Font size: +
5 minutes reading time (1044 words)

ችሎት መድፈር በኢትዮጵያ ሕግ: ሕጉና አተገባበር

"ችሎት መድፈር" ወይም Contempt of Court በአብዛኛው ሃገራት የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ግልጋሎት ላይ እየዋሉ ካሉ የሕግ ፅንሰ ሃሳቦች አንዱ ነው። ይህ የሕግ ፅንሰ ሃሳብ በእኛ ሃገር በሰፊው ሥራ ላይ እየዋለ ቢሆንም ከሕጉ መንፈስ ውጭ አተገባበሩ ላይ የሚታየው የሕግ አተረጓጎም ክፍተትና ልዩነት የተለያዩ የዜጎች መብት ጥሰቶችን ሲያስከትል ይታያል። 

ችሎት መድፈር በኢትዮጵያ ሕግ ምን ይመስላል? አተገባበሩና ችግሮቹስ?

"ችሎት መድፈር" ምን ማለት ነው?

ለሕግ ወይም ለፍርድ ቤት አለመታዘዝ፣ ለችሎት ክብር መንፈግ ወይም የፍርድ ቤትን ሥራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለማወክ መሞከር አልያም ደግሞ በዳኝነት ሥራው ጣልቃ መግባት በተለምዶ "ችሎት መድፈር" ተብሎ ይጠራል።

Black's Law የሕግ መዝገበ-ቃልም በተመሳሳይ ሁኔታ ችሎት መድፈርን " . . . it is the act of demeaning the court, preventing the justice administration, or disobeying a sentence of the court. It is a criminal and can lead to fines to imprisonment . . . በማለት ያስቀምጠዋል።

ለፍርድ ቤት አለመታዘዝ የምንለው በችሎት ሂደት ውስጥ በዳኛው የሚተላለፉ ትዕዛዞችን አለማክበር ወይም መተላለፍ ሲሆን፣ ለችሎት ክብር መንፈግ ደግሞ ፍርድ ቤት ማህበረሰብ ፍትሕ የሚያገኝበት ስፍራ በመሆኑ ሊሰጠው የሚገባውን አክብሮት ለተቋሙና ለዳኛው አለመስጠት ነው።

በሌላ በኩል  ፍርድ ቤትን ማወክ የዳኝነት ሂደቱ ሊካሄድ በማይችልበት ሁኔታ እንዲቋረጥ ማድረግ ወይም ለማቋረጥ መሞከር አልያም ደግሞ ዳኛው በነፃነት ተግባሩን እንዳያከናውን ጣልቃ መግባትን የችሎት መድፈር ልንለው እንችላለን። 

ይህ ፅንሳ ሃሳብ ቀደም ተብሎ በእንግሊዝ እና በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ግልጋሎት ላይ የዋለ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በአብዛኛው ሃገራት የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ይገኛል።

ምንም እንኳን የተለያዩ ጥፋቶች ለችሎት መደፈር ክስ የሚያጋልጡ ቢሆንም አብዛኞቹ የሕግ ሥርዓት እኚህን ጥፋቶች በሁለት አይነት የችሎት መድፈር ይከፍሉታል። የመጀመርያው ባለማወቅ ለሕጉ አለመታዘዝ ሲሆን በአመዛኙ ከግንዛቤ እጥረትና ከቸልተኝነት የመነጨ ነው።  በሌላ በኩል ሁለተኛው አይነት ችሎት መድፈር ደግሞ በፍቃደኝነት ወይም ሆን ብሎ ለሕጉ ታዛዥ አለመሆን ነው።

በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ችሎት መድፈር ተብሎ የሚጠራው ፍርድ ቤቶች በዕለት ተዕለት ተግባራቸው ውስጥ በፍርድ ቤት ውስጥ እና ከፍርድ ቤት ውጪ ሊፈጠሩ የሚችሉ ከችሎት ሂደቱ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ማንኛውንም የዳኝነት ሥራዎችን የሚያውኩ ወይም የሚያደናቅፉ ተግባራትን ለመግታት እንዲቻል ለፍርድ ቤቶች በሕግ የተሰጠ ስልጣን ነው። (ማንኛውም ሲባል የፍትሐብሄር ወይም የወንጀል ጉዳይ ላይ ሊሆን ይችላል)። ይህ ተጠያቂነትም በችሎት ውስጥ በተገኘ በማንኛውም ግለሰብ ችሎቱ ከተሰየመበት ጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያለው ባለ ጉዳይም ሆነ ችሎት በመከታተል ላይ ያለን ወይም ሌላ ከችሎቱ ውጭ የሆነ ግለሰብን ያካተተ ነው።

ችሎት መድፈር ከሌሎች እስር ከሚያስከትሉ የወንጀል ዓይነቶች ለየት የሚያደርገው ጉዳዩ የሚፈጠረው ችሎት ውስጥ በመሆኑ ጥፋተኛውን ወዲያው አስቀርቦ ጉዳዩ በልዩ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር ምንም አይነት ምስክር ወይም ማስረጃ ሳያስፈልገው የሚያስቀጣ መሆኑ ነው። በአመዛኙ አጥፊው ተከሳሽ ሊኖረው የሚችለውን በኢፌድሪ ህገ-መንግስት ምዕራፍ 3 የተካተቱ  መብቶችን የሚያሳጡት ቢሆንም የጥፋተኛውን የችሎት ነባራዊ ሁኔታ ግን ያገናዘበ ነው።

ችሎት መድፈር በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ የተካተተ በወንጀል የሚያስጠይቅ ጥፋት ነው። የሕጉ አንቀፅ 449  ፍርድ ቤትን መድፈር እንደየ ጥፋቱ ቅለትና ክብደት ከአንድ ዓመት የማይልበጥ እሥራት ወይም እስከ 3ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮን እንደሚያስከትል ይደነግጋል።

ምንም እንኳን በመርህ ደረጃ ጥፋት ፈፃሚው ላጠፋው ጥፋት በሕግ የተቀመጠውን  የሕግ ሥርዓት ተክትሎ ዓቃቤ ሕግ ክስ መስርቶና ማስረጃ አቅርቦ ቅጣት የሚያሰጥበት ባይሆንም፣ ጥፋት የፈፀመው ግለሰብ ድርጊቱን የፈፀመው ሊቆጣጠረው በማይችለው ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ከሆነ ያን ሊያስረዳ የሚችል ማስረጃ ቀርቦ ከተጠያቂነት ውጭ የሚሆንበት አግባብ ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ ግለሰቡ የአዕምሮ እክል ካለበት።

ቅጣት አወሳሰን

በወንጀል ወይም በፍትሐብሔር ችሎት ላይ ጥፈት የፈፀመ ግለሰብ ቅጣት የሚተላለፍበት ምክንያታዊና ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ የሕጉን አላማ ለማሳካት ነው። አንቀፅ 449 ሁለት ዓይነት ቅጣቶችን በአማራጭ አስቀምጧል፦

1ኛ. የእስር መቀጮ እና

2ኛ. የገንዘብ መቀጮ

ችሎት መድፈር የሚከሰትበት ችሎት የወቅቱን የጥፋት ደረጃና አጥፊውን ባማከለ መልኩ ቅጣት ሲያስተላልፍ ከእሥራ እና ከገንዘብ እንደ ጥፋቱ ደረጃ አንዱን ሊወስን ይችላል። ይህ ማለት ከሕጉ አረዳድ ሁለቱንም ቅጣት መወሰን የማይቻል እንደሆነና ቅጣቱ ሲተላለፍ የጥፋቱ ደረጃ ከግምት ገብቶ ጥፋተኛውንና ሌላውን ዜጋ ሊያስተምር የሚችለው የትኛው ቅጣት እንደሆነ ከጥፋተኛው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተመዝኖ ሊተላለፍ እንደሚገባ የሚያስረዳ  ነው።

አንድ ሰው በምን አይነት ሁኔታ ችሎት ደፈርክ ሊባል ይችላል?

አንድ ግለሰብ ችሎት ደፈረ ሊባል የሚችልበት ሁኔታ በወንጅል ሕጉ በግልፅ ተዘርዝሯል። በአንቀፅ 449 መሰረትም ለወንጀል ድርጊቱ ተጠያቂ የሚያደርገው ፍርድ ቤቱን ወይም የዳኝነት ሥራ በማከናወን ላይ ያለውን ዳኛ በማናቸውም መንገድ፦

  1. የሰደበ፣
  2. ያወከ፣
  3. በችሎቱ ላይ ያፌዘ፣
  4. የዛተ፣
  5. የፍርድ ቤቱን ሥራ በማናቸውም ሌላ መንገድ ያወከ እንደሆነ ነው።

ከላይ ለማየት እንደሞከርነው ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ሕግ እንደ ሌሎች ሃገራት ፅንሰ ሃሳቡን ከፋፍሎ የሚተነትን ባይሆንም ከሕጉ እንደምንረዳው ጥፋተኛው ጥፋቱን የሚፈፅመው አንድም ባለማወቅና በቸልተኝነት አልያም ደግሞ ሆን ብሎ በማወቅ እንደሆነ ነው።

የሚስተዋሉ ችግሮች

ችሎት መድፈርን በተመለከተ የወንጀል ሕጉ በዝርዝር ሰፋ ባለ ሁኔታ ባይተነትነውም አንቀፅ 449 በቂና ግልፅ የሆነ የማያሻማ መልዕክት አስቀምጧል። ይህም በአመዛኙ ከፅንሰ-ሃሳቡ ጋር ተያይዞ ያለው  ክፍተት የሕግ አረዳድና አተረጔጓም መሆኑን ከሚስተዋሉ ችግሮች መገንዘብ ይቻላል።

ይህ የፍርድ ቤት ስልጣን ወደ ፍርድ ቤት የሚመጣ ማንኛውም ዜጋ የዳኝነት ስርዓትን እንዳያስተጔጉል ወይም እንዳያደናቅፍ ከማድረግ በላይ ማንኛውም ሰው ሕግን እንዲያከብር እና ወደ ተቋሙ የሚመጣው ተገልጋይ ለእነዚህ ተቋማት የሚገባውን ክብር እንዲሰጥ ያስችላል። ከዚህም በተጨማሪ በዋነኛነትም ዳኞች ከማናቸውም ጫና ነፃ ሆነው ሥራቸውን በነፃነት (Judicial Independence) እንዲሰሩ በማድረግም የራሱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ።

ይሁን እንጂ በተጨባጭ ሕጉ በብዙ ፍርድ ቤት ዳኞች ያለአግባብ ጥቅም ላይ ሲውልና ተተርጉሞ ሲሰራበት ይስተዋላል። ዋነኛው ችግርም አንቀፁን በተለያየ ሁኔታ ትርጔሜ በመስጠት ከወጣለት አላማ ውጭ መገልገል ነው። ምንም እንኳን ፍርድ ቤት ከዳኛ ውጭ ብቻውን መገለፅ የማይቻልና ሁለቱ የማይነጣጠሉ ቢሆኑም አንድ አንድ ዳኞች አንቀፁን ከግል ክብር ጋር እያገናኙት በሚፈልጉትና በየትኛውም ስፍራ ጥቅም ላይ ሲያውሉት ይታያል። በተለይም ከባለ ጉዳይ ጠበቆች ጋር ባለው የዕለት ተዕለት  ሥራ ጋር ተያይዞ ጤናማ ካልሆኑ ግንኙነቶችና በዳኞች የስነ-ምግባር መጔደል ምክንያት በርካታ የጥብቅና ባለሙያዎች ለእስርና የገንዘብ መቀጮ ሲዳረጉ ይታያል። አንዳንድ ግዜም ጥፋተኛ የሆነው ግለሰብ በአግባቡ ውሳኔ ሳይተላለፍበት ያለ ውሳኔ በእስር የሚቆይበት ግዜ ይታያል።

በፍርድ ቤት የዕለት ተዕለት የዳኝነት ተግባር አንቀፁ የማያቅፋቸው ድርጊቶችን "ችሎት መድፈር" በማለት ተገልጋይ ዜጎች ሲቀጡና ሌሎች መሰረታዊ የግለሰብ መብቶቻቸው ሲጥሱ ማየትም የተለመደ ሆኗል። ለምሳሌ ያክል በችሎት ውስጥ ተከሳሽ ያለመናገር መብቱን ችሎት ከመድፈር ጋር አያይዞ የፍርድ ቤት የዳኝነት ሥራን አውኳል በማለት ግለሰቡን መቅጣት። ይህም መሰረታዊ ህገ-መንግስቱ የሚያስቀምጠውን መብቶች በግልፅ መበደል ይሆናል ። (የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 19(2) ይመልከቱ). አንድ አንድ ወቅትም በማስተማር ሊታለፉ የሚችሉ ቀላል ጥፋቶችን የእስር ሰለባ ሲያደርጔቸው ይስተዋላል።

ሌላው መሰረታዊው ችግር ቅጣት አወሳሰን ላይ ነው። ይህ አንቀፅ ምንም እንኳን እንደየ ጥፋት ደረጃው እስከ አንድ አመት የሚደርስ ቀላል እስር ወይንም እስከ 3ሺ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ የሚያስከትል እንደሆነ ሕጉ ቢያስቀምጥም፣ ብዙውን ግዜ ዳኞች የጥፋቱን ደረጃ ሳይመዝኑ እና የድርጊቱን ፈፃሚ ግለሰብ ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም ከሁለቱ ቅጣቶች የቱ ድርጊት ፈፃሚውን ያስተምረዋል ብለው ሳይመረምሩ ከገንዘብ ቅጣት እስርን መርጠው ሲቀጡ ይስተዋላል።

ማጠቃለያ

ይህ አንቀጽ ለወጣለት ዓላማ ሊውል ይገባል። የወንጀል ሕግ አላማ ዜጎችን ማረምና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ ስለሆነ ዜጎች ባለማወቅ ጥፋቱን ፈፅመው ለወንጀል ቅጣት እንዳይዳረጉ ሰፋ ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሊፈጠርላቸው ይገባል። በተለይም ደግሞ የማህበረሰባችንን ነባራዊ የሕግ ዕውቀት ያገናዘበ ሊሆን ይገባል።

ከዚህ በዋናነትም ዳኞች ህዝብን እንዲያገለግሉ ከተሰጣቸው ስልጣንና አደራ ባሻገር ልክ እንደማንኛውም ግለሰብና  ዜጋ  ከሕግ በታች መሆናቸውን ሊያስተውሉና በተሰጣቸው አደራ ትልቅ ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል። ይህ ሕግ ለታለመለት አላማ እንዲውልም ፍርድ ቤቶች በቁርጠኝነት ሊሰሩ የሚገባ ሲሆን የብቃትና የአተርጓጎም ልዩነት እንዳይኖር በሕጉ ዙርያ ተመሳሳይ አረዳድ እንዲኖር እንደተቋም መሥራት ከዛም ባለፈ ከሕጉ አላማ ውጭ ሕጉን በሚገለገሉበት ዳኞችም ላይ የሥነ-ምግባር ክትትል ማድረግ ያሻል።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የፍርድ አፈፃፀም መሠረታዊ ታሳቢዎችና ያጋጠሙ ችግሮች
የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች የፌዴራሉን መንግሥት ሕጎች አልፈፅምም ማለት ይችሉ ይሆ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 11 September 2024