- Details
- Category: Property Law
- Hits: 10225
እንደሌሎች መሰረታዊ መብቶች ሁሉ ለንብረት መብት ከፍተኛ ግምት የሰጠው የኢፊዴሪ ሕገ መንግስት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ እንደሚከበርለት፣ በሕግ መሰረት ንብረት የመያዝና በንብረት የመጠቀም፣ የሌሎች መብት ሳይቃረን ንብረቱ የማስተላለፍ መብቶችን ያጐናፀፈው ሲሆን የግል ንብረት ባለቤትነት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ብቻ ለንብረቱ ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ በቅድሚያ በመክፈል የግል ንብረትን ለመውሰድ እንደሚችል ነው መገንዘብ የሚቻለው።
የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 40 የግል ንብረት ሲል እንደ ዓላማ አድርጎ የወሰደው ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ ወይም ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ኢትዮጵያዊ ማሕበራት ወይም ሌሎች በሕግ በተለየ በጋራ የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው ማህበረሰቦች በጉልበታቸው ፣ በመፍጠር ችሎታቸው ወይም በካፒታላቸው ያፈሩት ተጨባጭ የሆነና ተጨባጭነት ጠባይ ሳይኖረው ዋጋ ያለው ውጤት መሆኑን ይገልፃል። ከዚህ ድንጋገ መገንዘብ እንደሚቻለው ሰዎች በሶሰት አግባቦች ንብረት ማፍራት የሚችሉ ሲሆን፤
ሀ/ ጉልበታቸው ተጠቅመው የሚያፈሩት፣
ለ/ በትምህርት ወይም በልምድ በሚያገኙት እውቅና ክህሎት ተጠቅመው የሚፈጥሩት ነገር፣
ሐ/ ካፒታላቸውን አፍስሰው ወይም ኢንቬስት አድርገው የሚያገኙት ትርፍ ወዘተ ሊሆን ይችላል።
እነዚህ የሃብት ማግኛ መንገዶች የሚፈጥሩት ወይም የሚያፈሩት ንብረት ተጨባጭነት ያላቸው (corporeal things) ወይም የተጨባጭነት ጠባይ የሌላቸው (incorporeal things) ሊሆኑ እንደሚችሉም ሕገ መንግስቱ በተጠቀሰው አንቀፅ ስር በግልፅ ያስቀመጠው ጉዳይ ነው። (አንቀፅ 40(2) ይመለከተዋል) ።
1.1 የንብረት ትርጉም እና ታሪካዊ አመጣጥ
ንብረት ምን ማለት ነው የሚለውን ጥያቄ የንብረት ሕግ ምንነት ከማየታችን በፊት መልስ ማግኘት ያለበት ጥያቄ ነው። ንብረት የሚለው ቃል በእንግሊዝኛው “Property” እየተባለ የሚገለፀው ሆኖ “ Proprius” ከሚለው ላቲን ቃል መምጣቱ ይነገራል። proprius የራስ የሆነ ነገር ማለት ነው። የኢትዮያ ፍትሃብሄር ሕግ ስለንብረት ምንነት ያስቀመጠው ትርጉም ባይኖርም ከተለያዩ ፅሑፎችና ስለንብረት ሕግ ከሚደነግገው የፍትሃብሄር ሕግ መረዳት እንደሚቻለው ፤ንብረት ማለት፦
ሀ/ ሌሎችን በማይጨምር ሁኔታ አንድ ነገር በባለቤትነት ሊያዝ የሚችል (appropriable) መሆን አለበት፣
ለ/ ይህ በባለቤትነት ሊያዝ የሚችል ነገር ጠቃሚነት ያለው (useful) መሆን አለበት። ይህ ማለት ግን ሁሉም ጠቃሚ ነገሮች የንብረት ትርጉም ይሰጣቸዋል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ፦ ፀሓይ፣ አየር /ወደ ሌላ ሓይል ካልተቀየረ በስተቀር/
ሐ/ ያ ነገር ዋጋ ያለው ወይም ዋጋ የሚያወጣ መሆን አለበት። ይኸውም በገንዘብ ሊገዛ የሚችል ወይም በሌላ ንብረት ሊለወጥ የሚችል መሆን አለበት (The thing must have pecuniary value) ።
በአጠቃላይ ንብረት ማለት በባሌበትነት ሊያዝ የሚችል፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታና ዋጋ ያለው ነገር ማለት ነው።
እንደ ሌሎች ሕጎች የንብረት ፅንሰ-ሓሳብም ቢሆን ሊያድግ የቻለው በሮማዊያን የሕግ ባለሙያዎች አማካኝነት መሆኑን ፅሑፎች ይጠቁማሉ:: በሮማዊያን የሕግ ስርዓት ከፍተኛ ግምትና ዕውቅና ሲሰጠው የነበረ የግል ንብረትን(private property) ነው:: የሕግ ባለሙያዎች ስለ ግል ንብረት /ባለሃብትነት/ የተዉት ትርጉም (definition) ባይኖርም የግል ንብረትን የሚመለከት ፅንሰ-ሓሳብ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የነበራቸውና ትልቅ ስራ የሰሩ ግን እነዚህ የሕግ ባለሙያዎች እንደነበሩ ነው:: ይሁን እንጂ ስራው ረዥም ግዜ የጠየቀና ቀስ በቀስ እየሰፋና እየነጠረ የመጣበት ሁኔታ እንደነበረ ነው:: የሕግ ባለሙያዎቹ ለመጀመሪያ ግዜ መረሬት የመንግስትና የጋራ (communual) ንብረት መሆኑን እና የግል ንብረት ምንነት ለያውቁ እንደቻሉ ነው ከተለያዩ ፅሑፎቸ መረዳት የሚቻለው::
የሮማዊያን ሕግ (The XII Tables) ስለንብረት ያካተተው ነገር ቢኖር ዶሚኔም (dominium) በሚል የሚታወቅ ሆኖ በቤት ውስጥ የሚገኙትን ሁሉም የንብረት ዓይነቶች የሚመለከት የነበረ ሲሆን የሁዋላ ሁዋላ ግን ንብረት የሚለው ፅንሰ-ሓሳብ ለብዙ ነገሮች ተፈፃሚ እንዲሆን እየተደረገ የመጣበት ሁኔታ እንደነበረ ነው::
በጥንታዊ የሮማዊያን ግዜ መሬት ሙሉ በሙሉ በመንግስት ይዞታ ስር የነበረ ሲሆን ቀደም ሲል ጎሳዎች የሁዋላ ሁዋላ ደግሞ ቤተሰብ በጊዚያዊነት እየተሰጣቸው በይዞታቸው ስር አድርገው ይጠቀሙበት እንደነበርም ፅሁፎች ይጠቁማሉ::
ከቅደም ተከተል አንፃር ሲታይም መጀመሪያ ባርያና ተንቀሳቃሽ ነገሮች እንደንብረት ይቆጠሩ አንደነበርና ቀጥሎም መሬትና ሌሎች የማይንቀሳቀሱ ነገሮች እነደንብረት መቆጠር እንደጀመሩ ነው መገነዘብ የሚቻለው:
የንብረት ሕግ ትርጉም
የንብረት ሕግ ማለት የንብረት መብት እንዴት እንደሚገኝ፣ እንዴት እንደሚተላለፍ፣ እንዴት እንደሚቋረጥ፣ የባለሃብትና የባለይዞታ መብቶች ምን እንደሆኑ … ወዘተ የሚገዛ ሕግ ሆኖ በአንድ አገር ኢኮኖሚ /ምጣኔ ሃብት/ ሁኔታ የሚኖረው ቦታና የሚያደርገው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።
የንብረት መብት በጣም ትልቅ እንደመሆኑ መጠን በተለያዩ ሕጎች ጥበቃ የሚደረግለት ነው። በፅሑፉ መግቢያ እንደተመለከተው የአንድ አገር የበላይ ሕግ በሆነው ሕገ መንግስት አማካኝነት መሰረታዊ የሆኑትን የንብረት መብቶች ተለይተው ይደነገጋሉ፣ በወንጀል ሕግ ውስጥም ንብረትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በማካተት በእነዚህ ንብረቶች ላይ ወንጀል የሚፈፅሙ ሰዎች እንዲቀጡ ይደረጋል። ይኸውም በኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ በስድስተኛው መፅሓፍ ላይ በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በሚመለከት ከአንቀፅ 666-684፣ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ከአንቀፅ 685-688፣ በሰው ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ ከአንቀፅ 689-691 እንዲሁም በንብረት መብቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በሚመለከት ደግሞ ከአንቀፅ 692-705 በዝርዝር ተመልክተው ይገኛሉ።
1.3 ንብረት በሚመለከት የሚራመዱ አመለካቶች /አስተሳሰቦች/
1.3.1 አዳም ሰሚዝ (Adam Smith theory) ፦ ለግል ባለቤትነት ከፍተኛ ግምት ሊሰጠው ይገባል ከሚል እምነቱ የመነጨ ሕግ አውጪ አካል ለግል ባለሃብትነት ትልቅ ግምት መስጠት አለበት ይላል።
1.3.2 ማርክሲስት ሰነ-ሓሳብ፦ የሶሻሊስት ስነ ሓሳብ የሚያራምድ እንደመሆኑ መጠን ህዝባዊ ባህሪ ላላቸው የንብረት ዓይነቶች ትልቅ ግምትና ጥበቃ ሊሰጣቸው ይገባል። እንዲህ ከተደረገ ብቻ ነው የግል ባለቤትና የካፒታሊስት ስርዓት ሊከስሙ የሚችሉ ይላል።
1.3.3 ሕጋዊ ንድፈ ሓሳብ (Legal Doctrine) ፦ ይህ ሓሳብ መሰረት የሚያደርገው የሕግ ሓይል በመሆኑ ይህ ንብረት በግል ባለቤትነት ይህ ደግሞ በጋራ ወይም በህዝብ ባለቤትነት ሊያዙ ይችላሉ ብሎ በሚያወጣው ሕግ መወሰን ያለበት ሕግ አውጪ ኣካል ነው ይላሉ።
1.3.4 ማሕበራዊ ጠቀሜታ (Social utility) መሰረት ያደረገ፦ አንድ ንብረት በግል ወይም በጋራ ባለቤትነት ሊያዝ የሚችል መሆኑን አለመሆኑን የሚወስነው ራሱ የንብረቱ ባህሪ /ተፈጥሮ/ ነው። ከግለሰብ ይልቅ ለህዝቡ የላቀ ጥቅም የሚሰጥ ከሆነ በጋራ ባለቤትነት የሚያዝ ይሆናል። በሕግ ውስጥ እንዲካተት ማድረግ እንጂ ሌላ ፋይዳ የለውም ይላሉ።
ሌሎች የሚራመዱ አመልካቶች፦
ስራን መሰረት ያደረገ ንድፈ ሓሳብ (Labour Doctrine) ፦ ይህ አስተሳሰብ የንብረት ባለሃብት መሆን የሚቻለው በስራ ነው። ሰርተህ ያገኘኸውን ነገር ባለቤት ትሆናለህ። በሌላ አባባል ማንኛውም ሰው ሰርቶ የሚያገኘውን ምርት፣ የሚያካብተውን ሃብት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚና ባለቤት ይሆናል። ይህ እምነት የመነጨው ደግሞ ካፒታል የስራ ውጤት ነው ከሚለው መሰረተ ሓሳብ ነው። በዚህ አስተሳሰብ እንደ ዋነኛ ሕግ (rule) ተደርጎ የሚወሰደው ስራ ሊበረታታ እንደሚገባና የንብረት ክፍፍሉም ምርታማነት ለማሳደግ ለሚደረገው ከፍተኛ ጥረት ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት ነው።
የሃይማኖት እምነት መሰረት ያደረገ ንድፈ ሓሳብ (Theologician Doctrine) ፦ ንብረት በግል ወይም በጋራ ባለቤትነት ሊያዝ የሚችለው በእግዚኣብሄር ፈቃድ ነው። ሕግ አውጪውም መከተል ያለበት የእግዚኣብሄር ትእዛዝ ነው ይላል።
ተፈጥሮ መሰረት ያደረገ ንድፈ ሓሳብ (Naturalist theory) ፦ ይህ አስተሳሰብ የንብረት ባለቤትነት መብት የሚገኘው ከተፈጥሮ ነው። ተፈጥሮ ራሱ ንብረት እንዲኖረን ወይም እንዳይኖረን ይወስናል። የንብረት ባለሃብትነት የተፈጥሮ ፀጋ ነው ይላሉ።
አንድ ነገር እጅ ማድረግ መሰረት ያደረገ ንድፈ ሓሳብ (the occupation theory) ፦ ይህ ንድፈ ሓሳብ ከጥንት ጀምሮ የነበረና እስካሁን ድረስም ለግል ባለሃብትነት እንደ ትልቅ መከላከያ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን፤ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ንብረቱ በእጁ /በቁጥጥሩ ስር/ አድርጎ የሚገኝ ሰው ለመጀመርያ ጊዜ ንብረቱ ያገኘና እጅ ያደረገ ነው ተብሎ ስለሚገመት ነው።
ለምሳሌ፦ ዓሳን በማጥመድ፣ እንስሳን በወጥመድ በመያዝ የሚገኝ ሃብት መጥቀስ ይቻላል።
ኢኮኖሚያዊ ንድፈ ሓሳብ (Economic theory) ፦ ምጣኔ ሃብት መሰረት ያደረገ የግል ባለሃብትነት መኖር ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ምክንያት ይሆናል። የተሳካለትና የላቀ ትርፍ የሚያገኝ የንግዱ ዓለም ሰው ውጤታማ የሆነ የገበያ ፍላጐት (demand) የማየት ችሎታው ከፍተኛ ነው። እንደዛ ዓይነት ችሎታ (power) የማይኖረው ከሆነ ግን ለድርጅቱ መውደቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
የግል ባለሃብትነት ፍፁም (absolute) አይደለም መሆንም የለበትም። ስለሆነም የግለሰብ መብት ውጤታማ ለማድረግና የሌሎች ጥቅም እንዳያውክ መንግስት ጣልቃ መግባት አለበት። አንድ ሰው ፍፁም (absolute) በሆነ ሁኔታ እንደፈለገው ንብረቱ ጫጫታ በሚፈጥር፣ መጥፎ ሽታ በሚያስከትል ወይም እሳት በሚያስነሳ ኣኳኋን ወዘተ… የሚጠቀምበት ከሆነ ሃብት/ንብረት የሚባለው ነገር ዋጋ ቢስ እንዲሆን ያደርገዋል። ስለዚህ የንብረት መብት በእውነት ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ በንብረት ባለቤቶች ላይ አንዳንድ ገደቦች (restrictions) ወይም ኣዎንታዊ ግዴታዎች በሕግ ሊጣልባቸው ይገባል።
- Details
- Category: Sentencing and Execution
- Hits: 29210
የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት ቅጣት የሚወሰንበት ሁኔታ
በሰንጠረዡ መሰረት ቅጣትን ለመወሰን በመጀመሪያ የሚነሳው መሰረታዊ ጥያቄ በዚህ ሰንጠረዥ መሰረት ቅጣትን እንዴት እንወስናለን የሚለው ነው፡፡ ማለትም፣
መነሻ ቅጣት እንዴት እንወስናለን?
በማክበጃዎች መሰረት እንዴት እንወስናለን ?
በማቅለያዎች መሰረት እንዴት እንወስናለን ?
የሚሉት ናቸው፡፡
የወንጀል ደረጃዎችን እንደወንጀሉ ከባድነት መለየት
በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 88(2) ዳኛው ቅጣትን ሲወስን የወንጀል አድራጊውን ግላዊ የአደገኛነት መጠን፣ ያለፈ የህይወት ታሪኩን፣ ወንጀሉን ለማድረግ ያነሳሱትን ምክንያቶችና የሀሳቡን አላማ፣ የግል ኑሮውን ሁኔታ፣ የትምህርቱን ደረጃ እንዲሁም የወንጀሉን ከባድነትና የአፈጻጸሙን ሁኔታዎች በማመዛዘን ነው ይላል፡፡
በዚህ ድንጋጌ የተመለከቱት ምክንያቶች የሚያመለክቱት የተፈጸመው ወንጀልና የተጣሰው የወንጀል ድንጋጌ አንድ ቢሆንም በዚህ ድንጋጌ ውስጥ ከተመለከቱት ምክንያቶች መሟላትና አለመሟላት አንጻር ቅጣት በተለያዩ ወንጀል አድራጊዎች መካከል ሊለያይ እንደሚችል ነው፡፡ ተመሳሳይ አይነት ወንጀል ሆኖ አንዱ ወንጀለኛ ዝቅተኛ ቅጣት ሲቀጣ ሌላው ደግሞ ከባድ ቅጣት ሊቀጣ እንደሚችል የሚያመለክት ነው፡፡ ይህም ወንጀሉ ተመሳሳይ ቢሆንም የተለያየ የከባድነት ደረጃዎች ሊኖሩት እንደሚችሉ የሚያመለክት ነው፡፡
ከዚህ በመነሳትም መመሪያው የተፈጸመው ወንጀል አንድ የወንጀል ህጉን ድንጋጌ የሚጥስ ቢሆንም ወንጀሉ እንደክብደቱ ደረጃዎች ሊወጡለት የሚችሉ መሆኑን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የወንጀል ደረጃዎች ለተለያዩ የወንጀል አይነቶች አዘጋጅቷል፡፡
በመመሪያው መሰረት ለወንጀሎች የተለያየ የወንጀል ደረጃ ሲወጣ ግን በአንቀጽ 88(2) ያሉትን ምክንያቶች በሙሉ በመስፈርትነት አልተጠቀመም፡፡ ምክንያቱም በድንጋጌዎች የተቀመጡት ቅጣትን ለመወሰን ያገለግላሉ ተብለው የተቀመጡት ምክንያቶች በተለያዩ የወንጀል ህጉ ውስጥ ተመልክተው እናገኛቸዋለን፡፡ እነዚህ ምክንያቶች አንዳንድ ጊዜ ቅጣቱን ለማክበድ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ቅጣቱን ለማቅለል ሊውሉ ይችላሉ፡፡
ለምሳሌ፣
1. የወንጀል አድራጊው ያለፈ የህይወት ታሪኩን በሚመለከት ቀድሞ ወንጀል አድርጎ የተቀጣ ከሆነ በማክበጃነት (አንቀጽ 84(1)(ሐ)፣ ቀድሞ ወንጀል ፈጽሞ ያልነበረና መልካም ጸባይ የነበረው ከሆነ በማቅለያነት (አንቀጽ 82(1)(ሀ) ያገለግላል፣
2. ወንጀሉን የፈጸመው በከሀዲነት፣ በምቀኝነት ከሆነ በማክበጃነት (አንቀጽ 84(1)(ሀ)፣ ከፍ ባለ ሀይማኖታዊ ወዘተ አላማ ከሆነ በማቅለያነት (አንቀጽ 82(1)(ለ) ያገለግላል፣ ወዘተ…
በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 189 እንደተመለከተው ዳኛው በቅድሚያ ማክበጃ ምክንያቶችን መሰረት አድርጎ እንደሚያከብድ ያስቀመጠ ስለሆነ፣ በማክበጃ ምክንያቶች መሰረትም ቅጣቱን ለማክበድ መጀመሪያ መነሻ ቅጣት ማስቀመጥ ስለሚያስፈልግ፣ መነሻ ቅጣቱ ሲወሰን ማክበጃና ማቅለያ ምክንያቶች ከመታየታቸው በፊት የሚወሰን ነው ማለት ነው፡፡
ስለሆነም የወንጀል ደረጃዎችን ለማውጣት በወንጀል ህጉ 88 ያሉት ምክንያቶች ሁሉ ሳይሆን ታሳቢ የተደረጉት በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በማክበጃነት ወይም በማቅለያነት ሊጠቀሱ የማይችሉ በአንቀጽ 88 የተመለከቱት ምክንያቶች ናቸው፡፡
ስለሆነም መመሪያው የወንጀል ደረጃዎችን ለማውጣት ቅድሚያ የሰጠው የወንጀል ደረጃውን ከወንጀሉ ከባድነት አንጻር ደረጃ በማውጣት ነው፡፡
ስለሆነም ጥፋት አድራጊው ጥፋተኛ የተባለበት የወንጀል ድንጋጌ አንድ ቢሆንም፣ የጥፋቱ አፈጻጸም አደገኛነትና ያስከተለው ጉዳት ከባድነት አንዱ ከሌላው የተለየ ከሆነ መነሻ ቅጣታቸውም ተመሳሳይ ሊሆን ስለማይገባው እንደወንጀሉ ከባድነት መነሻው ከዝቅተኛው ጀምሮ ከፍ እያለ ሊሄድ ይገባል የሚል መነሻ አለው፡፡ በዚህ መሰረትም በዚህ መመሪያ ለተወሰኑት ወንጀሎች የወንጀል ደረጃዎች ተዘጋጅተውላቸዋል፡፡
የመነሻ ቅጣት አወሳሰን
1.መመሪያው ህግ አውጪው ለእያንዳንዱ የወንጀል ድርጊት የቅጣት መነሻና ጣሪያ አድርጎ ያስቀመጣቸው የቅጣት መጠኖች ትርጉም ሊኖራቸው በሚችል መልኩም የቅጣት መመሪያው መዘጋጀት አለበት የሚልም መነሻ አለው፡፡ ማለትም በወንጀል አፈጻጸሙም ሆነ ከባድነቱ ቀላልና ዝቅተኛ የሚባለው የቅጣቱ መነሻ በወንጀል ህጉ የተቀመጠው መነሻ መሆን አለበት የሚል መነሻ አለው፡፡ ለምሳሌ ቅጣቱ ከ1 አመት ቀላል እስራት እስከ 5 አመት ጽኑ እስራት የሚል ከሆነ፣ ድንጋጌውን በመጣስ ከሚፈጸመው ወንጀል በተነጻጻሪ ቀላልና ዝቅተኛ የሚባለው የወንጀል ድርጊት መነሻ ቅጣቱ 1 አመት ቀላል እስራት መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ስለሆነም ለእያንዳንዱ የወንጀል ድንጋጌ ዝቅተኛ ደረጃ በወንጀል ህጉ ልዩ ክፍል የተቀመጠው ዝቅተኛ መነሻ ይሆናል፡፡
2.በወንጀል ድንጋጌው ውስጥ ለሚወድቀው ከፍተኛ የወንጀል ደረጃ ለድንጋጌው የተመለከተው ጣሪያ ላይ አይደርስም፡፡ ምክንያቱም በልዩ ክፍል የተመለከቱት የቅጣት ጣሪያ ላይ የሚደረሰው ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃዎች ሲኖሩ ነው፡፡ የወንጀል ህግ ቁጥር 183 ቅጣቱ እንዲከብድ ህጉ በደነገገ ጊዜ (84) ለቅጣቱ ማክበጃ የሆኑትን ምክንያቶች አይነትና ብዛት እንዲሁም ወንጀለኛው የፈጸመውን ጥፋት ከባድነት በማመዛዘን ፍርድ ቤቱ በዚህ ሕግ ልዩ ክፍል በተመለከተው አግባብነት ባለው ድንጋጌ ከተወሰነው ቅጣት ጣሪያ ሳያልፍ ቅጣቱን ይወስናል፡፡ ስለሆነም በህጉ አንቀጽ 84 የተመለከቱትን ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃዎች አምስት ሲሆኑ፣ ሁሉም ተማልተው ሲገኙ ጣሪያው ላይ እንዲደርስ ታሳቢ በማድረግ፣ ከአምስት እርከን በታች ለከፍተኛው ደረጃ መነሻ እንዲሆን ተደርጎአል፡፡
3.እያንዳንዱን የወንጀል አፈጻጸም በዝርዝር በማስቀመጥ ደረጃ ለማውጣት ስለማይቻል፣ መሰረታዊ ባህርዩን በመለየት፣ ከዚህ በተጨማሪ እያንዳንዱን የወንጀል ድርጊት የሚገልጸውን ባህርይ እየለየ ዳኛው ቅጣቱን ለማስቀመጥ እንዲችል ከሚገባው በላይ ሰፊ ባይሆንም ምክንያታዊ ፍቅድ ስልጣን (ዲስክሬሽን) ዳኛው ሊኖረው ይገባል የሚል መነሻም ያለው ነው፡፡ ስለሆነም በተቀመጠው ፍቅድ ስልጣን ውስጥ ዳኛው መነሻ ቅጣቱን ይወስናል ማለት ነው፡፡
ለእያንዳንዱ የወንጀል ደረጃ የቅጣት መነሻና መድረሻ የተወሰነበት ሁኔታ፣
በስልጣን አለአግባብ መገልገል ወንጀል 407(1)
በወንጀል ሕግ 407(1) ውስጥ ለሚወድቁ የወንጀል ድርጊቶች 6 የወንጀል ደረጃዎች አሉት፡፡
ዝቅተኛው ወይም ደረጃ 1 መነሻው ቅጣት የቅጣት እርከን 7 ሲሆን፣ ይህም በወንጀል ህጉ ከተቀመጠው መነሻ አንድ አመት የሚነሳ ነው፡፡
ከፍተኛ ደረጃ የተባለው ደግሞ መነሻ ቅጣቱ በእርከን 23 የተቀመጠ ሲሆን፣ ይህም ከ 6 አመት እስከ 7 አመት ከ2 ወር ነው፡፡
በ407(1) ከፍተኛ ለተባለው የወንጀል ደረጃ 6 (እርከን 23) አምስት የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች ቢኖሩና ቅጣቱ በአምስት እርከን ቢከብድ እርከን 28 ላይ ይደርሳል፡፡
የእርከን 28 ቅጣት ከ9 አመት እስከ 10 አመት ከ10 ወር ነው፡፡ በወንጀል ህጉ ለወንጀሉ የተቀመጠው የቅጣት ጣሪያ 10 አመት ጽኑ እስራትን ያካተተ ነው፡፡
ስለሆነም በዚህ እርከን ውስጥ ከ10 አመት ሳይበልጥ ቅጣቱ ይወሰናል ማለት ነው፡፡
በስልጣን አለአግባብ መገልገል ወንጀል 407(2)
በወንጀል ሕግ 407(2) ውስጥ ለሚወድቁ የወንጀል ድርጊቶች 4 የወንጀል ደረጃዎች አሉት፡፡
ዝቅተኛው ወይም ደረጃ 1 መነሻው ቅጣት የቅጣት እርከን 25 ሲሆን፣ ይህም በወንጀል ህጉ ከተቀመጠው መነሻ ሰባት አመት የሚነሳ ነው፡፡
ከፍተኛ ደረጃ የተባለው ደረጃ 4 መነሻው የቅጣት እርከን 28 ሲሆን የዚህም የቅጣት መነሻ ከ9 አመት እስከ 10 አመት ከ10 ወር ነው፡፡
በ407(2) ከፍተኛ ለተባለው የወንጀል ደረጃ 4 አምስት የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች ቢኖሩና ቅጣቱ በአምስት እርከን ቢከብድ እርከን 33 ላይ ይደርሳል፡፡
የእርከን 33 ቅጣት ከ14 አመት እስከ 16 አመት ከ10 ወር ነው፡፡ በወንጀል ህጉ ለወንጀሉ የተቀመጠው የቅጣት ጣሪያ 15 አመት ጽኑ እስራትን ያካተተ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ እርከን ውስጥ ከ15 አመት ሳይበልጥ ቅጣቱ ይወሰናል ማለት ነው፡፡
ከባድ ስርቆት 669
· በወንጀል ሕግ 669 ውስጥ ለሚወድቁ የወንጀል ድርጊቶች 9 የወንጀል ደረጃዎች አሉት፡፡
· ዝቅተኛው ወይም ደረጃ 1 መነሻው ቅጣት የቅጣት እርከን 7 ሲሆን፣ ይህም በወንጀል ህጉ ከተቀመጠው መነሻ 1 አመት የሚነሳ ነው፡፡
· ከፍተኛ ደረጃ የተባለው ደረጃ 9 መነሻው የቅጣት እርከን 27 ሲሆን የዚህም የቅጣት መነሻ ከ8 አመት ከ5 ወር እስከ 10 አመት ነው፡፡
· በ669 ከፍተኛ ለተባለው የወንጀል ደረጃ 9 (እርከን 27) አምስት የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች ቢኖሩና ቅጣቱ በአምስት እርከን ቢከብድ እርከን 32 ላይ ይደርሳል፡፡
· የእርከን 32 ቅጣት ከ13 አመት እስከ 15 አመት ከ8 ወር ነው፡፡ በወንጀል ህጉ ለወንጀሉ የተቀመጠው የቅጣት ጣሪያ 15 አመት ጽኑ እስራትን ያካተተ ነው፡፡
· ስለሆነም በዚህ እርከን ውስጥ ከ5 አመት ሳይበልጥ ቅጣቱ ይወሰናል ማለት ነው፡፡
በድንጋጌው ዝቅተኛ የወንጀል ደረጃና ከፍተኛ የወንጀል ደረጃ መካከል ያሉትን የወንጀል ደረጃዎች መነሻ ቅጣት አወሳሰን
በድንጋጌው ዝቅተኛው የወንጀል ደረጃና ከፍተኛው የወንጀል ደረጃ የሚያርፉበት ከታወቀ፣ በእነዚህ መሀከል ያሉት የተለያዩ የወንጀል ደረጃዎች በቁጥራቸው ልክ ከመነሻው እስከ መድረሻው ያለውን የቅጣት ዘመን በማካፈል የቅጣት መነሻቸው ተወስኗል፡፡
ምሳሌ 1፣
በ407(1) ስድስት የወንጀል ደረጃዎች አሉ፡፡
ዝቅተኛው ደረጃ መነሻው አንድ አመት ስለሆነ እርከን 7 ላይ ነው፡፡
ከፍተኛው ደረጃ 6 ደግሞ እርከን 23 ላይ ነው፡፡
በመካከላቸው 16 እርከን ልዩነት አለ፡፡
ስለሆነም 16 እርከን ለ5 ሲካፈል (የመነሻው የታወቀ ስለሆነ አንድ ይቀንሳል) የሚገኘው ውጤት 3 አካባቢ ነው፡፡ ስለሆነም ከዝቅተኛው ጀምሮ ለእያንዳንዱ 3 እርከን እያለፈ መነሻ ቅጣቱ ተቀምጧል፡፡ በማጠጋጋት አንዱን 4 እርከን ልዩነት እንዲኖረው ተደርገል፡፡
ምሳሌ 2፣
በ665 7 የወንጀል ደረጃዎች አሉ፡፡
ዝቅተኛው ደረጃ መነሻው አንድ 10 ቀን ስለሆነ እርከን 2 ላይ ነው፡፡
ከፍተኛው ደረጃ 2 ደግሞ እርከን 14 ላይ ነው፡፡
በመካከላቸው 12 እርከን ልዩነት አለ፡፡
ስለሆነም 12 እርከን ለ6 ሲካፈል የሚገኘው ውጤት 2 ነው፡፡ ስለሆነም ከዝቅተኛው ጀምሮ ለእያንዳንዱ 2 እርከን እያለፈ መነሻ ቅጣቱ ተቀምጧል፡፡
የገንዘብ መቀጮን በተመለከተ
የገንዘብ መቀጮውን በተመለከተም ለወንጀሉ ድርጊት ከተቀመጠው ጣሪያ ሳይበልጥ በድንጋጌው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወንጀል አድራጊ እስከመቀጮው ጣሪያ እንዲከፍል በሚያደርግ መልኩ፣የወንጀል ደረጃው ዝቅ እያለ በሄደ ቁጥርም የገንዘብ መቀጮ ጣሪያውም በዚያው መልክ እየቀነሰ እንዲሄድ በማድረግ ደረጃው ተዘጋጅቷል፡፡
ምሳሌ
በ407(1) ከፍተኛው የገንዘብ መቀጮ ብር 10000 ነው፡፡
ስለሆነም ከፍተኛው ደረጃ 6 ሲሆን ለዚህ መቀጮው እርከን 6 ነው፡፡ (10000)
የወንጀል ደረጃው ደረጃ 5 ከሆነ የመቀጮው እርከን 5 ነው፡፡ (7000)
በዚህ መልኩ ለሁሉም የወንጀል ደረጃዎች የቅጣት መነሻውን ለማወቅ የሚያርፉበት እርከን
ተመልክቷል፡፡
ደረጃ ለወጣላቸው ወንጀሎች ቅጣት አወሳሰን ዝርዝር አሰራር ማሳያ
ቅጣቱ የሚወሰንበት ቅደም ተከተል
1. ጥፋተኛ ተብሎ ሲወሰን ጥፋተኛ ተብሎ የተወሰነበት ድንጋጌም የሚታወቅ ስለሆነ፣ ለወንጀሉ ከወጡት የወንጀል ደረጃዎች አንጻር ደረጃው ይለያል፡፡
2. ለወንጀል ደረጃው የተቀመጠው የቅጣት እርከን ይለያል፡፡
3. በእርከኑ ውስጥ ዳኛው ቅጣቱን ይወስናል፡፡
በስልጣን አለአግባብ መገልገል የሚፈጸም ወንጀልን በተመለከተ
በመመሪያው መሰረት ዳኛው በወንጀል ህጉ አንቀጽ 407 ቅጣት ለመወሰን ከግምት የሚያስገባቸው ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነርሱም፣ የአጥፊው የስልጣን ደረጃ፣ በወንጀሉ ምክንያት የደረሰ ጥቅም ወይም ጉዳት እና ወንጀሉ የተፈጸመበት አላማ ናቸው፡፡
ምሳሌ 1.
በ407(1) መሰረት ጥፋተኛ የተባለው ሰው የስልጣን ደረጃው የመምሪያ ሀላፊ ሲሆን፣ በወንጀሉ ምክንያት ያገኘው የማይገባ ጥቅም 30000 ብር ነው፡፡
የዚህን ወንጀል አድራጊ ቅጣት ለመወሰን የመጀመሪያው ጥያቄ የስልጣን ደረጃው ምንድነው የሚል ነው፡፡ የስራ ሀላፊነቱ የመምሪያ ሀላፊ ስለሆነ መካከለኛ ባለስልጣን በሚለው ላይ ይወድቃል፡፡
የተገኘው ጥቅም ብር 30000 ስለሆነ መካከለኛ ጥቅም ወይም ጉዳት በሚለው ስር ይወድቃል፡፡ (ተከሳሽ በወንጀሉ ምክንያት ያገኘውን ጥቅም በገንዘብ ተምኖ ማስቀመጥ የማይቻል ከሆነ ዝቅተኛ ጥቅም በሚለው ካታጎሪ ውስጥ ይወድቃል፡፡)
በሶስተኛ ደረጃ የሚጠየቀውና የሚጣራው ወንጀሉን የፈጸመው በምን አላማ ነው የሚለው ነው፡፡ በመመሪያው መሰረት ሁለት መስፈርቶች አሉ፡፡ ወንጀሉን የፈጸመው በችግር ወይም በተጽእኖ ከሆነ ዝቅተኛው ካታጎሪ ውስጥ ሲወድቅ ከዚህ ውጭ ከሆነ ከባድ አላማ በሚለው ውስጥ ይወድቃል ማለት ነው፡፡
በመመሪያው እንደተመለከተው ወንጀሉን የፈጸመው በችግር ወይም በተጽአኖ መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ ከሌለ ከባድ አላማ እንዳለ እንደሚቆጠር ተመልክቷል፡፡
በዚህ ጉዳይ ወንጀል አድራጊው በችግር ወይም በተጽእኖ ወንጀሉን ለመፈጸሙ የሚያስረዳ ማስረጃ የለም፡፡ ስለሆነም የተፈጸመበት አላማ ከባድ አላማ ነው ማለት ነው፡፡
ከእነዚህ በመነሳት ወንጀለኛው (መካከለኛ ስልጣን ነው/ መካከለኛ ጥቅም ወይም ጉዳት ያገኘ ነው/ በከባድ አላማ የፈጸመ ነው፡፡ )
የእስራት ቅጣትን በተመለከተ፣
· በእነዚህ መለያዎች መሰረት በመመሪያው አባሪ ሶስት ከ407 አንጻር በተቀመጡት በየትኛው የወንጀል ደረጃ ውስጥ እንዳለ እንመለከታለን፡፡ በዚህ መሰረት በ407(1) ውስጥ በወንጀል ደረጃ 6 እናገኘዋለን፡፡
· በዚህ የወንጀል ደረጃ 6- እስራትን በተመለከተ ቅጣቱ የሚወድቀው እርከን 23 ላይ እንደሆነ በአባሪ ሶስት አራተኛው ኮለም (አምድ) ላይ ተመልክቷል፡፡ ስለሆነም የቅጣት እርከኑ ተለየ ማለት ነው፡፡
· በእርከን 23 የቅጣት ሬንጅ (ፍቅድ ስልጣን) ከ 6 አመት እስከ 7 አመት ከ2 ወር ነው፡፡
· ዳኛው በዚህ ሬንጅ ውስጥ የቤተሰብ አስተዳዳሪነቱን፣ የኑሮውን ሁኔታ ወዘተ ከግምት በማስገባት ቅጣቱን ይወስናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ቅጣቱን ለምሳሌ 6 አመት ብሎ ሊወስን ይችላል፡፡
የገንዘብ መቀጮን በተመለከተ፣
· የገንዘብ መቀጮን በተመለከተም በወንጀል ህጉ ከተቀመጠው አንጻር እንዴት እንደሚወሰን በመመሪያው ተመልክቷል፡፡
· ወንጀል አድራጊው የወንጀል ደረጃው በ407(1) ደረጃ 6 ላይ ነው፡፡ ለዚህ በአባሪ ሶስት የተመለከተው የመቀጮው እርከን 6 ነው፡፡
· የመቀጮ እርከን 6 ጣሪያው እስከ ብር 10000 ድረስ ነው፡፡
· ዳኛው ከዚህ ጣሪያ ሳያልፍ ቅጣቱን ይወስናል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ብር 8000 ብሎ ሊወስን ይችላል፡፡
· ይሁንና መቀጮ ሲወሰን ታሳቢ የሚደረጉ በርካታ ምክንያቶች ያሉ ስለሆነ መቀጮውን ላይወስንም ይችላል፡፡
የተፈጸመበት አላማ ከባድ ተብሎ በመመሪያው ከተጠቀሰውም በላይ በሆነ ጊዜ ቅጣቱ እንዴት ይወሰናል?
በመመሪያው እንደተመለከተው ከአላማው አንጻር ከባድ አላማ በላይም ሆኖ ዳኛው ቢያገኘው ማለትም ለምሳሌ ወንጀሉ የተፈጸመው የሀገር ምስጢርን ለሌላ አገር ለማሳለፍ ከሆነ፣ በአንቀጽ 407 መሰረት የተፈጸመበት አላማ ቅጣቱን እንደሚያከብደው ያስቀመጠ ስለሆነ በ407(1) ውስጥ ይወድቅ የነበረው በ407(2) ውስጥ ይወድቃል ማለት ነው፡፡
በ407(2) ውስጥ የነበረው ከአንድ በላይ ማክበጃ ምክንያቶች ተሟልተው የሚገኙበት ስለሆነ አላማው ከባድ አላማ ከተባለውም በላይ ከሆነ ከአንድ በላይ ማክበጃ ተደራርበው ስለሚገኙ በ407(3) ውስጥ ይወድቃል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የወንጀል ደረጃው ከዚህ በታች በተመለከተው መሰረት ይስተካከላል ማለት ነው፡፡
· የስልጣን ደረጃው ዝቅተኛ/ የተገኘው የጥቅም መጠን ዝቅተኛ/ የተፈጸመበት አላማ ከባድ አላማ ከተባለው በላይ ከሆነ በአንቀጽ 407(2) ደረጃ 7 ይሆናል፡፡
· የስልጣን ደረጃው መካከለኛ/የተገኘው ጥቅም መጠን ዝቅተኛ/ የተፈጸመበት አላማ ከባድ አላማ ከተባለው በላይ ከሆነ በአንቀጽ 407(2) ደረጃ 8 ይሆናል፡፡
· የስልጣን ደረጃው ዝቅተኛ/ የተገኘው የገንዘብ መጠን መካከለኛ ከሆነ/ የተፈጸመበት አላማ ከባድ አላማ ከተባለው በላይ ከሆነ በአንቀጽ 407(2) ደረጃ 9 ይሆናል፡፡
· የስልጣን ደረጃው መካከለኛ/የተገኘው ጥቅምም መካከለኛ ከሆነ/ የተፈጸመበት አላማ ከባድ አላማ ከተባለው በላይ ከሆነ በአንቀጽ 407(2) ደረጃ 10 ይሆናል፡፡
· በ407(2) በደረጃ 1 እና 2 ውስጥ የሚወድቀው ከአላማው አንጻር ሌላ ተደራቢ ማክበጃ ምክንያት በመኖሩ በ407(3) ደረጃ 11 ውስጥ የሚወድቅ ይሆናል፡፡
· በ407(2) በደረጃ 3 እና 4 ውስጥ የሚወድቀው ደግሞ ከአላማው አንጻር ሌላ ተደራቢ ማክበጃ ምክንያት በመኖሩ በ407(3) ደረጃ 12 ውስጥ የሚወድቅ ይሆናል፡፡
በሰው አካልና ጤንነት ላይ የሚፈጸም ወንጀልን በተመለከተ
በሰው አካልና ጤንነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ የወንጀል ህጉ ድንጋጌዎች ከ555-560 ድረስ ናቸው፡፡ እነዚህ ቀላል የአካል ጉዳት እና ከባድ የአካል ጉዳት በሚል የተከፈሉ ናቸው፡፡
በ555 መሰረት ጥፋተኛ ነው ተብሎ በተወሰነበት ሰው ላይ ቅጣት እንዴት ይወሰናል?
ቅጣቱን ለመወሰን ዳኛው ከግምት የሚያስገባው የደረሰው የጉዳት መጠንን እና አጥፊው የሙያ ግዴታ ያለበት መሆኑን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው፡፡ ስለሆነም የደረሰው ጉዳት፣ 1) ሊድን የሚችል ነው? 2) ዘላቂ የማይጠፋ ነው? 3) ለህይወቱ ያሰጋዋል? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሹን ያስቀምጣል፡፡
ምሳሌ ሁለት
· በቀረበው ጉዳይ ላይ በወንጀል ሰለባው ላይ የደረሰው ጉዳት ለህይወቱ የሚያሰጋ ነው፡፡
· ወንጀል አድራጊው ሙያዊ ግዴታ እንዳለበት ተረጋግጧል፡፡
ስለሆነም ወንጀለኛው ያደረሰው ጉዳት 1) ለህይወቱ የሚያሰጋ ነው እንዲሁም 2) ሙያዊ ግዴታ ያለበት ነው፡፡
· እነዚህን ሁለት መስፈርቶች ያሟላ የወንጀል ደረጃ 7 ነው፡፡
· የእስራት ቅጣቱን ለመወሰን ደረጃ 7 በእርከን 27 ላይ ይወድቃል፡፡
· በእርከን 27 ላይ የቅጣት መነሻና መድረሻው ከ8 አመት ከ5 ወር እስከ 10 አመት ነው፡፡
· ዳኛው በዚህ እርከን ውስጥ ቅጣቱን ይወስናል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ 9 አመት በሚል ሊወስን ይችላል፡፡
እነዚህ መስፈርቶች በተመሳሳይ በ558 እንዲሁም በ559 መሰረት ቅጣት ለመጣል የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ በመካከላቸው ያለው ልዩነት የወንጀል አድራጊው የሞራላዊ ሁኔታ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡
አንቀጽ 557 ንኡስ አንቀጽ በጥቅሉ ማቅለያ ነው፡፡
ስለሆነም በ557 (1) ከተመለከቱት ማቅለያዎች ተሟልተው ከሆነ ዳኛው ቅጣቱን ለመወሰን በሰንጠረዡ ወደተቀመጠው መስፈርት መሄድ ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡
የወንጀል ደረጃዎቹ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የቅጣት እርከኑን ለመወሰን ብቻ ነው ወደ557 የሚሄደው፡፡
ስለሆነም ከዚህ በላይ የተመለከትነው ምሳሌ ማለትም
· የደረሰው ጉዳት ለህይወቱ የሚያሰጋ ከሆነ እና ሙያዊ ግዴታ እያለበት ከሆነ የወንጀል ደረጃው 6 ነው፡፡
· በዚህ ደረጃ ላይ ያለ የሚወድቅበት የቅጣት እርከን 10 ለመቀጮ ደግሞ እርከን 4 ነው፡፡
· እርከን 10 ቅጣቱ ከ1 አመት ከ6 ወር እስከ 1 አመት ከ10 ወር ነው፡፡ ዳኛው በዚህ ውስጥ ይወስናል ማለት ነው፡፡
· የመቀጮ እርከን 4 ጣሪያው እስከ ብር 5000 ነው፡፡ ስለሆነም ዳኛው ከዚህ ባልበለጠ መቀጮውን ይወስናል ማለት ነው፡፡
በ557 ውስጥ ያሉት ማቅለያዎች ቢኖሩም በንኡስ አንቀጽ 2 በተመለከተው መሰረት ተጎጂው ፈቃዱን ቢሰጥም ተጎጂው እሺታውን የሰጠው የሚያስከትለውን ውጤት የማይረዳ መሆኑን መረዳት ከተቻለ በ557(1) መሰረት ከተደረሰበት የቅጣት እርከን 7 በመጨመር ቅጣቱ ይወሰናል ማለት ነው፡፡ በዚህ መሰረትም
1. ደረጃ 1 የቅጣት እርከኑ 5 (ከ6 ወር-9 ወር) የነበረው የቅጣት እርከኑ 12 (ከ2 አመት-2 አመት ከ6ወር) ይሆናል፡፡
2. ደረጃ 2 የቅጣት እርከኑ 6 (ከ8ወር- 1 አመት ) የነበረው የቅጣት እርከኑ 13 (ከ2 አመት ከ3 ወር-2 አመት ከ9 ወር) ይሆናል፡፡
3. ደረጃ 3 የቅጣት እርከኑ 7 (ከ1 አመት-1 አመት ከ3 ወር) የነበረው የቅጣት እርከኑ 14 (ከ2 አመት ከ6 ወር- 3 አመት ይሆናል፡፡
4. ደረጃ 4 የቅጣት እርከኑ 8 (ከ1 አመት ከ2 ወር -1 አመት ከ6 ወር) የነበረው የቅጣት እርከኑ 15 (ከ2 አመት ከ9 ወር-3 አመት ከ3 ወር ይሆናል)
5. ደረጃ 5 የቅጣት እርከኑ 9(ከ1 አመት ከ4 ወር-1 አመት ከ8 ወር) የነበረው የቅጣት እርከኑ 16 (ከ3 አመት-3 አመት ከ7 ወር ይሆናል)
6. ደረጃ 6 የቅጣት እርከኑ 10 ( ከ1 አመት ከ6 ወር-1 አመት ከ10 ወር) የነበረው የቅጣት እርከኑ 17 (ከ3 አመት ከ3 ወር-3 አመት ከ11 ወር ይሆናል፡፡
7. ደረጃ 7 የቅጣት እርከኑ 11 (ከ1 አመት ከ8 ወር-2 አመት ከ2 ወር) የነበረው የቅጣት እርከኑ 18 (ከ3 አመት ከ7 ወር-4 አመት ከ4 ወር) ይሆናል፡፡ ይሁንና ተጨማሪው 4 ወር በህጉ ከተቀመጠው ጣሪያ በላይ ስለሆነ ቅጣቱ ከ4 አመት አይበልጥም ማለት ነው፡፡
በወንጀል ህጉ 556 መሰረት ቅጣቱን ለመወሰን ዳኛው ከግምት የሚያስገባቸው የሚከተሉትን ነው፡፡
በድንጋጌው ቅጣቱን ለመወሰን ከግምት የሚገቡ በድንጋጌው ያሉ ሶስት መስፈርቶች አሉ፡፡
1. የደረሰው ጉዳት በ555 ከተመለከቱት ውጭ መሆኑ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በ556 መሰረት ጥፋተኛ ተብሎ ስለሚወሰን እናም በድንጋጌው ያሉት ማክበጃዎች ከሌሉ ደረጃ 1 ሆኖ በቅጣት እርከን 2 ውስጥ ስለሚወድቅ ቅጣቱ ከ10 ቀን እስከ ሶስት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ይወሰናል፡፡
2. ከዚህ ሌላ ቅጣቱን ለመወሰን ታሳቢ የሚደረጉት የሚከተሉት መስፈርቶች ናቸው፡፡ 1) ጉዳት ለማድረስ መሳሪያ መጠቀም አለመጠቀሙ፣ 2) የሙያ ወይም ሌላ ግዴታን በመተላለፍ እንደሆነ፣ 3) ተጎጂው በሽተኛ፣ ደካማ ወይም ራሱን መከላከል የማይችል እንደሆነ ናቸው፡፡
3. ስለሆነም ዳኛው ቅጣቱን ለመወሰን ወንጀል አድራጊው መሳሪያ መጠቀም አለመጠቀሙ፣ የሙያ ግዴታ ያለበት መሆን አለመሆኑን እና ተጎጂው በሽተኛ፣ ደካማ ወዘተ መሆኑን ከግምት በማስገባት ቅጣቱን ይወስናል ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ ወንጀል አድራጊው መሳሪያ ተጠቅሟል፣ ተጎጂው በሽተኛ ወይም ራሱን መከላከል የማይችል ነው፡፡ ይሁንና ወንጀል አድራጊው የሙያ ግዴታ የለበትም፡፡
ስለሆነም ሁለቱ ማክበጃዎች ተሟልተዋል ማለት ነው፡፡
ሁለት ማክበጃዎች ተሟልተው ሲገኙ ድርጊቱ የሚወድቀው በወንጀል ደረጃ 3 ላይ ነው፡፡
የወንጀል ደረጃ 3ትን በተመለከተ የተቀመጠው የቅጣት እርከን ለእስራቱ እርከን 7 ሲሆን፣ ለገንዘብ መቀጮው እርከን 5 ነው፡፡
እርከን 7 ቅጣቱ ከ1 አመት እስከ 1 አመት ከሶስት ወር ነው፡፡ ስለሆነም ዳኛው በዚህ ሬንጅ ወይም ፍቅድ ስልጣን ውስጥ ቅጣቱን ይወስናል ማለት ነው፡፡
የገንዘብ መቀጮውን በተመለከተ እርከን 5 እስከ ብር 7000 ድረስ ነው፡፡ ስለሆነም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 90 መሰረት ያሉትን መስፈርቶች መሰረት በማድረግ ከብር 7000 ሳይበልጥ መቀጮውን ይወስናል ማለት ነው፡፡
የስርቆት ወንጀልን በሚመለከት የቅጣት አወሳሰን
የስርቆት ወንጀልን በሚመለከት በ665 እና በ669 መሰረት የተለያዩ መስፈርቶች ቅጣቱን ለመወሰን ይውላሉ፡፡
በ665 መሰረት ቅጣት አወሳሰን
በ665 መሰረት ጥፋተኛ የተባለ ከሆነ፣ ደረጃውን ለመወሰን ከግምት የሚገባው በስርቆት ወንጀሉ የተገኘው ጥቅም መጠን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ደረጃው ይወሰናል ማለት ነው፡፡
1. የገንዘብ መጠኑ እስከ ብር 100 ከሆነ በደንብ መተላለፍ የሚታይ ስለሚሆን በዚህ ድንጋጌ መሰረት ቅጣት አይወሰንም፡፡
2. የገንዘብ መጠኑ ከብር 100 በላይ እስከ ብር 1000 ከሆነ የወንጀል ደረጃው 1 ሆኖ የቅጣት እርከኑ 2 ይሆናል፡፡
3. የቅጣት እርከን ሁለት ቅጣቱ ከ10 ቀን-3 ወራት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ዳኛው ቅጣቱን ይወስናል፡፡
4. ይህንን ወደግዴታ ስራ ወይም ወደመቀጮ ሊቀይረው ይችላል፡፡ ወደግዴታ ስራ ሲቀየር አንድ ቀን እስራት ከአንድ ቀን የግዴታ ስራ (8 ሰአት ጋር) እኩል ነው፡፡ መቀጮው ደግሞ እስከ ብር 500 ድረስ ነው፡፡
5. የገንዘብ መጠኑ ከብር 1000 በላይ እስከ ብር 2000 ከሆነ ደግሞ የወንጀል ደረጃው 2 የቅጣት እርከኑ 4 ይሆናል፡፡
6. የቅጣት እርከን 4 የቅጣት መነሻው ከ4 ወር-7 ወር ነው፡፡
7. ወዘተ
ይሁንና በስርቆት ከተገኘው የገንዘብ መጠን በተጨማሪ የስርቆት ወንጀሉ፣
1. ወንጀል በተፈጸመበት ሰው የእለት ኑሮ ወይም የድርጅቱ ስራ አደጋ ላይ ከወደቀ ከተቀመጠው እርከን በ2 ደረጃ ያድጋል፡፡ በዚህም መሰረት፣
· የወንጀል ደረጃው 1 ለሆነው የቅጣት እርከኑ 4 ይሆናል፡፡
· የወንጀል ደረጃው 2 ለሆነው የቅጣት እርከኑ 6 ይሆናል ማለት ነው፡፡
· ወዘተ…
2. የተሰረቀው ንብረት ፈንጂ ተቀጣጣይ ነገር ከሆነ በተመሳሳይ እርከኑ በ2 ደረጃ ያድጋል፡፡ በዚህም መሰረት፣
· የወንጀል ደረጃው 1 ለሆነው የቅጣት እርከኑ 4 ይሆናል፡፡
· የወንጀል ደረጃው 2 ለሆነው የቅጣት እርከኑ 6 ይሆናል ማለት ነው፡፡
ወዘተ…
3. በዚህ መመሪያ መሰረት እነዚህ ቅጣቱን የሚያከብዱ ሁኔታዎች ተሟልተው ሲገኙ የሚያስጨምሩት የእርከን መጠን ይደመራል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፣
· ወንጀሉ በተሰረቀው ሰው ወይም ድርጅት ስራ አደጋ ላይ የጣለ ከሆነ (2 እርከን ጭማሪ) እና የተሰረቀው ንብረት ፈንጂ ወይም ተቀጣጣይ ከሆነ (2 እርከን ጭማሪ) በድምሩ 4 እርከን ያስጨምራል ማለት ነው፡፡
· ስለሆነም የወንጀል ደረጃው 1 ለሆነው የቅጣት እርከኑ 6 ይሆናል፡፡
· የወንጀል ደረጃው 2 ለሆነው የቅጣት እርከኑ 8 ይሆናል፡፡
· ወዘተ
በ669 መሰረት ቅጣት አወሳሰን፣
በዚህ ድንጋጌ መሰረት ዳኛው ቅጣት ለመወሰን የሚጠቀምባቸው መስፈርቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡ 1) የገንዘቡ መጠን፣ 2) የተሰረቀው እቃ አይነት፣ 3) ድርጊቱን የፈጸመው አድራጊ ማንነት፣ 4) የወንጀል አፈጻጸሙ ነው፡፡
ስለሆነም በ669 መሰረት ጥፋተኛ ነው ተብሎ ከተወሰነ በኋላ ቅጣቱ ሲወሰን ከተራ ቁጥር 2 እስከ ተራ ቁጥር 4 ያሉት ማክበጃዎች ስለሆኑ በዚህ ደረጃ አንድ ማክበጃ፣ ሁለት ማክበጃ ወይም ሶስት ማክበጃ ተብለው ተለይተዋል፡፡
ምሳሌ
1. ወንጀል አድራጊው የሰረቀው ብር 2000 የሚያወጣ ነው፡፡
2. የተሰረቀው እቃ አይነት በ669 (1) ውስጥ ከተዘረዘሩት ዝርዝሮች ውስጥ የሚካተት አይደለም፡፡
3. የወንጀል አድራጊው ማንነት የወኪልነት ስልጣን የተሰጠው ሆኖ በእጁ የገባውን ንብረት ላይ ነው፡፡
4. በድርጊቱ አፈጻጸም አንጻር በ669(3) ውስጥ የሚወድቅ አይደለም፡፡
ስለሆነም ሁለት ነገሮች ተለይተዋል፡፡
1. የገንዘቡ መጠን ብር 2000 ይገመታል፡፡
2. አንድ ማክበጃ ተሟልቷል፡፡
ስለሆነም በ669 መሰረት እስከ ብር 2000 ሆኖ አንድ ማክበጃ የተሟላ ከሆነ የወንጀል ደረጃው 2 ነው፡፡
በ669 የወንጀል ደረጃው 2 የሆነ የመነሻ ቅጣት እርከኑ 9 ነው፡፡
የቅጣት እርከን 9 ቅጣት ከ1አመት ከ4 ወር- 1 አመት ከ8 ወር ነው፡፡ ስለሆነም ዳኛው በዚህ ማእቀፍ ውስጥ ቅጣቱን ይወስናል ማለት ነው፡፡
የውንብድና ወንጀሎችን በተመለከተ ቅጣት አወሳሰን፣
በ670 መሰረት ቅጣት አወሳሰን
የውንብድና ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ቅጣቱን ለመወሰን ዳኛው ከግምት የሚያስገባው ሁለት መስፈርቶችን ነው፡፡ እነርሱም፣
1. በወንጀሉ ለማግኘት የተፈለገው የንብረት መጠን ግምት፣ (ይህ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ድረስ በገንዘብ ግምት ተለይቶ ተቀምጧል፡፡
2. የሀይል አጠቃቀሙ፡፡ ይህንን በተመለከተ ሀይል የተጠቀመው እንዴት ነው ለሚለው ሶስት መስፈርቶች ተዘጋጅተዋል፡፡ እነርሱም 1) መሳሪያ ሳይዝ ከሆነ ዝቅተኛ፣ 2) መሳሪያ ይዞ ከሆነ መካከለኛ፣ 3) የጦር መሳሪያ ይዞ ከሆነ ደግሞ ከፍተኛ ይባላል ማለት ነው፡፡
ምሳሌ 1
1. ወንጀል አድራጊ ብር 8000 የሚገመት ገንዘብ ወስዷል፡፡
2. የሀይል ተግባሩ የተፈጸመው መሳሪያ በመያዝ ነው፡፡ (መካከለኛ የሚባል የሀይል አጠቃቀም ነው)
እነዚህ ሁለት መስፈርቶች ተሟልተው የሚገኙበትን በሰንጠረዡ ስንመለከት የምናገኘው በደረጃ 3 ነው፡፡
ደረጃ 3 ደግሞ የቅጣት እርከኑ 11 ነው፡፡
በቅጣት እርከን 11 ደግሞ ቅጣቱ ከ1 አመት ከ8 ወር -2 አመት ከ2 ወር ነው፡፡ ስለሆነም ዳኛው በዚህ ውስጥ ቅጣቱን ይጥላል ማለት ነው፡፡
ምሳሌ 2
1. ወንጀል አድራጊው ብር 8000 የሚገመት ገንዘብ ወስዷል፡፡
2. ወንጀሉ ሲፈጸም የሀይል ተግባሩን ለመፈጸም የጦር መሳሪያ ይዞ ነው፡፡
እነዚህ ሁለት መስፈርቶች ተሟልተው ሲገኙ በ670 መሰረት የወንጀል ደረጃው ደረጃ 4 ውስጥ ይወድቃል፡፡
ደረጃ 4 የቅጣት እርከኑ 13 ነው፡፡
የቅጣት እርከን 13 የቅጣት መነሻ ከ2 አመት ከ3 ወር- 2 አመት ከ9 ወራት ነው፡፡ ስለሆነም ዳኛው በዚህ ሬንጅ ውስጥ ቅጣቱን ይወስናል ማለት ነው፡፡
በ671 መሰረት የቅጣት አወሳሰን
በዚህ መሰረት ቅጣት ለመወሰን የተቀመጡ መስፈርቶች አሉ፡፡ እነርሱም፣
1. የገንዘብ መጠኑ፣
2. ወንጀሉ በቡድን መፈጸሙ ወይም የተጠቀመበት መሳሪያ ናቸው፡፡
ምሳሌ ቁ.1.
1. የገንዘብ መጠኑ እስከ ብር 2000 ከሆነ
2. ወንጀሉ በቡድን የተፈጸመ ከሆነ
በ671- ደረጃ 1 ላይ ይወድቃል፡፡ ይህም በቅጣት እርከን 21 ላይ ይወድቃል ማለት ነው፡፡
ምሳሌ ቁ.2
1. የገንዘብ መጠኑ እስከ ብር 2000 ከሆነ
2. የሀይል ተግባሩን ለመፈጸም ጉዳት የሚያደርስ መሳሪያ ተጠቅሞ የአካል ጉዳት ያደረሰ ከሆነ፣
በደረጃ 2 ውስጥ ይወድቃል፡፡ የቅጣት እርከኑም 22 ነው፡፡
ምሳሌ ቁ. 3
1. የገንዘብ መጠኑ እስከ ብር 2000 ከሆነ
2. ድርጊቱን ለመፈጸም የጦር መሳሪያ የተጠቀመ ከሆነና የአካል ጉዳት ያደረሰ ከሆነ
በደረጃ 3 ውስጥ ይወድቃል፡፡ የቅጣት እርከኑም 23 ይሆናል ማለት ነው፡፡
ደረጃ ላልወጣላቸው ወንጀሎች የቅጣት አወሳሰን
ጥፋተኛነቱ ከተረጋገጠ በኋላ ዳኛው የሚያደርገው የሚከተለውን ነው፡፡
1. በወንጀል ድንጋጌው ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር ወንጀሉን ዝቅተኛ፣ መካከለኛ ወይም ከባድ ብሎ ይለያል፡፡ ለዚህም ምክንያቱን ያስቀምጣል፡፡
2. በወንጀል ህጉ የተቀመጠውን ቅጣት ከመነሻው እስከ መድረሻው ለአራት እኩል ይከፍላል፡፡ (እርከን 1፣ እርከን 2፣ እርከን 3 እና እርከን 4 ይባላሉ፡፡)
3. በመቀጠል ለዝቅተኛው እርከን አንድ ውስጥ ቅጣት ይወስናል፣ ለመካከለኛው እርከን ሁለት ውስጥ ቅጣት ይወስናል፣ ለከባዱ እርከን ሶስት ውስጥ ቅጣት ይወስናል፡፡
4. ከዚህ በመቀጠል፣ የወሰነው ቅጣት በአባሪ አንድ በተያያዘው ሰንጠረዥ የሚወድቅበትን ዝቅተኛ እርከን ይለይና የተቀጣበትን እርከን ያስቀምጣል፡፡ (ማክበጃና ማቅለያ ምክንያቶች ከሌሉ ይህ አያስፈልግም፡፡)
ምሳሌ
1. ወንጀሉ የተፈጸመው አስገድዶ መድፈር ሲሆን፣ በ620 (1) መሰረት ጥፋተኛ ተብሏል፡፡
2. በ620 (1) መሰረት ቅጣቱ ከ5 አመት እስከ 15 አመት ነው፡፡
3. ዳኛው ከተፈጸመው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል አንጻር፣ ለምሳሌ በወንጀሉ ምክንያት የወንጀሉ ሰለባ የሆነችው ሴት የምታውቀውና የምታምነው በመሆኗ እናም ወንጀሉ ሊፈጸምባት ሲሞከር ባደረገችው መከላከል ሀይል በመጠቀም ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባት በመሆኑ ወንጀሉን የሚያከብደው ስለሆነ ‹መካከለኛ› አፈጻጸም ተብሎ ተሰይሟል በማለት ምክንያቱን ያስቀምጣል፡፡
4. በመቀጠል ከአምስት አመት እስከ አስራ አምስት አመት ያለው ልዩነት 10 አመት ነው፡፡ ይህ ለአራት ሲካፈል እያንዳንዱ ሁለት አመት ከ6 ወር ይሆናል፡፡ ስለሆነም
· እርከን አንድ-- ከ5 አመት እስከ 7 አመት ከ6 ወር
· እርከን ሁለት-- ከ7 አመት ከ6 ወር እስከ 10 አመት
· እርከን ሶስት-- ከ10 አመት እስከ 12 አመት ከ6 ወር
· እርከን አራት ከ12 አመት ከ6 ወር እስከ 15 አመት ይሆናል፡፡
5. ዳኛው መካከለኛ የወንጀል አፈጻጸም በማለት የመደበው ስለሆነ የሚወድቀው በእርከን 2 ውስጥ ነው፡፡
6. እርከን ሁለት ከ7 አመት ከ6 ወር እስከ 10 አመት ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ውስጥ ቅጣቱን ይወስናል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም 8 አመት ነው በማለት ወስኗል እንበል፣
7. 8 አመት እስራት እርከን 25 እና 26 ውስጥ ይወድቃል፡፡
8. መመሪያው ዝቅተኛውን እርከን እንዲመረጥ ስለሚያዝ እርከን 25 ይመረጣል ማለት ነው፡፡ (ማክበጃ እና/ወይም ማቅለያ ምክንያቶች ካሉ ለማክበድ ወይም ለማቅለል)
የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ በሚኖርበት ጊዜ የቅጣት አሰላል፣
ዳኛው መነሻ ቅጣቱን ከወሰነ በኋላ የቅጣት ማክበጃዎች ሲኖሩ ምን ማድረግ እንዳለበት እንዲሁም የቅጣት ማቅለያ ሲኖር ምን ማድረግ እንዳለበት በመመሪያው ተቀምጧል፡፡
ጠቅላላ ማክበጃና ማቅለያ በሚኖርበት ጊዜ የቅጣት አሰላል፣
ጠቅላላ ማክበጃዎችን በሚመለከት፣
በመመሪያው እንደተመለከተው፣
1. በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 84 በአምስት ንኡሳን አንቀጾች የተቀመጡት ምክንያቶች እያንዳንዳቸው እንደአንድ ማክበጃ ምክንያቶች ተወስደዋል፡፡ ማለትም በዝርዝሩ ውስጥ ከተመለከቱት ሁሉም ቢሟሉም፣ በከፊል ቢሟሉም አንዱ ብቻ ቢሟላም እንደአንድ ማክበጃ ምክንያት የሚወሰድ ነው፡፡
2. በዚህ ማክበጃ ምክንያት መሰረት በማድረግ ቅጣቱ የሚከብደው በአንድ የቅጣት እርከን ነው፡፡
3. ስለሆነም በሚኖረው የማክበጃ ቁጥር መሰረት ቅጣቱ ይከብዳል ማለት ነው፡፡
ምሳሌ ቁ 1
1. የተፈጸመው ወንጀል ከባድ የአካል ጉዳት ማድረስ ነው፡፡ (አንቀጽ 555)፡፡
2. የተፈጸመው ወንጀል ደረጃ 6 ሲሆን የቅጣት እርከን 23 ነው እንበል፡፡
3. በማስረጃ ተረጋግጠው የቀረቡ የቅጣት ማክበጃዎች፣
· በስግብግብነት፣
· በተለየ ክፋት ወይም ጨካኝነት
· የጦር መሳሪያ በመጠቀም ከሆነ
4. ከዚህ በላይ በተመለከተው መሰረት የተዘረዘሩት ምክንያቶች ሶስት ቢሆኑም በማክበጃነት ያሉት ምክንያቶች 2 ናቸው፡፡ (ስግብግብነትና የተለየ ክፋት ወይም ጨካኝነት በአንድ ድንጋጌ ውስጥ የተመለከቱ በመሆናቸው)
5. እነዚህ ምክንያቶች ወንጀሉን ለማቋቋምና መነሻ ቅጣቱን ለመወሰን አገልግለው ከሆነ አሁን በድጋሚ በማክበጃነት አይጠቀሱም፡፡
6. ስለሆነም ዳኛው በሁለት እርከን ወደላይ ቅጣቱን ከፍ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ እርከን 25 ይሆናል ማለት ነው፡፡
ጠቅላላ ማቅለያዎችን በሚመለከት፣
1. በቀላል እስራት ለሚያስቀጡ በአንድ ማቅለያ አንድ እርከን ይቀንሳል፡፡
2. የቅጣት መነሻቸው 1 አመት ጽኑ እስራት ለሆነ በእያንዳንዱ ማቅለያ ሁለት እርከን ይቀንሳል፡፡ ይሁንና ከስድስት ወር ጽኑ እስራት በታች አይወርድም፡፡
3. የቅጣት መነሻቸው ከአንድ አመት ጽኑ እስራት በላይ እስከ 7 አመት ጽኑ እስራት ለሆኑ ለእያንዳንዱ ማቅለያ በ2 እርከን ይቀንሳል፡፡ ይሁንና ከአንድ አመት ጽኑ እስራት በታች አይወርድም፡፡
4. የቅጣት መነሻቸው ሰባት አመትና ከሰባት አመት በላይ ለሆኑ ወንጀሎች በእያንዳንዱ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ሶሰት እርከን ይቀነሳል፡፡ ይሁንና ከአንድ አመት ጽኑ እስራት በታች አይወርድም፡፡
5. የቅጣት መነሻቸው እድሜ ልክ ጽኑ እስራት ለሆኑ ወንጀሎች በእያንዳንዱ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ሶስት እርከን ይቀነሳል፡፡ ይሁንና ቅጣቱ ሲቀል ከአስር አመት በታች አይወርድም፡፡
6. የቅጣት መነሻቸው የሞት ቅጣት ለሆኑ ወንጀለኞች በእያንዳንዱ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት አራት እርከን ይቀነሳል፡፡ ይሁንና ቅጣቱ ሲቀል ከሃያ አመት በታች አይሆንም፡፡
ምሳሌ
1. ጥፋተኛው በቸልተኝነት ሰውን በመግደል ወንጀል በመፈጸም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 543 (1) መሰረት ጥፋተኛ ተብሎ ተወስኗል፡፡
2. ዳኛው የፈጸመው ወንጀል ‹ዝቅተኛ› በሚል የወሰነ ሲሆን፣ ዝቅተኛ ለሆነው ወንጀል መነሻ ቅጣቱን በእርከን አንድ ከ6 ወር እስከ 1 አመት ከ3 ወር ባለው ውስጥ 1 አመት በማለት ወስኗል፡፡
3. በመመሪያው መሰረት 1 አመት እስራት ቅጣት የሚወድቅበት እርከን 6 እና 7 ሲሆኑ ዝቅተኛው እርከን 6 (ከ8 ወር-1 አመት) እንደሚሆን ታውቋል፡፡
4. የቀረቡ የማቅለያ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
· ከዚህ በፊት የነበረው የዘወትር ጸባይ መልካም ነበር፡፡
· ወንጀሉን ያደረገው ባልታሰበና ድንገተኛ አጋጣሚ ነው፡፡
· ወንጀሉን ከፈጸመ በኋላ በእውነት በመጸጸት ወንጀል ለደረሰበት አስፈላጊውን እርዳታ አድርጓል፡፡
5. ከዚህ በላይ እንደተመለከተው ሶስት ምክንያቶች ቢጠቀሱም፣ ሁለቱ በንኡስ አንቀጽ 82(1)(ሀ) ውስጥ የሚካተቱ ስለሆነ እንደ አንድ ማቅለያ ምክንያት ነው የሚታዩት፡፡ ስለሆነም ሁለት ማቅለያ ምክንያቶች አሉት፡፡
6. ወንጀሉ የሚያስቀጣው በቀላል እስራት ስለሆነ ለእያንዳንዱ ማቅለያ የሚደረገው ቅናሽ አንድ እርከን ነው፡፡ ስለሆነም ለሁለት ማቅለያ በሁለት እርከን ሲቀንስ እርከን 4 (ከ4 ወር-7 ወር) በሚለው ውስጥ ይወድቃል፡፡
7. ዳኛው ቅጣቱን በዚህ ውስጥ 4 ወር ብሎ ሊወስን ይችላል፡፡ ይህንን ወደግዴታ ስራ ወይም መቀጮ ሊቀይረው ይችላል ማለት ነው፡፡
ልዩ ማክበጃና ማቅለያ ምክንያቶች በሚኖሩበት ጊዜ የቅጣት አሰላል፣
1. ተደራራቢነትን በተመለከተ፣
ተደራራቢ ሆኖ በ184 በተመለከተው መሰረት የሚደመር በሆነ ጊዜ ዳኛው ለእያንዳንዱ ወንጀል ቅጣት መነሻ ካስቀመጠ በኁዋላ እነዚህን በመደመር የሚደርስበት ቅጣት የሚወድቅበት እርከን ላይ ቅጣቱ ይቀመጣል፡፡
ምሳሌ፣
• ጥፋተኛው በአንደኛው ወንጀል 2 አመት፣ በሁለተኛው ወንጀል 3 አመት መነሻ ቅጣት ይወሰናል፡፡
• እነዚህ ሲደመሩ 5 አመት ይሆናል፡፡
• 5 አመት በቅጣት እርከን 20 እና 21 ውስጥ ይወድቃል፡፡ ስለሆነም ዝቅተኛው ማለትም እርከን 20 የቅጣት መነሻው የሚያርፍበት እርከን ይሆናል ማለት ነው፡፡
• ከዚህ በመቀጠል በማስረጃ ተረጋግጠው የቀረቡ ጠቅላላ ማክበጃና ማቅለያ ምክንያቶችን መሰረት በማድረግ ቅጣቱ ይሰላል፡፡
ተደራራቢ ጥፋቱ በ187 ንኡስ አንቀጽ አንድ ሁለተኛ ፓራግራፍ ወይም ንኡስ አንቀጽ 2(ለ) ከሆነ፣
• ዳኛው ለከፍተኛው ወንጀል መነሻ ቅጣት ካስቀመጠ በሁዋላ ለከፍተኛው ወንጀል ከተቀመጠው ጣሪያ ሳይበልጥ በሁለት እርከን ያከብዳል፡፡
• ቀጥሎም ጠቅላላ ማክበጃ ምክንያቶችን መሰረት አድርጎ በእያንዳንዱ ምክንያት በአንድ እርከን ያሳድጋል፡፡
2. ደጋጋሚነትን በተመለከተ
• ደጋጋሚ ለሆነው ከአንድ እርከን ጀምሮ እጥፍ እስኪሆን ድረስ ቅጣቱን ያሳድጋል፡፡
• በመቀጠልም ጠቅላላ ማክበጃ ምክንያቶችን መሰረት በማድረግ ቅጣቱን ያከብዳል፡፡
3. ልዩ ማቅለያ ምክንያት በሚኖር ጊዜ
በወንጀል ሕጉ ቅጣትን በመሰለው እንዲያቀል በፈቀደ ጊዜ ፍርድ ቤቱ በዚህ መመሪያ በተመለከተው መሰረት ሳይወሰን ቅጣቱን በማቅለል ይወስናል፡፡
የቅጣት አሰላል ቅደም ተከተል (በማሳያ ምሳሌዎች ተደግፍ የቀረበ፣)
የወንጀል ደረጃ ለወጣላቸው የወንጀል አይነቶች
የወንጀል ቅጣቱ አሰላል ቅደም ተከተል፣
1. የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በዚህ መመሪያ በክፍል ሶስት በተመለከተው መሰረት የወንጀሉ ደረጃን ይወስናል፡፡
2. በመቀጠልም የወንጀሉ ደረጃ የሚወድቅበትን የቅጣት እርከን በአባሪ አንድ ከተያያዘው የቅጣት ሰንጠረዥ ላይ ይለያል፡፡
3. በመቀጠልም በእርከኑ በተቀመጠው የቅጣት መነሻና መድረሻ መካከል ባለው ፍቅድ ስልጣን (range) ውስጥ መነሻ ቅጣት ይወስናል፡፡
4. በማስረጃ የተረጋገጡ ልዩ የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች ካሉ በዚህ መመሪያ መሰረት ቅጣቱን አክብዶ ቅጣቱ የሚደርስበትን እርከን በማስቀመጥ ቅጣቱን ይወስናል፡፡
5. በመቀጠል በማስረጃ በተረጋገጡ ጠቅላላ ማክበጃ ምክንያቶች መሰረት እርከኑን በመጨመር ቅጣቱን ይወስናል፡፡
6. በማስረጃ በተረጋገጡ ማቅለያ ምክንያቶች መሰረት የሚቀነሰውን እርከን በመለየት ወርዶ እርከኑ የሚያርፍበትን በመለየት ቅጣቱን ይወስናል፡፡
7. የሚጣለው የእስራት ቅጣት እስከ ስድስት ወር ወይም ከስድስት ወር በታች በሚሆንበት ጊዜ በዚህ መመሪያ ተያይዞ በሚገኘው የቅጣት እርከን ሰንጠረዥ መሰረት በግዴታ ስራ እንዲለወጥ ሊወስን ይችላል፡፡
8. በቅጣት ማቅለያ ጊዜ የእስራት ቅጣትን ወደ መቀጮ መቀየር እንደሚቻል በህጉ በተደነገገው መሰረት ወደመቀጮ ሲቀየርም በዚህ መመሪያ መሰረት ይሆናል፡፡
ምሳሌ 1
• ጥፋተኛው የወ/ሕ አንቀጽ 665 በመጣስ ብር 3000 የሚያወጣ ንብረት በመስረቅ ተረጋግጦበታል፡፡
• ሁለት ማክበጃ ምክንያቶች መኖራቸው ተረጋግጣል፡፡
• ሶስት ማቅለያ ምክንያቶች መኖራቸው ተረጋግጣል፡፡
የቅጣት አወሳሰን ስርአት፣
1. በወንጀሉ ከተገኘው ጥቅም በ665 ደረጃ 3 ውስጥ ይወድቃል፡፡ ደረጃ 3 በቅጣት እርከን 6 ውስጥ የሚወድቅ ነው፡፡
2. የቅጣት እርከን 6 ቅጣት (ከ8 ወር-1 አመት ነው)
3. ዳኛው በዚህ ሬንጅ ውስጥ መነሻ ቅጣቱን ይወስናል፡፡ ለምሳሌ 10 ወር ሊሆን ይችላል፡፡
ሁለት ማክበጃ ምክንያቶች በመኖራቸው እርከኑን
በሁለት ያሳድጋል፡፡ ስለሆነም
4. እርከን 6 የነበረው እርከን 8 ይሆናል (ከ1 አመት ከ2 ወር- 1 አመት ከ6 ወር)
ሶስት ማቅለያ ምክንያቶች ስላሉ እርከኑን በሶስት
ሲቀንስ እርከን 5 ላይ ይወድቃል፡
5. እርከን 5 (ከ6 ወር--- 9 ወር)
6. በእርከኑ ውስጥ ቅጣቱን ይወስናል፡፡ ለምሳሌ 8 ወር በማለት ዳኛው ሊወስን ይችላል ማለት ነው፡፡
ምሳሌ 2፣
ጥፋተኛው በውንብድና ወንጀል 471 ጥፋተኛ ሆኖ
ተገኝቷል፡፡
• ጉዳት የሚያደርሱ መሳሪያዎችን በመያዝ እገልሀለሁ ብሎ አስፈራርቶ የአካል ጉዳት አድርሳል፡፤
• የተገኘው ጥቅም ብር 1500 ነው፡፡
እንደገና 10000 በማታለል ወንጀል 690 ጥፋተኛ ሆኖ
ተገኝቷል፡፡
• አንድ ማክበጃ ምክንያት እና 3 ማቅለያ ምክንያቶች መኖራቸው ተረጋግጣል፡፡
• በውንብድና ከተፈጸመው ጥፋት አንጻር በ671 ደረጃ 2 ውስጥ ይወድቃል፡፡
• የደረጃ ሁለት የቅጣት እርከን ደግሞ 22 ነው፡፡
• የቅጣት እርከን 22 ቅጣት መነሻና መድረሻ (ከ5 አመት ከ6 ወር- 6 አመት ከ7 ወር ነው)
• ዳኛው በዚህ ውስጥ ሲወሰን 6 አመት ይሆናል ብሎ ወስናል እንበል፡፡
• ለማታለል ወንጀል ከገንዘቡ መጠን አንጻር ደረጃ 4 ውስጥ ይወድቃል፡፡
• ደረጃ 4 ማታለል ለእስራት ቅጣት እርከን 8 ውስጥ ነው፡፡ (ከ1 አመትከ2 ወር - 1 አመት ከ6 ወር)፡፡
• ዳኛው እንበል 1 አመት ከ3 ወር ቅጣት አስቀመጠ፡፡
• ለውንብድና ወንጀል የተቀመጠው መነሻ 6 አመትና የማታለሉ 1 አመት ከ3 ወር ሲደመር 7 አመት ከ3 ወር ይመጣል፡፡
• 7 አመት ከ3 ወር የሚወድቅበት እርከን 24 እና 25 ናቸው፡፡
• ዝቅተኛው ስለሚመረጥ እርከን 24 ይሆናል (ለ6 አመት ከ6 ወር- 7 አመት ከ8 ወር፡፡
ጠቅላላ ማክበጃና ማቅለያ ምክንያቶች ከዚህ ቀጥሎ እንደሚከተለው ይሰላሉ፡፡
• አንድ ማክበጃ ምክንያት በመኖሩ በአንድ እርከን ሲያድግ የቅጣት እርከን 25 ውስጥ ይወድቃል፡፡
• ሶስት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች ስለአሉ፣ ለከባዱ መነሻው 1 አመት ስለሆነ ለእያንዳንዱ ማቅለያ ምክንያት በሁለት እርከን ይቀነሳል፡፡ ለሶስት ምክንያቶች 6 እርከን ሲቀነስ እርከን 19 ላይ ያርፋል፡፡ (ከ4 አመት- 4 አመት ከአስር ወር)
• ዳኛው በዚህ ውስጥ ቅጣቱን ይወስናል፡፡ ለምሳሌ 4 አመት ከ6 ወር ሊሆን ይችላል፡፡
• በማታለል ወንጀል በመቀጮ ለሚጣለው ቅጣት በእርከን 3 ውስጥ ማለትም ጣሪያው እስከ 3000 ብር ይላል፡፡ ስለሆነም ከብር 3000 ሳይበልጥ ቅጣቱ ይጣላል ማለት ነው፡፡
ደረጃ ላልወጣላቸው የቅጣት አወሳሰን ቅደም ተከተል
• የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በድንጋጌው ከተቀመጠው አንጻር የወንጀሉ ከባድነትን በተመለከተ ‹ዝቅተኛ› ወይም ‹መካከለኛ› ወይም ‹ከባድ› በማለት በቅድሚያ ዳኛው ይለያል፡፡
• ዳኛው ከባድ፣ ዝቅተኛ ወይም መካከለኛ ለማለት ምክንያቱን ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡
• በመቀጠል ጥፋተኛ በተባለበት የወንጀል ድንጋጌ መነሻና መድረሻ መካከል ያለውን ጊዜ ለአራት እኩል ይከፍላል፡፡
ምሳሌ
ቅጣቱ ከ1 አመት - 10 አመት ከሆነ ለአራት ሲከፈል
1. ከ1 አመት----3 አ/ከ3 ወር (እርከን አንድ)
2. ከ3 አ/ከ3 ወር----5 አ/ከ6 ወር (እርከን ሁለት)
3. ከ5አ/ከ6 ወር----7 አ/ከ9 ወር (እርከን ሶስት)
4. ከ7አ/ከ9 ወር-----10 አመት (እርከን አራት) ይሆናል፡፡
በመቀጠል፣
1. ዝቅተኛ ተብሎ ለተሰየመው በእርከን አንድ ውስጥ ቅጣቱ ይወሰናል፡፡ (ከ1 አመት-3 አመት ከ3 ወር)
2. መካከለኛ ለተባለው በእርከን ሁለት ውስጥ ቅጣቱ ይወሰናል፡፡ (ከ3አ/ከ3 ወር- 5 አመት ከ6 ወር)
3. ከባድ ለተባለው በእርከን ሶስት ውስጥ ቅጣቱ ይወሰናል፡፡ (ከ5 አመት ከ6 ወር-7 አመት ከ9 ወር)
4. ለምሳሌ በእርከን ሁለት የሚወድቅ ሆኖ ዳኛው 5 አመት ብሎ ሊወስን ይችላል፡፡
5. የተወሰነው ቅጣት የሚወድቅበት እርከን ይለይና ዝቅተኛው ይመረጣል፡፡
6. 5 አመት እርከን 20 እና 21 ውስጥ የሚወድቅ ነው፡፡
7. ከዚህ መሀል ዝቅተኛው እርከን 20 ይመረጣል፡፡
8. ከዚህ ቀጥሎ ደረጃ ለወጣላቸው እንዳለው በተመሳሳይ ቅጣቱ ይሰላል ማለት ነው፡፡
ምሳሌ 2
1. በወ/ሕ አንቀጸ 540 መሰረት ጥፋተኛ ተብሎ ተወስኗል፡፡
2. ዳኛው ጥፋቱን እንደክብደቱ ዝቅተኛ፣ መካከለኛ ወይም ከባድ ተብሎ ይሰየማል፡፡ በዚህ ጉዳይ ዝቅተኛ ተብሎ ተሰይማል፡፡
3. የወንጀል ድንጋጌው የቅጣት ሬንጅ ለአራት ይከፈላል፡፡
• እርከን አንድ (ከ5---9 አመት)
• እርከን ሁለት (ከ9—13 አመት)
• እርከን ሶስት (ከ13- 16 አመት
• እርከን አራት (ከ16-20 አመት ይሆናል፡፡
ዳኛው ጥፋቱን ዝቅተኛ ብሎ ስለሰየመ የመጀመሪያው እርከን ውስጥ 6 አመት ብሎ ወሰነ እንበል፡፡
4. 6 አመት በዋናው የቅጣት ሰንጠረዠ እርከን ውስጥ የትኛው ውስጥ እንደሚወድቅ እንለያን፡፤ (እርከን 21 እና 22 ናቸው)
5. ዝቅተኛው እርከን 21 ይወሰድና መነሻ ይሆናል፡፡
ከዚህ በመቀጠል እንደማክበጃ ምክንያቱና ማቅለያ ምክንያቱ ከእርከኑ ወደላይ እየተደመረ ወይም ወደታች እየተቀነሰ ይሰላል ማለት ነው፡፡
ምሳሌ
8. ጥፋተኛው በቸልተኝነት ሰውን በመግደል ወንጀል በመፈጸም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 543 (1) መሰረት ጥፋተኛ ተብሎ ተወስኗል፡፡
9. ዳኛው የፈጸመው ወንጀል ‹ዝቅተኛ› በሚል የወሰነ ሲሆን፣ ዝቅተኛ ለሆነው ወንጀል መነሻ ቅጣቱን በእርከን አንድ ከ6 ወር እስከ 1 አመት ከ3 ወር ባለው ውስጥ 1 አመት በማለት ወስኗል፡፡
10. በመመሪያው መሰረት 1 አመት እስራት ቅጣት የሚወድቅበት እርከን 6 እና 7 ሲሆኑ ዝቅተኛው እርከን 6 (ከ8 ወር-1 አመት) እንደሚሆን ታውቋል፡፡
11. የቀረቡ የማቅለያ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
· ከዚህ በፊት የነበረው የዘወትር ጸባይ መልካም ነበር፡፡
· ወንጀሉን ያደረገው ባልታሰበና ድንገተኛ አጋጣሚ ነው፡፡
· ወንጀሉን ከፈጸመ በኋላ በእውነት በመጸጸት ወንጀል ለደረሰበት አስፈላጊውን እርዳታ አድርጓል፡፡
12. ከዚህ በላይ እንደተመለከተው ሶስት ምክንያቶች ቢጠቀሱም፣ ሁለቱ በንኡስ አንቀጽ 82(1)(ሀ) ውስጥ የሚካተቱ ስለሆነ እንደ አንድ ማቅለያ ምክንያት ነው የሚታዩት፡፡ ስለሆነም ሁለት ማቅለያ ምክንያቶች አሉት፡፡
13. ወንጀሉ የሚያስቀጣው በቀላል እስራት ስለሆነ ለእያንዳንዱ ማቅለያ የሚደረገው ቅናሽ አንድ እርከን ነው፡፡ ስለሆነም ለሁለት ማቅለያ በሁለት እርከን ሲቀንስ እርከን 4 (ከ4 ወር-7 ወር) በሚለው ውስጥ ይወድቃል፡፡
ዳኛው ቅጣቱን በዚህ ውስጥ 4 ወር ብሎ ሊወስን ይችላል፡፡ ይህንን ወደግዴታ ስራ ወይም መቀጮ ሊቀይረው ይችላል ማለት ነው፡፡
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
1. በሙከራ ደረጃ ለቀረ ወንጀል፣ ማነሳሳት እና አባሪነትን በተመለከተ ሁለት እርከን ዝቅ ብሎ የቅጣቱ መነሻ ይሆናል፡፡
2. ዳኛው በህጉ ከተቀመጡት ውጪ ያሉ ማቅለያ ወይም ማክበጃ ምክንያቶችን በሚጠቀም ጊዜ ለጠቅላላ ቅጣት ማክበጃና ማክበጃ በሚኖረው ስሌት መሰረት እርከኑን ይወስናል፡፡
3. ዳኛው፣ የወንጀል አፈጻጸሙም ሆነ ባህርይው በዚህ መመሪያ ደረጃ በወጣላቸው ሊወከል የማይችል ሆኖ ባገኘው ጊዜ ወይም በዚህ መመሪያ በተቀመጠው መሰረት ቅጣቱን መወሰን ፍትህ የሚዛባ ነው ብሎ ያመነ ከሆነ፣ ምክንያቱን በማስቀመጥ የተለየ ቅጣት ሊጥል ይችላል፡፡
4. ዳኛው በዚህ እንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 1 በተደነገገው መሰረት መመሪያው ከሚያስቀምጠው በተለየ እርከን ላይ እንዲያርፍ በማድረግ በሚወስንበት ጊዜ ሁሉ፣ ይህንኑ ለሚመለከተው አካል ማስታወቅ ወይም መረጃውን ማስተላለፍ ይኖርበታል፡፡ ፍርድ ቤቶችም በዚህ መሰረት የሚያሰባስቡትን መረጃዎች ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የማስተላለፍ ግዴታ እንዳለባቸው መመሪያው አስቀምጧል፡፡
የንብረት ግምት በተመለከተ
1. ወንጀሉ የተፈጸመው በውጭ ገንዘብ ላይ ከሆነ፣ የገንዘቡ ምንዛሪ መጠን ቅጣቱ ሊወሰን ባለበት ጊዜ ባለው ምንዛሪ መሰረት ይሆናል፡፡
2. በወንጀሉ የተወሰደው ንብረት በሚሆንበት ጊዜ የንብረቱን ግምት በተመለከተ ተከሳሹ ክርከር ካቀረበ እና የተከሳሹ ክርክር ተቀባይነት ቢያገኝ የቅጣት እርከኑን የሚቀየር ከሆነ እና በፍርድ ቤቱ እምነት በአቃቤ ህግ የቀረበው ግምት ምክንያታዊ ያልሆነና ፍትህን ያዛባል ብሎ ሲያምን የራሱን ግምት በማስቀመጥ የወንጀል ደረጃውንና የቅጣት እርከኑን ይወስናል፡፡
- Details
- Category: Sentencing and Execution
- Hits: 18317
የመመሪያው አላማና ግብ
በመመሪያው አንቀጽ 3 የሚከተለው ተደንግጎ እናገኛለን
አንቀጽ 3 . የመመሪያው አላማና ግብ፣
1. የመመሪያው አላማ በወንጀል ፍትህ ስርአቱ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ባረጋገጠ መልኩ ውጤታማና ተገማችነት ያለው ቅጣት የሚሰጥበትን ስርአት በመመስረት ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል ነው፡፡
2. መመሪያው የሚከተሉት ግቦች ይኖሩታል፡፡
ሀ. በተቀራራቢና ተመሳሳይ የወንጀል ጉዳዮች መካከል ተቀራራቢነት ያለው የቅጣት አወሳሰን (ወጥነትን) ማረጋገጥ፣
ለ. እንደወንጀሉ ክብደትና አደገኛነት መሰረት ተመጣጣኝ ቅጣት ያለው የቅጣት አወሳሰን ማረጋገጥ ነው፡፡
2. የቅጣት እርከን ሰንጠረዥ
በመመሪያው ቅጣትን ለመወሰን ዝርዝር ሰንጠረዦች ተዘጋጅተዋል፡፡ እነዚህም ነጻነትን የሚያሳጡ ቅጣት ሰንጠረዥ እና የገንዘብ መቀጮ ሰንጠረዥ በሚል ተከፋፍለዋል፡፡
2.1. ነጻነትን የሚያሳጡ ቅጣት እርከን ሰንጠረዥ
ይህ በመመሪያው አባሪ አንድ ሆኖ ተያይዞ የሚገኝ ሰንጠረዥ ሲሆን የወንጀል ሕጉን ዝቅተኛ የቅጣት መነሻ (1 ቀን የግዴታ ስራ) እና ከፍተኛውን የሞት ቅጣት መሰረት በማድረግ 39 ደረጃዎች ያሉት የቅጣት እርከኖች እንዲኖሩት ሆኖ የተዘጋጀ ነው፡፡
አላማው አሁን በወንጀል ህጉ ያለውን በመነሻና በመድረሻ መካከል ያለውን ሰፊ ፍቅድ ስልጣን (discretion) በማጥበብ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 88 ንኡስ አንቀጽ 4 እንደተመለከተው ወጥነትንና ተመጣጣኝነትን ማረጋገጥ ነው፡፡
ሰንጠረዡ ሲዘጋጅ ለእያንዳንዱ የቅጣት እርከን መነሻና መድረሻ ያለው ሲሆን፣ የሚከተሉትን መሰረተ ሀሳቦች መሰረት ባደረገ መልኩ የተዘጋጀ ነው፡፡
- የቅጣት መነሻቸው ከዝቅተኛው ጀምሮ ከፍ እያለ ሲሄድ በመነሻውና በመድረሻው መካከል ፍቅድ ስልጣን (range) እንዲኖር ሆኖ ተዘጋጅቷል፡፡ (ሬንጁ ዝቅተኛው 3 ወር ሲሆን ከፍተኛው 5 አመት ነው፡፡
የቅጣት እርከን 1 ሬንጁ 3 ወር(በትክክል 2 ወር ከሃያ ቀን) ሆኖ ደረጃ በደረጃ እያደገ ይሄዳል፡፡
ከቅጣት እርከን 12 ማለትም (ከ2 አመት- 2 አመት ከ6 ወር) ጀምሮ ሬንጁ ከስድስት ወር ያላነሰ ነው፡፡
ከእርከን 21 ማለትም (ከ5 አመት መነሻ) ጀምሮ ሬንጁ ከአንድ አመት ያላነሰ ነው፡፡
ከእርከን 29 ማለትም (ከ10 አመት መነሻ) ጀምሮ ሬንጁ ከሁለት አመት ያላነሰ ነው፡፡
ከእርከን 34 ማለትም (ከ15 አመት መነሻ) ጀምሮ ሬንጁ ከሶስት አመት ያላነሰ ነው፡፡
በየደረጃው ያለው የቅጣት እርከን መነሻ ሲቀመጥ፣ ከቅጣት እርከኑ ዝቅ ብሎ ከነበረው የቅጣት እርከን አማካይን መነሻ
በማድረግ የቅጣት መነሻና መድረሻው ተወስኗል፡፡
ለዚህ መመሪያ አላማ የአንድ ቀን እስራት ከአንድ ቀን (8 ሰአት) የግዴታ ስራ ጋር ተመጣጣኝ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
በቅጣት ማቅለያ ጊዜ የእስራት ቅጣት ወደመቀጮ እንደሚቀየር በወንጀል ሕግ አንቀጽ 179 የሚደነግግ በመሆኑ ወደመቀጮ
ሲቀየር ስንት ሊሆን እንደሚችል በሚያሳይ መልኩም የቅጣት እርከኑ ተዘጋጅቷል፡፡
2.2. የገንዘብ መቀጮን የሚመለከተው ሰንጠረዥ፣
የወንጀል ህጉን አንቀጽ 90 መሰረት በማድረግ የገንዘብ መቀጮም ደረጃ ወጥቶለታል፡፡
መነሻ ያደረገውም በአንቀጽ 90(1 እና 2) መሰረት ነው፡፡
ዝቅተኛ መነሻ ግን ለሁሉም ተመሳሳይ በህጉ የተመለከተው ነው፡፡ (10 ብር እና 100 ብር)
በዚህ መሰረት የገንዘብ መቀጮ ከዝቅተኛው ጣሪያ 1000 ብር እስከ ብር 500 ሺህ ሊደርስ በሚችል መልኩ
ተዘጋጅቷል፡፡
3. መመሪያው የሚመራባቸው አጠቃላይ ድንጋጌዎች፣
- በወንጀል ሕግ 189 ፍርድ ቤቶች ቅጣትን ሲወስኑ መጀመሪያ ማክበድ እንደሚገባቸው ቀጥለው ደግሞ ማቅለያ ምክንያቶችን መሰረት በማድረግ ማቅለል እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ ይህም ቅጣቱን ለማክበድ በመጀመሪያ መነሻ ቅጣት ሊወስኑ እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ ስለሆነም ዳኞች ማክበጃና ማቅለያ ምክንያቶችን መሰረት አድርገው ቅጣት ከመወሰናቸው በፊት መነሻ ቅጣት ማስቀመጥ እንደሚገባቸው ያመለክታል፡፡ ስለሆነም ዳኞች በቅድሚያ መነሻ ቅጣት ሊያስቀምጡ እንደሚገባ መመሪያው ያስገድዳል፡፡
- በወንጀል ህጉ አንቀጽ 88 ንኡስ አንቀጽ 4 ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅጣት አወሳሰን ወጥነትና ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ መመሪያ እንደሚወጣ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ወንጀሎችን በተመሳሳይ ደረጃ የሚያስቀምጣቸውን ባህርይ መሰረት በማድረግ ለተመሳሳይ ወንጀሎች ተመሳሳይና ተቀራራቢ ቅጣት መቅጣት፡፡ (ወጥነት)፣ እንዲሁም የወንጀል ፍሬነገሩ ተመሳሳይ ቢሆንም እንደወንጀሉ ከባድነትና አደገኛነት ደረጃዎችን በማውጣት ቅጣት መቅጣት ( ተመጣጣኝነት/ትክክለኛነት) ለማረጋገጥ እንዲቻል ለወንጀሎች የወንጀል ደረጃ ሊወጣላቸውና በዚህ መሰረት ቅጣቱ ሊወሰን እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡
- ህግ አውጪው ለእያንዳንዱ የወንጀል ድርጊት የቅጣት መነሻና መድረሻ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ይህም እንደወንጀሉ ሁኔታ ከመነሻው ጀምሮ ቅጣቱን ሊወስን እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡ ስለሆነም በወንጀሉ ከባድነት ወይም አፈጻጸም ቀላል የሚባለው ለወንጀሉ ከተቀመጠው መነሻ ቅጣት ጀምሮ እንደወንጀሉ ከባድነት ደረጃ በደረጃ እያደገ በሚሄድ መልኩ ቅጣቱ ሊወሰን እንደሚገባው ያስቀምጣል፡፡
- ህግ አውጪው በወንጀል ልዩ ክፍሉ ለእያንዳንዳንዱ ወንጀል ያስቀመጠው ጣሪያ ላይ የሚደረሰው ጠቅላላ ማክበጃ ምክንያቶች ሲኖሩ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ስለሆነም ማክበጃ ምክንያቶችን መሰረት አድርጎ ቅጣቱ ከመክበዱ በፊት የሚቀመጠው መነሻ ቅጣት የወንጀሉ ከባድነት ከፍ ያለ ቢሆንም (በህጉ ካልተወሰነ በስተቀር (ለምሳሌ ያህል በሞት ይቀጣል፣ በእድሜ ልክ እስራት ይቀጣል በሚል መልኩ ካልተቀመጠ) ጣሪያው ላይ አይሆንም፡
ቅጣቱ እንዲከብድ ህጉ በደነገገ ጊዜ (84) ለቅጣቱ ማክበጃ የሆኑትን ምክንያቶች አይነትና ብዛት እንዲሁም ወንጀለኛው የፈጸመውን ጥፋት ከባድነት በማመዛዘን ፍርድ ቤቱ በዚህ ሕግ ልዩ ክፍል በተመለከተው አግባብነት ባለው ድንጋጌ ከተወሰነው ቅጣት ጣሪያ ሳያልፍ ቅጣቱን ይወስናል፡፡ (አንቀጽ 183)
- በተመሳሳይ የቅጣት እርከን ላይ ለሚገኙ ወንጀሎች በቅጣት ማክበጃና ማቅለያ መሰረት የሚኖረው ጭማሪ ወይም ቅነሳ ተመሳሳይ ሊሆን ይገባል፡፡
- ዳኞች በተቀመጠው ፍቅድ ስልጣን (range) ከመነሻው እስከ መድረሻው በመመሪያው ያልተመለከቱ ሌሎች ምክንያቶችን መሰረት በማድረግ ለመወሰን ይችላሉ፡፡
- መመሪያው በወንጀል ህጉ የተቀመጡትን የቅጣት አወሳሰን ድንጋጌዎች ለማስፈጸም የሚወጣ በመሆኑ፣ በወንጀል ህጉ ውስጥ የተቀመጡትን አጠቃላይ መርሆዎችና ድንጋጌዎች መሰረት አድርጎ እየተተረጎመ ሊሰራበት እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡
- Details
- Category: Sentencing and Execution
- Hits: 11405
ቅጣትን የሚመለከቱ የወንጀል ህጉ ድንጋጌዎች ይዘት
በወንጀል ህጉ ሁለተኛ ታላቅ ክፍል (ልዩ ክፍል) ለእያንዳንዱ የወንጀል ድርጊት መነሻና መድረሻ ቅጣት ተቀምጠዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የቅጣት መነሻና መድረሻዎች የሚከተሉትን ይመስላሉ፡፡
- ከ1 አመት እስከ 10 አመት
- ከ3 አመት እስከ 10 አመት
- ከ5 አመት እስከ 15 አመት
በህጉ ልዩ ክፍል ከተመለከቱት ቅጣቶች በተጨማሪ አጠቃላይ የቅጣት አወሳሰን ድንጋጌዎች አሉ፡፡
- አንቀጽ 88 (የቅጣቶች አወሳሰን)
- አንቀጽ 84 (ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃዎች)
- አንቀጽ 82 (ጠቅላላ የቅጣት ማቅለያዎች)
- አንቀጽ 85 (ልዩ የቅጣት ማክበጃዎች)
- አንቀጽ 83 (ልዩ የቅጣት ማቅለያዎች)
- ከአንቀጽ 179-189 (ቅጣቱ ሲከብደና ሲቀል ስለሚጣለው ቅጣት መጠን)
- ከአንቀጽ 190-200 (ቅጣትን ስለመገደብ) ናቸው፡፡
እነዚህን የተለያዩ ድንጋጌዎች መሰረት አድርጎ ቅጣት እንዴት ይወሰናል? በወንጀል ህግ አንቀጽ 189(1) የሚከተለው ተደንግጎ እናገኛለን፡፡
‹በአንድ ወንጀል ላይ ቅጣት የሚያከብዱና የሚያቃልሉ ጠቅላላ ምክንያቶች በተደራረቡ ጊዜ ፍርድ ቤቱ አስቀድሞ ማክበጃ ምክንያቶቹን ከግምት በማስገባት ያከብድና ቀጥሎ የሚያቃልሉትን ምክንያቶች መሰረት አድርጎ ቅጣቱን ያቃልላል›
ይላል፡፡
ከዚህ መረዳት እንደምንችለው መጀመሪያ ለማክበድ ከየት ይነሳል? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፡፡ ስለሆነም በግልጽ ባይቀመጥም ዳኛው፣
- በቅድሚያ መነሻ ማስቀመጥ እንደሚኖርበት፣
- ቀጥሎ ማክበጃ ምክንያቶች ከአሉ ቅጣቱን ማክበድ እንደሚኖርበት፣
- ቀጥሎ ማቅለያ ምክንያቶች ከአሉ ቅጣቱን ማቅለል እንደሚኖርበት፣
ያስረዳል፡፡
ይሁንና፣
- መነሻው ስንት ይሁን? በሕጉ መልስ የለም፡፡
- ማክበጃዎች ሲኖሩ በምን ያህል ሊከብድ ይገባል ? በሕጉ መልስ የለም፡፡
- ማቅለያዎች ሲኖሩ በምን ያህል ሊቀል ይገባል ? በሕጉ መልስ የለም፡፡
ስለሆነም በወንጀል ህጉ የተቀመጡትን የቅጣት ድንጋጌዎችና ስለቅጣት አወሳሰን የተቀመጡት ድንጋጌዎች በፍርድ ቤት የሚሰጡ ቅጣቶች፣
- ወጥነት፣
- ትክክለኛነት ያለው፣
ለማድረግ የሚያስችሉ አይደሉም፡፡
የቅጣት ውሳኔዎች ግምገማ
ቅጣት የተሰጠባቸው መዝገቦችን ስንመለከት፣
አቃቤ ህግ፣
- ቅጣቱ ከብዶ ይወሰን፣
- ተመጣጣኝ ቅጣት ይሰጠው፣
ከሚል ባለፈ ከብዶ ሲባል ከባዱ ምን ያህል እንደሆነ፣
- መነሻው ስንት ሆኖ ሊከብድ እንደሚገባ፣
- ተመጣጣኝ የሚሆነው ምንእንደሆነ ፣
የሚያመለክቱ አይደሉም፡፡
በተከሳሽ በኩል የሚቀርቡ የቅጣት አስተያየቶችም ጥቅል ሆነው ከሚቀርቡ በስተቀር ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ዳኛው ቅጣትን ሲወስንም፣ ቅጣትን ለማክበድ፣
- የወንጀል ሪከርድ አለው
- የወንጀል አፈጻጸሙ አደገኛነት አለው፣
- ድርጊቱ የተፈጸመው በአፍቅሮ ንዋይ በመሆኑ የሚሉ ምክንያቶችን በመጥቀስ፣
ቅጣቱን ለማቅለል
- የወንጀል ሪከርድ የለውም ስለሆነም አደገኛ አይደለም፡፡
- የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነው፡፡ ወዘተ የሚሉ ምክንያቶችን በመጥቀስ፣
ቅጣት ይወስናል፡፡
ይሁንና ዳኞች እነዚህን ምክንያቶች ይጥቀሱ እንጂ፣
- በየትኛውም መዝገብ ቅጣቱን ለመወሰን መነሻው ስንት መሆን እንዳለበት ተመልክቶ አይታይም፡፡
- በማክበጃነት የቀረቡትንና በማቅለያነት የቀረቡትን ምክንያቶች የሚቀበለውና የሚቀበሉትንና የማይቀበሉትን ከለዩ በኋላ፣ ከምክንያቶቹ ጋር ግንኙነቱን ለማስረዳት በማይቻል መልኩ በጥቅሉ የቅጣቱ መጠን ይቀመጣል፡፡
ስለሆነም፣
- መነሻ የቅጣት መጠኑ ስንት እንደሆነ፣
- በማክበጃነት የተቀመጡት ምክንያቶች ቅጣቱን በማክበድ ያላቸው አስተዋጽኦ እንዲሁም
- ማቅለያ ምክንያቶች እንዴት አገልግለው ቅጣቱ እንደቀለለ፣
ለማወቅ አይቻልም፡፡
ከዚህ አጠቃላይ ግንዛቤ በመነሳት በአገራችን ቅጣት አወሳሰን ምክንያታዊነት የጎደለው፣ በእርግጥም የተጣለው ቅጣት አግባብነት ያለው መሆኑን ለማስረዳት አይቻልም፡፡ በዚህም ምክንያት፣
በአንድ ዳኛ በተለያየ ጊዜ ወይም በተለያዩ ዳኞች ተቀራራቢና ተመሳሳይ ለሆኑ ወንጀሎች የሚሰጡ የተለያዩ ቅጣቶች መኖራቸው፣
ከዚህም የተነሳ በቅጣት አወሳሰን ተገማችነት የሌለው መሆኑ፣
ቅጣት አወሳሰን ግልጽነት የሌለውና በፍትህ አካላቱ ባለሙያዎች ላይ ተጠያቂ ለማድረግ የማያስችል ሆኖ እናገኘዋለን::