አገሬው ስለ ሕግ ሃያልነት ሲናገር "በሕግ አምላክ ሲባል እንኳን ሰው ወራጅ ውሃ ይቆማል" ይል ነበር፡፡ ሕግ ተፈጥሮንም እስከማቆም ሃይል እንዳለው አድርጎ ለመግለፅ ምን ዓይነት በሕግ የፀና እምነት ቢኖር ነበር ያስብላል፡፡ በሕግና ፍትሕ ላይ እምነት ያለው ሕዝብ ያለማንም አስገዳጅነት ለሕግ ተገዢ ነው፡፡ ክስተቶችንም ተከትሎ ለሕግ ያለውንም እምነት በተለያዬ መንገድ ይገልፃል፡፡ ግጭቶችን በጉልበት ከመፍታት በሕግ መፍታት ተመራጭ እንደሆነም ያምናል፡፡ በጉልበቱ አዳሪ ሲገጥመው ሰይፍን በሰይፍ ከመመለስ በሕግ አምላክ ቢል ይመርጣል፡፡ ከማትረባ ጉልበት በሕግ አምላክ ይሻላል የሚለውም ለዚህ ይመስላል፡፡ ስለዚህ የሕግ መከበር ሕበረተሰቡ ስለሕግና ፍትሕ ባለው አመለካከት ይወሰናል ማለት ነው፡፡ ሕግ በሕበረተሰቡ ውስጥ በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ እንዲያመጣ ከተፈለገ እያንዳንዱ ሰው ስለሕግ ያለው አመለካከት አብሮ መመለወጥና ማደግ ይኖርበታል፡፡ ሕበረተሰቡ ለሕግና ፍትሕ ያለው አመለካከት ሁለት ነገሮችን ይገልፅልናል፡፡ በአንድ በኩል ሕብረተሰቡ ስለሕግ ያለውን እምነት ሲገልፅልን በሌላ በኩል ደግሞ የሕግ መከበር ያለበትን ደረጃ ያሳየናል፡፡
ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት ሳይዋቀር በፊት አገሬው ስለሕግ የበላይነት የፀና እምነት ነበረው ማለት እንችላለን፡፡ አስገዳጅ ነገር ሳይኖር በአገር ደንብ ብቻ መንገድ ላይ ባላጋራውን ሲያገኘው በሕግ አምላክ ብሎ ተላላፊው መንገደኛ ጉዳዩን እንዲመለከትለት ያደርግ ነበር፡፡ ተላላፊው መንገደኛም ዳኝነቱን ተቀብሎ የግራ ቀኙን ጉዳይ ሰምቶ ይፈርዳል፡፡ ውሳኔው ከተስማማቸው ይፈጽማሉ ካልተስማቸው በአካባቢው ወዳለው ጭቃ ሹም ተያይዞ መሄድ ነው፡፡ ይህን ተላላፊ መንገደኛ ዳኛ የሕግ ሙሁር አበራ ጀንበሬ የመንገድ ዳሩ ፍርድ ቤት(የመንገድ ዳር ዳኛ) በማለት ሲገልፁት ከሳቴ ብርሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ "ዳኛ የውሃ ወራጅ ዳኛ" በማለት ይገልፀዋል፡፡ ስያሜው ምንም ይሁን ተላላፊውን መንገደኛ ዳኛ፣ ባላጋራዎችን ተከራካሪ አድርጎ ሲያቆማቸው የነበረው ያገር ደንብና ልማድ፣ፈቃደኝነትና ለሕግና ፍትሕ የፀና እምነት መኖር እንጅ ሌላ አስገዳጅ ሃይል አልነበረም፡፡
ሕዝብ ስለሕግና ፍትሕ ባለው የፀና እምነት ብቻ አገር ይዳኝ እንደነበር ሌላ ምሳሌ እንመልከት፡፡ በአዶልፍ ፓርለሳክ ተፅፎ ተጫኔ ጆብሬ መኮንን በተረጎመው የሃበሻ ጀብዱ መፃፍ የተገለፀ ነገር ነው፤ ታሪኩ 1928 ዓ.ም አካባቢ አዲስ አበባ ገበያ ላይ የተመለከተው ነበር፡፡ ለአንባቢ እንዲመችና የነገሩን ሥር እንዳልስተው ቢረዝምም ተርጓሚው እንደፃፈው ሙሉ ታሪኩን ላስቀምጠው፡-
"በጨርቅ ተራ ሁለት ገበያተኞች ይጨቃጨቃሉ፤ጨርቁን የሚገዛው ሰውየ እጅግ በጣም ረጅም ሲሆን ሻጩ ደግሞ በጣም አጭር ነው፡፡ እናም ገዥ በሚችለው መልኩ ክንዱን ዘርግቶ፣ጣቶችን ወጥሮ አስር ክንድ ለካና ምልክት አደረገ፡፡ ሻጩ ደግሞ በሚችለው ሁሉ ጣቶችን ወጥሮ አስር ክንድ ለካና እሱም ምልክት አደረገ፡፡ ሁለቱ በለኩት መካከል ከአንድ ክንድ የሚበልጥ ልዩነት መጣ፡፡ ገዥው ሻጩን አውቆ ክንዱን ሳይወጥር ይለካል ሲል አመረረ፡፡ ሻጩ በምኒልክ እየማለ ሃቀኛ ነጋዴ መሆኑን እግዚአብሔርን ምስክርነት ጠራ፡፡ በዚህ መሀል ብዙ ወሬኛ ገበያተኞች ከበቧቸው፡፡ በነዚህ ወረኞች ፊት ሁለቱም ደጋግመው ቢለኩም ልዩነቱ ተመሳሳይ ነበር፡፡ እናም መግባባት ባለመቻላቸው ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ዳኛ ፍለጋ መሄድ ነበርና ሸማቸውን አያይዘውና አቆላልፈው፣ ጎን ለጎን ግራና ቀኝ እጃቸውን በነጠላቸው ጫፎች ሸብ አድርገው አስረው ከቋጠሩ በኋላ ወደ ገበያው ሽምጋይ ዳኛ በብዙ ወረኞች ታጅበው ሄዱ፡፡