ሰበር ለመታረቅ በተደረገ ስምምነት ላይ የያዘው አቋም ሲፈተሽ

ኢትዮጵያ ውስጥ የዳኝነት ሥልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች ብቻ አይደሉም፡፡ ይህን ሥልጣን የተጎናፀፉ ብዙ አካላት አሉ፡፡ ለአብነት ያህል ለመጥቀስ፡- በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኘው የአስተዳደር ፍርድ ቤት ከሥራ መሰናበት፣ ደመወዝ መቁረጥና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች አስመልክቶ በመንግሥት ሠራተኛውና  በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት መካከል የሚነሳ አለመግባባት ላይ ዳኝነት ይሰጣል፡፡ ሕገ መንግሥቱን መተርጎም ላይ አለመግባባት ከተፈጠረ ዳኝነት የመስጠት ሥልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ በግብር ጉዳዮች ላይ የግብር ይግባኝ ሰሚ ኮሚሽን የዳኝነት ሥልጣን አለው፡፡ የማኅበራዊ ዋስትና መብትና ጥቅም  ጥያቄዎች ላይ የዳኝነት ሥልጣን ለማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ተሰጥቷል፡፡ የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሳ ጉዳዮች ላይ የዳኝነት ሥልጣኑ በየከተማ አስተዳደሮች ለሚቋቋሙ ጉባዔዎች ተሰጥቷል፡፡ የንግድ ውድድር ጨቋኝ የሆኑ ድርጊቶችና ያልተገባ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ደግሞ ዳኝነት የሚሰጥ የንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የሚባል ተቋም አለ፡፡ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶችም አሉ፡፡ ይሁን እንጂ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያለውን የዳኝነት ሥልጣን ያህል የተጎናፀፈ ፍርድ ሰጪ አካል ኢትዮጵያ ውስጥ የለም ለማለት ያስደፍራል፡፡ የዚህን ችሎት የዳኝነት ሥልጣን ሊወዳደር ወይም ሊበልጥ የሚችል ፍርድ ሰጪ አካል ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ፣ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ላይ ዳኝነት የመስጠት ሥልጣን ያለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ብቻ ነው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የዳኝነት ሥልጣን ያላቸው አካላትን በሙሉ የፍርድ ሰጪነት ሥልጣናቸውን ሲጠቀሙ መሠረታዊ የሕግ ስህተት አለመፈጸማቸውን ይቆጣጠራል፡፡ በተጨማሪ ይህ ችሎት አንድ የሕግ ድንጋጌን የተረዳበት ወይም የተረጎመበት መንገድ ሁሉም የሥር ፍርድ ቤቶች ሊከተሉ ይገባ ዘንድ ግዴታ አለ፡፡ ማለትም፣ ፍርድ ቤቶችና ሌሎች ፍርድ ሰጪ አካላት የሰበር ችሎቱ አንድን የሕግ ድንጋጌ ከተረጎመበት ውጪ አፈንግጠው የራሳቸውን ትርጉም መስጠት አይችሉም፡፡ ስለዚህ የሰበር ችሎቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ፍርድ ሰጪ አካላት ውስጥ ቁንጮ ላይ የሚቀመጥና የዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ሰፊ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነ ተቋም ነው፡፡

ሰፊ ሥልጣን ሲኖር ደግሞ ሊነጠል የማይችል አብሮ የሚመጣ ግዴታ አለ፡፡ ሰፊ ሥልጣን በጠለቀ ዕውቀት፣ ገደብ የለሽ አስተዋይነትና ሰባዊነት መታጀብ አለበት፡፡ የዜጎች ነፃነት፣ ሕይወትና ደስተኝነት ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር ሥልጣን የተሰጠው አካል ሁሉ ሥልጣኑን ሲጠቀም የመጠቀ ዕውቀት፣ የመተንተን ክህሎት፣ አስተዋይነትና ሰባዊነት በማይነጣጠል ሁኔታ ማንፀባረቅ አለበት፡፡ የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ሰፊ የዳኝነት ሥልጣን ቢጎናፀፍም የጠለቀ የሕግ ዕውቀት፣ ትንታኔ እና መርማሪነት ግን በውሳኔዎቹ ማንጸባረቅ የቻለ መስሎ አይታይም፡፡ ይህ ደግሞ በራሱ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ተገኔ ጌታነህ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ውሳኔዎች ይዞ በሚወጣው ቅጽ 15 መግቢያ ላይ ‹‹አልፎ አልፎ በውሳኔዎች ጥራትና ሥርጭት ሊታዩ የሚችሉ ችግሮች ሥርዓቱ እየተጠናከረ ሲሄድ የሚፈቱ ሲሆን፣ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል እኛም ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ጥረታችን ሊሳካ የሚችለው በውሳኔዎች ላይ በሕግ ምሁራንና ባለሙያዎች ገንቢ የሆኑ ትችቶችና አስተያየቶች ሲቀርቡ ነው፤›› ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ጽሑፌ አንድ ጭብጥን አስመልክቶ የሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ ሌላው ቀርቶ ጀማሪ የሕግ ተማሪዎች የሚማሩበት መጽሐፍ ላይ በቀላሉ የሚገኝ ዕውቀትን ማንፀባረቅ እንዳልቻለ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ ጭብጡን አስመልክቶ የዛሬ ስምንት ዓመት በብሔራዊ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያና በዘላቂ ግብርና ተሃድሶ ኮሚሽን ጉዳይ ላይ (የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች ቅጽ 7 ገጽ 148 ይመልከቱ) የሰጠውን ውሳኔ አሁን ደግሞ በቅርቡ በቦሮ ትራቭል የግንባታ ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና በአቶ ኤፍሬም ሽብሩ ጉዳይ ላይ ደግሞ ደግሞታል፡፡ (የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች ቅጽ 17 ገጽ 358 ጀምሮ ይመልከቱ)፡፡

ጭብጡ ምንድን ነው? ብዙ ጊዜ ሁለት ተዋዋዮች ውል ሲፈራረሙ ውሉን አስመልክቶ ክርክር ቢነሳ እንዴት ይፈታል የሚለውን የሚደነግግ አንቀጽ እንዲካተት ያደርጋል፡፡ ውሉ ውስጥ የሚካተተው አንቀጽ የሚከተለው ዓይነት መልዕክት ያዘለ ነው፡፡ ይኸውም «ውሉን አስመልክቶ ክርክር ቢነሳ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት በድርድር ወይም በዕርቅ ለመጨረስ ተስማምተናል፤» የሚል ነው፡፡ ይህ ስምምነት ቢኖርም አለመግባባት ሲፈጥር አንደኛው ተዋዋይ ጉዳዩን ቀጥታፍርድ ቤት ሊያቀርበው ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ ጉዳዩ የቀረበለት ፍርድ ቤት «ጉዳዩን አላይም በስምምነታችሁ መሠረት ክርክሩን ለድርድር ወይም ለዕርቅ አቅርቡት፤» ብሎ ሊመልስ ይችላልን?

የሰበር ችሎት ከላይ በጠቀስናቸው ጉዳዮች ላይ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ማየት የለበትም፤ ተከራካሪ ወገኖችን በስምምነታቸው መሠረት ድርድር ወይም ዕርቅ እንዲያደርጉ ፍርድ ቤቱ ሊመልሳቸው ይገባል ሲል ወስኗል፡፡ የሥር ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን በዕርቅ ወይም በድርድር ለመፍታት ስምምነት እያለ ያንን አልፈው አከራካሪው የፍሬ ነገር ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ በሚሰጡበት ጊዜም ሰበር ሰሚ ችሎት ይህን የመጨረሻ ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ተከራካሪ ወገኖችን እንደገና አለመግባባታቸውን ለመፍታት ድርድር ወይም ዕርቅ እንዲሞክሩ እያስገደደ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን የሰበር ችሎት አቋም የሚደግፍ ሕግ የለም፡፡ በተጨማሪ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ጊዜና ገንዘብ ላይ ከፍተኛ ብክነት የሚያሳድርና ድርድርና ዕርቅ የሚባሉትን የክርክር መፍቻ ዘዴዎች ተፈጥሮን ያላገናዘበ ስህተት ነው፡፡

አለመግባባትን በድርድር ወይም በዕርቅ ለመፍታት ስምምነት መኖር ፍርድ ቤቶችን ጉዳዩን ከማየት የሚገድብ ሕግ የለም

ለዚህ ጉዳይ አግባብነት ያለው ድንጋጌ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጋችንን አንቀጽ 244 (2) () ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ አንድ ፍርድ ቤት የቀረበለትን ጉዳይ አላይም ብሎ የሚመልሰው ጉዳዩ በሽምግልና ዳኝነት እንዲታይ ስምምነት (Arbitration agreement) ሲኖር ወይም ተከራካሪ ወገኖች በራሳቸው ተደራዳሪነት ወይም በሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት ክርክራቸው ላይ ተነጋግረው አለመግባባታቸው ላይ መፍትሔ ላይ በመድረስ የዕርቅ ስምምነት (Compromise) ወይም መሰል ግንኙነት ከፈጠሩ ብቻ ነው፡፡ በተለይ የፍርድ ሥነ ሥርዓት ሕጉ የእንግሊዝኛ ቅጅ ይህን በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ አለመግባባቱ ላይ መፍትሔ ለመፈለግ ድርድር (Negotiation) ወይም ዕርቅ (Conciliation) እንሞክራለን የሚል ስምምነት መኖር ግን ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ከማየት ይገድባቸዋል የሚል ሐሳብ በፍርድ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 245 (2) () ላይ የለም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ከታች () ላይ እንደምናብራራው ድርድርና ዕርቅ ተብለው የሚጠሩት የክርክር መፍቻ መንገዶች ተፈጥሮ ጋር የሚሄድ ስላልሆነ ነው፡፡ ተከራካሪ ወገኖች ተገደው እንዲደራደሩ ቢደረግ ወይም ለዕርቅ ቢቀርቡ አለመግባባታቸው ላይ መፍትሔ ሊገኝ አይችልም፡፡ ወይም በሌላ አነጋገር የዕርቅ ስምምነት (Compromise) ላይ ሊደርሱ አይችሉም፡፡

የሰበር ሰሚ ችሎት ብዙ ጊዜ ተከራካሪ ወገኖችን ጉዳያቸውን በድርድር ወይም በዕርቅ እንዲጨርሱ ከፍርድ ቤት አስወጥቶ የሚልካቸው የፍትሐ ብሔሩን አንቀጽ 1731 መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ውል በተዋዋይ ወገኖች መካከል ሕግ ስለሆነ ተዋዋይ ወገኖች ደግሞ ጉዳዩን ፍርድ ቤት ከማቅረባችን በፊት በድርድር ወይም በዕርቅ እንጨርሳለን ብለው ስለተስማሙ በሚል ሰበር ሰሚ ችሎት ተከራካሪ ወገኖች ጉዳያቸው ላይ የሥር ፍርድ ቤት ፍርድ የሰጠ ቢሆንም እንኳ፣ ፍርዱን ወደ ጎን እያደረገ ወደ ድርድርና ዕርቅ እንዲሄዱ እያስገደደ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ የውል ሕግ ራሱ አንድ ውል የጣሰ ሰው ውሉ ላይ የተጠቀሰውን ድርጊት በማናቸውም ሁኔታ ተገዶ እንዲፈጽም አይፈቅድም፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ስምምነቱን ቢሰጥም በግድ የድርድር ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀመጥ ወይም አስታራቂዎች (Conciliators) ፊት ቀርበህ ተደራደር ተብሎ መገደድ የለበትም፡፡ ይልቅ ስምምነቱን ስለጣሰ ካሳ እንዲከፍል መደረግ ነው ያለበት፡፡ ከታች እንደምናየው ተገዶ ቢቀርብም ፍቃደኝነቱና ፍላጎቱ እስከሌለ ድረስ የድርድሩ ወይም የእርቁ ሒደት ምንም ውጤት አያመጣም፡፡

የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ የድርድርና የዕርቅን ተፈጥሮ ያላገናዘበ ነው

ድርድር (Negotiation) ሁለት ተከራካሪ ወገኖች በመነጋገር ያልተግባቡበት ነጥብ ላይ በሁለቱም በኩል ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ለማግኘት የሚጥሩበት መንገድ ነው፡፡ በሁለቱም በኩል ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ከተገኘ ድርድሩ ‹‹የዕርቅ ስምምነት›› (Compromise) ማስገኘት ችሏል ማለት ነው፡፡ ድርድሩ የተሳካ ነው ማለት ነው፡፡ ዕርቅ (Conciliation)  ደግሞ ያው እንደ ድርድር ሲሆን፣ ልዩነቱ በዕርቅ ጊዜ በተከራካሪ ወገኖች መካከል የሚደረገውን ድርድር የሚያግዝ ሦስተኛ ወገን ከተከራካሪዎች በተጨማሪ መኖሩ ነው፡፡ ይህ ሦስተኛ ወገን አስታራቂ  (Conciliator) ይባላል፡፡ አስታራቂው እገዛውን የሚያደርገው የክርክሩን ጭብጥ በመለየት፣ ተከራካሪዎች የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያፈልቁ በመርዳት ወይም ራሱ መፍትሔ የሚለውን በመጠቆም ሊሆን ይችላል፡፡ አስታራቂ የራሱን መፍትሔ ያቀርባል እንጂ በተከራካሪ ወገኖች ላይ ውሳኔውን አይጭንም፡፡ የአስታራቂው የመፍትሔ ሐሳብ ላይ ሁለቱም ተከራካሪዎች በጽሑፍ ስምምነታቸውን ካልገለጹ በቀር በመፍትሔ ሐሳቡ ተከራካሪ ወገኖች ሊገደዱ አይችሉም፡፡ ስለዚህ የድርድርና የዕርቅ ሒደት (Process) እና ውጤት (Outcome) በተከራካሪ ወገኖች ሙሉ ትብብርና ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሰበር ሰሚ ችሎት አንድን ተከራካሪ ወገን ጉዳዩን ከፍርድ ቤት እንዲወጣ በማድረግ በድርድር ወይም በዕርቅ ጨርስ ብሎ ማስገደዱ አሳዛኝ ክስተት ያደርገዋል፡፡ ያለሁለቱም ተከራካሪዎች ሙሉ ፈቃድ ድርድር ወይም ዕርቅ ውጤት አያመጣም፡፡ ስለዚህ ትክክለኛው መንገድ ‹‹ክርክር ሲነሳ ጉዳዩን ለድርድር ወይም ለዕርቅ በማቅረብ ለመጨረስ ተስማምቻለሁ፤›› ብሎ የተስማማን ተከራካሪ ወገን ይህን ስምምነቱን ጥሶ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ይዞ ሲመጣ ለዕርቅ ወይም ለድርድር ዝግጁ ለሆነው ወገን ካሳ እንዲከፍል ማድረግ እንጂ ከፍርድ ቤት ጉዳዩን እንዲያወጣ ማስገደድ ስህተት ነው፡፡ ከድርድርና ዕርቅ ተፈጥሮ ጋር አይጣጣምም፡፡

የሰበር ሰሚ ችሎት ተከራካሪ ወገኖችን ለገንዘብና ለጊዜ ብክነትና ለስሜት መጎዳት የሚዳርግ ነው፡፡

ከላይ () እንደተመለከትነው ክርክር ሲነሳ ጉዳዩን ለድርድር ወይም ለዕርቅ ለማቅረብና ለመጨረስ የሚደረግ ስምምነት ክርክሩን በቀጥታበፍርድ ቤት ከመታየት አይገድብም፡፡ ጉዳዩን በቀጥታ ለፍርድ ቤት ማቅረብ የውል ጥሰት ቢሆንም መፍትሔው ካሳ እንዲከፈል ማድረግ ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 244 (2) () እንዲህ ዓይነት ስምምነት ጉዳዩን ከፍርድ ቤት ለማስወጣት ምክንያት ይሆናል አይልም፡፡ በአጠቃላይ አንድን ተከራካሪ እንዲደራደር ወይም ለዕርቅ እንዲቀርብ ማስገደድ የሕግ መሠረት የለውም፡፡ ቀደም ሲል ይህን ፈቃዱን የሰጠ ቢሆን እንኳ፡፡ በተጨማሪ ይህን ማድረግ ከድርድርና ከዕርቅ ጽንሰ ሐሳብ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡  ምክንያቱም የድርድርና የዕርቅ ጽንሰ ሐሳብ መሠረቱ የተከራካሪ ወገኖች መፍትሔ ላይ ለመድረስ ጽኑ ፍላጉትና ፍቃደኝነት ነው፡፡

ለመደራደር ወይም ለመታረቅ ተስማምተናል የሚል የውል ድንጋጌ እያለ በቀጥታክርክሩ ለፍርድ ቤት ሲቀርብ ክርክሩ ለድርድር ወይም ለዕርቅ ይመለስ ዘንድ የሚያስገድድ ሕግ አለ ብለን ብናስብ እንኳ፤ የሰበር ችሎቱ አቋም ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ ጉዳዩን መርምረው ማስረጃ ሰምተው የሥር ፍርድ ቤቶች የመጨረሻ ውሳኔ ከሰጡ በኋላ ይህን ውሳኔ በመሻር የሰበር ችሎቱ ተከራካሪ ወገኖች አለመግባባታቸውን ለድርድር ወይም ለዕርቅ እንደ አዲስ እንዲያቀርቡ ማዘዙ የሚጠቅመው አንዳች ነገር የለም፡፡ ከጊዜ፣ ከገንዘብ፣ ከተከራካሪ ወገኖች ሰሜትና ከፍትሕ አንፃር ስናየው እጅግ አሰከፊ ገጽታያለው ነው፡፡ በምሳሌ እንየው፡-

ሁለት ሰዎች የመኪና ሽያጭ ውል ገቡ፡፡ ይህን ውል አስመልከቶ አለመግባባት ቢፈጠር ፍርድ ቤት ከመሄዳቸው በፊት አለመግባባቱን በዕርቅ ለመጨረስ ተስማሙ እንበል፡፡ ከጊዜ በኋላ ገዥ መኪናው ጉድለት እንዳለበት ስለተረዳ ካሳ ብር 50,000 ሻጭ ይክፈለኝ ሲል ዕርቅ ሳይሞክር ቀጥታየመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውስጥ ክስ ይከፍታል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለዕርቅ የማቅረብ ስምምነት ቢኖርም እርሱን ወደ ጎን በመተው የፍሬ ነገር ጉዳዩ ላይ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ ለገዥ ካሳ ሻጭ ብር 50,000 እንዲከፍል ይወስናል፡፡ በዚህ ጊዜ ሻጭ ይግባኝ ያቀርባል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ያፀናል፡፡ ከዚህ በኋላ ይህ ጉዳይ ለሰበር ችሎት ይቀርባል፡፡ በዚህን ጊዜ የሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩ በዕርቅ ለመጨረስ መሞከር ስለነበረበት በሚል የሥር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔዎች ወደ ጎን በመተው ተከራካሪ ወገኖች በዕርቅ ጉዳዩን እንዲፈቱ ይወስናል፡፡ ይህን ማድረግ ግን ስህተት ነው፡፡

እዚህ ላይ መጤን ያለባቸው ዋና ጉዳዩች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ በሥር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ መዛባት ያለበት አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህን ውሳኔ አሽቀንጥሮ መጣል ተገቢ አይሆንም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተከራካሪ ወገኖች ወደ ዕርቅ መራናቸው ማለት የግድ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ይገደዳሉ ወይም ሊደርሱ ይችላሉ ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሻጭና ገዥ በፍርድ ቤት ያለቀውን ጉዳይ እንደገና «» ብለው እንዲጀምሩ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የዕርቁ ሒደት ካልተሳካ  (ብዙ ጊዜ አይሳካም ምክንያቱም የፍርድ ቤት ሒደቱ በተከራካሪዎች መካከል ያለውን ግንኙነት የማሻከር ውጤት ስላለው) እንደገና ሻጭ ክሱን ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያቀርብና ከላይ የተጠቀሰውን ሒደት ይደግማል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ ዕርቅና ድርድር ለክርክር መፈቻነት የሚመረጡበት መንገድ ክርክርን በቀላል ወጪ፣ በሚስጥር፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት ቢሆንም የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች ግን ይህን ዓላማ እንዲለቁ አድርጓቸዋል፡፡ በፍርድ ያለቀን ጉዳይ እንደገና ወደ ድርድር ወይም ዕርቅ መምራት ገንዘብም፣ ጊዜም ሚስጥራዊነትንና ሌሎች ጥቅሞችን አያስገኝም፡፡ እንዲያውም ተከራካሪ ወገኖችን ለተጨማሪ የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የጉልበት ብክነትና ስሜት መጉዳት የሚያጋልጥ ነወ፡፡

ማጠቃለያ

አለመግባባት ሲፈጠር አለመግባባቱን ለመፍታት ድርድር ወይም ዕርቅ በመጀመሪያ መሞከር አለበት ብለው ተከራካሪዎች ከተስማሙ ውጤቱ መሆን ያለበት ይህን ስምምነት ጥሶ ቀጥታክስ ፍርድ ቤት ያመጣ ወገን ካሳ እንዲከፍል ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ያለ ሁለቱ ተከራካሪዎች ፍላጎት ክርክሩን ከፍርድ ቤት ወጥቶ ወደ ድርድር ወይም ዕርቅ ይመራ የሚል ሕግ የለም፡፡ ቢኖርም አይሠራም፡፡ ምክንያቱም ድርድርና ዕርቅ ፍሬ ሊያስገኙ የሚችሉት ሁለቱ ተከራካሪዎች መተማመን ፈጥረው በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው ክርክራቸውን የሚፈቱበት መንገድን ፈጠራ በተሞላበት መንገድ ሲፈትሹ ነው፡፡ በመጨረሻም በሁሉም ተከራካሪ ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ሲገኝ ነው፡፡ ይህ ፍላጎት የሌላቸውን ተከራካሪዎች አንድ ክፍል ውስጥ አስገብቶ ተደራደሩና የጋራ ስምምነት ላይ ድረሱ ብሎ ማስገደድ አይቻልም፡፡ ይህንን መሞከር ውጤት ለሌለው ነገር ተከራካሪዎችን ለጊዜ፣ ለገንዘብ ብክነትና እንግልት መዳረግ ነው፡፡

ትክክለኛው መንገድ በድርድር ወይም በዕርቅ እጨርሳለሁ ብሎ ከተስማማ በኋላ ያለ በቂ ምክንያት በቀጥታ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ያመጣውን ወገን ካሳ እንዲከፍል ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ላቅ ያለ የሕግ ዕውቀትና ምርምር እንዲሁም ትንተና ሊያንፀባርቁ ይገባቸዋል የምንላቸው የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች ተከራካሪ ወገኖችን ያለአግባብ ከፍርድ ቤት ተገፍትረው እንዲወጡ የሚያደርጉና ያለፈቃዳቸው ውጤት አልባ የሆነ ድርድር ወይም ዕርቅ ውስጥ እንዲቸነከሩ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የሰበር ውሳኔዎች ለብዙ ዓመታት በፍርድ ቤት ሲታዩ የነበሩ ጉዳዮችን እልባት ካገኙ በኋላ  እንደገና ወደኋላ በመመለስ በዕርቅ ወይም ድርድር እንዲታዩና ዕርቁ ወይም ድርድሩ ሳይሳካ ሲቀር በፊት የተቀለበሰው የፍርድ ቤት ሒደቱ ‹‹›› ብሎ ከዜሮ እንዲጀምርና እንዲደገም በማድረግ የገንዘብ፣ የጊዜ ብክነትና የተከራካሪዎችን ስሜት የሚጎዳ ሁኔታ ፈጥረው ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይህን ሁኔታ በፍጥነት ያስተካክላል ስንል ተስፋ እናደርጋለን፡፡

{advpoll id='5' view_result='0' width='0' position='center'}

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በኢትዮጵያ አሠሪና ሠራተኛ ሕግ የሥራ ስንብት ክፍያ ምንነትና የሚስተዋሉ አንዳን...
የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ከአዲስ አበባ ምን ሊሆን ይችላል
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 28 March 2024