የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች የፌዴራሉን መንግሥት ሕጎች አልፈፅምም ማለት ይችሉ ይሆን?

የፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 53 መሠረት በተቋቋመ ወዲህ ላለፉት 24 ዓመታት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከ1100 በላይ አዋጆችን ያወጣ ሲሆን ከእነዚህም አዋጆች ውስጥ በምክር ቤቱ በሚገኙ የገዢው ፓርቲ አባላት መካከል ሞቅ ያሉ ክርክሮችና የልዩነት ሃሳቦች ያስተናገዱ በጣት የሚቆጠሩ አዋጆች መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ሞቅ ያሉ ንትርክ አዘልና የልዩነት ሃሳቦች ከተንፀባረቁባቸው ሕጎች መካከል ለአብነት ያህል በሚንስትሮች ምክር ቤት ከየካቲት 06 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚነት የነበረውንና ለሁለተኛ ጊዜ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 2/2010 የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀባይነት እንዲያገኝ በቀረበ ወቅት የተደረገው እልህ አስጨራሽ ክርክር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1101/2011 የፀደቀባት ሁኔታ የጋለ ክርክርን ያስተናገደ ነበር፡፡ የፌዴራሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታህሳስ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅን በ33 ተቃውሞ በ4 ድምፅ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡ በዚህ አዋጅ ላይ የተደረገው ክርክርና የሰላ ሂስ በምክር ቤቱ ባሉአባላት ብቻ ሳይወሰን ከምክር ቤቱ ውጪ ባሉ የፖለቲካና የሕግ ሊሂቃን መካከል የከረረ ክርክርና ትችት ሲያስተናግድ ሰንብቷል፡፡

የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ ሕገ-መንግሥታዊነቱንና ሥልጣኑን በተመለከተ የሚቀርበው ድጋፍና ትችት በግለሰቦች ደረጃ ብቻ የቀረ ሳይሆን የትግራይ ክልል ምክር ቤት በጥር 18 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው 5ኛ ዓመት 14ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይም የመከራከሪያ አድማስ ሆኖ በአዋጅ አፈፃፀም ላይ የክልል ምክር ቤቱን የውሳኔ ሃሳብ እስከማሰጠት ደርሷል፡፡

የዚህ ጽሑፍ መነሻ ሃሳብም የትግራይ ክልል ምክር ቤት በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በሰጠው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ሲሆን በዚህም አግባብ የክልሉ ምክር ቤት የፌዴራሉን መንግሥት ሕጎች አልተገብርም ማለቱን ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንፃር ያለውን ውጤት እና የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሥልጣንና ተግባርን አጠቃላይ እንድምታ የምንዳስስ ይሆናል፡፡

1. የማንነትና የአስተዳደር ወሰን በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት፡ መሠረቱ

የፌዴራሊዝም ሥርዓት በሚከተሉ ሀገሮች ውስጥ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎችን እና አለመግባባችን ተፈጥሯዊ ሲሆኑ መንግሥታትም ሕጎች በማበጀትና ተቋማዊ በሆነ አግባብ መፍትሄ ሲሰጧቸው ተመልክተናል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በሀገራችን የሕግ ሥርዓትም የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮችን በሚመለከት በፌዴራሉ ሕገ-መንግሥትና ከዚህ ሕገ-መንግሥት ከሚመነጩ የሕግ ሥርዓቶች አግባብ የሚነሱትን ጥያቄዎችና ቁርሾዎችን እልባት ለመስጠት ሲሞከር ለመመልከት ችለናል፡፡

የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን የመፍታት የተፈጥሮ ሥልጣን /Inherent Power/ ጥያቄው የቀረበበት የክልል ምክር ቤትና በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች መሆኑን ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 39 እና 47 ጥምር ንባብ በግልፅ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ጥያቄው የቀረበለት ክልል በሁለት ዓመት ውስጥ ውሳኔ ካልሰጠ ወይም በተሰጠው ውሳኔ ቅሬታ ያለው የትኛውም ወገን ጥያቄውን ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አቅርቦ የሚያስወስንበት አግባብ ያለ መሆኑን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 62/3/ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀፅ 20/3/ ላይ በግልፅ ተመልክቶ ይገኛል፡፡

በክልሎች መካከል የሚፈጠርን የአስተዳደር ወሰን አለመግባባትን በሚመለከት በተመሳሳይ ሁኔታ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 48 መሠረት ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች የጋራ ስምምነት አማካኝነት መፈታት ያለበት መሆኑ በግልፅ ተመልክቷል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክልሎችም ያልተስማሙ እንደሆነ በዚሁ ድንጋጌ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ለመጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀፅ 27 መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ በጉዳዩ ላይ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ መስጠት ያለበት መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ስራ አስፈፃሚ አካላትና አደረጃጀትን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 256/1994 አንቀጽ 11/1/ለ መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ በተቋቋመው የፌዴራል ጉዳዮች  ሚኒስቴር ሥልጣንና ተግባር ስር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በክልሎች መካከል የሚነሱ የትኛውንም አለመግባባቶች  ለመፍታት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ኃላፊነት ተሰጥቷታል፡፡ ይህም ሥልጣንና ኃላፊነት የፌዴራል ስራ አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር እንደገና ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀፅ 13/1/ መሠረት አዲስ ለተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር ተሰጥቷል፡፡

በአጠቃላይ አንድ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ህዝብ ማንነቴ አልታወቀልኝም፣ የራስ በራስ ማስተዳደር መብቴ ተሸራርፏል፣ በተፈጥሮ ያገኘሁት የአስተዳደር ወሰኔ ተቆርሶ ለሌላ ተሰጥቶብኛል ወይም በማንኛውም ሌላ ምክንያት በፌዴራሉ ሕገ-መንግሥት የተደነገገው መብቴ አልተከበረልኝም በሚል ጥያቄዎች ሲያቀርብ በክልሎች የአስተዳደር ስር በሚገኙ የተለያዩ መዋቅሮች፣ በፌዴሬሽን ም/ቤቱ እና በሰላም ሚኒስቴር በኩል እልባት የሚያገኝበት የሕግና ተቋማዊ አሰራሮች ተበጅተዋል፡፡

2. የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አስፈላጊነት በተመለከተ

የማንነት እና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮችን በሚመለከት በሀገራችን የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የሕግና ተቋማዊ አሰራሮች መበጀታቸውን ከላይ ለመግለፅ ሞክረናል፡፡ በሀገር ደረጃ የሚነሱ ጥያቄዎችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት ሕጎችና ተቋማዊ አሰራሮች ካሉ እዚህ ላይ የሚቀርበው ጥያቄ በፌዴራሉ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአዋጅ ቁጥር 1101/2011 የተቋቋመው የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አስፈላጊነት ነው፡፡

የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አስፈላጊነትን በተመለከተ የተሻለ እይታ እንዲኖረን የማንነት እና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎችና አለመግባባቶች የተነሱበትን ዋና መንስኤዎች /Main Cause/ እና የአሁን መንስኤዎች /immediate causes/ ማጥናት ተገቢ ይሆናል፡፡ እነዚህ መንስኤዎች አንደኛ በሌሎች የፌዴራል ሥርዓት አቀንቃኝ ሀገሮች ውስጥ በግልፅ እንደሚገኘው በኢትዮጵያ ውስጥ በፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች መካከል ግልፅ ሥርዓትን በዘረጋ መልኩ በሰነድ ላይ የተመሠረተ የድንበር አቀማመጥ /Delimitation/ የድንበር አከላለል /Demarcation/ አለመኖሩ፣ ሁለተኛ ይህን ችግር ተረድቶ በተደራጀ መልኩ በጥናት ላይ በተመሠረተ ሳይንሳዊ ዘዴ ታሪክን፣ ማንነትና የህዝብ አሰፋፈር መሠረት በማድረግ ችግሮቹን ለመፍታት ላለፉት 27 ዓመታት በክልሎችም ሆነ በፌዴራል መንግሥት ስር በሚገኙ ተቋማት ቀጣይነት ያለው መፍትሄ አለመሰጠቱ ሦስተኛ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት ከመፅደቁ በፊት በ1984-85 ዓ.ም አሁን ያሉት የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ቅርፅን ሳይንሳዊ ባልሆነ የፖለቲካ ውሳኔ በሚመስል መልኩ የመላ ህዝቡን አሳብና አመለካከት እንዲሁም ታሪክንና ማንነትን ታሳቢ ባለማድረግ የተወሰነ መሆኑ በፖለቲካ ሊሂቃኑና በህዝቡ መካከል ክርክሮችና አለመግባባትን መፍጠሩ እና አራተኛ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥያቄዎቹና አለመግባባቶቹ ሰፊ የሰብዓዊ ቀውሶችን እያስከተሉ በመምጣታቸው በተለይም ከሁለት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በላይ መፈናቀላቸው ጉዳዩ የተለየ ትኩረት የሚሻ አድርጎታል፡፡

እነዚህ የፖለቲካና የታሪክ ቁርሾዎች የኮሚሽኑን መመስረት እንደ ምክንያት የሚወሰዱ ጉዳዮች ሲሆኑ ኮሚሽኑ በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 1101/2011 ጠቅላላ መግቢያ ሀሳብ /Preamble Reading/ እና የኮሚሽኑ ሀላማን በሚደነግገው አንቀጽ 4 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው የኮሚሽኑ መመስረት ዋና ምክንያት በተደጋጋሚ የሚነሱና እየተከሰቱ ያሉ የማንነት ጥያቄዎችና የአስተዳደር ወሰን ይገባኛል አለመግባባቶችን ገለልተኛ በሆነ ተቋም በማያዳግም እና ሰላማዊ በሆነ የሳይንሳዊ ጥናት ግኝቶችን መሠረት ባደረገ መልኩ መፍትሄ ለመስጠት ያስፈለገ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በአጠቃላይ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ከዚህ ቀደም የተነሱ ጥያቄዎችንና ለወደፊት የሚመጡ አለመግባባቶችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በተደራጀ፣ አሳታፊ፣ ግልፅ፣ አካታችና ሳይንሳዊ ክዕሎትን መሠረት ባደረገ መልኩ መፍትሄ ለማፈላለግ የተዋቀረ ኮሚሽን ነው፡፡

3. የኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባር

የኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባር የኮሚሽኑን ባቋቋመው አዋጅ ቁጥር 1101/2011 አንቀጽ 5 ላይ በዝርዝር የተቀመጡ ሲሆን ኮሚሽኑ በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 48 እና 62 እንዲሁም በሌሎች ሕጎች ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ለክልሎች የተሰጠው ሥልጣንና ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው የሚከተሉት ዋና ዋና ሥልጣናትና ተግባራት ይኖሩታል፡፡

1ኛ) ከአስተዳደራዊ ወሰኖች አከላለል፣ ራስን በራስ ከማስተዳደር እንዲሁም ከማንነት ጥያቄዎች ጋር የተገናኙ ማናቸውንም ችግሮችንና ግጭቶችን በጥናት ለይቶ አማራጭ የመፍትሄ ምክረ ሃሳቦችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ፤

2ኛ) የአስተዳደራዊ ወሰኖች በቀጣይነት የሚወስኑበትንና የሚለወጡበትን መንገድ በተመለከተ አግባብነት ያላቸውን ሕገ-መንግሥታዊ መርሆችን ያገናዘበ፣ ግልፅና ቀልጣፋ ሥርዓት ወይም የሕግ ማሻሻያ እንዲዘረጋ ጥናት በማድረግ ምክረ ሃሳቦቹን ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብ፤

3ኛ)  ከጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚመሩለትን የአስተዳደራዊ ወሰን ውዝግቦችን መርምሮ ምክረ ሃሳቦችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ማቅረብ፤

4ኛ) በቀጣይነት አስተዳደራዊ ወሰኖች የግጭትና የትርምስ መንስኤ እንዳይሆን ሊወሰዱ የሚገባቸውን ዕርምጃዎችንም አስመልክቶ ምክረ ሃሳቦችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ማቅረብ እና

5ኛ) በሕዝቦች እኩልነትና ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር ለማድረግ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ዕርምጃዎች ማሻሻያ ምክረ ሃሳቦችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ፡

በአጠቃላይ የዚህ ኮሚሽን ሥልጣንና ተግባር ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ህዝቡን ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ በሀገሪቱ እስካሁን የተነሱ የማንነት፣ ራስን በራስ የማስተዳደርና የአስተዳደር ወሰን ውዝግቦችን እንዲሁም በቀጣይ እንደ አዲስ የሚነሱ ተመሳሳይ ጉዳዮችንና አለመግባባቶችን መንስኤያቸውን በመተንተን የመፍትሄ ምክረ ሃሳቦችን ለህዝብ፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለመንግሥት ስራ አስፈፃሚ አካል ማቅረብ ነው፡፡

4. ኮሚሽኑን ከሕገ-መንግሥቱ አንፃር፡

የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን በሚመለከት ከመቋቋሙ በፊትም ሆነ ከተቋቋመ በኋላ በሕግና በፖለቲካ ሊሂቃን መካከል እንዲሁም በጠቅላላ ማህበረሰቡ ዘንድ የውይይትና የክርክር አድማስ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የክርክሩ መነሻ ነጥቦች የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ ሕገ-መንግሥታዊነቱንና ሥልጣኑን በተመለከተ ሲሆን ይህንንም መሠረት በማድረግ ሁለት ተፃራሪ ቡድንተኞች ተፈጥረዋል፡፡

የመጀመሪያው ቡድን የሚያቀርበው መከራከሪያ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ  የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 39፣ 47፣ 48፣ 62/3/ እና 62/6/ እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 251/93 እና የክልሎችን ሕገ-መንግሥት በመጣስ የአስተዳደር ወሰንን እና የማንነት ጉዳይን ለመወሰን ለክልሎችን ለፌዴሬሽን ም/ቤት የተሰጠ ሥልጣን ይጋፋል የሚል ሲሆን በተቃራኒው ሌላኛው ቡድን ደግሞ ኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባሩን ምክረ ሃሳብ ለመንግሥት አካላት መስጠት እንጂ በራሱ ለሚቀርቡ ጉዳዮችና አለመግባባቶች ውሳኔ የሚሰጥ ተቋም አይደለም በመሆኑም ሕገ-መንግሥቱንም ሆነ ሌሎች ሕጎችን የሚጣረስ አይሆንም በማለት መከራከሪያ ነጥቦቻቸውን ያነሳሉ፡፡

በመርህ ደረጃ የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ ሕገ-መንግሥታዊነት ከመነጋገራችን በፊት ሁለት መሠረታዊ ነጥቦችን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ አንደኛ የፌዴራሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55/1/ መሠረት አስፈላጊ ሆኖ ሲታየው የተለያዩ ተቋሞችን ማደራጀት የሚችል መሆኑ በግልፅ ተቀምጧል፤ ሁለተኛ መንግሥት ሕግና ሥርዓትን በመላ ሃገሪቱ የማረጋገጥ ግዴታውን ለመወጣት ወቅቱ የሚጠይቀውን ተቋማዊ አደረጃጀት የመፍጠርና ሕጎች የማውጣት ተፈጥሯዊ የሆነ ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን አለው፡፡ በመሆኑም መንግሥት  ሕግን ተከትሎ መሠረታዊ የሕገ-መንግሥት ምሶሶዎችን /Constitutional Pillars/  ሳይጥስ የሚያወጣው ሕግ ላይ የሕገ-መንግሥታዊነትና የኢ-ሕገመንግሥታዊነት ሊነሳ አይችልም፡፡ ነገር ግን በየትኛውም አግባብ ዜጎች በኮሚሽኑ ላይ ስጋታቸውን ያቀረቡ እንደሆነ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጁን ሕገ-መንግሥታዊነት እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን፡፡

  1. የዚህን ኮሚሽን ሥልጣንና ተግባር በአግባቡ ስንመለከት ሕገ-መንግሥታዊ መርሆዎችን በማገናዘብ፣ ግልፅና፣ ቀልጣፋ ሥርዓት እና ሕጎች እንዲሻሻሉ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ችግሩንና መፍትሄውን በማጥናት ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ምክረ ሃሳብ ይሰጣል እንጂ በራሱ የመጨረሻም ሆነ የመጀመሪያ ውሳኔ አይሰጥም፡፡ በመሆኑም በዚህ አግባብ ያጠናውን ጥናት በምክረ ሃሳብ ደረጃ በሕገ-መንግሥቱ መጨረሻና ህጋዊ ውሳኔ ለመስጠት ሥልጣን ለተሰጠው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ በመሆኑ ኮሚሽኑ የተቋቋመበት አዋጁን ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ የሚያስብልበት የሕግ አግባብ የለም፡፡
  2. በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 62/1/ መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ-መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው ቢሆንም ምክር ቤቱ ሊያጋጥመው የሚችለውን የጊዜ እጥረትና የሙያዊ ክፍተቶች ታሳቢ በማድረግ በራሱ በሕገ-መንግሥቱ ምክር ቤቱን የሚረዳ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የተቋቋመ ሲሆን ይህም ጉባዔ በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 84 መሠረት ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮችን የማጣራትና ብሎም ለምክር ቤቱ ምክረ ሀሳብ የማቅረብ ሥልጣንና ተግባር ተሰጥቷታል፡፡ በመሆኑም በሕገ-መንግሥቱ ላይ የሚነሱ የትርጉም እና ተያያዥ ጥያቄዎችን ሙያዊ እገዛ ለምክር ቤቱ የሚሰጠው የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ይሆናል፡፡ በተቃራኒው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 62/3/ እና 62/6/ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችንና ቅራኔዎችን በሚመለከት የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ጉዳዩን እንዲፈታ ሥልጣን ቢሰጠውም በሕገ-መንግሥቱ ትርጓሜ ላይ የሙያዊ እርዳታ እንዲሰጠው አጣሪ ጉባኤ የተቋቋመለት ምክንያት ለዚሁም ሥልጣንና ተግባሩም የሚያገለግል ሆኖ ሳለ ነገር ግን ሕገ-መንግሥቱ ለሙያዊ ድጋፍ የሚረዳ ተቋም አላቋቋመም፡፡ ይህን ሕገ-መንግሥታዊ ክፍተት ለመሙላት እና በዚህ ወቅት የሚነሱ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችን እልባት ለመስጠት ያስችል ዘንድ ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጥ ኮሚሽን ማቋቋሙ የመንግሥትን መንግሥታዊ ሃላፊነት ከመወጣት በስተቀር ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን አዋጅ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ የሚያደርገው አይሆንም፡፡
  3. ከ1994 በፊት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ውስጥ የክልል ጉዳዮች ዘርፍ እየተባለ ይጠራ የነበረው የፌዴራል አርብቶአደሮች ጉዳዮች ሚኒስቴር በአሁን ወቅት የሰላም ሚኒስቴር በመባል እንደ አዲስ የተዋቀረው ተቋም በመጀመሪያ ሲዋቀር ከተሰጡት ተግባራትና ሥልጣኖች ውስጥ በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን የሚፈቱባቸውን ሁኔታዎች ያመቻቻል እልባትም እንዲያገኙ ጥረት ያደርጋል የሚል የተካተተበት ሲሆን ይህን ተግባር አሁን ከተዋቀረው ኮሚሽን አንፃር ስንመለከት ይህ ሚኒስቴር መ/ቤት ቀድሞውንም የፌዴሬሽን ም/ቤቱን በማገዝ ላይ የነበረ ይልቁንም ጠንካራ በሆነ መደላደል ውስጥ በመሆን ክልሎችን ሲያሸማግል የቆየ መሆኑ ሲታይ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ምክረ ሃሳብ ከሚሰጠው ኮሚሽን አንፃር ሰፋ ያለ ሥልጣን የተሰጠው መሆኑን ያሳያል፤ በመሆኑም ለተከታታይ 20 ዓመታት የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን ተግባር ሲፈፅም የነበረ ተቋምን ሕገ-መንግሥታዊነቱን ለመቃወም ምክንያት ከሌለ የሕገ-መንግሥቱን ክፍተት ተጠቅሞ ምክረ ሃሳብ ለሚመለከተው አካል እንዲያቀርብ የተቋቋመን ኮሚሽን ሕገ-መንግሥታዊነቱን ለመቃወም ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡
  4. ኮሚሽኑ የተቋቋመበት አዋጅ በራሱ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ እንዳልሆነ የሚያመላክት ነው፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 5 መጀመሪያ ላይ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 48 እና 62 እንዲሁም በሌሎች ሕጎች ለፌዴሬሽን ም/ቤቱ እና ለክልሎች የተሰጡ ሥልጣንና ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው ኮሚሽኑ ተግባሩን ይፈፅማል በማለት በግልፅ አመልክቷል፡፡ ይህ የመንደርደሪያ ሃረግ በግልፅ እንደሚያሳየው ኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባር የሚመዘነውም ሆነ የሚታየው ከእነዚህ ሕገ-መንግሥታዊ መርሆዎች አንፃር መሆኑን ነው፡፡

በመሆኑም ኮሚሽኑ የተቋቋመው የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮችን በተመለከተ የሙያዊ ድጋፍ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለመስጠትና ከዚህም ሙያዊ ምክረ ሃሳብ በመነሳት ምክር ቤቱ ግልፅ፣ ቀልጣፋ እና ተአማኒነት ያለው ውሳኔ እንዲሰጥ በማሰብ የተቋቋመ በመሆኑ አዋጅን ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ የሚያስብለው ህጋዊ ምክንያት የለም፡፡

5. ክልሎችና የፌዴራል ሕጎች ተፈፃሚነት

የፌዴራሊዝም ሥርዓት ተከታይ ሃገሮች ውስጥ በፌዴራሉ እና በክልል መንግሥታት መካከል የሚኖረውን ግንኙነት በተመለከተ አንድም ተወዳዳሪ ፌዴራሊዝም /Competitive federalism/ ሌላም ጊዜ የጋራ ፌዴራሊዝም /Cooperative federalism/ በመምረጥ በሕግ በማስቀመጥ ተግባራዊ ሲያደርጎ ይስተዋላል፡፡ በተወዳዳሪ ፌዴራሊዝም ውስጥ ሁለቱ መንግሥታት ያልተገደበ ነፃነት /Absolute autonomy/ ያላቸውና በጥቂት ሃገራዊ ጉዳዮች ላይብቻ የፌዴራል መንግሥቱ ፈላጭ ቆራጭ የሚሆንበት ሲሆን በተቃራኒው የጋራ /የመተባበር/ ፌዴራሊዝም ውስጥ ሁለቱ መንግሥታት በሕገ-መንግሥት አማካኝነት የተገደበ ነፃነት /Relative autonomy/ ያላቸውና በአብዛኛው ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የፌዴራል መንግሥቱ ሕግ እስከማውጣት የሚደርስ ሥልጣንን የሚያጎናፅፍ ነው፡፡

በሃገራችን የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የፌዴራል መንግሥቱ ዋና ዋና የሚባሉ ሃገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሕግ የማውጣት ሥልጣን በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 51 መሠረት ተሰጥቷታል፡፡ ክልሎችም በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 52/2/ መሠረት በራሳቸው የአስተዳደር ወሰን ተፈፃሚ የሚሆኑ ጥቂት ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ የፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣን ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ክልሎችም የፌዴራሉን መንግሥት ሥልጣን ያከብራሉ፣ ያስከብራሉ በተለይም የፌዴራሉን ሕጎች የመፈፀም ግዴታ ተጥለባቸዋል፡፡ ከዚህ ፅንሰ ሃሳብ ስንነሳ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም በመተባበር ላይ የተመሠረተ የመተባበር ፌዴራሊዝም /Cooperative federalism/ መሆኑን ያሳያል፡፡ በዚህ አግባብ የተመሠረተው የሀገራችን የፌዴራሊዝም ሥርዓት በባለፈው 9 ወራት ሳንቃ ገጥሞት የሚገባበት ያጣ ይመስላል፡፡ ክልሎች ከፌዴራሉ መንግሥት በላይ ነን ብሎ በማሰብ የፌዴራል መንግሥቱን ሕጎች እንዲሁም የፍርድ ቤቶችን ትዕዛዞች አንፈፅምም በማለት ላይ ናቸው፡፡ ይህ አካሄድ የፌዴራል ሥርዓቱን ከማጥፋቱም በላይ እንደ ሃገር የመቀጠላችን እጣ ፈንታ የሚወሰን ነው፡፡

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት በጥር 18 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው 5ኛ ዓመት 14ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮችን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1101/2011 አፈፃፀም በሚመለከት በሰጠው ውሳኔ አዋጁ የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 9/1/ የሚቃረን በመሆኑ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ነው በተጨማሪም አዋጁ በክልሉ ውስጥ እንዳይፈፀም ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡

ለመሆኑ የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች የፌዴራሉን መንግሥት ሕጎች ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ማለት ይችሉ ይሆን? አልፈፅምምስ ካሉ መፍትሄው ምን ይሆን? የሚሉት ጥያቄዎች በሁሉም ኢትዮጵያዊ ውስጥ መመላለሱ አይቀሬ ነው፡፡

የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች የፌዴራሉን መንግሥት ሕጎች ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ስለሆነ አንፈፅምም ማለት አይችሉም ምክንያቱም አንደኛ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት የወጡ ሕጎችን ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ለማለት የራሱ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ የተቀመጠ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም አግባብ የትግራይ ክልል ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 84/2/ እና የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባኤን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር በድጋሚ በወጣው አዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀፅ 4 መሠረት የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አዋጅን ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ለማስባል አቤቱታቸውን ማቅረብ አለባቸው፤ በዚህም አግባብ በአጣሪ ጉባዔ በሚሰጠው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ክልሉ ቅሬታ ካለው በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62/1/ እና 84/3/ሀ መሠረት ቅሬታውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀጥታ ማቅረብ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህን መሠረታዊ የሕገ-መንግሥት መርህ ወደኋላ በመተው የፌዴራል መንግሥቱ ያወጣውን አዋጅ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ነው አንፈፅምም ማለት በራሱ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ተግባር ነው፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 50/8/ መሠረት የተቀመጠውን የመከባበር ግዴታ የጣሰና ክልሉ የፌዴራል መንግሥቱን ያላከበረ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ በተያያዘም ተፈፃሚ እንዳይሆን በማለት የተጠቀሰው የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ የሆነው አንቀጽ 9/1/ ለተራ የሕግ ትምህርት ቤት ክርክር /Academic discourse/ ካልሆነ በቀር ግለሰቦችም ሆኑ ክልሎች አንድን ሕግ ተፈፃሚ እንዳይሆን በማሰብ እንደ ማጣቀሻ ድንጋጌ እንዲወስዱት ሳይሆን ሕግን ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ነው በማለት ውሳኔ የሚሰጠው ህጋዊ አካል እንዲጠቀምበት በማሰብ የተቀመጠ ድንጋጌ ነው፡፡ ሁለተኛ ይህ በፌዴራልና ክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት እንደ አንድ ተራ ሕገ-ወጥ የውል ግንኙነት ሳይሆን ሕግንና መርህን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ አንድ ክልል በፍትሃብሄር ህጉ አግባብ በሕገ-ወጥ መንገድ ከግለሰብ/ከድርጅት/ ጋር ውል ገብቶ እንደሆነ አልፈፅምም በማለት መታቀብ /Abstain/ ማድረግ የሚችል ሲሆን ነገር ግን በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ይህ አልጣመችም ያኛው ደግሞ ተመችቶኛል በማለት የሚኖርበት አግባብ የሌለና በሕግና በመርህ ብቻ ላይ መሠረት ያደረገ ግንኙነት ያለ በመሆኑ የክልሉ ተግባር ተገቢ ያልሆነ ሕግን ያልተከተለ ነው፡፡

ወደ ሁለተኛው ጥያቄ ስናልፍ የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች የፌዴራልን ሕግ አንፈፅምም ካሉ ያለው መፍትሄ የፌዴራል ሥርዓቱን እና ሕገ-መንግሥቱን ለመጠበቅ እና ለማስከበር መንግሥት ጣልቃ በመግባት ጉዳዩን ማስተካከልና ማረም ይገባዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትበን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 12 መሠረት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ የወደቀ በመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ጉዳዩን በማጣራትና ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሎች የመመሥረት ሥልጣን አለው፡፡

በአጠቃላይ የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች በፌዴራል መንግሥቱ የሚወጡ ሕጎች ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ናቸው አልፈፅምም የሚል መደምደሚያ ላይ በራሳቸው መድረስ የማይችሉና አድርገውትም ከሆነ ተግባሩ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ከመሆኑም አልፎ የፌዴራል ሥርዓቱን የሚገረስስ፤ ከሌሎች ክልሎች ጋር የመኖርን እጣ ፈንታ አደጋ ውስጥ የሚከት ተግባር በመሆኑ የክልሉ ምክር ቤት ውሳኔውን ወደኋላ መለስ ብሎ መመልከት ይኖርበታል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ችሎት መድፈር በኢትዮጵያ ሕግ: ሕጉና አተገባበር
ሳይፋቱ ፍቺ በተሻሻለው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Sunday, 19 May 2024