ተጨማሪ ሃሳቦች ስለ ግብርና እድገትና የመሬት ፓሊሲና ሕግ

ከዚህ በፊት ባለው ጽሁፍ የሚከተሉትን ሃሳቦች አቅርቤ ነበር። በዋናነት የእነዚህ ሃሳቦች ተግባራዊነት ዉጤት፤ አሁን ተበጣጥሶ የሚገኘውን በገጠር መሬት ላይ የግብርና ውሳኔ መብት በአንጻራዊነት እንዲማከል ማድረጉ ነው። የግብርና ውሳኔ ማለት፥ በአንድ እርሻ ላይ ምን ላምርት? መቼ ላምርት? ምን አይነት እና መጠን ያለው ማዳበሪያ ልጠቀም? ምን አይነት የውሃ ቴኬኖሎጂ ልጠቀም? ምን አይነት ማረሻ፥ ማጨጃ፥ እና መውቂያ ልጠቀም? ምን አይነት የመሬትና አፈር ጥበቃና አስተዳደር አሰራሮችን ልከተል? እና የመሳሰሉት ናቸው። ከግብርና ውሳኔዎች ጋር የሚገናኙ የገበያ ውሳኔዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ፤ ምን ያህል ምርቴን፥ መቼ፥ ለማን ልሽጥ? ምን ያህል ገንዘብ፥ ከማን፥ በምን ያህል ወለድ ልበደር? እነዚህና የመሳሰሉት ገበያ ነክ ውሳኔዎች ካነሳኋቸው ነጥቦች ጋር በቀጥታ አይገናኙም። እኔ ያነሳሁት የግብርና ውሳኔዎችን ነው።

አሁን ባለው ሁኔታ ሁለት አይነት መበጣጠሶች ይታያሉ። አንደኛው በቀደመው ጽሁፍ እንዳብራራሁት የመሬት መበጣጠስ አለ። በእርግጥ የመሬት መበጣጠሱ ሁኔታ እንደቦታው ይለያያል። እኔ ያደኩበትን አካባቢ ኢህአዴግ ከደርግ ነጻ እንዳወጣና ደርግን ተክቶ የሕዝብ አስተዳደር ሃላፊነትን ሲወስድ ካደረጋቸው ነገሮች አንደኛው መሬትን መልሶ ማከፋፈል ነው። ለምን? ምክንያቱም ጥቂት ‘አድሃሪያን’ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ጥሩ ጥሩ መሬቱን በብዛት ስለያዙት። እኔ በበኩሌ የመሬት ክፍፍልና ራሱን አልቃወምም። የኔ ነጥብ የዚህ መሬት ክፍፍልና የክፍፍሉ ስልት ስለፈጠረው የመሬት መበጣጠስ ነው። እንደገለጽኩት አንድ ገበሬ ከግማሽ ኳስ ሜዳ ያነሱ፥ ሶስትና አራት እርሻዎች ይኖሩታል። አንደኛው የጓሮ መሬት ሲሆን ሌሎች ከመኖሪያ ጎጆዉ በተለያየ አቅጣጫ በተለያየ እርቀት ይገኛሉ።  የመሬት መበጣጠስ የምለው ይሄን ነው። ሁለተኛው አይነት መበጣጠስ፥ የግብርና ውሳኔዎችን የመስጠት መብት መበጣጠስ ነው።

 

ኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል (economy of scale)

የሁለት አይነት መበጣጠሶች፥ መጠን/ስኬል ከሚያስገኘው ጥቅም መጠቀም እንዳንችል ሆኗል። ብዙ አይነት የስኬል ጥቅሞች አሉ። አንደኛው ስኬል የሚባለውና ብዙ የሚታወቀው፥ ‘ኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል’ ነው። ‘ኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል’ ማለት በብዛት በማምረት የሚገኝ የነፍስ ወከፍ ወጪ መቀነስና የምርት መጨመር ነው።

ለምሳሌ አንድ መፅሃፍን በ200 እና በ2000 ቅጂዎች ስናሳትመው፥ የነፍስ ወከፍ ወጪው ይለያያል። 200 መፅሃፍ ሲታተም የአንዱ መፅሃፍ ወጪ 800 ብር ሊሆን ይችላል። በሌላ መልኩ 2000 ሲታተም ግን የነፍስ ወከፍ ወጪው 80 ብር ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አንድን ምርት በብዛት በማምረት የሚገኝ ጥቅም ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? በብዙ ምክንያቶች።

 

አንደኛ ለምርቱ የሚያስፈልጉ ቋሚ ወጪዎች (fixed costs) ይኖራሉ። ትንሽ ቢመረትም፥ ብዙ ቢመረትም ቋሚ ወጪው ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ ቋሚ ወጪዎችን በሚገባ በመጠቀም፥ ምርትን ማላቅ ይቻላል። ሁለተኛው፥ በብዛት ማምረት ስፔሻላይዜሽንን ያበረታታል። ስፔሻላይዜሽን ደግሞ ምርትን ይጨምራል። ስፔሻላይዜሽን ምርትን የሚጨምረው ልምምድ በሚያመጣው የአቅም መዳበር፥ ከአንድ ስራ ወደ ሌላ ስራ በተደጋጋሚ በመዞር/በመቀያየር የሚባክን ጊዜና የትኩረት መባከንን ይቀንሳል። እንዲሁም ስፔሻላይዜሽን ለስታንዳርዳይዤሽንን ያመቻል። ይህ ደግሞ ምርታማነትን ይጨምራል። የአስተዳደርና የግብይት ወጪን በመጨመር።

ወደ ግብርናው ስንመጣ፥ መሬትና የግብርና ውሳኔ በተበጣጠሰበት ሁኔታ፥ “ከኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል” መጠቀም እንዳንችል  ያደርጋል። ለምሳሌ አንድ ጥልቅ የዉሃ ጉድጓድ በመቆፈር፥ ብዙ መሬትን በመስኖ ማምረት ቢቻልም፥ መሬቶች ተበጣጥሰው እያለ እንዲህ ማድረግ ግን አይቻልም። ለምሳሌ 500 000 ብር ወጪ በማውጣት፥ አሁን በ100 ገበሬዎች ተይዘው ያሉ መሬቶችን በመስኖ ለሚቀጥሉት 20 አመታት ማምረት ይቻላል እንበል። በዚህ ደግሞ እጅግ ምርትን መጨመር እንችላለን እንበል። አሁንም አንበልና እነዚህ መቶ ገበሬዎች ከመሬቱ የሚያገኙት አመታዊ አማካኝ ምርት 50 ኩንታል ነው እንበል። ማለትም እነዚህ መቶ ገበሬዎች በጠቅላላው ከመሬቱ በአመት 5000 ኩንታል ያመርታሉ። ነገር ግን ይህ ጉድጓድ ቢቆፈር በእነዚህ ገበሬዎች ተይዞ ካለው መሬት በጠቅላላው መስኖ በመጠቀም ብቻ (ሌላ የተሻሻለ ግብአት ሳንጠቀም) 15000 ኩንታል ለሚቀጥሉት ሃያ አመታት ማምረት ይቻላል። ከኤኮኖሚ አንፃር ይህ የመስኖ መሰረተ ልማት መገንባት አለበት። ግን ማን ይገንባው?

መቶ ገበሬዎች ያላችው የዉሳኔ መብት በራሳቸው ትንሽ መሬት ላይ ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ገበሬ “ጉድጓድ ልገንባ አልገንባ” የሚለውን ሲያስብ፥ የሚያሰላው ብጣሽ መሬቱን ነው። ከዚህ አንጻር ደግሞ እያንዳንዱ ገበሬ “ጥልቅ ጉድጓድ አያዋጣኝም” ብሎ ያስባል። የመስኖ ውሃን ለምሳሌ አነሳን እንጂ ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን “ልጠቀም አልጠቀም” የሚለውም በዚህ ይወሰናል። ማዳበሪያ፥ ማሽነሪዎች፥ አረም ማጥፊያ፥ እንዲሁም የግብርና ባለሙያ “ልጠቀም አልጠቀም” የሚለው በዚህ ይወሰናል።

የዉሃ ቴክኖሎጂ ሲታሰብም የሚታሰበው በገበሬው ጉልበት ሊሰሩ የሚችሉ ናቸው። ችግሩ “በኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል” መጠቀም አለመቻላችን ብቻ ሳይሆን፥ የሚባክነውን ሃብት ይጨምራል። እነዚህ 100 ገበሬዎች የዉሃ ማቆሪያ በጉልበታቸው ቢገነቡ፤ በዚህ መሬት ላይ መቶ የዉሃ ማቆሪያ ጎድጓዶች ይቆፈራሉ ማለት ነው። ለምርት ሊውል የሚችል ሰፊ ቦታ ጉድጓድ ይቆፈርበታል። 100 ጉድጓድ ለመቆፈር የሚወጣው ጉልበትና ገንዘብ ሲደመር ብዙ ነው። ከዚህ ሁሉ አንድ ትልቅ ጉድጓድ ይበቃ ነበር።

ባጭሩ መሬትና የግብርና ውሳኔ መበጣጠስ “ከኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል” እንዳንጠቀም ያደርጋል። የዚህ መገለጫ ስፔሻላይዜሽን አለመኖሩ ነው። እያንዳንዱ ገበሬ ባሉት ሶስትና አራት ትንንሽ መሬቶች ለመኖር የሚያስፈልጉትን የተለያዩ ሰብሎች ያመርታል። እንዲሁም ከብት ያረባል። ይህ ትልቅ ምርታማነት መጨመር እድልን ይቀንሳል። በዚህም የገጠር ኤኮኖሚ የግብይት ኤኮኖሚ ሳይሆን፥ ከእጅ ወደ አፍ እንዲሆን ያደርጋል። በዚህ ደግሞ ምርታማነት አይጨምርም።

 

ባዮሎጂ ኦፍ ስኬል (biology of scale)

ሁለተኛው አይነት ስኬል “ባዮሎጂ ኦፍ ስኬል” ነው። ስኬል የኤኮኖሚ ጥቅም ብቻ አይደለም ያለው። ተፈጥሮ አንድ ነች። ተፈጥሮን በመከፋፋል የባዮሎጂ ፍራግመንቴሽን ያመጣል። ግብርና የተፈጥሮ ሃብት ላይ የተመሰረተ ነው። ለምሳሌ እነዚህ መቶ ገበሬዎች በያዙት መሬት ላይ፥ ባብዛኛው ባቄላ በመዝራት፥ እና ተዳፋት የሆኑ መሬቶችን ከማረስ ይልቅ የፍራፍሬ ወይም የሌላ አይነት ዛፎች መትከል ይቻላል። በዚህ ትልቅ ጥቅም ማምጣት ይቻላል። የአፈር መሸርሸርን በመቆጣጠር የአፈር ለምነትን ማሻሻል ይቻላል። ፍርቲላይዘር ብንጠቀም፥ በውሃ ተጠርጎ አይሄድም። ስለዚህ ምን ያህል ማዳባሪያ መጠቀም እንዳለንብን እርግጠኛ መሆን እንችላለን። የንጥረነገርና የማዳበሪያ የአፈር ዉስጥ ዝውውር ቢኖርም እንኳን እዛው ነው። ባቄላ ናይትሮጅንን በአፈር ዉስጥ የማመቅ ብቃት አለው። ስለዚህ በሚቀጥለው አመት ባቄላ ተዘርቶበት በነበረው መሬት፥ ስንዴ ቢዘራ ምርት ይጨምራል።

ከዚህ ጋር የሚያያዛው የፓሊኔሽን “የኤኮኖሚ ኦፍ ስኬልም” ይኖራል። ንቦችና ተመሳሳይ ነፍሳት ለግብርና ምርታማነት እስከ 50 ከመቶ አስትዋዕፆ ይኖራቸዋል (የማስታወስ ችሎታየ ካልከዳኝ)። በመሆኑም ለሁሉም መሬት በሚል ንብ በጎን  ማነብ እንችላለን።

እንዲሁም ጠቅላላው መሬት ላይ አንድ አይነት ሰብል በመዝራት ይህ አዋጭ እንዲሆን ያደርጋል። ‘ባዮሎጂ ኦፍ ስኬል’ ማለት በሰፊ ቦታ አንድ አይነት ሰብል መዝራትን ብቻ አይመለከትም። በተመሳሳይ ቦታ የተለያየ ነገር ብንዘራም፥ ሰብሎቹ በባዮሎጂ አርስ በርስ መስተጋብር ያላቸው ከሆነ ይህን በማድረጋችን የተነሳ ምርት ሊጨምር ይችላል። ሰብሎች ብቻ አይደሉም የእርስ በርስ መስተጋብር ያላቸው። ስለዚህ የዶሮና አሳማ ምርትን ከበቆሎ ጋር አብሮ በማከናወን የሁሉንም ምርት መጨመር ይቻላል። አሁን ባለው የመሬትና የግብርና ውሳኔ መበጣጠስ፥ ‘ከባዮሎጂ ኦፍ ስኬል’ እንዳንጠቀም ያደርገናል።

እነዛ መቶ ገበሬዎች መሬቱን እና የመወሰን ስልጣኑን ተበጣጥሰውት ስለሆነ የያዙት፥ ከኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል እና ከባዮሎጂ ኦፍ ስኬን ተጠቃሚ እንዳንሆን ሆነናል። በዚህ ደግሞ እነሱ ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም እንጎዳለን።

 

ችግሩ የእውቀት ጉዳይ አይደለም

ልብ ሊባል የሚገባው ይህ ችግር የእውቀት ችግር አይደለም። በእርግጥ የእውቀት ችግር አለብን። ነገር ግን ይህ የእውቀት ችግር አይደለም። የኢንሰንቲቭ/የጥቅምና የትጋት ጉዳይ ነው። የመሬት መበጣጠስ ትጋትን ይበጣጥሳል። ስለዚህ ገበሬዎችን በማስተማር አይፈታም። የትጋት ችግርን በመፍታት ብቻ ነው የሚፈታው። አንዳንዴ መንግስት የእውቀት እና የትጋት ችግርን በሚገባ ሲለይ አይስተዋልም።

 

የግብይት ወጪ መናር

ገበሬዎች በጋራ ተነጋግረው፥ ተወያይተው፥ የግብርና ውሳኔዎችን በጋራ ሊወስኑ ይችላሉ። በሌላ አገር ንቦቻቸውን የሚያከራዩ አንቢዎች አሉ። ንብ አንቢዎች ማር ብቻ አይደለም የሚያመርቱት። የፓሊኔሽን አገልግሎትም ያቀርባሉ። ለዚህም ይከፈላቸዋል። ስለዚህ የንብ ቀፏቸውን በመኪና እየጫኑ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ይህን አገልግሎት በክፍያ ይቀርባሉ። ለንቦቻችውም ምግብ ያገኛሉ። በእነዚህ ሃገሮች አንድ ገበሬ በጣም ሰፊ መሬት ስላለው፥ ድርድር ወይም የግብይት ወጪው አነስተኛ ነው። በኛ አገር ቢሆን ይህ ንብ አንቢ ንቦቹ ሊሄዱበት በሚችሉ እርሻዎች ካሉ ገበሬዎች ጋር ሊደራደርና ሊስማማ ይገባል ማለት ነው። ከብዙ ሰዎች ጋር ድርድርና ስምምነት መፈፀም ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ከዚህ በፊት ባለው ፅሁፍ አሳይቻለሁ። 100 ገበሬዎቹ ተስማምተው በጋር የግብርና ውሳኔዎችን ማከናወን ከባድ ነው። የግብይት ውጪው ከፍተኛ ነው። ይህ ደግሞ በመሬትና በውሳኔ መበጣጠስ የመጣ ነው።

 

የተወሰደው መፍትሄ

የተወሰደው መፍትሄ መንግስት ብዙውን የግብርና ውሳኔ ከገበሬው መውሰድ ነው። ለምሳሌ የመስኖ መስረተ ልማትን ማቅረብ። የግብርና ባለሙያና ማቅረብ። የተሻሻሉ ዘሮችን ማቅረብ። የአፈር ጥበቃ ስራን በዘመቻ ማከናወን። ችግሩ፤ የግብርና ውሳኔ መተላለፍ ያለበት እዛው ማሳ ላይ እንጂ፥ ግብርና ሚኒስቴር ቢሮ አይደለም። ስለዚህ የፍላጎትና የአቅርቦት አልተገናኝቶ ይመጣል።

ሁለተኛ፥ መንግስት ሁሉንም ነገር ለሁሉም በበቂ ሁኔታ ማቅረብ አይችልም። ስለዚህ መንግስትም ስራዉን ካመት አመት በቁጥ ቁጥ እየሰራ ይገኛል። ሶስተኛ የአፈር ጥበቃን ስንመለከት፥ እዛ መቶ ገበሬዎች ላይ የሚሰራው የአፈር ጥበቃ ሁሉንም እኩል ስለማይጠቅምና እኩል ወጪ ስለማያስወጣ፥ የተሰራዉ እርከን ባጭር ጊዜ ውስጥ ይፈርሳል።

የግብርና ዉሳኔ መበጣጠስን በህብረት ስራ ማህበራት ማከናወን ቢቻልም፥ የግብርና ውሳኔን በሙሉ በማዕከልበመጠቅለለ አይከናወንም። ገበያን ወይም ግብአትን መሰረት ያደረጉ አይደሉም። እንዲሁም የሕብረት ስራ ማህበራትን አስመልክቶ ሰፊ የአስተዳደር ችግሮች አሉ።

 

ምን ይሻላል?

የመሬት ግብይትን በማበረታት የግብርና ውሳኔን መጠቅለል ቢቻልም፥ የመሬት ፓሊሲና ሕግ ግን ይህ እንዳይሆን አድርጓል። የሚከተሉት ለውጦች ያስፈልጋሉ

  • ገበሬው መሬቱን አስይዞ ገንዘብ እንዲበደር ሊፈቀድ ይገባል። ዞሮ ዞሮ የሚያስይዘው ባለቤትነቱን አይደለም። በመሬት የመጠቀም መብቱን ነው። ለዚህ ደግሞ “አንድ ገበሬ ለምን ያህል ጊዜ በመሬቱ የመጠቀም መብት” እንዳለው ግልጽ ሊሆን ይገባል። ምክንያቱም የመሬቱ ዋጋ የሚወሰነው ገበሬዉ መሬቱን ምን ያህል አመታት ወደ ፊት መጠቀም ይችላል በሚለው ነው። አሁን ባለበት ሁኔታ መሬት ሙት ካፒታል ሆኗል።
  • ገበሬው መሬቱን ሙሉ ለሙሉ እንዲያከራይ መፍቀድ። አሁን ያለውን ከግማሽ በላይ ማከራየት አይችልም የሚለውን ድንጋጌ ማንሳት።
  • ገበሬው መሬቱን ለግብርና ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም አገልግሎት እንዲያከራይ መፍቀድ።
  • ገበሬው ለምን ያህል ጊዜ መሬቱን ማከራየት ይችላል የሚለው የግብርና እና ሌላ አይነት ኢንቨስትመንት በሚያበረታታ አኳኋን መወሰን።
  • መንግስት ከገበሬዎች እየወረሰ ለባለሃብቶች የሚሰጠውን አስራር ማስቀረት። መንግስት ሊወርስ የሚችለው ለሕዝብ ጥቅም ሲሆን ብቻ መሆን አለበት። የሕዝብ ጥቅም የሚለው ደግሞ እጅግ በጠባቡ ሊተረጎምና በፍርድ ቤት ሊፈተሽ ይገባል። የካሳው መጠንም ገበሬው በመሬቱ ሲያገኝ ከነበርዉ ጥቅም ጋር ተመጣጣኝ መሆን አለበት።
  • የመሬት ግብይትን የሚያግዝ የመረጃ ስርአት መንግስት በማደራጀት ማቅረብ አለበት።
  • በብዙ ሰዎች ተበጣጥሶ ያለን ቦታ መከራየት የሚፈልግ ሰዉ፤ ከኪሳራ ሕግ ጋር የሚመሳሰል የጋርዮሽ የድርድር ስርአት መፍጠር። በዚህም የቀረበውን የኪራይ ሃሳብ አብዛኛው የገጠር መሬት ባለይዞታ ከደገፈና፥ አገርን ይጠቅማል ተብሎ ሲታሰብ፤ በሁሉም ላይ ተግባራዊ የሚሆንበት አስራር መዘርጋት። ለዚህም አስተማማኝ መመሪያና የቁጥጥር ስርአት መዘርጋት።

 

እነዚህ የለውጥ ሃሳቦች እንዴት እንደሚጠቅሙ ከላይ እና ከዚህ በፊት በወጣው ጽሁፍ ቀርቧል። በዚህ ጽሁፍ ደግሞ ሌላኛው አማራጭ ይቀርባል።

 

የእርሻ ኩባንያዎች

የግብርና ውሳኔን መጠቅለል የሚቻለው በኪራይ ብቻ አይደለም። ከላይ በተቀመጠው ምሳሌ መቶዎቹ ገበሬዎች መሬታቸውን አዋጥተው አንድ ኩባንያ ድርጅት ሊመሰርቱ ይችላል። በርጅቱ የሚኖራቸው ድርሻ እንዳዋጡት መሬት ይሆናል። በዚህም በድርጅቱ አክስዮን ይኖራቸዋል። ባለቤቶች ይሆናሉ። ነገር ግን ድርጅቱ የሚተዳደረው በባለሙያዎች ይሆናል። ማለትም በባለቤትነትና በአስተዳደር መካከል ልዩነት ይኖራል። በእርግጥ እንደ ባለ አክስዮን ቦርድ በመምረጥና አስተዳደሩን በመቆጣጠር ሚና ይኖራቸዋል። ድርጅቱ በራሱ ስም ገንዘብ መበደር ይችላል። ንብረት ማፍራት ይችላል። ውል ይዋዋላል። የገበሬዎች ሃላፊነት የተገደበ ነው። ገበሬዎች በምርት ሂደት ከተካፈሉ እንደ ባለይዞታ ሳይሆን በድርጅቱ ተቀጥረው ነው። በዚህም ደመወዝ ያገኛሉ።

የተዋጣው መሬት የድርጅቱ ይዞታ ይሆናል። ስለዚህ የግብርና ውሳኔ በድርጅቱ ይሰጣል። ይህን በማድረግ ከላይ የተጠቀሱትን የኤኮኖሚ እና የባዮሎጂ ስኬል ጥቅሞች ማግኘት ይችላል። በኪራይም ተመሳሳይ ጥቅም ማግኘት ቢቻልም፥ ገበሬዎቹ ኪራይ ብቻ ነው የሚያገኙት። ተከራዩ በመሬቱ ምንም ያምርት ምንም ኪራያቸውን ያገኛሉ። ስለዚህ ሪስኩን የወሰደው ተከራዩ ነው። መሬቱን በኩባንያ በመጠቅለል፥ ገበሬዎቹ የሚያገኙት ከትርፍ እንደ አክስዮናቸው መጠን መከፋፈል ነው። ገበሬዎቹ ሪስኩን ይካፈላሉ። ቢከስር ግን ሃላፊነታቸውን የተገደበ ነው።  ትልቁ ችግር አስተዳደሩን የመቆጣጠር ነው።

የተለመደ የግብርና ግብይት የእኩል ማረስ የሚባለው ነው። መሬትህን በሌላ በማሳረስ፥ ከሚገኘው ምርት እኩል ወይም በሌላ መልኩ መካፈል ነው። በዚህ ሪስኩንም አራሹና ባለይዞታው ይካፈሉታል።

ይህኛውን አማራጭ ለማበረታታት፥ ለግብርናው ልዩ ጸባይ በሚመች መልኩ የድርጅት ሕግ ማዳበር ሊጠይቅ ይችላል። ለሌሎች ንግዶች የሚውለው የንግድ ድርጅቶች ሕግ ለግብርና ላይስማማ ይችላል።

በአማራጮቹ መካከል ውድድር በመፍጠር፥ ለገበሬዎቹ አማራጭ በመስጠት፥ ምርትን ማላቅ ይቻላል። እንዲሁም የተለያዩ ቦታዎች ላይ ሁለቱ አማራጮች እኩል ተመራጭ ላይሆኑ ይችላሉ።

 

የግብርና ባለሙያ ቀጣሪን ማብዛት

ከዚህ በፊት ባለው ጽሁፍ መንግስት ብቸኛው የግብርና ባለሙያ ቀጣሪ መሆኑ የሚያመጣውን ችግር አይተናል። ከዚህ በላይ ያሉትን ሁለቱን አማራጮች መተግበር፥ ለግብርና ባለሙያዎች አማራጭ ቀጣሪ መፍጠር ነው። በዚህ ደግሞ ሰዎች መርጠው ወደ ግብርና ሙያ እንዲገቡና እንዲቆዩ ያደርጋል።

ከዚህ በተጨማሪ፥ የፌዴራል መዋቅሩ የሰጠንን የዴሞክራሲ ላብራቶሪነት ተስፋ በሚገባ ቢተገበር፥ ለግብርና ባለሙያዎች ተጨማሪ እድል ይፈጥራል።

 

አተገባበር

ከዚህ በላይ ያሉትን ሃሳቦች በሙሉ በሃገሪት መተግበር አያስፈልግም። በተወሰኑ አካባቢዎችና የተወሰኑ ምርቶችን ለማበረታት በሚል በሙከራነት ተግብሮ ፍሬውን መገምገም ያስፈልጋል። ሲያዩት፥ ሲሰሙት፥ ሲያነቡት ሎጂካል ስለመሰለን ብቻ በሃገር ደረጃ አንድን መፍትሄ መተግበር ሃብት ማባከን ነው። መጀመሪያ በሙክራ መተግበር፥ መረጃ መሰብሰብና መገምገም ያስፈልጋል።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Bank deposit method of proving Tax Evasion: the cu...
አንዳንድ ጉዳዮች ስለ ግብርና እድገትና የመሬት ፓሊሲና ሕግ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 18 April 2024