Font size: +
2 minutes reading time (362 words)

የይግባኝ የዳኝነት ክፍያ አግባብነትን በተመለከተ

ግምቱ ተለይቶ የሚታወቅ የፍትሐ ብሔር ክርክር ጉዳይ በመያዝ በፍርድ ቤት ክስ የሚመሰርት ወይም የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ የሚያቀርብ ማንኛውም ተከራካሪ በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ቁጥር 215/1 እና ስለ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ገንዘብ አከፋፈል በ1945 ዓ/ም በተደነገገው ደንብ መሠረት የዳኝነት ክፍያ ይከፍላል። በዚህ ክሱን በከፈተበት ፍርድ ቤት በተሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ተከራካሪ ደግሞ የይግባኝ አቤቱታውን ይግባኝ ለመስማት ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ያቀርባል። ይህ የይግባኝ አቤቱታ እንዲሰማለት ደግሞ በሥር ፍርድ ቤት የከፈለውን የዳኝነት ክፍያ 50% መክፈል ይጠበቅበታል። የዚህ አጭር ማስታወሻ ዓላማም የዚህ የይግባኝ የዳኝነት ክፍያ አግባብ የማይሆንበትን ኹኔታ መጠየቅ ነው።  

ከሶስቱ የመንግሥት አካላት አንደኛው የሆነው ፍርድ ቤት በተለያዩ ምክንያቶች (በማስረጃ ምዘና፣ በሕግ አተረጓጎምና አተገበባበር ወዘተ) ለተገልጋዩ/ለተከራካሪው ተገቢውን እና ትክክለኛውን አገልግሎት/ውሳኔ ባለመስጠቱ ምክንያት ተከራካሪው ውሳኔውን ለማሳረም የሚያወጣው የይግባኝ የዳኝነት ክፍያ አግባብነት በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይገባል። ይኸውም፣ ይግባኝ ባዩ በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ አግባብ አይደለም ተብሎ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሚሻር ከሆነ፣ ቀድሞውኑ ወደ ይግባኝ የሄደው በሥር ፍርድቤቱ ሥህተት ነውና የከፈለው የይግባኝ የዳኝነት ክፍያ ተመላሽ ሊደረግለት ይገባል። ነገር ግን የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም የሚፀና ከሆነ ይግባኝ ባዩ ላገኘው አገልግሎት የዳኝነት ክፍያውን ሊከፍል ይገባል።

ይህ የይግባኝ የዳኝነት ክፍያ ይግባኝ ባይ ጉዳዩ በይግባኝ ከታየለት በኋላ የረታ ወይም የቀድሞው ውሳኔ የተሻረለት ከሆነ የወጪና ኪሣራ ዝርዝር በማቅረብ ከተረቺው ሊጠይቅ ይችላል የሚል መከራከሪያ ሊቀርብ ይችላል። ነገር ግን ከዚህ ጋር በተያያዘ የሕጉ አንድምታ እና የሰበር ውሳኔዎች ትርጓሜ ሁል ጊዜ ተረቺ ወጪና ኪሣራ ሊሸፍን ይገባል የሚባለው ከቅን ልቦና ውጪ ሌላኛውን ተከራካሪ ለወጪ የዳረገ ተከራካሪ ካለ ብቻ ነው እንጂ በሁሉም ጉዳዮች ወጪና ኪሣራ ይሸፍናል ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ ባለፈም አሁን አሁን በሰፊው እየተለመደ የመጣው «ግራ ቀኙ ወጪያቸውን ይቻሉ» የሚል ትዕዛዝ ይህ እንዳይቻል ያደርጋል።

በመሆኑም፣ ይህ ሀሳብ ቢተገበር ሁለት ጥቅም አለው። አንደኛው ጥቅም አንድ ተከራካሪ ያለጥፋቱ በመንግሥት አካል (በሥር ፍርድ ቤት) በተሰራበት ስህተት በይግባኝ መንገላታቱ ሳያንስ ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረግ የሚያድነው መሆኑ ነው። ከላይ እንደገለፅነው የውሳኔው በይግባኝ መሻር የሚያመላክተው የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሥህተት መሆኑን ነው። ሁለተኛው እና ዋነኛው ጥቅም ግን መንግሥት እንደማንኛውም ግለሰብ እና አገልግሎት ሰጪ ሁሉ ራሱ በዘረጋው አሰራር ከገዛ ራሱ ሥህተት ተጨማሪ ገቢ ማግኘት የለበትም የሚለውን መሠረታዊ የፍትሐዊነት ዕሳቤን በመተርጎም የፍትሕ ተደራሽነትን ማጎልበት ነው።

በአጭሩ የዚህች አጭር ማስታወሻ ድምዳሜ በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ታይቶ የተሻረ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ የተከፈለ የዳኝነት ክፍያ ለይግባኝ ባዩ ተመላሽ ሊሆን ይገባል የሚል ነው፤ ምክንያቱም ለዚህ ወጪ የተዳረገው በሥር ፍርድ ቤቱ ሥህተት ነውና።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የኢትዮጵያ የብር ኖቶችና የባንኮች አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓተ-ልማድ ከአካል-ጉዳ...
ስለቅድመ ሳንሱር

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024