አንዳንድ ምልከታዎች ስለ መገናኛ ብዙኃን እና የሐሰት ዘገባዎች

ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እጅግ መሠረታዊ መብት ከመሆኑ የተነሳ የተለያዩ ሀገራት ሕጋዊ ጥበቃ የሚያደርጉለት ሲሆን በአለማችን ላይ በአንባገነንነታቸው የሚታወቁ መንግሥታት ሰይቀሩ መብቱ ሳይሸራረፍ በሀገራቸው እንደሚጠበቅ ይከራከራሉ። በዚህ ጽሑፍ ሀሳብን በነፃነት መግለጽ መብት በሰፊው ከሚተገበርበት ስለ መገናኛ ብዙኃን መብት እንመለከታለን። በመጀመሪያው ክፍል የመገናኛ ብዙኃን ለምን የሐሰት ዘገባዎችን ይሠራሉ በተለይም በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙ ወይም ዋነኛ የፋይናንስ ምንጫቸው በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ከመንግሥት የሆነ የሚለውን እናያለን። በመቀጠል የመገናኛ ብዙኃን የሰሩት ፕሮግራም እውነታን ያዘለ ሆኖ ሳለ የእርምት ወይም መልስ የመስጠት መብት ያለው አካል ሐሰተኛ ማስተባበያ ይዞ ቢቀርብ የማስተላለፍ ግዴታ አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚለውን እንመለከታለን። በመጨረሻም ነፃ ሚዲያ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከሀገራችን ሕጎች አንፃር አጭር ዳሰሳ እናካሔዳለን።

የመገናኛ ብዙኃን ለምን የሐሰት ዘገባዎችን ይሠራሉ

በተለያዩ ግዜያት ሚዲያዎች የሐሰት ዘገባ ሲሰሩ ይስተዋላሉ። ይህ ተግባር በተለይ የዴሞክራሲ ሥርዓት ባልዳበረባቸው ሀገራት በብዛት ይደጋገማል። ሀገራችንም በተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት በዚህ ረገድ ክስ ይቀርብባታል። ለሚዲያ ሐሰተኛ ዘገባዎች በዋናነት ነፃ አልመሆናቸው ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ለዚህም ነው የመገናኛ ብዙኃን እና የመረጃ ነፃነትን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 590/2000 በመግቢያው ላይ የመገናኛ ብዙኃን የአሠራር ነፃነት ላይ መሰናክል የነበሩ መዋቅራዊ እና ተቋማዊ ችግሮችን ማስወገድ ሀሳብን በነፃነት ለመግለጽ እና የመገናኛ ብዙኃንን ነፃነት ለማዳበር መሠረት እንደሚሆን የሚያስቀምጠው። ይህ የሐሰት ዘገባ በግል ከተያዙ መገናኛ ብዙኃን ይልቅ በመንግሥት ይዞታ ሥር ባሉ ወይም ከመንግሥት የፋይናንስ ድጋፍ በሚደረግላቸው ሚዲያዎች ላይ በብዛት ይስተዋላል።  ይህን አስመልክቶ የናዚ የፕሮፖጋንዳ ሚኒስቴር የነበረው ጄሴፍ ጊበን ሲናገር ውሸትን በብዛት ማምረት ከቻልክ ይህንንም ማስቀጠል የምትችል ከሆነ ሕዝቡ በመጨረሻ ያምናል። ይህም ውሽት ሊቀጥል የሚችለው መንግሥት ውሽቱ በሕዝቡ ላይ ከሚያስከትለው ፖለቲካዊ፣ ኢኪኖሚያዊ እንዲሁም ወታደራዊ መዘዝ ሕዝቡን መከልከል ሲችል ነው። ሰለዚህ ለእንዲህ ዓይነት መንግሥት የሚበጀው የአለውን ሁሉ ኃይል አሟጦ የልይነትን ሀሳብን /dissenting ideas/ መደፍጠጥ ነው። ሰለሆነም እውነት የውሸት የባህሪ ጠላቱ ሰለሆነ በአምክንዮ እውነት የአንድ አገዛዝ ዋነኛ ጠላት ነው በማለት ሀሳቡን ያስቀምጣል።

ለመሆኑ መገናኛ ብዙኃን ስለምን የሐሰት ዘገባዎችን ይሠራሉ?

መገናኛ ብዙኃን የሚዋሹበት ምክንያት የተለያዩ ሲሆን የሚከተሉት ግን በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

ሀ/ ይዞታ

አንድ መገናኛ ብዙኃን በግል ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ስር ሊሆን ይችላል። ሚዲያው ሙያዊ ግዴታውን እንዳይወጣ በባለቤትነት የሚቆጣጠሩት አካላት ሚና ከፍተኛ ነው። ይህ ደግሞ የዴሞክራሲ ባሕል ባልዳበረባቸው ሥርዓቶች ውስጥ የከፋ ነው። ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው ደግሞ በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ ወይም የገንዘብ ድጋፍ በመንግሥት የሚደረግላቸው ሚዲያዎች መረጃ በመደበቅ፣ በማዛባት እና የሐሰት ዘገባ በማቅረብ ከግል ሚዲያ የባሱ ናቸው። ሀገራችንም በዚህ ረገድ በዜጎቿም ሆነ በአለም አቀፍ ሰብዓዊ ተቋማት በተደጋጋሚ ክስ ሲቀርብባት ይስተዋላል።  

ለ/ የገንዘብ ድጋፍ

አንድ ሚዲያ ሲቋቋም ወይም ፕሮግራም ሲሠራ ስፖንሰር ያደረገውን አካል ፍላጎት ውሽትም ቢሆን ሊያቀርብ ይችላል። ለዚህም በሀገራችን ጎልቶ ባይታይም አሁን አሁን የቢራ ፈብሪካዎች አሉታዊ ተፅኖ ስፖንሰር ባደረጉት ፕሮግራም ላይ እየተስተዋለ ነው። ይህን አስመልክቶ ታዋቂው የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ ጆን ስዌይተን ለእርሱ ስንብት በተደረገ የራት ግብዣ ፕሮግራም ላይ ለወጣት ባልደረቦቹ ይህን ንግግር አድርጎ ነበር።

'ከእናንተ ውስጥ አሁን አንዳችሁም ቅን የሆነውን የራሱን ምልከታ የሚጽፍ የለም፤ የአንድ ጋዜጠኛ የዘወትር ተግባሩ እውነትን ማጥፋት፣ ስም ማጉደፍ እና ለኩርማን እንጅራ ሲል ሙያውን በገንዘብ መለወጥ ሆናል። እኛ የከበርቴዎች አሸንጉሊት እና ደምስሮች ሆነናል፤ እነሱ ስርቅ ሲላቸው እኛን ያንቀናል። የኛ እውቀት፣ እድል እና ህይወት የነርሱ ሆናል። እኛ (ጋዜጠኞች) በሙያችን ዝሙትን የምንፈፅም ምሁሮች ነን።'

ይህ ንግግር እውነታን ያዘለና በሥነ ምግብር የማይመራ የሚዲያ ተቋም እንዴት የገንዘብ እና የባለኃብት ሎሌ እንደሚሆን የሚያሳይ ነው።  

ሐ/ ምንጭ

የተሳሳተ የመረጃ ምንጭ ብቻ ተቀብሎ ተገቢውን ማጣራት ሳያደርግ ፕሮግራም የሚያቀርብ የሚዲያ ተቋም መሳሳቱ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡

መ/ ተፅዕኖ መቋቋም አለመቻል

ከፍተኛ የሕዝብ እና የተደራጁ አካላትን ተፅዕኖ መቋቋም የማይችሉ የሚዲያ ተቋማት እነዚህን አካላት ላለማስከፋት ሲሉ ሚዛናዊ እና እውነተኛ ያልሆነ ዘገባን ያቀርባሉ። ለዚህም እንደ ምሳሌ ማንሳት የሚቻለው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጣን የቀሰቀሰ ፆታዊ ጥቃት ለአብነት ያክል በህንድ ሀገር በተደጋጋሚ የደረሰውን መጥቀስ ይቻላል።  

ሠ/ የተቃኘበት ርዕዮተ ዓለም

አንድ ሚዲያ ነፃ ሳይሆን ቀርቶ በአንድ ርዕዮተ ዓለም ብቻ ከተቃኘ ስለሌሎች አስተሳሰቦች ሲሠራ መረጃ ማዛባቱ አይቀርም። ለምሳሌ በሊቤራሊዝም አስተምህሮ የተጠመቀ ሚዲያ ልማታዊ ዴሞክራሳዊ እንደ አበቃለት ያትታል፤ በተቃራኒውም እንደዚሁ፤

እርምትን ወይም መልስ የመስጠት መብትን በማስተናገድ ረገድ የመገናኛ ብዙኃን ግዴታ

መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ሲያቀርቡ ይዘቱ በሕጉ የተጠቀሱትን ገደቦች እንደማይጣረስ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ከዚህም ውስጥ ዘገባው የሌሎችን ሦስተኛ ወገኖች ክብር እና ሰብዕና የማይነካ መሆን ይኖርበታል።  ነገር ግን ይህን ሳያከብሩ የቀሩ እንደሆነ አዋጅ ቁ 590/2000 በአንቀጽ 40/1/ሀ ሥር በመገናኛ ብዙኃን የቀረበ የፍሬ ነገር ዘገባ መልካም ስሙ እና ክብሩ የተጎዳበት ማንኛውም ሰው በቀረበበት መገናኛ ብዙኃን ላይ የእርምት ወይም መልስ የመስጠት መብት አለው ይላል። ነገር ግን የቀረበው ዘገባ እውነት ሆኖ የእርምት ጥያቄው ሐሰት ቢሆን መገናኛ ብዙኃን ምን ማድረግ አለባቸው? ይህን ለመረዳት ይረዳን ዘንድ በአሜሪካ የተከሰተ አንድ ታሪክ እንደ ማሳያ እናንሳ። ጄን አከር ና ባለቤቷ የነበረው ስቲቭ ዊልሰን እኤአ ከ1996 ዓ.ም ለFOX TV በመርማሪ በጋዜጠኝነት መሥራት ጀመሩ። በዚህ ወቅት monsato corporation የተባለ ኩባንያ የሚያመርተው bovine growth hormone የተባለው በሄርሞን የታከመ ወተት በተጠቃሚው ላይ ዘርፈ ብዙ ችግር እንደሚያስከትል የሚያሳይ ዶክመንተሪ ሰርተው አቀረቡ። በዘገባው ቅር የተሰኘው ኩባንያ ሐሰተኛ የሆነ የእርምት ፕሮግራም እንዲቀርብለት ለጣቢያው አመለከተ። ጣቢያውም የእርምት ፕሮግራም እንዲሰሩ ጥንዶቹን አዘዛቸው። ነገር ግን ጥንዶቹ የሙያችንን ነፃነት የሚጋፋ ስለሆነ እርማቱን አናቀርብም በማለት ተከራከሩ። ይህን ተከትሎ ውላቸው በጣቢያው እንዲቋረጥ ተደረገ። የሥራ ውሉ አላግባብ ነው የተቋረጠው በማለት ክስ አቅርበው ይወሰንላቸዋል። በውሳኔውም ቅር በመሰኘት ጣቢያው ይግባኝ በማለት ውሳኔው እንዲሻር ያስደርጋል። ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱም ምክንያት ያደረገው በሀገሪቱ የሐሰት ዘገባን የሚከለክል ሕግ የለም በማለት ነው። ይህን ውሳኔ የደገፉ ሌሎች አካላትም የጣቢያው ውሳኔ አግባብነት ያለው ነው ምክንያቱም ጣቢው ሚዛናዊ ለመሆን ማስተባበያውን ማቅረብ አለበት በማለት ይከራከራሉ። በኛ ሀገርስ ለሚለው አዋጅ ቁ 590/2000 አንቀጽ 40/1/ሐ ን መመልከት አግባብነት ይኖረዋል። በዚህም መሠረት ማስተባበያው ለቀረበው ጉዳይ ተመጣጣኝ፣ አግባብነት ያለው እና ሕጋዊ ይዘት ያለው መሆን ይኖርበታል። እዚህ ላይ 'ሕጋዊ ይዘት' ሚለውን መለኪያ ማየት ይገባል። ሀሰተኛ የሆነ ነገርን በማስተባበያነት መዘገብ በሕጉ ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29 /6 እና በአዋጅ ቁ 590/2000 መግቢያ ላይ በተመለከተው መሠረት መገናኛ ብዙኃን የሕዝብን ደህንነት፣ ሰላም እና ፀጥታን የሚያናጋ ዘገባ ማቅረብ ስለማይችሉ ነው።  ከዚህም በላይ ሥርጭቶቹ የሚተላለፉበት የአይር ሞገድ እና ኃብት የሕዝቡ ሰለሆነ በሕዝብ ኃብት እራሱ ሕዝቡን የሚጎዳ ነገር ማቅረብ ከሞራል አንፃር አግባብ አይሆንም። ነገር ግን ጉዳዩ የሕዝብን ጥቅም ሳይሆን በግልፅ የግለሰብ ጉዳይ ከሆነ ማስተባበያው ሐሰት ቢሆንም እንኳን የግለሰቡ መልስ የመስጠት መብት ሊከበር ይገባል።

ነፃ ሚዲያ ከአዋጅ ቁ.590/2000 አንፃር

አንዳንዶች ነፃ ሚዲያ የሚባል ነገር የለም -independent media is a myth- በማለት ይገልፃሉ። ለመሆኑ ነፃ ሚዲያ ምን ማሟላት አለበት ለሚለው አዋጅ ቁ.590/2000 በአንቀጽ 4 ሥር መልስ ይሰጠና። ዋናው መለኪያ የትኛውም ሚዲያ ከቅድመ ምርመራ ነፃ መሆን አለበት የሚለው ነው። ሌላው ገደቦች የሚጣሉት በሕገ መንግሥቱ እና እሱን ለማስፈፀም በሚወጣ ሕግ ብቻ ነው። የሚወጡ ሕጎችም ከሕገ መንግሥቱ ገደቦች ውጭ ሌላ ገደብ ማስቀመጥ አይችሉም። ይህም ማለት ከገደቦቹ ውጭ ማናቸውም የመገናኛ ብዙኃንን ነፃነት የሚያስተጓጉል አስተዳዳራዊ እርምጃ ሕገወጥ ነው። ለዚህም የመንግሥት አካላት መገናኛ ብዙኃን ግዴታቸውን እንዲወጡ መብታቸውን ሊያከብሩላቸው ይገባል።

ማጠቃለያ

በአንድ ሀገር ውስጥ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመጣ ከመንግሥትም ሆነ ከሚዲያ ባለሙያዎች የሚጠበቁ ጉዳዮች ሙሉ ለሙሉ ሊሟሉ ይገባል። በመንግሥት በኩል የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት ሚዲያ የማይተካ ሚና አለው ብሎ በፖሊሲ ከማስቀመጥ ባሻገር ለሚዲያ አካላት በተግባር የተደገፈ የፋይናንስ እና የሥልጠና ድጋፍ መስጠት አለበት። በተጨማሪም የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን ሪፖርት ከማስተባበል የዘለለ ግላዊ ሳንሱርን (self censure ship) ከሚያመጡ የአተግገባበር ድርጊቶች እራስን መከልከል እና ይህን ተግባር በሚፈፅመው አካል ላይ የተጠያቂነት በሕል እንዲኖር መሥራት ይጠበቅበታል። ሚዲያውም በተለይ የሕዝብ ሚዲያው ለሚዲያ ሥነ ምግባር ተገዢ መሆንን በማዳበር ተገቢውን ሀላፊነት ሊወጣ ይገባዋል። ለዚህም የሚጠቀምበት ኃብት የሕዝብ መሆኑን በመገንዘብ የአንድ አካል ልሳን ከመሆን ሕዝባዊነትን መላበስ ይገባዋል። ይህን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው አንፃራዊ ነፃ ሚዲያን መገንባት የምንችለው። አለበለዚያ ነፃ ሚዲያ የሚባለው ቅዠት እንድሆነ ይቀራል። 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

(Non) retroactivity of Ethiopian Criminal Law
ያለ ፈጣን የፍርድ ሂደት ዋስትና የሚያስከለክል የወንጀል ድንጋጌ የሕገ መንግሥቱ...
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 19 April 2024