በዚሁ አዋጅ የፌዴራል የጥብቅና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ ያገኙ ጠበቆች ሁለት ወይም ከሁለት በላይ በመሆን የንግድ ማኅበር ባልሆነና ኃላፊነቱ ባልተወሰነ ማኅበር የጥብቅና ሙያ አገልግሎት ድርጅት ማቋቋም እንደሚችሉና ከፍትሕ ሚኒስቴር ፈቃድ እንደሚያገኙ በአንቀጽ 18 ሥር በመደንገግ ስለጥብቅና ሙያ አገልግሎት ድርጅት ፈቃድ አሰጣጥ እና ከዚሁ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች አዋጁን ተከትሎ በሚወጣ መመሪያ እንደሚወሰን አንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ 4 ይገልፃል፡፡

ነገር ግን የዚህ አዋጅ ድንጋጌ እስካሁን ድረስ ተፈጻሚነት ያላገኘ ስለሆነ ወይም የጥብቅና አገልግሎት ድርጅትን የሚመለከት መመሪያ ስላልወጣ ጠበቆች ተደራጅተው አገልግሎቱን ሊሰጡ አልቻሉም፡፡ ከቁጥጥርና አስተዳደር አንፃርም ሲታይ የጥብቅና ሙያ አገልግሎት ድርጅት ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ሥራን በአግባቡ ለማከናውንም አልተቻለም፡፡

በመሆኑም የአዋጁ አንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ 4 ድንጋጌ እስካሁን ሥራ ላይ ያልዋለ በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተለይ ፍትሕ ሚኒስቴርና የጠበቆች ማኅበር በመተጋገዝ የጥብቅና አገልግሎት ድርጅትን የሚመለከት ሕግ እንዲወጣ ቢደረግ የጥብቅና አገልግሎት አሰጣጥን ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንዲሁም የጠበቆች ተደራጅቶ የመሥራት ፍላጎ ለማሟላት የሚረዳ ይሆናል፡፡