በተለይ ሕገ መንግሥት የመንግሥትን ሥልጣን በሕግ አውጪ፣ በሕግ አስፈፃሚ እና በሕግ ተርጓሚ በመከፋፈል የእያንዳንዱን ሥልጣንና ተግባር በጥቅሉ ዘርዝሮ ይገኛል፡፡ በሕገ መንግሥት ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ጥቅል ድንጋጌዎች በተዋረድ በሚወጡ ሕጎች የሚዘረዘሩ፣ የሚብራሩና ሥርዓት የሚበጅላቸው ናቸው፡፡ በተዋረድ የሚገኙ ሕጎች ከሚባሉት መካከል አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ይገኙበታል፡፡ በአብዛኛው ሀገር የሕገ መንግሥቱን ጥቅል ድንጋጌዎች ወደ ዝርዝር ሕጎች የመለወጥና እንዲፈጸሙ የማድረግ እንዲሁም ሌሎች ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን ዜጎች የመረጧቸው ተወካዮች በሚገኙበት ምክር ቤት ወይም ሕግ አውጪ ተብሎ በሚታወቅ አካል ሥር ያደርጉታል፡፡ ዜጎች የመረጧቸው ተወካዮች (ሕግ አውጪው አካል) በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ጥልቅ ዕውቀት ስለሌላቸው ወይም ዝርዝር ጉዳዮችን ለማየት ጊዜ ስለማይኖራቸው ዋና ዋና ድንጋጌዎችን በአዋጅ በማውጣት ዝርዝር ወይም ቴክኒካል ጉዳዮችን ለአስፈጻሚው አካል በውክልና ይሰጡታል፡፡ የመንግሥት አስፈጻሚው አካልም በአዋጁ በተሰጠው ውክል ሕጎችን በደንብ ወይም በመመሪያ በማውጣት ሕጎቹን ያስፈጽማል፡፡ በተለይ አስፈጻሚው አካል የሚያወጣቸው ደንቦችና መመሪያዎች ተፈፃሚነታቸው ለዜጎች ቅርብ የሆኑና በዕለት ተዕለት ኑሮአችን ውስጥ የሚያጋጥሙ በመሆናቸው መንግሥት ከዜጎች ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት የሚወስኑ ናቸው፡፡ ይህ አካል ባንክም ታንክም (ገንዘብም ሥልጣንም) ያለው የመንግሥት ቀኝ እጅ ስለሆነ ብዙ ጊዜ ሕጎችን በሚያስፈጽምበት ጊዜ ሊያደርስ የሚችለውን በደል ሕግ አውጪውና ሕግ ተርጓሚው (ፍርድ ቤት) በጋራ ቁጥጥር ያደርግበታል፡፡ እዚህ ጋር ማስፈጸም ሲባል ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን ብቻ ሳይሆን፣ በሕጎቹ መሠረት አስተዳደራዊ ውሳኔ የመወሰን እንዲሁም ቅሬታን መስማትና ማስፈጸምን ያጠቃልላል፡፡ ሕግ አውጪው አስፈጻሚ አካሉ ሕግ ከማውጣቱ (ደንብና መመሪያ) በፊት መከተል ስለሚገባው መሠረታዊ መርህ፣ ውሳኔ ሲወስንና ቅሬታ ሲሰማ መከተል የሚገባው ሥነ ሥርዓት በሕግ አስቀድሞ በመደንገግ አሠራሩን ይቆጣጠረዋል፡፡ ሕግ ተርጓሚው ወይም ፍርድ ቤቱ ደግሞ ሕጉ ከወጣ በኋላ ወይም አስፈጻሚ አካሉ ውሳኔ ከወሰነ በኋላ ሕጉ ወይም ውሳኔው አግባብነት ያለው ስለመሆኑ ቁጥጥር ያደርግበታል፡፡ ይህ ዓይነቱም አሠራር በአብዛኛው ሀገር ተመሳሳይነት አለው፡፡

ሕግ አውጪው አስፈጻሚ አካሉ ደንብና መመሪያ ከማውጣቱ በፊት መከተል ስለሚገባው መሠረታዊ መርህ፣ ውሳኔ ሲወስንና ቅሬታ ሲሰማ መከተል የሚገባው መርህና ሥነ ሥርዓት ከሚደነገግበት የሕግ ዓይነት አንዱ ‹‹የአስተዳደር ሕግና ሥነ-ሥርዓት›› በመባል ይታወቃል፡፡ እንግዲህ መንግሥት ከሕዝብ ያገኘውን ሥልጣን በአግባቡና በሥርዓት ሥራ ላይ እንዲያውል በማንኛውም የፖለቲካ ማኅበረሰብ ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ማረጋገጥ የመንግሥትን ሥልጣንና ተግባር ይበልጥ ለመቆጣጠር የሚረዳ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም በውስጡ መሠረታዊ ሕገ-መንግሥታዊ መርሆዎች የያዘና ከዚሁ ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተለየ እንዳልሆነ ብዙዎቻችን የምንስማማበት ጉዳይ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉት እነዚህን ጥቅል ድንጋጌዎች ሕግ አውጪው (በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) እና በሕግ አስፈጻሚው (በሚኒስትሮች ምክር ቤትና ተጠሪ ተቋሞቻቸው) በተዋረድ በሚገኙ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ማውጣት ሥራ ላይ ማዋል የተለመደ አሠራር መሆኑም ይታወቃል፡፡ የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማ በኢትዮጵያ የአስተዳደር ሕግና ሥነ-ሥርዓት አስፈላጊነትን ለማሳየት ነው፡፡ 

የአስተዳደር ሕግ ምንነትና ጠቀሜታ 

የአስተዳደር ሕግ በአንድ ሀገር ሊገኙ ከሚገባቸው ብሔራዊ የመንግሥት /የሕዝብ/ ሕጐች አንዱ ሲሆን ዋና ጠቀሜታውና ተግባሩ የመንግሥት አስተዳደር /አስፈፃሚ/ መሥሪያ ቤቶች በሕግ የሚሠጣቸውን ሥልጣን የሚጠቀሙበትን ሥነ-ሥርዓት እና መርሆዎች በማስቀመጥ በሕገ መንግሥትና በሌሎች ሕጐች የተገለፁት የግለሰቦች መብቶች እንዳይጣሱ መጠበቅ፣ እንዲሁም የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ሥልጣናቸውን ከሕግ ውጭ ሲጠቀሙ ሊደረግ የሚገባውን የቁጥጥር ዘዴ በተለይም የአስተዳደር ውሳኔዎች በፍርድ ቤት ስለሚታዩበት ሁኔታ የሚገዛ ሕግ ነው፡፡

የአስተዳደር ሕግን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ በአንድ በኩል የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶችን የሚያቋቁም እና ሥልጣን የሚሠጥ መሠረታዊ ወይም ዋና የአስተዳደር ሕግ / Substantive Administrative Law/ ሲሆን በሌላ በኩል በመሠረታዊ ወይም በዋና ሕጉ የተሰጠውን ሥልጣን የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች የሚጠቀሙበትን መርህና ሥነ-ሥርዓት የሚገዛ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ /AdministrativeProcedure Law/ ነው፡፡

የአስተዳደር ሕግ ስንል በዋናነት የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች በሕግ የተሠጣቸውን ሥልጣን በተግባር ሲያውሉ ሊከተሉ የሚገባቸውን መርሆዎች፣ ሥነ-ሥርዓት እና በአስተዳደር ውሳኔ ቅር የተሰኘ ወገን ለፍርድ ቤት ይግባኝ የሚልበትን ሁኔታ የሚገዛ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ እንደሆነ ብዙዎች የአስተዳደር ሕግ ምሁራን ይስማሙበታል፡፡ የተለያዩ የአስተዳደር ሕግ ሙሁራን የሰጡትን የአስተዳደር ሕግ ምንነት በመዳሰስ ስለአስተዳደር ሕግ የሚከተሉትን ነጥቦች በአጭሩ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

የአስተዳደር ሕግ፡-

-    የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶችን ሥልጣንና አደረጃጀት የሚገዛ መሆኑ፤

-    የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣን የሚጠቀሙበትን ሥነ - ሥርዓትና መርሆችን የሚይዝ መሆኑ፤

-    የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ሥልጣናቸውን በተግባር ሲያውሉ ቁጥጥር ስለሚደረግባቸው ሁኔታዎች /ዘዴዎች/ የሚገልጽ መሆኑ፤

-   የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች የሚቋቋሙበትን የፓርላማ ሕጎች፣ የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶቸች ራሳቸው የሚያወጡትን የበታች ወይም የውክልና ሕጎች፣ እንዲሁም ከአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች አሠራር ጋር በተገናኘ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡትን ውሳኔዎች እና መፍትሔዎች የሚያጠቃልል መሆኑን ለመረዳት እንችላለን፡፡ 

የአስተዳደር ሕግም ሆነ ሥነ ሥርዓቱ የሕገ መንግሥታዊ ሕግን ጠባይ የሚጋራ በመንግሥት የአስተዳደር ተቋማትና በግለሰብ መካከል በሚደረገው ግንኙነት የሕግ የበላይነት የሚያሰፍን ሕግ እንደመሆኑ የመንግስት አካላት ግልጽነት፣ ተጠያቂነትንና ውጤታማነት እንዲሁም ቀልጣፋነትን መሠረት አድርገው እንዲሠሩ ያስገድዳቸዋል፡፡ በተለይም የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ ለመንግስት አስተዳደር ተቋማት የተሰጣቸውን በጣም ሰፊ የሆነ ሕግ ለማስፈፀም ሥልጣን ሲፈቀድላቸውም ሕግ ለማውጣትና የመዳኘት ሥልጣናቸውን በመገደብና የዘፈቀደ አሰራር በማስወገድ አስተዳደራዊ በደሎች እንዳይፈጸሙ ጉልህ ሚና የሚጫወት ሕግ ነው፡፡

እንግዲህ ስለአስተዳደር ሕግ ምንነትና ጠቀሜታው በአጭሩ ይህን ያህል ካልን ይበቃናል፡፡ የሚገርመው በኢትዮጵያ ሀገራችን የመንግስት የአስተዳደር አካላት ሥልጣናቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉበት የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ የለም፡፡ ይህ ሕግ ባለመኖሩም በሀገራችን በአስተዳደር በኩል ብዙ ችግሮችና እንከኖች እንደሚኖሩ ለመገመት የሚከብድ አይሆንም፡፡ እነዚህም ከአስተዳደር አካላት የሕግ አወጣጥ፣ የሕግ አፈፃፀም እና የውሳኔ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ሊታዩ የሚችሉ ናቸው፡፡ የአስተዳደር አካላት የተሰጣቸውን የውክልና ሥልጣን መሠረት በማድረግ አስተዳደራዊ ሕግ ሲያወጡ ሊከተሉት የሚገባ ወጥነት ያለው ሥርዓት ካልተዘረጋ፣ ሕግን በማስፈጸም ረገድ ግልጽና ወጥነት ያለው የአሠራር ሥርዓት ከሌለ፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱም ተገማችነቱን የሚያረጋግጥ ሥርዓት ካልወጣለት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡት መሠረታዊ መርሆዎች በትክክል ይተገበራሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡

የአስተዳደር ሕግና ሥነ-ሥርዓት ባለመኖሩ የተከሰቱትን ችግሮች ዘርዝሮ ለማብራራት በእውነት አቅም ያጥረኛል፡፡ ለምሳሌ ያህል በመሬት አስተዳደር፣ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በምርጫ ቦርድ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ በበጎ አድራጎትና ማህበራት፣ በኮንስተራክሽንና ከተማ ልማት፣ በንግድ ምዝገባና ፈቃድ፣ በኢንቨስትመንት ረገድ የሚወጡትን መመሪያዎች አስቡት…? ‹‹መመሪያ ነው!›› የሚለውን አጭር አሰልቺ ቃል አስቡት? መመሪያው ስለማይታተም ማግኘች አለመቻላችንን አስቡት? የአስተዳደር ሕግና ሥነ ሥርዓቱ ቢታሰብበት ምን ይመስላችኋል?