መብትዎን ይወቁ - እንደ አሠሪ ወይም እንደ ሠራተኛ ያለበዎት ግዴታ

Feb 18 2014

ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኛ ከሆኑ መሠረታዊ ሕጋዊ መብትና ግዴታ አለበዎት፡፡ ከአሠሪና ሠራተኛ መብትና ግዴታ ተያይዘው ያሉ መብቶች አጅግ በርካታ ቢሆኑም ዋና ዋና የሚባሉትን ግዴታዎች ቢያወቁ ለርሶ ጠቃሚ ይሆናል በሚል እምነት የአሠሪና ሠራተኛ ግዴታዎች ጠቅለል ባለ መልኩ አቅርበነዋል፡፡

የአሠሪ ግዴታዎች

አሠሪ የሚከተሉት ግዴታዎች አሉበት፡፡

  • ሥራ የመስጠትና ውሉ በሌላ ሁኔታ ካልገለጸ በስተቀር መሣሪያና ጥሬ ዕቃ የማቅረብ ግዴታ
  • ደሞዝና ሌሎች ክፍያዎችን የመፈጸም ግዴታ
  • የሰራተኛውን ሰብአዊ ክብር፣ ከስራ ጋር የተያያዘ ጤንነትና ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ
  • ሕጉ በሚያዘው መሰረት የተለያዩ ሁኔታዎችን በመዝገብ የመያዝ እና አግባብ ባለው አካል ሲጠየቅ መዝገብ የማቅረብ ግዴታ
  • የስራ ዓይነቱን ዘመንና ሲከፈለው የነበረውን ደሞዝ የሚያሳይ የምስክር ወረቀት ለሰራተኛው የመስጠት ግዴታ እና
  • በሕጎችና በሥራ ውል ደንቦች እና መመሪያዎችን እንዲሁም ትዕዛዞችን የማክበር ግዴታዎች አሉበት፡፡

የሠራተኛ ግዴታዎች

ሠራተኛየሚከተሉት ግዴታዎች አሉበት፡፡

  • ሥራውን እራሱ የመስራት (በሌላ ሰው ማሠራት የተከለከለ ነው)፣ በአካልና በአዕምሮ ሁኔታ በስራ ቦታ ብቁ ሆኖ መገኘትና ትዕዛዝን የመፈጸም፡፡ አሠሪው የሚሰጣቸው ትዕዛዛት ግን ሁልጊዜም በስራ ውሉና በስራ ደንቡ መሠረት የተሰጡ መሆን አለባቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉ ትዕዛዛትን ሠራተኛው የመፈጸም ግዴታ የለበትም፡፡
  • መሣሪያዎችና ዕቃዎችን ሁሉ በጥንቃቄ የመጠበቅ
  • የንብረትና የህይወት አደጋ እንዳይደርስ ወይም አስጊ ሁኔታ ሲፈጠር ተገቢውን ዕርዳታ የመስጠትና እነዚህ እና የድርጅቱን ጥቅም የሚነኩ ሌሎች ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ወዲያውኑ ለአሠሪው የማስታወቅና
  • በሕጎችና በሥራ ውል ደንቦች እና መመሪያዎችን እንዲሁም ትዕዛዞችን  የማክበር ግዴታዎች ናቸው፡፡

እነዚህን ግዴታዎች አለመወጣት እንደሁኔታው ከስራ እስከማባረር የሚያደርስ ውጤት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ሰራተኛ የአሰሪውን ንብረት ከአደጋ መከላከል የሚገባው ሆኖ ሳለ በተቃራኒው በአሰሪው ንብረት ላይ ሆነ ብሎ ወይም በከባደ ቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ ያለማስጠንቀቅያ ከስራ የሚያስባርር ድርጊት ነው፡፡ 

Read 9537 times Last modified on May 22 2015
Liku Worku

Liku Woku is a founder and administrator of Abyssinia Law. He graduated From Mekelle University with LLB (2007) and the University of London with a LLM in Advanced Legislative Studies (2012). Currently, he is a consultant and attorney at law. Before joining the advocacy world Mr. Liku worked as a Draft Person and Public Prosecutor at Ministry of Justice and Part-time Lecturer at Addis Ababa University. As a founder of abyssinialaw he is responsible for the development of free access to Public legal information.