Font size: +
9 minutes reading time (1850 words)

በገጠር መሬት የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝና አርሶ አደሩ

መሬት ካለው ተፈጥሮዋዊ ባሕርይም ሆነ ግዙፍነት የተነሳ በሃገራችን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማዕከል ሆኖ እስካሁን ዘልቋል፡፡ በተለይም አብዛኛው ሕዝብ በእርሻ  የሚተዳደር ባለበት ሃገር የመሬት ጉዳይ የኢኮኖሚያዊ መሣሪያ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ የሆነ ጠቀሜታ አለው፡፡ የሃገሪቱን የመሬት ስሪት (land tenure) ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከተው በእያንዳንዱ ሥርዓት የተለየ ባሕርይ ይዞ እናገኘዋለን፡፡

በ1966 ዓ.ም በፊት የነበረው የመሬት ስሪት የራሱ ሆነ ባሕርይ የነበረው ሲሆን “የርስት ጉልት” ግንኙነትን ያማከለ ነበር፡፡ መሬት በአብዘኛው የቤተ ክርስቲያን ይዞታ፣ የርስት ጉልት ይዞታ በሚል የተከፋፈለ ነው፡፡ ይህ የመሬት ስሪት በሃገሪቱ አብዛኛውን ክፍል በሚሸፍነው እና መተዳደሪያ መሬት ያለውን አርሶ አደሩን የሚያገል፣ የባለቤትነትም ሆነ የመጠቀም መብትን ዋስትና በማይሰጥ መልኩ የተዋቀረ እንደመሆኑ መሬት በጥቂቶች እጅ እንዲሆን ያደረገ ነበር፡፡

የ1966 ዓ.ም ተከትሎ የመጣው ለውጥ ቀደም ሲል የነበረውን የርስት ጉልት ግንኙነት በመሻር በመሬት ላይ አዲስ መዕራፍ ከፍቷል፡፡ በጊዜው ወደ ሥልጣን የመጣው የደርግ ሥርዓት ይከተል በነበረውን የሶሻሊስት ርዮተ ዓለም በመመራት ኢኮኖሚውን የሚመሩትን ዋና ዋና ነገሮች ከግል ባለቤትነት ወደ ሕዝብ ባለቤትነት ሲያሸጋግር መሬትም የገጠር መሬትን የሕዝብ ኃብት ለማድረግ በሚል አዋጅ ቁጥር 31/67 የሕዝብ ኃብት በሚል ታወጀ፡፡ አዋጁም መሬት አይሸጥም አይለወጥም የሚለውን ጥብቅ የሆነና የመሬት ጉዳይን ከሌሎች ንብረቶች የሚለየውን ገደብ ይዞ ብቅ ብሎ ነበር፡፡ 

ምንም እንኳን እንደ አዲስ የተደረገው የመሬት ስሪት ለውጥ ከገባር ሥርዓት አውጥቶ ወደ ሕዝብ ያሸጋገረ ክስተት ቢሆንም መሬት ተጠቃሚውን መብት ያጣበበ ነበር፡፡ የገጠር መሬትን የሕዝብ ለማድረግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 31/67 አንቀጽ 5 አንድ የመሬት ተጠቃሚ  በይዞታ የያዘውን መብት መሸጥ፣ መለወጥ፣ በስጦታ ማስተላለፍ፣ በማስያዝ፣ በወልድ አገድ ወይም በሌላ ሁኔታ ማስተላለፍ እንደማይችል ገደብ ያስቀምጣል፡፡

ቀጣዩ የሽግግር መንግሥትም በተመሳሳይ መሬት የሕዝብ ሆኖ እንደሚቀጥልና የመሬት ተጠቃሚ ሆኑ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች መሬት የማግኘት መብት እንዳለቻውና የመሬት የመጠቀም መብታቸውና ባለይዞታነታቸው ሕጋዊ ዋስትና እንደሚሰጣቸው በመግለጽ የሽግግር ሥራውን ሕገ መንግሥታዊ መሠረት በማስያዝ ቀርቧል፡፡

የመሬት ስሪት በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት

“የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የተፈጥሮ ኃብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው፡፡” (አንቀጽ 40(3)) ይህ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ የገጠር መሬትን በእጁ ያደረገ ባለይዞታ መሬቱን መሸጥም ሆነ መለወጥ አይችልም፡፡ ባለይዞታው ከመሸጥ ከመለወጥ ውጪ ያሉ ሌሎች መሬቱን ተከትሎ የሚመጡ መብቶችን መጠቀም ይችላል የሚል አንድምታ ያለው ነው፡፡ የመሬት የይዞታና የመጠቀም መብት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት አቋም ያለው ነው፡፡ የመሬትና የተፈጥሮ ኃብት አጠቃቀምና ጥበቃን በተመለከተ ለሚወጡ ሕጎች በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 51(5) መሠረት የፌደራል መንግሥት ሥልጣን ያለው ቢሆንም   በአንቀጽ 52(2)(መ) እንደተቀመጠው ክልሎች በፌደራል የሚወጠውን የሕግ መርህ በመከተል መሬትን ለማስተዳደር ሕግ የማውጣት ሥልጣን ተሰጦዋቸዋል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማም የመሬት ባለይዞታ የሆነው አርሶ አደር በመሬት የመጠቀም መብቱ እስከምን ድረስ ነው? የፌደራልና የክልል የመሬት አጠቃቀም አዋጅ ስለመጠቀም መብት በተለይ ስለዋስትና ምን ዓይነት አቋም አላቸው? የሚለውን ሚዳስስ ይሆናል፡፡

ዋስትና የሚለው ሃሳብ የሚመጣው አንድ ሰው በውል ለገባው ግዴታ እንደ መተማመኛ መያዣ ሆኖ የቀረበው ነገር የገባውን ግዴታ ባይፈፅም አሳልፎ የሚሰጥበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱን አሠራር በመሬት አውድ አውርደን ስንመለከተው አንድ የመሬት ባለይዞታ ለገባው ግዴታ  በመሬት “የመጠቀም መብቱን” በዋስትና መልኩ የሚያቀርብበት አግባብ መኖር አለመኖሩን ነው፡፡ የመጠቀም መብት እና ዋስትና ሊገናኙ የሚችሉት አንድ የመሬት ባለይዞታ የገባውን ግዴታ መፈፀም ባይችል ግዴታው ሊሸፈን እስከሚችልበት ድረስ ባለገንዘቡ ባለይዞታውን በመተካት በመሬቱ ምርት እንዲጠቀም ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ለዋስትና ማያዣነት ይቀርባል ወይስ አይቀርብም የምንለው ጉዳይ በመሬት የመጠቀም መብትን እንጅ የመሬት ይዞታነቱን አይደለም፡፡ ምክንያቱም በመሬት መጠቀም መብቱ ከይዞታ የጠበበ በመሆኑ ነው፡፡ የመጠቀም መብት መሬቱን እያረሰ በፍሬው በመጠቀም ብቻ ተገድቦ የሚቀር ነው፡፡

በመሬት የመጠቀም መብት፣ ሕገ መንግሥት እና የፌደራልና ክልሎች የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መወሰኛ አዋጅ

ወደ ዋና ነጥባችን ስንመጣ በመሬት የመጠቀም መብቱን በዋስትና ማስያዝ የሚችለው ማን ነው? ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ የፌደራል እና ክልል ሕጎች ምን ዓይነት አቋም አለቸው? የሚለውን እንመለከታለን፡፡

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት መሬትን ተከትለው የሚመጡ መብቶችን በተመለከተ በአንቀጽ 40(3) “መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ” ብሎ ገደብ ከማስቀመጡ ውጪ ዝርዝር ሁኔታዎችን አልደነገገም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ስለመሬት አጠቀቀም ዝርዝር ሁኔታዎች በሕግ እንደሚደነገግ በማስቀመጥ አልፎታል፡፡

በፌደራል ደረጃ የሚወጡ የመሬት ሕጎች በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል ተፈፃሚ ከመሆናቸው ባሻገር ክልሎች መሬትን ለማስተዳደር ለሚያወጡት ሕግ፣ ደንብና መመሪያ እንደ አቅጣጫ ጠቋሚ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ በፌደራል መንግሥቱ የተለያዩ ሕግና ደንቦች ወጥተው ሥራ ላይ የዋሉ ሲሆን እነዚህም አዋጅ ቁ. 89/89፣ 456/97፣ 455/99 እና ደንብ ቁጥር 135/99 ናቸው፡፡ ስለ አርሶ አደር በመሬት የመጠቀም መብት በእነዚህ ሕጎች ተደንግጎ ይገኛል፡፡

አዋጅ ቁጥር 456/99 አንድ የመሬት ባለይዞታ የመሬት ባለይዞታ መብቱን በስጦታ የመስጠት፣ የማውረስ እንዲሁም ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት የማከራየት መብት አለው በማለት ይደነግጋል (አንቀጽ 5(2)፣ 8(1-3)፣ 8(5) ይመለከተዋል)፡፡ ይህ አዋጅ ክልሎች በግዛት ወሰናቸው የሚገኙ መሬቶችን ለማስተዳደር በፌደራል ደረጃ የወጡትን መሪ መርሆችን በመከተል ሕግ እንዲያወጡ ያስገድዳል (አንቀጽ 17ን ይመለከተዋል)፡፡

በፌደራል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 456/97 የተደነገገው አርሶ አደሩ የመጠቀም መብቱን በዋስትና ማስተላለፍ እንደሚችል ሳይሆን በአንቀጽ 8(4) በሊዝ ሥርዓት መሬትን  የተከራየ ባለኃብት የመጠቀም መብቱን እንደ ዋስትና ማስያዝ እንደሚችል ነው፡፡ ይህን የፌደራል ሕግ ተከትሎ ክልሎችም የራሳቸውን ሕግ ሲያወጡ በፌደራል ሕጉ ከተደነገገው ውጪ አዲስ ነገር አልጨመሩም፡፡ የአማራ ክልል በአዋጅ ቁጥር 133/98 አንቀጽ 19(1)፣ የኦሮሚያ ክልል በአዋጅ ቁጥር 130/99 አንቀጽ 15(15)፣ የደቡብ ክልል በአዋጅ ቁጥር 110/99 አንቀጽ 8(4)፣ የትግራይ ክልል በአዋጅ ቁጥር 136/200 አንቀጽ 15(3) አንድ የገጠር መሬትን በሊዝ የተከራየ ባለኃብት የመጠቀም መብቱን በዋስትና ማስያዝ ይችላል በማለት ቢደነግጉም የገጠር መሬትን በይዞታነት የያዘ አርሶ አደር የመጠቀም መብቱን በዋስትና ሊያስዝበት የሚችልበትን አግባብ ግልጽ ሳያደርጉ አልፈውታል፡፡ የሁሉም ክልሎች የገጠር መሬት ሕጎች ስለ አርሶ አደሩ የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ መቻል አለመቻል የራሳቸውን ድንጋጌ ሊያስቀምጡ ያልቻሉት የፌደራል መንግሥት ባወጠው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መርህ መመራት በሚል ትርጓሜ የሚያሰጥ ነው፡፡

የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ እና የሰበር እይታ

የአርሶ አደሩን መሬት የመጠቀም መብት በዋስትና ማስያዝ በተመለከተ ያለውን ክፍተት ተከትሎ የተለያየ ይዘት ያላቸው በዋናነት ሁለት አቋሞች ይንፀባረቃሉ፡፡ በአንድ በኩል አርሶ አደሩ መሬት የመጠቀም መብቱን በዋስትና ማስያዝ አይችልም የሚል አቋም ሲንጸባረቅ በሌላ በኩል አርሶ አደሩ መሬት የመጠቀም መብቱን በዋስትና ማስያዝ አልተከለከለም የሚል አቋም ይስተዋላል፡፡

የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ አይቻልም የሚለው አቋም

የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ የማይችልበት ዋና ምክንያት ሕገ መንግሥቱ መሬት አይሸጥም አይለወጥም በማለት የደነገገው ድንጋጌ መተርጎም ያለበት ባለመሬቱ ከይዞታው እንዳይፈናቀል ከሚለው መሠረተ ሃሳብ በመነሳት ነው፡፡ ይህ ዓይነት ትርጓሜ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረጃም የተሰጠ ነው፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአዋጅ ቁጥር 454/97 በተሰጠው ሥልጣን በፍ/ብ/መ/ቁ 69291 ቅፅ 13 ላይ  በሰጠው የሕግ ትርጉም መሬትን ተከትሎ የሚመጣ የዋስትና መያዣ ውል ሕጋዊ አይደለም በማለት አሳሪ ትርጉም አስቀምጧል፡፡ በሰበር ቀርቦ የታየው ጉዳይ መታየት የጀመረው በኦሮሚያ ክልል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ጉዳዩ አመልካችና ተጠሪ የብድር ውል አድርገው ተጠሪ ያላትን ሦስት ቁርጥ መሬት ለአመልካች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲጠቀምበት ግዴታ በገባችው መሠረት የተፈጠረ ክርክር ነው፡፡ ሰበር ሰሚው ፍርድ ቤት ግራ ቀኙ ያደረጉት ውል በመሠረታዊ ይዘቱና ባሕርይው ተጠሪ በመሬቱ ላይ ያላትን የመጠቀምና የይዞታ መብት ለዘለቄታው ለአመልካች በብር 1020 ለመሸጥ መሆኑን የሚያሳይ ነው በማለት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 40(3) እና(4) ጠቅሶ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የመንግሥትና የሕዝብ ኃብት ነው፤ አርሶ አደሩም ከመጠቀምና ከይዞታው መብቱ መፈናቀል አይገባውም፡፡ አመልካችና ተጠሪ ያደረጉት ውል በመሠረታዊ ይዘቱና ሞራላዊ ባሕርይው የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የሚጥስና አርሶ አደሩን የባለይዞታ መሆንን በመሬት የመጠቀም መብትን እና ከይዞታ ያለመፈናቀል መብት የሚጥስ ከመሆኑ በተጨማሪ የፌደራል ሕግ ያወጣውን አዋጅ 456/97 እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ያወጣውን አዋጅ 130/99 ድንጋጌዎች የሚቃረን ሕገ ወጥ የሆነ ውል ነው በማለት ምክንያቱን ተንትኖ አስፍሯል፡፡

ከዚህ ሰበር ውሳኔ በቀላሉ መረዳት የሚቻለው አንድ የገጠር መሬት ባለይዞታ የሆነ አርሶ አደር የመሬት ይዞታ መብቱንም ሆነ የመጠቀም መብቱን በዋስትና በእዳ ማስያዝ አይችልም፡፡ የፌደራልና የክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መወሰኛ አዋጆች አርሶ አደሩ የመጠቀም መብቱን በዋስትና ማስተላለፍ ይችላል ባላሉበት ሁኔታ ውሉ መደረጉ ከሕጉ ጋር ይቃረናል የሚል ዕይታ ያለው ነው፡፡

የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ አልተከለከለም የሚለው አቋም

ሁለተኛው አቋም የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ ሊከለከል አይገባም የሚለው ነው፡፡ የዚህ አስተሳሰብ አራማጆች ምክንያቶቻቸውን ከሕግ እሳቤ እና አርሶ አደሩ በመሬት ላይ ካለው ተጓዳኝ መብት ይዘት አንፃር በመነሳት ያስቀምጣሉ፡፡ በፌደራልና በክልል የገጠር መሬት አጠቃቀም በሕግ ደረጃ የተያዘው አቋም ተመሳሳይ ቢሆንም ስለ አርሶ አደሩ የመጠቀም መብቱን በዋስትና ማስያዝ በተመለከተ ያለውን መብት ሳይወስኑ ማለፉቸው አከራካሪ ጉዳይ ነው፡፡ የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ መሬትን የመሸጥም ሆነ የመለወጥ ውጤት አያስከትልም፡፡ የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ አልተከለከለም የሚል አቋም አራማጆች የፌደራልና የክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መወሰኛ አዋጆች ለግል ባለኃብቱ መሬትን የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ ፈቅደው አርሶ አደሩን በተመለከተ በዝምታ ማለፋቸው አግባብ አይደለም የሚል ክርክር ያነሳሉ፡፡ በተጨማሪም በግልጽ ያልተከለከለ ድርጊት እንደተፈቀደ ይቆጠራል በሚለው የሕግ አተረጓጎም የአዋጆቹ ድንጋጌ ሊታይ ይገባዋል የሚል ሃሳብም ያቀርባሉ፡፡ የአርሶ አደሩን በመሬት የመጠቀም መብት በዋስትና የማስያዝ መብት የፌደራልና ክልል የመሬት ሕጎች የያዙትን አቋም ከሕገ መንግሥቱ ጋር መመልከት አስፈላጊ ነው በማለት ያስቀምጣሉ፡፡

በተጨማሪም የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40(3) “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የተፈጥሮ ኃብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው፡፡” በማለት ያስቀምጣል፡፡ ይህ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ መሬትን በተመለከተ ከሌሎች ንብረቶች በተመለከተ ያስቀመጠው አቋም መሬት ያለውን መብት ገድቦ በማስቀመጥ የመብቱን ስፋትና ጥበት በመወሰን ነው፡፡  የገጠር  መሬትን በእጁ ያደረገ ባለይዞታ መሬቱን መሸጥም ሆነ መለወጥ አይችልም፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ባለይዞታው ከመሸጥ ከመለወጥ ውጪ ያሉ ሌሎች መሬቱን ተከትለው የሚመጡ መብቶችን መጠቀም አይችልማ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁን ከዚህ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ ይዘት መረዳት የሚቻለው አንድ ባለመሬት መሬትን ከመሸጥ ከመለወጥ ውጪ ያሉ መብቶች እንደተፈቀደለት ነው፡፡ በመሬት የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ ደግሞ ራሱን የቻለ ከመሸጥ ከመለወጥ ክልል ውጭ ያለ ድርጊት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ መሬት ባለይዞታ በሕግ አግባብ የያዘውን የይዞታ መሬት እስካልሸጠውና እስካለወጠው ድረስ የመጠቀም መብቱን በዋስትና የማስያዝ መብት እንዳለው የሚያመላክት ነው፡፡ ከመሬቱ ጋር ህይወቱን አስተሳስሮ ኑሮውን ለሚመራው አርሶ አደር የመጠቀም መብቱን በዋስትና እንዳያሲዝ ገድቦ ለግል ባለኃብቱ መፍቀድ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡  የሁለተኛው አቋም አራማጆች ስለመጀመሪያው አቋም አራማጆች ለሚነሳው መከራከሪያ ሕገ መንግሥቱንና የአርሶ አደሩን የመጠቀም መብት ነጣጥሎ ከመመልከት የመጣ ነው በማለት መልስ ለመስጠት ይሞክራሉ፡፡

በመጀመሪያው የሕግ ዕይታ እንደ ጸሐፊው አስተያየት አንድ ባለመሬት የመጠቀም መብቱን በዋስትና ማስያዝ ከተፈቀደለት የገባውን ግዴታ መፈፀም በማችይልበት ጊዜ መሬቱን ለባለመብቱ አሳልፎ ይሰጣል፤ ይህ ሁናቴ ደግሞ መሬትን እንደ መሸጥ የሚቆጠር ስለሆነ አርሶ አደሩን ከመሬቱን በማፈናቀል ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎችን ይንዳል የሚል መከራከሪያ የሚቀርብ ነው፡፡ ሆኖም ግን በዋስትናው መሠረት መሬቱ ወደ ባለገንዘቡ ይተላለፋል ከማለት ይልቅ አርሶ አደሩ ከይዞታው የማይፈናቀልበትን ሁኔታ በማመቻቸት በመብቱ ተጠቃሚ የሚያደርግበትን አግባብ መፍጠር የተሻለ ነው፡፡ የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ በጊዜ ገድቦ መፍቀድ ውጤቱ የመጠቀም መብትን በኪራይ በማስተላለፍ ከሚያስከትለው ውጤት የተለየ ስለማይሆን የመጠቀም መብትን ማከራየት ፈቅዶ የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ አለመፍቀድ የመሬት ባለቤት የሆነውን አርሶ አደር መብት ማጥበብ ስለሚሆን በጊዜ ገደብ ማስቀመጡ አማራጭ ሃሳብ ነው፡፡

ባለመሬቱ የገባውን ግዴታ ባለመፈፀሙ መሬቱን ለባለዕዳው አሳልፎ በመስጠት ሊፈናቀል ይችላል የሚለውን ፍራቻ ለማስቀረት ለግል ባለኃብቶች የተሰጠውን የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ እንደሚችል ያስቀመጠውን ሁኔታ በተመሳሳይነት መጠቀሙ ተመራጭ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በአማራ ክልላዊ ብሔራዊ መንግሥት የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 133/98 አንቀጽ 19(5) የግል ባለኃብቶች የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ የሚችሉት ለ25 ዓመት ነው በማለት ገድቦ መብቱን ጠብቋል፡፡ አርሶ አደሩን የመጠቀም መብቱን በዋስትና እንዲያስይዝ እንደ ግል ባለኃብቶች ፈቅዶ መሬቱ ከእጃቸው ግዴታ ባለመፈፀማቸው ምክንያት ለባለዕዳው እንዳይተላለፍ በጊዜ ገደብ ማስቀመጡ የሁለቱን ወገን ሃሳብ አቻችሎ ለመሔድ የሚያስችል ሚዛናዊ ሁኔታ መፍጠር ይቻላል፡፡

አርሶ አደሩ የመጠቀም መብቱን በዋስትና ባለማስያዙ ከሚያጣው ጥቅም በተጨማሪ ውጤቱ በሌሎች ተጓዳኝ መብቱም እንዳይጠቀም ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የፌደራል የመሬት ሕጎችና ሁሉም የክልል የመሬት አዋጆች ለኢንቨስተሮች ከአርሶ አደሩና ከመንግሥት በኪራይ ወይም በሊዝ መሬት ማግኘት እንደሚችሉ ደንግገዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም በሊዝ የተከራየ ባለኃብት የመጠቀም መብቱን በዋስትና ማስቀመጥ እንደሚችልም አስቀምጠዋል፡፡ በፌደራልና ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መወሰኛ አዋጆች “ኪራይ” አርሶ አደሩ የይዞታ መሬቱን ለሌው የሚያከራይበት ሲሆን፤ “ሊዝ” ደግሞ አንድ ባለኃብት የገጠር መሬትን ከመንግሥት በኪራይ የሚያገኝበት አሰራር እንደሆነ በትርጓሜ ክፍላቸው ይደነግጋሉ፡፡ በሊዝ የተከራየ ባለኃብት ብቻ የመጠቀም መብቱን በዋስትና እንዲያስይዝ መፍቀድ አርሶ አደሩ መሬቱን የማከራየት መብቱን በተዘዋዋሪ ከማጥበብና ከመገደብ ጋር ተይያዞ ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ምክንያቱም አንድ መሬት ሊከራይ የፈለገ ባለኃብት መሬት ሊከራይ የሚችለው ሰፊ መብት ሊሰጠው የሚችለውን ሁኔታ መርጦ ነው፡፡ በሊዝ የሚከራይ ባለኃብትም ከአርሶ አደሩ በኪራይ ከሚያገኘው የተሻለ የመጠቀም መብቱን በዋስትና የማስያዝ መብት የሚሰጠው ስለሆነ ከአርሶ አደሩ ምንም ዓይነት የኪራይ ውል እንዳያደርግ ገፊ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

በአጠቃላይ የአርሶ አደሩን በይዞታ የመጠቀም መብት በዋስትና ማስያዝ ግልጽ የሆነ ድንጋጌ አለመቀምጡ እንዲሁም ከመንግሥት በሊዝ የተከራየን የግል ባለኃብት የመጠቀም መብቱን በዋስትና እንዲያስይዝ ፈቅዶ ከአርሶ አደሩ በኪራይ ያገኘውን የመጠቀም መብት በዋስትና ማስያዝ ይችላል አይችልም የሚለውን ጉዳይ ሁሉም ሕጎች ሳይደነግጉ ማለፋቸው አከራካሪ ጉዳይ ነው፡፡

ሕጎች ግልጽ ሆነው ባልተቀመጡ ወቅት ለትርጉም ክፍት ከመሆናቸው የተነሳ ማስተካከያ እስከሚደረግባቸው የተጠቃሚውን መብት ሊያጣብቡ የሚችሉበት ሁኔታ ሰፊ ከመሆኑ በተጨማሪ ወጥ የሆነ የሕግ አሠራር እንዳይኖር በር ከፋች ነው፡፡ በተለየም እንደ መሬት ባሉ ጉዳዮች አከራካሪ የሆነ ጉዳዮች ሲኖሩ ተፋፃሚ የሚሆነው ስፋት ባለው የኅብረተሰብ ክፍል እንደመሆኑ እና መሬት ካለው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ አንፃር ጉዳዩ ትኩረት የሚሻው ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በጣልቃ ገብ እና የተያዘ ወይም የተከበረ ንብረት ይለቀቅኝ  አቤቱታ ላይ የዳኝነ...
Joint Ownership of Land and Right of Secession in ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 16 July 2024