Font size: +
6 minutes reading time (1228 words)

የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝ (Stop Payment Order) የሚሰጠው መቼ እና እንዴት ነው?

ቼክ ጥሬ ገንዘብን ተክቶ በመገበያያነት አገልግሎት ላይ የሚውል የሚተላለፍ የንግድ ወረቀት አይነት ነው። በሀገራችን በቼክ መገበያየት እጅግ የተለመደ ተግባር ሲሆን ቼክም ሌሎች የሚተላለፉ የንግድ ሰነዶች ካላቸው እውቅናና ተቀባይነት በላቀ አገልግሎት ላይ እየዋለ ያለ እና በህብረተሰቡም ዘንድ እውቅና ያለው ሰነድ ነው። በሰነዱ ላይ ህብረተሰቡ የጣለው እምነትና በስፋት አገልግሎት ላይ መዋሉም በሰነዱ ላይ በተለያዩ ጊዜያት እና በስፋት የፍርድ ቤት ክርክሮች እንዲነሱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ እሙን ነው። ታዲያ በዚህ ሰነድ በስፋት አገልግሎት ላይ መዋልና በሕጋችን ውስጥ ሰነዱን አስመልክቶ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ማሻሻል እና ክፍተቱን መሙላት አስፈላጊና ለሰነዱ ቀጣይነትም አስተማማኝ ዋስትና ነው።

በዚህ አጭር ጽሑፍ ውስጥም በተለይም ቼክን በተመለከተ በስፋት የሚያጋጥመውንና በሕጋችን ሽፋን የተሰጠውን   የቼክ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ (Stop Payment Order) በተመለከተ ጥቂት ምልከታ ለማድረግ ነው። በጉዳዩ ላይ በስፋት አንባቢዎች ግንዛቤን ከፈለጉ ጸሐፊው የኢትዮጵያ የባንክ እና የሚተላለፉ የንግድ ሰነዶች ሕግ በሚል የታተመውን መጽሀፍ ማንበብ እንደሚችሉ በዚሁ ለመግለጽ እወዳለሁ።

የቼክ ክፍያ ባንክ አልፈጽምም ሊል የሚችለው መቼ ነው

ቼክ ህጉ የሚፈልገውን ፎርማሊቲዎች(የንግድ ሕግ አንቀጽ 827ን  ይመለከቷል) አሟልቶ ለከፋዩ ባንክ ክፍያ እንዲፈጸም ከቀረበ በኋላ ከፋዩ ባንክ ለአምጪው ክፍያ አልፈጽምም ሊል ከሚችልባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝ በአውጪው ለባንኩ የተሰጠ እንደሆነ ነው(የኢትዮጽያ የባንክ እና የሚተላለፉ የንግድ ሰነዶች ሕግ መጽሐፍ፣ ገጽ 179)። በንግድ ሕጋችን አንቀጽ 857 የእንግሊዝኛው ቅጂ እንደተመለከተውም በአውጪው የሚሰጥ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ የቼኩ ከፋይ ባንክ ቼኩን ክፍያ አልፈጽምም ለማለት በቂ ምክንያት(sufficient authority) ነው በማለት ያሰቀምጣል። በተመሳሳይ መልኩ የአማርኛው የንግድ ሕግ አንቀጽ 857 ቅጂ ቼኩ ከመከፈሉ በፊት አውጪው እንዳትከፍል ብሎ የነገረው እንደሆነ ባንኩ የቼኩን ዋጋ አልከፍልም ለማለት ይችላል ይላል። እነዚህ የንግድ ሕጉ ድንጋጌዎች አንደኛ በጣም ጥቅል የሆነ ሀሳብ የያዙ በመሆኑ የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝን የሚያስፈጽሙት ባንኮች በምን በምን ምክንያት ክፍያ ይቁም ትዕዛዝን ተቀብለው ማስፈጸም እንዳለባቸው ባለመግለጹ ለቼክ ተገልጋዮችም ሆነ ለባንኮች የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥር ይሆናል። ሁለተኛውና ዋናው ችግር አንቀጹ የቼክ ከፋይ ባንኮች የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝን እንደ ግዴታ መፈጸም እንዳለባቸው ሳይሆን አልከፍልም ለማለት ይችላል እና በቂ ምክንያት ነው በሚሉ የላሉ ቃላቶች በማስቀመጡ ባንኮችም ቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝን መቀበልና ያለመቀበል መብት ያላቸው እና በባንኮች በጎ ፈቃድ(ስልጣን)(Discretion) ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የሚያሳብቅ የህግ አንቀጽ ነው።

የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝ መስጠት የሚቻልበት መንገድ

 ሌላው ጉዳይ ህጉ የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝ በምን በምን መንገዶች ይሰጥ( ማለትም በቃል ይሁን፣ በጽሑፍ፣ በስልክ፣ በፋክስ ወይም በሌሎች የመገናኛ መንገዶች) ያስቀመጠው ነገር ባለመኖሩ አንዱ የክርክርና የውዝግብ በር የሚከፍት ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው( ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ ጨምሮ ማብራሪያ የሚሰጠውን የኢትዮጽያ የባንክና የሚተላለፉ የንግድ ሰነዶች ህግ መጽሐፍን በማጣቀሻነት ቢያነቡት የተሻለ ግንዛቤ ማግኘት ይችላሉ)። ከዚህ በዘለለ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ የሚሰጠው ቼኩን የጻፈው አውጪው ብቻ እንደሆነ በህጉ ላይ መቀመጡ በቀጣይነት ቼክ የሚተላለፍ ሰነድ በመሆኑና በጀርባ በመፈረም የተላለፈላቸው ቀጣይ የቼኩ ተጠቃሚዎች የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝ እንዳይሰጡና መብታቸው የተገደበ እንዲሆን ያደርግባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በቼኩ ላይ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ ለማሰጠትም አውጪው መፈለግና አውጪው ክፍያ ይቁም ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ማስደረግ ያለባቸው በመሆኑ በዚህ ሂደት አላስፈላጊና ከፍተኛ መጉላላት እንዲሁም በዚሁ የፍለጋ ጊዜ ውስጥ ቼኩ እንደቀረበ የሚከፈል የክፍያ ሰነድ በመሆኑ ቼኩ ከነጭራሹ ተከፍሎ መብታቸውን እስከማጣት የሚያደርስ ጉዳት ሊደርስባቸው ስለሚችል በዚህ ረገድ ህጉ ያለበትን ክፍተት መሙላት ይጠበቅበታል።

የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝ ከብሔራዊ ባንክ መመሪያ አንጻር

ከቼክ ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮችን ለመዳኘት ብሔራዊ ባንክ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ መመሪያዎችን አውጥቷል። ይሁንና ግን እነዚህ መመሪያዎች የቼክ እንቅስቃሴን፣ የቼክ ሂሳብ መክፈትን፣ በቂ ስንቅ ሳይኖር ቼክ መጻፍንና ሌሎች የተንቀሳቃሽ ሂሳብ ጉዳዮችን ከሚመለከቱ ውጪ ስለ ቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝ የሚመለከት አንድም ድንጋጌዎች አልነበሯቸውም። በቅርቡ የወጣው የብሔራዊ ባንክ መመሪያ፣ መመሪያ ቁጥር SBB/61/2016 ግን በአንቀጽ 6 የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝን የተመለከቱ አንቀጾችን አስቀምጧል። ይህ መመሪያም ቢሆን ስለቼክ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ ያስቀመጣቸው ድንጋጌዎች አሁንም ቢሆን ብዙውን የአሰራርና የህግ ክፍተት የሸፈኑ አይደሉም። ይሁንና ግን መመሪያው በአንቀጽ 6 ላይ እንዳስቀመጠው ከሆነ አንድ ቼከን የጻፈው አውጪው የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝ ቢደርሰው እንኳን የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዙ ለከፋዩ ባንክ የተሰጠው በዚሁ መመሪያ አንቀጽ 5 ላይ የተቀመጠውንና በቂ ስንቅ ሳይኖር ቼክ መጻፍ የሚያስከትለውን አስተዳደራዊ ሀላፊነት ወይም የወንጀል ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ ከሆነ ላይቀበለው ይችላል ይላል።( በአውጪው ላይ በቂ ሂሳብ ሳይኖር ቼክ በመጻፉ የሚጣሉ አስተዳደራዊ እርምጃዎች እና የወንጀል ተጠያቂነት ምንድናቸው የሚለውን ለመመልከት የኢትዮጽያ የባንክ እና የሚተላለፉ የንግድ ሰነዶች ሕግ መጽሐፍን ይመልከቱ) በመመሪያው ላይም የቼክ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ በመመሪያው ላይ የተቀመጠውን ቅጣት ለመሸሽ ተደርጓል ተብሎ የሚታሰብባቸውን መሰረቶች አስቀምጧል። እነዚህ መሰረቶችና የህግ ግምቶችም አንደኛ የቼክ ክፍያ ይቁም ጥያቄው ለባንኮች ሲቀርብ የአውጪው ሂሳብ ውስጥ የተጻፈውንና ለተከፋዩ የሚከፈለውን የገንዘብ መጠን ሊሸፍን የሚችል በቂ ስንቅ(ሂሳብ) ቼኩ በሚጻፍበት እና ወይም ለክፍያ በሚቀርብበት ጊዜ( ይህ አገላለጽ በራሱ ግልጽነት ይጎድለዋል። ምክንያቱም በንግድ ሕጉ አንቀጽ 830 ላይ የተቀመጠው አውጪው ቼኩን በሚጽፍበት ጊዜ በሂሳቡ ውስጥ ሊያዝበት የሚችል በቂ ሂሳብ እና ይህንኑ ሂሳብ የማንቀሳቀስ መብት ጭምርም ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ያለበት መሆኑን እንጂ መመሪያው እንደሚነግረን ለክፍያ በሚቀርብበት ጊዜ በቂ ስንቅ እስካለው ድረስ የሚል አይደለም። በመሆኑም መመሪያው የንግድ ሕጉን ድንጋጌዎች እስካልተሻሻለ ድረስ የመጠበቅ የህግ መስመር መከተል ነበረበት።) ሌላው አውጪው የቼክ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ ሰጥቶ በ15 ቀናት ውስጥ ለቼኩ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ መስጠት ምክንያት የሆነው ጉዳይ የቼኩ መጥፋት ወይም መሰረቅ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅበታል።

መመሪያው ባንኮች ከእነዚህ ምክንያቶች ውጪየቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝን ለመቀበልም ሆነ ላለመቀበል ሌሎች ምክንያቶችን ከግምት ላያስገቡ እንደሚችሉ ጠቅሷል። በመሆኑም መመሪያው ምክንያቶቹን መሰረቅና መጥፋት ብቻ ብሎ ለመዝጋት መሞከሩ ከዚህ ውጪ በተለያዩ ምክንያቶች በሀይል፣ በጫናና በዛቻ ወይም በሌላ ምክንያት አንድ ግለሰብ ቼክን የጻፈ ከሆነ የቼክ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ በመስጠት ቼኩ እንዳይከፈል የሚያደርጉበትን መንገድ የዘጋ ነው። ሌላው መመሪያው የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ ምክንያቶች የቼኩ መሰረቅ ወይም መጥፋት ብቻ መሆኑን በአንድ በኩል ለመግለጽ እየሞከረ በሌላ በኩል ባንኮች ሌሎች ምክንያቶችን ተቀባይነት ያላቸው ምክንያቶች ናቸው ብለው ላይቀበሉ ይችላሉ በማለት ሌላ ቀዳዳና መብት ለመስጠት ይዳዳዋል። ይህ ሁኔታም ባንኮች ምክንያቶቹን በአስገዳጅነት እንዳይፈጽሟቸው ቀዳዳ የሚፈጥር እና ለትርጉም የተጋለጠ ያደርገዋል። ሌላው ነጥብ ደግሞ የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝ በንግድ ህገጉ ድንጋጌ መሰረት በምን ምክንያት ይሰጣል የሚለው ባልተገለጸበት ሁኔታ በመመሪያው ላይ ለማስቀመጥ መሞከሩ የንግድ ህጉ የሰጠውን እና በማናቸውም ምክንያቶች ይሁን የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ መስጠቱ ብቻ በቂ ነው የሚል የሚመስለውን ድንጋጌ የሚሽር አዋጅን በመመሪያ የመሻር ተግባር የሚያስመስል ነው የሚሉም አልጠፉም።

የቼክ ሂሳብ እንቅስቃሴን በተመለከተ

የቼክ ሂሳብ እንቅስቃሴ  በንግድ ህጋችን በዝርዝር ባልተቀመጡት ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ ባንክ በየጊዜው የቼክ እንቅስቃሴን የሚመለከቱ መመሪያዎችን ያወጣል። መመሪያዎቹ በተለይም የዘመናዊ ግብይት ስርዓቱ እየዘመነ እና ቀልጣፋ እየሆነ ሲመጣ  በሚመጡ አዲስ የአሰራርና የቼክ አጠቃቀም እንዲሁም በየጊዜው የቼክ ተፈላጊነትን ለማስፋፋት በማሰብ የሚወጡ እንደሆኑ መመሪያዎቹን በመመልከት መገመት አያዳግትም።

በቅርቡ በብሔራዊ ባንክ የወጣው የቼክ አጠቃቀም መመሪያ ቁጥር SBB/64/2016 መግቢያ በግልጽ እንደሚያመለክተውም ቼክን በመገበያያነት መጠቀም ጥሬ ገንዘብን የማይጠቀም ማህበረሰብ (Cashless Society) ለመፍጠርና ቀልጣፋ የግብይት ስርዓትን ለመገንባት አስፈላጊ በመሆኑ እንዲሁም ብሔራዊ ባንክም ቀልጣፋ፣ ውጤታማና የተረጋጋ የክፍያ ስርዓት የመዘርጋት ኋላፊነት ስላለበት ቼክን የተመለከተው መመሪያ ተሻሽሎ እነደወጣ ይጠቅሳል። ከዚህ በተጨማሪ ግን በዋናነት የቼክን ህጋዊ የመገበያያ ሰነድነት እና ተቀባይነት ያለው፣ እምነት የሚጣልበት ሰነድ ሆኖ እንዲቀጥል ማስቻል ለመመሪያው መሻሻል ምክንያት ነው።

በተሻሻለው መመሪያ መሰረትም በቀድሞው መመሪያ ውስጥ ያልተካተቱ ለምሳሌ የቼክ ሂሳብ ለመክፈት የሚያስፈልጉ  ነገሮች ምን ምን እንደሆኑ ከመዘርዘር አልፎ ቢያንስ በትንሹ የቼክ ሂሳብ የሚከፍተው ሰው የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር ያለው እንዲሆን ይጠበቃል በማለት አስቀምጧል። ከዚህ በፊትም የግብር መለያ ቁጥር ሳያመጡ የቼክ ሂሳብ የከፈቱ ሰዎችም መመሪያው በስራ ከዋለበት ስድስት ወራት ውስጥ ማቅረብ እንዳለባቸው ይገልጻል። መመሪያው በሌሎች ነጥቦች ላይም ዝርዝር ነጥቦችን የያዘ በመሆኑ ይህንኑ መመሪያ በማጣቀስ የተሻሻሉትን የቀድሞውን መመሪያ ድንጋጌዎች እንዲሁም አዲስ የተጨመሩ ነጥቦችን መመልከት ይቻላል።

በአጠቃላይ ግን ለዚህ ሁሉ ክርክር መፍትሄ የሚሆነው የንግድ ሕጉ ማሻሻያ ከተግባራዊው የባንኮች አሰራር፣ ከፍርድ ቤት ክርክር መነሻዎች እንዲሁም ከሌሎች አገሮች ልምድና ተሞክሮ በመነሳት ሰፊ ዳሰሳ በማድረግ ህጉ ምሉዕ እንዲሀን እንዲሁም በቼክ ላይ ያለው ተአማኒነት እንዲሰፋ የሚያደርግ የህግ ድንጋጌ ማውጣት ነው።

በአጠቃላይ ባንኮች የቼክን ክፍያ አልፈጽምም ሊሉ ከሚችሉበት ምክንያት ውስጥ አንዱ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ (Stop payment Order) በአውጪው ሲሰጥ ነው። አውጪውም መጀመሪያ ለባንኮች የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ ሲሰጥ ባንኮቹ ለዚሁ ትዕዛዝ ምክንያት የቼኩ መሰረቅ ወይም መጥፋት መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። በሌላ በኩል ባንኮች የቼክ አውጪ ግለሰቦቸ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ ሲሰጥ የተከፋዩ መብትም በዚህ ምክንያት እንዳይጣበብ መጠንቀቅ ይገባቸዋል። የቼክ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ (Stop payment order) በህጉ አግባብ የተሰጠ መሆኑ ከተረጋገጠ ባንኮች ደንበኞቻቸውን ከሂሳባቸው ላይ ያለአግባብ ወጪ እንዳይሆንባቸውና የደንበኞቻቸውን ተአማኒነት ለማግኘት በከፍተኛ ሁኔታ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በመሆኑም ባንኮች የቼክ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ የቼክ አውጪውንም ሆነ የተከፋዩን መብት የሚነካ መሆኑን በመገንዘብ ለደንበኞች ጥቅም ለማስከበር በህጉ አግባብ የቼክ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝን መተግበር ተገቢ ነው።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የልዩ ምርመራ ኦዲት ግኝቶችና የወንጀል ውጤታቸው
Ethiopia’s Accession to World Trade Organization (...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 12 October 2024