Font size: +
17 minutes reading time (3328 words)

ስለዊዝሆልድንግ ታክስ

መግቢያ

በታክስ ሥርዓት ላይ ጥናታቸውን የሰሩ ባለሙያወች “the tax system must be dynamic with in the dynamic world ” - ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ የታክስ ሥርዓቱ ተለዋዋጭ ካልሆነና ዓለም በፈጠረው ቴክኖሎጅ የሚደረገውን የታክስ ስወራ ተግባር መከላከል፣ መቆጣጠር እንድሁም ድርጊቱ ተፈፅሞ ከተገኘ ሊቀጣ የሚችል ሥርዓት ካልዘረጋ የአንድ ሀገር ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል ይላሉ፡፡ እኔም ይህንን ሀሳብ ከሚጋሩ ባለሙያዎች አንዱ ነኝ፡፡ በመሆኑም አንድት ጠንካራ ሉዓላዊት ሀገር ለመገንባት ዘመናዊ ዓለምን ያማከለ ዘመናዊ የታክስ ሥርዓት መዘርጋት ስፈልጋል፡፡ ይህ ተግባር ደግሞ ገቢን በግልፅነትና ተጠያቂነት፣ በፍትሃዊነትና እኩልነት እንድሁም በዘላቂነት መሰብሰብና ማሳደግ የሚችል ሕግ ከማውጣት ይጀምራል፡፡ ሕግ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የወጣውን ሕግ ማስፈፀም የሚችል ተቋም እና ሠራተኛ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ተቋሙ እና እያንዳንዱ ሠራተኛ ደግሞ በየደረጃው የወጡ ሕጎችን ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የማሳወቅ ሞራላዊ ግደታ አለበት፡፡ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወድህ በግብር ይግባኝ ኮሚሽን እና በፍ/ቤቶች ቅሬታ እያስነሳያለው የግብር ዓይነት ተቀንሶ የሚያዝ ታክስ/ዊዝሆልድንግ ታክስ ሲሆን ለዚህ ጽሑፍ ዓላማ ከእነዚህ ታክሶች አንዱ የሆነውን እና በንግድ ማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞና በተግባር የአፈፃፀም ችግር የሚታይበትን በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 አንቀፅ 92 ላይ የተቀመጠውን በሀገር ውስጥ ከሚፈፀሙ ክፍያወች ላይ ተቀንሶ የሚያዝ ግብርን በዝርዝር ለመዳሰስ እምክራለሁ፡፡ ወደ ጉዳዩ ከመግባቴ በፊት ግን ዊዝሆልድንግ ታክስ ምን ማለት እንደሆነ ትርጉም ሰጥቼ ማለፍ እፈልጋለሁ፡፡

  1. ተቀንሶ የሚያዝ ታክስ( withholding tax)

1.1 በሀገር ውስጥ ከሚፈፀሙ ክፍያወች ላይ ተቀንሶ የሚያዝ ታክስ /withholding of tax from domestic payments/

               ሀ. ትርጉም /definition/

የትርጉም ጥያቄ ስናነሳ ለመሆኑ ተቀንሶ የሚያዝ ታክስ (withholding tax) ምን ማለት ነው? በህጉ የተሰጠው ትርጉም አለ ወይ? ከማንኛው ሂሳብ ላይ ነው ተቀንሶ የሚያዘው?በሀገር ውስጥ ከሚፈፀሙ ክፍያወች ላይ ተቀንሶ የሚያዝ ታክስስ ምንድነው? ከመጀመሪያው ፅንሰ ሀሳብ (concept) ጋር የሚለይበት ሁኔታ አለ ወይ ?የሚል ጥያቄ በአዕምሮችን ውስጥ እንድፈጠርብን ያደርጋል፡፡

በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/08 አንቀፅ 2(44) ላይ በግልፅ እንደተደነገገው ተቀንሶ የሚያዝ ታክስ(ዊዝሆልድንግ ታክስ) ማለት በፌደራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 ክፍልአስር መሰረትከተከፋይ ሂሳቦች ላይ ተቀንሶ ”መያዝ ያለበት ታክስ ነው፡፡ የገቢ ግብር አዋጁ ክፍል አስር በአዋጁ ከአንቀፅ “88-98” ያለውን ድንጋጌ የሚይዝ ነው፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለውዊዝሆልድንግ ታክስ ከተሰብሳቢ ሂሳብ ላይ ሳይሆን ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀንሶ የሚያዝ ታክስ መሆኑን ነው፡፡ ይህም ማለት በህጉ በተመለከቱት ሂሳቦች ላይ አንድ ሰው ግብይት በማካሄድ ሂሳብ ሲከፍል ከሚከፍለው ክፍያ ላይ ቀንሶ በመያዝ የሚከፈል ታክስ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ዊዝሆልድንግ ታክስ ከተሰብሳቢ ሂሳብ ላይ ተቀንሶ የሚያዝበት ልዩ ሁኔታ የለም ማለት አይደለም፡፡ በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 አንቀፅ 2(26) እና 93 መሰረትዊዝሆልድንግ ታክስከራስ ገቢ (ከሚሰበስበው ገቢ) ላይግብር ቀንሶ መያዝንም ይጨምራል፡፡ በዚህ ሁኔታ ገቢውን የሚያገኘውም ሆነ ግብሩን ቀንሶ በመያዝ የሚከፍለው ራሱ ገቢውን ያገኘው ሰው ይሆናል፡፡ ይህ በእንድህ እያለ(as such)፡-

በሀገር ውስጥ ከሚፈፀሙ ክፍያወች ላይ ተቀንሶ የሚያዝ ታክስን /withholding of tax from domestic payments/ በተመለከተ በተግባር ኦድተሮች ቅድሚያ ግብር ክፍያ ነው የሚል ትርጉም በመሰጠት በሚያወጡት የውሳኔ ማስታወቂያ ላይ ዊዝሆልድንግ ታክስ /ቅድሚያ ግብር ክፍያ/ በማለት (interchangabely) ሲጠቀሙበት እናስተውላለን፡፡ ይህም ግብር ከፋዩ ሰው/ድርጅት/የበጀት አመቱ ተጠናቆ ገቢውን አሳውቆ እስከሚከፍል ድረስ ከዚህ ሰው ጋር ግብይት ያከናወነው ገዥ ወገን ከሚከፍለው ክፍያ ላይ ቀንሶ በማስቀረት ሊከፍል የሚገባው ታክስ ነው ከሚል ፅንሰ ሀሳብ የመነጨ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ይህ በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 አንቀፅ 92 ላይ የተደነገገው ታክስ የዊዝሆልድንግ ታክስ አንዱ ክፍል (part and parcel of withholding tax) ሲሆን ትርጉሙም በሀገር ውስጥ ከሚፈፀሙ ተከፋይ ሂሳቦች ላይ ተቀንሶ የሚያዝ ታክስ ነው፡፡ ልዩነቱ ተቀንሶ ሚያዝ ታክስ /ዊዝሆልድንግ ታክስ/ ጠቅላይ ፅንሰ ሀሳብ(general concept) በመሆኑ በገቢ ግብር አዋጁ ከአንቀፅ 88-98 ያለውን ታክስ የሚያጠቃልል ሲሆን በሀገር ውስጥ ከሚፈፀሙ ክፍያወች ላይ ተቀንሶ የሚያዝ ታክስ ደግሞ በዚሁ አዋጅ አንቀፅ 92 ላይ የተደነገገ የዚሁ የዊዝሆልድንግ ታክስ አካል /subset/ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ከዚህ በኋላ ለዚህ ጽሑፍ ዓላማ ይህንን ታክስ በአጭሩ ዊዝሆልድንግ ታክስ እያልኩ እገልፀዋለሁ፡፡

ለ. ዓላማ

የታክሱን ዓላማ ስናነሳ ለመሆኑ አንድ ሰው የሌላን ሰው ግብር ቀንሰህ በመያዝ ክፈል በማለት ህጉ ግደታ የጣለው ለምንድነው? የራሱ ግብር ባልሆነ ነገር ላይ የዊዝሆልድንግ ግደታ ለምን ይጣልበታል? የሕግ አውጭው ዓላማ /intention of the legislator/ ምንድነው የሚሉ ጥያቄወችን እንድናነሳ ያደርገናል፡፡

  • ይህ የታክስ ዓይነት የመጣበት ዋነኛ ዓላማ የመንግስት ካዝና በበጀት ዓመቱ ውስጥ /12 ወር ጊዜያት/ ገንዘብ እንዳያጣና በማጣቱ ምክንያት የሚገነቡ የህዝብ መሰረተ ልማቶች እንዳይቋረጡ ለማድረግ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ መንግስት ከዓመት እስከ ዓመት በወራት ሳይወሰን በካዝናው ገንዘብ እንድኖረው ማድረግ ነው፡፡ መንግስት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ብዙ ቢሊየን ብሮችከማገኝና የዛኔ ካዝናየን ከማጨናንቅ በዓመት የማገኘው ገንዘብ በየወሩ ተከፋፍሎ ወደካዝናየ ቢገባ ካዝናየ ሁልጊዜ ያለምንም የወራት ልዩነት ገንዘብ ስለሚኖረው ልማትን ለማፋጠን አመቺ ነው ከሚል እሳቤ/justification/የመጣ ነው፡፡ በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 አንቀፅ 18 መሰረት የንግድ ትርፍ ግብር የሚከፈለው በዓመት ነው፡፡ ይህ ማለት መንግስት ገቢ የሚያገኘው ዓመት /12 ወር/ ጠብቆ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የዊዝሆልድንግ ታክስ ፅንሰ ሀሳብ የመጣውመንግስት ገቢ የሚያገኘውና ካዝናው የሚሞላው በበጀት ዓመቱ መጨረሻ በጊዜ ተወስኖ በመሆኑ ማለትም የበጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ባሉት ወራት መንግስት ገቢ ስለማያገኝካዝናው ባዶ ይሆናል /እጥረት ይገጥመዋል/ ማለት ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ግብር የመክፈያው ጊዜ እስከሚደርስ ድረስ ከምትከፍለው ክፍያ ላይ እየቀነስክ በመያዝ ግብር ክፈለኝ፤ካዝናየን ሙላልኝ ከሚል የመንግስት የፖሊሲ እሳቤ የመጣ ነው፡፡ አንድ የመንግስት ሠራተኛበወሩ መጨረሻ ደምወዙን አግኝቶ በአንድ ጊዜ ኪሱን ከሚያጨናንቅና ሌላ ጊዜ ኪሱ በአንፃሩ ባዶ ከሚሆን በሁሉም ቀን መጠነኛ ገንዘብ በኪሱ ቢኖረው ጥሩ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሠራተኛው እቃ ለመግዛት የሚችለው ደምወዝ ሲወጣ ወር ጠብቆ ይሆናል፤ደምወዝ ከመውጣቱ በፊት እቃ ለመግዛት የመግዛት ዓቅም/purchasing power/ አይኖረውም ማለት ነው፡፡ ልክ እንደ መንግስት ሠራተኛ መንግስትም በአንድ ጊዜ ግብር አግኝቼ ካዝናየን ከማጨናንቅና ሌላ ጊዜ ካዝናየ ብርድ ከሚበርደው ሁልጊዜ መጠነኛ ጥጋብ ይሁንልኝ፤መጠነኛ ገንዘብ ላግኝ ከሚል የኢኮኖሚ ፖሊሲ/ecomonomic policy/ የመነጨ የታክስ ዓይነት ነው፡፡
  • ሌላው ዓላማ የመንግስትን ገቢ መጨመር ነው፡፡ ገንዘብ ዋጋ /value/ አለው፡፡ የዋጋ ግሽበት/inflation/ ባለባቸው ሀገሮች የአንድ ገንዘብ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነስ በመሄድ የመግዛት አቅሙ/purchasing power/  ይዳከማል፡፡ መንግስት አንድ ሚሊዮን ብር በበጀት ዓመቱ ከሚያገኝና ይህንን ገንዘብ በ12 ወራት ውስጥ እየተቆራረጠ ቢያገኘው በወራት እየተከፋፈለ የሚያገኘው ገንዘብ የበለጠ የመንግስትን ገቢ ይጨምራል፡፡ ምክንያቱም ባገኘው ገንዘብ ልክ ሌላ ገንዘብ የሚያስገኝ ስራ ስለሚሰራና ትርፍ ስለሚያገኝ ነው፡፡ ለምሳሌ በየወሩ የሚያገኘውን ገንዘብ ባንክ ቢያስቀምጠው ወለድ ያገኛል፡፡
  • የታክስ ስወራ ተግባርን/tax evasion/ ይከላከላል፡፡ አሁን በደረስንበት የሉላዊነት ዘመን /era of globalization/ገቢ የሚያገኝ ሰው ገቢውን የሚደብቅበትና የሚያሳንስበት ብዙ ሁኔታወች አሉ፡፡ ስለዚህ ከፋዩ /ገዥው/ ከሚከፍለው ክፍያ ላይ ግብር ቀንሶ የሚያስቀር ከሆነ ሻጩ ሊደብቅ የሚችለውን ግብር በቅድሚያ ለመንግስት እየከፈለ ነው፡፡ ይህ በሁለት መልኩ ይታያል፡፡
  1. በአዋጁ አንቀፅ 92 (1)መሰረት ገዥው ከሚከፍለው ክፍያ ላይ 2% ቀንሶ ሲያስቀር ሻጭው በ2% ልክ ቀንሶ ሊያስቀር የሚችለውን ገቢ እና ግብር ገዥው እያዳነ ነው ማለት ነው፡፡
  2. በአዋጁ አንቀፅ 92 (4) መሰረት ሻጭው/አቅራቢው/ የታክስ መለያ ቁጥሩን ካልሰጠ ገዥው ከሚከፍለው ክፍያ ላይ 30% ቀንሶ ሲያስቀር ሻጭው በ30% ልክ እና ከዚህ ባነሰ መልኩ ሊደብቅ የሚችለውን ገቢ እና ግብር ገዥው እያዳነ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ህጉ የዊዝሆልድንግ ታክስ ቀንሰህ በመያዝ ክፈለኝ ሲል በአንድ በኩል ሻጩ/አቅራቢው/ ሊደብቅ የሚችለውን ግብር አድንልኝ እያለ ነው፡፡

እነዚህን ዓላማወች በዝርዝር ያነሳሁበት ምክንያት የዊዝሆልድንግ ታክስ የሚደነግገውን የሕግ ክፍል ስንተረጉም ይህንን ዓላማ በሚያሳካ መልኩ መተርጎም ስላለብን እና ከዚህ ቀጥሎ የማቀርባቸውን ነጥቦች በአመክንዮ/withlogic/ ለመረዳት ያመች ዘንድ ነው፡፡

ሐ. የታክሱ መሰረቶች /tax bases/

በአዋጁ አንቀፅ 92 (1)(ሀ) እና(ለ) ላይ እንደተደነገገውድርጅት (በታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/08 አንቀፅ 2(5)፣ (6) እና (23) የተሰጠውን ትርጉም የሚይዝ ሲሆን) ፣ የመንግስት መስሪያ ቤት ( የፌደራል እና የክልል መንግስት መስሪያ ቤቶች ) ፣ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት /non governmental organization/እና ባለስልጣኑ በመመሪያ ግደታ የሚጥልባቸው ግብር ከፋዮች ( ይሁን እንጅ ባደረኩት ማጣራት ባለስልጣኑ እስከአሁን ድረስ ያወጣው መመሪያ የለም) ፡-

  • በኢትዮጵያ ውስጥ
    • በአንድ ግዥ ወይም በአንድ የእቃ አቅርቦት ውል ከ10 ሽህ ብር በላይ ለሆነ ክፍያ ወይም
    • በአንድ የአገልግሎት ውል ከ3‚000 ብር በላይ ለሚፈፀምክፍያ ለሻጩ/አቅራቢው ከሚከፈለው ክፍያ ላይ 2%ቀንሰው በመያዝ ለባለስልጣኑ ግብር የመክፈል ግደታ አለበት፡፡ አቅራቢው ወገን የታክስ መለያ ቁጥሩን ካልሰጠ ደግሞ 30%ከክፍያው ላይ ቀንሰው የመያዝ ግደታ አለባቸው፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለው ግዥው ከ10 ሽህ ብር በታች ከሆነ ወይም አገልግሎቱ ከ3‚000 ብር በታች ከሆነ የዊዝሆልድንግ ታክስ የመክፈል ግደታ የለባቸውም ማለት ነው፡፡

ለምሳሌ.አንድ “xy”የሚባል ድርጅት ወይም የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮወይም የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቢ ሕግወይም UNICEFበባህር ዳር ከተማ ከሚገኝ “AB” ከተባለ የጨርቃ ጨርቅ አምራች ድርጅት ጋር ለሰራተኞቻቸው የ100‚000 ብር የደንብ ልብስ ግዥ ቢፈፅሙ ሻጩ/አቅራቢው የታክስ መለያ ቁጥር ከሰጣቸው ከሚከፍሉት ክፍያ ላይ 2% ቀንሰው በማስቀረት ለባለስልጣኑ ዊዝሆልድንግ ታክስ መክፈል አለባቸው ማለት ነው፡፡ በዚህ ምሳሌ የ100‚000 ብር 2% 2000 ብር ይሆናል ፤ ስለዚህ ገዥወቹ ወገኖች ለሻጩ ከሚከፍሉት ክፍያ ላይ 2000 ብር በማስቀረት 2ሽውን ለመንግስት ግብር እንድሁም 100‚000 ብር -2000 ብር 98, 000 ለገዥው መክፈል አለባቸው ማለት ነው፡፡ ሻጭው የታክስ መለያ ቁጥሩን ካልሰጠ ግን የግዥውን ጠቅላላ ክፍያ 30%( 100,000*30%)30,000 ብር ለመንግስት ግብር እንድሁም 100‚000-30,000 ሰባ ሽህ ብር ለሻጭው መክፈል ይኖርበታል ማለት ነው፡፡

በተግባር ግን ታክስን ለመሰወር ሲባል በህጉ የተቀመጡት ከ10,000 ብር በላይ የሆኑ የግዥ ክፍያወች ወይም ከ3,000 ብር በላይ የሆኑ የአገልግሎት ክፍያወች የክፍያውን መጠን በህጉ ከተቀመጠው የገንዘብ መጠን በማሳነስ በተለያየ ጊዜ ይከፍላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የግዥ /አገልግሎት/ ክፍያችን ከ10,000 /3,000 / ብር በታች ስለሆነ ዊዝሆልድንግ ታክስ የመሰብሰብ ግደታ የለብንም የሚል መከራከሪያ ያነሳሉ፡፡ ህጉ ለእንደዚህ አይነት እኩይ ተግባርየሚያስቀምጠው መልስ አለወይ የሚለውን እናያለን፡፡

በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 አንቀፅ 92(2) መሰረትእቃወች ወይም አገልግሎቶች ከ10,000/3,000/ ብር በሚያንስ መልኩ ተነጣጠለው ቢቀርቡና በመደበኛው አሰራር በአንድ አቅርቦት እንደሚቀርቡ እንድሁም የተከፈለው ገንዘብ ጠቅላላ ድምር ከ10,000/3,000/ ብር እንደሚበልጥ የሚገመት ከሆነገዥው ወገን አሁንም የዊዝሆልድንግ ታክስ የመሰብሰብና የመክፈል ግደታ ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የክፍያ መጠንን አሳንሶ በተለያየ  ጊዜ በመክፈል የግዥ /አገልግሎት ክፍያየ በህጉ ከተመለከተው የገንዘብ መጠን ስለሚያንስ የዊዝሆልድንግ ታክስ አልከፍልም የሚለው መከራከሪያ የሕግ መሰረት ስለሌለውና ህጉ ይህንን ተግባር ለመዳኘት ግልፅ ድንጋጌ ስላስቀመጠ በሕግ የተቀመጠውን አሰራር ብትከተሉና የሚተበቅባችሁን ታክስ በወቅቱ ብታሳውቁ የተሻለ ነው የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

መ. በአዋጁ አንቀፅ 92(1) እና 92(4) ላይ ያለው የግብር ምጣኔ ለምን ተለያየ ?what is the rational behind it ?

በአዋጁ አንቀፅ 92(1) ላይ ገዥው ወገን ከሚፈፅመው ክፍያ ላይ 2% ቀንሶ የሚይዘው ሻጩ/አቅራቢው የታክስ መለያ ቁጥር ካለው እና ከሰጠው ነው፡፡ ምክንያቱም ሻጩ/አቅራቢው የታክስ መለያ ቁጥር ካለው እና ከሰጠ በዚህ ቁጥር አማካኝነት ባለስልጣኑ ተከታትሎ ሻጩ/አቅራቢውን የቀረውን 28% ማስከፈል ስለሚችል ሻጩ/አቅራቢው ከታክስ ሊሰወርበት የሚችልበት ምክንያት ስለሌለ ነው፡፡ ሻጩ/አቅራቢው የታክስ መለያ ቁጥር ከሌለው እና ካልሰጠ ግን በገዥ ክፍያ ምክንያት ገቢ ያገኘውን ሻጭ ማግኘት ስለማይቻል ከታክስ ሊሰወር የሚችልበት ሁኔታ ስላለ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን የታክስ ስወራ ተግባር ለመከላከል ሲባል ገዥው ወገን ከሚፈፀመው ክፍያ ላይ ሻጩ/አቅራቢው ካገኘው ገቢ ሊከፍል የሚገባውን ግብር 30% ዊዝሆልድ አድርጎ በማስቀረት መንግስት ማግኘት ያለበትን ግብር እንድከፍል ህጉ ግደታ ይጥላል ማለት ነው፡፡

ሠ. ተቀንሶ በሚያዘው የግብር ምጣኔ ላይ በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 አንቀፅ 92(4) እና በሚኒስተሮች ምክር ቤት የፌደራል ገቢ ደንብ ቁጥር 410/09 አንቀፅ 63 መሰረት የተቀመጠው መስፈርት እና በተግባር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያየዘ የሚነሳው ጥያቄ  የገቢ ግብር ኣዋጁና ደንቡ ይቃረናል? ደንብ አዋጅን መሻር ይችላል ወይ? በአዋጁ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት የተወሰኑ ውሳኔወች እጣፋንታቸው ምንድነው? የባለስልጣኑ እና የግብር ከፋዩ እጣ ፋንታ ምንድነው?በተግባርስ እየተከናወነ ያለው ምንድነው?  የሚል ነው፡፡

በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 አንቀፅ 92(1) እና (4) ላይ በግልፅ እንደተደነገገው አቅራቢው ለገዥው የታክስ መለያ ቁጥሩን ከሰጠው ገዥው ከሚከፍለው ጠቅላላ ክፍያ ላይ 2% ቀንሶ ማስቀረት አለበት፡፡ የታክስ መለያ ቁጥሩን ካልሰጠው ደግሞ 30% ቀንሶ ማስቀረት አለበት፡፡  በአዋጁ መሰረት ከሚከፈለው ክፍያ ላይ ተቀንሶ የሚያዘውን የግብር ምጣኔ ለመወሰን እንደመስፈርት የተቀመጠው የታክስ መለያ ቁጥር ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በደንብ ቁጥር 410/09 አንቀፅ 63 መሰረት ሻጩ/አቅራቢው ከታክስ መለያ ቁጥር በተጨማሪ የንግድ ፍቃድ የማቅረብ ግደታ አለበት ይላል፡፡ ይህንን በተመለከተ ባለሙያወች ሁለት አይነት ክርክር ያነሳሉ፡፡

Argument- 1 ደንቡ እና አዋጁ ይቃረናሉ፤ደንብ አዋጅን መሻር አይችልም ፡፡ በመሆኑም በሕግ አተረጓጎም መርህ ተፈፃሚነት ያለው በአዋጁ ላይ የተቀመጠው መስፈርት ብቻ ነው፡፡ ይህም ማለት ሻጩ ማቅረብ ያለበት የታክስ መለያ ቁጥር ብቻ ነው የሚል ክርክር ያነሳሉ፡፡

Argument- 2 ደንቡ እና አዋጁ አይቃረኑም፤ ደንቡ አዋጁን አይሽርም የሚሉ አሉ፡፡ የክርክራቸውም መነሻ የአዋጁ አንቀፅ 92(1) እና (4) አሳሪ የሆነ መስፈርት (Exhaustive criteria)አላስቀመጠም፡፡ አዋጁ መስፈርቱን ያስቀመጠው ፈቃጅ በሆነ መልኩ /illustrative & permissive way/ነው፡፡ ንዑስ አንቀፅ አራት ላይ ሻጭው የታክስ መለያ ቁጥር መስጠት አለበት ይላል እንጅ የታክስ መለያ ቁጥር ብቻ መስጠት አለበት አይልም፡፡ የደንብ ዓላማ ደግሞ በአዋጅ ላይ የተደነገገን ነገር ማብራራት እና አዋጁን ለማስፈፀም የሚረዱ ዝርዝር ነገሮችን መደንገግ ነው፡፡ በመሆኑም ደንቡ በአንቀፅ 63 ላይ የንግድ ፍቃድን እንደ መስፈርት ማስቀመጡ አዋጁን የሚጥስ/የሚሽር/ ሳይሆን በአዋጁ የተቀመጠውን ፈቃጅ መስፈርት በመከተል አዋጁን ለማስፈፀም ሲባል የተቀመጠ ተጨማሪ መስፈርት ነው፡፡ ስለሆነም አዋጁ መጀመሪያውንም ሌላ መስፈርት በደንብ እንዳይጨመር በማሰብ አሳሪ በሆነ መልኩ ያላስቀመጠው በመሆኑ እና ደንብ ደግሞ አዋጅን ማስፈፀምና በአዋጁ ላይ ግልፅ ያልሆኑ ነገሮችን በማብራራት የሕግ አውጭውን ዓላማ ማሳለጥ በመሆኑ ደንቡ አዋጁን አብራራው እንጅ አልሻረውም በሚል ይደመድማሉ፡፡ እኔ በበኩሌ ሁለተኛውን ክርክር እጋራለሁ ምክንያቱም አዋጁ የታክስ መለያ ቁጥር መስጠት ብቻ በሚል አላስቀመጠም፡፡ አዋጁ “ብቻ” በማለት አሳሪ መስፈርት አለማስቀመጡ በራሱ ሕግ አውጭው ሌላ ተጨማሪ መስፈርት ሚኒስተሮች ምክር ቤት ማውጣት እንደሚችል የሚጠቁምና መብት የሚሰጥ በመሆኑ እንድሁም የደንብ ዓላማ አዋጁን በመከተል ዝርዝር ነገር ማውጣት ስለሆነ ደንቡ ዝርዝር ነገር አወጣ እንጅ በመሰረታዊ ደረጃ አልሻረውም የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

ይህ ክርክር በእንድህ እንዳለ አዋጁ እና ደንቡ በተግባር በግብር ከፋዮች እንድሁም በባለስልጣኑ ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛል፡፡ የገቢ ግብር አዋጁ የወጣው ነሀሴ 12 ቀን 2008 ዓ.ም ሲሆን ከሀምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በተገኘ ገቢ ላይ ተፈፃሚነት አለው፡፡ ደንብ ቁጥር 410/09 ደግሞ ነሀሴ 19 ቀን 2009 ዓ.ም የወጣ ሲሆን ልክ እንደ አዋጁ ወደኋላ ተመልሶ ከሀምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በተገኘ ገቢ ላይ ተፈፃሚነት እንዳለው የደንቡ አንቀፅ 71 ይደነግጋል፡፡ በተግባር እየተፈጠረ ያለው ችግር ደንቡ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ (እስከ ነሀሴ 19/2009 ዓ.ም) ባለስልጣኑም ሆነ ግብር ከፋዩ ግብሩን እያሰሉ የነበረው በአዋጁ መሰረት በተቀመጠው መስፈርት ነበር፡፡ ይህም ማለት ሻጭው/አቅራቢው የታክስ መለያ ቁጥር ከሰጠ ገዥው ከክፍያውላይ 2% ያስቀራል፤ካልሰጠ ደግሞ 30% ያስቀራል ማለት ነው፡፡ ባለስልጣኑም በዚህ መስፈርት ነበር በኦድት ወቅት ሲያሰላ የነበረው፡፡ ይሁን እንጅ ደንቡ ከወጣ በኋላ (ከነሀሴ 19/2009 ዓ.ም በኋላ) ደንቡ ወደላኋ ሄዶ ከሀምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በተገኘ ገቢ ላይ ተፈፃሚ ይሆናል ስለሚል እና የደንቡ አንቀፅ 63 ሻጩ/አቅራቢው ከታክስ መለያ ቁጥር በተጨማሪ የንግድ ፍቃድም ማቅረብ አለበት ስለሚል ከሀምሌ 1 /2008 ዓ.ም እስከ ነሀሴ 19 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ግብይት የፈፀሙ ድርጅቶች ሻጩ የታክስ መለያ ቁጥር ሲሰጣቸው 2% አስቀርተው ነበር፤ሳይሰጣቸው ሲቀር ደግሞ 30% ቀንሰው አስቀርተው ነበር፡፡ ነገር ግን ባለስልጣኑ የደንቡን ወደኋላ በመሄድ ያለውን ተፈፃሚነት በመከተል ሻጩ የታክስ መለያ ቁጥር ሲሰጣችሁ ያስቀራችሁት 2% ስህተት ነው ፡፡ ምክንያቱም ሻጩ የንግድ ፈቃድ አልሰጣችሁም፡፡ ከምትከፍሉት ክፍያ ላይ 2% ማስቀረት የነበረባችሁ ሻጩ የታክስ መለያ ቁጥር እና የንግድ ፍቃድ ሲሰጣችሁ ነበር፡፡ ሁለቱ ነገሮች ባልቀረቡበት ሁኔታ ከምትከፍሉት ክፍያ ላይ 30% ማስቀረት ነበረባችሁ በማለት ባለስልጣኑ በድርጅቱ ላይ ፍሬ ግብር ፣ ወለድና ቅጣት እየጣለ ይገኛል፡፡

ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ደግሞ ደንቡ ባልወጣበት ጊዜ የምንመራው በአዋጁ ነው፡፡ ስለዚህ በአዋጁ መሰረት ቀንሰን ያስቀረነው ግብር ትክክል ነው የሚል ቅሬታ ያነሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ባለስልጣኑ እንደሚለው በደንቡ መሰረት ቀንሰን እንያዝ ብንል እንኳን ግብይቱ ተፈፅሞ አልቋል፡፡ ገዥም ክፍያውን ከፍሎ ሻጭም እቃውን አስረክቦ እና ክፍያውን ተቀብሎ ሄዷል፡፡ አሁን ተነስተን የሸጠልንን/አገልግሎት የሰጠንን ሰው የንግድ ፍቃድክን አምጣ ካላመጣክ ከምከፍልህ ክፍያ ላይ 30% ታክስ አስቀራለሁ ማለት አንችልም፡፡ የሀገሪቱ የንግድ ሕግና የገበያ ሥርዓት ይህንን ለማድረግ አይፈቅድልንም የሚል መከራከሪያ ያነሳሉ፡፡ ሁለቱን ወገኖች ( ባለስልጣኑን እና ድርጅቶችን) ለማስታረቅ /to make strike abalance beteween them/የሚከተለውን ሀሳብ አቀርባለሁ፡፡

  • ደንቡ እስከሚወጣ ጊዜ ድረስ ተፈፃሚነት ያለው አዋጁ ነው፡፡ ስለዚህ ድርጅቱ በአዋጁ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ግብር ቀንሰው መያዛቸው ትክክል ነው፡፡ ደንቡ ባልወጣበትና ተጨማሪ ግደታ ባልተጣለባቸው ሁኔታ ባለስልጣኑ የሰራችሁት ስራ ህገ ወጥ ነው በማለት ተጨማሪ ፍሬ ግብር፣ ወለድና ቅጣት ክፈሉ ሊል አይገባም፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ አይነት አሰራር የህጋዊነትን መርህ/principle of legality/ የሚጥስ ስለሆነ ነው፡፡ በመሆኑም ምንም እንኳን ደንቡ ከሀምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በተገኘ ገቢ ላይ ወደኋላ ተፈፃሚ ይሆናል ቢልም ከሀምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም እስከ ደንቡ የወጣበት ነሀሴ 19/2009 ዓ.ም ድረስ በተግባር ሲሰራበት የነበረው እና በሕግ ደረጃም ያለው አዋጁ ብቻ በመሆኑ ሕግና አሰራር በሌለበት ሁኔታ እንድሁም ባለስልጣኑም በዚሁ አሰራር ሲሰራ በቆየበት ሁኔታ ድርጅቶች የሰራችሁት የግብር ሰሌት ትክክል አይደለም ሊባሉ አይቻልም፡፡ ከርትዕ/equity/፣ ከፍትህ/fairness/እና ከአመክንዮ/logic/አንፃርም ተገቢነት ያለው አሰራር አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በድርጅቶቹ ላይ ግደታ ለመጣልም ግብይቱ ተፈፅሞ ያለቀ በመሆኑ የሀገሪቱ የገበያ ሁኔታ እንደገና ሻጭውን የንግድ ፍቃድ ያላቀረብክ በመሆኑ ከምከፍልህ ክፍያ ላይ 30% አስቀራለሁ ብለህ እንድትነሳና እንድትሰራ የሚፈቅድ አይደለም፡፡ ስለዚህ ባለስልጣኑ ደንቡ ምንም እንኳን ግደታ ቢጥልበትም ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በመነሳት ከሀምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም እስከ ደንቡ የወጣበት ነሀሴ 19/2009 ዓ.ም ድረስ በአዋጁ መሰረት የግብር ስሌታቸውን ያከናወኑ ድርጅቶችን በተመለከተ በአዋጁ መሰረት እንድዳኙ/መፍትሄ እንድያገኙ/ሰርኩላር ደብዳቤ መፃፍ አለበት፡፡ ደንቡ ከወጣ ከነሀሴ 19/2009 ዓ.ም በኋላ ግብይት የፈፀሙ ድርጅቶች ግን በአዋጁና በደንቡ መሰረት መዳኘት ስላለባቸው ሻጩ/አቅራቢው/የታክስ መለያ ቁጥር እና የንግድ ፍቃድ ማቅረቡን በማረጋገጥ ሁለቱንም ካቀረበ ከሚከፍሉት ክፍያ ላይ 2% ፤ሁለቱንም ካላቀረበ ወይም ከሁለት አንዱን ካላቀረበ ደግሞ 30% ቀንስው መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን ባላደረጉ ድርጅቶች ላይ ሕግ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ተፈፃሚና አስገዳጅ ስለሆነ እንድሁም ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት ስለማያድን ባለስልጣኑ ተጨማሪ ፍሬ ግብር ፣ ወለድና ቅጣት መጣሉ ትክክል ነው ብየ አስባለሁ፡፡ በአጠቃላይ ባለስልጣኑ የራሱንና የድርጅቶችን ጥቅም ለማጣጣም ከላይ ባስቀመጥኩት መሰረት ለሁለት ከፍሎ በማየት ሁለት አይነት አሰራር መከተል አለበት እንጅ በጭፍኑ በሁሉም ድርጅቶች ላይ ደንቡን አልተከተላችሁም በማለት ተጨማሪ ፍሬ ግብር ፣ ወለድና ቅጣት መጣል የለበትም የሚል አቋም አለኝ፡፡

 

ረ. የዊዝሆልድንግ ታክስ ከፋይ ማነው? ሰብሳቢ ማነው?

በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 አንቀፅ 2(26) እና በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/08 አንቀፅ 2(43) መሰረት በመርህ ደረጃ ታክስ ቀንሶ ገቢ ማድረግ ሃላፊነት ያለበት በሚደረገው ግብይት ላይ ከፋይ/ገዥ/ የሆነው ወገን ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ በአዋጁ አንቀፅ 92(1) ላይ የተጠቀሱት ሰወች ናቸው፡፡

ይህ ሰው የዊዝሆልድንግ ታክስ የመክፈል ግደታ አለበት ስንል ታክሱን የሚከፍለው ከራሱ ኪስ አውጥቶ አይደለም፡፡ ከዋናው ግብር ከፋይ ከሻጩ/አቅራቢው/ የሰበሰበውን ገንዘብ ቀንሶ በመያዝ ሻጩ የሚከፍለውን ግብርገዥው ከሚከፍለው ክፍያ ላይ ቀንሶ በማስቀረት ይከፍላል ማለት ነው፡፡ በዚህ ታክስ ላይ ሰብሳቢው አካል ከኪሱ አውጥቶ የሚከፍለው ታክስ ባለመሆኑ የሚሰበሰበው ታክስ ከመጀመሪያው የመንግስት ንብረት ነው፡፡ የመንግስት ንብረት በሆነ ነገር ላይ ደግሞ የቀዳሚነት መብት የሚኖረው መንግስት ብቻ ነው፡፡ በዊዝሆልድንግ ታክስ ላይ ባለስልጣኑ ለተበዳሪው ግብር ከፋይ ክሊራንስ ቢሰጥም ባይሰጥም ባለስልጣኑ ቀዳሚነት መብት አለው፡፡ (አዋጅ ቁጥር 983/08 አንቀፅ 33(1)(ሀ)፣ 34(1)(2) እና (7) መመልከት ይቻላል፡፡)

ምክንያቱም ዊዝሆልድንግ ታክስ ከመጀመሪያው የሰብሳቢው (የግለሰብ) ንብረት ሳይሆንየመንግስት ንብረት ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ታክስ ላይ ቴክኒካሊ /technicaly/ ወይም በአሰራር ደረጃ ሰብሳቢውም ሆነ ከፋዩ ገዥው ወገን ነው፡፡ ነገር ግን በእውነታውከኪሱ አውጥቶ ታክሱን የሚከፍለው ዋና ግብር ከፋይ የሆነው ሻጩ/አቅራቢው/ ወገን ነው፡፡

ሰ. ግብር ቀንሶ ገቢ የማድረግ ሃላፊነት የተጣለበት ሰው ያሉበት ግደታወች ምንድናቸው?

በተግባር ብዙ ድርጅቶች የሌላ ሰው ግብር የመሰብሰብ እና የመክፈል ግደታ የለብኝም?ግብሩን መክፈል ያለበት ገቢውን ያገኘው ሰው ነው?ባልስበስብና ባልከፍል እንኳን ልከፍል የሚገባኝ ወለድና ቅጣት እንጅ ፍሬ ግብሩን ልከፍል አይገባም?ፍሬ ግብሩን ዋናው ግብር ከፋይ የከፈለልኝ በመሆኑ ወለድና ቅጣት ሊጣልብኝ አይገባም?እና የመሳሰሉት ጥያቄወች ሲነሱ ይስተዋላል፡፡

በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 አንቀፅ 96፣ 97እና ደንብ ቁጥር 410/09 አንቀፅ 62 መሰረት ግብር ቀንሶ ገቢ ማድረግ ሃላፊነት የተጣለበት ሰው የሚከተሉት ግደታወች አሉበት፡

  • ከሚከፍለው ክፍያ ላይ ግብር ቀንሶ የመያዝ
  • ተቀንሶ የተያዘውን ግብር ለባለስልጣኑ የማሳወቅ
  • ክፍያ ከፈፀመበት ወር በኋላ ባሉት ሰላሳ (30) ቀናት ውስጥ ለባለስልጣኑ የመክፈል
  • ግብር ተቀንሶ ክፍያ ለሚፈፀምለት ሰው ተከታታይ ቁጥር ያለው ህጋዊ ደረሰኝ መስጠት አለበት፡፡

የዊዝሆልድንግ ታክስ ግብር ከፋይ እነዚህ ግደታወች ካሉበት እነዚህን ግደታወች ባይወጣ የሚመጣው ህጋዊ ውጤት/legal consequence/ ምንድነው የሚለውን ደግሞ ቀጥሎ እናያለን፡፡

ሸ. ዊዝሆልድንግ ታክሱን ቀንሶ አለመያዙ፣ አለማሳወቁ ወይም አለመክፈሉ ያለው ህጋዊ ውጤት

በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር979/08 አንቀፅ 97(3) እንድሁም በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/08 አንቀፅ 37(9) እና አንቀፅ 106(1) ላይ በግልፅ እንደተደነገገው ግብር ቀንሶ የመያዝ ግደታ ያለበት ሰው ግደታውን ካልተወጣ ሰብስቦ መክፈል የነበረበትን ፍሬ ግብር፣ ወለድና መቀጫ የመክፈል ግደታ አለበት፡፡ ስለዚህ የሌላን ሰው ግብር የመክፈል ግደታ የለብኝም በማለት እነዚህን ግደታወች ለማስቀረት የሚቀርበው መከራከሪያ የሕግ መሰረት የለውም፡፡ ህጉ ፍሬ ግብር ፣ ወለድና ቅጣት እንድከፍል ግደታ የጣለበት ዋነኛ ምክንያት ከላይ በመግቢያችን የጠቀስነውን የታክሱን ዓላማ ለማሳካት ነው፡፡

ነገር ግን ይህ የሌላን ሰው ግብር የመክፈል በሕግ ግደታ የተጣለበት ሰው መብቱን የሚያስከብርበት ሥርዓት አለ፡፡ በገቢ ግብር አዋጁ አንቀፅ 97(4) መሰረትየከፈለውን ፍሬ ግብር ክፍያ ከተፈፀመለት ሰው ላይ የማስመለስ መብት/subrogation right/ አለው፡፡ የማስመለስ መብት ያለው የከፈለውን ፍሬ ግብር ብቻ ነው፡፡ የከፈለውን ወለድና ቅጣት ማስመለስ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ህጉ ማስመለስ ይችላል ብሎ በግልፅ የደነገገው ፍሬ ግብሩን ብቻ ስለሆነና ወለድና ቅጣት በጊዜው መከፈል የነበረበት ግብር ዋጋ /value/ ስለሆነ ነው፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ሌላው የሚነሳው ጉዳይ ዋናው ግብር ከፋይ ግብሩን ከከፈለ  የዊዝሆልድንግ ታክስ ቀንሶ በመያዝ መክፈል ግደታ ያለበት ሰው እጣ ፍንታ ምን ይሆናል የሚለው ነው፡፡  

በደንብ ቁጥር 410/09 አንቀፅ 64(1) እና(2)መሰረት የዊዝሆልድንግ ታክስ ለባለስልጣኑ የመክፈል ግደታ ያለበት ሰው ታክሱን ያልከፈለ ቢሆንም ዋናው ግብር ከፋይ ግብሩን የከፈለ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ካቀረበ ግን መክፈል የነበረበትን ፍሬ ግብር ክፈል አይባልም፡፡ ምክንያቱም ከመጀመሪያው በዊዝሆልድንግ ታክስ ፅንሰ ሀሳብ ውስጥ ዋናው ግብር ከፋይ ሻጭው/አቅራቢው ወገን ስለሆነ ነው፡፡ ገዥው የሻጭውን ግብር ነው እየሰበሰበ የሚከፍለው፡፡ ስለዚህ ዋናው ግብር ከፋይ ግብሩን ከከፈለ መጀመሪያውኑም ገዥው ወገን የሚሰበስበውና የሚከፍለው የዋናውን ግብር ከፋይ ግብር በመሆኑ የተከፈለ ግብርን ክፈል የሚባልበት አመክንዮ /logic/ የለም፡፡ ገዥው ወገን ማድረግ የሚጠበቅበት ዋናው ግብር ከፋይ ግብሩን ከፈለ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ ብቻ ነው፡፡ የዚህ ድንጋጌ የተገላቢጦሽ ንባብ/ab contrario reading/የሚያሳየው ማስረጃ ካላቀረበ ፍሬ ግብር የመክፈሉ ግደታ የማይቀርለት መሆኑን ነው፡፡

ይሁን እንጅ የዊዝሆልድንግ ታክስ የመክፈል ግደታ ያለበት ሰው ዋናው ግብር ከፋይ ግብሩን የከፈለ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ቢያቀርብም ወለድና ቅጣት ከመክፈል አይድንም፡፡ ምክንቱም በደንቡ አንቀፅ 64(2) መሰረት ማስረጃ ማቅረብ የተጣለውን ቅጣት አያስቀርም ብሎ ስለደነገገ እና በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/08 አንቀፅ 37(9) መሰረት የሚጣለው ወለድ በጊዜው መከፈል የነበረበት ገንዘብ ዋጋ በመሆኑ ቀሪ የሚሆንበት የአመክንዮም ሆነ የሕግ መሰረት ስለሌለ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ በኩል ጥያቄ የምታነሱ ድርጅቶች በህጉ የተቀመጠውን መብትና ግደታችሁን አውቃችሁ ከወለድና መቀጫ ብትድኑ የተሻለ ነው የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

ቀ. ማካካሻ ወይም ተመላሽ የማግኘት መብት

በተግባር በባለሙያወች እና በባለስልጣኑ ደንበኞች ዘንድ ተመላሽ መጠየቅ የሚችለው የዊዝሆልድንግ ታክስ የመክፈል ግደታ ያለበት ነው ወይሰ ዋናው ግብር ከፋይ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ውዝግብ /confusion/ አለ፡፡

በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 አንቀፅ 98(3) መሰረት የግብር ማካካሻ የማግኘት መብት ያለው ዋናው ግብር ከፋይ ነው፡፡ ይህም መብት ተፈፃሚ የሚሆነው ዊዝሆልድ ተደርጎ የተከፈለው ግብር ግብር ከፋዩ በግብር ዓመቱ ከሚፈለግበት ግብር በልጦ የተገኘ ሲሆን ነው፡፡ በብልጫ የተከፈለው ግብር በታክስ አስተዳደር አዋጁ አንቀፅ 49 በተቀመጠው ቅደም ተከተል መሰረት ለግብር ከፋዩ ይመለስለታል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ የሞከርኩት ከዊዝሆልድንግ ታክሶች አንዱ የሆነውን በሀገር ውስጥ ከሚፈፀሙ ክፍያወች ላይ ተቀንሶ የሚያዝ ታክስን ብቻ ነው፡፡ በቀጣይ በሌሎች የታክስ አይነቶች ላይ ሌላ ጽሑፍ ይዥ እቀርባለሁ፡፡ ጽሑፉን አንብባችሁ አስተያየት ለምትስጡኝ ሁሉ ከወዲሁ ለማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

               ሰላማችሁን ያብዛላችሁ-ክቡራን አንባቢወቼ

 

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Stolen Asset Recovery in Ethiopia: Critical Legal ...
ደረሰኝ አለመቁረጥ እና የወንጀል ተጠያቂነት

Related Posts

 

Comments 1

Abebe
Guest - Gizachew Lefebo (website) on Saturday, 13 April 2024 21:29

Thank you so much

Thank you so much
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 01 November 2024