06 March 2018 Written by 

አዋጅ ቁጥር 1/2009 - የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

 

 

 

የሕዝብን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

 

መንግስት ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን የመጠበቅ፣ የሀገርን ሠላምና ህልውና፣ የሕዝብንና የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ እና ኢንቨስትመንትና መሠረተ ልማቶችን ከጥቃት የመጠበቅ ሕገመንግስታዊ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ፤

ሕገ መንግስታዊ ሥርአቱን፣ የሕዝብን ሠላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥሉ በተለይም የኢንቨስትመንትና የልማት እንቅስቃሴን በማዳከም ላይ ያነጣጠሩ በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች በውጭ ሀይሎች ድጋፍ ጭምር የተፈፀሙ ሕገወጥ ተግባራት ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋት፣ ለተቋማት እና መሠረተ ልማቶች መውደም እንዲሁም ለብጥብጥና ሥርዓት አልበኝነት ምክንያት መሆናቸውን እና ይህን ሁኔታ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን በመረዳት፤

እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ለመቆጣጠር እና ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ልዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት እንደሚያስፈልግ በሕገ መንግስቱ የተደነገገ በመሆኑ፤

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግስት አንቀፅ 93(1)(ሀ) መሠረት የሚከተለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡

 

ክፍል አንድ

ጠቅላላ

1. አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅ ‘‘የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር  1/2ሺ’’ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

 

2. ትርጓሜ

ለዚህ አዋጅ አፈፃፀም ሲባል:-

1/  ‘‘የሕግ አስከባሪ አካል’’ ማለት የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የክልል ፖሊስ እና ሌሎች የፀጥታ አካላት ነው፤

2/  ‘‘የመርማሪ ቦርድ’’ ማለት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 93 (5) የተመለከተው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ ነው፤

3/  ‘‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት’’ ማለት ይህን አዋጅ ለማስፈፅም በዚህ አዋጅ አንቀጽ 6 መሠረት የተቋቋመ የአስቸኳይ ጊዜ አስፈፃሚ ኮማንድ ፖስት ነው፤

4/  ‘‘ሕግ’’ ማለት የፌደራል ሕገ መንግስት፣ እንደአግባብነቱ በፌደራል ወይም በክልል መንግስታት ሕግ አውጪ ወይም ሥልጣን ባለው ሕግ አስፈፃሚ አካል የወጣ የክልል ሕገመንግስት፣ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ነው፤

5/  ‘‘ሰው’’ ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፤

6/  በዚህ አዋጅ በወንድ ጾታ የተገለፀው ድንጋጌ የሴትንም ፆታ ይጨምራል፡፡

 

3. የተፈፃሚነት ወሰን

1/ ይህ አዋጅ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

2/ በአዋጁ መሠረት የሚወሰድ እርምጃ ተግባራዊ ወይም ቀሪ የሚሆንበትን አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ ይወስናል፣ ይህንኑ ለሕዝብ ያሳውቃል፡፡

 

ፍል ሁለት

በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎችና የማይፈቀዱ ተግባራት

 

4 በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎች

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ ሕገ መንግስታዊ ሥርአቱን ለማስከበርና የሕዝብና የዜጎች ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን:-

1/   ማንኛውም ሁከት፣ ብጥብጥና በሕዝቦች መካከል መጠራጠርና መቃቃር የሚፈጥር ይፋዊ ሆነ የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ፅሁፍ ማዘጋጀት፣ ማተምና ማሰራጨት፣ ትእይንት ማሳየት፣ በምልክት መግለፅ ወይም መልዕክትን በማናቸውም ሌላ መንገድ ለህዝብ ይፋ ማድረግ ሊከለክል ይችላል፣

2/   ማናቸውም የመገናኛ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም እንዲቋረጥ ሊያደርግ ይችላል፣

3/   የሕዝብና የዜጎች ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል ስብሰባና ሰልፍ ማድረግ፣ መደራጀት፣ በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስ ሊከለክል ይችላል፣

4/   የሕዝብን ሠላምና ፀጥታ በማደፍረስ ተግባር ላይ ተሳትፏል ብሎ የሚጠረጥረውን ማናቸውም ሰው ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ፣ እያጣራ ወይም እያስተማረ ለመልቀቅ፣ ይህ አዋጅ ተፈፃሚ ሆኖ ባለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ይችላል፣

5/   ወንጀል የተፈፀመባቸውን ወይም ሊፈፀምባቸው የሚችሉ ዕቃዎችን ለመያዝ ሲባል ማናቸውንም ቤት፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበርና እንዲሁም ማናቸውንም ሰው ለማስቆም፣ ማንነቱን ለመጠየቅ፣ ለመፈተሽ ይችላል፤ በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ ዕቃዎችን በማስረጃነት ለፍርድ ቤት መቅረባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ተጣርተው ለባለመብቱ ይመልሳል፣

6/   የሰዓት እላፊ ተፈፃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ይወስናል፤ ለተወሰነ ጊዜ አንድን መንገድ፣ አገልግሎት መስጫ ተቋም ለመዝጋት እንዲሁም ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቁ ለማዘዝ ይችላል፣

7/   የተቋማትና የመሠረተ ልማቶች ጥበቃ ሁኔታን ይወስናል፣

8/   የሕዝብና የዜጎች ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል የጦር መሣሪያ፣ ስለት ወይም እሳት የሚያስነሱ ነገሮችን ይዞ መንቀሳቀስ የማይቻልባቸውን ቦታዎች ለይቶ ሊወስን ይችላል፣

9/   በሠላም መደፍረስ ምክንያት የፈረሱ የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች ከሚመለከተው ክልል እና ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመተባበር መልሶ እንዲቋቋሙ ያደርጋል፣

10/  ሕዝብ የሚጠቀምባቸውን ወይም ፈቃድ የወጣባቸው የንግድ ሥራዎች ወይም የመንግስት ተቋማት እንዳይዘጉ፣ አገልግሎት እንዲሰጡ ወይም የሥራ ማቆም እንዳይደረግ ሊያዝ ይችላል፣

11/  በዚህ አዋጅ የተመለከቱ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን ለማስፈፀም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ተመጣጣኝ ሀይል ለመጠቀም ይችላል፣

12/  ኃላፊነቱን ለመፈፀም ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ይፈፅማል፡፡

 

5. የማይፈቀዱ ተግባራት

ማናቸውም የሕግ አስከባሪ አካል እና ባልደረባ በዚህ አዋጅ አፈፃፀም ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግስት አንቀጽ 1 የተመለከተውን የመንግስት ስያሜ መቀየር፣ በአንቀፅ 18 የተመለከተውን ኢሰብአዊ አያያዝ መፈፀም፣ በአንቀጽ 25 የተመለከተውን የሰዎችን የእኩልነት መብት የሚጥስ ተግባር መፈፀም፣ በአንቀፅ 39(1) እና (2) የተመለከተውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን መብት መጣስ የተከለከለ ነው፡፡

ፍል ሶስት

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት እና የመርማሪ ቦርድ መቋቋምና ሀላፊነት

6. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት መቋቋምና ኃላፊነት

1/   የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ አግባብነት ካላቸው አካላት የተውጣጣ አባላትን የያዘ (ከዚህ በኋላ ‘‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት’’ ተብሎ የሚጠራ) በዚህ አዋጅ ተቋቁማል፡፡

2/   ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱን አባላት ይመርጣል፡፡

3/   የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 የተመለከቱ ተግባራትን በበላይነት ይመራል፣ ያስፈፅማል፡፡

4/   የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ የሕግ አስከባሪ አካላትን በአንድ እዝ ስር አድርጎ በላይነት ይመራል፤ ያዛል፡፡

 

7. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ ግዴታ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ሥር የተደረጉ ሰዎችን ስም እና የሚቆዩበትን ቦታ ለመርማሪ ቦርዱ ያሳውቃል፡፡

 

8. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ

1/  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ በዚህ አዋጅ ተቋቁማል፡፡

2/  የመርማሪ ቦርዱ ሰባት አባላት የሚኖሩት ሲሆን፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ከሕግ ባለሙያዎች የተውጣጡ ሆነው በምክር ቤቱ ይመደባሉ፡፡

 

9. መርማሪ ቦርዱ ሥልጣንና ተግባር

መርማሪ ቦርዱ:-

1/  በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የታሰሩትን ግለሰቦች ስም  በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ያደርጋል፣ የታሰሩበትን ምክንያት ይገልፃል፣

2/  በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚወሰዱት እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢሰብአዊ እንዳይሆኑ ይቆጣጠራል፣ ይከታተላል፣

3/  ማናቸውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ ኢሰብአዊ መሆኑን ሲያምንበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት እርምጃውን እንዲያስተካክል ሀሳብ ይሰጣል፣

4/  በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃዎች ኢሰብአዊ ድርጊት የሚፈፅሙትን ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ያደርጋል፣

5/  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቀጥል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ሲቀርብ ያለውን አስተያየት ለምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡

 

ክፍል አራት

 

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

10. ተፈፃሚነታቸው የታገዱ ሕጎች

በቪዬና ኮንቬንሽን የተመለከተው የዲፕሎማቲክ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረኑ የፍሬ ነገርና የሥነ-ሥርዓት ሕጎች ለዚህ አዋጅ አፈፃፀም ይህ አዋጅ በሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜያት ተፈፃሚነታቸው ታግዶ ይቆያል፡፡

 

11.የመተባበር ግዴታ

ማንኛውም ሰው የዚህን አዋጅ አፈፃፀም እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ እና የሕግ አስከባሪ አካልና ባልደረባ የሚወስዷቸውን የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎች የማክበርና ለዚሁ የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡

 

12.የወንጀል ተጠያቂነት

1/  በዚህ አዋጅ የተመለከቱ ከአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎች ጋር የተያያዙ ግዴታዎችን ተላልፎ የተገኘ ማናቸውም ሰው እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡

2/  በዚህ አዋጅ አንቀጽ 11 የተመለከተውን የመተባበር ግዴታ የጣሰ ማንኛውም ሰው እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ይቀጣል፡፡

 

13. ደንብና መመሪያ የማውጣት ሥልጣን

1/  የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን አዋጅ ለማስፈፀም ደንብ ያወጣል፡፡

2/  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት አዋጁንና በአዋጁ መሠረት የሚወጣውን ደንብ ለማስፈፀም መመሪያ ያወጣል፡፡

 

14.አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ

1/   ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ወራት የፀና ይሆናል፡፡

2/   የስድስት ወር ጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ የአዋጁ ተፈፀሚነት ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ ሊወስን ይችላል፡፡

3/   ይህ አዋጅ በሕገመንግስቱ አንቀጽ 93(2)(ለ) መሠረት በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀባይነት እንዲያገኝ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

4/   የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወር ጊዜ ገደቡ ሲጠናቀቅ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የጊዜ ገደቡ በየአራት ወሩ እንዲታደስ ሊያደርግ ይችላል፡፡

5/   ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን በመገናኛ ብዙሀን ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል፡፡

 

አዲስ አበባ ጥቅምት 15 ቀን 2009 ዓ.ም

ይለማርያም ደሳለኝ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ

ጠቅላይ ሚኒስትር

 

Abyssinia Law | Making Law Accessible!

Abyssinia Law is  a legal resource portal providing open access to primary and secondary legal materials for Ethiopia, such as laws, court decisions, articles, contact guidance and Lawyers Directory - with texts supplemented by online videos, a discussion forum and user blog. The service gives free access to Federal and State consolidated laws of Ethiopia (with status information whether the law is amended, repealed or effective)

Website: www.facebook.com/ethiopianlaws