Font size: +
6 minutes reading time (1195 words)

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራትን ፈቃድ ከማደስ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮች

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ከበጎ አድራጎት ኮሚቴ በቀር ለሁሉም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሦስት የህልውና ደረጃዎችን ያስቀምጣል፡፡ እነዚህም ምስረታ፣ ምዝገባ እና ፈቃድ ናቸው፡፡ ምስረታ የምንለው የበጎ አድራጎት ድርጅቱን ወይም ማህበሩን ለመፍጠር አስፈላጊ የሚሆኑበት የመጀመሪያ ደረጃ ነው፡፡ የዚህ ደረጃ ዋነኛ መለያው ሶስት ወር ገደማ በሚሆነው በዚህ ጊዜ ውስጥ ድርጅቱ ወይም ማህበሩ ሕጋዊ ሰውነት የሌለውና በሕግ ፊት ውጤት ያላቸውን ተግባራት ለማከናወን ያለው ብቃትም ውሱን መሆኑ ነው፡፡ በተለይም በድርጅቱ ወይም በማህበሩ ስም ገንዘብ የማሰባሰብ ብቃቱ ውሱን ወይም በሕግ የተገደበ ይሆናል፡፡ ይህ የመጀመሪያ ደረጃ ድርጅቱ ወይም ማህበሩ ሲመዘገብ ወይም ባለመመዝገቡ ምክንያት ህልውናውን ሲያጣ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ህልውና ቀጣዩ ደረጃ ምዝገባ ሲሆን ድርጅቱ ወይም ማህበሩ በህግ ፊት እውቅና የሚያገኝበት በመሆኑ ከሶስቱ ደረጃዎች ውስጥ ወሳኝ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ አንድ ድርጅት ወይም ማህበር በተመዘገበ ጊዜ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ በሕግ ፊት ውጤት ያላቸውን ተግባራት ለማከናወን ብቁ ይሆናል፡፡ በሌላ አባባል አንድ በመመስረት ላይ የነበረ ድርጅት ወይም ማህበር ሲመዘገብ ውል መዋዋልን የመሰሉ የሕግ ትርጉም ያላቸውን ተግባራት ማከናወን ይችላል፡፡ ለአንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር ይህ ማለት ሰራተኞችን በመቅጠር እና ክንውኖችን በመተግበር የተቋቋመበትን ዓላማ ለማስፈፀም የሚያስችል ብቃት በሕግ ፊት ያስገኝለታል ማለት ነው፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ወይም ማህበሩ በሕግ በተቀመጡ ምክንያቶች ካልፈረሰ በቀር ሕጋዊ ሰውነቱን ይዞ ላልተወሰነ ጊዜ ይቆያል፡፡

ይሁን እንጂ ምዝገባ እና ተያይዞ የሚመጣው ሕጋዊ ሰውነት ማግኘት የበጎ አድራጎት ደርጅቱ በሕግ ፊት ውጤት ያላቸውን ተግባራት ለማከናወን ያገኘውን ብቃት እውን ለማድረግ አያበቁትም፡፡ ለዚህ የግድ ፈቃድ ማግኘት አለበት፡፡ ፈቃድ መስጠት ማለት አንድ ደርጅት ወይም ማህበር ባስቀመጠው አካባቢ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማስፈጸም ክነውኖችን ወይም ፕሮጀክቶቸን ለመተግበር የሚፈቅድለት ሰርትፍኬት የሚያገኝበት ሂደት ነው፡፡ አንድ ደርጅት ወይም ማህበር በሕግ የተቀመጡ መስፈርቶችን አሟልቶ በተቋቋመ ጊዜ ወዲያውኑ ፈቃድ የሚያገኝ ሲሆን ፈቃዱ በየጊዜው (በየሦስት ዓመት) መታደስ አለበት፡፡

ይህ አጭር ፅሁፍ በሁለት ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፤ እነዚህም የበጎ አድራጎት ደርጅቶችና ማህበራት ፈቃድ ለማሳደስ ሊሟሉ የሚገባቸው ቅድመ-ሁኔታዎች እና እነዚህ ቅድመ-ሁኔታዎች በዘርፍ አስተዳዳሪዎች የፕሮጀክት ስምምነት ለመፈፀም ከሚጠየቁት መመዘኛዎችና ለጋሾች የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ከሚያስቀምጧቸው ቅድመ-ሁኔታዎች ጋር ያላቸው ትስስር ናቸው፡፡

ፈቃድ ለማሳደስ ሊሟሉ የሚገባቸው ቅድመ-ሁኔታዎች

የፈቃድ እድሳት በሚያሳድሰው ድርጅት ወይም ማህበር ማመልከቻ ሲቀርብ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ሲሆን ለዚህም ሦስት ቅድመ-ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቅድመ-ሁኔታዎች የእድሳት ክፍያ ከመፈጸምና የተሟላና ትክክለኛ የሥራ አፈፃጸምና የኦዲት ሪፖርት ማቅረብን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ሦስተኛውና ጠቅለል ያለው ቅድመ-ሁኔታ ግን የበጎ አድራጎት ደርጅቱ ወይም ማህበሩ የአዋጁን ድንጋጌዎች ወይም በአዋጁ መሰረት የወጡ ደንቦችና መመሪያዎችን ወይም የኤጀንሲውን ትእዛሶች ወይም የራሱን መተዳደሪያ ደንብ ያልጣሰ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ በሌላ አባባል ድርጅቱ ወይም ማህበሩ የአዋጁን፣ የደንቡን፣ የኤጀንሲውን መመሪያዎች ወዘተ… የጣሰ እንደሆነ ፈቃዱ ላይታደስለት ይችላል፡፡

የበጎ አድራጎት ደርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ፈቃድ ለማሳደስ ሊሟሉ የሚገባቸውን ቅድመ-ሁኔታዎች በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪዎችን ሰጥቷል፡፡ የኤጀንሲው ድህረ-ገፅ እንደሚያመለክተው የተጠናቀሩት ቅድመ-ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፡ -

-        የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ያለፉት ሶስት ዓመታት የሥራ አፈፃፀም እና ኦዲት ሪፖርቶች የተሟላና ትክክለኛ መሆኑ ሲረጋገጥ፤

-   የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት የአዋጁ ድንጋጌዎች ወይም አዋጁን ለማስፈፀም የወጡ ደንቦችንና መመሪያዎችን ወይም በኤጀንሲው የተሰጡ ትዕዛዞችን ወይም የራሱን መተዳደሪያደንብ ያልጣሰ መሆኑ ሲታመንበት፤

-    የቀጣይ ሦስት ዓመታት የሥራና በጀት ዕቅድ ኤጀንሲው ባወጣው መመሪያ ቁጥር 8 አንቀጽ 20 መሠረት ተዘጋጅቶ በቦርዱ ወይም በስራ አስፈፃሚ ጸድቆ ሲቀርብ፤

-        የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ከሚመለከተው የመንግሥት አስፈፃሚ አካል ጋር የገባው የፕሮጀክት ስምምነት ፣

-        ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ግብር የከፈለበትን ደረሰኝ ኮፒ፣ እና

-        የፈቃድ የማሳደሻ ክፍያ 400 ብር ሲፈጸም የታደሰውን የምስክር ወረቀት ይዘው ይመለሳሉ፡፡

ምንም እንኳ እነዚህ ቅድመ-ሁኔታዎች በሙሉ ከአዋጁ ወይም በቀጣይነት ከወጡት ደንብና መመሪያዎች ድንጋጌዎች የሚመነጩ ቢሆኑም ሁለቱ መመዘኛዎች በዚህ የበጀት ዓመት ፈቃዳቸውን ለሚያሳድሱት 1804 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የስጋት ምንጭ ሆነዋል፡፡

ከነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው የሚቀጥሉትን ሦስት አመታት የሥራና የበጀት እቅድ አስቀድመው እንዲያቀርቡ የሚጠይቀው ነው፡፡ የድርጅቶቹን ቀጣይነትና የእንቅስቃሴዎቻቸውን ተገማችነት ከማረጋገጥ እና ክንውኖቻቸውን በአግባቡ መቆጣጠር እንዲችሉ ከማድረግ አንፃር የዚህ ቅድመ-ሁኔታ አስፈላጊነት ግልፅ ነው፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ ነዋሪ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በለጋሾች ላይ ጥገኛ የመሆን አዝማሚያን ከመቀነስ አኳያ ያለው ጠቀሜታም ጉልህ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መመዘኛ በድርጀቶቹ እና በለጋሾቻቸው መካከል ያለውን ግንኙነት የሚወስኑ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ አይመስልም፡፡ አጅግ በተሳካ ሁኔታ ውስጥ እንኳን ቢሆን ቀድመው ለተለዩ ክንውኖችና ፕሮጀክቶች ለመጪው አንድ አመት ገንዘብ ማግኘት እንደሚችሉ እርግጠኛ ለመሆን የሚችሉ ድርጅቶች ቢኖሩ አንኳ ቁጥራቸው ትንሽ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ገንዘብ የሚያገኙት ለጋሽ ድርጅቶች ከአንድ የበጀት አመት ላልበለጠ ጊዜ ለሚተገበሩና ባስቀመጡዋቸው ጉዳዮች ዙሪያ ለሚያተኩሩ ፕሮጀክቶች ድጋፍ ለመስጠት ለሚያወጡዋቸው ማስታወቂያዎች ምላሽ በመስጠት ነው፡፡ ስለዚህም የሦስት ዓመት የሥራና የበጀት እቅድ ማዘጋጀት ቢቻል የሚመሰገን ሃሳብ ቢሆንም በተግባር ለመፈፀም የሚቻል ግን አይሆንም፡፡

ይህ መመዘኛ ከዚህ በተጨማሪ ፈቃድ በማደስ እና የገንዘብ ድጋፍ በማግኘት መካከል ሊኖር በሚገባው ቅደም ተከተል ጋር በተያያዘ ሌላ ጥያቄም ያስነሳል፡፡ በአጠቃላይ ለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ ከማድረጋቸው በፊት ድጋፍ የሚደረግለት ድርጅት ለሚያካሂደው ፕሮጀክት የትገበራ ጊዜ የታደሰ ፈቃድ ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፡፡ ይህም የድጋፍ ጥያቄ ከመቅረቡ ቀድሞ መፈጸም አለበት፡፡ እዚህ ላይ እየተነጋገርን ያለነው የፕሮጀክት ሃሳብ ለማሰባሰብ ለወጣ ማስታወቂያ ምላሽ ለመስጠት ወይም ሌላ ድጋፍ የማድረጊያ ሂደት ተጠቃሚ ለመሆን ስለሚጠየቅ መመዘኛ ነው፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ገንዘብ ፈቃድ ላልታደሰለት ድርጅት ወይም ማህበር በለጋሾች የሚለቀቅበትን መንገድ ለማሰብ አይቻልም፡፡ በመሆኑም የትኛውም የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር ሊተገበር የሚችል የሦስት ዓመት የበጀት እቅድ ሊያዘጋጅና ሊያቀርብ አይችልም፡፡

ተመሣሣይ ጥያቄዎችን የሚያስነሳው ሁለተኛው ፈቃድ ለማሳደስ የሚጠየቀው ቅድመ-ሁኔታ ደግሞ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ከሚመለከተው የመንግሥት አስፈፃሚ አካል ጋር የገባውን የፕሮጀክት ስምምነት እንዲያቀርብ የሚጠይቀው ነው፡፡ የሚጠየቀው ስምምነት እድሳቱ በሚጠየቅበት ጊዜ ቀድመው የተጠናቀቁ ወይም በመካሄድ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን የተመለከተ ከሆነ አስፈላጊነቱ ግልፅ አይደለም፡፡ በአንፃሩ የሚጠየቀው ስምምነት በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ከሆነ በሚመለከታቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ዘንድ ሁለት ዋና ዋና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በመጀመሪያ ለታቀዱት ፕሮጀክቶች በቂ የገንዘብ ድጋፍ ወይም ምንጭ መኖሩን እርግጠኛ መሆን ስለማይችሉ መተግበራቸው እርግጠኛ ላልሆኑ ፕሮጀክቶች ከመንግስት አካላት ጋር ስምምነት ለመግባት ይጠየቃሉ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ወደፊት የፕሮጀክት ስምምነቶቹን ለማክበር ስለማይችሉ ራሳቸውን ለተለያዩ አሉታዊ እርምጃዎችና ቅጣቶች የሚያዘጋጁበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ይህ ቅድመ-ሁኔታ የፕሮጀክት ስምምነቶችን ለመፈራረም መሟላት ካለባቸው መመዘኛዎች አኳያ በዘርፍ አስተዳዳሪዎች ዘንድ ያለውን ተሞክሮና አሰራር ታሳቢ ያደረገ አይመስልም፡፡ ስምምነቶቹን ከመፈራም በፊት ሊሟሉ ከሚገባቸው መመዘኛዎች መካከል የታደሰ ፈቃድ እና ለታቀደው ፕሮጀክት የተገኘ የገንዘብ ድጋፍ መኖሩ ይገኙባቸዋል፡፡ የመንግስት አካላት ፕሮጀክቶቹን ከአጠቃላይ የልማት እቅዶቻቸው ጋር ለማጣጣም እና የታቀዱ ፕሮጀክቶችን ለማስፈፀም አስፈላጊው ግብአት መኖሩን ማረጋገጥ ያለባቸው በመሆኑ እነዚህን መመዘኛዎች ማስቀመጣቸው ምክንያታዊ ነው፡፡ በአንፃሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በሁለቱ ደረጃዎች ሊያሟሏቸው በማይችሏቸው ቅድመ-ሁኔታዎች ይገደባሉ፤ የፕሮጀክት ስምምነት ለመፈረም የታደሰ ፈቃድ ያስፈልጋል፣ ፈቃድ ለማደስ ደግሞ የፕሮጀክት ስምምነት መፈራረም ያስፈልጋል፡፡

ማጠቃለያ

በአጭሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ፈቃዳቸውን ለማሳደስ ለሚቀጥሉት ሦስት አመታት የሥራና የበጀት እቅድ እንዲሁም ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር የተፈረመ የፕሮጀክት ስምምነት ማቅረብ አለባቸው፡፡ የዘርፍ አስተዳዳሪዎች ደግሞ ስምምነት ለመፈራረም የታደሰ ፈቃድ እና ፕሮጀክቶቹን ለመተግበር የሚያስችል የገንዘብ አቅም ወይም ምንጭ መኖሩን ቀድመው ማረጋገጫ ይፈልጋሉ፡፡ ለጋሾች በበኩላቸው የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የታደሰ ፈቃድ እና ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር የተፈረመ ስምምነት ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ሁኔታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሥራቸውን በአግባቡ መተግበር የማይችሉበት አዙሪት ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ከዚያም አልፎ የፈቃድ መሰረዝ ወይም የገንዘብ ድጋፍ ባለማግኘቱ እዳውን መክፈል ያለመቻል ለመፍረስ የሚያበቃ እንደመሆኑ ይህ ሁኔታ በድርጅቱ ወይም በማህበሩ ህልውና ላይ አደጋ ሊፈጥር ይችላል፡፡

ምንም እንኳ በዚህ ፅሁፍ የተዳሰሱትን ጭብጦች አንጥሮ ለማውጣትና መፍትሄ ለመስጠት ተጨማሪና ጥልቅ ጥናት የሚያስፈልግ መሆኑ ባይካድም ፈቃድን ከማሳደስ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች ሁለት መነሻዎች ያሏቸው ይመስላሉ፡፡ በመጀመሪያ ይህ የበጀት አመት በ2002 ዓ.ም. በአዋጁ መሰረት የተመዘገቡ ወይም እንደገና ምዝገባ ያደረጉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለሦስት አመታት በሥራ ላይ ቆይተው ለመጀመሪያ ጊዜ ፈቃድ የሚያድሱበት ነው፡፡ በመሆኑም ተፈፃሚነት ያላቸውን ድንጋጌዎች ከመተግበር አኳያ ክፍተቶችና ችግሮች መከሰታቸው የግድ ነው፡፡ በተለይም ለበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የመጀመሪያ ዙር የፈቃድ አሰጣጥ ሂደት ከምዝገባ ጋር የተካሄደ መሆኑ ይህንን አስተያየት የሚያጠናክር ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ እስከአሁን ያለው አሰራር ኤጀንሲው፣ የዘርፍ አስተዳዳሪዎች እና ለጋሾች የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራትን ከመቆጣጠርና ከመደገፍ አኳያ የየራሳቸውን ሚና በሚጫወቱበት ሂደት የሚያስቀምጧቸውን ቅድመ-ሁኔታዎችና መመዘኛዎች የማጣጣም ሥራ ገና ያልተጠናቀቀ መሆኑ ነው፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ለተለያዩ አካላት ተጠያቂነት ያለባቸው መሆኑን ታሳቢ ስናደርግ ይህ ሁኔታ መከሰቱ እምብዛም አያስደንቅም፡፡

በመጨረሻም እነዚህን ክፍተቶችና ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ይቻል ዘንድ ኤጀንሲው፣ የዘርፍ አስተዳዳሪዎች እና ለጋሾች ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ የምክክር ሂደት ችግሮቹ ሲፈጠሩ መፍትሄ ለመሻትም ሆነ በቀጣይነት የተጣጣመ አሰራር ለመፍጠር ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ሳንሱር እና ሕግ፡ ከትናንት እስከዛሬ
Exploring Issues in the Renewal of Licenses for Ch...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 12 December 2024