መብትዎን ይወቁ - በፖሊስ መያዝ፣ ማረፊያ ቤት መወሰድ ጋር በተያያዘ

Feb 14 2014

ፖሊስ ካስቆምዎ

 • ፖሊሱን ማናገር አይጠበቅቦትም፡፡ ሁሉጊዜም ቢሆን ያለመናገር ወይም ዝም የማለት መብት አለዎት፡፡ ያለመናገር ወይም ዝም የማለት መብት ማለት በተጠረጠሩበት ወንጀል ምንም ዓይነት መግለጫ ያለመስጠት መብት ማለት ሲሆን ስምና አድራሻዎትን ወይም ስለማንነትዎ መናገር ግን ግዴታዎ መሆኑን ያስታውሱ፡፡
 • ፖሊስን ሁል ጊዜ የሚታሰሩ እንደሆነ የመጠየቅ መብት አለዎት፡፡ ፖሊስ የማያስረዎት እንደሆነ ከነገሮዎት ሁልጊዜም ቢሆን ፖሊስን ትተውት ሊሄዱ ይችላሉ፡፡
 • ለመፈተሽ ፈቃደኛ አለመሆኖትን ሁልጊዜም ቢሆን ለፖሊስ መግለጽ ይኖርቦዎታል፡፡ ከዚህ የዘለለ ፖሊስ በሚያደርገው ፍተሻ አካላዊ ትግል ማድረግ ለበለጠ ወንጀል ኃላፊነት ስለሚያጋልጥዎ አካላዊ ትግል ከፖሊስ ባልደረባ ጋር አያድርጉ፡፡
 • ከፖሊስ ጋር በሚያደርጉት ንግግር ሁልጊዜ በአካባቢዎ ያሉ ምስክር ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ማስታወስ አለበዎት፡፡
 • ጠበቃ ለማግኘት ወይም ስልክ ለመደወል ጊዜ ስለማይኖርዎት፣ ውሳኔ ከመወሰንዎ በፊት ወይም ፍርድ ቤት ከመቅረብዎ በፊት በአብዛኛው ጊዜ ስለማያገኙ ከዚህ የሚከተሉትን ማወቅና ማጥናት አስፈላጊ ነው፡፡
 • ሁልጊዜ ያለመናገር ወይም ዝም የማለት መብት አልዎ፡፡ ይህንን መብትዎን ለመጠቀም ‹‹ያለመናገር ወይም ዝም የማለት መብት አለኝ ስለዚህ ጠበቃ ማናገር እፈልጋለሁ›› ማለት ይችላሉ፡፡
 • አብዛኛውን ጊዜ በማረፊያ ቤት ሊቆዩ ስለሚችሉ፡-
  • በ48 ሰዓት ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት እንዳልዎ ይወቁ፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በማረፊያ ቤት ሊቆዩ የሚችሉት ለ48 ሰዓት ብቻ ነው፡፡
  • ፖሊስ አንዳንድ ጊዜ በተፈለጉ ጊዜ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ዋስትና በማቅረብ ሊለቅዎ ስለሚችል በዋስትና ከማረፊያ ቤት መውጣት ይችሉ እንደሆን የመጠየቅ መብት አልዎት፡፡ በዋስትና ከወጡ ፍርድ ቤት በፈለገዎ ሰዓት የመቅረብ ኃላፊነት እንዳለበዎት አይዘንጉ፡፡

በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ወይም ከታሠሩ

ልብ ይበሉ፡- ፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀርቡ ጠበቃ የሚያስፈልገዎት ከሆነ ጠበቃ መቅጠር እንደሚፈልጉ ለፍርድ ቤቱ ማስታወቅ ይችላሉ፡፡ በራስዎ ጠበቃ ማቆም የማይችሉ ነገር ግን ጠበቃ ያስፈልገኛል ያሉ እንደሆነ ይህንኑ ለፍርድ ቤቱ ያስታውቁ፡፡ በተለይ ቋንቋውን በማያወቁት ክልል ባለፍርድ ቤት የሚዳኙ ከሆነ ይህ መብት እንዳልዎ ይወቁ፡፡

እንደገና ልብ ይበሉ፡- በአንድ የወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው ፖሊስ ጣቢያ ቀረቡ ማለት ወይም በአንድ ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት ቀረቡ ማለት ወንጀለኛ ነዎት ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፖሊሶችና ዓቃቤ ሕጎች በተጋነነ የወንጀል አንቀጽ ወይም ከሚገባው በላይ ክስ ሊመሠርቱ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም በተጠረጠሩበት ወይም በተከሰሱበት ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኛ እስከሚባሉ ድረስ መረበሽ አይገባም፡፡

Read 8620 times Last modified on May 22 2015
Liku Worku

Liku Woku is a founder and administrator of Abyssinia Law. He graduated From Mekelle University with LLB (2007) and the University of London with a LLM in Advanced Legislative Studies (2012). Currently, he is a consultant and attorney at law. Before joining the advocacy world Mr. Liku worked as a Draft Person and Public Prosecutor at Ministry of Justice and Part-time Lecturer at Addis Ababa University. As a founder of abyssinialaw he is responsible for the development of free access to Public legal information.