Font size: +
4 minutes reading time (896 words)

የግልግል ስምምነት /Arbitration Agreement/ እና የፍርድ ቤቶች ሥልጣን

ከረጅም ጊዜ በኋላ ይህንን የጻፍኩት በቅርቡ ባነበብኩትና ሰበር የግልግል ስምምነትና የፍርድ ቤቶች ሥልጣንን አስመልክቶ በሰጠው ውሳኔ ላይ የተወሰነ ሐሳብ መስጠት ስለፈለኩ ነው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ብቻ የሚጠቅመኝን የውሳኔ ክፍል በማውጣት እጠቀማለሁ እንጂ ሁሉንም ፍሬ ሐሳብ አልዳስስም ነገር ግን ማንበብ ለሚፈልግ ሰው ውሳኔው ያለበት ቅጽና መዝገብ ቁጥር አስቀምጣለሁ (ቅጽ 25 መ.ቁ 180793)፡፡

በውሳኔው ሐተታ ላይ ‹‹…ይህ መርህ የግልግል ዳኛው የግልግል ዳኝነት ስምምነቱ ዋጋ ያለው መሆን አለመሆኑን በተመለከተ የሚነሳ ክርክር ጭምር ሰምቶ መወሰን እንዲችል ሥልጣን የሚሰጠው ቢሆንም ይህ መርህ… በአገራችን በከፊል ተቀባይነት ባለማግኘቱ በዚህ ድንጋጌ መሠረት በአገራችን የግልግል ዳኛ የግልግል ዳኝነት ስምምነቱ ዋጋ የለውም በሚል የሚነሳ ክርክር በራሱ ሰምቶ መወሰን እንዲችል ሥልጣን አልተሰጠውም፡፡ ስለሆነም በአገራችን የግልግል ዳኝነት ስምምነት ዋጋ የለውም በሚል የሚቀርብ ክርክር ሰምቶ የመወሰን ሥልጣን ያለው ገላጋይ ዳኛው ወይም የግልግል ዳኝነት አካሉ ሳይሆን መደበኛ ፍ/ቤት ነው›› የሚል መደምደሚያ አስቀምጧል፡፡ ከዚህ የውሳኔ ክፍል መረዳት እንደምንችለው አንዱ ወገን የግልግል ዳኝነት ስምምነቱ ሕጋዊ መሆን አለመሆኑ መረጋገጥ ያለበት በግልግል ጉባዔው ነው ሲል ተቃራኒው ደግሞ የግልግል ስምምነቱ ሕጋዊነት ላይ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣንያለው ፍርድ ቤት ነው የሚል ክርክር ይዞ እንደቀረበ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

ይህ ውሳኔ መሠረት ያደረገው የፍ/ብ/ሕ/ቁ 3330/3/ን ሲሆን የተጠቀሰው አንቀጽ የዘመድ ዳኛው በማንኛውም ሰዓት የዘመድ ዳኛው ስምምነት ዋጋ ያለው ወይም የሌለው ነው ብሎ በሥልጣኑ ሊወስን አይችልም የሚል ነው፡፡ አንባቢ ልብ እንዲል የምፈልገው በቀጣይ ክፍል ይህንን ውሳኔ ከአዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንጻር የምፈትሸው መሆኑን ነው፡፡

ሰዎች ውል ሲዋዋሉ አለመግባባት ቢፈጠር በፍርድ ቤት ወይም ከፍርድ ቤት ውጪ ባሉ አማራጭ የሙግት መፍቻ መንገዶች ለመፍታት ሊስማሙ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ መፍቻ መንገዶች ደግሞ አንዱ የግልግል ዳኝነት ነው፡፡ የግልግል ዳኝነት ስምምነት የሚጸናው በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ሲያገኝ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ማለትም ውሉን ሲዋዋሉ አንዱ ፍርድ ቤት ለመሄድ እየፈለገ ሌላው ደግሞ ጉዳዬን በግልግል ዳኝነት መፍታት እፈልጋለሁ ቢል ከጅምሩም የግልግል ስምምነቱ የሚፈረም አይሆንም፡፡ ሌላው ሊሠመርበት የሚገባው ነጥብ ሰዎች ውሉን ሲፈርሙ ወይም አለመግባባቱ ከተከሰተ በኋላ ጉዳያቸውን በግልግል ለመጨረስ ሊስማሙ ይችላሉ፡፡ በሁለቱም ጊዜያት ግን ጉዳዩን ወደ ግልግል ለመውሰድ ፈቃዳቸውን መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

አንባቢ ግን እንዲገነዘብ የሚያስፈልገው ዋና ነጥብ ስለ ፍርድ ቤትም ሆነ ስለ ግልግል ዳኝነት ለማውራት በቅድሚያ አለመግባባት መኖር እንዳለበት ነው፡፡ አለመግባባት ከሌለ ስለ መፍቻ መንገዱ መነጋገር አላስፈላጊ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች የተቋቋሙት በሕግ ሲሆን የግልግል ዳኝነት ጉባዔ ግን ሥልጣኑን የሚያገኘው በውል ነው፡፡ የግልግል ውል በውስጡ በርካታ ፍሬ ነገሮችን ሊይዝ ይችላል፡፡ ስለ ግልግል ዳኞች ብዛት፣ ጉዳዩ ስለሚመራበት ሕግ፣ ግልግሉ ተቋማዊ ስለመሆን አለመሆኑ፣ ተቋማዊ ከሆነ የተመረጠው ተቋም፣ ስለ ቋንቋ፣ ስለ ይግባኝ መብት፣ የግልግል ጉባዔው መቀመጫ ስለሚያደርገው ቦታ/አገር ይካተታሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም ተዋዋዮች የግልግል ውሳኔው እንዲሰጣቸው የሚፈልጉበት ጊዜ (ለምሳሌ በ3 ወር፣ በ6ወር) ወይም የግልግል ጉባዔው ውሳኔ እንዲሰጥበት የሚፈለገው ጭብጥ ተለይቶ ሊቀመጥ ይችላል፡፡ በተለይ ዓለም ዓቀፍ የግልግል ዳኝነት ስምምነት ከሆነ ከዚህ የሰፉ ሐሳቦችን ሊያካትት እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ውሎች ውስጥ እንደሚታየው በአጻጻፍ ስህተት ምክንያት ብዙ ችግሮች ሲደርሱ ይስተዋላሉ፡፡ የመጀመርያው ችግር የግልግል ዳኝነት ትርጉም/ምንነትን ካለመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡

ተዋዋዮች አለመግባባትን ስለመፍታት የሚል አንቀጽ ያስቀምጡና ጉዳዩ በግልግል እንዲያልቅ ይፈራረማሉ፡፡ አለመግባባቱ ሲፈጠር ግን እኔ እንደዚህ መሆኑን ባውቅ ኖሮ አልዋዋልም የሚል ሐሳብ ይንጸባረቃል፡፡ የግልግል ዳኝነት ከሚያስወጣው ወጪ አንጻር ፍ/ቤት ይሻለኝ ነበር ብሎ የሚናገር ሰው መስማት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ እንደምሳሌ ለመጥቀስ በበርካታ ውሎች ላይ ‹‹ተዋዋዮች አለመግባባታቸውን በግልግል ይፈታሉ…›› የሚል ድፍንፍን ያለ ነገር ተቀምጦ መመልከት አዲስ አይደለም፡፡ ከግልግል ስምምነት አቀራረጽ አንጻር ይህንን ስንመለከተው ብዙ ክፍተት ያለበትና ለትርጉም የተጋለጠ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በአንዳንድ ውሎች ደግሞ ‹‹…ተዋዋዮች አለመግባባታውን በሽምግልና ይፈታሉ… እያንዳንዱ ወገን አንድ አንድ ገላጋይ ይመርጣል፤ ሁለቱ ደግሞ አንድ የመሐል ገላጋይ ዳኛ ይመርጣሉ…›› የሚል እንመለከታለን፡፡ ይህ ስምምነት ደግሞ ስለ ግልግል ዳኞች ብዛት እንጂ ሌላ የሚያመለክተው ነገር ስለማይኖር ለአፈጻጸም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ የስያሜ ችግሩ አንደኛው ነው፤ ይኸውም በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት Arbitration ግልግል ተብሎ ተተርጉሟል በአንጻሩ Mediation ስምምነት ሲሆን Conciliation ማስታረቅ የሚል ፍቺ አለው፡፡ ሽምግልና እንደዚህ ነው የሚል ቁርጥ ያለ ስያሜ የሌለው ሲሆን ከባሕሪው በመነሳት ግን ማስማማት ወይም ማስታረቅ ነው ማለት እንችላለን፡፡ በአንዳንድ የግልግል ስምምነቶች ደግሞ ጉዳዩ ተቋማዊ ይሁን ተቋም አልባ የማይለይበት አለ ‹‹… ተዋዋዮች አለመግባባታቸውን በግልግል ይፈታሉ ለዚህ ተፈጻሚ የሚሆነው ሕግ (የተመረጠው ተቋም ሕግ ተጽፎ) ነው›› በማለት ይደመድማል፡፡  በአጠቃላይ የግልግል ዳኝነት ጉባዔ ሥልጣን የሚመነጨው ከግልግል ስምምነቱ እስከሆነ ድረስ ስምምነቱ በአግባቡ መጻፍ ይኖርበታል፡፡

በግልግል ዳኝነት ከሚታወቁ ጽንሰ ሐሳቦች አንዱ የግልግል ጉባዔው ሥልጣን አለኝ የለኝም የሚለውን ጉዳይ በራሱ መወሰን ይችላል (the theory of competence-competence) የሚባለው ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ ይህ ጽንሰ ሐሳብ ዓለም ዓቀፋዊ ሲሆን በዋነኛነትም የግልግል ጉባዔያት የፍርድ ቤት እገዛ ሳያሻቸው እንዲዳኙ የቀረበላቸውን ጉዳይ ተመልክተው ሥልጣን እንዳላቸው ወይም እንደሌላቸው መወሰን ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ሌላኛው በሰፊው ተቀባይነት ያገኘ መርህ ደግሞ የግልግል ስምምነቱና ዋናው ውል የተለያዩ ናቸው (the theory of separability) የሚለው ነው፡፡ ይህም አንድ ውል ፈራሽ መሆኑ የግልግል ስምምነቱ ፈራሽ እንዲሆን አያደርገውም እንደማለት ነው፡፡ 

በአዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀጽ 19/1/ ሥር በግልጽ ተቀምጦ ይገኛል ‹‹በተዋዋይ ወገኖች መካከል የጸና የግልግል ዳኝነት ስምምነት መኖር አለመኖርን ጨምሮ ጉዳዩን የማየት ሥልጣን አለኝ ወይም የለኝም በሚለው ላይ ጉባዔው የመወሰን ሥልጣን አለው…››፡፡ በፍትሐብሔር ሕጉም ቢሆን በአንቀጽ 3330/2/ ሥር ‹‹በተለይም የራሱን ሥልጣን የሚመለከቱትን ክርክሮችን በሥልጣኑ እንዲወስን ለዘመድ ዳኛው ሊፈቀድለት ይችላል›› ይላል፡፡ የግልግል ስምምቱና ዋናው ውል መካከል ስላለው ግንኙነት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀጽ 19/1/ን መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡      

ከእነዚህ ድንጋጌዎች የምንረዳው የግልግል ጉባዔው ያለው ሥልጣን በቀድሞውም ሆነ በአዲሱ ሕግ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ነው፡፡ ይህ ከሆነ ታዲያ ሰበር በምን አግባብ ሥልጣኑን ለፍርድ ቤቶች ሰጠ? ምንም እንኳን ውሳኔው የተሰጠው በተሻረ ሕግ ቢሆንም የሕጉ አተረጓጎም የዳበረ የግልግል ዳኝነት ሕግና አሠራር በሌላቸው አገሮች ሁልጊዜ በፍርድ ቤቶችና በግልግል ጉባዔያት መካከል ሥልጣንን በተመለከተ ክርክር ሲፈጠር መመልከት አዲስ አይደለም፡፡ ፍርድ ቤቶች በሕገ መንግሥት የተመሠረቱ ተቋማት እንደመሆናቸው መጠን ይህንኑ ማስረጽ የሚፈልጉ ሲሆን በአንጻሩ ተዋዋዮች ደግሞ የመዋዋል ነጻነታቸው እንዲከበርላቸው ይፈልጋሉ፡፡

የግልግል ጉባዔ ሥልጣኑ የሚያገኘው በውል መሠረት ከሆነና የግልግል ውሉ ሕጋዊ ነው አይደለም የሚለው ጉዳይ መሠረታዊ ከሆነ በምንም መልኩ ፍ/ቤቶች ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ለመወሰን ሥልጣን ሊኖራቸው አይገባም፡፡ ከዚህ አንጻር የግልግል ዳኝነት አዋጁ አንቀጽ 19 ዘመናዊ የሆነውን ጽንሰ ሐሳብ ለማካተት መሞከሩ የሚደነቅ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም በአዋጅ ቁጥር 1237/2013 መሠረት የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የግልግል ጉባዔው ሥልጣኑን በራሱ የመወሰን መብቱን በተመለከተ የሚሰጠው ትርጉም እንደተጠበቀ ሆኖ በበኩሌ ግን ሁልጊዜም ቢሆን የግልግል ጉባዔያት በራሳቸው የሚቆሙና የሚሠሩ /autonomous/ ሊሆኑ ይገባል፡፡  

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን - የሴቶች ጥቃት ችግር - ሴቶች
ስለባልና ሚስት የጋራ እና የግል ንብረቶች በተመለከተ የፌዴራሉን የቤተሰብ ሕግና...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 12 October 2024