በፌዴሬሽን እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ም/ቤቶች የተሰጡ ውሳኔዎች ሕገ-መንግሥታዊነት
በዓለማችን እና በሀገራችን የተከሰተውን የኮቪድ-19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ በሀገራችን የፌደራል መንግሥትና የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች መታወጃቸው ተከትሎ የሀገራዊ ምርጫን መራዘምና ክልላዊ ምርጫ በትግራይ መከናወኑን ከሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች አኳያ እንደሚከተለው አስቀምጣለሁ፡፡
በቅድሚያ ጥቂት በሆነችው ትልቅ ኢ-ሕገመንግሥታዊ ውሳኔን በመግለጽ ልጀምር፡፡ በሕገ-መንግሥታችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊደነገግ የሚገባው በሁለት ምክንያቶች ማለትም፡-
1ኛ/ በሰው ሰራሽ አደጋ (የውጪ ወረራ ሲከሰት እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰት)
2ኛ/ በተፈጥሮ አደጋ (ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የህዝብ ጤንነትን አደጋ ላይ የሚጥቅ ሁኔታ ሲከሰት) ስለመሆኑ የፌደራሉ ሕገ-መንግሥት አ.ቁ 93(1) የሚደነግግ ሲሆን በ2ኛው የተፈጥሮ አዳጋ ሲከሰት የፌደራል መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን ክልላዊ መንግሥቶች አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማውጣት ሥልጣን ይኄው የሕግ መንግሥት አንቀጽ 93(1)(ለ) መብትን ይሰጣቸዋል፡፡ በመሆኑም የሀገራችን የበላይ ሕግ የሆነው አካል ለሁለቱም መንግሥታት እኩል ሥልጣን በሰጠው ጉዳይ ላይ የአንደኛው ከአንደኛው የሚበልጥበት ወይም አንደኛው በአንደኛው ላይ የበላይ የሚሆንበት ሁናቴ የለም፡፡ ነገር ግን የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በክልሎች ከሚወጡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ሁሉ የበላይ ስለመሆኑ መደንገጉ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡
ነገሩ ያለፈ ቢሆን ይህን መጠቆሜ ለነገሩ ትኩረት እንዲሰጥ መግለጹ አስፈላጊ ነው፡፡
የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት
ሀ/ ሕገ-መንግሥታዊ ውሳኔ
ኮቪድ-19 የኮሮና ወረርሽኝ በዓለማችን እና በሀገራችን ተከስቶ የሰው ህይወት ነጥቆ ቤቶቻችንን፣ጎረቤቶቻችንን፣ መንደራችንን እና ሀገራችንን በሀዘን ጥቁር ማልበሱ እና እያለበሰ መገኘቱ ዛሬም መጽናኛ ያጣንለት ሀዘናችን፣ፈውስ ያላገኘንበት እሮሮችን እና ወገሻ ያላከመው የልብ ስብራታችን ነው፡፡
ይህን ወረርሽኝ ተከትሎ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2012ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ አግባብና ትክክለኛ ነው፡፡ የለውጡ መንግሰት ወደ ሥልጣን ከመጣበት እና በህዝብ ካለው ታመኝነት አኳያ ፤ ጥሩ አቅም አላቸው የሚባሉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ውስጥ ለሰላማዊ ትግል መግባታቸውን ተከትሎ ፤ የቀድሞ ገዢ ፓርቲ የነበረው ህወኃት ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ለመዋሀድ ፍቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ ወደ ተፎካካሪ ፓርቲነት መቀየሩ እና ሀገራዊ፣ክልላዊ እና አካባበያዊ ምርጫ የማስፈጸም ሥልጣን የተሰጠውን የምርጫ ቦርድን በበላይነት እንዲመሩት በህዝቡ እጅግ ታማኝነት የተጣለባቸው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንዲመሩት መደረጉ ተከትሎ ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በከፍተኛ ጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎት የነበረ ቢሆንም የወረርሽኙ መከሰትና የወረርሽኙ ባህሪ ምርጫውን ለማስፈጸም እንዳይቻል አድርጓታል፡፡
በዚህም ምክንያት የፌደራል መንግሥቱ አራት አማራጮችን ማለትም፡-
1ኛ/ ሕገ-መንግሥት ማሻሻል
2ኛ/ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ‘በባለአደራ መንግሥትነት እና በውስን ሥልጣን’ ብቻ እንዲቆ ማድረግ
3ኛ/ የሕገ-መንግሥት ትርጉም መጠየቅ እና
4ኛ/ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የቆይታ ጊዜ በማራዘም በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ከነሙሉ ስልጣኑ ማቆየት
አቅርቦ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቶ ጉዳዩን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ሲሆን ምክር ቤቱም ከቀረቡት አራቱ ምርጫ 3ኛውን የህ-መንግሥት ትርጉም በመምረጥ ሕገ-መንግሥትን የመተርጓም ሥልጣን ለተሰጠው የፌደሬሽን ምክር ቤት መላኩ ይታወሳል፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤትም በሕገ-መንግሥቱ አ.ቁ 93 መሰረት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስደንገግ የሚያበቃ ምክንያቶች በተከሰቱ ጊዜ በሕገ-መንግሥቱ ከተደነገጉት 106 አንቀጾች ውስጥ ከአራቱ ማለትም፡-
1ኛ/ አንቀጽ 1- የኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜን
2ኛ/ አንቀጽ 18-ኢሰብአዊ አያያዝ የተከለከ ስመሆኑ
3ኛ-አንቀጽ 25-የእኩልነት መብት
4ኛ/ አንቀጽ 39- ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት እስከ መገንጠል ድረስ ያለቸው መብቶች
በስተቀር ሎሎች የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች ለጊዜው ተፈጻሚ እንዳይሆኑ ታግደው ሊቆዩ እንዲችሉ ማድረግ የሚቻል ስለመሆኑ የሕገ-መንግሥቱ አ.ቁ 93(4)(ሐ) በደነገገው መሰረት በሕገ-መንግሥቱ አ.ቁ 58 ላይ የተመለከተውን የፌደራል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተመራጮች የሥልጣን ዘመንን ማራዘሙ ሕገ-መንግሥታዊ ነው፡፡
ለ/ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ውሳኔዎች
- የክልል መንግሥታትን ሥልጣን ማራዘሙ
የፌዴሬሽን ም/ቤት በሕገ-መንግሥቱ አ.ቁ 62 ላይ ከተሰጡት ስልጣኖች ውስጥ አንደኛው የፌደራል ሕገ-መንግሥቱን መተረጓም ነው፡፡ ይህም በመሆኑ የፌደራል መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና የምርጫው ጊዜ መግጠሙን አስመልክቶ ለተፈጠረው ክፍተት የሕገ-መንግሥት ትርጉም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ጉዳዩ የተመራለት፡፡ ነገር ግን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተመራለት እና ከተጠየቀው ጉዳይ በመውጣት የክልል መንግሥታትን እና ምክር ቤቶችን የሥልጣን ዘመን አራዝሟል፡፡ ይህ በቅደሚያ፡-
ሀ/ ከተጠየቀው የሕገ-መንግሥት ትርጉም ውጪ የሰጠው ውሳኔ በመሆኑ አግባብ አይደለም
ለ/ የክልል መንግሥታትን እና ምክር ቤት የሥልጣን ዘመን የሚወሰነው በራሳቸው የክልል ሕገ-መንግሥቶች ከመሆኑም በላይ የክልላቸውን ሕገ-መንግሥት የሚተረጉምም ምስለ ፌዴሬሽን ም/ቤት የሆነ ኮሚቴ አላቸው፡፡ ስለሆነም የፌዴሬሽን ም/ቤት የክልሎችን ሕገ-መንግሥት የመተርጓም ሥልጣን የሌለው ከመሆኑም በላይ የፊደራላዊ ሥርዓት በተዘረጋበት ሀገራችን እና ዲሞክራሲያዊ የፌደራል ሥርዓትን ለመትከል ደፈ ቀና የሚል የለውጥ መንግሥት ባለበት ሁናቴ የክልል ም/ቤት የሥልጣን ዘመንን እና የክልል መንግሥታትን የሥልጣን ዕድሜ አራዝሜያለው በማለት የሰጠው ውሳኔ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እና የዲሞክራሲውን ጉዞ የሚገታ ብቻ ሳይሆን የሚያቆም ነው፡፡
- የትግራይ ክልል አዲስ ተመራጭ መንግሥትን ከፌዴሬሽኑ እና ከፌደራል መንግሥታት ጋር ግንኙነት እንዳይኖረው ማገዱ
በሀገራችን የነበረውን የብሔሮችን ጭቆናን ዕውቅና በመስጠት እና በዘመናዊው የሀገር ምስረታው ውስጥ ሁሉም ብሔሮች ሚና እንዲኖራቸው በማድረግ እና ተጋግዘው የብሔሮች እኩልነት የሰፈነበት፣ዲሞክራሲ የተረጋገጠበት፣ሰላም የበዛበት እና የበለጸገች ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት የፖለቲካና የሕግ የቃል-ኪዳን ሰነድ የሆነው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት በ1987ዓ.ም ጸደቀ፡፡
ስለሆነም የእነዚህ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች ስብስብ የሆነው የፌዴሬሽን ም/ቤት እነዚህ ወንድማማች የሆኑ ህዝቦች በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ስር የሰደደ አንድነት እንዲኖራቸው ሊሰራ የሚገባው አካል ስለመሆኑ በሕገ-መንግሥቱ አ.ቁ 62(4) ተመልክቷል፡፡ ስለሆነም የፌዴሬሽን ም/ቤት ክልሎችን አስመልክቶ ውሳኔ ሲያሳልፍ ሁሌ መሰረት ሊሆነው እና ትኩረት ሊያደርግ የሚገባው ወንድማማችነትን እና አንድነትን መፍጠር ላይ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ግን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ሲፈጸም ዝም ብሎ ይመልከት ማለት አይደለም፡፡ ይልቁን እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ በግልጽ በሕገ-መንግሥቱ አ.ቁ 62(9) ላይ እንደ ተመለከተው የፌደራል መንግሥት ጣልቃ በመግባት ጉዳዩ እንዲያስተካክለው ሊያስደርግ ይገባል እንጂ ክልሉን ከፌዴሬሽኑ እንዲወጣ የሚያደርግ ማንኛውም ግንኙነት እንዲቋረጥ ውሳኔ መስጠት የሕገ-መንግሰቱን ታሪካዊ ዳራ እና የብሔርና ብሔረሰቦች ለእኩልነትና ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር ያደረጉትን ትግል ያላገናዘበ ነው፡፡ ይህም የዲሞክራሲ ግንባታውን ጉዞ ወደ ኃላ በማዞር ወደ 1967ዓ.ም የሚመልሰው ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ሊታረም ይገባዋል፡፡
2.የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ም/ቤት
ሀ/ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ውሳኔዎች
- የፌደራል መንግሰት ሥልጣን መራዘሙን መቃወሙ
በሀገራችን በተዘረጋው የፌደራል ሥርዓት የክልል መንግሥታት እና የፌደራል መንግሥት ሥልጣንን በመከፋፈል እና በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ደግሞ እኩል ሥልጣን እንዲኖራቸው እና በጋራ እዲወስኑ ሥልጣንን (Concurrent power) ሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም መንግሥታቱ በጋራና በእኩልነት ሥልጣንን በመጠቀም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ሕገ-መንግሥቱ ጸድቆል፡፡
በዚህም የፌደራል ህዝብ ተወካይ እና የፌዴሬሽን ም/ቤቶችን የሥልጣን ዘመን የሚወስነውም ሆነ ሕገ-መንግሥታዊ የሕግ ግጭቶች ሲኖሩ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው በፌደራሉ ሕገ-መንግሥት መሰረት የፌደራሉ የፌዴሬሽን ም/ቤት ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ይህ የፌዴሬሽን ም/ቤት ለቀረበለት ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ውሳኔ በመስጠት የፌደራሉን ህዝብ ተወካይ እና የፌዴሬሽን ም/ቤቶችን የሥልጣን ዘመን በማራዘም በሥልጣን ላይ ያለው የብልጽግና ፓርቲ ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ እስኪከናወን የሥልጣን ዘመኑ ተራዝሟል፡፡
ስለሆነም የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በሌለው ሥልጣን ላይ እና ውሳኔ ሊሰጥበት የማይችልበት ጉዳዩ ላይ በብቸኝነት ባለስልጣ ስለመሆኑ ሕገ-መንግሥቱ ያቋቋመውን የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔን አልቀበልም በማለት በውሳኔው ስልጣናቸው የተራዘመላቸውን አካለት ሕገ-ወጥ ናቸው ሀገሪቷ መንግሥት የላትም በማለት ዘመቻ ማካሄዱ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡
- ከፌደራሉ መንግሥታዊ አካላት ጋር ግንኙነቴን አቁሜያለሁ ማለቱ
ማንኛውም በሀገራችን የሚገኙ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመፈቃቀድና በጋራ ባጸደቁት ሕገ-መንግሥት ላይ እራሳቸውን የማስተዳደር መብት ያላቸው ሲሆን በፌዴሬሽኑ ለመቆየት የማይፈልጉ በሚሆንበት ጊዜ እስከ መገንጠል ድረስ ያላቸውን መብትን በሕገ-መንግሥቱ አስከብረዋል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ክልል ህዝባዊ የምርጫ ሥርዓትን (Referendum) ተከትሎ በሚደረግ ህዝባዊ ውሳኔ ከፌዴሬሽኑ እራሱን እስካላገለለ ድረስ ከፌደራሉ የመንግሥት አካላት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አላደርግም በማለት ውሳኔ የማይችልና ድርጊቱም ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ብቻም ሳይሆን የፌደራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ነው፡፡
- ክልላዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሙ
በሀገራችን የሚከናወኑ ሀገራዊ፣ክልላዊ እና አካባቢዊ ምርጫዎችን ሁሉ እንዲያስፈጽምና እንዲያካሂድ የተቋቋመው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑ በሕገ-መንግሥቱ አ.ቁ 102 ላይ ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም የትግራይ ክልላዊ መንግሰት የሥልጣን ዘመኑ መጠናቀቅን ተከትሎ ምርጫ ለማከነወን በወሰነው ውሳኔ መሰረት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን እንዲያስፈጽም ጠይቆ አሉታዊ ምላሽ ቢሰጠውም እንኳ ምርጫ ቦርዱ ሕገ-መንግሥዊ ግዴታውን እንዲወጣ በፍ/ቤት ወይም በፌዴሬሽን ም/ቤት በኩል አቤቱታ ከማቅረብ ባለፈ በራሱ ክልላዊ ምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሙ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡
ለ/ ሕገ-መንግሥታዊ ውሳኔ
የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ለብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝቦች የሉዓላዊነት ሥልጣን የሰጠ በመሆኑ እና እራስን በመራስ የማስተዳደር መብታቸው እስከ መገንጠል ድረስ ያከበረ ከመሆኑም በላይ ይህ መብታቸው በማንኛውም ሁናቴ ታግዶ ሊቆይ የማይችል ምልዑ መብታቸው (absolute rights) ነው፡፡ እራስን በራስ ማስተዳደር የሚለው መብት ደግሞ የሚያስተዳድረው አካልን መምረጥ ብሎም ይህ አካል በሥልጣን ተለይቶ በተሰጠው ጉዳይ ላይ በሚሰጠው ውሳኔ መገዛትን የሚጨምር ነው፡፡
በመሆኑም የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የራሱን ምክር ቤት ምርጫ ለማካሄድ ውሳኔ ካደረገ ይህን እንዳይፈጸም ሊከለክለው የሚችል ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ የለም፡፡ የፌዴሬሽን ም/ቤትም የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎችን የሥልጣን እና የምርጫ ዕድሜ የመወሰን ሥልጣን የለውም፡፡ ይህን የሚወስነው በክልሉ የበላይ ሕግ የሆነው የክልሉ ሕገ-መንግሥት ብቻ ነው፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments