ሳንሱር እና ሕግ፡ ከትናንት እስከዛሬ

የሰው ልጅ ሐሳቡን ለሌላው መግለጽ መጀመሩ ሰዎች የጋራ ባሕርያትን ይዘው ወደ አዲስ ስልጣኔ፤ ወደ አዲስ ሕይወት እንዲወጣ አድርጎታል፡፡ ነገር ግን የዚህ ትስስር ድንበር የለሽ መሆን ጉዳት አለው በማለት፤ በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ ምክንያቶች መረጃን የመለዋወጡ ሂደት ገደብ እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ ገደብ እንዲደረግ የሚያስገድዱት ዋነኛ ምክንያቶች ሦስቱን ዋነኛ ተቋማት መጠበቅ በሚል ሐሳብ ስር ይጠቃለል፡፡ እነዚህም ተቋማት ቤተሰብ፣ ቤተ እምነት እና ቤተ መንግሥት ናቸው፡፡ ቤተሰብን መጠበቅ ስንል ቤተሰብ የኅብረተሰብ መሠረት በመሆኑ ቤተሰብን እና ስርዓቱን የሚጎዱ ነገሮች (Obscene) በአደባባይ እንዳይኖሩ ማድረግ ማለታችን ነው፡፡ ቤተ እምነትን የሚያጎድፉ ነገሮችም (Blasphemous) እንዲሁ:: እንዲሁም በሦስተኝነት በሕግ የተዘረጋውን ስርዓት ለመጠበቅ ሲባል ሲሆን  ይሄም የግደባ ሂደት ሳንሱር (Censorship) ይባላል፡፡

የሕግ ማዕቀፉ እና ልምዱ ምን ይላል?

ከላይ የጠቀስናቸውን ሦስት ተቋማት ከመጠበቅ አንፃር የተለያዩ ሀገሮች የተለያየ የህግ ማዕቀፍ ዘርግተው ጥበቃ ያደርጋሉ፡፡ ከጥንታዊቷ ሮም እስከ የዘመናችን ነጻ እና ለዘብተኛ (Liberal) ሀገሮች ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች በመነሳት የሐሳብ ዝውውርን በሕግ ሲገድቡ ነበር፤ አሁንም ይገድባሉ፡፡ ነገር ግን የሕግ ገደቡ ያለ አግባብ ተለጥጦ የግለሰቦችን መብት መግፈፍ ሲጀምር ያኔ የገደቡ ስህተት ይጀምራል፡፡ ለምሳሌ የሮማን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከመካከለኛው ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ ለተከታዮቹ 500 ዓመታት፤ አብዛኛውን የሳይንስት አስተምህሮቶች (የጋሊሊዮን መሬት በፀሐይ ዙሪያ ትሽከረከራለችን የሚል እሳቤን ጨምሮ) እንደ የኑፋቄ ትምህርት (Heresy) በመቁጠር፤ በኅብረተሰቡ ውስጥ ምንም ዓይነት ስርጭት እንዳይደረግ በማለት በሕግ ገድባ ቆይታለች፤ ሕጉንም የተላለፉትን ከእስራት እስከሞት ትቀጣ ነበር፡፡ ይሄም የተደረገው የሕግ ገደብ የሳይንሱን ዕድገት አቀጭጮት ነበር፡፡ በጥቅሉ አሁን ባለው አለም አቀፍ እሳቤ ሕሳብን ማሰራጨት ሙሉ ለሙሉ የተፈቀደ መብት (Absolute Right) እንዳልሆነ ጥቅል ስምምነት ቢኖርም፤ ገደቡ ከየት ይጀምር የሚለው ግን አከራካሪ ነው፡፡

ምኑ ይገደብ?

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ሊገደብ የሚገባው መብት የትኛው መሆን አለበት የሚለው ሐሳብ ስምምነት  ላይ ያልተደረሰበት ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ኀልዮት ሊቃውንት የተለያየ ሐሳብ ይሰነዝራሉ፡፡ መንግሥት ራሱን እንደ ጠባቂ እና ሁሉን አድራጊ (state as Big Brother) በማድረግ ይህ የተፈቀደ ነው፤ ይህ ደግሞ የተከለከለ ነው የሚል ከሆነ የዜጎችን መብት ሊያቀጭጭ ይችላል የሚለው እሳቤ አንዱ ነው፡፡ ይህም - ይሄን ብትናገር፣ ብትጽፍ፣ ብታሰራጭ ዋ! - ማለት ሳንሱር በማስፈራራት (Censorship through intimidation) የሚለው ሐሳብ ነው፡፡ ሊቃውንቱም ይህ መሆን የሌለበት ነገር ነው ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት እንደ የኅብረተሰቡ ተወካይነቱ (As agent of the Society) ኅብረተሰቡ የማይቀበላቸውን ነገሮች በሕግ መገደቡ ተገቢ ነው የሚለውን ሐሳብ እናገኛለን፡፡ ይህም ማለት መንግሥት እና ኅብረተሰቡ በሚገደበው ነገር ላይ ስምምነት አላቸው እንደማለት ነው - Censorship through consensus፡፡ ይሄም የኅብረተሰቡን የሞራል እሴቶች የሚፃረሩ ጉዳዮች ላይ ገደብ መጣሉ ተገቢ ነው ወደሚለው ሐሳብ ያደርሰናል፡፡

ስንጠቀልለውም በቀዳሚነት (As a Rule) ሐሳብን የመግለጽ ገደብ አይኑር፤ ነገር ግን ኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሊያመጡ የሚችሉ ነገሮች ላይ ገደብ ማድረግ ይገባል ወደሚለው ድምዳሜ እንደርሳለን፡፡

ገደብ በኢትዮጵያ (Censorship In Ethiopia)

የተጻፈ ሕግ በሀገራችን መተግበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በጣሊያን ወረራ ጭምር በፖለቲካ ቢሮ አማካኝነት ቁጥጥር የነበረ ቢሆንም  ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ላይ ገደብ በማድረግ ቀዳሚነቱን የያዘው፤ የ1935ት ዓመተ ምህረቱ “የቴአትርና የሲኒማ አደራረግን ስለመመርመር” የወጣው አዋጅ ቁጥር 37/1935 ነው፡፡

በርግጥ ነገር ግን ለሳንሱር መሠረት የሆነው የሕግ ማዕቀፍ የተዘረጋው ከወረራው መቀልበስ በኋላ በወጣው አዋጅ ነው፡፡ በዚህ ‹ልዩ ልዩ ጨዋታዎችን ለመመርመር በወጣ አዋጅ› አንቀጽ 4 መሰረት፡ ‹‹ማንኛውንም ፊልም፣ ቲያትር እና ሪቪው ይህንም የመሰለ የልዩ ልዩ ጨዋታ ሁሉ የጨዋታ መርማሪ ሳይመረምራቸው ለሕዝብ እንዲታዩ ማቅረብ አይቻልም›› በማለት ይደነግግ ነበር፡፡ አስከትሎም አንቀጽ 7 ላይ ‹‹የጨዋታ መርማሪው ‹‹ማንኛውንም ፊልም፣ ቲያትር እና ሪቪው ይህንም የመሰለ የልዩ ልዩ ጨዋታ ሕዝብ ይየው ወይም አይየው ብሎ የሚወስን የሕዝብን ፀጥታና ንፅህና (ብልግና የሌለበት መሆኑን) አይቶ ነው፡፡›› በማለት የገደቡ ምክንያት ደህንነት እና ንፅህናን መጠበቅ እንደሆነ ቢነግረንም፤ ስርዓቱን የሚያስኮርፉ ማናቸውም ድምፆችን ለመገደብ እንደ መሳሪያ ተደርጎ ይሠራበት ነበር፡፡ ይህ ሕግ  ንጉሡ ከሥልጣን እስከ ወረዱበት ዘመን ድረስ ዘልቆ ከስርዓቱ ጋር አብሮ ከሰመ፡፡

ደርግ ወደስልጣን በመጣበት የመጀመሪያ የሽኩቻ ዓመታት ገደቦቹ ላልተው ነበሩ ቢሆንም፤ ስልጣኑን አጥብቆ ሲይዝ ግን የበለጠ አክርሮ የተለያዩ አዋጆችን እና ደንቦችን እያከታተለ ያወጣ ጀመር፡፡ ኅብረተሰባዊነትን ይቃወማሉ ያላቸውን ሐሳቦችም በኅብረተሰባዊነት ስም እየማለ ሲያሻው በሕግ አሊያም በጉልበት ‹ሐሳብ የሚታሰብ እንጅ የሚነገር አይደለም› (You can thought anything but, you can’t express it) በሚል ብሂል ሳንሱርን አክርሮ ይሰራበት ነበር፡፡

በንጉሡ እና በወታደራዊው መንግሥት ስርዓቶች ወቅት የነበረውን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን ግፍ የበለጠ የሚነግረን የለም፡፡ ሎሬት ፀጋየ እንዲህ ይላሉ፡-

“ከፃፍኳቸው 41 ቴአትሮች ውስጥ (ከተረጐምኳቸውና በእንግሊዝኛም ከፃፍኳቸው ጭምር)፣ ዐሥራ ሁለቱን ሳንሱር ሙሉ በሙሉ አግዶብኛል፡፡ ሃያ አንዱን ቆራርጦብኛል፡፡ ሦስቱን ግማሽ ለግማሽ ጐራርዶብኛል፡፡ አራቱ ግን ገና ለመድረክ [አልቀረቡም] ከሦስቱ የሥነ ግጥም መጻሕፍቶቼ ውስጥ (ሁለቱ ገና አልታተሙም)፣ በሠላሳ ሰባት ነጠላ ዝርዝር ግጥሞቼ ምክንያት፣ የሳንሱር ቢሮ፣ የፀጥታው ክፍል ቢሮና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቴ ቢሮ ከፍተኛ ሹማምንት ገስፀውኛል፡፡ ቀጥተውኛል፡፡ ዝተውብኛል፡፡ በአንዲት “ጆሮ ገድፍ” በምትባል ትንሽ ቴአትር ምክንያት የጃንሆይ መንግሥት ፀጥታ ቢሮ፣ ለሃያ አራት ሰዓት በቁጥጥር ስር አውሎኛል”

‹ሳንሱር ደህና ሰንብች›

የደርግ ስርዓት መገርሰስ ካመጣቸው መሠረታዊ ለውጦች አንዱ ሐሳብን በነጻነት የመግለጻ መብት መከበሩ ነው፡፡ የሳንሱር ቢሮም መዘጋቱ፡፡ ለዚህም መብት የመጀመሪያ ከለላ የሆነው የ1983 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር ነው፡፡ ቻርተሩ በአንቀጽ አንድ ዓለም አቀፉ የሰብኣዊ መብት ደንጋጌ (Universal Declaration of Human Right) ያለምንም ገደብ ለኢትዮጵያዊያን ተግባራዊ የሚደረግ ሰነድ መሆኑን ከደነገገ በኋላ በተለይም እያንዳንዱ ግለሰብ የእምነት፣ ሐሳብን መግለጽ፣ የመደራጀት መብት አለው›› በማለት ይደነግጋል፡፡ ይሄንም ተከትሎ 1985ቱ የፕሬስ ሕግ መውጣት ሀገሪቱ ሐሳብን የመግለጽ መብትን ያለገደብ ለማክበር ቆርጣ መነሳቷን አመላካች ሆነ፡፡

ለዚህ ነጻነት ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ ለመስጠት በማሰብም በ1987 ዓ.ም በወጣው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊት ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ፡- ‹‹ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችል፡፡›› በማለት በአመለካከት ደረጃ ምንም ዓይነት ገደብ እንደሌለ አስረግጦ ሲያበቃ፤ በተመሳሳይ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ደግሞ ‹‹ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው፡፡ ይህ ነጻነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛወም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን ያካትታል፡፡›› ብሎ መብቱን ያሰፋዋል፡፡ እንዲሁም በዚሁ አንቀፅ ንዑስ ቁጥር 3 ላይ  ‹‹የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ ነው፡፡›› በማለት ነፃነትን በሰፊው ያውጃል፡፡ ነገር ግን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በሕግ ገደብ ሊደረግበት እንደሚችል አንቀፁ ያትታል፡፡

‹ሳንሱር እንደገና›!?

እነዚህ ሁሉ መብቶች በሰፊው በሕግ ከለላ ማግኝታቸው ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘበት የመጀመሪያው ዐሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደ ትልቅ እምርታ የሚታይ ሲሆን ይሄንም ተከትሎ በሀገሪቱ ውስጥ የፕሬስ መስፋፋት እንዲሁም ሐሳብ መግለጫ ሜዳው መስፋት አሳይቷል፡፡ የተለያዩ መጽሔቶች ጋዜጦች እና የስነጽሑፍ ሥራዎች (መጽሐፍትን ጨምሮ) ስርጭትም በሚታይ ሁኔታ መስፋፋት ጀመረ፡፡ ይህ ሁኔታ ያልሰከነ በመሆኑ የሚታማውን የቅድመ 97 የፕሬስ ዘመን የሚጨምር ሲሆን ለዓመታት በቋሚነት የቆዩትን እንደነ ጦቢያና ጦማር የመሳሰሉትን የሕትመት ውጤቶችን ይዞ ዘልቋል፡፡ የምርጫ 97 ውጤት ደም አፋሳሽ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መንግሥት በጉዳዩ ላይ የፕሬስ ተቋማት ሰራተኞችን እና ጋዜጠኞችን ማሰሩን አስከትሎ ጠበቅ ያለ አቋም መያዝ ጀመረ፡፡


አዋጆቹ

ከምርጫ 97 በሁዋላ ምንም እንኳን የወንጀል ሕጉ ሐሳብን ከመግለጽ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ ወንጀሎች እንደሚያስቀጡ ቢደነግግም ከዚህ በተጨማሪ ጋዜጠኞችን የሚጫኑ ቅጣቶችን በማከል ከብዙ አተካራ በኋላ የመገናኛ ብዙኃን እና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ሕግን አፀደቀ፡፡ ከብዙ አካላትም በዋነኛነት ከጋዜጠኖች ሕጉ አፋኝ  እና ሕገ መንግሥቱንም የሚፃረር መሆኑን በመግለጽ ተቃውሞ መሰማት ጀመረ፡፡

በማስከተልም አወዛጋቢው የፀረ-ሽብር ሕግ ለፓርላማ ቀርቦ ፀደቀ፡፡ የመገናኛ ብዙኃን እና የመረጃ ነጻነት አዋጅ እንዲሁም የፀረ-ሽብር ሕጉ ሐሳብን ከመገደብ (Censorship) ጋር ያላቸው ተዛምዶ በዋነኛነት ተዘዋዋሪ ነው፡፡ ይሄም ማለት የመገናኛ ብዙኃን እና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ያስቀመጠው እስከ አንድ መቶ ሽሕ ብር የሚደርስ ቅጣት አቅመ ደካማውን ፕሬስ በአንዴ ከገበያ ውጭ ሊያደርገው ስለሚችል ጋዜጠኞች ራሳቸውን እንዲገድቡ (Self Censorship) የሚያስችል መሆኑ፤ እንዲሁም የፀረ-ሽብር ሕጉ ግልጽ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን ጭምር በሽብር ተግባርነት የሚፈርጅ መሆኑ ዜጎች ራሳቸውን እንዲገድቡ እና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ ማድረጉ ነው፡፡ ይሄም በሕግ ቋንቋ ‹Chilling Effect› ወይም ‹ስጋት ለበስ ቅልበሳ› የሚባለው ነው፡፡ ይህም ማለት ዜጎች ቅጣትን በመፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ከመጠቀም ወደኋላ ማድረግ (discouragement of the legitimate exercise of a constitutional right) ነው፡፡

እነዚህ ቀጥተኛ ያልሁኑ የራስን ግደባ ሁኔታዎች እንዳሉ ሆነው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መንግሥታዊ ተቋማት ‹የሥራ ውል› በሚል መጠሪያ፤ ለሕትመት የሚበቁ ጽሑፎችን በመርማሪ አስመርምረን ነው የምናትመው ማለታቸው፤ ጉዳዩን ከማባስም አልፎ በሕገ መንግሥት በግልጽየተከለከለውን ሳንሱር በእጅ አዙር እየመጣ ነው እንዴ? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡

ከነዚህ ሕጎች እና ደንቦች በተጨማሪ እያደገ የመጣውን የድረ-ገጽ ተጠቃሚ ቁጥር መሠረት በሚያደርግ መልኩ ከምርጫ 97 ወዲህ ትክክለኛ ቁጥራቸውን ማወቅ የማንችላቸው ድረገጾች በኢትዮጵያ ብቸኛ የቴሌኮምኒኬሽን አገልግሎት አቅራቢ በሆነው በኢትዮቴሌኮም ሰርቨር እንዳይታዩ የሆኑ ሲሆን፤ ይሄም እገዳ (Censorship) ከአረቡ ዓለም መነቃቃት በኋላ እጅግ ተባብሶ በመቀጠል እንደ አልጀዚራ ያሉትን ዓለማቀፍ የዜና አውታሮችን ከማገድ ጀምሮ፤ የግለሰቦችን የማኅበራዊ ድረ-ገጽ አድራሻ እስከማፈን ቀጥሏል፡፡ (ከዚህ ጋርተያይዞ የዞን 9ኝን የጦማሮች ምን ጻፉ ጽሁፍ እዚህይመልከቱ) መንግሥት ለዚህ እና ከእገዳ ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽ፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮን መንግሥታቸው ሀገሪቱን ከማረጋጋት አኳያ ማፈኑን እና የአፈና አቅማችን እያጠናከርን ነው ከማለታቸው በስተቀር፤ በደፈናው ‹እኔ አላገድኩም› የሚል  ነው ፡፡(በተለይ የተለያዩ የፊስቡክ ገጾች እና ጦማሮችን የመዝጋት ልምድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ መጥቶ የአቤ ቶክቻው የግል ፊስቡክ ገጽ፣ የዞን ዘጠኝ የፌስ ቡክ ገጽ እና ጦማር፣ ድምጻችን ይሰማ እንዲሁም በቀዳሚነት የተዘጋው የቀድሞው አዲስ ነገር ጋዜጣ የፌስ ቡክ ገጽ ይታወሳሉ፡፡)

ስናጠቃልልም የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በግልጽ እገዳን እና አፈናን (Censorship) ከመከልከሉም በተጨማሪ፤ ኢትዮጵያዊያን መረጃ የማግኝት መብታቸው በሰፊው የተከበረላቸው መሆኑን ያትታል፤ ነገር ግን በተለይም ከምርጫ 97 ማግስት ጀምሮ መንግሥት በሚያወጣቸው ሕጎች እንዲሁም ከሕግ ውጭ በሆኑ አካሄዶች እነዚህን መብቶች እያጠበባቸው እና እየገፋቸው እንደሆነ እውነታዎች ያሳያሉ፡፡ ይሄም በሀገሪቱ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ (Singular Discourse) እንዲኖር መፈለጉም የዜጎችን በሕገ መንግሥት የተሰጠ መብት፤ በአዋጅ መንጠቅና ግፋም ሲል በጉልበት ወደመቀማት እየመራው ነው የሚለውን እሳቤ አጉልቶታል፡፡ ነገር ግን የBen Shahn ፖስተር “You have not converted a man because you have silenced him." ይለናል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

International Criminal Court and African Union: Se...
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራትን ፈቃድ ከማደስ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 28 March 2024