ዓባይ ከቅኝ ገዥዎችና ከዓለም አቀፍ ሕግ አንፃር

ሳፔቶ ሩባቲኖ የተባለ ኩባንያን በማቋቋም ወዲያው የባህር ንግዱን ማጧጧፍ ጀመረ፡፡ ከአሥራ ሁለት ዓመታት በኋላ የኢጣሊያ መንግሥት የጂቡቲን ጠረፋማ አካባቢ እንዲሁ በገንዘብ በመግዛት ከራስ ዱሜራ እስከ ራስ አሊ ከተቆጣጠረችው ፈረንሣይ ጋር ለመሻማት ኩባንያውን ከነካፒታሉ በመግዛት የአሰብን ጠረፋማ አካባቢዎች ተቆጣጠረ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ግብፅን ስታስተዳድር የነበረችው እንግሊዝ ሱዳን ላይ የተቀሰቀሰውን ኃይለኛ የሙስሊም መሠረታውያን (ፋንዳሜንታሊስቶች) አብዮት ለመከላከል ሁነኛ አጋር ሆና እንድትቆምላት ኢጣሊያ ከቆላማዎቹ የቀይ ባህር አካባቢዎች በመነሳት ወደ ደጋማው የኢትዮጵያ ግዛት (ኤርትራ) ግዛቷን እንድታስፋፋ አበረታታቻት፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሱዳን ሙስሊም ፋንዳሜንታሊስቶች በሱዳን ምሥራቃዊ ክፍል የመሸገውን ለእንግሊዝ ያደረ የግብፅ ጦር በመክበብ በውኃ ጥም ሊፈጁት ሆነ፡፡ 

በዚህ ከበባ የተደናገጠችው እንግሊዝ ወታደሮችዋን ነፃ ለማስወጣት የኢትዮጵያን ዕርዳታ ጠየቀች፡፡ ዓድዋ ላይ በአፄ ዮሐንስና በአድሚራል ሕይወት መካከል እ.ኤ.አ. በ1804 ውል ታሰረ፡፡ የውሉ ምሰሶ እንግሊዝ በመገስገስ ላይ የነበረውን የኢጣሊያ ኃይል እንድታስወጣ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ሠራዊትዋን በመላክ የእንግሊዝን ጦር ከእልቂት እንድትታደግ ለማድረግ የሚል ነበር፡፡ አፄ ዮሐንስ ሠራዊታቸውን በመላክ ደርቡሾችን በመደምሰስ በእልቂት አፋፍ ላይ የነበሩትን የእንግሊዝ ወታደሮች ነፃ አወጡ፡፡ በዚህም ዕርምጃቸው ከደርቡሾቹ ጋር ደም ተቃቡ፡፡ እንግሊዝ በበኩሉዋ ታሪካዊ ክህደት በመፈጸም ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› ብላ የኢጣሊያን እንቅስቃሴ በዝምታ መደገፍዋን ቀጠለች፡፡ የካቲት 5 ቀን 1865 ኢጣሊያ ምፅዋን በመቆጣጠር ወደ ደጋማዎቹ የሐማሴን ወረዳዎች መግፋት ቀጠለች፡፡ ሆኖም ከሁለት ዓመታት በኋላ ጥር 26 ቀን 1867 በራስ አሉላ የተመራው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከኰሎኔል ዴ ክሪስቶፎረስ መሪነት ዶጋሊ (ከምፅዋ ሃያ ኪሎ ሜትር) ላይ በመሸገው የ500 ወታደሮች ክምችት ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመፈጸም ወታደሮቹን ከነአዛዣቸው ደመሰሰ፡፡ 

በውጊያው የተደመሰሱትን ወታደሮች ደም ለመበቀል ኢጣሊያ በጀኔራል ሳን ማርሳኖ የተመራ አዲስ ወታደራዊ ኃይል በማንቀሳቀስ ከኢትዮጵያውያን ጋር ለመግጠም ዝግጅቱን አጠናቀቀ፡፡ አፄ ዮሐንስም ወራሪውን ኃይል ለመመከት መሸጉ፡፡ ከወደ ጎንደር ይመጡ የነበሩ ወሬዎች ግን ጄኔራል ማርሳኖን ለመግጠም ለንጉሠ ነገሥቱ የተረጋጋ መንፈስ የሚሰጡ አልነበሩም፡፡ የዓድዋውን ስምምነት ቃል ኪዳን በማፍረስ ታሪካዊ ክህደት የፈጸመችው እንግሊዝ ኢትዮጵያን ለሁለት ኃይለኛ ጠላት አሳልፋ ሰጠች፡፡ ከቀይ ባህር አልፎ ደጋማውን አካባቢ እየተቆጣጠረ የነበረው ኢጣሊያ በአንድ በኩል፣ የጣናን ሐይቅ ነፋሻማ ግዛቶች ሊቆጣጠር የሚፈልገው ገድሎ ሊሞት ቆርጣ የተነሳ የደርቡሽ ኃይል በሌላ በኩል ተሰልፈዋል፡፡ አፄ ዮሐንስ ቃል ኪዳናቸውን በማክበር ለፈጸሙት ተግባር ምላሹ ይህ መሆን እንደሌለበት ለእንግሊዝዋ ንግሥት ቪክቶርያ የተማፅኖ ደብዳቤዎችን በተደጋጋሚ ቢልኩም ምላሽ አላገኙም፡፡ ደርቡሾች የኢትዮጵያን ሰሜን ምዕራብ ክልል ጥሰው በመግባት ሰላማዊውን የጐንደር ሕዝብ ፈጁ፣ ገዳማትን አቃጠሉ፡፡ ሕፃናትን እያፈኑ አጋዙ፣ ከብቶችን እየነዱ ድንበር አሻገሩ፡፡ ይህ ዜና ከጣሊያን ወረራ በበለጠ የአፄ ዮሐንስን ህሊና ይበልጥ ተፈታተነ፡፡ የውጊያ ስትራቴጂያቸውን ለመቀየር ተገደዱ፡፡ የጣሊያንን ወራሪ ጦር ከደርቡሽ በኋላ ለመግጠም ፊታቸውን ወደ ጎንደር አዞሩ፡፡ 

እዚያ ሲደርሱ በሕዝቡና በንብረቱ ላይ የደረሰው ውድመት ከተነገራቸው በላይ ሆኖ አገኙት፡፡ መተማ ላይ ውጊያው ተጀመረ፡፡ በቂም በቀል ቆርጠው የተነሱትን ደርቡሾች ለማሸነፍ ከፍ ያለ መስዋዕትነት ጠየቀ፡፡ ከሞት የተረፈው የደርቡሽ ጦር እግሬ አውጭኝ ብሎ መሸሽ ጀመረ፡፡ አፄ ዮሐንስ ግን ወታደሮቻቸውን በማስከተል ወደ ሱዳን ምድር ዘልቀው በመግባት እልህና ወኔ በተሞላበት መንፈስ ጦርነቱን አስቀጠሉ፡፡ የኋላ ኋላ ግን ከአንድ የደርቡሽ ወታደር በተተኮሰ ጥይት ደረታቸውን ተመትተው ከፈረሳቸው ወደቁ፡፡ ይህን ዜና የሰማው የደርቡሽ ኃይል የመልሶ ማጥቃት ውጊያውን አጠናከረ፡፡ ኢትዮጵየውያኑ ግን ምንም እንኳ ከፍተኛ ድካምና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ቢያድርባቸውም ንጉሠ ነገሥታቸውን አሳልፈው ላለመስጠት የመከላከሉንና ወደ ኋላ የማፈግፈጉን ውጊያ ቀጠሉበት፡፡ ቁስለኛውን ንጉሠ ነገሥት ተሸክመው መተማ ላይ ደረሱ፡፡ አሁንም ደርቡሾተ በመከታተል ንጉሠ ነገሥቱ ያረፉበት ድንኳን በተኩስ እሩምታ አነደዱት፡፡ በማያቋርጥ ደም መፍሰስ አቅማቸው እየደከመ የመጣው ክንደ ብርቱው ዮሐንስ አራተኛ አሸለቡ፡፡ የንጉሣችንን ሬሳ አሳልፈን አንሰጥም በማለት በርካታ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በድንኳኑ ዙሪያ በደርቡሾች ጥይት ተቆሉ፡፡ ደርቡሾች ግን የልብ ልብ ተሰማቸው፡፡ ተጨማሪ ኃይል መጉረፍ ቀጠለ፡፡ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ድንኳን ሰብረው በመግባት የአፄ ዮሐንስን አንገት ቆርጠው ወሰዱ፡፡ ረሃብ፣ በሽታና ፍጹም ተስፋ የመቁረጥ ስሜት የሰሜን ኢትዮጵያን ወረረ፡፡ 

ኢጣሊያና አፄ ምኒሊክ

አፄ ዮሐንስ በመጋቢት ወር 1889 ከተሰው በኋላ ጣሊያኖች ተራራው ሁሉ ሜዳ መስሎ ታያቸው፡፡ ወዲያውኑም ከረንንና አሥመራን ያዙ፡፡ ከአፄ ዮሐንስ ሞት በኋላ በሁለተኛው ሳምንት ወሎ ላይ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ተሰኝተው ዘውድ ከደፉት ንጉሥ ምኒሊክ ጋር ‹‹የቀረበ ግንኙነትን›› መፍጠር ለቀጣዩ ስትራቴጂያቸው አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ውለው ሳያድሩ ተገነዘቡ፡፡ የአፄ ምኒሊክን አመኔታ ለማግኘት ጀኔራል ማርሳኖ 45,000 ጠብመንጃዎች ከበቂ ጥይት ጋር በገፀ በረከትነት ለንጉሠ ነገሥቱ ላከ፡፡ አንባቢያን እዚህ ላይ መጠራጠራቸው አይቀርም፡፡ ይህንን ያህል መሣሪያ የኢጣሊያ መንግሥት ለኢትዮጵያ እንዴት ሰጠ? የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም ጥያቄ ነው፡፡ ጉዳዩን ከውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ጋር ስናያይዘው ግን እንቆቅልሹ ይፈታልናል፡፡ 

ጄኔራል ማርሳኖ ኢጣሊያ የተቆጣጠረችውን አዲስ ግዛት ‹‹ሕጋዊነት›› ይኖረው ዘንድ ከአፄ ምኒሊክ ጋር ለመነጋገርና ውል ለመፈራረም ከአሥመራ ወደ አዲስ አበባ በበቅሎ ተንቀሳቀሰ፡፡ ለሥራ ጉዳይ ወሎ የነበሩት አፄ ምኒሊክ ወደ ቤተ መንግሥታቸው እስኪመለሱ ድረስ እንኳን ኢጣሊያዊው ጀኔራል ትዕግሥት አነሰው፤ ውጫሌ ከተማ ላይ ሁለቱም ተቀመጡ፡፡ ውሉ በጣሊያንኛና በአማርኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ ቀረበ፡፡ ከአንቀጽ 17 በስተቀር ሌሎቹ አንቀጾች የኢጣሊያ ቅኝ ግዛትና (ኤርትራ) የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ከየት እስከ የት እንደሚሆን የሚገልጹ ሲሆን፣ አንቀጽ 17 ግን የጣሊያንኛውና የአማርኛው ቅጅ የተመሰቃቀለ ነበር፡፡ 


የጣሊያንኛው ቅጅ እንዲህ ይነበባል፡፡ (በግርድፉ)

አንቀጽ 17፡- ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር የሚያደርጓቸው ግንኙነቶች ሁሉ በኢጣሊያ መንግሥት አማካይነት ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡ 

የአማርኛው ቅጅ፡-


አንቀጽ 17፡- ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ከአውሮፓ መንግሥት ጋር ለሚያደርጓቸው ግንኙነቶች የኢጣሊያን መንግሥት ዕርዳታ ለመጠየቅ ይችላሉ፡፡  

በነገራችን ላይ ሁለቱም ቅጂዎች የአፄ ምኒሊክ ፊርማና ማህተም አርፎባቸዋል፡፡ የጣሊያንኛው ቅጂ ኢትዮጵያን በቀጥታ በኢጣሊያ ሞግዚትነት ሥር የሚያስገባ ስለሆነ ማርሳኖ የኢትዮጵያ ወዳጅና ሠራዊትዋን በጦር ኃይል ለማጠናከር በጎ ዓላማ ያለው መሆኑን በማስመሰል፣ አፄ ምኒሊክና አስተርጓሚዎቻቸው ጭምር ከውጫሌ ውል በስተጀርባ ዓላማ ላይ አንዳች ጥርጣሬ እንዳያድርባቸው በማስመሰል በኩል የተሳካላት ይመስላል፡፡ ጀኔራል ማርሳኖ የጣሊያንኛውን ቅጂ ወዲያው ለአገሩ መንግሥት በቴሌግራም አስተላለፈ፡፡ ዜናው የአውሮፓ ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና ሬዲዮ ጣቢያዎች ‹‹ሰበር ዜና›› ሆኖ ናኘ፡፡ የአውሮፓ ጋዜጠኞችና ዲፕሎማቶች የማርሳኖን ተዓምራዊ ጥበብ ለመቅሰም የሮምን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ኮሪደሮች አጣበቡ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ሞግዚት ሆና ልትተዳደር ተስማማች›› ድንቅ ዜና፡፡

አፄ ምኒሊክ ይህን ሸፍጥ እንዲሰሙ ለአውሮፓ መንግሥታት እንዲህ የሚል ደብዳቤ ላኩ፡፡ ‹‹እኔ በትክክል በአማርኛ ቋንቋ ቅጂው ላይ የፈረምኩት ውል የጣሊያኖችን ትብብር ለመጠየቅ እንደሚችል የሚገልጽ እንጂ፣ ጣሊያኖቹ እንደሚሉት ለማድረግ ግዴታ ያለብኝ መሆኑን በጭራሽ የፈረምኩት ውል የሌለ መሆኑን ዓለም እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ፤›› አሉ፡፡ የኢጣሊያ መንግሥት ለአፄ ምኒሊክ ደብዳቤ የሚከተለውን ምላሽ ሰጠ፡፡ ‹‹የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ›› እንዲሉ፣ ‹‹የውላችን የጣሊያንኛ ቅጂ ፍጹም ግልጽ ነው፡፡ አለመግባባቱ የተፈጠረው የአማርኛው ቅጂ ውዥንብርን በሚያመጣ ሁኔታ በመጻፉ ሊሆን ይችላል፤›› አለ፡፡ 

በሁለቱም መንግሥታት መካከል በውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ትክክለኛ ትርጉም ላይ ስምምነት ሳይደረስ አርባ አምስት ዓመታት አለፉ፡፡ ሁለት ዓበይት ጦርነቶችም ተካሄዱ፡፡ የቅኝ ግዛቶቻቸውን ለማርጋት ፈረንሣይ፣ እንግሊዝና ኢጣሊያ በ1906 ዓ.ም. ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ግን ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ አንቀጽ 17 በጣሊያኖቹ መንገድ እንዳልፈረሙና ሐሳብ እንዳልነበራቸው ኢጣሊያ አረጋግጣላቸዋለች፡፡ 

ኢጣሊያ በውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ሰበብ ኢትዮጵያን በሞግዚትነት ለመቆጣጠር የማይቻላት መሆኑን ከተገነዘበች በኋላ በጥቅምት ወር 1896 (ከዓድዋ ጦርነት አምስት ወራት ቀደም ብሎ መሆኑ ነው) ጦሯን ከኤርትራ መሬት በማንቀሳቀስ በንጉሥ መንገሻ ዮሐንስና በልብ ወዳጃቸው የአከለ ጉዛዩ አርበኛ ደጃዝማች ባህታ ሐጐስ ላይ የተጠናከረ ጥቃት በመሰንዘር ትግራይን ከኤርትራ ጋር አዋሃደች፡፡ ይሁን እንጂ በዓድዋ ጦርነት ሦስት ግዙፍ ክፍለ ጦሮችዋና ምርጥ የጦር ጀኔራሎችዋን ያጣችው ኢጣሊያ ግዛትዋ በመረብ፣ በለሳና ሙና ወንዞች ብቻ ወስና እንድትይዝ ተገደደች፡፡

ከሰላም ለእንግሊዝ ተሰጠች፡፡ በዓድዋ የደረሰባትን ውርደት ለመበቀል ጊዜ በመጠበቅ ዝግጅትዋን ቀጠለች፡፡ ከዓድዋ በኋላ ኢጣሊያ የውጫሌን ውል ለመቅደድና ከምድረ ኤርትራ ጠቅልላ ለመውጣት ባትገደድም ሥራ ያጡ ዜጐችዋን ነፋሻማው የጣና ሐይቅ አካባቢ ለማስፈር የነበራት ምኞት ግን እውን ሳይሆን ቀረ፡፡ ይልቁንም እንግሊዝ የጣና ሐይቅ ባለቤት መሆንዋን በሐይቁም ዙሪያ ግድቦችንና መስኖዎችን ለመሥራት እንደምትችል ኢጣሊያ አምና ተቀበለች፡፡ ከዚህም አልፎ በእንግሊዝ ፈቃድና ብርታት ሰጪነት ኤርትራን በቅኝ የያዘችው ኢጣሊያ ሚያዝያ 15 ቀን 1891 ከእንግሊዝ ጋር በገባችው ውል ‹‹የኢጣሊያ መንግሥት የተከዜን ወንዝ አቅጣጫ የሚቀይር ማናቸውም የመስኖ ወይም ሌላ የግንባታ ሥራ ላለመሥራት›› ቃል ገብታ ፈረመች፡፡

በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መካከል ስለ ጣና ሐይቅ ጉዳይ ግንቦት 15 ቀን 1902 ዓ.ም. የተደረገ ውል
እንግሊዝ አፄ ምኒሊክን ለዚህ ስምምነት ድርድር ስትጋብዝ በመሠረቱ የኢትዮጵያና የሱዳንን ድንበር ለመከለል በሚል ቢሆንም ቅሉ፣ ልክ እንደ ውጫሌው ውል ይህም ስምምነት ውስጠ ወይራ ነበር፡፡ የውሉ አንቀጽ 3 እንደሚከተለው ይነበባል፡፡ 

3ኛ ክፍል

ጃንሆይ ዳግማዊ ምኒሊክ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ከጥቁር ዓባይና ከባህር ዳር፣ ከሶባት ወንዝ ወደ ነጭ ዓባይ የሚወርደውን ውኃ ከእንግሊዝና ከሱዳን መንግሥታት ጋር አስቀድሞ ሳይሰስማሙ ወንዙን ተዳር እስከ ዳር የሚደፍን ሥራ እንዳይሠሩ፣ ወይም ወንዙን የሚደፍን ሥራ ለመሥራት ለማንም ፈቃድ እንዳይሰጡ በዚህ ውል አድርገዋል፡፡ ለንጽጽር ያህል የእንግሊዝኛው ቅጅ እነሆ፤


Article III


The Emperor Menelik engages not to constitute or to allow to be constructed any work across the blue Nile, the lake Tana, or the Sobat which would arrest the flow of their waters into the Nile, except in agreement with the government of Great Britain and the Sudan.  

እንግሊዞች አፄ ምኒሊክን ለማግባባት የውሉ ርዕስ የዳር ድንበር ጉዳይ በማስመሰል በጣና፣ በዓባይና በባሮ ወንዞች ላይ ብቸኛ ባመብት የሚያደርጋቸውን ውል አስፈረሟቸው፡፡ የውሉ መፈረም ለእንግሊዞች በኢትዮጵያ የውኃ ሀብት ላይ ወሳኝነት እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በላይ፣ ምናልባትም ዋናዋ የእንግሊዝ ተፎካካሪ ፈረንሣይ በአካባቢው እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ከዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ጋር መልካም ሊባል የሚችል ግንኙነቶችን እየፈጸመች ስለነበር፣ እጅዋን ወደ ጣና ሐይቅና ዓባይ ወንዝ እንዳትሰነዝር ለመከላከል ያደረገችው ዘዴ ይመስላል፡፡ አለበለዚያ ኢትዮጵያ በዚያ ዘመን ጣናን ወይም ዓባይን ልትገደብ ትችላለች የሚል ሥጋት አድሮባቸዋል ለማለት ያስቸግራል፡፡ በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ በኩል ደግሞ የሱዳኑ ድንበር በውል እስከተረጋገጠላቸው ድረስ ጣናንና ዓባይን እንዳይገድቡ ውል ቢፈጽሙ ባይፈጽሙ የሚያመጣላቸው ለውጥ አልነበረም፡፡ 


በግብፅና በሱዳን መካከል ዓባይ ወንዝን በተመለከተ የተደረጉ ወሳኝ የውል ስምምነቶች

1.    የ1929 ውል

ይህ ውል በእንግሊዝና እሷ በምታስተዳድራት ግብፅ መካከል የተፈረመ ነው፡፡ ውሉ በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ሁልጊዜ ከሚጠቀሱት ሰነዶች አንዱ ሲሆን የሚከተለውን ዓብይ ምዕራፍ ያዘለ ነው፡፡ የግብፅ አስተዳደር ከዚህ በፊት ያደረገው ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በቀር በናይል ወንዝና በቅርንጫፎቹ (ነጭና ጥቁር ዓባይ ለማለት ነው) እንዲሁም ናይል በሚመነጭባቸው ሐይቆች ላይ (ቪክቶሪያ ሐይቅና ጣና ሐይቅ) ማናቸውም የመስኖ፣ ወይም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ መገንባትና ሌሎች ሥራዎችን ማካሄድ አይቻልም፡፡ ይህ ውል ተፈጻሚ የሚሆነው በእንግሊዝ ሥር በሚተዳደሩ አገሮች ላይ ሆኖ የወንዙን ውኃ ጥራት በማጥፋት ወይም ፍሰቱን በማስተጓጐል የግብፁን ጥቅም የሚጎዳ ሥራ የተሠራ እንደሆነ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ግንባታዎች የሚሠሩ ቢሆን እንኳን አስገዳጅ ሁኔታ ቢፈጠር ሥራዎቹ ምን ጊዜም በግብፅ ቁጥጥርና ክትትል መካሄድ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ በተለይ የሱዳን አስተዳደር ባለሥልጣናት እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች ከመጀመራቸው በፊት ግብፅን በቅድሚያ ማስፈቀድ እንዳለባቸው ስምምነቱ ይገልጻል፡፡ 

የ1929 የናይል ወንዝ ስምምነት እንግሊዝ ከግብፅ ጋር የነበራትን ልዩ ትስስር በግልጽ ያሳየ ሲሆን፣ ሱዳንም የግብፅን የውኃ ፍላጐት እስካልነካች ድረስ ትራፊዋን ለማግኘት መጠነኛ መብት ሰጥቷታል፡፡ ኬንያና ኡጋንዳ ሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮችና የአንግሊዝ ቅኝ ሥር የነበሩ ሲሆን፣ እስከዛሬም ድረስ በ1929 ውል ተቀዳደው ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን እንግሊዝ ጣናንም፣ ቪክቶሪያንም፣ ናይልንም ሁሉንም ግብፅ ብቻ በብቸኝነት እንዳሻት እንድትጠቀምባቸው ለምን ፈለገች? ጂኦ ፖለቲካዊ ምክንያትዋ ምን ነበር? አንደኛ የግብፅ ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ አውሮፓን፣ አፍሪካንና እስያን የምታገኛኝ በመሆንዋ፣ ሁለተኛ ፈረንሣይ በሰሜን አፍሪካና በምሥራቅ አቅጣጫም ሶሪያንና ሊባኖስን በቅኝ ገዢነት ታስተዳድር ስለነበር ለግብፅ የተለየ ትኩረትና ድጋፍ በማድረግ እንግሊዝ የታሪካዊ ጠላትዋን የፈረንሣይን ኃይል ማዳከም ወይም ቢያንስ የኃይል ሚዛን መጠበቅ ስላስቻላት፣ ሦስተኛ ከግብፅና ከሱዳን በቀር በሌሎቹ የናይል ወንዝ ተፋሰስ አገሮች ላይ የነበራት የቅኝ ገዥነት ሥልጣን በማንኛውም ጊዜ በአካባቢው ይንቀሳቀሱ ከነበሩት ኃያላን አገሮች ማለትም ጀርመን፣ ቤልጂየምና ኢጣሊያ በኩል ቁርቁስ ሊነሳ የሚችልበት አጠራጣሪ ሁኔታ የነበረ በመሆኑ፣ አራተኛ ግብፅ ቁልፍ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ የነበረው (አሁንም ቢሆን ጠቀሜታው እንዳለ ነው) ስዊዝ ቦይ ባለቤት በመሆንዋ ስለሆነም ግብፅ በእርሻ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ግንባታና በአግሮ ኢንዱስትሪ ማበልፀግ ለዚህም የናይልን የማያቋርጥ ፍሰት ለግብፅ ማረጋገጥ የእንግሊዝና የግብፅን ትስስር ዘላቂነት እንዲኖረው ስለሚያደርገውና አምስተኛ ከሁሉም በላይ ደግሞ የግብፅ ሜዳማ በረሃዎች ከናይል ወንዝ በሚቀርብላቸው ንፁህ ውኃና ለም አፈር ሰፋፊና ዘመናዊ የእርሻ ሥራዎችን ለማከናወን ምቹ በመሆናቸው፣ የእንግሊዝ ካፒታሊስቶች ፋብሪካዎቻቸው ጥሬ ዕቃ ለማቅረብ ግብፅን ማልማት ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ 


የ1959 ውል

እ.ኤ.አ. በ1959 ግብፅና ሱዳን ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ ሊወጡ ሲሉ በእንግሊዝ አፈራራሚነት በሁለቱ አገሮች የተፈረመ ውል አለ፡፡ ውሉ የዓባይን ወንዝ አጠቃቀም ከፍ ወዳለ ደረጃ በማድረስ ከ1929 ውል አንስቶ በየጊዜው ውኃ አነሰኝ በማለት ስታጉረመርም የነበረችውን ሱዳንን በመጠኑም ቢሆን እርካታ የሰጣት ውል ነው ለማለት ይቻላል፡፡ የ1959 የናይል ወንዝ አጠቃቀም ዓበይት ስምምነቶች የሚከተሉት ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ 


1.  በ1929 በእንግሊዝ መንግሥትና በግብፅ አስተዳደር መካከል የተፈረመው ስምምነት (ስምምነቱን ማስታወሻ በመላላክ ነበር የፈጸሙት) ስለ ዓባይ ወንዝ አጠቃቀም በከፊል ብቻ የተመለከተ መሆኑን ለማስታወሻ የ1959 ዓ.ም. ውል ርዕስ ‹‹የናይልን ውኃ ሙሉ በሙሉ በጥቅም ላይ ስለማዋል›› የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ 

2.  የ1959 ውል የ1929ን ውል ሳይሽርና ሳይሸራርፍ እንዳለ ያስቀጥላል፡፡ 

3. ውሉ ግብፅና ሱዳን በዚያ ጊዜ ሲጠቀሙበት የነበረውን ዓመታዊ የውኃ መጠን እንደተጠበቀ ያፀድቃል፡፡ ስለዚህም ግብፅ በዓመት 48 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ልትጠቀም፣ ሱዳን በበኩሏ በዓመት ስድስት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ልታስቀር በእንግሊዝ አፈራራሚነት ሁለቱም አገሮች ተስማምተዋል፡፡ 

4. በውሉ መሠረት ሱዳን ከዚያ በፊት ወደ ግጭት ሊያደርሳት የነበረውን የአስዋን ግድብ ግንባታ የፈቀደች ሲሆን፣ ሱዳንም የሮዘሪስን የውኃ ማጠራቀሚያ ግድብ፣ እንዲሁም ከድርሻዋ በላይ እስካልሄደች ድረስ ሌሎች አነስተኛ ግድቦችን ልትሠራ እንደምትችል ግብፅ ተስማምታለች፡፡ 

5.   ግብፅ ለምታካሂዳቸው የመስኖ ማስፋፊያ ሥራዎች ሱዳን በዓመት በአማካይ 1.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በብድር ለመስጠት (በገንዘብ የሚመለስ) ተስማምታለች፡፡ 

6. ከሁለቱም አገሮች በእኩል ቁጥር የተሾሙ አባላት የሚገኙበት አንድ የጋራ ቋሚ ቴክኒካል (የሙያተኞች) ኮሚቴ ተመሥርቷል፡፡ 

7. በዚህ የ1959 ስምምነት ውስጥ የአንባቢያንን ትኩረት የሚስበው አንቀጽ ሌሎቹ የናይል ወንዘ ተፋሰስ አገሮች የይገባናል ወይም ይመለከተናል ጥያቄ በተናጠል ወይም በኅብረት ቢያነሱ፣ ግብፅና ሱዳን ምን ዕርምጃዎችን ሊወስዱ እንደሚችሉ የሰፈረው ነው፡፡ በዚህ መሠረት፣ 

7.1 ሌሎች የናይል ወንዝ ተጋሪዎች በሚያነሱት ጥያቄ ምክንያት ድርድር ማድረግ አስፈላጊ ሲገኝ፣ ቋሚ የቴክኒክ ኮሚቴው በጥናት የሚደርስበትን መሠረት በማድረግና ሁለቱም መንግሥታት በቅድሚያ በመመካከር አንድ አቋም ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ይህን አቋም ይዞ በመቅረብ ኮሚቴው ጥያቄ አለኝ ከሚለው አገር መንግሥት ጋር ይነጋገራል፤ ይደራደራል፡፡ ድርድሩን ተከትሎ ከግብፅና ሱዳን ውጭ ያሉት የተፋሰሱ አገሮች በወንዙ ላይ የልማት ሥራዎችን ለማካሄድ ስምምነት ላይ የደረሱ እንደሆነ፣ ቁሚ ኮሚቴው የእነዚያን አገሮች የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት በማነጋገር ስለልማት ሥራዎቹ የአፈጻጸም ቴክኒካዊ ጉዳዮች፣ እንዲሁም ጥገናን በተመለከተ ዝርዝር ስምምነት ላይ ይደርሳል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በእነዚህ ነጥቦች ላይ ከተስማማ ኮሚቴው ራሱ የልማት ሥራዎቹን ሒደት ይቆጣጠራል፡፡

7.2     ከሁለቱ አገሮች ውጭ ያሉት የተፋሰሱ አገሮች በናይል ወንዝ ላይ ድርሻ እንዲኖራቸው ጥያቄ የሚያነሱ በመሆኑ፣ ሁለቱ አገሮች የተነሱትን ጥያቄዎች በማጥናት አንድ አቋም ይይዛሉ፡፡ በጥናቱ መሠረት የናይልን ወንዝ ውኃ ለአንዱ አገር ወይም ለሌላው ማካፈል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ ከአስዋን ግድብና ከመሳሰሉት በመቀነስ ከሁለቱም አገሮች ድርሻ ላይ በእኩል ተቀንሶ ለጠያቂዎቹ አገሮች እንዲደርሳቸው ይደረጋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ድርሻ እንዲያገኙ ጠይቀው ከተፈቀደላቸው አገሮች የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ሁኔታዎችን በማመቻቸት በተፈቀደው የውኃ መጠንና አጠቃቀም ዙሪያ ኮሚቴው ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋል፡፡

አንባቢያን ሊገነዘቡ እንደሚችሉት ውሉ ኢፍትሐዊ ብቻ ሳይሆን ጦር የሚያማዝዝ ነው፡፡ ውኃ ጠይቀን የምንጠቀምበትን እንኳን በጋራ ኮሚቴው ቁጥጥርና ክትትል ሥር ነው የምንጠጣው፡፡ ግንባታ ቢፈቀድልንም በኮሚቴው ቁጥጥርና ክትትል ይደረግብናል፡፡ ሱዳን ድንገት ከሌሎቹ የተፋሰስ አገሮች ጋር ብሔራዊ ጥቅሟን አገናዝባ እንዳትወግን በማናቸውም ጥያቄዎች ላይ ከግብፅ ጋር በመነጋገር አንድ ዓይነት አቋም መያዝ እንዳለባት ትገደዳለች፡፡ ተፈጥሮ የለገሰንን ፀጋ ተከፋፍለንና ተሳስበን እንዳንጠቀምበት የጌቶችና የለማኞች ግንኙነት ተመሥርቷል፡፡ አፍሪካውያን ይህ ውስብስብ ችግር ባስከተለው የውል ስምምነት የተነሳ ወደ ግጭት ብናመራ የምንጎዳው እኛው አፍሪካውያን ነን፡፡ ቅኝ ገዥዎች እንደ ልማዳቸው ቦምብ ቀብረውብን ሄደዋል፡፡ ውሉ ዋናዋን የወንዙ ባለቤት ኢትዮጵያን እንደባይተዋር ያገለለ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ ውሉ እንደማይመለከታትና እንደማትቀበለው ተቃውሞዋን በየጊዜውና በየመድረኩ ስታቀርብ ቆይታለች፡፡ ለአጠቃላይ መፍትሔ ዘላቂ ሰላምና የጋራ ዕድገት ሲባል ይህ የቅኝ ገዥዎች ውል መቀደድ አለበት፡፡ ከዚህ በመለስ የሚደረጉ ንግግሮች ችግሩን ለሌላ ጊዜ ከማስተላለፍ ውጭ ውጤት የላቸውም፡፡ የተፋሰሱ አገሮች በዚህ በኩል የጀመሩት እንቅስቃሴ ሳይቀዘቅዝ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ 


ዓለም አቀፍ ሕግ

ዓለም አቀፍ ሕግ ሲባል ሰፊ ትርጉም ያለው ነው፡፡ አሁን ለያዝነው የድንበር ተሻጋሪ ወንዝ (ናይል) ጉዳይ ግን ዓለም አቀፍ ሕግ ማለት፣ 


1. መንግሥታት እርስ በርስ ለብዙ ዓመታት በመሠረቱት ግንኙነት በተሻጋሪ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ ያዳበሩት እንደ ሕግ የሚቆጥሩት አሠራር አለ፡፡ ይህም ልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ (Customary International Law) ይባላል፡፡ በልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ማንኛውም የተፋሰስ አገር ወንዙን ለጋራ ጥቅም ፍትሐዊና አግባብ ባለው መንገድ  (In a reasonable and equitable manner) መጠቀም እንዳለባቸው ያስገድዳል፡፡  


2. በበርካታ አገሮች የሚፀድቁ ነገር ግን ገና በእያንዳንዱ አባል አገር ያልተፈረሙና ሕግ ይሆኑ ዘንድ በፓርላማዎቻቸው ያልፀደቁ ስምምነቶች (International Conventions) በተለያዩ ጊዜያት እየዳበሩ የመጡ ሲሆን፣ ከፍ ሲል ከጠቀስነው ልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ ብዙም ሳይርቁ ፍትሐዊና አግባብ ያለው አጠቃቀም የሚለውን መርህ ይዘው፣ በሌላ በኩል ደግሞ የወንዙን ብዝኅ ሕይወታዊ ተፈጥሮ አጠባበቅ ላይ በርከት ያሉ ድንጋጌዎችን ያሰፈሩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ 

3. ሦስተኛው የዓለም አቀፍ ሕግ ገጽታ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሚያቋርጧቸው አገሮች ወንዞቹን በተመለከተ በመካከላቸው እንደ ሕግ ሆኖ የሚፀና፣ ሌሎቹ ግን (በግልጽ ካልተቀበሉት በቀር) የማይመለከታቸው ስምምነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ስምምነትም በፈራሚዎቹ አገሮች መካከል እንደ ዓለም አቀፍ ሕግ ሆኖ ይሠራል፡፡ 

4. ተሻጋሪ ወንዝ ማለት ከአንድ አገር ተነስቶ የሌላ/የሌሎችን አገሮች ድንበር የሚያቋርጥ ዓለም አቀፍ ወንዝ ሲሆን፣ የከርሰ ምድር ውኃውንና ገባር ወንዞቹን አይመለከትም (አያካትትም)፡፡ ፍትሐዊና አግባብ ባለው መንገድ (In a reasonable and equitable manner) የሚለው የዓለም አቀፍ ሕግ መርህ ይዘን የተጓዝን እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ አቋም ሙሉ በሙሉ በዓለም አቀፍ ሕግ የሚደገፍ መሆኑን፣ የግብፅና የሱዳን አቋም ደግሞ ከዓለም አቀፍ ሕግ መርህ ያፈነገጠና ወደ ግጭት ሊያመራ የሚችል ግትር አቋም መሆኑን ለማየት ይቻላል፡፡

ለአብነት ያህል ‹‹ከመጓጓዣ አገልግሎት ውጭ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ጥቅም ላይ ስለማዋል›› በሚል ርዕስ በ1997 የፀደቀ አንድ ዓለም አቀፍ ስምምነት (ኮንቬንሽን)፣ የተፋሰስ አገሮች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በድንበሮቻቸው ክልል አግባብ ባለውና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ (In a reasonable and equitable manner) እንዲጠቀሙ ያስገድዳል፡፡ አግባብ ያለውና ፍትሐዊ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ውኃ አጠቃቀም ሥርዓት ከአገሮቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሳ የሚኖረው የውኃ ክፍል ተጨባጭ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አስገዳጅነት፣ እንዲሁም የወንዙን ውኃ ለመንከባከብ፣ ለመጠበቅ፣ ለማልማትና ውኃውን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው፡፡

በተለይም ማንኛውም የተፋሰሱ አገር በሌላው አገር ጥቅም ላይ ከፍ ያለ ጉዳት እንዲደርስና በመሳሳብ ሳይሆን በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ የውኃ አጠቃቀም ሥርዓት እንድታበጅ ኮንቬንሽኑ ያስገድዳል፡፡ በወንዙ አጠቃቀም የተነሳ አንድ አገር በሌላው ጥቅም ላይ ከፍ ያለ ጉዳት አድርሶ እንደሆነ ግን ጉዳቱን ለመጠገን ወይም ለመቀነስ ካሳ እንዲሰጥ ተቀራርቦ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ ኮንቬንሽኑ እያንዳንዱ የተፋሰስ አገር የጋራ በሆነው የተፈጥሮ ሀብት ዙሪያ ስለሚያከናውነው ማናቸውም የልማት ተግባር ከሌሎቹ አገሮች ጋር በየጊዜው እየተቀራረቡ ሐሳብ መለዋወጥ፣ መረጃና መግለጫ መሰጣጠት እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ አንድ የተፋሰስ አገር በወንዙ ላይ የሌላውን ተፋሰስ አገር ጥቅም ከፍ ባለ ደረጃ የሚጎዳ ዕቅድ ከመተግበሩ በፊት ቴክኒካዊ መረጃዎችን ለዚያ አገር በወቅቱ መላክ ይኖርበታል፡፡ ተቀባዩ አገርም በዕቅዱ ላይ የደረሰበትን ግምገማ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ምላሹን መላክ ይኖርበታል፡፡ 

የግምገማ ውጤቱን  በዚህ ጊዜ ውስጥ ያልላከ እንደሆነ ፕሮጀክቱን እንደተቀበለው ተቆጥሮ ሥራው ይቀጥላል፡፡ ቅሬታውን በጽሑፍ የላከ እንደሆነ ግን ድርድር ይጀመራል፡፡ ዕቅዱ የሌላውን /የሌሎቹን አገሮች በወንዙ የመጠቀም መብት ላይ ከፍ ያለ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑ የተረጋገጠ እንደሆነ፣ በጋራ ስምምነት ሥራው ለጊዜው እንዲቆም ይደረጋል፡፡ ይህ ከመደረጉ በፊት ግን ሁልጊዜ በአንድነት መነጋገርና መግባባት መቅደም እንደሚኖርበት የተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ዓለም አቀፍ ሕግ ይደነግጋል፡፡ 


ማንኛውም የተፋሰስ አገር በሌላው አገር የሚሠሩ ሥራዎች ከፍ ያለ ጉዳት ያደርሱብኛል ብሎ ሲያምን ጉዳዩን ለውይይት የማቅረብ፣ ከፍ ሲልም ወደ ዓለም አቀፍ የዳኝነት አካል የመውሰድ መብት ይኖረዋል፡፡ ማንም የተፋሰስ አገር በድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ላይ የሞኖፖል ሥልጣንም ሆነ መብት ስሌለው ቅሬታ ሲያነሳ ቅሬታውን በድርድር ወይም በክርክር መጨረስ ይኖርበታል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቀባይነትን በማግኘት ላይ የሚገኘው የአካባቢና የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ዓለም አቀፍ ሕግ የተፋሰስ አገሮች ውሱን የሆነውን የወንዝ ውኃ ለመሻማት ከሚያደርጉት አጥፊ ውድድር እንዲታቀቡ ይማፀናል፡፡ የእያንዳንዱ አገር ጥቅምና የውኃ ፍላጎት ከአካባቢያዊና ከብዝኃ ሕይወታዊ ጥቅም በላይ መታየት እንደሌለበት ዓለም አቀፍ ሕግ ያስጠነቅቃል፡፡ ልዩ ልዩ ዝርዝር ድንጋጌዎችንም አስፍሯል፡፡ ስለዚህም የውኃ ብክለትን፣ ብክነትን፣ ወንዞችን ከጨረራማና ኑክሌር ፍሳሾች፣ ከኢንዱስትሪ ተረፈ ምርት ዝቃጮችና ኬሚካላዊ ጭሶች ነፃ እንዲሆኑ የተፋሰስ አገሮች ተደጋግፈው እንዲሠሩ ዓለም አቀፍ ሕግ ያሳስባል፡፡ (1992 ሄልሲንኪ ላይ የፀደቀውን ኮንቬንሽን ማየት ይቻላል) 

ግብፅና ሱዳን ግን ዓባይን ለእነሱ ብቻ እንደተፈጠረ የፈጣሪ ስጦታ አድርገው ስለሚያዩት፣ ቅኝ ገዥዎችም ጉዳዩን አወሳስበውት በመሄዳቸው፣ ይልቁንም የዓባይን ምንጭ ጣናን ለመቆጣጠር ተደጋጋሚ ወረራዎችን ፈጽመው ዓላማቸው ስለከሸፈባቸው ዓለም አቀፍ ሕጉን እየተቃወሙ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከብሔራዊ ጥቅሟ አኳያ ብቻ ሳይሆን ከላይ እንደተመለከትነው ከዓለም አቀፍ ሕግጋትም አንፃር ጥያቄዋ ፍፁም ፍትሐዊና ትክክለኛ ነው፡፡ 


ማጠቃለያ

ዓባይ ወንዝ በተለይም ለግብጾች ለም የእርሻ መሬት የንፁህ ውኃ ምንጭ ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ የወርቅና የግንባታ ማቴሪያሎች አቅራቢም ሆኖ ዘልቋል፡፡ 

‹‹የምን ውኃ ብቻ የምን አፈር ብቻ፣ 

ወርቅም እናፍሳለን በፍየል ስልቻ፤››

የዓባይ ውኃ የመቶ ዓመታት መጠኑ (ከፍታና ዝቅታ) በግብፆች የተመዘገበ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የክረምት ወራት ዝናብ አጥሮ የወንዙ መጠን በቀነሰ ቁጥር የግብፅ መስኖዎች እንዲሁ ይደርቃሉ፡፡ በአገሪቱ ችጋር ገብቶ የፖለቲካ አለመረጋጋት በየጊዜው ያጋጥም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ዓባይን ማስቆም እንደምትችል ከጥንት ጀምሮ በግብፅ ውስጥ የመላምት ሥጋት አለ፡፡ ኢትዮጵያውያንና ግብፃውያን (ኑብያን ጨምሮ) የአንድ ወንዝ፣ እምነትና ሥልጣኔ ውል ቢሆኑም ከመቀራረቡ ይልቅ ልዩነቱ እየሰፋ በየጊዜው አላስፈላጊ ጦርነቶችን አካሂደዋል፡ ግብፃውያን ‹‹ኢትዮጵያ ዓባይን ብትነካ አስቀድመን እንወራታለን›› ሲሉ፣ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው ‹‹የግብፅን በረሃዎች በደም እናጥለቀልቃለን፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ተገቢ ያልሆነ ውጥረት በከፊል ግብፆች ከሚያሳድሩት መሠረት የሌለው ሥጋት የሚመነጭ ነው፡፡ ይልቁንም ግብፆች የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዳሉት ‹‹ወደ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ›› በመውጣትና በቅኝ ገዥዎች ከተቀመጡት ውሎች ተላቀው፣ በፍፁም አፍሪካዊ እምነት በዓለም አቀፍ ሕግ ለመመራት ቢወስኑ የሚበጃቸው ይመስለኛል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Criminalizing and Prosecuting Illicit Enrichment i...
ለግብር ከፋይነት የሂሳብ መዝገብ ስለመያዝ እና ገቢን ስለማስታወቅ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 23 April 2024