በዳኛው ገጠመኝ እንጀምር። የአንዱ የኦሮሚያ ወረዳ ፍ/ቤት ዳኛ ለተዘዋዋሪ ችሎት በሕዝብ ትራንስፖርት እየሄደ ነበር። መኪናው ውስጡ ሞልቶ ረዳቱ ከላይ ለመጫን ይቃጣዋል። መኪናው ላይ የተፃፉ ጥቅሶች እንቅጩን ይናገራሉ።
"ታሪፍ እንጂ ትራፊክ የለም፣ ጠጋ ጠጋ በሉ"
"የሰው ልጅ ክቡር ነው፣ ትርፍ ሰው የለም ግቡ"
"ሞላ የሰው ስም ነው፣ገባ ገባ በሉ"
ወዘተ።
እና ዳኙዬ ተጣብቆ ቆሞ ከቦታው ደረሰና ችሎት ስራውን ይጀምራል። መኪና ውስጥ ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረ ባለ ጉዳይ ውጭ ቆሞ ከጓደኛው ጋር "ቆሞ የመጣው ሶዳ (አማቻችን) እዚህ ደርሶ ወንበር አገኘ" እያለ ይሳለቃል። ችሎት ተደፈረ? ፖሊስ የለም። የቀበሌ ታጣቂ እንኳን የለም።
ሰውየው ተራ ደርሶት ተጠራና ይገባል። ዳኛው ከንግግሩ ላይ ንዴት ይነበባል። ሰውየው ግን ቀላል ፎጋሪ አይደለም "ቅድም እኮ ዳኛ መሆንህን ባውቅ እነሳልህ ነበር" ብሎ ፈገግ አለ። ከፈገግታው ጥፊ ይሻላል። ችሎት ተደፈረ? የለም የለም! ይህ የዳኛው እውነተኛ ገጠመኝ ነው።