ምትክ ዳኛ መሾም ለምን አስፈለገ?    

ፍርድ ቤቶች የሚመለከቷቸው ጉዳዮች ዘርፈ ብዙ እንደመሆናቸው መጠን እንደየጉዳዩ ሁኔታ በቀላሉ የቀረቡ ማስረጃዎችን እና የተከራካሪ ወገኖችን ክርክር በመስማት ብቻ ከሚወሰንባቸው መዛግብት አንስቶ እጅግ ጥልቅ የሆነ ምርመራ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን መመልከትና እውነትን ከችሎት ውጭ በሚደረግ ምልከታና ምርመራ ማፈላለግ እንዲሁም እንደጉዳዩ ዓይነት የሂሳብ ምርመራ ማድረግ የሚጠይቁ መዛግብቶች በርካታ ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች (ዳኞች) ከሚመለከቷቸው መዛግብት ብዛትና ከሚኖርባቸው የሥራ ጫና አንፃር ከችሎት ሥራ በተጨማሪ ከችሎት ውጪ የክርክር ምክንያት የሆኑ ስፍራዎች ላይ እየተገኙ አስፈላጊ ማጣራትና ምርመራ ከሚያደርጉ ይልቅ ፍርድ ቤቶች በሚሾሟቸው ምትክ ዳኞች በኩል ሥራዎቹ ቢከናወኑ የፍርድ ቤቶችን/ዳኞችን የሥራ ጊዜና ጫና ይቀንሳል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም በሀሰት የሚቀርቡ ክሶችን ወይም ክርክሮችን ውድቅ ለማድረግ ለክርክር ምክንያት በሆኑ ስፍራዎች በመገኘትና በቂ ምርመራና ማጣራት በማድረግ በቀላሉ ለመወሰን ያግዛል፡፡

የምትክ ዳኞች የሥራ ኃላፊነት ምንድን ነው?           

ምትክ ዳኞች በፍርድ ቤት ከተሸሙ በኋላ የሚከተሉትን የሥራ ኃላፊነቶች መወጣት እንዳለባቸው የሥነ ሥርዓት ሕጉ ይጠቁማል፡፡ እነዚህም፡ -

ክርክር ከሚደረግበት ጉዳይ ጋር በተያያዘ የክርክሩ ምክንያት በሆነው ስፍራ ላይ በመገኘት አስፈላጊ የሆኑና ከክርክሩ ጋር የተያያዙ ለፍርድ ቤት ውሳኔ አሠጣጥ የሚጠቅሙ ነጥቦችን ማጣራትና መመርመር፤

የክርክር ምክንያት በሆነ ስፍራ በመገኘት እንደአስፈላጊነቱ የምስክሮች ቃል መቀበል እና ማስረጃዎች መሠብሠብ፤

የክርክር ምክንያት በሆነ ስፍራ በመገኘት ከተደረገው ማጣራት፣ ምርመራ፣ የምስክሮች ቃልና የተሰባሰቡ ማስረጃዎች እንዲሁም ችሎቱ እንዲጣራለት ከፈለገውና ትዕዛዝ ከሠጠባቸው ነጥቦች አንፃር ለፍርድ ቤቱ በፅሁፍ መግለጫ /ራፖር/ የማቅረብ፤

ራፖር በቀረበበት ጉዳይ ላይ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የመሀላ ቃል በመስጠት በግልፅ ችሎት ከተከራካሪዎችና ከፍርድ ቤቱ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠት፤

በፍርድ ቤት ሲታዘዝ ሒሳብ ማጣራት አስፈላጊ በሆነባቸው ክርክር እና መዛግብት ላይ የሒሳብ ምርመራ አጣርቶ ከአስተያየት ጋር ራፖር የማቅረብ ኃላፊነቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ፍርድ ቤቶች/ዳኞች ከምትክ ዳኞች ጋር በተያያዘ የተጣለባቸው ኃላፊነት ምንድን ነው?       

ክርክር እየተደረገበት የሚገኝ ጉዳይ ላይ በስፍራው በመገኘት ነገሮችንና የክርክር መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን እንዲሁም ሂሳብ ማጣራትና መመርመር አስፈላጊና የሚጠቅም መሆን አለመሆኑን ተመልክቶ አስፈላጊና ጠቃሚ ሆኖ ሲገኝ ምትክ ዳኛ የመሾም ወይም እንዲሾም የማድረግ፤

ምትክ ዳኛ ሲሾም በስፍራ ተገኝቶ የሚጣራው ወይም ሒሳብን በተመለከተ የሚያጣራቸውን ነጥቦችና እንደአስፈላጊነቱ ሊሰበስባቸው የሚገቡ እና የማስረጃ ዓይነቶችንና ቃል ሊቀበላቸው የሚገባ ምስክሮችን ዓይነት በማመላከት ግልፅነት ያለው ትዕዛዝ መስጠት፤

ምትክ ዳኛው የሚያቀርበው ራፖር በተሠጠው ትዕዛዝ መሠረት ከምትክ ዳኛው አስተያየት ጋር መቅረቡን ማረጋገጥና የጎደለ ነገር ካለ በድጋሚ እንዲጣራ የማድረግ፤

በፍርድ ቤቱ ሲታመንበት ወይም ተከራካሪ ወገኖች ሲጠየቁ ምትክ ዳኛው በግልፅ ችሎት በመሐላ ቃል ስለራፖሩ ቃሉን እንዲሰጥ የማድረግ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ተከራካሪ ወገኖች ከምትክ ዳኞች አንፃር ለፍርድ ቤት ሊያነሱ የሚችሉት ምን ዓይነት ጥያቄዎች ናቸው?

ተከራካሪ ወገኖች ክርክር በሚያደርጉበት ጉዳይ ላይ በፍርድ ቤት የተሾመ ምትክ ዳኛ በሚያቀርበው መግለጫ (ራፖር) ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ምትክ ዳኛው ስላጣራው እና ስለመረመረው ጉዳይ የመሀላ ቃል ፈፅሞ በግልፅ ችሎት ስለ ሁኔታው እንዲያስረዳ ለመጠየቅ ይችላሉ፡፡

ምትክ ዳኛ ሊሾም የሚችለው በምን ዓይነት ጉዳዮች ላይ ነው?

የዕለት የገበያ ሁኔታ ማወቅ በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ፤

የካሣ ልክ ማረጋገጥ በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ፤

ካንድ ሀብት የተገኘ የዓመት ትርፍ ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ፤

ያለአግባብ የተወሰደ ንብረት የሀብት ግምት ማጣራት በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ፤

እንደ የመተላለፊያ መብቴ ተጣበበብኝ፣ ያለአግባብ የባለቤትነት መብቴ ተጣበበብኝ እና ይህን መሰል በሆኑ ለክርክር ምክንያት በሆነው ስፍራ ተገኝቶ ሁኔታዎችን ማጣራትና መመርመር የሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ፣

የሂሳብ ምርመራ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉ የምትክ ዳኞችን የሥራ ተሳትፎ የሚጠይቁ ጉዳዮች ናቸው፡፡      

የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 132፣ 133፣ 134 እና 135 ተግባራዊ አፈፃፀም ምን ይመስላል?

ሥነ ሥርዓት ሕጉ ክርክር የተነሳባቸው ጉዳዮች ላይ በስፍራ ተገኝቶ ማጣራት እና መመርመር በሚያስፈልጋቸው እንዲሁም የሒሳብ ምርመራ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ምትክ ዳኛ መሾም እንዳለበት እና ምትክ ዳኛውም አስፈላጊውን ማጣራትና ምርመራ አድርጎ በሚያቀርበው መግለጫ /ራፖር/ መሠረት ፍርድ ቤቶች ሊወስኑ እንደሚገባ ቢያመለከትም በፌደራልም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች በኩል ሕጉ ሲተገበር አይታይም፡፡  

በሕጉ መሠረት በምትክ ዳኛ ማጣራትና ምርመራ ተደርጎባቸው በሚቀርቡ መግለጫዎች /ራፖር/ መሠረት ፍርድ ሊሰጥባቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች ላይ የምትክ ዳኛ ሳይሾም፣ ማጣራትና ምርመራ ሳይደረግ እንዲሁም መግለጫ ሳይቀርብባቸው ፍርድ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በፍርድ ቤቶች በኩልም በዕለት ተዕለት ሥራቸው ውስጥ ከዳኞች ውጪ ተያያዥ ሥራዎችን ሲያከናውኑ የሚታዩት ረዳት ዳኞች እንጂ ምትክ ዳኞች አይደሉም፡፡ ረዳት ዳኞችም በመዛግብት ላይ ክስ ሲሰሙ፣ ቀጠሮ ሲሰጡ እንዲሁም የምርመራ መዛግብት ላይ ፍርድ በመስጠት ዋና ዳኞችን ሲያግዙ አለፍ ሲልም የውርስ ሀብት የማጣራት ሥራ ሲሰሩ እንጂ በሥነ ሥርዓት ሕጉ የተቀመጠውን የምትክ ዳኛ ተግባራት ሲያከናውኑ አይታዩም፡፡

ፍርድ ቤቶች ክርክር ያስነሳ ንብረት ከሚገኝበት ስፍራ ተገኝቶ መመርመርና ማጣራት የሚጠይቁ ጉዳዮችን እንዲያጣሩ የሚያደርጉት በብዛት በክፍለ ከተማ አስተዳደር አካላት በኩል ተጣርቶ በፅሁፍ ይገለፅ በሚል መሆኑም ድንጋጌው ተግባራዊ አለመደረጉን ከማሳየቱ ባሻገር ከተዓማኒነት አንፃር በተከራካሪ ወገኖች ቅሬታ የሚያስነሳ አሠራር ነው፡፡     

ድንጋጌዎቹ ተፈፃሚ ሊሆኑ ያልቻሉት በርግጥ ምትክ ዳኞችን ሊያስሾሙ የሚችሉ ጉዳዮች ስለሌሉ? ወይስ ፍርድ ቤቶች ምትክ ዳኞችን ለመሾም የሚያስችል መዋቅርና አሠራር ስለሌላቸው? የሚሉ ጥያቄች በዳኞች ወይም ፍርድ ቤቶች ሊታዩ የሚገባቸው ናቸው፡፡  

የመፍትሔ ሀሳቦች

የሕግ አውጪው ወይም ፍርድ ቤቶች የምትክ ዳኞችን ተሳትፎ የሚጠይቁ ጉዳዮችን ዓይነት፣ ምትክ ዳኞች ሊኖራቸው ስለሚገባው የትምህርት ደረጃና የሥራ ልምድ፣ ምትክ ዳኞች እንዴት፣ በማንና በምን ሁኔታ እንደሚሾሙ የሚያመላክት እንዲሁም ምትክ ዳኞች ሊሰሩ ስለሚገባበት ሁኔታና ሌሎች ተያያዥ ነጥቦች የሚያመላክት ሕግ እንዲወጣ ማድረግና ድንጋጌዎቹም መፈፀማቸውን በአግባቡ መከታተል ለሕጉ ተፈፃሚነት መፍትሔ ይሆናል ባይ ነኝ፡፡