1ኛ) በፍታብሔር ሕግ ቁጥር 2105(2) የህሊና ጉዳት በሕጉ በግልፅ ካልተመለከተ በቀር የገንዘብ ካሳ የማያስከፍል መሆኑ ተደንግጓል። በሌሎች ህጎች ስለ ሞራል ካሳ የተደነገጉ ድንጋጌዎች እንዳሉ ሆነው በፍትሐብሔር ሕጉ ከውል ውጪ ስለሚደርስ ሃላፊነት ስር የገንዘብ ካሳ የሚያስገኙ የህሊና ጉዳት ዓይነቶች በፍተሐብሔር ሕጉ ከቁጥር 2106 እስከ ቁጥር 2115 ድረስ ያሉት ብቻ ናቸው።

ለምሳሌ በፍ/ብ/ህ/ቁ. 2113 በአካል ጉዳት ግዜ ለህሊና ጉዳት የገንዘብ ኪሳራ ሊወሰንላቸው የሚገባው በጉዳቱ አካሉ ለጎደለ ብቻ ነው። (እዚህ ላይ ህጋችን የተጎጂውን አደጋው ሲደርስበት ያጋጠመውን ድንጋጤ፥ በጉዳቱ የደረሰበትን ህመምና ስቃይ pain & suffering ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አይመስለኝም።) እስኪ አስቡት የአካል ጉዳት ደርሶባችሁ ታክማችሁ ብትድኑ እካላችሁ እስካልጎደለ ድረስ በገንዘብ ረገድ ያጣችሁትን ወይም የምታጡትን እንጂ በአደጋው የደረሰባችሁን ድንጋጤ እና የህመም ስሜት (none-pecuniary damages) ካሳ አይከፈላችሁም ማለት ነው።

ስለዚህ የጉዳት ካሳ ዓላማው ተጎጂውን መካስ ስለሆነ ጉዳት መድረሱ እስከተረጋገጠ ድረስ ለሁሉም የህሊና ጉዳቶች የገንዘብ ካሳ ይገባቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለሆነም በፍ/ብ/ህ/ቁ. 2105(2) ላይ (የሕሊና ጉዳት በሕጉ በግልፅ ካልተመለከተ በቀር ስለ ጉዳት ካሳ የገንዘብ ኪሳራ አያስከፍልም)) ተብሎ መደንገጉ የተጎጂውን የመካስ መብት ከማጣበብ በቀር ፋይዳው አልገባኝም።

2ኛ/ ሌላው የገንዘብ ካሳ የሚያስገኙ ናቸው ተብለው በሕጉ በግልፅ የተመለከቱት የህሊና ጉዳት አይነቶችም ቢሆኑ ለጉዳቱ የሚከፈለው ከፍተኛ የካሳ መጠን 1000 ብር መሆኑ በፍ/ብ/ህ/ቁ. 2116 ላይ ተመልክቷል። (በእርግጥ ሕጉ በወጣበት ዘመን 1000 ብር በጣም ከፍተኛ የገንዘብ መጠን እንደነበረ አያጠያይቅም በጊዜው ይህ የገንዘብ መጠን መኖሪያ ቤት ይገዛ እንደነበር እድሜ ጠገብ አዛውንቶች ሲያወሩ ሰምቻለሁ በዚህ ዘመን ግን ለቤት ኪራይም አይሆን።)

ሕጉ ከወጣ ድፍን 55 አመት ቢሆነውም ሀገሪቱ ከምትገኝበት ኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታ እና ከብራችን የመግዛት አቅም ጋር በተጣጣመ መልኩ እስካሁን መሻሻል ሲገባው ተረስቷል። ስለዚህ ሕጉ መሻሻል ይገባዋል።

እስኪ አስቡት በፍ/ብ/ህ/ቁ. 2114 ላይ የተደፈረች ሴት ወይም በሃይል የተገሠሠች ልጃገረድ ለደረሰባት የህሊና በደል ካሳ እንደሚከፈል ተደንግጓል። እስኪ አንዲት ካለፈቃዷ ተገዳ ብትደፈር ክብረ ንፅህናዋንም ብታጣ ሊደርስባት የሚችለውን የሞራል ስብራት አስቡት ... ታዲያ ለዚህ አንድ ሺ ብር? ይህ ራሱ ሌላ የሞራል ጉዳት ያስከትላል። እውን ህሊናችን ይህን ያህል ርካሽ ነው?