- Details
- Category: Non-Contractual Liability (Tort Law)
ጥፋት ሳይኖር አላፊነት (Strict liability)
ባለፈው ክፍል ጥፋት ምን እንደሆነ የጥፋት ዓይነቶችንና ጥፋት በምን ላይ ሊፈፀምና እንዴት አላፊነትን ሊያስከትል እንደሚችል አይተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ አንድ ሰው ጥፋት ሳይኖረው እንዴት ተጠያቂ እንደሚሆን እንመለከታለን፡፡ በእንግሊዝኛው /Strict liability/ የሚባለው ነው፡፡ ስለጥፋት ሳይኖር አላፊነትን የሚደነግጉት ቁጥሮች ከ2066 እስከ 2089 ያሉት ናቸው፡፡ እነዚህን ቁጥሮች በንዑስ ክፍሎች ስንከፍላቸው፡፡
ቁጥር 2066-2070 ድረስ ያሉት አንድ ሰው የሚሰራው ስራ ምክንያት ሆኖ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት በማድረስ ተጠያቂ የሚሆንበት ሁኔታን ሲደነግጉ
በቁጥር 2071 -2076 ድርሰ ደግሞ እንሰሳት በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት ባለእንሰሳው ተጠያቂ የሚሆንበትን ሁኔታ ይደነግጋሉ፡፡
እንዲሁም ከቁጥር 2077-2080 ድረስ ያሉት ደግሞ የህንፃ ባለቤቶች በንብረት ወይም በሰው ላይ ለሚደርሱት ጉዳት ተጠያቂ ስለመሆናቸው ይደነግጋሉ፡፡ መኪናዎች ከቁጥር 2081-2084 ስር 5 ባለሞተር ተሽከርካሪ ባለቤቶችና ሌሎች እንዴት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ሲደነግጉ ቁጥር 2085 ስለተሰሩ ዕቃዎችና የሚያስከትሉት ተጠያቂነት ይደነግጋል፡፡ ቀጥለን እነዚህን አፍታተን አንድ ባንድ እንመለከትለን፡፡
ከሥራ ጋር የተያያዘ አላፊነት
አስፈላጊ ሆኔታ /Necessity/ ቁጥር /2066/
በራስ ወይም በሌላ ሰው ላይ ወይም በራስ ንብረት ላይ ወይም በሌላ ሰው ንብረት ላይ በእርግጠኝነት ሊደርስ ከሚችል አደጋ ለመከላከል በሌለ ሰው ላይ ሆን ብሎ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ጉዳት አደራሹ ተጠያቂ ይሆናል፡፡
በአስፈላጊ ሁኔታ ስር ሆኖ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ማድረስ በኢፊዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 76 መሠረት ተጠያቂ አያደርግም፡፡ ሆኖም ግን በፍትሐብሔር ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ምክንያት ሊሆን የሚችለው በድርጊቱ ተበዳዩች /Victims/ መኖር ነው፡፡ ሕግ ይህን የሚያደርገው አስፈለጊ በሆነ ሁኔታ ስር ድርጊቱን ፈፅሞ ጉዳቱን ባደረሰ እና የተበዳዩ ጥቅም መሃል /balance/ ለመጠበቅ ነው፡፡ ሕግ አድራጊውንና ጉዳት አድራሹን ድረግትህ ጥፋት አይደለም ይበል እንጂ ካሣ አትከፍልም አላለም፡፡
ሌላው መነሳት ያለበት ጥያቄ አንድ ሰው የሌላ ሰውንና ንብረት በእርግጠኝነት ሊደርስ ከሚችል አደጋ በመከላከልና ጉዳት በማድረሱ እንዴት ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡ ምናልባትም ተበዳዩ የሚያውቀው ጉዳት ያደረሰበትን እንጂ ሰውነቱ ወይም እና ንብረቱ ከአደጋ የተጠበቀለትን ሰው ስላልሆነ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን አደጋው እንዳይደርስ የተከላከለው ሰው በቁጥር 2162 ጥቅሙ ወይም ሰውነቱ ከአደጋ የጠበቀለትን ሰው መጠየቅ ይችላሉ፡፡
በመጨረሻም ከቁጥር 2066 ጋር ቁጥር 2103ትን አብረን ማንበብ አለብን በቁጥር 2066 መሠረት ጉዳት ለደረሰበት ሰው የካሣው መጠን የሚወሰነው በ2091 መሠረት ሳይሆን በቁጥር 2103 መሠረት በርትዕ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው በንብረት ላይ ለደረሰ አደጋ ነው፡፡
በሰው አካል ላይ ጉዳት ስለማድረስ ቁጥር /2087/
ከዚህ ቀደም ቁጥር 2038ን ስንወያይ አንድን ሰው ያለፍላጉት ብንነካ ጥፋተኛ እንደሚያደርገን ተመልክተናል፡፡ በዚህ ቁጥር መሠረት ግን ጥፋተኛ ለመባል በተሰነካው ሰው ጉዳት ማድረሰ ቅደመ ሁኔታ እንዳል ሆነ ተልክተናል፡፡ በቁጥር 2067 መሠረት ተጠያቂ ለመሆን አንድ ሰው በሥራው በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ማድረስ ቅደመ ሁኔታ ነው ለዚህም ነው ቁጥር 2087 /1/ አንደ ሰው በሠራው ሥራ በሌላ ሰው አካል ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ኃላፊ ነው በማለት የደነገገው ፡፡
ሆኖም ግን ጉዳቱ የደረሰው በሚከተሉት ምክንያት ከሆነ ጉዳት አድራሹ ተጠያቂ አይሆንም፡፡
1.ሥራው በሕግ የተፈቀደ ወይም የተያዘ ከሆነ ይህን በምሳሌ እናስረዳ፡፡ ቁጥር 18 ስር የሰው አካል የማይደፈር መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ይህ ማለት ግን አንድ ሰው በሕክምና ጥበብ በኩል ጉዳት የማያደርስበት መሆኑ ከተረጋገጠ አካሉን አሳልፎ ለመስጠት ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድን ኩላሊት አሳልፎ መስጠት እንደሚቻል የሕክምና ጥበብ ይነግረናል፡፡ ይህን ለማድረግ ግን ኩላሊቱን የሚሰጠው ሰውዩ ሰውነት መቀደድ አለበት ይህም ጉዳት ያደርስበታል፡፡ ይህን ጉዳት ያደረሰው ቀዳጅ ሐኪም ግን ተጠያቂ አይሆንም፡፡
2.ጉዳቱ የደረሰው ራስን ለመከላከል ከሆነ ጉዳት አድራሹ አላፊ አይሆንም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በጩቤ ሌላውን ሰው ለመውጋት ቢንደረደርና ሊወጋ በነበረው ሰው ጥቃት ቢቆስል ተከላካዩ ለደረሰው ጉዳት አላፊ አይሆንም፡፡
3.አደጋው የደረሰው በተበዳዩ ጥፋት ምክንያት ብቻ ከሆነ አድራጊው አላፊ አይሆንም እዚህ ነጥብ ላይ ግልፅ መሆን ያለበት ለጉዳቱ ምክንያት የተጉጂው ጥፋት ብቻ መሆኑን መንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የጉዳት አድራሹ ምንም ዓይነት ሚና መኖር የለበትም፡፡
አደገኛ ሥራ ቁጥር / 2069/
እዚህ ቁጥር ስር አራት ዓይነት ሥራዎች ተዘርዝረዋል እነሱም፡፡
የሚፈነዱ ወይም መርዝ የሚሆኑ ቅመማትን በሥራ ላይ መዋል ወይም ማከማቸት፡፡
ከፍተኛ ጉልበት ያለው የኤሌክትሪክ መስመር መዘርጋት፡፡
የመሬትን የተፈጥሮ መልክ መለወጥ
በተለይ አደገኛ የሆነ የኢንዱስትሪ ሥራ ማካሄድ ናቸው፡፡
አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ የመጀመሪያው እነዚህ የተዘረዘሩት የሥራ ዓይነቶች /Enumerative / ወይስ /Exhaustive/ ናቸው፡፡ የሚለው አከራካሪ ነው፡፡
ሁለተኛው ነጥብ እነዚህ ሥራዎች ሊከለከሉ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ አስፈላጊ ናቸውና፡፡ ሶስተኛ በእነዚህ የሥራ ዓይነቶች ላይ የተሰማሩትን ወይም ባለቤቶችን ተጠያቂ ለማድረግ በመጀመሪያ ሥራው በሌላ ሰው ላይ አደጋ ያደረሰ መሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ አባባል በሥራውና በደረሰው ጉዳት መሃል የምክንያትና ውጤት ግንኙነት መኖሩን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ጥፋት መኖሩን ማሳየት አያስፈልግም፡፡ ይህም በመሆኑ ቁጠር 2086 ስር እንደተደነገገው እላይ ባስቀመጥናቸው ሥራዎች ምክንያት አደጋ በሚፈጥርበት ወይም በሚደርስበት ጊዜ የዚህ ሥራ ባለቤቶች አንዳች ጥፋት ያለደረጉ መሆናቸውን በማስረዳት ወይም የጉዳቱ ምክንያት ሳይታወቅ በመቅረት ወይም ጉዳቱን ለመከላከል አንችልም ነበር ወይም ጉዳቱ የደረሰው በሌላ ሶስተኛ ወገን ጥፋት ነው በማለት ከአላፊነት ሊያመልጡ አይችሉም፡፡
አንድ ነጥብ እንጨምርና ወደሚቀጥለው ቁጥር እንሻገር በዚህ ቁጥር መሠረት የሥራው ባለቤቶች አላፊ የሚሆኑት ጉዳቱ የደረሰው በሰው ላይ ሲሆን ነው፡፡ በእነዚህ ሥራዎች ምክንያት በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ብቻውን አላፊነትን አያስከትልም አላፊነትን ለማስከተል በቁጥር 2070 መሠረት ከሚከተሉት አንዱ መሟላት አለበት፡፡
1. በሥራው ምክንያት ጉዳት ደረሰበት የተባለው የጉረቤት ንብረት ሙሉ በሙሉ መውደም አለበት ወይም
2. በጉረቤት ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰው የሥራው ባለቤት በሰራው ጥፋት መሆን አለበት
ስለሆነም በሥራው ምክንያት የጉረቤት ንብረት ዋጋ ቢቀንስ የሥራው ባለቤት አላፊ አይሆንም፡፡
በእጅ የተያዘ ነገር ጉዳት ሲያደርስ
ባለፈው ንዑስ ክፍል ሰው በሰራው ሥራ ምክንያት ጉዳት ሲያደርስ እንዴት አላፊ እንደሚሆንና መከላከያው ምን እንደሆነ ተመልክተና፡፡ በዚህ ስር አራት ንዑስ ክፍሎችን እንመለከታለን እነሱም፣
1.እንሰሶች ከ2071-2076
2.ሕንፃ 2077-2080
3.መኪናዎችና ባለሞተር፣ ተሽከርካሪዎች 2081-2084
4.የተሰሩ ዕቃዎች ናቸው፡፡
አንድ ሁለት ነጥቦችን እናንሳና እያንዳንዱን እንመልከት በአራቱም ላይ ባለቤቶች ኃላፊ ናቸው፡፡ እንደገና በ1፣2፣እና 3 ስር ባለይዞታዎችም አላፊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በአንደኛ እና በሶስተኛ ስር ተቀጣሪዎችም አላፊ የሚሆኑበት ሆኔታ አለ፡፡ በመጨረሻም ሕንፃው በሚያደርሰው ጉዳት ሕንፃውን የሰራው ኢንጅነር አላፊ ሊሆን ይችላል፡፡
እንሰሳው ላደረሰው ጉዳት አላፊ መሆን
አንድ እንሰሳ ለሚያደርስው ጉዳት እንደሁኔታው አላፊ የሚሆኑት የሚከተሉት ናቸው፡፡
1.የእንሰሳው ባለሀብት፣
2.የእንሰሳው ጠባቂ፣
3.እንሰሳውን ለመጠበቅ የተቀጠረ ፣
የእንሰሳው ባለሀብት ቀጥር /2071/
የእንሰሳው ባለቤት በሁለት ሁኔታዎች ስር አላፊ ሊሆን ይችላል፡፡ የመጀመሪያ ቁጥር 2071 ስር እንደተደነገገው እንሰሳው በርሱ ይዞታ ስር ሆኖ ድንገት በማምለጥ ወይም ያደርጋል ተብሎ ያልተጠበቀውን ጉዳት ሲያደርስ ኃላፊ ይሆናል፡፡ እንዲሁም አንድ እንሰሳ በተያዥነት የተረከበው ሰው ዘንድ ወይም ለባለሀብቱ ወይም ለሌላ ሰው የሚሰራ ሰው ይዞታ ስር ባለበት ጊዜ ጉዳት ቢያደርስ ባለቤቱ ኃላፊ ይሆናል፡፡ ከአላፊነት የሚያድነው እንሰሳው ይዞታው ስር የነበረ ሰው ጥፋት በመስራቱ እንሰሳው ጉዳት ካደረሰ ብቻ ነው፡፡
የእንሰሳው ጠባቂ ቁጥር /2072/
የእንሰሳ ጠባቂ የተባሎትን በሶስት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው እንሰሳውን ለግል ጥቅሙ የሚያውለው ሲሆን ሁለተኛው እንሰሳውን በኪራይ የተረከበ ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ እንሰሳውን ለመጠበቅ ለመቀለብ ወይም ደግሞ በማናቸውም ሌላ ዓይነት ሁኔታ እንሰሳውን የተረከበና በራሱ ጠባቂነት ውስጥ ያለ ነው፡፡ በእንዲህ ያለ ሁኔታ እንሰሳው ጉዳት ቢያደርስ አላፊ የሚሆነው ይኸው እንሰሳ በእጅ የሚገኘው ሰው ነው፡፡
ቀጥለን አላፊነትን እነዚህ ሰዎች እንዴት እንደሚወጡ እንመለከታለን፡፡ እንሰሳው ባለሀብቱ ይዞታ ስር ባለበት ጊዜ እንሰሳው ጉዳት ሲያደርስ አላፊነቱን የሚወጣው እንደ እንሰሳው ዓይነት ይወስናል፡፡ እንሰሳው የሰው አገልጋይ ከሆነ ቁጥር 2074 /1/ መሠረት የዚህ እንሰሳ ባለቤት የሆነው ሰው እንስሳውን ጉዳት ለደረሰበት ሰው በመልቀቅ /ባለቤትነቱን በማስተላለፍ/ ከአላፊነቱ ለመዳን ይችላል፡፡
ይህ የሚሆነው እንሰሳው ጉዳት ያደረሰው በግል ባለሃብቱ ወይም በባለቤቱ ሥልጣን ስር በሚተዳደር ሰው ጥፋት ካልሆነ ነው፡፡ በአንዳቸው ጥፋት ከሆነ ግን የአላፊነቱ መጠን የእንሰሳውን ባለቤትነት በማስተላለፍ ብቻ አይወሰንም፡፡
እንዲሁም እንሰሳው የቤት እንሰሳ ሳይሆን የቤት አራዊት ከሆነ ጠባቂው /holder/ የእንሰሳውን ዋጋ በመክፈል አለፊነቱን ይወጣል /2075/ ጉዳት የደረሰው በጠባቂው ጥፋት ከሆነ የእንሰሳውን ዋጋ በመክፈል አላፊነቱን ይወጣል፡፡ ዋጋውም የሚሆነው በቁጥር 2075 /1/ መሠረት ጉዳት በደረሰበት ጊዜ የእንሰሳው ዋጋ ነው፡፡
ከዚህ የምንረዳው ቁጥር 2072/1/ እና ቁጥር 2155/1/ አብረን ስናነብ የእንሰሳው ባለቤትና የጠባቂው አላፊነት በአንድነትና በተናጥልም /several and joint/ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ቁጥር 2073 ስር እንደተደነገገው አንድ እንሰሳ በሌላ ሰው ወይም ንብርት ላይ ጉዳት ቢያደርስ የእንሰሳው ባለሃብት እንሰሳው ጉዳት ያደረሰበትን ተበዳይ ከካሣ በኃላ የእንሰሳው ጠባቂ የነበረውን ሰው ሊጠይቅ ይችላል፡፡ በመሆኑም ጉዳት የደረሰበት ሰው ባለሀብቱን እና ጠባቂውን ወይም ከሁለቱ አንዱን መርጦ መክሰስ ይችላል፡፡
በመጨረሻ እንሰሳት በአዝዕርት ላይ ወይም በሣር ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ ፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ቁጥር 2076 /1/ መሠረት ጉዳቱ የደረሰበት ሰው የእንስሳው ባለሀብት ወይም ጠባቂ እስኪክሰው ድረስ ጉዳት ያደረሱትን እንሰሳት በመያዥነት ሊይዝ ይችላል፡፡ እንዲሁም ከእንስሳው ግምት መጠን በላይ የሆነውን ጉዳት ለማስቀረት እንስሳውን መግደል አስፈላጊ ሲሆን እንስሶቹን ለመግደል መብት አለው ለምሳሊ ውሻና ድመት የመሳሰሉትን ማለት ነው፡፡ ጉዳቱ የደረሰበት ሰው ጉዳት ያደረሱትን ወይም ሊያደርሱ የነበሩትን ቢይዝም ቢገድልም ለባለቤቱ ሳይዘገይ ማሳወቅ አለበት ወይም ባለቤቱን ሳያውቅ ለማግኘት የሚችልበትን አስፈላጊውን ማድረግ አለበት፡፡
ህንፃ
ህንፃዎች ተደርምሰው ወይም ወድቀው አደጋ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ የመደርመሳቸው ወይም የመውደቃቸው ምክንያት ጥገና ያለማግኘት ሊሆን ይችላል ወይም በመሬት መንቀጥቀጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ተደርምሰው ወይም ወድቀው አደጋ ሲያደርሱ ባለቤቱ በቁጥር 2076 /1/ መሠረት አላፊ ይሆናል፡፡ የህንፃው ባለቤት አላፊ የሚሆነው ምንም ጥፋት ሳይኖርበት ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ምናልባት የህንፃው ባለቤት ከህንፃው ተጠቃሚ ነው ከሚል ግምት ሊሆን ይችላል፡፡
ህንፃው በሰው ላይ ጉዳት ያደረሰው ከመጀመሪያውኑ ህንፃውን የሰራው ሰው ሕንፃውን በትክክል ሳይሰራው ሰለቀረ ይሆናል፡፡ይህ በሚሆንበት ጊዜ የህንፃው ባለቤት ለተጉጂው ካሣ ከፍሎ ኢንጅነሩን መልሶ መጠየቅ ይችላል /2077/2//በተመሳሳይ ህንፃው ውስጥ የሚኖር ሰው ህንፃውን በፍትሐብሔር ቁጥር ከ2953-2954 መሠረት ማደስ ሲገባው ባለማደሱ ህንፃው ወድቆ ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ቢያደርስ የህንፃውን ባለቤት ተጉጂው ከሶ ህንፃው ውስጥ የሚኖርውን ሰው መጠየቅ እንደሚችል ቁጥር 2077/2/ ይደነግጋል፡፡ የጉዳቱ ምንጭ የሌላ ሰው ጥፋትም ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜም በተመሳሳይ አጥፊውን መጠየቅ ይችላል፡፡
ባለቤቱ ጉዳት ያደረሰውን እንዴት ሊክስ እንደሚችል ቁጥር 2078 ይነግረናል አንዱ መንገድ ለተጉዳው ሰው ህንፃውን በመልቀቅ ማለት የህንፃውን ባለቤትነት በማስተላለፍ ነው፡፡ አንዳንድ ጥያቄዎችን እናንሳ ህንፃው ሙሉ በሙሉ ከወደመስ ይህ ቁጥር እንዴት ይተረጉማል? ጉዳቱ የደረሰበት ሰው ቁጥር 2053ትን በመተላለፍ ወደ ህንፃው የገባ ከሆነስ?
ከላይ የህንፃው ባለቤት ጉዳት ለደረሰበት ሰው ህንፃውን በማስረከብ አላፊነቱን እንደሚወጣ ተመልክተናል፡፡ አላፊነቱ በዚህ ብቻ የሚያበቃው ለጉዳቱ ምክንያት የህንፃው ባለቤት ጥፋት ወይም በእርሱ በሥልጣኑ ስር የሚያሳድረው ሰው ጥፋት ያልሆነ እንደሆነው ነው /2078/2// በሌላ አባባል ለጉዳቱ መድረስ የህንፃው ባለቤት ጥፋት ምክንያት ከሆነ የካሣው መጠን ከህንፃው ዋጋ በላይ ሊሆን ይችላል ማለት ነው ፡፡
የባለህንፃውን ጥፋት ለማስረዳት ቁጥር 2079ኝን እንደምሳሌ ልንወስድ እንችላለን በዚህ ቁጥር መሠርት ከሌላ ሰው ቤት ምክንያት ጉዳት ይደርስብኛል ብሎ የሚሰጋ ሰው የዚሁ አስጊ የሆነው ህንፃ ባለቤት ይህ ጉዳት ከመድረሱ በፊት አስቀድሞ አስጊውን ሁኔታ ለማስወገድ የህንፃውን ባለቤት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ መጠየቅ ይችላል፡፡ ይህ ማስጠንቀቂያ ተነግሮት አስፈላጊውን እምርጃ የህንፃው ባለቤት ሳይወስድ ቢቀርና በዚህም ምክንያት ጉዳት ቢደርስ የህንፃው ባለቤት አላፊ የሚሆነው በአጥፊነት ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ የህንፃው ባለቤት ህንፃውን ወደ ተጐጂው ለማስተላለፍ ብቻ አለፊነቱን መወጣት አይችልም፡፡ አላፊነቱ ከዚህም ሊበልጥ ይችላል፡፡ ሕጉ ይህን መንገድ የመረጠው የህንፃውን ባለቤት ለመቅጣትም ጭምር ነው፡፡
በመጨረሻም ቁጥር 2080 መሠረት በአንድ ህንፃ ውስጥ የሚኖር /occupier/ ከዚህ ህንፃ እየወደቁ በሌላው ሰው ላይ ጉዳት ለማያደርሱት ተንቀሳቃሽ ነገሮች አላፊ ነው፡፡
መኪናዎችና ባለሞተር ተሽከርካሪዎች በእንግሊዝኛ /Machines and motor vehicles/ ቁጥር / 2081/
መኪናዎች ወይም /Machines/ የተባሉት ቋሚ ወይም ተንቀሳቃሽ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በኢንዱስትሪ ተተክለው ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ጫማ ለመስራት የሚያለግል ማሽን ሊሆን ይችላል፡፡ መንገድ ለመጥረግ የምንጠቀምበት ቡልዶዘርም ሊሆን ይችላል፡፡ ውሃ ከዋና ቦይ ለመሳብ የምንጥቀምበት የውሃ መሳቢያ ሞተርም ሌላ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ ለባለሞተር ተሽከርካሪዎች /Vehicles/ ምሳሌ ደግሞ የሰውና የጭነት ማመላለሻ መኪናዎችን መውሰድ እንችላለን፡፡
መኪናዎችና ባለሞተር ተሽከርካሪዎች ለሚያደርሱት ጉዳት ባለቤት አላፊ ሊሆን ይችላል፡፡ ጠባቂ ወይም ሠራተኛውም አላፊ ሊሆን ይችላል፡፡ የመኪናዎችና የባለሞተር ተሽከርካሪዎች ለሚያደርሱት ጉዳት በቁጥር 2081 /1/ መሠረት ባለቤት አላፊ የሚሆነው አደጋውን ያደረሰው ይህን መኪና ወይም ይህን ባለሞተር ተሽከርካሪ ለማንቀሳቀስ ወይም ለመንዳት ያልተፈቀደለት ሰው እንኳን ቢያሽከረክር ወይም ቢነዳም ነው፡፡ ሆኖም አደጋው በደረሰ ጊዜ መኪናው ወይም ተሽከርካሪው ተስርቆበት ከሆነና ይህንንም ማስረዳት ከቻለ ባለሀብቱ አላፊ አይሆንም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በቁጥር 2082/1/ መሠረት አንድ ሰው ባለሞተር ተሽከርካሪውን ወይም መኪናውን ለግል ጥቅሙ ሲገለገልበት ወይም ሲጠቀምበት ተሽከርካሪው ወይም መኪናው ጉዳት ካደረሰ ለደረሰው ጉዳት አላፊ ሊሆን የሚችለው ይህ ሰው ነው፡፡
አንድ የመኪና ወይም የሞተር ተሽከርካሪ ባለቤት መኪናውን ለማንቀሳቀስ ወይም ለመንዳት ሠራተኛ ሊቀጥር ይችላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ጉዳቱ የደረሰው ግን በሠራተኛው ጥፋት ምክንያት ካለሆነ በቁጥር 2082/2/ መሠረት አላፊ የሚሆነው ባለቤቱ ነው፡፡
ስለሆነም በመኪና ወይም በሞተር ተሽከርካሪ ጉዳት የደረሰበት ሰው ባለሀብቱን ተጠቃሚውን ወይም ሠራተኛውን በአንድነት ወይም በተናጥል በቁጥር 2155/1/ መሠረት ሊከስ ይችላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ በቁጥር 2083 /1/ መሠረት የመኪናው ወይም የባለሞተር ተሽከርካሪው ባለቤት ለተጐጂው ካሣ ከከፈለ በኃላ የከፈለውን ከጠባቂው መቀበል ይችላል፡፡ ከጠባቂው የሚቀበለው የካሣ መጠን በቁጥር 2083/2/ ስር ተደንግጓል፡፡ ባለቤቱ ጥፋት ካልሰራ ለምሳሌ በ4ኛ መንጃ ፍቃድ የሚሽከረከረውን ባለሞተር ተሽከርካሪን 3ተኛ መንጃ ፍታድ ያለው ሰው እንዲያሽከረክር ባለቤቱ ቢያዝ ወይም ባለቤቱ ስልጣን ስር ያለ ሰው ጥፋት ካልሰራ ለምሳሌ ልጁ ባለቤቱ ከጠባቂው የሚቀበለው መጠን የከፈለውን ሙሉ ካሣ ነው፡፡
የተሽከርካሪዎች ግጭት ቁጥር /2084/
ሁለት ተሽከርካሪዎች ሊጋጡ ይችላሉ፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ አንዳቸው ጥፋት መስራታቸው ካልተረጋገጠ በቀር ሁለቱም አሽከርካሪዎች ለጉዳቱ አኩል አስተዋፅዎ እንዳደረጉ የቆጠራል፡፡ይህ በሚሆንበት ጊዜ ቁጥር 2084/2/ እንደደነገገው የእያንዳንዱ ተሽከርካሪ ባለሀብት ወይም ለአደጋው አላፊ የሆነው ሰው በአደጋው ምክንያት ከደረሰው ጉዳት ገሚሱን ይከፍላል፡፡ የጉዳቱ መጠን ብር 1000 ከሆነ አያንዳንዳቸው ብር 500 ይከፍላሉ ማለት ነው፡፡
ነገር ግን አደጋው የደረሰው በአንደኛው መኪና ነጂ ስህተት መሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠ እንደሆነ /የትራፊክ ፖሊስ ኘላን/ ስህተቱን የሰራው አሽከርካሪ ለአደጋው ሙሉ በሙሉ አላፊ ይሆናል ወይም ለአደጋው ከግማሽ በላይ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል፡፡
የተሰሩ ዕቃዎች ቁጥር /2085/
በእንግሊዝኛው /Manufactured goods / የተባሉ ናቸው ሌላ አገር / Product liability/ የሚባለው ነው፡፡ ተጉጂው ዕቃዎቹን በመግዛት ባለቤት የሆነ ሰው ነው፡፡ /የፍትሐብሔር ቁጥር 1143 እና 1186 በአንድ ላይ ተመለከቱ/ አላፊነቱ ደግሞ የሚያርፈው ዕቃዎቹን በሰራው ሰው ላይ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያት ሊሆን የሚችለው የተሰሩ ዕቃዎች ጉደሎዎች / Defective / መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ታዲያ ተጉጂው ዕቃውን ከሰሪው እስካልገዛ ድረስ ነው ይህ ከሆነ ጉዳያቸው የሚፈታው በውል ሕግ መሠረት ነው፡፡
ሌላው መሟላት ያለበት ሰሪው ዕቃውን የሰራው ለትርፍ መሆን አለበት እንዲሁም ተጉጂው አስፈላጊውን መደበኛ ፍተሻ /Necessary customary examination/ ማድረግ አለበት፡፡ የተሰሩ ዕቃዎች ምን እንደሆኑም መለየት አለብን፡፡ ለምሳሌ እንጀራ የተሰራ ዕቃ ነው፣ ጤፍ ግን አለደለም ስለሆነም እንጀራን ለመሰራት የተወሰነ ሂደት / process / እንደሚያስፈልግ ሌላም ውጤት የተሰራ ዕቃ ነው ለማለት በተወሰነ ሂደት ውስጥ ማለፍ አለበት፡፡
አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳና ወደ ሚቀጥለው ቁጥር እንለፍ፡፡ አንድ ዕቃ ሰሪ የተመረዘ ወይም የተበከለ ዕቃ ሽጦ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ቢደርስ ዕቃ ሰሪው ተጠያቂ የሚሆነው በጥፋተኝነት / Fault/ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዕቃው ላይ ያለው ጉድለት በተራ ፍተሻ / Customary Examination / ሊገኝ የሚችል ሆኖ ሳለና ተጉጂው ይህን ሳያደርግ ቀርቶ ጉዳት ቢደርስበት ዕቃ ሰሪው ተጠያቂ አይሆንም፡፡ እንደሁም ተጉጂው ዕቃው የተሰራለትን ዓላማ በመለወጥ / Change the purpose/ ተጠቅሞ ጉዳት ቢደርስበት ዕቃ አምራቹ ተጠያቂ አይሆንም ለምሳሌ ለፊት ቅባትነት የተሰራውን በምግብነት ብጠቀም እንደማለት ነው፡፡
መከላከያ እና ሌሎች ነገሮች ቁጥር 2086 እና 2087
እስካሁን ድረስ የእንስሳ፣ የህንፃ፣ የባለ ተሽከርካሪ እና ባለመኪና ባለቤቶች እንዲሁም ዕቃ አምራቶች እንዴት አላፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመልክተናል፡፡ እነዚህ ሰዎች ከአላፊነት ሊድኑ የሚችሉት ጉዳቱ የደረሰው በቁጥር 2086/2/ መሠረት በከፊልም ሆነ በሙሉ ከተበደዩ ጥፋት መሆኑን ሲረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ቁጥር 2086/1/ ስረ እንደተደነገገው አንደኛ ጥፋት አልሰራንም ፣ ወይም የጉዳቱ ምክንያት አይታወቅም ወይም ጉዳቱን ለመከላከል አይቻልም ነበር ወይም ጉዳቱ የደረሰው በሌላ ሶስተኛ ወገን ጥፋት ነው በማለት ከአላፊነት ሊያመልጡ አይችሉም፡፡
ሆኖም ቁጥር 2087 ስር እንደተደነገገው ከእንስሳት፣ከህንፃ ፣ ከሞተር እና ዕቃዎች አምራቶች ባለቤቶች ሳይሆን የሌሎች ዕቃዎች ባለቤት የሆኑ ሰዎችን አላፊ ለማድረግ ባለቤቶቹ ወይም በእነሱ ሥልጣን ስር ያሉ ሰዎች ጥፋት መስራታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ዛፍ ተቆርጦም ይሆን በሌላ ምክንያት ወድቆ በአንዲት መኪና ላይ ጉዳት ቢያደርስ የዛፍን ባለቤት ወይም ዛፍ ቆራጩን አላፊ ለማድረግ ባለቤቱ ወይም ዛፍ ቆራጩ ጥፋት የሰራ መሆኑን ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም ከእንሰሳ ከህንፃ ፣ ከሞተር እና ከአደገኛ ኢንዱስትሪ ባለቤቶች እንዲሁም ከዕቃ አምራቶች ዘንድ ተቀጥሮ የሚሰራ ሰው በእነዚህ ውስጥ ሲሰራ ጉዳት ቢደርስበት ከውል ውጪ ያሉ ደንቦችን ጠቅሶ መከራከር አይችልም 2088/1/ እንዲህ በሆነ ጊዜ ጉዳቱ የሚያደርስው ነገር የሚመራው በተደረገው የውል ደንብ መሠረት መሆኑን ቁጥር /2088/2// ይደነግጋል፡፡
በመጨረሻምአንድ ሰው በህንፃው፣ በእንስሳው፣ ወይም በሌላ ነገር ሲጠቀም ጉዳት ሊደርስበት ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ ተጐጂው ከውል ውጪ ሀላፊነት ደንቦችን በመጥቀስ መከራከር የሚችለው የእነዚህ ነገሮች ባለቤት በዚህ ግንኙነት አንዳች ጥቅም ካገኘም ወይም ባለሀብቱ ወይም ጠባቂው ጥፋት ከሠሩ ብቻ ነው፡፡