች ንብረት በፓሊስ ቁጥጥር ስር ከገባ የባለቤትነቱ ጉዳይ ላይ አከራካሪነት የሌለው ከሆነ ፈጣን በሆነ መልኩ ማስረጃው በተለያየ መንገድ እንዲያዝ በማድረግ (በፎቶ፣ በቪዲዮና በመሳሰሉት) ስርአት ባለው መንገድ ለተበዳዮች ተመላሽ መሆን እንደሚገባ የሚደነግግ ስርአት በረቂቅ ሕጉ ላይ ሊኖር ይገባል።
  2. ተጨማሪ ጥቃት እንዲጠበቁ ማድረግ፡-ተበዳዮች ከተጠርጣዎች ወይም ከተጠርጣሪ ጋር ግንኙነት ባላቸው ሰዎች ሊደርስባቸው ከሚችል ወይም ከደረሰባቸው ጥቃት የሚጠበቁበት ጠንካራ ስርአት ሊኖር ይገባል። ምርመራውን የሚያከናውኑና የሚከታተሉ አካላቶች ከጥቃት ጋር በተያያዘ አቤቱታ ሲቀርብላቸው ፈጣን የሆነ ምላሽ ትኩረት በመስጠት ሊያከናውኑ የሚችሉበት ግዴታ ሊጣልባቸው ይገባል።
  3. ተበዳዮች የስነ-ልቦና ህክምና ክትትል እንዲያገኙ ማድረግ፣ -የወንጀል ድርጊቱ ከፍ ያለ የስነ-ልቦና ችግር በተበዳዮች ላይ ካስከተለ ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚረዳ የህክምና እገዛ በመንግስት ወጪ ለተበዳዮች ሊመቻች ይገባል። በተለይም ከፍ ያለ የስነ-ልቦና ቀውስ የሚያስከትሉ እንደ ከባድ ውንብድና፣ የፆታዊ ጥቃት ወይም የአካላዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ የግል ተበዳዮች የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ በረቂቅ ሕጉ ላይ ለአስፈፃሚ አካላቶች እንደግዴታ ሊቀመጥ ይገባል።
  4. የደረሰባቸውን ጉዳት የሚካሱበትን መንገድ እንዲመቻች ማድረግ።
  5. በግል አቤቱታ አቅራቢነት በሚቀርቡ ክሶች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ አላቀርብም ሲል ተበዳዮች በራሳቸው ክስ የሚያቀርቡበትን ስርአት በሚሰራ መልኩ ማበጀት። በግል ክስ አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስቀጡ ወንጀሎች ላይ ዐቃቤ ሕግ በተለያየ ምክንያት ክስ አላቀርብም በሚልበት ጊዜ ተበዳዮች የከሳሽነት ስልጣን እንዲኖር ማድረግ። በሌሎች ሀገራት በግል ክስ ከሚያስቀጡ ወንጀሎች ውጭ ባሉ ሌሎች የወንጀል ድርጊቶች ላይም ዐቃቤ ሕግ ክስ አልመሰርትም በሚልበት ጊዜ ተበዳዮች የመክስሰ ስልጣን እንዲያገኙ የሚደረግ ሲሆን ይህ ልምድ በረቂቁ ሕጉ ላይም ታሳቢ ሊደረግ ይገባዋል።
  6. በሚዲያ በሚሰጡ መግለጫዎች ላይ መግለጫ ከመሰጠቱ በፊት ተበዳዮች አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ማድረግ። በምርመራ ክፍልና በዐቃቤ ሕግ ቢሮ የተፈፀሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ለሚዲያ የሚሰጡ መግለጫዎች በግል ተበዳዮች ወይም በህብረተሰቡ ላይ ተጨማሪ ከፍ ያለ የስነ-ልቦናና ሌሎች ጫናዎችን እንዳያስክትሉ ከፍ ያለ ጥንቃቅ ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይም ከፆታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ላይ ወይም በአሰቃቂ ሁኔታ የሰው ህይወት በጠፋባቸው የወንጀል ድርጊቶችን ዝርዝር የሚዲያ ሀተታ ማቅረብ ተበዳዮች በደላቸውን ደጋግመው እንዲያስቡት፣ ሀፍረት እንዲሰማቸው ከማድረግ ባለፈ ማህበረሰቡ ያልተገባ ፍርሀትና ስጋት ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል። በዚህም በረቂቅ ሕጉ ለሚዲያ የሚቀርቡ ዘገባዎች የግል ተበዳዮችን፣ የማህበረሰቡንና፣ የተጠርጣሪዎችን ወይም የተከሳሾችን መብት በምን አግባብ ባጠጣመ መልኩ ሊሰጥ እንደሚችል ስርአት ሊደረግበት ይገባል።
  7. የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት ለተበዳዮችም። አሁን በስራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ስነ -ስርአት ሕግ አንቀፅ 37 የተፋጠነ ፍትሕ መብትን ለተጠርጣሪዎች የሰጠ ነው። በረቂቅ ደረጃ ያለው የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግም ምርመራ ፈጥኖ መከናወን የሚገባው ለተጠርጣዎች የተፋጠነ ፍትሕን እንዲያገኙ ከማድረግ መርህ እንፃር እንደሆነ ደንግጎ ይገኛል። ተጠርጣሪዎች በተለያየ ምክንያት የተፋጠነ ፍትሕ እንዲገኝ ባይፈለጉና ምርመራው እዲራዘም ቢፈልጉስ ? ለተበዳዮች እንደመብት የተፋጠነ ፍትሕ ይሰጠኝ የሚል ግዴታ በሕጉ ሊቀመጥ አይገባም ወይ የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል። የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት የተጠርጣሪ መብት ብቻ ሳይሆን ተበዳዮችም ሊጎናፀፉት የሚገባ መብት ነው። በእርግጥ የተፋጠነ ፍትሕ ለተጠርጣሪ መስጠት በተዘዋዋሪም ቢሆን ለተበዳዮችም ጥቅም ይሰጣል ቢባልም እደመብት ግን ለተጠርጣዎች በተሰጠ የተፋጠነ ፍትሕ መብት ላይ ተበዳዮች መጠየቅ የሚችሉ አይሆኑም። ተበዳዮች ራሳቸውን ችለው የመብቱ ተጠቃሚ መሆን ደግሞ ይገባቸዋል። ረቂቅ ሕጉ ከዚህም አንፃር ለተበዳዮች የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት ሊሰጣቸው ይገባል።

3.2.የወንጀል ተጎጂዎች የተሳትፎ መብት በክርክር ሂደት

  1. በግል ክስ አቅራቢነት የሚቀርብ ክስ ላይ የተበዳዮች የተሳታፊነት ሚና። በግል ክስ አቅራቢነት በሚቀርቡ ክሶች ላይ ዐቃቤ ሕግ በተለያዩ ምክንያች ክስ ለመመስረት ሳይፈልግ ወይም ሳይችል ሲቀር ተበዳዮች በራሳቸው ሀላፊነት ክስ የሚከሱበት ሊሰራ የሚችል ስርአት ሊዘረጋ ይገባዋል። ይህ መብት ከግል ክስ አቤቱታ አቅራቢነት ውጭ ባሉ ሌሎች ወንጀሎች ላይም ቢሆን ዐቃቤ ሕግ መክሰስ የማይችል ከሆነ መብቱን ለተበዳዮች በመስጠት የግል ክስ የሚዳብርበት ሁኔታ ታሳቢ ሊደረግ ይገባል።
  2. ጥብቅ የዋስትና ሕግ እንዲኖር ማድረግ

በወንጀል የሚጠረጠሩ ሰዎች በመርህ ደረጃ ንፁህ ናቸው ተብሎ ይገመታሉ። በዚህም ምክንያት ለሁሉም ተጠርጣሪዎች በሚባል ደረጃ አብዛኛዎቹ ወንጀሎች ዋስትና ሊፈቀድላቸው ይገባል። በውስን ሁኔታ ግን ዋስትና በመርህ ደረጃ ክልከላ እንዲኖር መደረጉ ለተበዳዮች ብቻ ሳይሆን ለሚጠረጠሩና ለሚከሰሱ ሰዎችም ጭምር ጠቀሜታ ይኖረዋል። በተለይም ታስቦ በሚፈፀሙ የሰው መግደል ወንጀሎች፣ ሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሱ ከባባድ ወንጀሎች ላይ ዋስትና በመርህ ደረጃ የማይከለከል ከሆነ ተበዳዮች በፍትሕ ስርአቱ ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርግ ከመሆኑ ባለፈ ተበዳዮች በፍትሕ ስርአቱ በሚኖራቸው የማይተካ ሚና ላይ ከፍ ያለ አሉታዊ ተፅእኖ ያስከትላል። ከባባድ በሚባሉ ወንጀሎች ላይ በምርመራ እውነታን በቀላሉ እንዲወጣ ለማድረግም መንገዱ እጅግ ከባድ እንዲሆን ያደርገዋል። ከዚህ አንፃር በውስን ወንጀሎች ላይ ዋስትና በመርህ ደረጃ ክልከላ ሊደረግበት ይገባል።

በሌላ በኩል በልዩ ሁኔታ ዋስትና በሚከለከልበት ሁኔታ ላይም የግል ተበዳዮች በተከሳሽ ወይም በተጠርጣሪ የቀድሞ ባህሪና ሁኔታ ላይ፣ ስለአኗኗሩና ስለቤተሰባዊ ሁኔታው፣ አስቀድሞ ስለነበራቸው ግንኙነት፣ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠርጣሪው ተበዳዩ ላይ ስለፈጠረባቸው ወይም ስለሚፈጥርባቸው ተፅእኖ፣ በዋስትና ቢለቀቅ ስለሚያስከትለው የስነ-ልቦናና መሰል ጫናዎች እናም በሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ የተጠርጣሪዎችን መብት ባላጠበበ መልኩ ተበዳዮች አስተያየታቸውን ለፓሊስ፣ ለዐቃቤ ሕግና፣ ለፍርድ ቤት እንዲገልፁ የሚያስችል ስርአት መዘርጋት ይገባል። የዋስትና አፈቃቀድ ስርአትም በዘፈቀደና ለተጠርጣሪዎች ወይም ለተከሳሾች መብት ብቻ ታሳቢ በማድረግ መፈፀም የማይገባው ሲሆን አስፈላጊውን አይነት ሀሳብ ለመስማትና ማስረጃ ለመመርመር ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ገለልተኛ ሆነው እንዲያዩ ለማድረግ የሚያስችል ራሱን የቻለ ችሎትም ማደረጃት አስፈላጊ ከሆነ በዚያ አግባብ የሚደራጅ ችሎት እንዲኖር ማድረግ ይገባል።

ከዋስትና መብት በመርህ ደረጃ ለሁሉም ወንጀሎች መፈቀድ ጋር ተያይዞ በጥብቅ ሊታሰቡባቸው ከሚገቡ ነገሮች ውስጥ ተጠርጣሪዎች በቀጣይ በክርክሩ ሂደት እንዲገኙና ሌሎች ተጨማሪ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችሉ ስርአቶችን መዘርጋት ይገኝበታል። ከዚህም ውስጥ ከሀገር እንዳይወጡ እግድ መስጠት፣ ከተወሰነ ክልል ውጭ እንዳይንቀሳቀስ ማገድን፣ ማስረጃ ሊያጠፋ በሚችልባቸው የተወሰኑ ቦታዎች እንዳይደርስ ማገድን፣ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ አግባብ ላለው የምርመራ አካል ሪፓርት እንዲያደርግ ማድረግና ሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎች በሕጉ ውስጥ ሊደነገግ ይገባዋል።

  1. አስፈላጊ ሲሆን የችሎት ክርክሮች በዝግ እንዲሆኑ ማድረግና ተበዳዮች በቀላሉ የፍርድ ቤት ቀጠሮን እንዲያውቁ የሚያስችል ስርአት መዘርጋት።

ችሎቶች በግልፅ ችሎት እንዲሆኑ መደረጉ ዳኛች ስራቸውን በግልፅነት ህዝብ እየተመለከታቸው እንዲሰሩ በማድረግ የተጠያቂነት ስርአትን በአግባቡ ለማስፈን ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። ሁሉም የክርክር ሂደቶች በግልጽ ችሎት እንዲሆኑ ማድረግ ደግሞ በውስን ጉዳዮች ላይ በተበዳዮችና በምስክሮች ላይ ከፍ ያለ አሉታዊ ተፅእኖ ሊኖረው ይችላል። የተከራካሪዎችን የግል ሀይወት፣ የህዝቡን ሞራል የሚነካና የሀገር ደህንነትን ለመጠበቅ ሲባል ችሎቶች ዝግ እንዲደረጉ የሚደረግ መሆኑ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 20(1) ላይ የተቀመጠ ቢሆንም ይህንን ድንጋጌ ለተበዳይ በሚሰራ መልኩ አስፋፍቶና አብራርቶ በሥነ-ሥርዓት ሕጉ ውስጥ ማስቀመጥ ይገባል። ተበዳዮች በተለይ ለህዝብ ግልፅ በሚሆኑ መረጃዎች የተነሳ ለዳግም በደል የሚጋልጡበት ብዙ ሁኔታዎች ያሉ በመሆኑ እነዚህን ሁኔታዎች በግልፅ ችሎት ጉዳዮችን ማየት የሚያስገኘውን ጥቅም ባመዛዘነ መልኩ በሥነ-ሥርዓት ሕጉ ውስጥ አስገዳጅ ድንጋጌ እንዲኖር በማድረግ ተበዳዮችን መጠበቅ ይገባል።

  1. የሚቀርቡ የመከላከያ ማስረጃዎች እነማን እንደሆኑ ማሳወቅ። መከላከያ ማስረጃ ሆነው የሚቀርቡ ሰዎች እነማን እንደሆኑ ዐቃቤ ሕግ አስቀድሞ የመከላከያ ማስረጃ ዝርዝር ሊደርሰው ይገባል። የማስረጃ ዝርዝር አስቀድሞ የመድረስ መብት በክርክሩ ለሚሳተፉ ሰዎች አስቀድመው ዝግጅት እንዲያደርጉ በማድረግ አስፈላጊውን ጥያቄ ለመጠየቅ እንዲረዳ ያደርጋል። እውነትን በማውጣት ሂደት መስቀለያ ጥያቄ መጠየቅ እስካሁን ካሉ መንገዶች የራሱ የሆነ ችግር ቢኖርበትም ከፍ ያለ ጥቅም እየሰጠ ነው። መስቀለያ ጥያቄ በአግባቡ ለማቅረብ ከፍ ያለ ዝግጅት ማድረግ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ በዘርፉ ያሉ ሙሁራን ይገልፃሉ። እንደነ አሜሪካ ባሉ ሀገራት መስቀልያ ጥያቄ ከመጠየቁ በፊት ተከራካሪ ወገኖች መስቀለያ ጥያቄ ስለሚጠየቀው ግለሰብ ማንነት በማወቅ፣ የቅድመ ጥያቄ መጠይቆችን በመላክና በማጣራትና በሌሎችም መንገዶችም ዝግጅት ያደርጋሉ ። በሀገራችን መሰል ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችል ስርአት ባይኖርም በተለያዩ መንገዶች አስቀድሞ ዝግጅት ይደረጋል። ከነዚህም መሀከል ስለምስክሮቹ ማንነት አስቀድሞ ማወቅ፣ በተበዳዮች፣ በተከሳሾችና በምስከሩ መሀከል ያለውን የዝምድናና መሰል ግንኙነት በማጣራት ፣ በወቅቱ ምስክሮቹ ስለነበሩበት ሁኔታና ስለአጠቃላይ ባህሪያቸው በማጥናት ሊሆን ይችላል። ይህን ለማድረግ በምስክርነት የሚቀርቡ የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ ለተከራካሪ ወገኖች አስቀድሞ ሊደርስ ይገባል። ይህ መብት ለተከሳሽ ብቻ ሳይሆን ለዐቃቤ ሕግ የተሰጠ መብት መሆን ይገባዋል። በዚህ መልኩ ለዐቃቤ ሕግ መድረስ በሚገባው የመከላከያ ማስረጃ ዝርዝር ላይ ተበዳዮች ዝርዝሩን እንዲመለከቱት በማድረግ ስለምስክሮቹ ወይም ስለማስረጃው አስተያየት እንዲሰጡ ሊደረግ ይገባል። ይህ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል አስገዳጅ የሕግ ድንጋጌ በረቂቅ ሕጉ ላይ መቀመጥ አለበት።
  2. መስቀለኛ ጥያቄ በተበዳዮች ላይ ህመም እንዳይፈጥርባቸው የመጠበቅ መብት። በምስክር አሰማም ተበዳዮች ስለደረሰባቸው ጉዳትና በዝርዝር አስተያየት እንዲሰጡ ማድረግ(የሟች ቤተሰቦች ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ማድረግን ጨምሮ )በመስቀልኛ ጥያቄ ወቅት እውነትን ለማውጣት በሚል የሚቀርቡ ጥያቄዎች ተበዳዮችን የሚያሳቅቁ፣ ክብራቸውን የሚነካ መሆን አይገባውም። የቀደመ ተጠቂነታቸውን በማውሳት፣ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌለውን የግል ህይወታቸውን በማንሳት፣ በማስፈራራትና ዛቻ በሚመሰል ቃል ወይም የድምፅ መጠን በመናገር፣ የመናቅና የማጥላላት ስሜት በማሳየት፣ በደረሰው በደል እጃቸው እንዳለበት በሚያስመስል በሟሽሟጠጥና በሌሎችም በማናቸውም መንገዶች ተበዳዮችን ለዳግም ሀፍረትና መሸማቀቅ እንዲደርስባቸው ከሚያደርግ ጥያቄ የመጠበቅ መብት ተበዳዮች ሊኖራቸው ይገባል። ይህንን የተበዳዮች መብት በመጠበቅ ረገድ በዐቃቤ ሕግና በፍርድ ቤቶች ላይ ግዴታ ሊጣል የሚገባ ሲሆን ተበዳዮች የደረሰባቸውን ሁሉ አቀፍ ጉዳት ሳይቆራረጥ ለምስክርነት አላማ በሚባል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በደላቸውን እንዲተነፍሱ በሚያስችል ሁኔታም ለፍርድ ቤቱ እንዲገልፁ ሊደረግ ይገባል።

3.3.የወንጀል ተጎጂዎች መብት የጥፋተኝነት ፍርድ ከተሰጠ በኋላ

የጥፋተኝነት ፍርድ በተከሳሾች ላይ ከተሰጠ በኋላ ተበዳዮች ተከታዮችን መብት እንዲጎፀፉ ሊያደርግ የሚስችል የሕግ ጥበቃ በረቂቅ ሕጉ ላይ ሊያገኙ ይገባል።

  1. በተከሳሽ በኩል የሚቀርቡ የቅጣት ማቅለያ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ማድረግ።
  2. በዐ/ሕግ በኩል የሚቀርቡ ማክበጃዎች ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ማድረግ።
  3. የተጎጂነት ውጤት አስተያየት ለፍርድ ቤት እንዲሰጡ ማድረግ(Victims impact statement)።
  4. በፍርድ ቤት በሚቀርብ በገደብ የመለቀቅ አቤቱታ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ማድረግ።
  5. ተከሳሾች በይቅርታ፣ በምህረትና በአመክሮ ከእስር ሲለቀቁ ሀሳባቸውን እንዲሰጡና እንዲያውቁ የሚደረግበት ስርአት ማበጀት።
  6. በፍርድ ቤት በሚሰጡ ውሳኔዎች ላይ ይግባኝ እንዲቀርብ ቅሬታ የማቅረብ መብት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ በዐ/ሕግ ተነሳሽነት በሚቀርቡ ይግባኞች ላይ አስተያየት መስጠት የሚቻልበትን አሰራር ማበጀት።
  7. በተከሳሾች በኩል በሚቀርቡ ይግባኞች ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ማድረግ።

 

ይህንን ጽሑፍ እስከነሙሉ ማጣቀሻው (footnote) ከዚህ ያውርዱ

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ARTICLE REVIEW - Seyoum Yohannes, the Normative Ba...
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን - የሴቶች ጥቃት ችግር - ሴቶች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 05 November 2024