የሕዝብ ተሳትፎ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለው ሚና

ቀደም ባሉት ጊዜያት የፍትሕ ሥርዓት ቅቡልነት እና የሕዝብ አመኔታ መሠረት ተደርገው የሚወሰዱት ቢሮክራሲ፣ ምክንያታዊነት እና ሞያን መሠረት ማድረግ ነበር፡፡ በመሆኑም በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ዋና ተዋናዮች የሕግ ባለሞያዎች እና ሌሎች የፍትሕ አካላት ባለሞያዎች ሲሆኑ፣ ሌሎች ማህበረሰብ አካላትን ያገለለ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ስለሆነም መንግሥት እና የሕግ ሰዎች ፍትሕ የማስፈን ሀላፊነትን በብቸኝነት በመያዝ አባታዊ የአስተዳደር ዘዴ (Paternalistic Approach) ሲከተሉ ነበር፡፡ የዚህም አጠቃላይ አሠራር ሁሉን ነገር ለባለሙያ የመተው (Leave to the professional) የምንለው ነው፡፡ ይህም የወንጀል ተጠቂዎችን እና ባለጉዳዮችን እንዲረሱ በማድረግ ኒልስ ክሪስቲ እንደተባሉ አንድ ፀሐፊ አባባል “የራሳቸውን ጉዳይ በባለሙያዎች ተሰርቀዋል”፡፡

የዚህ አይነት አሠራር ሁሉም ችግር የሚፈታው በባለሙያ ነው የሚል አመለካከት ህብረተሰቡ እንዲያዳብር አድርጓል፡፡ ነገር ግን ማህበሰቡ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ በተለያየ ደረጃ የሚኖራቸው ተሳትፎ ወሳኝ እና ቁልፍ ባለድርሻ መሆኑ እውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡ በዚህ ጽሑፍም የማህበረሰብ ተሳትፎ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡

2. የማህበረሰብ ተሳትፎ መነሻ ጽንሰ ሐሳብ

ሕዝባዊ አገልግሎት ውጤታማ የሚሆነው የተገልጋዩ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ንቁ ተሳትፎ ሲኖር እና ተሳትፎአቸው ወሳኝ እንደሆነ ሲሰማቸው ነው የሚለው መርህ የማህበሰብ ተሳትፎ መሠረት ነው፡፡

3. የማህበረሰብ እና ማህበረሰብ ተሳትፎ ትርጓሜ

3.1. የማህበረሰብ ተሳትፎ ትርጓሜ

በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው እና ያገባናል የሚሉ የማህበረሰብ አካላት በሥርዓቱ በተለያዩ ሂደቶች እና ደረጃዎች ከመረጃ መስጠት እና መቀበል እስከ ውሳኔ ሰጭነት እና አስፈፃሚነት ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበት ሁኔታ ነው፡፡

3.2. የማህበረሰብ ትርጓሜ

ማህበረሰብ ማለት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን ማለትም በአሉታዊም ሆነ በአውንታዊ መልኩ ተጽእኖ የሚያሳድርባቸውን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ባለድርሻ አካላትንም ይጨምራል፡፡ ማህበረሰብ በብዙ መልኩ ይገለፃል፡፡ ከነዚህ መካከል፡-

በአንድ በተወሰነ ጂኦግራፊያዊ አካባቢ የሚኖሩ፤

የጋራ የሆኑ መገለጫዎች ወይም ሌላ የጋራ ባህሪ ያላቸው (ለምሳሌ፡- ፆታ፣ እድሜ፣ ብሔር፣ አካል ጉዳት፣ ሀይማኖት ወ.ዘ.ተ.)

ተመሳሳይ ጥቅም፣ ልምድ ወይንም ምክንያት ያላቸው (ለምሳሌ፡- የወንጀል ተጠቂያች፣ የቀድሞ ጥፋተኞች ወ.ዘ.ተ.)

4. ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚመለከቱ ሕጎች

4.1. አለም አቀፍ ስምምነቶች

በርካታ አለም አቀፍ እና አህጉራዊ ስምምነቶች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ ተሳትፎ መኖር እንደሚገባው ይደነግጋሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በሰብአዊ መብት ዘርፍ ተጠቃሽ የሆኑት የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ (UDHR) እና የአለም አቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች የቃልኪዳን ስምምነት (ICCPR) ለማህበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ የሆነውን የመረጃ ነኀነት መብትን ከማረጋገት በዘለለ የመሳተፍ መብትን እንደ አንድ መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡ በተጨማሪም የ1993 የቬና ሰብዓዊ መብት ድንጋጌ የዲሞክራሲ፣ ልማት፣ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን እና በተለይም ዲሞክራሲ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ የዜጎችን ሙሉ ተሳትፎ ያረጋገጠ መሆን እንደለበት ያስቀምጣል፡፡

እንዲሁም በርካታ የአለም አቀፍ እና አህጉራዊ የአካባቢ ጥበቃ ስምምነቶች ሕዝባዊ ተሳትፎ ለአካባቢያዊ ፍትሕ እና ውጤታማ አካባቢ ጥበቃ መሆኑን አጽንኦት ይሰጡታል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የ1992 የሪዮ ድንጋጌ በመርህ 10 ላይ የሕዝብ ተሳትፎ ለአካባቢያዊ ደህንነት እና ፍትሕ አስፈላጊ መሆኑን በግልፅ ያስቀምጣል፡፡

4.2. ሀገራዊ ሕጎች

የኢ.ፌ.ዴ.ሬ. ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 42(2) ላይ የዜጎችን በተናጠልም ሆነ በጋራ ያላቸውን የመሳተፍ መብት

“ዜጎች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ በተለይም አካል የሆኑበትን ማህበረሰብ የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ፕሮጀተቶች ላይ ሃሳባቸውን እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት አላቸው::”

በማለት ይደነግጋል፡፡ በአንቀጽ (29(3) ላይ የተሳትፎ አንድ ሁኔታና ለተጨማሪ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ የሆነውን መረጃ የማግኘት መብትን አረጋግጧል፡፡ ዝርዝር አፈፃፀሙ በመገናኛ ብዙኋንን የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 ላይ ተደንግጓል፡፡ ከሁሉም በላይ አንቀጽ 8 ላይ “የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሀገሪቱ ሉአላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸውንና ይሄንንም በሚመርጧቸው ተወካዮች እና በቀጥታ በሚያደርጉት ተሳትፎ እንደሚገልፁ ያስቀምጣል፡፡ አንቀጽ 12 በመንግሥት አሠራር ላይ ግልፀኝነትና የተጠያቂነትን መርህ መሰረታዊነት ያስቀምጣል፡፡ በመጨረሻም በአንቀፅ 13 ላይ ከላይ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች የማስፈፀም ግዴታ

“በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌዴራል መንግሥትና የክልል ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና የዳኝነት አካሎች በዚህ ምዕራፍ የተካተቱትን ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡”

በማለትያስቀምጣል፡፡

ህገ-መንግስቱን መሰርት አድርገው የወጡ ሌሎች ፖሊሲዎችና ሕጎች አብዛኛዎቹ በተለያዩ ዘርፎች እና ደረጃዎች የሕዝብን አሳታፊ የሆነ አሠራር እና ውሳኔ ሰጭነት እንዲኖር ያስገድዳሉ፡፡

5. የማህበረሰብ ተሳትፎ አይነቶችና ደረጃዎች

የማህበረሰብ ተሳትፎ አይነቶች በርካታ ሲሆኑ በዋናነት በሚከተሉት አምስት ደረጃዎች ይቀመጣሉ፡፡

መረጃ ማግኘት (Informative)፡- የመረጃ ልውውጥ እና ግብረ-መልስ ቻናሎች መኖር አንዱ አይነት የማህበረሰብ ተሳትፎ እና ለሌሎች አይነት ተሳትፎዎች ውጤታማነት ወሳኝ ነው፡፡ ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለቸው እውቀት፣ አመለካከት እና አመኔታ ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፡፡ መረጃ ለአመኔታ መጐልበት ወሳኝ ነው፡፡ እንግሊዝ ሀገር የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ውጤታማ የሆነ የኮሙኒኬሽን ሥራ አንድ ሰው ስለ ወንጀል ያለው አመለካከት ላይ ጉልህ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ ሰዎች ኢ-መደበኛ ካልሆኑ መንገዶች በሚያገኙአቸው የተዛቡ መረጃዎች የተነሳ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የተሳሳተ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በመሆኑም ወቅታዊ የሆነ ግልጽ እና ትክክለኛ መረጃ መስጠት የአመለካከት ክፍተቱን በመሙላት ህብረተሰቡ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለውን አመኔታ ያሳድጋል፡፡

ሀሳብ መስጠት /Consultation/፡- በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ አስተያየት፣ ሃሳብ፣ ትችት እና አማራጮችን ማቅረብን የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ ደረጃ በብቃት ለማሳተፍ ተሳታፊዎች በቅድሚያ በቂ መረጃ ሊኖራቸውና ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የሚኖራቸው ተሳትፎ ለይምሰል ብቻ ይሆናል፡፡

ማካተት /Involvement/፡- በዚህ ደረጃ ሥራዎች በቀጥታ ከማህበረሰቡ ጋር በመሆንና ፍላጐታቸውን በአግባቡ በመረዳት ጥቅማቸው መጠበቁን ባረጋገጠ ሁኔታ የሚሰራበት የተሳትፎ ሁኔታ ነው፡፡

በትብብር መሥራት /Collaborative/፡- በማናቸውም ጉዳዮች ላይ ማለትም ጭብጥ ከመመስረት ጀምሮ በመለየትም ሆነ ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ ከሕዝብ ጋር ግንባር በመፍጠር ድርሻ እንዲኖራቸው ሲደረግ ነው፡፡

የወሳኝነት ድርሻ ወይም የበቃ ተሳትፎ /Empower/፡- ጉዳዩን ተመልክቶ ውሳኔ መስጠት ሙሉ በሙሉ በማህበረሰቡ እጅ በሚሆንበት ጊዜ ኑው፡፡

6. የማህበረሰብ ተሳትፎ በፍትሕ ሥርዓት ያለው ሚና

ወንጀልን መከላከል፡- የወንጀል ሕግ መሰረታዊ አላማ ወንጀልን መከላከል ነው፡፡ ከማህበራዊ ማህበረሰባዊ ባህልና ልምድ መነሻ በማድረግ ወንጀልን በመከላከል ዙሪያ የማይተካ ድርሻ አለው፡፡ ይሄም በተለያየ መልኩ ማለትም፡-

ሀ) ለወንጀል መከሰት የሆኑ ሁኔታዎችን በማጥናትና በመለየት መፍትሄ መፈለግ

ለ) የወንጀል ስጋቶችን በመለየት ከመፈፀማቸው አሰቀድሞ መፍትሄ በመስጠት፣ ወንጀል ከተፈፀመም ወደ ባሰ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በመፍታት

ለዚህ ሁነኛ ምሳሌ የሚሆነው የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ነው፡፡ በመሆኑም በድሬዳዋም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ የወንጀል በተለይም ከባድ ወንጀሎች ቁጥር ለመቀነስ እንደተቻለ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ሐ) ስለ ወንጀል እና ቅጣቱ በተጨባጭ መረጃ ስለሚኖራቸው ሌሎች ሰዎች ወደ ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይገቡ ያደርጋል፡፡

ወንጀሎችንና ወንጀለኞችን በማጋለጥ፡- ፖሊስ በሁሉም ቦታ አይገኝም፡፡ በሌላ መልኩ ወንጀል የሚፈፀመው በህብረተሰቡ ውስጥ ሲሆን ወንጀለኞችም በህብረተሰቡ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ በመሆኑም ወንጀል መፈፀሙና ወንጀለኞች ከህብረተሰቡ ሊሰወሩ አይችሉም፡፡ በማ/አ/ፖ/አ በአሁኑ ሰዓት ወላጆች ልጆቻቸውን ከሕግ ተጠያቂነት መቅረት እንደሌለባቸው በማመን ማጋለጥ የጀመሩበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡

በማስረጃነት፡- የወንጀል ምርምራ ያለህብረተሰብ ተሳትፎ ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም በምርመራም ሆነ በፍርድ ሂደት አስረጅ ምስክር በመሆን እና ማስረጃዎችን በማቅረብ የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡ ህብረሰተቡን አሳታፊ ማድረግ በማስረጃ ማሰባሰብ ላይ ያለው ጉልህ ለውጥ ለማየት ቀደም ባሉት ጊዜያት ፖሊስ ብርበራ በሚያካሂድበት ጊዜ ታዛቢ ለማግኘት ይቸገር የነበረ ሲሆን በአሁን ሰዓት ይህ ችግር በማ/አ/ፖ/አ በአብዛኛው ሊቀረፍ ችሏል፡፡

ግጭቶችን መፍታት፡- ማህበረሰቡ በግጭት አፈታት እንዲሳተፍ ማድረግ በተለይም ቀላል እና ጥንቃቄ የሚሹ ጉዳዮችን በአማራጭ የግጭት መፍቻ መንገዶች እንዲፈታ ማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ ከነዘህም መካከል፡-

አሸናፊ እና ተሸናፊ ስለማይኖር ችግሩን በዘለቄታዊነት እንዲፈታ ያደርጋል፤

ማህበራዊ መግባባትን ይፈጥራል፤

አንዳንድ ጥንቃቄ የሚፈልጉ ጉዳዮችን በጥንቃቄ ለመፍታት፤

ችግሮች እንዳይባባሱ ሁነኛ መፍትሄ በመስጠት፡፡

የፍትሕ አካላትን ጊዜ እና ወጪ መቆጠብ፡- ከላይ የተገለፁት ጥቅሞች በምርመራም ሆነ በፍርድ ሂደት ሊጠፋ የሚችለውን ረጅም ጊዜ ከማስቀረት በተጨማሪ ተያይዞ የሚወጣውን ወጪ ይቀንሳል፡፡ አማራጭ የግጭት መፍቻ መንገዶች ወደ ፍትሕ ተቋማት የሚሄዱትን ጉዳዮች ይቀንሳሉ፡፡ ይህም ባለጉዳዮች ጊዜያቸውን እና ሀብታቸውን ወደ ልማት ሥራ እንዲያውሉት እድል ይፈጠራል፡፡

የተፋጠነ ፍትሕ ለመስጠት፡- የፍትሕ አካላት ከላይ በተገለፀው መልኩ የሚያባክኑትን ጊዜና ሃብት ወደ ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች በማዞር የተፋጠነ ፍትሕ እንዲሰጡ ያደርጋል፡፡

የሕግ የበላይነት ማስፈን፡- ዜጐች መብቶቻቸውንና ግዴታቸውን በማወቅ ለሕግ ተገዥነታቸው እንዲጨምርና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡

ብልሹ አሠራርን ለማስቀረት፡- ማህበረሰቡ ከፍትሕ አካላት ጋር በተከታታይ በሚያደርጉት ምክክር ብልሹ አሰራሮችን ነቅሶ በማውጣት የጋራ መፍትሄ በማፈላለግ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት እድል ይፈጥራል፡፡

ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያላቸው አመኔታ እንዲጨምር፡- ዜጎች በፍትሕ ሥርዓት ላይ ያላቸውን አመኔታ በመጨመር የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው በማድረግ ውሳኔዎች በአግባቡ እና በፍጥነት እንዲፈፀሙ ያደርጋል፡፡

ጥራቱን ለጠበቀ ውሳኔ፡- የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት አና የሚሰጡ ውሳኔዎች የሁሉንም ተፎካካሪ ጥቅሞች ያማከለ እና የማህበረሰብን እውቀት ያገናዘበ ስለሚሆን ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ያርጋል፡፡

ግልፀኝነት እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን

የዲሞክራሲ ባህል እንዲጐለብት

7. የማህበረሰብ ተሳትፎ የአፈፃፀም መርሆች

ወቅታዊነት/Timeliness/Early Involvement፡- የማህበረሰብ ተሳትፎ በግልጽ መርሀ-ግብር ሊመራ እና ማህረሰቡ ለተሳትፎ የሚፈለግበት ጊዜ በተቻለ መጠን በውጤቱ ላይ ለውጥ ሊያመጣ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ ሊያደርግ በሚችልበት ወቅት ሊሆን ይገባል፡፡

ተጽእኖ ፈጣሪነት (Influence)፡- በማህበረሰበ የተነሱ ጉዳዮች እና የተሰጡ አስተያየቶች በሚፈለገው ውጤት (የመጨረሻ ውሳኔ) ላይ ከግምት ሊገቡ ይገባል፡፡

ውጤታማ የተሳትፎ መድረኮች(Effective Forums)፡- እንደጉዳዩ ተጨባጭ ሁኔታ ህብረተሰቡን ውጤታማ በሆነ መልኩ ሊያሳትፉ የሚችሉ የመረጃ መለዋወጫ እና ውሳኔ መስጫ አማራጮች መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ግብረ-መልስ (Feedback)፡- ማህበረሰቡ የሚሰጠው ግብአት እንዴት በውሳኔ እንደሚካተት እና በምን ያህል መጠን ውሳኔው ላይ ተጽእኖ እንዳሳረፈ ሊገለጽላቸው ይገባል፡፡

ቀጣይ እና ዘለቄታዊነት (Sustainability)፡- በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የህብረተሰቡ ተሳትፎ የአንድ ወቅት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ቀጣይ እና ዘለቄታዊ ሊሆን ይገባል፡፡

ግልፀኝነት(Open and Transparent)፡- የማህበረሰብ ተሳትፎ ለማሳለጥ የመንግሥት ግልጸኝነት ወሳኝ ነው፡፡ አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት የመረጃ ነፃነት ሕዝብ በበቂ መረጃ ላይ ተመስርቶ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ያበረታታል፡፡ በሌላ መልኩ የመረጃ ነፃነት አናሳ መሆን ህዝቡ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዳያደርግ ያደጋል፡፡

የማህበረሰቡን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ምስገባት (Adapted to the context)፡- የማህበረሰቡን ማህበራዊ ተቋማት፣ እሴቶች እና ባህል ማወቅ እና ማክበር ያስፈልጋል፡፡ በተግባራዊነትም ጊዜ የማህበረሰቡን ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን ከግምት ያስገባ ሊሆን ይገባል፡፡

በእኩልነት መርህ መሠረት አካታችነት (Inclusive and Equitable)፡- በተቻለ መጠን የተለያየ ጥቅም ያላቸውን ሁሉንም አካላት ያቀፈ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በተለይም /Vulnerable Groups በአግባቡ ሊወከሉ ይገባል፡፡

8. በማህበረሰብ ተሳትፎ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች እና ተግዳሮቶች

የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት፡- አንዳንድ የማህበረሰብ አካላት የሚያደርጉትን ተሳትፎ ከቀጥታ ከገንዘብ ጥቅም ጋር ለማያያዝ መሞከራቸው

ወጪ፡- አሳታፊ የሆነ አሠራር ተጨማሪ ወጪ ያለው መሆኑ እና ይህንንም ለማሟላት የሚያጋጥም የፋይናንስ እጥረት

የአመለካከት እና ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፡- በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በማህበረሰብ ውስጥ ሰርፀው ያሉ የአመለካከት ችግሮች እና ለረጅም ጊዜ ሰፍነው የቆዩ ጐጂ ልማዳዊ ባህሎች እና አስተሳሰቦ ዜጎች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዳያደርጉ ማድረጉ፣

ለምሳሌ - የሴት ልጅ ግርዛት

                - በሙስናና ኮንትሮባንድ ላይ ያሉ አመለካከቶች

                - የፍትሕ ጉዳይ አይመለከተኝም ብሎ የማሰብ

አልፎ አልፎ ህብረተሰሱ ለተሳትፎ የሚፈለገው ሁሉ ነገር ከተወሰነ በኋላ መሆኑ የህብረተሰቡ ተሳትፎ በውጤቱ ላይ ምንም አይነት ለውጥ እንዳያመጣ ያደርጋል፡፡ ይሄም በሌላ ጊዜ ህብረተሰቡ ለመሳተፍ ተነሳሽነት እንዲያጣ ያደርገዋል፡፡

አልፎ አልፎ ህጐት የማህበረሰብን ተሳትፎ ግልጽ በሆነ ዘርዘር ባለ መልኩ ያለማስቀመጣቸውና እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ድንጋጌዎች መኖራቸው፡፡

በብዙ ጉዳዮች ላይ ሁሉንም የማህበረሰብ አባላት ማሳተፍ አስቸጋሪ ስለሚሆን ተሳትፎ በፍቃደኞች ወይም በወኪሎች አማካኝነት ይሆናል፡፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ የሁሉንም ስብጥር ጥቅሞች ላይሞክሩ ይችላሉ፡፡ ይህም ሰዎች ያለመወከል ስሜት በማዳበር የሂደቱን ቅቡልነት ይቀንሰዋል፡፡

በአሳታፊ (Participatory) እና የውክልና (Representative) ዲሞክራሲ መካከል ያለውን ልዩነት ግልጽ የሆነ ግንዛቤ ያለመኖር፣

ሕጐችን በጠባቡ መተርጐም

የህብረሰተቡን ተሳትፎ እንደፎርማሊቲ ጉዳይ ብቻ በመቁጠር ለይምሰል (Window dressing) ብቻ መተግበር፡፡

ለሕዝብ ተሳትፎ የሚያዙት ከፍለ ጊዜዎች አጭር መሆን

ህብረሰተቡ የሰጠው አስተያየት ከምን ደረጃ እንደደረሰ ገለፃ አለማድረግ፣

ማህበረሰቡን አሳታፊ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የፍርድ ቤትን ነፃነት አልፎ አልፎ ሊጋፋ ይችላል፡፡ በመሆኑም በፍርድ ቤት ነፃነት እና በማህበረሰብ ተሳትፎ መካከል መገፋፋት እንዳይኖር ከፍተኛ ጥንቃቄ መኖር ይጠበቅበታል፡፡

9. የማህበረሰብ ተሳትፎን ለማጠናከር ምን ሊደረግ ይገባል

የመረጃ ነፃነት መብትን በማጠናከርና የመንግሥት አሠራርን ግልጽ የማድረግ ሥራ ማጠናከር፤

የተለያዩ የአመለካከት ችግሮች በአንድ ጀምበር የሚቀረፉ ስላልሆነ ግልጽ የሆነ ፍኖተ ካርታ በማውጣት በትምህርት እና ስልጠና በታገዙ ስትራቴጂዎች እንዲቀረፉ መሥራት፤

የማህበረሰቡን ተሳትፎ ወቅታዊነት ማስጠበቅ እና በቂ የሆነ የተሳትፎ ጊዜ መመደብ፤

ህጐች በሚወጡበት ጊዜ የህብረተሰብ ተሳትፎን ግልጽ እና ሂደቱን በዝርዝር ማስቀመጥ፤

የህብረሰተቡን የተሳትፎ ውጤት በግልጽ ማሳወቅ፤

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 107/2/ ከሌሎች የቤተሰብ ሕጉ ድንጋጌዎች እና ከሕገ መ...
ፍርዶች ዳግመኛ ሰለሚታዩባቸው መንገዶች (Review of Judgments)
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 20 April 2024