- Details
- Category: Property Law
ስለይዞታ (Possession)
የይዞታ ትርጉም፦
የፍ/ሕግ ቁጥር 1140 ያስቀመጠው ትርጉም፤ “ይዞታ ማለት አንድ ሰው አንድን ነገር ብእጁ አድርጎ በእውነት የሚያዝበት ሆኖ ሲገኝ ነው” የሚል ነው። ከዚህ ትርጉም መገንዘብ የሚቻለው ይዞታ ማለት አንድ የሚንቀሳቀስ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረት አሻሚ ወይም ድብቅ ባልሆነ ሁኔታ በቁጥጥር ስር በማድረግ ልታዝበት የምትችል ማለት ነው። እዚህ ላይ ንብረቱን መቆጣጠርና ማዘዝ መቻል ብቻ ሳይሆን በንብረቱ መጠቀምና መገልገልም ይጨምራል።
አንድ ሰው በተለያየ መንገድ ባለይዞታ መሆን ይችላል። ለምሳሌ ። የአላባ ተጠቃሚ በመሆን፣ የንብረቱ ባለሃብት በመሆን፣ አንድ ንብረት በመያዥነት (pledge) በመያዝ ወዘተ። ይዞታ በአንድ ሰውና በአንድ ንብረት መካከል ስለሚኖር ግንኙነት የሚገልፅ እንጂ የንብረት ባለሃብትነት መብት ማለት አይደለም፤ እንዲያውም ከባለሃብትነት መብት የጠበበ መብት ያለው ነው።
ይዞታ ስለመኖሩ የሚያረጋግጡ መለኪያዎች /መመዘኛዎች/
ሀ/ አንድ ዕቃ (corpus) መኖር አለበት ብቻ ሳይሆን ይህንን ዕቃ በይዞታ ስር የማድረግ ሓሳብ (Animus) መኖር አለበት። ስለዚህ ይህ ነጥብ የሚያብራራልን ነገር ቢኖር ይዞታው በቁጥጥር ስር ከማድረግ በተጨማሪ ለመጠቀምና ለመገልገል በሚል ሓሳብ የተያዘ መሆን እንደአለበት ነው።
ለ/ ቀጥተኛ ያልሆነ /ተዘዋዋሪ/ ይዞታ በሚመለከት ደግሞ ዕቃው በሌላ ሰው እጅ የተያዘ ሆኖ ንብረቱ የመቆጣጠርና የመጠቀም ሓሳብ (intention) ግን ከባለይዞታው ጋር ሊቀር ይችላል። አብዛኛው ጊዜ ሲታይ ግን ሓሳብ (Animus) ዕቃውን ወደ ሄደበት ይከተላል ነው የሚባለው።
በዚህ ዙርያ ሁለት ንድፈ - ሓሳባዊ አስተያየቶች ይንፀባረቃሉ
- 1)ሳብጀክቲቭ (subjective) ንድፈ ሓሳብ /ሳቪኒ በሚባል የሕግ ሙሁር የሚራመድ ሓሳብ/ ሆኖ ባለይዞታ ለመሆን አንድ ሰው አንድ ነገር በፍላጐቱ ለራሱ ብሎ የያዘው መሆን አለበት። ዋናው ነገር የሰውየው ሓሳብና ፍላጐት ነው መታየት ያለበት የሚል ነው።
- 2)ኦብጀክቲቭ (objective) ንድፈ ሓሳብ / ሄሪንግ በሚባል ሙሁር የሚራመድ/ ሆኖ አንድ ሰው ባለይዞታ ነው ለማለት ምን ሓሳብ አለው ሳይሆን መታየት ያለበት ዕቃውን ከማን እጅ ጋር ነው ያለው የሚል ነገር ነው መታየት ያለበት። ይኸውም ዕቃውን በእጁ ያስገባ የዚያ ንብረት ባለይዞታ መሆኑን ይገመታል ይላሉ።
ይዞታ የሚገኝበትና የሚቀርበት ሁኔታ
1.ይዞታ የሚገኝበት ሁኔታ ሁለት ነገሮችን አካትቶ የያዘ ነው፦
የመጀመርያው ሁኔታ ዕቃውን በአካል መቆጣጠር እና እንደ ባለይዞታ መጠን የመጠቀምና የመገልገል ሓሳብ ሲኖር ነው። በመርህ ደረጃ ሁለቱ ሁኔታዎች ተማልተው መገኘት የግድ የሚል ሆኖ ፤ በልዩ ሁኔታ ግን ሁለቱ ሊለያዩ ይችላሉ።
ለምሳሌ፦ የኣእምሮ በሽታ ያለው ሰው የማሰብ ችሎታው ስለሚያጣ ወይም ስለሚቀንስ የሞግዚቱ ፈቃድ ያስፈልገዋል። በሌላ ሁኔታ ደግሞ አንድ ሰው አንድ ንብረት /ዕቃ/ በኣካል ሊይዘው /በቁጥጥሩ ስር ሊያደርገው/ ይችለል፤ ሆኖም የባለይዞታነት ሓሳብ ግን በሌላ ሰው ሊኖር ይችላል።
ለምሳሌ፦ በወካይና በተወካይ መካከል የሚታይ ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል።
2.ይዞታ የሚቀርበት ሁኔታ፦
ሀ/ ይዞታ የሚጠፋበት አንድ ምክነያት በባለይዞታ ፈቃድ ሁለቱ ሁኔታዎች ሲጠፉ ነው።
-ለሌላ ሰው ሲተላለፍ፤ ይኸውም ዕቃው በአካል ለሌላ ሰው ሊተላለፍ ይችላል። እንዲሁም ዶክሜንት በማግኘት ሊሆን ይችላል። በዶክሜንት አማካኝነት ሊተላለፉ የሚችሉ የማይንቀሳቀሱና ልዩ ተንቀሳቃሽንብረቶች ናቸው።
-ባለይዞታው ዕቃውን /ንብረቱን/ አያስፈልገኝም ብሎ የጣለው አንደሆነ ነው።
ለ/ ባለይዞታ የመሆን ሓሳብ ቢኖርም ንብረቱ የጠፋ እንደሆነ /ለምሳሌ እንስሳ ሲጠፋ ጊዜ/
ሐ/ ባለይዞታ የመሆን ሓሳብ ጠፍቶ ንብረቱ ግን ከእጁ ሳይወጣ ሊቆይ የሚችልበት ሁኔታ ሲኖር። ለምሳሌ ፦ ንብረቱ ሸጦ ሲያበቃ ወደ ገዢ ሳያስተላልፈው የቀረ እንደሆነ።
የይዞታ ሕጋዊ ውጤት
ባለይዞታ መሆን ከሚያስከትላቸው ውጤቶች አንዱ በባለይዞታነቱ ክስ የማቅረብ እና የንብረቱ ባለሃብት እንደሆነ የመገመት መብት አለው ። ማድረግ የማይችለው ነገር ቢኖር ባለሃብት ያልሆነ ባለይዞታ ከሆነ ንብረቱ የማስተላለፍ መብት ላይኖረው ይችላል። ባለይዞታ እንደባለሃብት የመገመት መብት ኣለው ስንል በሁለት ምክንያቶች ነው።
1)አብዛኛው ጊዜ የአንድ ንብረት ባለሃብት የዛ ንብረት ባለይዞታም ስለሚሆን፤
- 2)አንድ ሰው ከንብረት ባለሃብት ፈቃድ ውጭ ባለይዞታ ለመሆን አስቸጋሪ ስለሚሆን ወይም ስለማይቻል ነው።
ይዞታ ጉድለት ያለበት እንዲሆን የሚያደርጉ ሁኔታዎች
1 ቀጣይነትየሌለውመሆን፦
የአንድ ንብረት ባለይዞታ የሆነ ሰው ጥንቁቅ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ ይዞታውን ሊጠቀምበት እንደሚገባ ይጠበቃል። ምክንያቱም በይዞታ ላይ ቀጣይነት ያለው አጠቃቀም ከሌለ አንድ ሰው በአንድ ነገር ላይ ይዞታ አለው ለማለት ስለሚያስቸግር ነው። ይህ ማለት ግን አልፎ አልፎ የማቋረጥ ሁኔታ አይኖርም ማለት አይደለም። አንድ ሰው በአንድ ነገር ላይ የነበረው የይዞታ መብት ተቋርጧል አልተቋረጠም ለማለት እንደ ነገሩ /ንብረቱ/ እና የሚሰጠው አገልግሎት ዓይነት የሚለያይ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፦ አንድ የእርሻ መሬት ባለይዞታ የሆነ ሰው መሬቱን በክረምት ወቅት ብቻ ሊጠቀምበት ይችላል። የእርሻ መሬቱ በበጋ ወቅት አለመጠቀሙ ባለይዞታ አይደለም ሊያሰኘው አይችልም። የማቋረጡ ሁኔታ አልፎ አልፎ መሆኑን ቀርቶ ለተራዘመና ላልተለመደ ጊዜ የቆየ እንደሆነ ግን በባለይዞታውና በንብረቱ መካከል የነበረ ግንኙነት እንደተቋረጠ ስለሚቆጠር ባለይዞታነት አለ ለማለት ያዳግታል (ፍ/ሕግ ቁ.1142)
2 ይዞታውበሓይልየተገኘእንደሆነ፦
የባለይዞታነት መብት ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚገኝና ጥቅም ላይ የሚውል መሆን ይገባዋል። ይዞታው የተገኘው በሓይል የሆነ እንደሆነ ግን ጉድለት ያለበት ነው ይባላል። በአንዳንድ የሕግ ስርዓቶች አንድ ነገር በሓይል የተገኘ እንደሆነ ለዘለቀይታው ጉድለት ያለበት ሆኖ ይቀጥላል። በርከት ባሉ ሌሎች የሕግ ስርዓቶች ግን በሓይል የተገኘ ይዞታ ጉድለት ያለበት ሆኖ የሚቆየው ለአንድ ዓመት ብቻ ነው። የእኛ የሕግ ስርዓት ደግሞ የፍ/ሕጉ የአማርኛው ቅጂ ሁለት ዓመት ብሎ ሲደነግግ እንግሊዝኛው ቅጂ ግን አንድ ዓመት መሆኑን ያመለክታል። ስለዚህ በእኛ የሕግ ስርዓት ባለይዞታ የሆነ ሰው ንብረቱ በሓይል የተወሰደበት እንዲመለስለት ወይም የተፈጠረበት ሁከት እንዲወገድለት ክስ ማቅረብ ያለበት በሁለት ዓመት ውስጥ ነው። ይዞታዬን በሓይል ተወሰደብኝ ወይም በይዞታዬ ላይ ሁከት ተፈጠረብኝ የሚል ሰው /ባለይዞታ/ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ሰው ክስ የማቅረብ መብት የለውም። ምክንያቱም ሕጉ ከቀድሞው ባለይዞታ ቀጥሎ ጥበቃ ያደረገለት ለወቅቱ ባለይዞታ በመሆኑ ነው።/ፍ/ሕግ ቁ.1148/
3 ይዞታውበደብቅየተያዘእንደሆነ፦
እንደ ሌሎች ሕጋዊ መብቶች ሁሉ ይዞታ ጥቅም ወይም አገልግሎት ላይ መዋል ያለበት ግልፅ በሆነ ሁኔታና ህዝብ እያወቀው መሆን አለበት። ይዞታህን ለማወቅ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሁሉ እንዲያውቁት በግልፅ መታየት አለበት ማለት ነው። ባለዞታው ይዞታውን በግልፅና ሌላ ሰው በሚያውቀው መንገድ /ሁኔታ/ የማይጠቀምበት ከሆነና በድብቅ የመያዙ ነገር ሆነ ብሎ ያደረገው እንደሆነ ይዞታው ድብቅ ነው ይባላል። በድብቅ የተያዘው ንብረት ባለይዞታ እኔ ነኝ የሚል ወገን ይዞታውን ለማስመለስ ክስ ማቅረብ ያለበት በሁለት ዓመት ውስጥ ነው። በሌላ በኩል አንድ ንብረት በድብቅ ይዞ የቆየ ሰው በደብቅ የመጠቀሙ ነገር ቢያቆምና በግልፅ መጠቀም ቢጀምር የቀድሞው ባለይዞታ ግን ይህንን ነገር እያወቀ ዝም ያለ እንደሆነ ድብቅነቱ ይቀራል ብቻ ሳይሆን አዲሱ ባለይዞታ በይርጋ አማካኝነት ሙሉ በሙሉ ባለይዞታ የሚሆንበት ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል። ይህ አዲስ ባለይዞታ ይዞታውን በነጠቀው ወይም በይዞታው ላይ ሁከት የፈጠረበትን ሰው ላይ ክስ ማቅረብ ወይም እንደየሁኔታው ይዞታውን በሓይል የመከላከል መብቱ የተጠበቀ ይሆናል። (ፍ/ሕግ ቁ.1146(2))
4 እውነተኛ ይዞታ ስለመኖሩ የሚያጠራጥር እንደሆነ፦
አንድ ሰው የአንድ ነገር ባለይዞታ እንዲሆን የሚጠበቀው በማያሻማ ወይም በማያጠራጥር ሁኔታ ነው። የሚያጠራጥር ሁኔታ ሊኖር የሚችለው ደግሞ የይዞታ መመዘኛ ከሆኑት ዋንኛ ነገሮች አንዱ ሲጠፋ ነው ማለት ይቻላል። በተለይ ይህንን ነገር የሚከሰተው አንድ ሰው የአንድ ነገር ባለይዞታ ነው ወይስ ስለባለይዞታ ሆኖ ነገሩን የያዘ ነው የሚለውን ነገር ለመለየት አስቸጋሪ ሲሆን ነው።
በአጠቃላይ ባለይዞታ መሆንኑ የሚያረጋግጡ መመዘኛዎች (element) ስለመኖራቸው ወይም አለመኖራቸው አጠራጣሪ ነገር በሚኖርበት ጊዜ ባለይዞታ ነው ለማለት አስቸጋሪ ይሆናል። (ፍ/ሕግ ቁ. 1146(3))።
የይዞታ መብት የሕግ ጥበቃ ያስፈለገበት ምክንያት
የይዞታ መብት የሕግ ጥበቃ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት እያንዳንዱ ዜጋ ወይም ሕ/ሰብ በአጠቃላይ ንብረቱን በሰላም እንዲጠቀምበትና እንዲገለገልበት ለማስቻል ነው። ይህ የይዞታ መብት ከፍ/ሕግ አልፎ በኢፌዴሪ ሕገ መንግስትም ትልቅ ቦታ ያገኘና ጥበቃ የተደረገለት መብት ነው /አንቀፅ 40/።
አንድ ዕቃ ወይም ንብረት በእጁ ያስገባ ሰው አብዛኛው ጊዜ ባለይዞታ ነው ሲባል የግድ ዕቃውን ተሽክሞ መሄድ አለበት ማለት አይደለም። ለምሳሌ፦ የቤት ስራተኛ የምትሰራበት ቤት ንብረት ስለያዘች ብቻ ባለይዞታ ነኝ ማለት አትችልም። አንድ ሰው ለሌላ ሰው ብሎ አንድ ንብረት የሚይዝበት ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜም ንብረቱን የያዘ ሰው ባለይዞታ ነው እንደማይባል ፍ/ሕጉ ያስቀምጣል። በሌላ ሰው ስም ንብረት መያዝ ሊኖር የሚችለው ባለይዞታ የሆነ ሰው ከሌላ ሰው ጋር በሚያደርገው ስምምነት ንብረቱን እንዲይዝለት የሚያደርግበት ሁኔታ ሲኖር ነው። ስምምነቱ ሲቋረጥ ደግሞ ንብረቱ ወደ ባለይዞታው ይመለሳል ማለት ነው። በሌላ መንገድ ደግሞ መጀመርያ ባለይዞታ የነበረ ሰው ኃላ የበላይዞታነት መብቱ ለሌላ ሰው ያስተላለፈው እንደሆነና ዕቃው ግን ለተወሰነ ጊዜ ለአዲሱ ባለይዞታ ሳያስተላልፈው በእጁ ያቆየው እንደሆነ ባለይዞታ መሆኑ ቀርቶ ስለሌላ ሰው ሆኖ ንብረት የያዘ ሰው ነው ይባላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ ስለሌላ ሰው ሆኖ ንብረት የመያዝ ውጤት ምንድነው የሚል ነው ? ስለሌላ ሰው ሆኖ ንብረት የመያዝ ውጤት፦
1.በያዘው ንብረት ላይ በይርጋ አማካኝነት የባለሃብትነት መብት ማረጋገጥ አይችልም
2.እንደ ባለይዞታ ክስ የማቅረብ መብት አለው።
3.ከባለይዞታ ጋር ስምምነት በማድረግ ወደ ባለይዞታነት መለወጥ ይችላል