Font size: +
10 minutes reading time (1960 words)

የአክሲዮን መያዣ አመሠራረትና የመያዣ ተቀባዩ መብቶች

መያዣ ለአንድ ግዴታ አፈፃፀም ማረጋገጫ የሚሰጥ የንብረት ዋስትና ነው፡፡ ዋና ግዴታ በሌለበት መያዣ ስለማይኖር መያዣ በንብረት ላይ የሚፈፀም ደባል ግዴታ (accessory obligation) ነው፡፡ መያዣ በሚንቀሳቀስ ወይም በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚመሠረት ሲሆን በዚህ ጽሑፍ ምልከታ የሚደረግበት የአክሲዮን መያዣ የሚንቀሳቀስ ንብረት መያዣ /pledge/ በመሆኑ ከማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ ጋር በተገናኘ በንጽጽር ካልሆነ በቀር የሚነሱ ነጥቦች አይኖሩም፡፡ የፍትሐብሔር ሕጋችን ፕሌጅ ከውል የሚመሠረት ግዴታ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡

የሕጉ አንቀጽ 2825 የመያዣ ውል ማለት አንድ ባለዕዳ በባለገንዘቡ በኩል የገባውን ግዴታ ለመፈፀም መቻሉን በማረጋገጥ መያዣ ተብሎ የሚጠራውን ዕቃ ለመስጠት የሚገደድበት ውል ማለት ነው ሲል ግልጽ ትርጉም ይሰጣዋል፡፡ በመያዣ ሊሰጥ የሚችለውን ነገር በመወሰን ረገድ የፍትሐብሔር ሕጉ የሚታይም ሆነ የማይታይ ተንቀሳቃሽ ንብረትን ሊያካትት እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ሕጉ በቁጥር 2829 በመያዣነት የሚሰጠው አንድ ተንቀሳቃሽ ንብረት (a chattel) ወይም በጠቅላላው ዕቃ ተብለው ከሚጠሩ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች አንዱ (a totality of effects) ወይም አንድ የገንዘብ መጠየቂያ መብት ሰነድ (a claim) ወይም በአንድ ተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለ የመብት መጠየቂያ ሰነድ ለመሆን እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ አክሲዮን የአንድ የንግድ ማኅበር (የአክሲዮን ማኅበር ወይም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር) የአባልነት ማስረጃና በካፒታሉ ውስጥ ያለ ድርሻ (ጥቅም) ማረጋገጫ ነው፡፡ አክሲዮን የገንዘብ መጠየቂያ ሰነዶች (claims) ውስጥ የሚወድቅ ግዙፍነት የሌለው ተንቀሳቃሽ ንብረት (incorporeal Movable) ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉን አንቀጽ 1125 ይመለከቷል፡፡ አክሲዮን በመያዣ የሚሰጥበት የሕግ ማዕቀፍ በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2863-2874 እንዲሁም በንግድ ሕጉ ቁጥር 329 ላይ የተካተተ ሲሆን በዚህ ጽሑፍ የአክሲዮን መያዣ የሚቋቋምበትን ሁኔታ እና አክሲዮን በመያዣ የተቀበለ ባለገንዘብ ያሉትን መብቶች የተመለከቱ ነጥቦችን ለማየት ሙከራ ይደረጋል፡፡

የሚንቀሳቀስ ንብረት መያዣ (ፕሌጅ) አመሠራረት

የፕሌጅ ፅንስ ሃሣብ በዋናነት የአንድን ተንቀሳቃሽ ንብረት ይዞታ አሳልፎ በመስጠት ዋስ መሆን የሚቻልበት የግዴታ ዓይነት ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2825 ያመለክታል፡፡ የፕሌጅ ዋስትና አንድ ሰው ለራሱ ወይም ሌላ ሦስተኛ ወገን ለሚገባው ግዴታ ተፈፃሚነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ፕሌጅ ተፈፃሚነት ያለው በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ መሆኑ ከማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ (Mortgage) የተለየ ያደርገዋል፡፡ በመርህ ደረጃ ፕሌጅ ሊመሠረት የሚችለው የሚንቀሳቀሰውን ንብረት በማስተላለፍ ነው፡፡ እንዲያውም የንብረቱ ይዞታ ካልተላለፈ ፕሌጅ አልተቋቋመም ሊባል ሁሉ ይችላል፡፡ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2832 በሕጉ ላይ ተገልጾ ካልተፈቀደ በቀር በመያዣ ተሰጥቶ ተይዘዋል የተባለው ዕቃ ከባለዕዳው እጅ ሳይወጣ በመያዣ እንደ ተሰጠ ሆኖ ሊቆጠር እንደማይችል ይደነግጋል፡፡ በሕግ ከተፈቀደው በቀር መያዣው በባለዕዳው እጅ ይሆናል ብለው ቢዋዋሉ እንኳን ውሉ እንደማይፀና ጨምሮ ደንግጓል፡፡ ሆኖም ሕጉ ሲፈቅድ በልዩ ሁኔታ /as an exception/ የንብረቱ ይዞታ ሳይተላለፍ ፕሌጅ ሊመሠረት የሚችልበት የሕግ አግባብ አለ፡፡ ይህም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2830 ላይ የተመለከተው ሲሆን በተለይ በዕቃው ለማዘዝ የሚያስችሉት ሰነዶች ከተሰጡት ባለገንዘቡ መያዣውን እጅ እንዳደረገ ያህል ይቆጠራል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ንብረቶች ባለቤትነታቸው ያለምዝገባ ወረቀት (title deed) ሊተላለፍ ስለማይችል የንብረት ይዞታ መተላለፍ ሳያስፈልግ ፕሌጅ ሊፈፀም ይችላል፡፡ ለእነዚህ ዓይነት ዋስትና በምሳሌነት የሚያገለግሉት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1186(2) የተጠቀሱት ልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች እንደ መኪና፣ አክሲዮን የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ዓይነት ንብረቶች ናቸው፡፡

ንብረቱን ለባለገንዘቡ ከማስተላለፍ (dispossession) በተጨማሪ የሚንቀሳቀስ ንብረት መያዣ በሕጉ በተቀመጠው የአሠራር ሁኔታ ፎርም መሠረት ካልተፈፀመ በሕግ ፊት የፀና አይሆንም፡፡ ይህ የፎርም መስፈርት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2828 ላይ የተደነገገ ሲሆን ዋስትና የተሰጠበት ግዴታ ከፍተኛው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን በግልጽ ተጠንቅቆ በመያዣው ውል ውስጥ መመልከት ይገባዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ውሉ ፈራሽ አንደሚሆን ሕጉ በግልጽ ደንግጓል፡፡ በተጨማሪም የመያዣው ውል ከ500 ብር በላይ የሆነ እንደሆነ ውሉ በጽሑፍ ካልተደረገና ይኸውም እርግጠኛ ቀን ካገኘበት ዘመን ጀምሮ ካልሆነ በቀር አይፀናም፡፡ ስለዚህ ከ500 ብር በላይ የሆነ የሚንቀሳቀስ ንብረት መያዣ በጽሑፍ እንዲፈፀም ሕጉ ግዴታ ይጥላል፡፡ እንዲህ ዓይነት የመያዣ ውል ደግሞ በጽሑፍ እንዲደረግ ሕጉ ግዴታ ካስቀመጠ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1727 መሠረት በውሉ ግዴታ ያለባቸው አስያዡ እና መያዣ ተቀባዩ መፈረም ያለባቸው ሲሆን በሁለት ምስክሮች ፊትም ካልተረጋገጠ የሚፀና አይሆንም፡፡

የአክሲዮን መያዣ አመሠራረት

አክሲዮን ተንቀሳቃሽ ንብረት እንደመሆኑ መጠን የአክሲዮን መያዣ የሚንቀሳቀስ ንብረት መያዣን በሚመለከቱ ደንቦች የሚገዛ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከላይ የተገለፁት የፕሌጅ አመሠራረት ሁኔታዎች ለአክሲዮን መያዣም ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡ የአክሲዮን መያዣው በውል ሊመሠረት ይገባል፤ ውሉም ዋስትና የተገባበትን ግዴታ ከፍተኛ ገንዘብ ሊያመለክት ይገባል፤ ግዴታው ከ500 ብር በላይ ከሆነ ደግሞ ውሉ በጽሑፍ ሊደረግ፣ በመያዣ ሰጪው (ባለአክሲዮኑና) በመያዣ ተቀባዩ (ባለገንዘቡ) ሊፈርምና፣ በሁለት ምስክሮች ፊት ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ የገንዘብ መጠኑ ከ500 ብር በላይ ሆኖ በጽሑፍ ካልተደረገ፤ በምሥክሮችም ካልተረጋገጠ በሕግ ፊት የፀና አይሆንም፡፡ ከእነዚህ መስፈርቶች በተጨማሪ አክሲዮን ልዩ ተንቀሳቃሽ እንደመሆኑ መጠን መያዣ ተቀባዩ የአክሲዮን ሰርተፊኬቱን በመቀበል ፕሌጁ ሊፈፀም ይችላል፡፡

ሆኖም የፍትሐብሔር ሕጉ “የገንዘብ መጠየቂያ ሰነዶችን ወይም ግዙፍ ያልሆኑ ሌሎች ሀብቶችን ስለ ማስያዝ” በደነገገበት ከቁጥር 2863-2874 ልዩ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች ውስጥ ከቁጥር 2864-2866 ያሉት በመያዣ የሚሰጠው መብት የተለያዩ ባህሪያትን ባገናዘበ መልኩ የፎርም ሁኔታዎችን ይደነግጋል፡፡ የመጀመሪያው የሰነድ ማስረጃ የሌለው ገንዘብ (claim) ሲሆን እንዲህ ዓይነት ገንዘብ በመያዣ ሲሰጥ ዋስትና የሚሰጥበት ገንዘብ ማንኛውም ብዛት ቢኖረው በመያዣው የተሰጠው የገንዘብ መጠየቅ መብት ማስረጃ የምን ያህል ገንዘብ እንደሆነና ዋስትና የሚሰጥበት ገንዘብ ስንት እንደሆነ አብዛኛውን ልክ በግልጽ የሚያመለክት የጽሑፍ ማስረጃ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም በመያዣ የተሰጠው የገንዘብ መጠየቂያ መብት የመያዣው ገንዘብ ባለዕዳ እንዲያውቀው ካልተደረገ ወይም እሱ የተረጋገጠ ቀን በተመለከተበት ጽሑፍ ውሉን ካልተቀበለ የተሰጠው መያዣ አይፀናም፡፡ ይህ በቁጥር 2864 የተደነገገው ሲሆን ተፈፃሚነቱ የሰነድ ማስረጃ (ወይም ሰርተፊኬት) ላለው ለአክሲዮን ድርሻ መያዣ እንዳልሆነ ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል፡፡

የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2865 ደግሞ በሰነድ ላይ ያልተገለፀ መብት (ከገንዘብ መጠየቂያ መብት ውጭ ላሉ) መያዣ ሲሰጥ የመያዣው ውል የሚከናወነው ለእነዚህ መብቶች ማስተላለፍ በተደነገገው ሥርዓት (ፎርም) እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ እነዚህ ዓይነት መብቶች በመያዣ ሲሰጡ የመብቱ ዓይነትና ዋስትና የሚሰጥበትን ግዴታ በዝርዝር የሚገልጽ ጽሑፍ እንዲኖር ሕጉ ያስገድዳል፡፡ የዚህ ድንጋጌ የተፈፃሚነት ወሰን የአክሲዮን መያዣን ስለማጠቃለሉ አከራካሪ ነው፡፡ በአንድ በኩል ድንጋጌው በሰነድ ላይ ያልተገለፀ መብትን የሚመለከት ነው፡፡ የአክሲዮን ድርሻ ደግሞ ዝርዝር ሁኔታው (መጠኑ፣ የአክሲዮኑ ዓይነት፣ የምዝገባ ቁጥር፣ ስለመተላለፉ ሁኔታ፣ ድርሻው በሙሉ ወይም በከፊል ስለመከፈሉ ወ.ዘ.ተ) በአክሲዮን ሰርተፊኬት የሚገለጹ በመሆኑ ሰነድ አልባ (በሰነድ ላይ ያልተገለፀ) ነው የሚባል አይሆንም፡፡ ድንጋጌው ሰነድ የማያስፈልጋቸውን የቅጂ መብት (copyright) መያዣን ዓይነት መብቶችን የሚመለከት ስለመሆኑ መከራከር አሳማኝ ይመስላል፡፡ የዚህ ድንጋጌ የተፈፃሚነት ወሰን ከአካዳሚክ ክርክር ያለፈ ስለመሆኑ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተወሰነ አንድ ፍርድ አመላካች ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰ/መ/ቁ 39256 ሐምሌ 2 ቀን 2001 ዓ.ም. በሰጠው ፍርድ “ስም የተፃፈበት አክሲዮን ማስተላለፍም ሆነ በመያዣነት ለመያዝ አክሲዮኖቹ በሌላ ሰው የተላለፉ ወይም በመያዣነት የተያዙ መሆኑን በአክሲዮን ማህበሩ ዋና መስሪያ ቤት በሚገኘው የአክሲዮን መዝገብ ማስመዝገብ እንደሚያስፈልግ ሕግ ቁጥር 341(2) እና የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2865(1) ድንጋጌዎች ለመገንዘብ ይቻላል” በማለት የሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት (የከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች) የአክሲዮን ድርሻዎች እንደማንኛውም ግዙፍነት ያላቸው ተንቀሳቃሽ ንብረት በመቁጠር በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2828(2) እና ሌሎች የውል ሕግ ጠቅላላ ድንጋጌዎች መሠረት በማድረግ መወሰናቸው አግባብነት የለውም በማለት ሽሮታል፡፡

የሰበር ሰሚ ችሎቱ ፍርድ መሠረት ያደረገው የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2865ን ሲሆን ይህ ድንጋጌ ለአክሲዮን መያዣ ተፈፃሚ ስለመሆኑ መመርመር አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በመጀመሪያ ድንጋጌው በርዕሱም ሆነ በይዘቱ ከያዘው ጽንሠ ሀሣብ ለመረዳት እንደሚቻለው ድንጋጌው “በሰነድ ላይ ያልተገለጸ መብት” በመያዣ ስለሚሰጥበት ሁኔታ ነው፡፡ የአክሲዮን ድርሻ ደግሞ በአክሲዮን ሰርተፊኬት ላይ በዝርዝር የሚገለጽ መብት በመሆኑ ከ2865 የአፈፃፀም ወሰን ውጭ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የገንዘብ መጠየቂያ ሰነዶች መያዣን የሚመለከተው ክፍል የአክሲዮን መያዣ ሊከተለው ስለሚገባው ፎርም ያልደነገገ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህ የፍትሐብሔሩ ልዩ ክፍል ስለ ፎርም የሚለው ነገር ከሌለ ደግሞ ለሚንቀሳቀስ ንብረት በጠቅላላው የተቀመጡት ደንቦች (የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2828) እና ስለ ውል በጠቅላላው በሚለው የፍትሐብሔሩ ክፍል (የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1727) ተፈፃሚ መሆናቸው አይቀርም፡፡ በእነዚህ ድንጋጌዎች መሠረት የአክሲዮን መያዣ የዋስትናውን መጠን በሚገልጽ ውል ሊመሠረት የሚገባው ሲሆን የገንዘብ መጠኑ ከ500 ብር በላይ ከሆነ ደግሞ በጽሑፍ ሆኖ በተዋዋዮቹና በምስክሮቹ መፈረሙ የግድ ይሆናል፡፡

በተጨማሪም መያዣ የተቀበለው ባለገንዘብ የአክሲዮን ሰርተፊኬቱን በእጅ በማድረግ አክሲዮኑን ለሚያስተዳድረው አካል ሊያስመዘግበው ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2865 ለአክሲዮን መያዣ ተፈፃሚ ይሆናል ቢባል እንኳን ስለ ሚንቀሳቀስ መያዣ የተቀመጡት አጠቃላይ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው ድንጋጌው በ341(2) መሠረት የመያዣ መብቱን የማስመዝገብ ግዴታን የጨመረ ስለመሆኑ መከራከር አሳማኝ ነው፡፡ ይህ አቋም በልዩ ድንጋጌዎች የተቀመጡ ደንቦች ጉዳዩን በተመለከተ ጠቅላላ ድንጋጌዎች የሚያስቀምጡትን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ በመቀረፃቸው የጠቅላላ ድንጋጌዎች የፎርማሊቲ መስፈርት ተፈፃሚ ስለሚሆኑ ነው፡፡ ሁለቱ ድንጋጌዎች እስካለተቃረኑ ድረስ የሁለቱም መስፈርት እንዲሟሉ ማድረግ የሕግ አውጪውን ፍላጐት በአግባቡ ለመተግበር ይረዳል፡፡

የገንዘብ መጠየቂያ ሰነዶች በመያዣ ስለሚሰጡበት ሁኔታ ከተቀመጡት ደንቦች ለአክሲዮን መያዣ አመሠራረት ረብ ያለው የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2866 ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ በንግድ ሕግ ቁጥር 325 በሃገሪቱ እውቅና የተሰጣቸውን ሁለት ዓይነት አክሲዮኖችን ያገናዘበ ድንጋጌ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት አክሲዮኑ ለአምጪው ተብሎ የተፃፈባቸው ሲሆኑ እነዚህ አክሲዮኖች ለሌላ ሲተላለፉም ሆነ በመያዣ ሲሰጡ እንደማንኛውም ተላላፊ የንግድ ወረቀት የአክሲዮን ማረጋገጫ ሰነዱን አሳልፎ በመስጠት ያለአንዳች ፎርማሊቲ ማከናወን እንደሚቻል ከፍ/ህ/ቁ 340(1) እና የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2866(2) መረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የባለ አክሲዮኑ ስም የተፃፈበት አክሲዮን ሲሆን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2866(1) መሠረት በመያዣ ውል በግልጽ ሠፍሮ መያዣ ተቀባዩ ሰነዱን በእጁ ሊያደርግ ይገባል፡፡

አክሲዮን በመያዣ የተቀበለ ባለገንዘብ መብቶች

የፍትሐብሔር ሕጉ እና የንግድ ሕጉ አክሲዮን በመያዣ የተቀበለ ባለገንዘብን መብቶች ይዘረዝራሉ፡፡ መብቶቹን በመደንገግ ረገድ የፍትሐብሔር ሕጉ ከንግድ ሕጉ የተሻለ ዘርዘር ያሉ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ አክሲዮን በመያዣ የተቀበለ ባለገንዘብ ካሉት መብቶች መካከል ባለዕዳው ግዴታውን ከመያዣው ሽያጭ ዋጋ ከሌሎች ባለገንዘቦች ቀድሞ የመቀበል መብት አንዱ ነው፡፡ ይህ መብት የመያዣው ዋና ዓላማ ሲሆን ከግል ዋስትና (personal security) በተሻለ ለባለገንዘቡ የዕዳ አከፋፈል ዋስትና ይሆናል፡፡ የሚንቀሳቀስ መያዣ ለተቀበለ ባለገንዘብ ያሉት ሌሎች መብቶችም እንደአስፈላጊነቱ ለአክሲዮን መያዣ ተቀባይ ተፈፃሚ እንደሚሆኑ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2874 ይደነግጋል፡፡ ሆኖም በዚህ ጽሑፍ ቀጣይ ክፍል ለማየት የሚሞከሩት መብቶች ግን በንግድ ሕጉ ወይም በፍትሐብሔር ሕጉ በተለያየ ሁኔታ የተደነገጉ ወይም አከራካሪ አተገባበር ያላቸውን መብቶች ይሆናል፡፡

በሁለቱ ሕጎች በተለያየ መልኩ የተገለፀው የመጀመሪያው መብት በጉባኤዎች ጽምፅ የመስጠት መብት ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ አክሲዮኖች በመያዣ በተሰጡ ጊዜ በአክሲዮኔሮች ጉባኤ ላይ የሚቀመጠው አክሲዮኔሩ ራሱ ነው አንጂ አክሲዮን በመያዣ የተቀበለው ባለገንዘብ አይደለም በሚል ይደነግጋል፡፡ (2870) ከዚህ ድንጋጌ ተቃራኒ በሆነ መልኩ የንግድ ሕጉ አንቀጽ 329(1) አንድ አክሲዮን በመያዣ የተሰጠ እንደሆነ ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በቀር በጉባኤዎች ድምፅ የመስጠት መብት አክሲዮኑን በመያዣ ለተቀበለው ነው ሲል ይደነግጋል፡፡ የንግድ ሕጉ ድንጋጌ ተቃራኒ ስምምነት በሌለ ጊዜ በመያዣ የተቀበለውን ባለገንዘብ መብት ይጠብቃል፡፡ በአብዛኛው (በተለይ በባንኮች) የሚደረጉ የመያዣ ውሎች በጠቅላላ ጉባኤ ላይ ድምፅ የመሰጠት መብትን በተመለከተ ምንም ዓይነት ድንጋጌ የላቸውም፡፡ ይህም የንግድ ሕጉ መያዣ ተቀባዩ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ድምፅ የመስጠት መብቱን ባከበረው መልኩ የመተግበሩ ሁኔታ ሰፋ ያለ ነው፡፡ መያዣ ሰጪውና ተቀባዩ በጠቅላላ ጉባኤ ላይ ድምፅ የመስጠት መብትን በተመለከተ ያደረጉት ስምምነት በሌለበት ሁኔታ ወይም ስምምነቱ ለባለአክሲዮኑ መብት በማይሰጥበት ሁኔታ የፍትሐብሔር ሕጉና የንግድ ሕጉ ተቃራኒ ይሆናሉ፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ ባለአክሲዮኑ በጉባኤዎች ድምፅ የመስጠት መብት አለው ሲል፤ የንግድ ሕጉ ደግሞ ይህ መብት የመያዣ ተቀባዩ ስለመሆኑ ደንግጓል፡፡ እንዲህ አይነት ተቃርኖ ባጋጠመ ጊዜ “ልዩ ሕግ ከጠቅላላው ሕግ ቅድሚያ ይሰጠዋል” የሚለው የሕግ ትርጓሜ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ በዚሁ መሠረት አክሲዮንን በተመለከተ ዝርዝር ድንጋጌ ያሉት የንግድ ሕጉ ተፈፃሚ ስለሚሆን በጉባኤዎች ላይ ተገኝቶ ድምፅ የመስጠትን መብት ለመያዣ ተቀባዩ ያጎናጽፈዋል፡፡ ሆኖም ባለአክሲዮኑ ዕዳውን በአግባቡ በመክፈል ላይ ባለበት ሁኔታ ድምፅ የመስጠት መብቱን ማጣቱ ፍትሐዊ አይሆንም፡፡ ባለአክስዮኑ አክሲዮኑን በመያዣ በመስጠቱ የባለቤትነት መብቱን ሊያጣ አይገባውም፡፡ አክሲዮን በመያዣ መስጠት ማስተላለፍ ወይም መሸጥ ባለመሆኑ የባለአክሲዮኑ ሰፊ የባለቤትነትን መብት በንግድ ሕጉ ድንጋጌ ይሸረሸራል፡፡

ሁለተኛው የመያዣ ተቀባዩ አከራካሪ መብት የአክሲዮን መያዣው የትርፍ ድርሻን (dividend) ይጨምራል ወይስ አይጨምርም? የሚለው ነጥብ ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 2867 እንደ ጥቅም ድርሻ (ዲቢዳንድ) የሆኑ በተወሰነ ጊዜ ወለድ ወይም ሌላ ጥቅም የሚያስገኙ የገንዘብ መጠየቂያ ሰነዶች በመያዣ በተሰጡ ጊዜ ተቃራኒ የሆነ ስምምነት ካልኖረ በቀር መያዣነታቸው የሚፀናው ወደ ፊት የሚያስገኙት ትርፎች ላይ ነው፡፡ እንጂ፤ የመክፈያቸው ጊዜ ባለፉት ትርፎች ላይ አይደሉም ሲል ይደነግጋል፡፡ ድንጋጌው በንዑስ ቁጥር 2 እነዚህ ተጨማሪ ትርፎች በልዩ ሰነዶች ላይ ተለይተው በመዘርዘር የተመለከቱ ከሆኑ በሕጉ ላይ በተፈቀደው ደንብ መሠረት ራሳቸው መያዣ ሆነው ካልተሰጡ በቀር በመያዣው ውል ውስጥ እንደገቡ አይቆጠርም ይላል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ዋናው ባለዕዳ ግዴታውን መፈፀም ካቆመበት ጊዜ ጀምሮ አክሲዮኖቹ የሚያሰገኙት የትርፍ ድርሻ አስቀድሞ በፕሌጅ ውሉ ላይ ለግዴታው መፈፀሚያነት ይውላሉ ተብሎ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ በቀር የትርፍ ድርሻዎቹ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ባለአክሲዮኑ እንጂ በዋስትናው ተጠቃሚ የሆነው ባለገንዘብ አይደለም፡፡ ይህም በመሰረታዊነት በማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ (Mortgage) የተያዘ የማይንቀሳቀስ ንብረት ፍሬ ያለምንም ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታ ባለዕዳው ግዴታውን መፈፀም ካቆመበት ጊዜ ጀምሮ ለእዳው ማቀናነሻ ለማድረግ የሞርጌጅ ውል ለባለገንዘቡ ከሚሰጠው መብት (የፍ/ብ/ሕ/ቁ 3093(2)) በተለየ ሁኔታ ለፕሌጅ የማይሠራ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ እዳው መፈፀም ካቆመበት በኋላ ያለው የትርፍ ድርሻ (current benefits) ግን ለመያዣ ተቀባዩ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

ከላይ የጠቀስነው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ግን የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 2867ን በመያዣ ሰጪውና ተቀባዩ መካከል የትርፍ ድርሻን (dividend) የተመለከተ ስምምነት መኖር አለመኖሩን ሳያረጋግጥ የትርፍ ድርሻውን አክሲዮኑን በመያዣ ለተቀበለው ባለገንዘብ እንዲሰጥ ወስኗል፡፡ በዚህ ረገድ ችሎቱ የመያዣ መብቱን መሠረቱ የተባሉት ደብዳቤዎችና የአክሲዮን መዝገብ አክሲዮኖቹ በመያዣ ከተሰጡ ጀምሮ የበሰሉትን የትርፍ ድርሻ ለመቀበል በሚያስችል መልኩ ስምምነት ስለመኖሩ ሳያረጋግጥ መያዣ ተቀባዩን ባለመብት ማድረጉ አግባብ አይደለም፡፡ ሆኖም መያዣ ተቀባዩ ባለዕዳው ክፍያውን ካቋረጠበት ጊዜ በኋላ የበሰሉ የትርፍ ድርሻዎችን ለመውሰድ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2867 የማይከለከለው በመሆኑ (ክፍያ የቆመበት ጊዜ በፍርዱ ተወስኖ ቢሆን ኖሮ) የተወሰኑ የትርፍ ድርሻ የሚያገኝበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ችሎቱ ባደረገው ማጣሪያ መያዣውን የመሰረቱት ደብዳቤዎች የትርፍ ድርሻን የተመለከተ ነገር ካልያዙ የመክፈያ ጊዜ ያለፉትን ትርፎች ሊመለከት እንደማይገባ መወሰን ይችል ነበር፡፡

በአጠቃላይ የአክሲዮን ድርሻ ልዩ ተንቀሳቃሽ ሲሆን ባለአክሲዮኑ በመያዣ በመስጠት ሊጠቀም የሚችልበት የሕግ አግባብ በሕጋችን ተደንግጓል፡፡ የአክሲዮን መያዣ ሲመሰረት (በተለይ ከብር 500 በላይ ከሆነ) በጽሑፍ ውል ተደርጎ በተዋዋይ ወገኖችና በምስክሮች ተፈርሞ በአክሲዮን መዝገብ ሊገባ ያስፈልጋል፡፡ የአክሲዮን መያዣ የመክፈያቸው ጊዜ ባለፉ የትርፍ ድርሻዎች ላይ ተፈፃሚ እንዲሆን በመያዣ ውሉ በግልጽ ካልተመለከተ ትርፎቹን እንደማያካትት ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 39256 የተከተለው አተረጓጎም የአክሲዮን መያዣ በአክሲዮን መዝገብ ከመግባት ሌላ ተጨማሪ የውልና የምሥክር መስፈርት አያስፈልገውም ማለቱ ለጸሐፊው አሳማኝ አልሆነም፡፡ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2865 አክሲዮንን ለመሰለ በሰነድ ላይ ለሚገለጽ መብት ተፈፃሚ አይሆንም፡፡ የትርፍ ድርሻም ቢሆን በመያዣ ውሉ ባልተካተተበት ሁኔታ ወደፊት በሚያስገኙት ትርፍ ላይ ካልሆነ በቀር የመክፈያ ጊዜያቸው ባለፉት ትርፎች ላይ ተፈፃሚ አይሆንም፡፡ የንግድ ሕጉም ቢሆን በጉባኤ ድምፅ የመሰጠትን መብት ከባለአክሲዮኑ እንዲወጣ መፍቀዱ የባለቤትነትን መብት የሚሸረሽር በመሆኑ ፍትሐዊ አይደለም፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Constitutional Special Interest of the State of Or...
ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብትን በመተርጎም በኩል ስለታየው ችግር

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 13 June 2024