ሰበር ለመታረቅ በተደረገ ስምምነት ላይ የያዘው አቋም ሲፈተሽ

ኢትዮጵያ ውስጥ የዳኝነት ሥልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች ብቻ አይደሉም፡፡ ይህን ሥልጣን የተጎናፀፉ ብዙ አካላት አሉ፡፡ ለአብነት ያህል ለመጥቀስ፡- በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኘው የአስተዳደር ፍርድ ቤት ከሥራ መሰናበት፣ ደመወዝ መቁረጥና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች አስመልክቶ በመንግሥት ሠራተኛውና  በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት መካከል የሚነሳ አለመግባባት ላይ ዳኝነት ይሰጣል፡፡ ሕገ መንግሥቱን መተርጎም ላይ አለመግባባት ከተፈጠረ ዳኝነት የመስጠት ሥልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ በግብር ጉዳዮች ላይ የግብር ይግባኝ ሰሚ ኮሚሽን የዳኝነት ሥልጣን አለው፡፡ የማኅበራዊ ዋስትና መብትና ጥቅም  ጥያቄዎች ላይ የዳኝነት ሥልጣን ለማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ተሰጥቷል፡፡ የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሳ ጉዳዮች ላይ የዳኝነት ሥልጣኑ በየከተማ አስተዳደሮች ለሚቋቋሙ ጉባዔዎች ተሰጥቷል፡፡ የንግድ ውድድር ጨቋኝ የሆኑ ድርጊቶችና ያልተገባ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ደግሞ ዳኝነት የሚሰጥ የንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የሚባል ተቋም አለ፡፡ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶችም አሉ፡፡ ይሁን እንጂ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያለውን የዳኝነት ሥልጣን ያህል የተጎናፀፈ ፍርድ ሰጪ አካል ኢትዮጵያ ውስጥ የለም ለማለት ያስደፍራል፡፡ የዚህን ችሎት የዳኝነት ሥልጣን ሊወዳደር ወይም ሊበልጥ የሚችል ፍርድ ሰጪ አካል ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ፣ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ላይ ዳኝነት የመስጠት ሥልጣን ያለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ብቻ ነው፡፡

  9877 Hits