የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ

Jun 19 2019

 

 

 

አዋጅ ቁጥር ---/2012

የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓትን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ

 

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞከራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት መንግስታዊ አሰራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበትና ማናቸውም የመንግስት ባለሥልጣን ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን የተመለከተ በመሆኑ፤

ዘመናዊ መንግሥት ከጊዜ ወደ ጊዜ ልዩ ልዩ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን የመስጠት ተግባሩን እያስፋፋ በመምጣቱ ምክንያት በአስተዳደር ተቋማቱ በኩል ከዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት መፍጠሩ በሰዎች መብቶችና ጥቅሞች ላይ የሚያስከትለው ጣልቃገብነት በሕግ የሚመራና ለሕግ የሚገዛ መሆኑን ማረጋገጥ በማስፈለጉ፤

የአስተዳደር ተቋሞች በሕግ የተሰጣቸውን አስተዳደራዊ ውሳኔ የመስጠት እና መመሪያ የማውጣት ሥልጣንና ተግባራት በሥራ ላይ ሲያውሉ በሕግ መመራታቸውንና ከተፈቀደላቸው የሥልጣን ክልል አለማለፋቸውን ለማረጋገጥ በሕግ ቁጥጥርና እርምት የሚደረግበት ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤

የአስተዳደር ተቋሞች በስልጣናቸው አላግባብ በመጠቀም ወይም ተግባራቸውን በአግባቡ ባለመወጣት ከሚያደርሱት በደል ዜጎችን መጠበቅና በደል ሲደርስባቸውም መፍትሄ የሚያገኙበት ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ፤

የአስተዳደር ተቋሞች የውሳኔ አሰጣጥና የመመሪያ አወጣጥ መርሆዎችና ሥነ-ሥርዓት  እንዲሁም በአስተዳደራዊ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ቅር የተሰኘ ሰዉ የውሳኔዎቹንና የመመሪያዎቹን ሕጋዊነት በፍርድ ቤት የሚያስመረምርበት ሥርዓት በመደንገግ የግልጽነትና የተጠያቂነት ባህል በማዳበር አስተዳደራዊ ፍትህን ማስፈን አስፈላጊ በመሆኑ፤

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 55(1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

 

ክፍል አንድ

ጠቅላላ ድንጋጌዎች

 

አንቀጽ 1 - አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅ "የፌደራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር ……/2012" ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

 

አንቀጽ 2 - ትርጓሜ

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ፤

 1. “የአስተዳደር ተቋም” ማለት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት አስፈጻሚ አካል ሆኖ በሕግ የተደራጀ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሲሆን ለፌደራል መንግሥት ተጠሪ የሆነ የከተማ አስተዳደርንም ይጨምራል፤ ሆኖም የፖሊስ፣ የመከላከያና የደህንነት ተቋሞችን አይጨምርም፤
 2. “መመሪያ” ማለት ሕግ አውጪው አካል በሚሰጠው የውክልና ስልጣን መሰረት በአስተዳደር ተቋም የሚወጣና በሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ውጤት የሚያስከትል የሕግ ሰነድ ሲሆን በስራ ላይ ያለ መመሪያን የሚያሻሻል ወይም የሚሽር የሕግ ሰነድንም ይጨምራል፤
 3. “የአስተዳደር ውሳኔ” ማለት መመሪያ ማውጣትን ሳይጨምር የአስተዳደር ተቋም በዕለት ተዕለት ተግባሩ በሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ የሚሰጠው ውሳኔ ነው፤
 4. "ሰው" ማለት ማናቸውም የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፤
 5. በዚህ አዋጅ በወንድ ጾታ የተገለጸው የሴትን ጾታ ይጨምራል፡፡

 

ክፍል ሁለት

የአስተዳደር መመሪያዎች

ንዑስ ክፍል አንድ

መርህ

አንቀጽ 3 - መመሪያ ስለማውጣት

 1. ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት መመሪያ ያወጣል፡፡
 2. የአስተዳደር ተቋም መመሪያ የሚያወጣው በዚህ አዋጅ በተደነገገው ሥነ-ሥርዓት መሠረት ብቻ ነው፡፡

 

አንቀጽ 4 - መመሪያ ስለሚወጣበት ጊዜ

 1. ማንኛዉም የአስተዳደር ተቋም ሊያወጣ የሚገባውን መመሪያ በተገቢው ጊዜ ማዉጣት አለበት፡፡
 2. ማንኛዉም የአስተዳደር ተቋም ሊያወጣ የሚገባውን መመሪያ አለማውጣቱ በሕግ በተሰጠው ኃላፊነት ሊሰጥ የሚገባዉን አገልግሎት ወይም አስተዳደራዊ ዉሳኔ ላለመስጠት ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡
 3. ማንኛውም ሰዉ መብቱን ወይም ጥቅሙን በሚመለከት የአስተዳደር ተቋም መመሪያ ያላወጣ ቢሆንም የአስተዳደር ውሳኔ እንዲሰጠው የመጠየቅ መብት አለው፡፡

 

አንቀጽ 5 - መመሪያ እንዲወጣ ጥያቄ ስለማቅረብ

 1. ማንኛውም ሰው አንድ የአስተዳደር ተቋም ሊያወጣው የሚገባዉን መመሪያ በተገቢው ጊዜ ሳያወጣ ቢቀር መመሪያውን እንዲያወጣ በጽሁፍ ሊጠይቀው ይችላል፤
 2. ጥያቄው የቀረበለት የአስተዳደር ተቋም በሠላሳ የሥራ ቀናት ውስጥ መመሪያውን የማውጣት ሂደት መጀመር ወይም ምክንያቱን በመግለጽ ጥያቄውን ውድቅ ማድረግ አለበት፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሁለት

የቅድመ መመሪያ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት

 አንቀጽ 6 - የመመሪያ አወጣጥን የሚመለከት መዝገብ ስለማደራጀት

 1. ማንኛዉም የአስተዳደር ተቋም የሚያወጣውን መመሪያ በተመለከተ የሚከተሉትን የያዘ መዝገብ ማደራጀት አለበት፤

ሀ. በተቋሙ በመታየት ላይ ያለ ረቂቅ መመሪያ ርዕሰ ጉዳይ እና የመመሪያውን አወጣጥ መርሃ ግብር፤

ለ. የረቂቅ መመሪያው ዝግጅት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚያመለክት መረጃ፤

ሐ. ረቂቅ መመሪያውን በተመለከተ የታተሙ ማስታወቂያዎች፤

መ. በረቂቅ መመሪያው ላይ አስተያየት ስለሚቀርብበት ጊዜ፤

ሠ. ረቂቅ መመሪያውን በተመለከተ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 8 እና 9 መሠረት የተሰበሰቡ አስተያየቶችንና በአስተዳደር ተቋሙ በአስተያየቶቹ ላይ የተወሰዱ አቋሞችን፡፡

 1. ማንኛውም ሰው በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሰረት የሚደራጀውን መዝገብ መመልከት ወይም አስፈላጊውን ወጪ ሸፍኖ ቅጂውን መውሰድ ይችላል፡፡

 

አንቀጽ 7 - ማስታወቂያ ስለማዉጣት

 1. የአስተዳደር ተቋም መመሪያ ከማውጣቱ በፊት ስለሚያወጣው ረቂቅ መመሪያ በጋዜጣ እና የተቋሙን ድረ ገጽ ጨምሮ በሌሎች የመገናኛ ብዙሃን የሚከተሉትን መረጃዎች የያዘ ማስታወቂያ ማውጣት አለበት፤
 2. የመመሪያውን ረቂቅ ለማዘጋጀት መሰረት የሆነውን ሕጋዊ ስልጣን እና በመመሪያው ስለሚካተቱት ርዕሰ ጉዳዮች፤
 3. የረቂቅ መመሪያውን ቅጂ ማግኘት የሚቻል ስለመሆኑና የሚገኝበትን ሁኔታ፤
 4. በረቂቅ መመሪያው ላይ ሰዎች አስተያያታቸውን መቼ እና እንዴት ሊያቀርቡ እንደሚችሉ፤
 5. በዚህ አዋጅ አንቀጽ 6 በተመለከተው መዝገብ የሰፈሩ መረጃዎችን የትና መቼ ማግኘት እንደሚቻል የሚገልፅ መረጃ፡፡

 

አንቀጽ 8 - ረቂቅ መመሪያን ለአስተያየት ስለመላክ

 1. የአስተዳደር ተቋም በዚህ አዋጅ አንቀጽ 7 በተደነገገው መሰረት ለሕዝብ ያሳወቀውን ረቂቅ መመሪያ ለሚመለከታቸው የአስተዳደር ተቋማትና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ለአስተያየት መላክ አለበት፡፡
 2. የሚመለከታቸው የአስተዳደር ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በረቂቅ መመሪያው ላይ አስተያየት ካላቸው አስተያየታቸውን ተቋሙ በሚወስነው የጊዜ ገደብ ውስጥ በጽሁፍ መላክ አለባቸው፡፡ ተቋሙ የሚወስነው የጊዜ ገደብ በማናቸውም ሁኔታ ከ15 የሥራ ቀናት ማነስ የለበትም።

 አንቀጽ 9 - የውይይት መድረክ ስለማዘጋጀት

 1. የአስተዳደር ተቋሙ በመመሪያው ረቂቅ ላይ የጽሑፍ አስተያየት መቀበያ ጊዜ ካበቃበት ጊዜ አንስቶ በ30 ቀናት ውስጥ ማንኛውም ሰው የሚሳተፍበት የውይይት መድረክ ማዘጋጀት አለበት፡፡
 2. ማንኛውም በዚህ አዋጅ አንቀጽ 8 መሠረት ያልተስተናገደ በመድረኩ የሚሳተፍ ሰው አስተያየቱን በጽሑፍ ጭምር ሊያቀርብ ይችላል፡፡
 3. የአስተዳደር ተቋሙ በሚያዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ አስተያየቶችን ማስተናገድ የሚያስችል በቂ ጊዜ መመደብ አለበት፡፡

 አንቀጽ 10 - ከመመሪያ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ነጻ ስለመሆን

 1. ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም መመሪያ ሲያወጣ በዚህ አዋጅ ከአንቀጽ 6 እስከ 9 ባሉት ድንጋጌዎች ከተመለከቱት ግዴታዎች በሚከተሉት ሁኔታዎች ነጻ ይሆናል፤

ሀ. የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ በመኖሩ በግዴታዎቹ ሥርዓት ውስጥ ለማለፍ ጊዜ የማይፈቅድ ሲሆን፤

ለ. ቅድመ ማስታወቂያ ማውጣቱ የሕዝብን ጥቅም የሚጎዳ ሆኖ ሲገኝ፤ ወይም

ሐ. ቅድመ ማስታወቂያ ማውጣቱ የመመሪያውን ተፈጻሚነት ፋይዳ ቢስ የሚያደርግ ሲሆን፡፡

 1. የአስተዳደር ተቋም መመሪያ ሲያወጣ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት ከግዴታ ነጻ እንዲሆን ያደረገውን ምክንያት የያዘ ዝርዝር መግለጫ ማዘጋጀት አለበት፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሦስት

መመሪያ ስለማጽደቅና ስለተፈፃሚነቱ

አንቀጽ 11 - መመሪያ ስለሚጸድቅበት ጊዜና ሁኔታ

 

 1. የአስተዳደር ተቋሙ በተዘጋጀው መመሪያ ረቂቅ ላይ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 8 እና 9 መሠረት የተወሰነው የጽሑፍ አስተያየት ማቅረቢያና የውይይት መድረክ ማካሄጃ ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ መመሪያውን ማጽደቅ አይችልም፡፡
 2. የአስተዳደር ተቋሙ መመሪያውን ከማጽደቁ በፊት በረቂቁ ላይ የቀረበ ማናቸውንም አስተያየት ከግምት ወስጥ ማስገባት አለበት።
 3. የአስተዳደር ተቋሙ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) የተመለከተውን ግዴታ ለመወጣት በአስተያየቱ መሠረት ማስተካከያ ማድረግ ወይም አስተያየቱን የማይቀበል ከሆነ፣ የማይቀበልበትን ምክንያት የሚያብራራ ጽሑፍ ማዘጋጀት አለበት።
 4. የአስተዳደር ተቋሙ ረቂቅ መመሪያውን ከማጽደቁ በፊት ለአስተያየት ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መላክ አለበት፡፡
 5. ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የረቂቅ መመሪያውን ሕጋዊነት አስመልክቶ በ15 የሥራ ቀናት ውስጥ አስተያየቱን ለአስተዳደር ተቋሙ መላክ አለበት፡፡ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ አስተያየቱን ከአልላከ አስተያየት እንደሌለው ተቆጥሮ መመሪያውን የማጽደቁ ሂደት ይቀጥላል፡፡

አንቀጽ 12 - በመመሪያው ረቂቅና በሚወጣው መመሪያ መካከል ልዩነት ስለመኖር

 1. የአስተዳደር ተቋሙ በማስታወቂያ ከተመለከተው ረቂቅ መመሪያ ጋር መሠረታዊ ልዩነት ያለው መመሪያ ማዉጣት አይችልም፤ ሆኖም መሠረታዊ ልዩነት ያለው መመሪያ ለማውጣት ከፈለገ የተጀመረውን የመመሪያ አወጣጥ ሂደት በማቋረጥ አዲስ የመመሪያ አወጣጥ ሂደት ከመጀመር አይከለከልም፡፡
 2. አንድ በመጨረሻ መልክ የተዘጋጀ መመሪያ በማስታወቂያ ከተመለከተው የመመሪያው ረቂቅ መሠረታዊ ልዩነት አለው ሊባል የሚችለው በሚከተሉት ሁኔታዎች ነው፤

                ሀ. የረቂቅ መመሪያው የተፈጻሚነት ወሰን በጉልህ የተለወጠ ከሆነ፤ ወይም

                ለ. ረቂቅ መመሪያው አዳዲስ ግዴታዎችን አካትቶ የተገኘ ከሆነ፡፡

 

አንቀጽ 13 - የማብራሪያ ጽሑፍ

ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም መመሪያ በሚያወጣበት ጊዜ የሚከተሉትን መረጃዎች የያዘ ማብራሪያ ማዘጋጀት አለበት፤

 1. መመሪያው የወጣበት የሕግ መሠረትና ዓላማ፤
 2. በማስታወቂያው የተሰራጨው ረቂቅና የመጨረሻ ሆኖ በወጣው መመሪያ መካከል የይዘት ልዩነት ካለ የተደረጉትን ለውጦች ከነምክንያቶቹ የሚገልጽ ማስታወሻ፤
 3. በረቂቅ መመሪያው ላይ የቀረቡ አስተያየቶችና የተወሰዱ እርምጃዎች ማጠቃለያ፡፡

 አንቀጽ 14 - የመመሪያ ይዘትና ቅርጽ

 1. በአስተዳደር ተቋም የሚወጣ ማንኛዉም መመሪያ ከመመሪያው ዋና ይዘት በተጨማሪ የሚከተሉትን መያዝ አለበት፤

ሀ. መመሪያው እንዲወጣ የሥልጣን ምንጭ የሆነውን ሕግ፤

ለ. የመመሪያውን አጭር ርእስ፤

ሐ. የተሻሩ ወይም ተፈጻሚነታቸው የታገዱ መመሪያዎች ካሉ ይህንኑ የሚመለከት ድንጋጌ፤

መ. የዚህ አዋጅ አንቀጽ 17 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መመሪያው የወጣበትንና ተፈጻሚ የሚሆንበትን ቀን፡፡

 1. ማንኛውም መመሪያ በአጭርና በግልጽ ቋንቋ መጻፍ አለበት፡፡
 2. የአስተዳደር ተቋም ሌላ አካል ያወጣቸውን በሥልጣኑ ክልል የሚወድቁ መመሪያዎች ወይም የሥነ-ምግባር ደንቦች በሙሉ ወይም በከፊል በማጣቀስ የራሱ መመሪያ አካል ማድረግ ይችላል፡፡ በዚህ መንገድ የመመሪያው አካል ያደረጋቸውን ሰነዶች ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ አለበት፡፡

አንቀጽ 15 - የመመሪያዎች ምዝገባ

 

 1. ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም መመሪያ እንዳወጣ ወዲያውኑ መመሪያውን ከነማብራሪያው ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በመላክ እንዲመዘገብ ማድረግ አለበት፡፡
 2. ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በሥራ ላይ የነበረ መመሪያን ይህ አዋጅ በወጣ ከ90 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በመላክ እንዲመዘገብ ማድረግ አለበት፡፡
 3. የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመዘገበውን መመሪያ ከነማብራሪያው ለሕዝብ ክፍት ማድረግ አለበት፡፡ መመሪያው ስለመመዝገቡም ለአስተዳደር ተቋሙ ወዲያውኑ ማሳወቅ አለበት፡፡

አንቀጽ 16 - መመሪያውን ተደራሽ ስለማድረግ

 

 1. የፌድራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 15 መሠረት የመዘገበውን መመሪያ በድረ ገጹ ላይ መጫን አለበት፡፡
 2. ማንኛዉም የአስተዳደር ተቋም ያወጣውን መመሪያ፣

ሀ.  አሳትሞ ለሚመለከታቸው መንግስታዊና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ማሠራጨት፣ እና

ለ.  በተቋሙ ድረ ገጽ ላይ መጫን፣

አለበት፡፡

 1. ማንኛዉም የመመሪያውን ቅጂ ማግኘት የሚፈልግ ሰው ወጪውን ሸፍኖ ከአስተዳደር ተቋሙ መውሰድ ይችላል፡፡

አንቀጽ 17 - የመመሪያ ተፈጻሚነት

 1. በዚህ አዋጅ አንቀጽ 15 መሠረት ያለተመዘገበና በአንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ 2(ለ) መሠረት በአስተዳደር ተቋሙ ድረ ገጽ ላይ ያልተጫነ መመሪያ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡
 2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት ተፈጻሚነቱን ያጣ ነባር መመሪያ በዚህ ክፍል ንዑስ ክፍል ሁለት የተደነገገውን የቅድመ መመሪያ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ተከትሎ እንደ አዲስ እንዲወጣ ሊደረግ ይችላል፡፡

 አንቀጽ 18 - ስለመመሪያ ክለሳ

ማንኛዉም የአስተዳደር ተቋም ያወጣውን መመሪያ አፈጻጸም በተመለከተ በየጊዜው እየገመገመ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡

 

ክፍል ሦስት

የአስተዳደር ውሳኔዎች

ንዑስ ክፍል አንድ

የአስተዳደር ውሳኔ አጀማመር

 አንቀጽ 19 - የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄ ስለማቅረብ

የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄ ጉዳዩ በሚመለከተዉ ሰዉ ወይም በወኪሉ ሊቀርብ ይችላል፡፡

አንቀጽ 20 - የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄ የሚቀርብበት ሁኔታ

 1. የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄ በጽሑፍ ሆኖ እንደሁኔታዉ በአካል፣ በተመዘገበ ፖስታ ወይም በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ሊቀርብ ይችላል፡፡
 2. የአስተዳደር ተቋም የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄ የሚቀርብበትን ቅጽ ሊያዘጋጅ ይችላል፡፡

አንቀጽ 21 - የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄን ስለመመዝገብ እና ለውሳኔ ስለማቅረብ

የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄ የቀረበለት ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም ወዲያውኑ ለጥያቄ አቅራቢዉ ደረሰኝ መስጠት እና ጥያቄው በተገቢዉ ጊዜ እንዲመዘገብና ለውሳኔ እንዲቀርብ ማድረግ አለበት፡፡

አንቀጽ 22 - የአስተዳደር ውሳኔን በአስተዳደር ተቋም አነሳሽነት ስለመጀመር

የአስተዳደር ውሳኔ በሚመለከተዉ የአስተዳደር ተቋም አነሳሽነት ሊጀመር ይችላል፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሁለት

የአስተዳደር ውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎች

 

 አንቀጽ 23 - የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠው ሰው

የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ የአስተዳደር ተቋሙ የበላይ ኃላፊ ወይም ሥልጣን የተሰጠዉ የተቋሙ የሥራ ኃላፊ ወይም ሠራተኛ ብቻ መሆን አለበት፡፡

 

 አንቀጽ 24 - በሕግ የተሰጠ ሥልጣን ወሰንን አለማለፍ

የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ ለአስተዳደር ተቋሙ በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን ወሰን ማለፍ የለበትም፡፡

 

አንቀጽ 25 - የግል እና የሕዝብ ጥቅምን ማመዛዘን

የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ የአስተዳደር ተቋሙን ተገልጋይ የግል ጥቅም እና በአስተዳደር ተቋሙ ዓላማ የተመለከተውን የሕዝብ ጥቅም ማመዛዘን አለበት፡፡

 

አንቀጽ 26 - አግባብነት በሌለዉ ጉዳይ ወይም ፍላጎት አለመመራት

የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ ለጉዳዩ አግባብነት በሌለዉ ጉዳይ ወይም ፍላጎት መመራት የለበትም፡፡

አንቀጽ 27 - ሙያዊ ውሳኔ መሥጠት

የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ ሙያዉ የሚጠይቀዉን ሥነ-ምግባር፣ ትጋት እና ጥንቃቄ ማክበር አለበት፡፡

 አንቀጽ 28 - ተገልጋይን፣ ተቃዋሚን እና ሕዝብን ማድመጥ

በዚህ አዋጅ አንቀጽ 20 ወይም 22 መሠረት የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ የአስተዳደር ውሳኔ ከመሥጠቱ በፊት የሚመለተዉን ሰው ፍሬ ነገር እና ማስረጃ በሚገባ ማድመጥ እና መመርመር እንዲሁም እንደነገሩ ሁኔታ የሦስተኛ ወገን ተቃዋሚን እና የሕዝብን አስተያዬት ማድመጥ አለበት፡፡

 አንቀጽ 29 - በቅን ልቦና መወሰን

የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ በቅን ልቦና መወሰን አለበት፡፡

 አንቀጽ 30 - በቂ ምክንያት መስጠት

የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ ለአስተዳዳር ውሳኔው በቂ ምክንያት መስጠት አለበት፡፡

 አንቀጽ 31 - የጥቅም ግጭትን ማስቀረት

የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ ከተገልጋዩ ጋር የሥጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ያለው ከሆነ ወይም በማናቸውም ሁኔታ የጥቅም ግጭት የሚያስከትልበት ከሆነ ጉዳዩን ከማየት እራሱን ማግለል አለበት፡፡

 አንቀጽ 32 - የተገልጋዮችን እኩልነት ማክበር

የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ ሁሉንም ተገልጋዮች በዘር፣ በብሄር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሀይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በማህበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት መጠን፣ በትውልድ ሁኔታ ወይም በሌላ ምክንያት ልዩነት ሳያደርግ ማስተናገድ አለበት፡፡

 አንቀጽ 33 - በተገቢዉ ጊዜ መወሰን

 1. የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ የአስተዳደር ውሳኔዉን ሳይዘገይ በተገቢዉ ጊዜ መስጠት እና በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ ጥቅሞች በውሳኔው መዘግየት ምክንያት ለጉዳት እንዳይጋለጡ ማድረግ አለበት፡፡
 2. የአስተዳደር ውሳኔ በተገቢው ጊዜ ሳይሰጥ መቅረት የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ እንደተሰጠ ውሳኔ ይቆጠራል፡፡

 አንቀጽ 34 - ተገማች መሆን

የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ በፍሬ ነገር ተመሳሳይ የሆኑ ጉዳዮችን በተመሳሳይ ሁኔታ መወሰን አለበት፡፡

 አንቀጽ 35 - ግልጽ መሆን

የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱ ግልጽነትን የተከተለ እንዲሆን ማድረግ አለበት፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሦስት

የአስተዳደር ውሳኔ አፈፃፀም

 አንቀጽ 36 - የአስተዳደር ውሳኔውን ለተገልጋዩ ስለመስጠት

ማንኛውም የአስተዳደር ውሳኔ ወዲያዉኑ ለተገልጋዩ በጽሑፍ መሠጠት አለበት፡፡

 አንቀጽ 37 - የአስተዳደር ውሳኔን የሚፈጽመው ሰው

ማንኛውም የአስተዳደር ውሳኔ የሚፈጸመው ውሳኔውን በሰጠው ሰዉ ወይም በሚመለከተዉ አካል ይሆናል፡፡

 

ንዑስ ክፍል አራት

በአስተዳደር ውሳኔ ላይ ስለሚቀርብ ቅሬታ

 አንቀጽ 38 - ቅሬታ የማቅረብ መብት

ማንኛውም ሰዉ በተላለፈበት የአስተዳደር ውሳኔ ላይ ለአስተዳደር ተቋሙ ቅሬታ የማቅረብ መብት አለው፡፡

 አንቀጽ 39 - የቅሬታ ማስተናገጃ አካል ማቋቋም

ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም የቅሬታ ማስተናገጃ አካል ማቋቋም እና ይህንኑ ለተገልጋዮች ይፋ ማድረግ አለበት፡፡

አንቀጽ 40 - የአስተዳደር ውሳኔው አፈፃፀም መታገድ

ማንኛውም ቅሬታ የቀረበበት የአስተዳደር ውሳኔ ቅሬታው ተመርምሮ እስኪወሰን ድረስ አይፈጸምም፡፡ ሆኖም የውሳኔው ሳይፈጸም መቆየት በሕዝብ ላይ የማይመለስ ጉዳት የሚያስከትል ከሆነ የአስተዳደር ተቋሙ የበላይ ኃላፊ ዉሳኔዉ እንዲፈጸም ሊያዝ ይችላል፡፡

 አንቀጽ 41 - ቅሬታውን ስለመመርመርና ስለመወሰን

 

 1. የአስተዳደር ተቋሙ የቅሬታ ማስተናገጃ አካል ቅሬታውን በሚገባ መመርመር እና የዉሳኔ ሀሳብ ለአስተዳደር ተቋሙ የበላይ ኃላፊ ወይም እሱ ለወከለዉ የሥራ ኃላፊ ማቅረብ አለበት፡፡
 2. የአስተዳደር ተቋሙ የበላይ ኃላፊ ወይም እሱ የወከለዉ የሥራ ኃላፊ በቅሬታ ማስተናገጃ አካል የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ተመልክቶ የሰጠው ውሳኔ የተቋሙ የመጨረሻ ውሳኔ ይሆናል፡፡

 አንቀጽ 42 - የቅሬታ ውሳኔውን ለተገልጋዩ ስለመስጠት

የአስተዳደር ተቋሙ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 41 መሠረት የተሰጠውን ውሳኔ ወዲያዉኑ ለቅሬታ አቅራቢው በጽሑፍ መስጠት አለበት፡፡

 

ክፍል አራት

በፍርድ ቤት የሚደረግ የአስተዳደር መመሪያዎችና ውሳኔዎች ክለሳ

ንዑስ ክፍል አንድ

የክለሳ አጀማመር

 አንቀጽ 43 - የክለሳ አቤቱታ ስለማቅረብ

የዚህ አዋጅ አንቀጽ 45 ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣

 1. ማንኛውም ጉዳዩ የሚመለከተው ሰው የአስተዳደር መመሪያ በፍርድ ቤት እንዲከለስ አቤቱታ ማቅረብ ይችላል፤
 2. ማንኛውም በአስተዳደር ውሳኔ ጥቅሙ የተነካበት ሰው ውሳኔው በፍርድ ቤት እንዲከለስ አቤቱታ ማቅረብ ይችላል፡፡

  አንቀጽ 44 - የክለሳ አቤቱታ ስለሚቀርብበት ፍርድ ቤት

 

 1. የአስተዳደር መመሪያ ወይም ዉሳኔ እንዲከለስ አቤቱታ የሚቀርበው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይሆናል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔም የመጨረሻ ይሆናል፡፡
 2. የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክለሳ አቤቱታዎችን የሚያስተናግድ የአስተዳደር ጉዳይ ችሎት ያደራጃል፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሁለት

የክለሳ መርሆዎች

 አንቀጽ 45 - የክለሳ ምክንያት

 1. የአስተዳደር መመሪያ በፍርድ ቤት የሚከለሰው፣

ሀ.  በዚህ አዋጅ ክፍል ሁለት የተመለከቱትን የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌዎች ሳይከተል የወጣ፣

ለ.  ከአስተዳደር ተቋሙ የሥልጣን ገደብ ውጪ የወጣ፣ ወይም

ሐ. ሕግን የጣሰ፣

ሲሆን ነው፡፡

 1. የአስተዳደር ውሳኔ በፍርድ ቤት የሚከለሰው በዚህ አዋጅ ክፍል ሦስት የተደነገጉትን መርሆዎች የጣሰ ሲሆን ነው፡፡

 አንቀጽ 46 - የክለሳ አቤቱታ የሚቀርበው በመጨረሻ ውሳኔ ላይ ስለመሆኑ

ማንኛውም የፍርድ ቤት ክለሳ አቤቱታ የሚቀርበው የመጨረሻ በሆነ የአስተዳደር ውሳኔ ላይ ብቻ ነው፡፡

 አንቀጽ 47 - አስተዳደራዊ መፍትሄዎችን አሟጦ ስለመጨረስ

 1. በሕግ በሌላ ሁኔታ ካልተደነገገ በቀር ማንኛውም ለፍርድ ቤት የክለሳ አቤቱታ የሚያቀርብ ባለጉዳይ አቤቱታውን ከማቅረቡ በፊት በአስተዳደር ተቋሙ ውስጥ ያሉትን አስተዳደራዊ መፍትሄዎች አሟጦ መጨረስ አለበት፡፡
 2. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ቢኖርም የአስተዳደር ተቋሙ አስተዳደራዊ መፍትሄ የመስጠቱን ሂደት ከሚገባው ጊዜ በላይ ያራዘመ እንደሆነ አስተዳደራዊ መፍትሄ አሟጦ መጨረስ ግዴታ አይሆንም፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሦስት

የክለሳ ሥርዓት

  አንቀጽ 48 - የክለሳ አቤቱታ የሚቀርብበት ጊዜ

 

 1. በዚህ አዋጅ አንቀጽ 45 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) መሠረት የአስተዳደር መመሪያ በፍርድ ቤት እንዲከለስ የሚቀርብ አቤቱታ መመሪያው ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር የ90 ቀናት ጊዜ ውስጥ መቅረብ አለበት፡፡
 2. በዚህ አዋጅ አንቀጽ 45 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) ወይም (ሐ) መሠረት የአስተዳደር መመሪያ በፍርድ ቤት እንዲከለስ የሚቀርብ አቤቱታ በማናቸውም ጊዜ ሊቀርብ ይችላል፡፡
 3. በዚህ አዋጅ አንቀጽ 47(2) የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ የአስተዳደር ውሳኔ በፍርደ ቤት እንዲከለስ የሚቀርብ አቤቱታ ባለጉዳዩ ውሳኔውን እንዲያውቀው ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር የ30 ቀናት ጊዜ ውስጥ መቅረብ አለበት፡፡

  አንቀጽ 49 - የጽሑፍ መልስ ስለማቅረብ

የክለሳ አቤቱታ የቀረበበት የአስተዳደር ተቋም በ15 የሥራ ቀናት ዉስጥ የጽሑፍ መልስ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱ ሊያዝ ይችላል፡፡

  አንቀጽ 50 - ሰነዶችን ስለማቅረብ

የክለሳ አቤቱታ የቀረበበት የአስተዳደር ተቋም አቤቱታ የቀረበበትን መመሪያ ወይም ዉሳኔ በተመለከተ አስፈላጊ ሰነዶች እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ  ሊያዝ ይችላል፡፡

 

 

ንዑስ ክፍል አራት

የክለሳ ዉሳኔ አሰጣጥ እና አፈፃፀም

 አንቀጽ 51 - የክለሳ ዉሳኔ አሰጣጥ

 

 1. ፍርድ ቤቱ የክለሳ አቤቱታውን በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ መርምሮ ዉሳኔ መስጠት አለበት፡፡
 2. ፍርድ ቤቱ የክለሳ አቤቱታ የቀረበበትን የአስተዳደር መመሪያ ወይም ዉሳኔ ሊያፀና ወይም በሙሉ ወይም በከፊል ሊሽር ይችላል፡፡
 3. ፍርድ ቤቱ የክለሳ አቤቱታ የቀረበበትን የአስተዳደር መመሪያ ወይም ውሳኔ በሙሉ ወይም በከፊል ሲሽር የአስተዳደር ተቋሙ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተጠቆሙ ግድፈቶችን አስተካክሎ መመሪያውን እንደገና እንዲያወጣ ወይም እንዲያሻሽል፣ ወይም ውሳኔ ሰጥቶበት የነበረውን ጉዳይ እንደገና መርምሮ እንዲወስን ሊያዘው ይችላል፡፡

  አንቀጽ 52 - የክለሳ ዉሳኔ አፈፃፀም

 

 1. በፍርድ ቤት የተሰጠ የአስተዳደር መመሪያን ወይም ዉሳኔን የማፅናት ወይም የመሻር ዉሳኔ ወዲያዉኑ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
 2. ፍርድ ቤቱ የአስተዳደር መመሪያው ወይም ዉሳኔው እንዲሻሻል ካዘዘ የአስተዳደር ተቋሙ በዚህ አዋጅ ክፍል ሁለት እና ሦስት የተመለከቱትን የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌዎች እና መርሆዎች አክብሮ መመሪያውን ወይም የአስተዳደር ውሳኔውን በተገቢዉ ጊዜ ማሻሻል አለበት፡፡
 3. በፍርድ ቤቱ የተሰጠ የአስተዳር መመሪያን ወይም ዉሳኔን በሙሉ ወይም በከፊል የመሻር ዉሳኔ ወይም የማሻሻል ትዕዛዝ የክለሳ አቤቱታ የቀረበበትን መመሪያ ወይም ውሳኔ ሕጋዊ ኃይል በሙሉ ወይም በከፊል ያስቀራል፡፡

 

ክፍል አምስት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

  አንቀጽ 53 - የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ተፈፃሚ ስለመሆኑ

በዚህ አዋጅ ክፍል አራት ባልተመለከቱ የክለሳ ሥነ-ሥርዓት ጉዳዮች ላይ አግባብነት ያላቸዉ የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡

 አንቀጽ 54 - የጉዳት ካሳ ስለመጠየቅ

ከአስተዳደር መመሪያ ውይም ውሳኔ ጋር በተያያዘ ጥፋት ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ማንኛውም ተገልጋይ መመሪያውን ያወጣው ወይም ውሳኔውን የሰጠው የአስተዳደር ተቋም አግባብ ባለዉ ሕግ መሠረት ካሳ እንዲከፍለው የመጠየቅ መብት ይኖረዋል፡፡

 አንቀጽ 55 - መረጃ የመስጠት ግዴታ

ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም ከመመሪያ ማውጣት ወይም ከአስተዳደር ውሳኔ መስጠት እና እነዚህን ከመፈጸም ጋር በተያያዘ በሌላ የአስተዳደር ተቋም ሲጠየቅ መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡

 አንቀጽ 56 - ደንብ የማውጣት ሥልጣን

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም የሚያስፈልግ ደንብ ሊያወጣ ይችላል፡፡

 አንቀጽ 57 - አዋጁ የሚጸናበት ጊዜ

ይህ አዋጅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡

 

አዲስ አበባ -------- ቀን 2012 ዓ.ም

ሳህለ ወርቅ ዘውዴ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ

ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት

Read 6364 times Last modified on Jun 20 2019
Abyssinia Law | Making Law Accessible!

Abyssinia Law is  a legal resource portal providing open access to primary and secondary legal materials for Ethiopia, such as laws, court decisions, articles, contact guidance and Lawyers Directory - with texts supplemented by online videos, a discussion forum and user blog. The service gives free access to Federal and State consolidated laws of Ethiopia (with status information whether the law is amended, repealed or effective)

Leave a comment